በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በብሔራት ላይ የመከረው ምክር

ይሖዋ በብሔራት ላይ የመከረው ምክር

ምዕራፍ አሥራ አምስት

ይሖዋ በብሔራት ላይ የመከረው ምክር

ኢሳይያስ 14:​24–19:​25

1. ኢሳይያስ ስለ አሦር የጻፈው የፍርድ መልእክት ምንድን ነው?

ይሖዋ ሕዝቡን ስለ ክፋታቸው ለመቅጣት በሌሎች ብሔራት ሊጠቀም ይችላል። ሆኖም እነዚያ ብሔራት የሚያሳዩትን ከልክ ያለፈ ጭካኔና ኩራት እንዲሁም ለእውነተኛ አምልኮ ያላቸውን ጥላቻ ቸል ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። ከዚህም የተነሣ ይሖዋ ከረጅም ጊዜ በፊት ኢሳይያስ ‘ስለ ባቢሎን የተነገረውን ሸክም’ እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። (ኢሳይያስ 13:​1) ይሁን እንጂ ወደፊት ባቢሎን ትልቅ ስጋት መፍጠሯ አይቀርም። በኢሳይያስ ዘመን አሦር የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ በመጨቆን ላይ ነበር። አሦር ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አጥፍቶና በአብዛኛው የይሁዳ ክልል ላይ ውድመት አድርሶ ነበር። ነገር ግን የአሦራውያኑ ድል ውስን ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል:- እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ . . . አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፣ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፣ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።” (ኢሳይያስ 14:​24, 25) ኢሳይያስ ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አሦራውያን በይሁዳ ላይ እንዲያንዣብብ አድርገውት የነበረው የስጋት ደመና ተገፍፏል።

2, 3. (ሀ) ጥንት ይሖዋ እጁን የዘረጋው በማን ላይ ነበር? (ለ) ይሖዋ ‘በሁሉም ብሔራት ላይ’ እጁን ይዘረጋል ማለት ምን ማለት ነው?

2 ይሁንና የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጠላት ስለነበሩት ሌሎች ብሔራትስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱም ቢሆኑ ከፍርድ አያመልጡም። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ [“የመከረው ምክር፣” NW  ] ይህ ነው፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል [“መክሮአል፣” NW ]፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው?” (ኢሳይያስ 14:​26, 27) የይሖዋ ‘ምክር’ እንዲሁ በሐሳብ ደረጃ የሚቀር አይደለም። ይህ ቁርጥ ውሳኔው ነው። (ኤርምያስ 49:​20, 30) የአምላክ “እጅ” የሚለው አባባል ሥራ ላይ ያለውን ኃይሉን የሚያመለክት ነው። በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 14 የመጨረሻ ቁጥሮችና ከኢሳይያስ 15 እስከ 19 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ይሖዋ በፍልስጥኤም፣ በሞዓብ፣ በደማስቆ፣ በኢትዮጵያና በግብጽ ላይ የመከረው ምክር ተመዝግቦ ይገኛል።

3 ይሁን እንጂ ኢሳይያስ የተናገረው የይሖዋ እጅ ‘በብሔራት ሁሉ ላይ እንደተዘረጋች’ ነው። በመሆኑም እነዚህ ኢሳይያስ የተናገራቸው ትንቢቶች በጥንቱ ዘመን የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ቢያገኙም በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ይሖዋ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ እጁን በሚዘረጋበት ‘የፍጻሜ ዘመንም’ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። (ዳንኤል 2:​44፤ 12:​9፤ ሮሜ 15:​4፤ ራእይ 19:​11, 19-21) ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከረጅም ዘመን በፊት በእርግጠኝነት ምክሩን አሳውቋል። የተዘረጋች እጁን ሊመልሳት የሚችል የለም።​—⁠መዝሙር 33:​11፤ ኢሳይያስ 46:​10

በፍልስጥኤም ላይ የሚነሳ ‘እንደሚበርር እሳት ያለ እባብ’

4. ይሖዋ በፍልስጥኤም ላይ የተናገረው ሸክም ዝርዝር ምንድን ነው?

4 መጀመሪያ የተጠቀሰው ፍልስጤም ነው። “ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ሸክም ሆነ። ፍልስጥኤም ሆይ፣ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፣ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 14:​28, 29

5, 6. (ሀ) ዖዝያን ለፍልስጥኤም እንደ እባብ የሆነባት እንዴት ነው? (ለ) ሕዝቅያስ ለፍልስጥኤማውያን ምን ሆኖባቸዋል?

5 ንጉሥ ዖዝያን ፍልስጥኤም የፈጠረችውን ስጋት ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ነበረው። (2 ዜና መዋዕል 26:​6-8) ለባላንጣው ጎረቤቱ ለፍልስጥኤም እንደ እባብ ሆኖበት የነበረ ሲሆን በበትሩም ይኮረኩመው ነበር። ዖዝያን ከሞተ በኋላ ማለትም ‘በትሩ ሲሰበር’ የታመነው ንጉሥ ኢዮዓታም መግዛት ቢጀምርም ‘ሕዝቡ ገና ይበድል ነበር።’ ከዚያም አካዝ ነገሠ። ሁኔታዎች ተለወጡና ፍልስጥኤም በይሁዳ ላይ የተሳካ ወታደራዊ ወረራዎችን አካሄደች። (2 ዜና መዋዕል 27:​2፤ 28:​17, 18) ይሁን እንጂ አሁን ሁኔታዎቹ እንደገና አዲስ መልክ እየያዙ ነው። በ746 ከዘአበ ንጉሥ አካዝ ሲሞት ወጣቱ ሕዝቅያስ ዙፋኑን ወረሰ። ፍልስጥኤማውያን በለስ እንደ ቀናን እንቀጥላለን ብለው አስበው ከነበረ እጅግ ተሳስተዋል። ሕዝቅያስ ለሕልውናቸው የሚያሰጋ ጠላት ሆኖባቸዋል። የዖዝያን ዘር የሆነው (‘ከሥሩ’ የወጣው ‘ፍሬ’) ሕዝቅያስ ‘እንደሚበርር እሳት ያለ እባብ’ ማለትም በመብረቅ ፍጥነት ጥቃት ለመሰንዘር የሚወረወርና እንደ እባብ መርዝ ጠላቶቹን የማቃጠል ኃይል ያለው ሆኖ ነበር።

6 ይህ ለአዲሱ ንጉሥ ተስማሚ መግለጫ ነበር። ‘ፍልጥኤማውያንን እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ የመታው ሕዝቅያስ’ ነው። (2 ነገሥት 18:​8) የአሦር ንጉሥ የነበረው የሰናክሬም ዜና ታሪክ እንደሚለው ከሆነ ፍልስጥኤም የሕዝቅያስ ተገዥ ሆና ነበር። ፍልስጥኤም በረሃብ ስትሰቃይ ‘ድሀ ’ የተባለው የተዳከመው የይሁዳ መንግሥት አስተማማኝ ደህንነትና የተትረፈረፈ ቁሳዊ ነገር ያገኛል።​—⁠ኢሳይያስ 14:​30, 31ን አንብብ።

7. ሕዝቅያስ በኢየሩሳሌም ተገኝተው ለነበሩት መልእክተኞች እምነቱን መግለጽ የነበረበት እንዴት ነው?

7 ከአሦር ጋር በምናደርገው ውጊያ ከእኛ ጋር ተባበሩ ለማለት ሳይሆን አይቀርም ወደ ይሁዳ የመጡ መልእክተኞች ነበሩ። ምን መልስ ሊሰጣቸው ይገባል? “ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መመለስ ይገባል?” ሕዝቅያስ ከውጭ ኃይሎች ጋር ኅብረት በመፍጠር ለደኅንነቱ ዋስትና ለማግኘት መጣር ይኖርበታልን? የለም! መልእክተኞቹን “እግዚአብሔር ጽዮንን እንደ መሠረተ፣ የሕዝቡም ችግረኞች በእርስዋ ውስጥ እንደሚጠጉ ነው” ብሎ ሊመልሳቸው ይገባል። (ኢሳይያስ 14:​32) ንጉሡ በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረው ይገባል። የጽዮን መሠረት የጸና ነው። ከተማይቱ በላይዋ ካንዣበበው የአሦራውያን ጥቃት ለመሸሸግ አስተማማኝ ቦታ ትሆናለች።​—⁠መዝሙር 46:​1-7

8. (ሀ) ዛሬ አንዳንድ ብሔራት እንደ ፍልስጥኤም የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ጥንት እንዳደረገው ሁሉ ዛሬ ያሉትን ሕዝቦቹን ለመደገፍ ምን አድርጓል?

8 ዛሬም አምላክን የሚያመልኩ ሰዎችን ልክ እንደ ፍልስጥኤም አጥብቀው የሚቃወሙ አንዳንድ ብሔራት አሉ። ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተጥለዋል። ሥራቸው ታግዷል። የተወሰኑትም ተገድለዋል። ተቃዋሚዎች ‘በጻድቅ ነፍስ ላይ ማድባታቸውን’ አይተዉም። (መዝሙር 94:​21) ይህ የክርስቲያኖች ቡድን በጠላቶቹ ፊት እንደ ‘ድሃና’ ‘ችግረኛ’ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ጠላቶቻቸው በረሃብ ሲሰቃዩ እነርሱ በተትረፈረፈ መንፈሳዊ ነገር ደስ ይላቸዋል። (ኢሳይያስ 65:​13, 14፤ አሞጽ 8:​11) ይሖዋ በዘመናችን ፍልስጥኤማውያን ላይ እጁን ሲዘረጋ እነዚህ “ድሆች” መሸሸጊያ ያገኛሉ። የሚሸሸጉት የት ነው? ኢየሱስ የማዕዘን ድንጋይ ከሆነለት ‘የእግዚአብሔር ቤተሰብ’ ዘንድ ነው። (ኤፌሶን 2:​19, 20) ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለትን የይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ማለትም ‘የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌምን’ ጥበቃም ያገኛሉ።​—⁠ዕብራውያን 12:​22፤ ራእይ 14:​1

ሞዓብን ዝም አሰኝቶታል

9. ቀጥሎ ያለው ሸክም የተነገረው ስለ ማን ነው? ይህስ ሕዝብ የአምላክ ሕዝብ ጠላት ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

9 ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ የነበረችው ሌላዋ የእስራኤል አጎራባች ሞዓብ ናት። ከፍልስጥኤማውያኑ በተለየ መልኩ ሞዓባውያን የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው የሎጥ ዝርያ በመሆናቸው ከእስራኤላውያን ጋር የደም ትስስር ነበራቸው። (ዘፍጥረት 19:​37) ይህ ዝምድና ቢኖርም ሞዓብ በታሪኳ ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረች። ለምሳሌ ያህል በሙሴ ዘመን የሞዓብ ንጉሥ እስራኤላውያንን ይረግምልኛል በሚል ነቢዩ በለዓምን ቀጥሮ ነበር። ሞዓብ ይህ አልሳካላት ሲል ደግሞ እስራኤላውያንን ለማጥመድ የፆታ ብልግናንና የበዓል አምልኮን እንደ መሣሪያ ተጠቅማበታለች። (ዘኍልቁ 22:​4-6፤ 25:​1-5) እንግዲያው ‘ስለ ሞዓብ የተነገረውን ሸክም ’ እንዲጽፍ ይሖዋ ኢሳይያስን በመንፈሱ ማነሳሳቱ ምንም አያስገርምም።​—⁠ኢሳይያስ 15:​1ሀ

10, 11. ሞዓብ ምን ይደርስባታል?

10 የኢሳይያስ ትንቢት እንደ ዔር፣ ቂር (ወይም ቂርሐራሴት) እና ዲቦን ያሉትን ጨምሮ በሞዓብ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞችንና ቦታዎችን በሚመለከት የተነገረ ነው። (ኢሳይያስ 15:​1ለ, 2ሀ) ሞዓባውያን ስለ ቂርሐራሴት የዘቢብ ቂጣ ያለቅሳሉ። ምናልባት ይህ በከተማዋ በብዛት ይገኝ የነበረ ነገር ሳይሆን አይቀርም። (ኢሳይያስ 16:​6, 7 NW) በወይን ምርታቸው የሚታወቁት ሴባማና ኢያዜር በቸነፈር ይመታሉ። (ኢሳይያስ 16:​8-10 ) “የሦስት ዓመት ጊደር” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍ የሚችል ስም ያላት ዔግላት ሺሊሺያ የሚያሳዝን የጭንቀት ድምፅ እንደምታሰማ ፍርጥም ያለች ጊደር ትሆናለች። (ኢሳይያስ 15:​5) ‘የዲሞን ውኃ ’ በታረዱት ሞዓባውያን ደም ሲሞላ የምድሪቱ ሣር ይደርቃል። በምሳሌያዊ መንገድም ይሁን ቃል በቃል “የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ።” ይህ የሚሆነው የጠላት ኃይል ወንዞቻቸውን ስለሚገድብባቸው ይመስላል።​—⁠ኢሳይያስ 15:​6-9

11 ሞዓባውያን የሐዘን ልብስ የሆነውን ማቅ ይለብሳሉ። ኃፍረታቸውንና የደረሰባቸውን ሰቆቃ ለማሳየት ራሳቸውን ሙልጭ አድርገው ይላጫሉ። የገጠማቸውን ከባድ ሐዘንና ውርደት ለማሳየት ጢማቸውንም ‘ይላጫሉ።’ (ኢሳይያስ 15:​2ለ-4 ) ይህ ፍርድ መፈጸሙ የማይቀር መሆኑን የተገነዘበው ኢሳይያስ ራሱ ስሜቱ ተነክቷል። ስለ ሞዓብ በተነገረው ወዮታ ከተሰማው ኃዘን የተነሣ ሆዱ እንደ መሰንቆ ክር ተንቀጥቅጦበታል።​—⁠ኢሳይያስ 16:​11, 12

12. ኢሳይያስ ስለ ሞዓብ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

12 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው? በቅርቡ ነው። “እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር:- በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፣ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል።” (ኢሳይያስ 16:​13, 14) ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሞዓብ አሳዛኝ መከራ እንደደረሰባትና ብዙዎቹ ቦታዎቿ ሰው አልባ እንደሆኑ የሚያሳይ አርኬኦሎጂያዊ ማስረጃ አለ። ሳልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶር ለእርሱ ይገብሩ ከነበሩት ገዥዎች መካከል የሞዓቡ ሳላማኑ እንደሚገኝበት ጠቅሷል። የሞዓቡ ንጉሥ ካሙሱንዳቢ ለሰናክሬም ገብሯል። የአሦር ንጉሠ ነገሥታት አስራዶንና አሸርባኒፓል የሞዓባውያኑ ነገሥታት ሙሱሪ እና ካማሻልቱ የእነርሱ ተገዥዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። ሞዓባውያን በሕዝብ ደረጃ የነበራቸውን ሕልውና ጭራሽ ካጡ ብዙ መቶ ዓመታት ተቆጥረዋል። የሞዓባውያን ከተሞች ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ አንዳንድ ፍርስራሾች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ኃያል ስለነበረችው ስለዚህች የእስራኤል ጠላት እስካሁን ድረስ በቁፋሮ የተገኘው ግዑዝ ማስረጃ እጅግ በጣም ጥቂት ነው።

ዘመናዊቷ “ሞዓብ” ትጠፋለች

13. ዛሬ ከሞዓብ ጋር የሚመሳሰለው ድርጅት የትኛው ነው?

13 ዛሬም ከጥንትዋ ሞዓብ ጋር የምትመሳሰል ዓለም አቀፍ ድርጅት አለች። እርሷም ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ዋነኛ ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ናት። (ራእይ 17:​5) ሞዓብም ሆነ እስራኤል የአብርሃም አባት የታራ ዝርያ ናቸው። በተመሳሳይም ሕዝበ ክርስትና ልክ ዛሬ እንዳለው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ምንጭዋ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ እንደሆነ ትናገራለች። (ገላትያ 6:​16) ይሁን እንጂ እንደ ሞዓብ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም መንፈሳዊ ግልሙትናን እንዲሁም ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ ውጭ ለሌሎች አማልክት የሚቀርብ አምልኮን ስለምታበረታታ ብልሹ ሆናለች። (ያዕቆብ 4:​4፤ 1 ዮሐንስ 5:​21) በቡድን ደረጃ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የመንግሥቱን ምሥራች የሚሰብኩትን ሰዎች ይቃወማሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​9, 14

14. ይሖዋ በዘመናዊቷ “ሞዓብ” ላይ የመከረው ምክር ቢኖርም የዚህች ድርጅት አባል የሆኑ ግለሰቦች ምን ተስፋ አላቸው?

14 በመጨረሻ ሞዓብ ጸጥ እንድትል ተደርጋለች። ሕዝበ ክርስትናም የሚገጥማት ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም። ይሖዋ የአሦርን ዘመናዊ አምሳያ በመጠቀም ባድማ ያደርጋታል። (ራእይ 17:​16, 17) ይሁን እንጂ በዚህች የዘመናችን “ሞዓብ” ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ተስፋ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ ሞዓብ በሚናገረው ትንቢት መካከል እንዲህ ይላል:- “ዙፋንም በምሕረት ይቀናል፣ በዚያም ላይ በዳዊት ድንኳን ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል።” (ኢሳይያስ 16:​5) በ1914 ይሖዋ በንጉሥ ዳዊት መስመር ገዢ የሆነውን የኢየሱስን ዙፋን በሰማይ አጽንቶአል። የኢየሱስ ንግሥና የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ሲሆን ለዳዊት በተገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል። (መዝሙር 72:​2፤ 85:​10, 11፤ 89:​3, 4፤ ሉቃስ 1:​32) ብዙ ቅን ሰዎች የዘመናችንን “ሞዓብ” ትተው በመውጣት ሕይወት ለማግኘት ሲሉ ራሳቸውን ለኢየሱስ አስገዝተዋል። (ራእይ 18:​4) ኢየሱስ ‘ፍትሕን ለአሕዛብ ግልጽ እንደሚያደርግላቸው’ ማወቃቸው ለእነዚህ ሰዎች ምንኛ የሚያጽናና ነው!​—⁠ማቴዎስ 12:​18፤ ኤርምያስ 33:​15

ደማስቆ የበሰበሰ ፍርስራሽ ትሆናለች

15, 16. (ሀ) ደማስቆና እስራኤል በይሁዳ ላይ የወሰዱት የጥላቻ እርምጃ ምን ነበር? ይህስ በደማስቆ ላይ ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው? (ለ) ስለ ደማስቆ የተነገረው ሸክም ማንንም ጭምር ይመለከታል? (ሐ) ዛሬ ክርስቲያኖች ከእስራኤል ምሳሌ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

15 ቀጥሎ ኢሳይያስ የመዘገበው ‘ስለ ደማስቆ የተነገረውን ሸክም ’ ነው። (ኢሳይያስ 17:​1-6ን አንብብ።) ከእስራኤል በስተ ሰሜን የምትገኘው ደማስቆ “የሶርያ ራስ” ነች። (ኢሳይያስ 7:​8) በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ ዘመን የደማስቆው ረዓሶን ከእስራኤሉ ፋቁሔ ጋር ግንባር ፈጥሮ ይሁዳን ወርሮ ነበር። ይሁን እንጂ በአካዝ ጥያቄ የአሦሩ ሳልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶር በደማስቆ ላይ ተነስቶ ድል ካደረጋት በኋላ ብዙዎቹን ነዋሪዎች በግዞት ወስዷል። ከዚያ በኋላ ደማስቆ ለይሁዳ ስጋት የምትፈጥር አገር መሆኗ አክትሟል።​—⁠2 ነገሥት 16:​5-9፤ 2 ዜና መዋዕል 28:​5, 16

16 እስራኤል ከደማስቆ ጋር ግንባር በመፍጠሯ ምክንያት ሳይ​ሆን አይቀርም ይሖዋ ስለ ደማስቆ የተናገረው ሸክም ከዳተኛ በሆ⁠ነው ሰሜናዊው መንግሥት ላይ የተነገረውንም የፍርድ መልእክት የሚያካትት ነው። (ኢሳይያስ 17:​3-6) እስራኤል በመከር ጊዜ ብዙም አዝመራ እንደማይሰጥ ማሳ ወይም በአብዛኛው ፍሬው ከቅርንጫፉ ላይ እንደተራገፈ የወይራ ዛፍ ትሆናለች። (ኢሳይያስ 17:​4-6) ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ ልብ ሊሉት የሚገባ እንዴት ያለ ምሳሌ ነው! ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጠው ይፈልጋል። እንዲሁም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ከልብ የቀረበ ቅዱስ አገልግሎት ብቻ ነው። በወንድሞቻቸው ላይ የሚነሱትንም አጥብቆ ይጠላል።​—⁠ዘጸአት 20:​5፤ ኢሳይያስ 17:​10, 11፤ ማቴዎስ 24:​48-50

በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ማሳደር

17, 18. (ሀ) በእስራኤል የነበሩ አንዳንዶች ይሖዋ ለተናገረው የፍርድ ቃል የሰጡት ምላሽ ምንድን ነው? ሆኖም የሕዝቡ አጠቃላይ ዝንባሌ ምንድን ነው? (ለ) ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች በሕዝቅያስ ዘመን ከነበሩት ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

17 ኢሳይያስ ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፣ ዓይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፤ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፣ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፣ አያይም።” (ኢሳይያስ 17:​7, 8) አዎን፣ በእስራኤል ያሉ አንዳንዶች የይሖዋን ማስጠንቀቂያ ይሰማሉ። ለምሳሌ ያህል ይሁዳ የማለፍን በዓል ስታከብር የእስራኤል ነዋሪዎች አብረዋት እንዲያከብሩ ሕዝቅያስ ግብዣ ባቀረበ ጊዜ አንዳንድ እስራኤላውያን ለጥሪው ምላሽ በመስጠት ወደ ደቡብ ተጉዘው ከወንድሞቻቸው ጋር በንጹሕ አምልኮ ተባብረዋል። (2 ዜና መዋዕል 30:​1-12) ያም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የእስራኤል ነዋሪዎች ጥሪውን ይዘው በመጡት መልእክተኞች ላይ አፊዘውባቸዋል። አገሪቱ ፈውስ የማይገኝላት ከሃዲ ሆናለች። በመሆኑም ይሖዋ በእርሷ ላይ የመከረው ምክር ተፈጽሟል። አሦር የእስራኤልን ከተሞች ታጠፋለች፣ ምድሪቱ ባድማ ግጦሹም ደረቅ ይሆናል።​—⁠ኢሳይያስ 17:​9-11ን አንብብ።

18 ዛሬ ስላለውስ ሁኔታ ምን ማለት ይቻላል? እስራኤል ከሃዲ ብሔር ሆና ነበር። ሕዝቅያስ በዚያ ብሔር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ወደ ንጹሕ አምልኮ እንዲመለሱ ለመርዳት የሞከረበት መንገድ ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሃዲ በሆነችው የሕዝበ ክርስትና ድርጅት ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች ለመርዳት የሚያደርጉትን ሙከራ የሚያስታውሰን ይሆናል። ከ1919 አንስቶ ‘የአምላክ እስራኤል’ መልእክተኞች ሰዎች በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ ለመጋበዝ ወደ ሕዝበ ክርስትና ሲሄዱ ኖረዋል። (ገላትያ 6:​16) አብዛኞቹ ጥሪውን ለመቀበል እምቢተኞች ሆነዋል። በመልእክተኞቹም ያፌዙ ብዙዎች ናቸው። ይሁንና አንዳንዶች ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በዛሬው ጊዜ እነዚህ ሰዎች በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሆነዋል። እንዲሁም ከእርሱ የተማሩ በመሆን ‘ዓይኖቻቸው የእስራኤሉን ቅዱስ ለማየት’ በመቻላቸው ደስ ይላቸዋል። (ኢሳይያስ 54:​13) ቅዱስ ባልሆኑት መሠዊያዎች የሚቀርበውን አምልኮ ማለትም ለሰው ሠራሽ አማልክት ያደሩ መሆንና በእነርሱ መታመንን ትተው ወደ ይሖዋ ዞር ብለዋል። (መዝሙር 146:​3, 4) እያንዳንዳቸው በኢሳይያስ ዘመን እንደኖረው እንደ ሚክያስ “እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፣ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል” ይላሉ።​—⁠ሚክያስ 7:​7

19. ይሖዋ የሚገስጸው ማንን ነው? ይህስ ለእነርሱ ምን ማለት ይሆናል?

19 ይህ ሟች በሆኑ የሰው ልጆች ላይ ትምክህታቸውን ከሚጥሉ ሰዎች ምንኛ የተለየ ነው! በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የሰው ልጅ በዓመፅና በሁከት ማዕበል እየተናወጠ ነው። እረፍት የሌለው ዓመፀኛው የሰው ዘር “ባሕር” ሕዝባዊ ተቃውሞንና ዓመፅን ያነሳሳል። (ኢሳይያስ 57:​20፤ ራእይ 8:​8, 9፤ 13:​1) ይሖዋ ይህንን ሁከተኛ የሰው ዘር ክፍል ‘ይገሥጸዋል።’ ሰማያዊ መንግሥቱ ችግር ፈጣሪ የሆኑትን ድርጅቶችና ግለሰቦች ሁሉ ያጠፋል። እነዚህም “እየሸሹ ይርቃሉ፣ . . . ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረውም ትቢያ ይበተናሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 17:​12, 13፤ ራእይ 16:​14, 16

20. እውነተኛ ክርስቲያኖች በብሔራት ‘ቢበዘበዙም’ ምን ትምክህት አላቸው?

20 ውጤቱስ ምን ይሆናል? ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “በመሸ ጊዜ፣ እነሆ፣ ድንጋጤ አለ፤ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፣ የበዘበዙንም ዕጣ ይህ ነው።” (ኢሳይያስ 17:​14) ብዙዎች የይሖዋን ሕዝብ በማንገላታትና አክብሮት በጎደለው መንገድ በመያዝ በዝብዘዋቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ታላላቅ ከሚባሉት የዓለም ሃይማኖቶች መካከል ስላልሆኑና መሆንም ስለማይፈልጉ አንዳንድ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው አክራሪ ተቃዋሚዎች በቀላሉ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች የሚደርስባቸው መከራ የሚያበቃበት ‘ማለዳ’ በፍጥነት እየተቃረበ እንዳለ እርግጠኞች ናቸው።​—⁠2 ተሰሎንቄ 1:​6-9፤ 1 ጴጥሮስ 5:​6-11

ኢትዮጵያ ለይሖዋ ስጦታ ታመጣለች

21, 22. ቀጥሎ የፍርድ መልእክት የሚቀበለው ብሔር የትኛው ነው? ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው?

21 ከግብጽ በስተደቡብ የምትገኘው ኢትዮጵያ ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች ከይሁዳ ጋር ጦርነት ገጥማለች። (2 ዜና መዋዕል 12:​2, 3፤ 14:​1, 9-15፤ 16:​8) ኢሳይያስ በዚህች ብሔር ላይ የሚመጣውን ፍርድ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- “በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፣ ክንፍ ያላቸው መርከቦች [“ነፍሳት፣” NW ] ላሉባት፣ . . . ምድር ወዮላት!” (ኢሳይያስ 18:​1-6ን አንብብ።) * ይሖዋ፣ ኢትዮጵያ ‘እንደምትቆረጥ፣ እንደምትወገድ እና እንደምትመለመል’ ተናግሯል።

22 ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መገባደጃ ላይ ግብጽን ድል አድርጋ በመያዝ ለ60 ዓመታት ያህል ገዝታታለች። የአሦር ንጉሠ ነገሥታት አስራዶንና አሸርባኒፓልም በተራቸው ወረራ አካሂደዋል። አሸርባኒፓል ቲቤዝን ሲያጠፋ አሦር ግብጽን ስለተቆጣጠረች ኢትዮጵያ በአባይ ሸለቆ የነበራት የበላይነት አክትሟል። (በተጨማሪ ኢሳይያስ 20:​3-6ን ተመልከት።) በዘመናችንስ?

23. “የኢትዮጵያ” ዘመናዊ አምሳያ የሚኖረው ድርሻ ምንድን ነው? ወደ ፍጻሜው የሚመጣውስ ለምንድን ነው?

23 ስለ ‘ፍጻሜው ዘመን’ በሚናገረው የዳንኤል ትንቢት ውስጥ ኢትዮጵያና ሊቢያ ጦረኛውን “የሰሜን ንጉሥ” ‘እንደሚከተሉት’ ማለትም ለእርሱ አመራር ምላሽ እንደሚሰጡ ተጠቅሷል። (ዳንኤል 11:​40-43) በተጨማሪም ኢትዮጵያ ‘ከማጎጉ ጎግ’ የውጊያ ሠራዊት ጋር እንደተሰለፈች ተደርጋ ተጠቅሳለች። (ሕዝቅኤል 38:​2-5, 8) የሰሜኑን ንጉሥ ጨምሮ የጎግ ሠራዊት በይሖዋ ቅዱስ ብሔር ላይ ጥቃት ሲሰነዝር የሕልውናው ፍጻሜ ይሆናል። በመሆኑም የይሖዋን ሉዓላዊነት ስለተቃወመ ይሖዋ በዘመናችን እንደ “ኢትዮጵያ” በተመሰለው ወገን ላይ እጁን ይዘረጋል።​—⁠ሕዝቅኤል 38:​21-23፤ ዳንኤል 11:​45

24. ይሖዋ ከብሔራት “እጅ መንሻ” የተቀበለው በምን መንገድ ነው?

24 ይሁንና ትንቢቱ በመጨመር እንዲህ ይላል:- “በዚያን ዘመን ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር፣ ከረጅምና ከለስላሳ ሕዝብ፣ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ከሆነ ወገን፣ . . . እጅ መንሻ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም ወደሚገኝበት ስፍራ ወደ ጽዮን ተራራ ይቀርባል።” (ኢሳይያስ 18:​7 ) ብሔራት የይሖዋን ሉዓላዊነት ባይገነዘቡም አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን ሕዝብ የሚጠቅም እርምጃ ወስደዋል። በአንዳንድ አገሮች ባለ ሥልጣኖች ይሖዋን ለሚያመልኩ የታመኑ ሰዎች በሚበጅ መንገድ ድንጋጌዎችን አስፈጽመዋል እንዲሁም የፍርድ ብያኔ ሰጥተዋል። (ሥራ 5:​29፤ ራእይ 12:​15, 16) ሌሎች ስጦታዎችም አሉ። “ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ። . . . መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” (መዝሙር 68:​29-31) ዛሬ ይሖዋን የሚፈሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ዘመናዊ “ኢትዮጵያውያን” አምልኮአቸውን እንደ “እጅ መንሻ” እያቀረቡ ነው። (ሚልክያስ 1:​11) የመንግሥቱን ምሥራች በምድር ዙሪያ በመስበኩ መጠነ ሰፊ ሥራ እየተሳተፉ ነው። (ማቴዎስ 24:​14፤ ራእይ 14:​6, 7) ይህ ለይሖዋ የሚቀርብ እንዴት ግሩም ስጦታ ነው!​—⁠ዕብራውያን 13:​15

የግብጽ ልብ ይቀልጣል

25. በ⁠ኢሳይያስ 19:​1-11 ፍጻሜ መሠረት የጥንቷ ግብጽ ምን ደርሶባታል?

25 በስተ ደቡብ በኩል የምትገኘው የይሁዳ የቅርብ ጎረቤት ግብጽ ከረጅም ጊዜ አንስቶ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጠላት ነበረች። ኢሳይያስ ምዕራፍ 19 በነቢዩ የሕይወት ዘመን ግብጽ ውስጥ የነበረውን ያልተረጋጋ ሁኔታ ይዘግባል። ግብጽ ውስጥ ‘ከተማ በከተማ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ እየተነሳ’ የሚካሄድ የእርስ በርስ ጦርነት ነበር። (ኢሳይያስ 19:​2, 13, 14) ታሪክ ጸሐፊዎች በተመሳሳይ ወቅት የተለያዩ የአገሪቱን ክፍሎች የሚቆጣጠሩ ተቀናቃኝ ሥርወ መንግሥታት እንደነበሩ የሚያሳይ ማስረጃ ያቀርባሉ። እጅግ የሚኩራሩበት ጥበብም ሆነ ‘ከንቱ አማልክቶቻቸውና የሚጠነቁሉ መናፍስት ጠሪዎቻቸው’ ግብጽን ‘ከጨካኝ ጌታ እጅ’ ሊያድኗት አልቻሉም። (ኢሳይያስ 19:​3, 4) ግብጽ ተራ በተራ በአሦር፣ በባቢሎን፣ በፋርስ፣ በግሪክ እና በሮም ድል ተነስታለች። እነዚህ ሁሉ ክንውኖች በ⁠ኢሳይያስ 19:​1-11 ላይ ያለው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ የሚያሳዩ ናቸው።

26. ትንቢቱ የላቀ ፍጻሜውን ሲያገኝ የዘመናዊው “ግብጽ” ነዋሪዎች ለይሖዋ የፍርድ መልእክት የሚሰጡት ምላሽ ምን ይሆናል?

26 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግብጽ ብዙውን ጊዜ የምታመለክተው የሰይጣንን ዓለም ነው። (ሕዝቅኤል 29:​3፤ ኢዩኤል 3:​19፤ ራእይ 11:​8) እንግዲያው ኢሳይያስ ‘ስለ ግብጽ የተናገረው ሸክም ’ የበለጠ ፍጻሜ ይኖረዋል ማለት ነው? አዎን፣ ይኖረዋል! የትንቢቱ የመክፈቻ ቃላት እያንዳንዱ ሰው ልብ እንዲል የሚያነሳሱ ሊሆኑ ይገባል:- “እነሆ፣ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፣ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።” (ኢሳይያስ 19:​1) በቅርቡ ይሖዋ በሰይጣን ድርጅት ላይ እርምጃ ይወስዳል። በዚህ ወቅት የዚህ የነገሮች ሥርዓት አማልክት ከንቱ መሆናቸው ይታያል። (መዝሙር 96:​5፤ 97:​7) ‘የግብጽም ልብ በፍርሃት ይቀልጣል።’ ኢየሱስ ስለዚህ ጊዜ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- “በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።”​—⁠ሉቃስ 21:​25, 26

27. ‘በግብጽ’ ውስጥ ምን ዓይነት መከፋፈል እንደሚኖር በትንቢት ተነግሯል? ይህስ ዛሬ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

27 ይሖዋ የፍርድ እርምጃውን የሚያስፈጽምበት ጊዜ መዳረሻ ላይ ስለሚኖሩት ሁኔታዎች ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፣ ሰውም ባልንጀራውን፣ ከተማም ከተማን፣ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።” (ኢሳይያስ 19:​2) የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሣቱ ‘ኢየሱስ በሥልጣኑ መገኘቱን’ የሚያሳይ ‘ምልክት’ ሆኗል። በጎሣ ምክንያት የሚነሡ ፍጅቶች፣ ደም አፋሳሽ የሆነው ዘር ማጥፋትና ዘር ማጽዳት እየተባለ የሚጠራው እንቅስቃሴ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዲረግፍ ምክንያት ሆነዋል። እንደነዚህ ያሉት ‘የምጥ ጣር’ የሆኑ ነገሮች ፍጻሜው እየቀረበ በሄደ መጠን ይባስ እየከፉ ይሄዳሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​3 NW , ማቴዎስ 24:7, 8

28. በፍርድ ቀን የሐሰት ሃይማኖት ይህንን የነገሮች ሥርዓት ለመታደግ ምን ሊያደርገው የሚችለው ነገር አለ?

28 “የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፣ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቁሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ።” (ኢሳይያስ 19:​3) ሙሴ ፈርዖን ፊት በቀረበ ጊዜ የግብጽ ካህናት የይሖዋን ኃይል ሊገዳደሩ ባለመቻላቸው ኃፍረት ተከናንበዋል። (ዘጸአት 8:​18, 19፤ ሥራ 13:​8፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​8) በተመሳሳይም በፍርድ ቀን የሐሰት ሃይማኖቶች ይህንን ብልሹ ሥርዓት ለመታደግ አይችሉም። (ከ⁠ኢሳይያስ 47:​1, 11-13 ጋር አወዳድር።) የኋላ ኋላ ግብጽ ‘ጨካኝ ጌታ ’ በሆነው በአሦር እጅ ወድቃለች። (ኢሳይያስ 19:​4) ይህም የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ለሚጠብቀው አስፈሪ የወደፊት ዕጣ ጥላ ይሆናል።

29. የይሖዋ ቀን ሲመጣ ፖለቲከኞች ምን የሚፈይዱት ነገር ይኖራል?

29 ይሁንና ስለ ፖለቲካ መሪዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱስ ማድረግ የሚችሉት ነገር ይኖር ይሆን? “የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቁርና ሆነች።” (ኢሳይያስ 19:​5-11ን አንብብ ።) ሰብዓዊ አማካሪዎች በፍርድ ቀን የሚያደርጉት ነገር ይኖራል ብሎ መጠበቅ እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል! የዓለምን እውቀት ሁሉ መጠቀም ቢችሉም አምላካዊ ጥበብ አይኖራቸውም። (1 ቆሮንቶስ 3:​19) ይሖዋን አንቀበልም ብለው ፍልስፍና፣ ገንዘብ፣ ተድላና ሌሎች አማልክትን ለማገልገል ፊታቸውን ወደ ሳይንስ መልሰዋል። ከዚህ የተነሣ ከመታለልና ግራ ከመጋባት በስተቀር ስለ አምላክ ዓላማ ምንም ዓይነት እውቀት የላቸውም። ሥራቸው ሁሉ ከንቱ ነው። (ኢሳይያስ 19:​12-15ን አንብብ ።) “ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፤ እነሆ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?”​—⁠ኤርምያስ 8:​9

ለይሖዋ ምልክትና ምሥክር መሆን

30. ‘የይሁዳ ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ’ የምትሆነው በምን መንገድ ነው?

30 ‘የግብጽ’ መሪዎች “እንደ ሴቶች ” አቅመ ደካማ ቢሆኑም አምላካዊ ጥበብ ለማግኘት የሚመጡ ግለሰቦች ይኖራሉ። የይሖዋ ቅቡዓንና ጓደኞቻቸው ‘የአምላክን በጎነት ይናገራሉ።’ (ኢሳይያስ 19:​16፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9) በሰይጣን ድርጅት ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። ኢሳይያስ ይህን ሁኔታ አሻግሮ በመመልከት እንዲህ ይላል:- “የይሁዳም ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል።” (ኢሳይያስ 19:​17 ) የታመኑት የይሖዋ መልእክተኞች ለሰዎች እውነቱን ያሳውቃሉ። ይህም ይሖዋ ይመጣሉ ብሎ በትንቢት የተናገራቸውን መቅሰፍቶች ማወጅን ይጨምራል። (ራእይ 8:​7-12፤ 16:​2-12) ይህ ለዓለም የሃይማኖት መሪዎች የሚረብሽ ዜና ነው።

31. (ሀ) በጥንት ዘመን ‘የከነዓን ቋንቋ’ በግብጽ ከተሞች የተነገረው እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችንስ?

31 ይህ እወጃ የሚያስገኘው አስገራሚ ውጤት ምንድን ነው? “በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከነዓን ቋንቋ የሚናገሩ፣ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።” (ኢሳይያስ 19:​18) ጥንት ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው ወደ ግብጽ የሸሹት ዕብራውያን የዕብራይስጥን ቋንቋ በግብጽ ከተሞች ይናገሩ በነበሩበት ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ኤርምያስ 24:​1, 8-10፤ 41:​1-3፤ 42:​9–43:​7፤ 44:​1) ዛሬ በዘመናዊቷ “ግብጽ” ግዛት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነውን ‘ንጹሕ ልሳን’ መናገርን የተማሩ ሰዎች አሉ። (ሶፎንያስ 3:​9) ከአምስቱ ምሳሌያዊ ከተሞች መካከል የአንዲቱ ስም “የጥፋት ከተማ” የሚል ነው። ይህም ‘የንጹህ ልሳን’ የተወሰነው ክፍል የሰይጣንን ድርጅት ከማጋለጥና ‘ከማፍረስ’ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚያመለክት ነው።

32. (ሀ) በግብጽ ምድር መካከል የሚገኘው “መሠዊያ” ምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓኑ በግብጽ ዳርቻ እንደ “ዓምድ” የሆኑት እንዴት ነው?

32 የይሖዋ ሕዝብ ለሚያከናውነው መልእክቱን የማወጅ ሥራ ምስጋና ይግባውና ታላቁ የአምላክ ስም በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እንደሚታወቅ ምንም ጥርጥር የለውም። “በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፣ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 19:​19) እነዚህ ቃላት ከአምላክ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና የመሠረቱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያላቸውን ቦታ የሚያመለክቱ ናቸው። (መዝሙር 50:​5) እንደ “መሠዊያ” ሆነው መሥዋዕቶቻቸውን ያቀርባሉ። “የእውነት ዓምድና መሠረት” በመሆን ደግሞ ስለ ይሖዋ በመመሥከር ላይ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​15፤ ሮሜ 12:​1፤ ዕብራውያን 13:​15, 16) እነርሱም ሆኑ ጓደኞቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” ከ230 በሚበልጡ አገሮችና የባሕር ደሴቶች የሚገኙ በመሆናቸው ‘በምድሪቱ መካከል’ ይገኛሉ ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ‘የዓለም ክፍል አይደሉም።’ (ዮሐንስ 10:​16፤ 17:​15, 16) ድንበሩን ተሻግረው ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመቀበል በዚህ ዓለምና በአምላክ መንግሥት ድንበር ላይ የቆሙ ያህል ነው።

33. ቅቡዓኑ ‘በግብጽ’ እንደ “ምልክት” እና “ምስክር” የሆኑት እንዴት ነው?

33 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፣ እርሱም መድኃኒትንና ኃያልን ሰድዶ ያድናቸዋልና።” (ኢሳይያስ 19:​20) ቅቡዓኑ እንደ “ምልክት” እና “ምስክር” በመሆን በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። (ኢሳይያስ 8:​18፤ ዕብራውያን 2:​13) በምድር ዙሪያ የተጨቆኑ ሰዎች ጩኸት ይሰማል። ይሁን እንጂ ሰብዓዊ መንግሥታት ሊረዷቸው አልቻሉም። ይሖዋ ግን ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ አዳኝ አድርጎ በመላክ ቅን የሆኑ ሰዎችን ሁሉ ነፃ ያወጣል። እነዚህ የመጨረሻ ቀናት በአርማጌዶን ጦርነት ሲደመደሙ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች እፎይታንና ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ።​—⁠መዝሙር 72:​2, 4, 7, 12-14

34. (ሀ) ይሖዋ በግብጻውያኑ ዘንድ ‘የታወቀ የሚሆነው’ እንዴት ነው? የሚያቀርቡለት መሥዋዕትና የሚሰጡት እጅ መንሻስ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ “ግብጽን” የሚመታው መቼ ነው? ከዚያ ቀጥሎ የሚከናወነው ፈውስስ ምንድን ነው?

34 እስከዚያው ድረስ ግን ሁሉም ዓይነት ሰዎች ይድኑ ዘንድ ትክክለኛውን እውቀት እንዲያገኙ የአምላክ ፈቃድ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) በመሆኑም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፣ ግብጻውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቁርባን ያመልካሉ፣ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል። እግዚአብሔርም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ እርሱም ይለመናቸዋል ይፈውሳቸውማል።” (ኢሳይያስ 19:​21, 22) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ካሉት ብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ግለሰብ ‘ግብጻውያን’ ይሖዋን አውቀው “ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡለታል። (ዕብራውያን 13:​15) ራሳቸውን ለእርሱ በመወሰን ለይሖዋ የሚሳሉ ሲሆን የታማኝነት አገልግሎት ማከናወን የሚያስችል የሕይወት ጎዳና በመከተል ይህን ስዕለታቸውን ይፈጽማሉ። ይሖዋ በአርማጌዶን በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ ከሚያሳርፈው ‘ምት’ በኋላ በመንግሥቱ አማካኝነት የሰውን ዘር ይፈውሳል። በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የሰው ልጅ መንፈሳዊ፣ አእምሮአዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ፍጽምና ያገኛል። ይህ በእርግጥም ፈውስ ነው!​—⁠ራእይ 22:​1, 2

‘ሕዝቤ የተባረከ ይሁን’

35, 36. በ⁠ኢሳይያስ 19:​23-25 ፍጻሜ መሠረት በጥንቱ ዓለም በግብጽ፣ በአሦር እና በእስራኤል መካከል የነበረው ግንኙነት ምንድን ነው?

35 ቀጥሎ ነቢዩ ስለ አንድ አስገራሚ ክንውን ይተነብያል:- “በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፣ አሦራዊውም ወደ ግብጽ፣ ግብጻዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብጻውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ [“ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ፣” NW ]። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:- ሕዝቤ ግብጽ፣ የእጄም ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን ብሎ ይባርካቸዋልና በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፣ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል።” (ኢሳይያስ 19:​23-25) አዎን፣ በግብጽና በአሦር መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት የሚመሠረትበት ቀን ይመጣል። እንዴት?

36 ይሖዋ ጥንት ከነበሩት ብሔራት ሕዝቡን ሲታደግ ወደ ነፃነት የሚያደርስ አውራ ጎዳና ያዘጋጀላቸው ያህል ነበር። (ኢሳይያስ 11:​16፤ 35:​8-10፤ 49:​11-13፤ ኤርምያስ 31:​21) ይህ ትንቢት በተወሰነ መጠን ፍጻሜውን ያገኘው ባቢሎን ድል ተነስታ ግዞተኞች ከአሦር፣ ከግብጽ እንዲሁም ከባቢሎን ወደ ተስፋይቱ ምድር በተመለሱ ጊዜ ነበር። (ኢሳይያስ 11:​11) ይሁን እንጂ ስለ ዘመናችን ምን ማለት ይቻላል?

37. ዛሬ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ‘በአሦር’ እና ‘በግብጽ’ መካከል አውራ ጎዳና አለ በሚያሰኝ መንገድ እየኖሩ ያለው እንዴት ነው?

37 ዛሬ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች “በምድር መካከል በረከት” ሆነዋል። እውነተኛውን አምልኮ ያስፋፋሉ። የመንግሥቱን መልእክት በሁሉም ብሔራት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ያዳርሳሉ። ከእነዚህ ብሔራት መካከል አንዳንዶቹ እንደ አሦር በእጅጉ በወታደራዊ ኃይል የሚታመኑ ናቸው። ሌሎች ብሔራት ደግሞ በዳንኤል ትንቢት ውስጥ በአንድ ወቅት ‘የደቡብ ንጉሥ’ ሆና እንደተገለጸችው እንደ ግብጽ ላላ ያለ አቋም ያላቸው ናቸው። (ዳንኤል 11:​5, 8) በወታደራዊ ኃይል ከሚታመኑትም ሆነ ላላ ያለ አቋም ካላቸው ብሔራት ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ ጎዳና መጓዝ ጀምረዋል። በዚህ መንገድ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በአንድነት ‘ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ’ ላይ ናቸው። በእነርሱ መካከል የብሔር ልዩነት የለም። እርስ በርሳቸው ከልብ የሚዋደዱ ከመሆናቸው የተነሣ ‘ከግብጽ ወደ አሦር ከአሦርም ወደ ግብጽ ይመጣሉ’ ሊባል ይችላል። ከአንዱ ወደ ሌላው የሚወስድ አውራ ጎዳና የተዘረጋ ያህል ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​17 NW 

38. (ሀ) እስራኤል ‘የግብጽ እና የአሦር ሦስተኛ’ የምትሆነው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ‘ሕዝቤ የተባረከ ይሁን’ የሚለው ለምንድን ነው?

38 ይሁንና እስራኤል ‘ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ’ የምትሆነው እንዴት ነው? ‘በፍጻሜው ዘመን’ መጀመሪያ ላይ በምድር ላይ ይሖዋን ከሚያገለግሉት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ነበሩ። (ዳንኤል 12:​9፤ ገላትያ 6:​16) ከ1930 ወዲህ ግን ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ብቅ ብለዋል። (ዮሐንስ 10:​16ሀ፤ ራእይ 7:​9) የግብጽና የአሦር አምሳያ ከሆኑት ብሔራት ወጥተው ወደ ይሖዋ የአምልኮ ቤት ይጎርፋሉ። ሌሎችም እንዲመጡ ይጋብዛሉ። (ኢሳይያስ 2:​2-4) ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጋር ተሰልፈው ተመሳሳይ የስብከት ሥራ ያከናውናሉ፣ ተመሳሳይ ፈተናዎች በጽናት ይጋፈጣሉ፣ አንድ ዓይነት ታማኝነትና የአቋም ጽናት ያሳያሉ እንዲሁም ከአንድ መንፈሳዊ ገበታ ይመገባሉ። በእርግጥም ቅቡዓኑና “ሌሎች በጎች” ‘አንድ መንጋ እረኛቸውም አንድ’ ነው። (ዮሐንስ 10:​16ለ) ይሖዋ ይህን ቅንዓታቸውንና ጽናታቸውን ሲመለከት ስለመደሰቱ የሚጠራጠር ይኖራልን? ‘ሕዝቤ የተባረከ ይሁን’ በማለት መናገሩ ምንም አያስገርምም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 አንዳንድ ምሁራን ‘ክንፍ ያላቸው ነፍሳት ላሉባት ምድር’ የሚለው መግለጫ በኢትዮጵያ አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የአንበጣ መንጋ የሚያመለክት ነው ይላሉ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 191 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍልስጥኤማውያን ተዋጊዎች በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ (በ12ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግብጻውያን የተዘጋጀ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ ምስል)

[በገጽ 192 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ የአንድ ሞዓባዊ ጦረኛ ወይም አምላክ ምስል (በ11ኛውና በ8ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መካከል ባለው ጊዜ የተሠራ)

[በገጽ 196 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶርያዊው ተዋጊ ግመል ሲጋልብ (በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ)

[በገጽ 198 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓመፀኛ የሆነው የሰው ዘር “ባሕር ” ሕዝባዊ ተቃውሞንና ዓመፅን ያነሳሳል

[በገጽ 203 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግብጽ ካህናት የይሖዋን ኃይል ሊገዳደሩ አልቻሉም