ይሖዋ ንጉሥ ነው
ምዕራፍ ሃያ
ይሖዋ ንጉሥ ነው
1, 2. (ሀ) የይሖዋን የቁጣ ጽዋ የሚጎነጩት እነማን ናቸው? (ለ) ይሁዳ ከቅጣት ታመልጥ ይሆን? እንዴት እናውቃለን?
ባቢሎን፣ ፍልስጥኤም፣ ሞዓብ፣ ሶርያ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኤዶም፣ ጢሮስ፣ አሦር ሁሉም የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ይጎነጫሉ። ኢሳይያስ በእነዚህ ጠላት ብሔራትና ከተሞች ላይ የሚደርሰውን ጥፋት በትንቢት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ይሁዳስ? የይሁዳ ነዋሪዎች በኃጢአተኛ አካሄዳቸው ሳይቀጡ ይቀራሉን? ታሪካዊ ዘገባው ከቅጣት እንደማያመልጡ የማያሻማ ማረጋገጫ ይሰጣል!
2 የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችው ሰማርያ ምን እንደደረሰባት ልብ በል። ይህ ብሔር ከአምላክ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ሳያከብር ቀርቷል። በዙሪያው ከነበሩት አሕዛብ ጸያፍ ተግባር አልራቀም። ይልቁንም የሰማርያ ሰዎች ‘እግዚአብሔርን ያስቆጡ ዘንድ ክፉ ነገር በማድረጋቸው እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጥቶ ከፊቱ ጥሏቸዋል።’ ‘የእስራኤል ሕዝብ ከምድሪቱ’ በኃይል ተባርሮ ‘ወደ አሦር ፈልሷል።’ (2 ነገሥት 17:9-12, 16-18, 23፤ ሆሴዕ 4:12-14) እስራኤል የገጠማት ነገር እህቷ ይሁዳም ምን እንደሚጠብቃት የሚጠቁም ነበር።
ኢሳይያስ ይሁዳ እንደምትጠፋ ይተነብያል
3. (ሀ) ይሖዋ የሁለቱን ነገድ የይሁዳ መንግሥት የተወው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ለማድረግ ወስኗል?
3 አንዳንዶቹ የይሁዳ ነገሥታት ታማኝ የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ታማኞች አልነበሩም። እንደ ኢዮአታም በመሰሉት የታመኑ ነገሥታት የግዛት ዘመን እንኳ ሕዝቡ ከሐሰት አምልኮ ሙሉ በሙሉ አልራቀም ነበር። (2 ነገሥት 15:32-35) የይሁዳ ክፋት የባሰ ደረጃ ላይ የደረሰው ደም በተጠማው ንጉሥ በምናሴ ዘመን ነበር። በአይሁዳውያን አፈ ታሪክ መሠረት ምናሴ የታመነው ነቢይ ኢሳይያስ በመጋዝ ተሰንጥቆ እንዲሞት ትእዛዝ በማስተላለፍ አስገድሎታል። (ከዕብራውያን 11:37 ጋር አወዳድር።) ይህ ክፉ ንጉሥ “እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን” አስቷል። (2 ዜና መዋዕል 33:9) በምናሴ የግዛት ዘመን ምድሪቱ ከነዓናውያን ከነበሩበት ጊዜ በከፋ ሁኔታ ተበላሽታ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። . . . ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፣ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፣ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፣ አስቆጥተውኝማልና።”—2 ነገሥት 21:11-15
4. ይሖዋ በይሁዳ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል? ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
4 ተገልብጦ ውስጡ ያለው ነገር ሁሉ እንደፈሰሰ ወጭት ምድሪቱ ነዋሪ አልባ ትሆናለች። ይሁዳና ኢየሩሳሌም የሚጠብቃቸው ይህ ጥፋት በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል። እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “እነሆ፣ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፣ ባድማም ያደርጋታል፣ ይገለብጣትማል፣ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል።” (ኢሳይያስ 24:1) በንጉሥ ናቡከደነፆር ዘመን ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ በወራሪው የባቢሎን ሠራዊት በወደሙና የይሁዳ ነዋሪዎች በሰይፍ ስለት፣ በረሃብና በቸነፈር ባለቁ ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። በሕይወት የተረፉት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በምርኮ የተወሰዱ ሲሆን ቀርተው የነበሩትም ጥቂቶች ወደ ግብጽ ሸሽተዋል። በዚህ መንገድ የይሁዳ ምድር ተንኮታኩቶና ሙሉ በሙሉ ነዋሪ አልባ ሆኖ ነበር። የቤት እንስሳት እንኳ አልቀሩም። ኦና የቀረው ምድር አራዊትና አእዋፍ የሚኖሩበት የፍርስራሽ ክምር ብቻ ያለበት ምድረ በዳ ሆኖ ነበር።
5. ከይሖዋ ፍርድ የሚያመልጥ ይኖር ይሆን? አብራራ።
5 በመጪው ፍርድ ወቅት በይሁዳ የተለየ አያያዝ የሚደረግላቸው ይኖሩ ይሆን? ኢሳይያስ መልሱን ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፣ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፣ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፣ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፣ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፣ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል። ምድር መፈታትን ትፈታለች፣ ፈጽማም ትበላሻለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።” (ኢሳይያስ 24:2, 3) ባለጸጋ መሆን ወይም በቤተ መቅደስ የማገልገል መብት ማግኘት የሚያመጣው ለውጥ አልነበረም። እገሌ ከገሌ ተብሎ የሚቀር የለም። ምድሪቱ ፍጹም ከመበላሸቷ የተነሳ በሕይወት የተረፉት ሁሉ ማለትም ካህን፣ ባሪያ፣ ጌታ፣ ገዥና ሻጭ ሳይል ሁሉም ወደ ግዞት መወሰድ ነበረባቸው።
6. ይሖዋ በረከቱን ከምድሪቱ የሚያነሳው ለምንድን ነው?
6 ኢሳይያስ የሚያሻማ ነገር እንዳይኖር ሲል መጪው ጥፋት ምን ያህል ስፋት እንዳለውና የሚመጣበት ምክንያት ጭምር ምን እንደሆነ ግልጽ አድርጓል:- “ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ። ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፣ ሕጉን ተላልፈዋልና፣ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፣ የዘላለሙንም [“ላልተወሰነ ጊዜ የሚዘልቀውን፣” NW] ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ።” (ኢሳይያስ 24:4-6) እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ሲወርሱ ምድሪቱ ‘ወተትና ማር የምታፈስስ’ ሆና አግኝተዋታል። (ዘዳግም 27:3) ያም ሆኖ ሕልውናቸው በይሖዋ በረከት የተመካ ነበር። በሥርዓቱ ቢሄዱና ትእዛዙን ቢጠብቁ ምድሪቱ “እህልዋን ትሰጣለች።” ሕጉንና ትእዛዙን ቢተላለፉ ግን ምድሪቱን ለማልማት የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ‘ከንቱ ይሆናል’ ምድሪቱም “እህልዋን አትሰጥም።” (ዘሌዋውያን 26:3-5, 14, 15, 20) የይሖዋም መርገም ‘ምድርን ትበላለች።’ (ዘዳግም 28:15-20, 38-42, 62, 63) አሁን ይሁዳ የሚጠብቃት ይህ እርግማን ነው።
7. የሕጉ ቃል ኪዳን ለእስራኤላውያን በረከት የሚሆነው እንዴት ነው?
7 ከኢሳይያስ ዘመን 800 ዓመት ቀደም ብሎ እስራኤላውያን በፈቃደኛነት ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና በመመሥረት ከዚያ ጋር ተስማምተው ለመኖር ቃል ገብተው ነበር። (ዘጸአት 24:3-8) የሕጉ ቃል ኪዳን የይሖዋን ትእዛዝ ቢጠብቁ የተትረፈረፈ በረከቱን እንደሚያገኙ ቃል ኪዳኑን ቢያፈርሱ ደግሞ በረከቱን እንደሚያጡና በጠላቶቻቸው በምርኮ እንደሚወሰዱ የሚገልጽ ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6፤ ዘዳግም 28:1-68) በሙሴ አማካኝነት የተሰጠው ይህ የሕግ ቃል ኪዳን ላልተወሰነና ገደብ ለሌለው ጊዜ ተግባራዊ የሚሆን ነበር። መሲሑ እስኪመጣ ድረስ እስራኤላውያንን የሚጠብቃቸው ቃል ኪዳን ነበር።—ገላትያ 3:19, 24
8. (ሀ) ሕዝቡ ‘ሕጉን የተላለፉትና’ ‘ሥርዓቱን የለወጡት’ እንዴት ነው? (ለ) ‘ከሚረግፉት’ መካከል ‘ታላላቆቹ’ የመጀመሪያ የሆኑት እንዴት ነው?
8 ይሁን እንጂ ሕዝቡ “ላልተወሰነ ጊዜ የሚዘልቀውን ቃል ኪዳን” አፍርሷል። ከመለኮታዊ ምንጭ ያገኙትን ሕግ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ተላልፈዋል። በሕግ ነክ ጉዳዮች ረገድ ይሖዋ ከሰጣቸው የተለየ ዘጸአት 22:25፤ ሕዝቅኤል 22:12) ከዚህ የተነሣ ሕዝቡ ከምድሪቱ ይወገዳል። ምሕረት የሌለው ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ ጥበቃውንና ሞገሱን በማንሳቱ ምክንያት ‘ከሚረግፉት’ ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ‘ታላላቆች’ ማለትም ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው ናቸው። በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የኢየሩሳሌም ጥፋት እየተቃረበ ሲመጣ በመጀመሪያ ግብጻውያን ከዚያም ባቢሎናውያን የይሁዳን ነገሥታት ገባር ንጉሥ አድርገው ይገዟቸዋል። በዚህ መሠረት ወደ ባቢሎን በምርኮ ከተወሰዱት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል ንጉሥ ኢዮአቄምና ሌሎች የንጉሣዊው ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።—2 ዜና መዋዕል 36:4, 9, 10
አሠራር በመከተል “ሥርዓቱን ለውጠዋል።” (ደስታ ከምድሪቱ ይሸሻል
9, 10. (ሀ) ግብርና በእስራኤል ውስጥ የነበረው ሚና ምንድን ነው? (ለ) ‘እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች መቀመጡ’ ያለው ትርጉም ምንድን ነው?
9 የእስራኤል ብሔር በግብርና የሚተዳደር ኅብረተሰብ ነው። ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የተሠማሩት በእርሻና በከብት እርባታ ሥራ ነው። በመሆኑም የእርሻ ሥራ በእስራኤላውያኑ ሕግ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ተሰጥቶታል። በሰባት ዓመት አንድ ጊዜ ምድሪቱ የምታርፍበት ሊከበር የሚገባው የሰንበት ዕረፍት ተደንግጎ የነበረ ሲሆን ይህም አፈሩ መልሶ ለምነቱን እንዲያገኝ ይረዳዋል። (ዘጸአት 23:10, 11፤ ዘሌዋውያን 25:3-7) ብሔሩ እንዲያከብራቸው የታዘዘው ሦስቱ ዓመታዊ በዓላትም ከእርሻ ወቅቶች ጋር እንዲገጣጠሙ ተደርጓል።—ዘጸአት 23:14-16
10 የወይን እርሻዎች በምድሪቱ በብዛት ይገኙ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች የወይን እርሻ ውጤት የሆነው የወይን ጠጅ ‘ልብን ደስ የሚያሰኝ’ የአምላክ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። (መዝሙር 104:15) እያንዳንዱ ‘ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ መቀመጡ’ በአምላክ የጽድቅ አገዛዝ ሥር የሚያገኘውን ብልጽግና፣ ሰላምና መረጋጋት የሚያመለክት ነው። (1 ነገሥት 4:25፤ ሚክያስ 4:) ጥሩ የወይን ምርት የሚገኝበት ወቅት እንደ በረከት የሚታይ ሲሆን ለደስታና ለዝማሬም ምክንያት ይሆናል። ( 4መሳፍንት 9:27፤ ኤርምያስ 25:30 NW) ውጤቱ ተቃራኒ ሲሆን ደግሞ የተገላቢጦሽ ይሆናል። ወይኑ ሲረግፍ ወይም ምንም ፍሬ ሳይሰጥ ሲቀርና የወይን እርሻው እሾኽ የበቀለበት ባድማ ሲሆን ይሖዋ በረከቱን ከእነርሱ እንደወሰደ ግልጽ ይሆናል። ይህ ታላቅ የኃዘን ወቅት ይሆናል።
11, 12. (ሀ) የይሖዋ ፍርድ የሚያስከትለውን ሁኔታ ኢሳይያስ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢሳይያስ ከፊታቸው ምን የጨለመ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ጠቅሷል?
11 እንግዲያው ኢሳይያስ ይሖዋ ከምድሩ በረከቱን መውሰዱ የሚያስከትለውን ውጤት በምሳሌ ለማስረዳት የወይን እርሻንና ፍሬውን መጠቀሙ ተገቢ ነበር:- “የወይን ጠጅ አለቀሰች፣ የወይን ግንድ ደከመች፣ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። የከበሮው ሐሤት ቀርቶአል፣ የደስተኞች ድምፅ ዝም ብሎአል፣ የመሰንቆ [“የበገናው፣” NW] ደስታ ቀርቶአል። እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፣ የሚያሰክርም መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል። ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ቤት ሁሉ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ። ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፣ የምድርም ሐሤት ፈልሶአል። ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፣ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል [“የፍርስራሽ ክምር ሆኗል፣” NW]።”—ኢሳይያስ 24:7-12
12 ከበሮና በገና ይሖዋን ለማወደስና ደስታን ለመግለጽ የሚያገለግሉ ተወዳጅ መሣሪያዎች ናቸው። (2 ዜና መዋዕል 29:25፤ መዝሙር 81:2) በዚህ የመለኮታዊ ቅጣት ወቅት ሙዚቃቸው አይሰማም። አስደሳች የወይን መከርም አይኖርም። በሮችዋ ‘የፍርስራሽ ክምር’ በሆኑትና ማንም እንዳይገባባቸው ‘ቤቶቿ ሁሉ በተዘጉት’ በኢየሩሳሌም ፍርስራሽ ውስጥ የደስታ ድምፅ አይሰማም። በተፈጥሮ በጣም ለም የነበረው የዚያ ምድር ነዋሪዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ጊዜ ምንኛ የጨለመ ነው!
ቀሪዎች ‘እልል ይላሉ’
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ስለ መከር አሰባሰብ ያወጣቸው ሕጎች ምንድን ናቸው? (ለ) ኢሳይያስ ከይሖዋ ፍርድ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች እንዳሉ ለማስረዳት ስለ መከር አሰባሰብ የሰጠውን ሕግ እንደ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ሐ) ከፊታቸው መከራ የሞላባቸው የጨለማ ወቅቶች ይጠብቋቸው የነበረ ቢሆንም የታመኑ አይሁዳውያን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችሉ ነበር?
13 እስራኤላውያን የወይራ ፍሬ ለመሰብሰብ ፍሬው እንዲረግፍላቸው ዛፉን በበትር ይመቱ ነበር። የአምላክ ሕግ የቀሩትን ፍሬዎች ለመልቀም ወደ ቅርንጫፎቹ እንዳይወጡ ይከለክላቸው ነበር። የወይን ፍሬያቸውንም ከሰበሰቡ በኋላ የቀረውን ለመልቀም መመለስ አልነበረባቸውም። ከመከሩ የቀረውን ፍሬ ለድሆች ማለትም “ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም” ቃርሚያ መተው ነበረባቸው። (ዘዳግም 24:19-21) ኢሳይያስ እነዚህን በሚገባ የሚታወቁ ሕግጋት መሠረት በማድረግ ከይሖዋ ፍርድ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ስለመኖራቸው የሚገልጸውን የሚያጽናና እውነታ በምሳሌ አስረድቷል:- “የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፣ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፣ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል። እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፣ እልልም ይላሉ፣ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ [“በብርሃን ምድር፣” NW]፣ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል።”—ኢሳይያስ 24:13-16ሀ
14 ከመከር በኋላ በዛፉ ወይም በወይኑ ተክል ላይ የሚቀር ፍሬ እንደነበረ ሁሉ ይሖዋ የፍርድ እርምጃውን ከወሰደ በኋላ “ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም” ያህል የሚቀሩ ጥቂቶች ይኖራሉ። በቁጥር 6 ላይ እንደተጠቀሰው ነቢዩ “ጥቂት ሰዎች ይቀራሉ” በማለት ስለ እነዚሁ ሰዎች ተናግሯል። ምንም ጥቂት ቢሆኑ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ከሚመጣው ጥፋት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። ከጊዜ በኋላም ቀሪዎች ከምርኮ ተመልሰው በምድሪቱ መኖር ይጀምራሉ። (ኢሳይያስ 4:2, 3፤ 14:1-5) ቅን የሆኑ ሰዎች ጨለማ የሆነ የፈተና ወቅት የሚገጥማቸው ቢሆንም ከፊታቸው የነፃነትና የደስታ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ከመመልከታቸውም ሌላ ኢሳይያስ እውነተኛ የአምላክ ነቢይ እንደነበረ ይገነዘባሉ። ስለ መልሶ መቋቋም የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ በዓይናቸው በማየታቸው በደስታ ይፈነድቃሉ። ከሜድትራኒያን የባሕር ደሴቶች፣ ‘በብርሃን ምድር’ (በፀሐይ መውጫ፣ በምሥራቅ) ካለችው ባቢሎን ወይም ከሌላ ሩቅ ቦታም ቢሆን ከየተበታተኑበት “ለጻድቁ ክብር ይሁን” በሚል ዝማሬ አምላክን ያወድሳሉ!
ከይሖዋ ፍርድ ማምለጥ አይቻልም
15, 16. (ሀ) ኢሳይያስ በሕዝቡ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ሲያስብ ምን ተሰምቶታል? (ለ) ታማኝ ያልሆኑት የምድሪቱ ነዋሪዎች ምን ይገጥማቸዋል?
15 አሁን ግን የሚደሰቱበት ጊዜ አይደለም። ኢሳይያስ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች በወቅቱ ወደ ነበረው ሁኔታ ሲመልሳቸው እንዲህ ብሏል:- “እኔ ግን:- ከሳሁ፣ ከሳሁ፣ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፤ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ። በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፣ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፣ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፣ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። ምድር ተሰባበረች፣ ምድር ፈጽማ ደቀኢሳይያስ 24:16ለ-20
ቀች፣ ምድር ተነዋወጠች። ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገደገዳለች፣ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፣ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም።”—16 ኢሳይያስ በሕዝቡ ላይ በሚደርሰው ነገር እጅግ አዝኗል። በዙሪያው ያለው ነገር ሕመምና ወዮታ አስከትሎበታል። ወንጀለኞች በዝተው የምድሪቱን ነዋሪ እያስጨነቁት ነው። ይሖዋ ጥበቃውን ሲያነሳ ከዳተኛ የሆኑት የይሁዳ ነዋሪዎች ቀን ከሌት የስጋት ኑሮ ለመምራት ይገደዳሉ። ለሕይወታቸው ዋስትና አይኖራቸውም። የይሖዋን ትእዛዛት በመተዋቸውና አምላካዊውን ጥበብ ቸል በማለታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው ቅጣት የሚያመልጡበት ቀዳዳ የለም። (ምሳሌ 1:24-27) ምንም እንኳ በምድሪቱ ያሉ ወንጀለኞች ሕዝቡን በሐሰትና በማታለል ወደ ጥፋት ለመምራት ምንም ችግር እንደሌለ ሊያሳምኑት ቢሞክሩም ጥፋት መምጣቱ አይቀርም። (ኤርምያስ 27:9-15) ጠላት ከውጭ መጥቶ ይበዘብዛቸዋል፤ በምርኮም ያግዛቸዋል። ይህ ሁሉ ነገር ኢሳይያስን አስጨንቆታል።
17. (ሀ) ማምለጥ የማይቻለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ የቅጣት ኃይል ከሰማይ ሲገለጥ ምድሪቱ ምን ትሆናለች?
17 ይሁንና ነቢዩ ምንም ማምለጫ እንደሌለ የመናገር ግዴታ ነበረበት። አሞጽ 5:18, 19 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ የቅጣት ኃይል ከሰማይ በመገለጥ የምድሪቱን መሠረት ያናጋል። ምድሪቱ ከኃጢአቷ ክብደት የተነሣ እንደሰከረ ሰው ትውተረተርና ትወድቃለች። እንደገና መነሳትም አትችልም። (አሞጽ 5:2) ይሖዋ የሚሰጠው ፍርድ የመጨረሻ ይሆናል። ምድሪቱ ፍጹም ጥፋትና ውድመት ይጠብቃታል።
ሰዎች በየትም አቅጣጫ ለማምለጥ ቢሞክሩ ይያዛሉ። አንዳንዶች አንዱን ችግር ያመልጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌላ ችግር ላይ ይወድቃሉ። ምንም አስተማማኝ ሁኔታ አይኖርም። ሁኔታው ከአንዱ ወጥመድ አምልጦ ሌላ ወጥመድ ውስጥ ከሚወድቅ የሚታደን እንስሳ የተለየ አይሆንም። (ከይሖዋ በክብር ይገዛል
18, 19. (ሀ) ‘በከፍታ ያለው ሠራዊት’ ማንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል? ‘በግዞት ቤት የሚዘጉትስ’ እንዴት ነው? (ለ) ‘በከፍታ ያለው ሠራዊት’ ‘ከብዙ ቀን’ በኋላ የሚጎበኘው እንዴት ነው? (ሐ) ይሖዋ ‘ወደ ምድር ነገሥታት’ ትኩረቱን የሚያዞረው እንዴት ነው?
18 አሁን ደግሞ የኢሳይያስ ትንቢት አድማሱን በማስፋት የይሖዋን ዓላማ የመጨረሻ አፈጻጸም ይጠቁማል:- “በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፣ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። ግዞተኞች በጉድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፣ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፣ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጐበኛሉ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፣ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።”—ኢሳይያስ 24:21-23
19 ‘በከፍታ ያለ ሠራዊት’ የሚለው መግለጫ ‘የጨለማ ዓለም ገዦች በሰማያዊ ስፍራም ያሉ የክፋት መንፈሳዊ ሠራዊት’ የሆኑትን አጋንንት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 6:12) እነዚህ የዓለም ኃይል በነበሩት መንግሥታት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበራቸው። (ዳንኤል 10:13, 20፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ዓላማቸው ሰዎችን ከይሖዋና ከንጹህ አምልኮው ማራቅ ነው። እስራኤላውያን በዙሪያቸው እንዳሉት አሕዛብ ልማድ በብልሹ ልማዶች ተጠላልፈው የአምላክ መለኮታዊ ቅጣት እንዲወርድባቸው በማሳሳት ረገድ በጣም ተሳክቶላቸዋል! ይሁን እንጂ ሰይጣንና አጋንንቱ አምላክ ፊቱን በእነርሱና እነርሱ በአምላክ ላይ እንዲያምፁና ሕጉን እንዲተላለፉ ባደረጓቸው ‘የምድር ነገሥታት’ ላይ ሲያዞር ስለ ሥራቸው መልስ ለመስጠት ይገደዳሉ። (ራእይ 16:13, 14) ኢሳይያስ ሁኔታውን በምሳሌያዊ መንገድ ሲገልጽ እንደሚሰበሰቡና ‘በግዞት ቤት እንደሚዘጋባቸው’ ተናግሯል። ‘ከብዙ ቀንም በኋላ’ ምናልባትም ሰይጣንና አጋንንቱ (‘የምድር ነገሥታትን’ አይጨምርም) በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ለጊዜው ብቻ ሲፈቱ አምላክ የሚገባቸውን የመጨረሻ የቅጣት እርምጃ ይወስድባቸዋል።—ራእይ 20:3, 7-10
20. ጥንትም ሆነ በዘመናችን ይሖዋ ‘ንጉሥ የሆነው’ እንዴትና መቼ ነው?
20 በዚህ መንገድ ይህ የኢሳይያስ ትንቢት ለአይሁዳውያን ግሩም ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የጥንቷ ባቢሎን እንድትወድቅ በማድረግ አይሁዳውያኑን ወደ ትውልድ አገራቸው ይመልሳቸዋል። በ537 ከዘአበ ለሕዝቡ ሲል በዚህ መንገድ ኃይሉንና ሉዓላዊነቱን ሲያሳይ በእርግጥም ‘አምላካችሁ ነግሦአል’ ሊባልላቸው ይችል ነበር። (ኢሳይያስ 52:7) በዘመናችንም ይሖዋ በ1914 ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማያዊ መንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ ሲሾም ‘ነግሦአል።’ (መዝሙር 96:10) በ1919 መንፈሳዊ እስራኤልን ከታላቂቱ ባቢሎን እስር ነፃ በማውጣት የንግሥና ሥልጣኑን ባሳየበት ጊዜም ‘ነግሦአል።’
21. (ሀ) ‘ሙሉ ጨረቃና አንጸባራቂዋ ፀሐይ የሚያፍሩት’ እንዴት ነው? (ለ) ታላቅ ፍጻሜውን የሚያገኝ የሚያስተጋባ ጥሪ የትኛው ነው?
21 ይሖዋ ታላቂቱ ባቢሎንንና የቀረውን ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ እንደገና ‘ንጉሥ ይሆናል።’ (ዘካርያስ 14:9፤ ራእይ 19:1, 2, 19-21) ከዚያ በኋላ የይሖዋ ንጉሣዊ አገዛዝ ዕጹብ ድንቅ ከመሆኑ የተነሣ አንጸባራቂ የሆነችው ሙሉ ጨረቃም ሆነች ቀን ላይ ደምቃ የምትታየው ፀሐይ አይወዳደሩትም። (ከራእይ 22:5 ጋር አወዳድር።) ፀሐይና ጨረቃ ራሳቸውን ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ክብር ጋር በማወዳደራቸው የሚያፍሩ ያህል ነው። ይሖዋ የሁሉ የበላይ ገዥ ይሆናል። ሁሉን ቻይነቱና ክብሩ ለሁሉም ግልጽ ሆኖ ይታያል። (ራእይ 4:8-11፤ 5:13, 14) ይህ እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው! በዚያ ወቅት በመዝሙር 97:1 ላይ ያለው ጥሪ ታላቅ ፍጻሜውን አግኝቶ በመላው ምድር ያስተጋባል:- “እግዚአብሔር ነገሠ ምድርም ሐሴትን ታድርግ፣ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው።”
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 262 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙዚቃና ደስታ በምድሪቱ አይሰሙም
[በገጽ 265 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መከር ከተሰበሰበ በኋላ ዛፍ ላይ እንደሚቀር ፍሬ አንዳንዶች ከይሖዋ የቅጣት እርምጃ በሕይወት ይተርፋሉ
[በገጽ 267 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢሳይያስ ሕዝቡ ስለሚጠብቀው ዕጣ ሲያስብ እጅግ አዝኗል
[በገጽ 269 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፀሐይም ሆነች ጨረቃ በክብር ከይሖዋ ጋር አይተካከሉም