በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አምላክ ለቀሪዎቹ ምሕረት አሳየ

ይሖዋ አምላክ ለቀሪዎቹ ምሕረት አሳየ

ምዕራፍ ስድስት

ይሖዋ አምላክ ለቀሪዎቹ ምሕረት አሳየ

ኢሳይያስ 4:​2-6

1, 2. ነቢዩ ኢሳይያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?

ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት አንድ አካባቢ ኃይለኛ በሆነ ዓውሎ ነፋስ ይመታል። የተከሰተው ኃይለኛ ነፋስ፣ ነጎድጓዳማ ዝናብና ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቤቶችን በማፈራረስ፣ ሰብል በማውደምና የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ምድሪቱን እንዳልነበረች ያደርጋታል። ሆኖም አካባቢውን ያወደመው ዓውሎ ነፋስ ወዲያው ያልፍና ፀጥታ ይነግሣል። ከዚህ ውድመት ለተረፉት ሰዎች ይህ የመልሶ መቋቋምና የግንባታ ጊዜ ነው።

2 ነቢዩ ኢሳይያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን በሚመለከት ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚከሰት በትንቢት ተናግሯል። የመለኮታዊ ፍርድ ጥቁር ደመና በሚያስፈራ መንገድ እየተከማቸ ነው። ደግሞም ይህ የሆነበት በቂ ምክንያት አለ! የብሔሩ ኃጢአት ከብዶ ነበር። ገዥዎቹም ሆኑ ሕዝቡ ምድሪቱን በግፍና በደም መፋሰስ ሞልተዋት ነበር። ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት የይሁዳን ኃጢአት በማጋለጥ በዚህ ዓመፀኛ ብሔር ላይ ፍርዱን እንደሚያስፈጽም አስጠንቅቋል። (ኢሳይያስ 3:​25) ከዚህ ዓውሎ ነፋስ ማግስት ይሁዳ ጨርሶ ባድማ ትሆናለች። ይህ ሁኔታ ኢሳይያስን አሳዝኖት መሆን አለበት።

3. በ⁠ኢሳይያስ 4:​2-6 ላይ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መልእክት ምን ምሥራች ይዟል?

3 ይሁን እንጂ ምሥራች አለ! እንደ ዓውሎ ነፋስ የሚመጣው የይሖዋ የጽድቅ ፍርድ ካለፈ በኋላ በሕይወት የሚተርፉ ቀሪዎች ይኖራሉ። አዎን፣ ይሖዋ በይሁዳ ላይ የሚወስደው የፍርድ እርምጃ በምሕረት የለዘበ ነው! በ⁠ኢሳይያስ 4:​2-6 ላይ በመንፈስ አነሳሽነት ተመዝግቦ የሚገኘው የኢሳይያስ መልእክት ያንን የተባረከ ጊዜ አሻግሮ በመመልከት የተነገረ ነው። ፀሐይ ከደመናው በስተጀርባ ብርሃኗን የፈነጠቀች ያህል ትዕይንቱ በ⁠ኢሳይያስ 2:​6–4:​1 ላይ ከተገለጹት የፍርድ እርምጃዎችና መልእክቶች በአዲስ መልክ ብቅ ወዳሉት ውብ ምድርና ሕዝብ ይቀየራል።

4.ኢሳይያስ ቀሪዎቹ ተመልሰው ስለ መቋቋማቸው የተናገረውን ትንቢት መመርመር የሚገባን ለምንድን ነው?

4 የቀሪዎቹን መልሶ መቋቋምና ከዚያ በኋላ የሚያገኙትን የተረጋጋ ሕይወት በተመለከተ የሚናገረው የኢሳይያስ ትንቢት “በዘመኑ ፍጻሜ” ማለትም በጊዜያችንም ተፈጻሚነት ይኖረዋል። (ኢሳይያስ 2:​2-4) እንግዲያውስ ይህንን ወቅታዊ መልእክት እንመርምር። ይህን የምናደርገው ትንቢታዊ መልእክት ያዘለ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ስለ ይሖዋ ምሕረትና እኛም በግለሰብ ደረጃ የእርሱን ምሕረት ማግኘት ስለምንችልበት መንገድ ስለሚያስተምረንም ነው።

“የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ”

5, 6. (ሀ) ኢሳይያስ ከመጪው ዓውሎ ነፋስ በኋላ የሚኖረውን ሰላም የሰፈነበት ጊዜ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) “ቁጥቋጥ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ይህስ ስለ ይሁዳ ምድር ምን ይጠቁማል?

5 ኢሳይያስ ከፊታቸው ከሚጠብቃቸው ከባድ ጥፋት ባሻገር ስለሚያገኙት የበለጠ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ በማሰብ ፍቅራዊ በሆነ ስሜት መናገር ይጀምራል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ ለጌጥና ለክብር ይሆናል፣ ከእስራኤልም ወገን ላመለጡ ሰዎች የምድሪቱ ፍሬ ለትምክሕትና ለውበት ይሆናል።”​—⁠ኢሳይያስ 4:​2

6 ኢሳይያስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ መልሶ መቋቋም ነው። “ቁጥቋጥ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘እንደ ቀንበጥና ቅርንጫፍ ያለ የሚበቅልን ነገር’ ያመለክታል። ከይሖዋ ከሚገኝ ብልጽግና፣ ጭማሪ እና በረከት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ መንገድ ኢሳይያስ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው የይሁዳ ባድማነት እስከ መጨረሻው እንደማይቀጥል የሚጠቁም ተስፋ ሰጥቷል። በአንድ ወቅት የበለጸገ የነበረው የይሁዳ ምድር በይሖዋ በረከት እንደገና የተትረፈረፈ ፍሬ መስጠት ይጀምራል። *​—⁠ዘሌዋውያን 26:​3-5

7. የይሖዋ ቁጥቋጥ ‘ለጌጥና ለክብር’ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

7 ኢሳይያስ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ለውጥ ታላቅ መሆኑን ለማመልከት ሕያው የሆኑ መግለጫዎችን ተጠቅሟል። የይሖዋ ቁጥቋጥ “ለጌጥና ለክብር” ይሆናል። “ጌጥ” የሚለው ቃል ይሖዋ የተስፋይቱን ምድር በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ለእስራኤላውያን በሰጠበት ጊዜ ምድሪቱ የነበራትን ውበት ያስታውሰናል። በጣም ውብ ከመሆኗ የተነሣ “የምድር ሁሉ ጌጥ [“ፈርጥ፣” ኒው አሜሪካን ባይብል]” እንደሆነች ተደርጋ ተቆጥራለች። (ሕዝቅኤል 20:​6) ስለዚህ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ይሁዳ መልሳ የቀድሞ ክብሯንና ውበቷን እንደምታገኝ ለሕዝቡ ማረጋገጫ የሚሰጡ ነበሩ። በእርግጥም ደግሞ በምድር ላይ እንደ ፈርጥ ትሆናለች።

8. ተመልሳ የተቋቋመችው ምድር የተላበሰችውን ውበት እያጣጣሙ የሚደሰቱት እነማን ይሆናሉ? ኢሳይያስስ ስሜታቸውን የገለጸው እንዴት ነው?

8 ይሁንና ምድሪቷ ዳግም በምትላበሰው ውበት የመደሰት አጋጣሚ የሚያገኙት እነማን ናቸው? ኢሳይያስ ‘ከእስራኤል ወገን ያመለጡት’ እንደሆኑ ጽፏል። አዎን፣ አስቀድሞ ከተነገረው የሚያዋርድ ጥፋት የሚተርፉ አንዳንዶች ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 3:​25, 26) ከተራፊዎቹ መካከል የቀሩት ወደ ይሁዳ ተመልሰው በመልሶ ግንባታው ሥራ ይካፈላሉ። ለእነዚህ ተመላሾች ማለትም ‘ከእስራኤል ላመለጡት ሰዎች’ ተመልሳ የምትቋቋመው ምድራቸው የምትለግሰው የተትረፈረፈ ፍሬ ‘ለትምክህትና ለውበት’ ይሆንላቸዋል። (ኢሳይያስ 4:​2 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ከተማዋ በባድማነት ያሳለፈችው የውርደት ወቅት በአዲስ የኩራት መንፈስ ይተካል።

9. (ሀ) ኢሳይያስ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት በ537 ከዘአበ ምን ነገር ተከናውኗል? (ለ) ‘ያመለጡ’ የተባሉት ሰዎች በግዞት እያሉ የተወለዱትን ይጨምራሉ ማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

9 ልክ ኢሳይያስ እንደተናገረው በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉና ብዙ እስራኤላውያን በተገደሉ ጊዜ እንደ ዓውሎ ነፋስ ያለው ፍርድ መጥቷል። አንዳንዶቹ በሕይወት ተርፈው ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ምሕረት ባይሆን ኖሮ ሰው የሚባል ባልቀረ ነበር። (ነህምያ 9:​31) በመጨረሻ ይሁዳ ሙሉ በሙሉ ባድማ ሆነች። (2 ዜና መዋዕል 36:​17-21) ከዚያም የምሕረት አምላክ በ537 ከዘአበ ‘ያመለጡት ሰዎች’ እውነተኛውን አምልኮ ለማቋቋም ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ ፈቀደ። * (ዕዝራ 1:​1-4፤ 2:​1) ከግዞት የተመለሱት እነዚህ ሰዎች ያሳዩት ልባዊ ንስሐ በ⁠መዝሙር 137 ላይ ውብ በሆነ መንገድ ተገልጿል። ይህ መዝሙር የተጻፈው በምርኮ እያሉ ወይም ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ሳይሆን አይቀርም። በይሁዳም መሬቱን አርሰው ዘር ዘርተዋል። አምላክ ምድሪቱ ፍሬያማ እንደነበረችው ‘ኤድን ገነት’ እንድታብብ በማድረግ ጥረታቸውን እየባረከላቸው እንዳለ ሲመለከቱ ምን እንደተሰማቸው ገምት!​—⁠ሕዝቅኤል 36:​34-36

10, 11. (ሀ) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ግዞት ሥር ነበሩ ማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎችን የባረካቸው እንዴት ነው?

10 በዘመናችንም ተመሳሳይ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተከናውኗል። በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ መንፈሳዊ ምርኮኛ ሆነው ነበር። (ራእይ 17:​5) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ምንም እንኳ ብዙ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ትተው የነበረ ቢሆንም ከአንዳንድ ባቢሎናዊ ሐሳቦችና ድርጊቶች ገና አልተላቀቁም ነበር። ቀሳውስቱ በቆሰቆሱት ተቃውሞ ምክንያት አንዳንዶቹ ቃል በቃል ወኅኒ ወርደው ነበር። መንፈሳዊ ምድራቸው ማለትም ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ርስታቸው ባድማ ሆኖ ነበር።

11 ይሁን እንጂ በ1919 የፀደይ ወቅት ይሖዋ ለእነዚህ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ምሕረት አሳየ። (ገላትያ 6:​16) ንስሐቸውንና እርሱን በእውነት ለማምለክ ያላቸውን ፍላጎት በመመልከት ቃል በቃል ከነበሩበት ወኅኒ ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊውም ምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። እነዚህ ‘ያመለጡ ሰዎች’ አምላክ ወደሰጣቸውና ብዙ ፍሬ እንዲያፈራ ወዳደረገው መንፈሳዊ ርስት ተመልሰዋል። ይህ መንፈሳዊ ርስት ጋባዥና ማራኪ እይታ ያለው በመሆኑ አምላክን የሚፈሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀሪዎቹ ጋር በአምልኮ ለመተባበር ተስበዋል።

12. የኢሳይያስ ቃላት ይሖዋ ለሕዝቡ ያሳየውን ምሕረት ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?

12 እዚህ ላይ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት አምላክ ለሕዝቡ ያሳየውን ምሕረት ጎላ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ለይሖዋ ጀርባቸውን ቢሰጡም እርሱ ግን ንስሐ ለገቡት ቀሪዎች ምሕረት አሳይቷል። ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችም እንኳ ተስፋ ኖሯቸው ወደ ይሖዋ መመለስ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል። ይሖዋ የተሰበረውን ልብ ስለማይንቅ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች በፍጹም የይሖዋን ምሕረት ሊያገኙ እንደማይችሉ ሊሰማቸው አይገባም። (መዝሙር 51:​17) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል።” (መዝሙር 103:​8, 13) በእርግጥም እንዲህ ያለውን መሐሪ አምላክ ሁላችንም ልናወድሰው ይገባል!

ቀሪዎች በይሖዋ ፊት ቅዱስ ይሆናሉ

13. በ⁠ኢሳይያስ 4:​3 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ምሕረት የሚያሳያቸውን ቀሪዎች ኢሳይያስ የገለጻቸው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ ምሕረት የሚያሳያቸው ቀሪዎች እነማን እንደሆኑ አይተናል። አሁን ግን ኢሳይያስ ስለ እነርሱ ይበልጥ ዝርዝር መግለጫ ይሰጣል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጽዮን የቀረ በኢየሩሳሌምም የተረፈ፣ በኢየሩሳሌም ለሕይወት የተጻፈ ሁሉ፣ ቅዱስ ይባላል።”​—⁠ኢሳይያስ 4:​3, 4

14. ‘የቀሩት’ እና ‘የተረፉት’ የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋስ ምሕረት የሚያሳያቸው ለምንድን ነው?

14 ‘የቀሩ’ እና ‘የተረፉ’ የተባሉት እነማን ናቸው? በፊተኛው ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ያመለጡት ሰዎች ማለትም ወደ ይሁዳ የመመለስ አጋጣሚ የሚያገኙት ግዞተኛ አይሁዳውያን ናቸው። አሁን ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ምሕረት የሚያደርግበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጽ ኢሳይያስ ‘ለእርሱ ቅዱስ እንደሚሆኑ’ ተናግሯል። ቅድስና ማለት “ሃይማኖታዊ ንጽሕና ወይም ጥራት፤ የተለየ መሆን” ማለት ነው። ቅዱስ መሆን በቃልም ይሁን በድርጊት ንጹሕና የጠሩ መሆንን እንዲሁም ትክክለኛና አግባብ ስለሆነው ነገር ይሖዋ ያወጣውን የአቋም ደረጃ ጠብቆ መገኘትን ይጨምራል። አዎን፣ ‘ለእርሱ ቅዱስ’ ለሆኑት ሰዎች ምሕረቱን ያሳያቸዋል እንዲሁም ወደ ‘ቅድስቲቱ ከተማ’ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ይፈቅድላቸዋል።​—⁠ነህምያ 11:​1

15. (ሀ) ‘በኢየሩሳሌም ለሕይወት የተጻፉ’ የሚለው አገላለጽ የትኛውን የአይሁዳውያን ልማድ ያስታውሰናል? (ለ) የኢሳይያስ ቃላት ምን ልብ ሊባል የሚገባው ማስጠንቀቂያ ይዘዋል?

15 እነዚህ የታመኑ ቀሪዎች በዚህች ምድር መኖራቸውን ይቀጥሉ ይሆን? ኢሳይያስ ‘በኢየሩሳሌም ለሕይወት ይጻፋሉ’ ሲል ቃል ገብቷል። ይህም አይሁዳውያን የነበራቸውን የእስራኤልን ቤተሰቦችና ነገዶች በጥንቃቄ የመመዝገብ ልማድ ያስታውሰናል። (ነህምያ 7:​5) አንድ ሰው ሲሞት ስሙ ከመዝገቡ ላይ ይፋቅ ስለነበር በመዝገቡ ላይ መጻፍ በሕይወት መኖርን የሚያመለክት ነው። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ይሖዋ የሕይወት ሽልማት የሚሰጣቸው ሰዎች ስም ስለተጻፈበት ምሳሌያዊ መዝገብ ወይም መጽሐፍ እናነባለን። ይሁን እንጂ እነዚህን ስሞች ይሖዋ ከመጽሐፉ ‘ሊደመስሳቸው’ ስለሚችል በዚህ መዝገብ ላይ መቆየታቸው በሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። (ዘጸአት 32:​32, 33፤ መዝሙር 69:​28) እንግዲያው የኢሳይያስ ቃላት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ማስጠንቀቂያ ያዘሉ ናቸው። ተመላሾቹ በምድራቸው መኖራቸውን የሚቀጥሉት በይሖዋ ዓይን ቅዱስ ሆነው እስከ ቀጠሉ ድረስ ብቻ ነው።

16. (ሀ) ይሖዋ በ537 ከዘአበ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ ከፈቀደላቸው ሰዎች የሚፈልገው ነገር ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ለቅቡዓን ቀሪዎቹና ‘ለሌሎች በጎች’ ያሳየው ምሕረት ከንቱ ሆኖ አልቀረም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

16 በ537 ከዘአበ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ቀሪዎች እውነተኛውን አምልኮ መልሶ የማቋቋም ትክክለኛ የሆነ ውስጣዊ ግፊት ስለነበራቸው ይህን አድርገዋል። በአረማዊ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ወይም ኢሳይያስ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥባቸው በነበሩት ርኩስ ድርጊቶች የተጠላለፈ ማንኛውም ሰው ወደዚያ የመመለስ መብት አልነበረውም። (ኢሳይያስ 1:​15-17) ወደ ይሁዳ መመለስ የሚችሉት ይሖዋ እንደ ቅዱስ አድርጎ የተመለከታቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። (ኢሳይያስ 35:​8) በተመሳሳይም ዛሬ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ባላቸው “ሌሎች በጎች” የሚደገፉት ቅቡዓን ቀሪዎች በ1919 ከመንፈሳዊው ምርኮ ነፃ ከወጡ በኋላ በአምላክ ዓይን ቅዱስ ሆነው ለመገኘት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። (ዮሐንስ 10:​16) ከባቢሎናዊ ትምህርቶችና ድርጊቶች ሁሉ ራሳቸውን ነፃ አድርገዋል። በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጠብቀው ለመገኘት ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 1:​14-16) ይሖዋ ያሳያቸው ምሕረት መና አልቀረም።

17. ይሖዋ ‘በሕይወት መጽሐፍ’ የሚጽፈው የእነማንን ስም ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?

17 ይሖዋ በእስራኤል የነበሩትን ቅዱሳን እንደተመለከተና ‘ስማቸውን ለሕይወት እንደጻፈው’ አስታውስ። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ‘ሰውነታችንን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት’ አድርገን በማቅረብ በአእምሮና በአካል ንጹሕ ለመሆን የምናደርገውን ጥረት ይመለከታል። (ሮሜ 12:​1) እንዲህ ዓይነቱን የሕይወት ጎዳና የሚከተሉ ሁሉ በአምላክ ዘንድ ‘በሕይወት መጽሐፉ’ ውስጥ ይመዘገባሉ። ይህ ምሳሌያዊ መዝገብ በሰማይም ሆነ በምድር የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የተገባቸውን ሰዎች ስም የያዘ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​3፤ ሚልክያስ 3:​16) እንግዲያውስ በአምላክ ዓይን ቅዱስ ሆነን ለመቀጠል የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ያን ጊዜ ስማችን በዚያ ውድ “መጽሐፍ” ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ እንችል ይሆናል።​—⁠ራእይ 3:​5

ፍቅራዊ ጥበቃ እንደሚያገኙ የተሰጠ የተስፋ ቃል

18, 19. በ⁠ኢሳይያስ 4:​4, 5 መሠረት ይሖዋ የሚያከናውነው የማንጻት ሥራ ምንድን ነው? ይህስ የሚከናወነው እንዴት ነው?

18 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ ተመልሳ የተቋቋመችው ምድር ነዋሪዎች እንዴት ቅዱሳን እንደሚሆኑና ምን በረከቶች ከፊታቸው እንደሚጠብቋቸው ይገልጻል። እንዲህ ብሏል:- “ጌታም የጽዮንን ቈነጃጅት እድፍ ባጠበ ጊዜ፣ የኢየሩሳሌምንም ደም በፍርድ መንፈስና በሚያቃጥል መንፈስ ከመካከልዋ ባነጻ ጊዜ፣ . . . እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራ ላይ ባለ ማደሪያ ሁሉ በጉባኤአቸውም ላይ በቀን ዳመናንና ጢስን በሌሊትም የሚቃጠለውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በክብርም ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል።”​—⁠ኢሳይያስ 4:​3-5

19 ቀደም ሲል ኢሳይያስ ከላይ አለባበሳቸውን አሳምረው በሥነ ምግባር ብልግና የቆሸሹትን “የጽዮን ቆነጃጅት” አውግዟቸው ነበር። ራሳቸውን እንዲያነጹ አጥብቆ በማሳሰብም በአጠቃላይ ሕዝቡ በደም አፍሳሽነት ተጠያቂ እንደሆነ አጋልጧል። (ኢሳይያስ 1:​15, 16፤ 3:⁠16-23) አሁን ግን አምላክ ራሱ ‘እድፋቸውን’ ማለትም የሥነ ምግባር ቆሻሻቸውን ‘ስለሚያጥብበትና’ ‘ያፈሰሱትን ደም ስለሚያነፃበት’ ጊዜ አሻግሮ ተመልክቷል። (ኢሳይያስ 4:​4 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ) ይህ የማንፃት ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? ‘በፍርድ መንፈስና በሚቃጠል መንፈስ’ ነው። በኢየሩሳሌም ላይ ሊመጣ ያለው ጥፋትና ወደ ባቢሎን በግዞት መወሰዳቸው ንጹሕ ባልሆነ ብሔር ላይ የሚፈነዳ የአምላክ ፍርድና የሚነድድ ቁጣ ነበር። እነዚህን መከራዎች በሕይወት አልፈው ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት ቀሪዎች ትሕትናን የተማሩና የጠሩ ይሆናሉ። ለይሖዋ ቅዱስ የሚሆኑትና ምሕረቱን የሚያገኙትም ለዚህ ነው።​—⁠ከ⁠ሚልክያስ 3:​2, 3 ጋር አወዳድር።

20. (ሀ) “ዳመና፣” “ጢስ” እና ‘የሚቃጠል እሳት ብርሃን’ የሚሉት መግለጫዎች ምን ነገር ያስታውሱናል? (ለ) ታጥበው የነጹት ግዞተኞች መፍራት የማያስፈልጋቸው ለምን ነበር?

20 ይሖዋ ከእድፍ ለነጹት ቀሪዎች ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው በኢሳይያስ በኩል ቃል ገብቷል። “ዳመና፣” “ጢስ” እና ‘የሚቃጠል እሳት ብርሃን’ የሚሉት መግለጫዎች ይሖዋ እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ ምን ያህል እንደተንከባከባቸው የሚያስታውሱን ናቸው። ‘የደመናና የእሳት አምድ’ ከሚያሳድዷቸው ግብጻውያን የጠበቃቸው ሲሆን በምድረ በዳ ሳሉም መርቷቸዋል። (ዘጸአት 13:​21, 22፤ 14:​19, 20, 24) ይሖዋ በሲና ተራራ በተገለጠላቸው ጊዜ ‘ተራራው ሁሉ ይጤስ ነበር።’ (ዘጸአት 19:​18) ከዚህ በኋላ ንጹሕ የሆኑት ግዞተኞች የሚፈሩበት ምክንያት አይኖርም። ይሖዋ ጠባቂያቸው ይሆናል። በቤታቸውም ሆነ በቅዱስ ጉባኤ አንድ ላይ ሲቀመጡ ይሖዋ በመካከላቸው ይሆናል።

21, 22. (ሀ) ብዙውን ጊዜ ዳስ ወይም ጎጆ የሚሠራበት ዓላማ ምን ነበር? (ለ) ታጥበው የነጹት ቅቡዓን ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

21 ኢሳይያስ ስለሚያገኙት መለኮታዊ ጥበቃ የሰጠውን መግለጫ ሲደመድም ስለ ዕለታዊ የሕይወት ጉዳዮች በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በቀን ከሙቀት ለጥላ፣ ከዐውሎ ነፋስና ከዝናብም ለመጠጊያና ለመሸሸጊያ ጎጆ [“ዳስ፣” NW ] ይሆናል።” (ኢሳይያስ 4:6) ብዙውን ጊዜ ዳስ ወይም ጎጆ የሚሠራው በወይን ወይም በሌላ የእርሻ ቦታ ሲሆን ከበጋው የሚያቃጥል ፀሐይ እና ከክረምቱ ቅዝቃዜና ነፋስ ለመዳን የሚያገለግል ከለላ ነው።​—⁠ከ⁠ዮናስ 4:​5 ጋር አወዳድር።

22 የስደት ትኩሳትና የተቃውሞ ዓውሎ ነፋስ ሲገጥማቸው ራሳቸውን ንጹሕ ላደረጉት ለእነዚህ ቀሪዎች ይሖዋ ጥበቃ የሚያገኙበት የደህንነታቸው ምንጭና መሸሸጊያ ይሆንላቸዋል። (መዝሙር 91:​1, 2፤ 121:​5) በዚህ መንገድ ከፊታቸው ግሩም ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር:- የባቢሎንን ንጹህ ያልሆኑ እምነቶችና ድርጊቶች ወደኋላ ከተዉና የይሖዋ የፍርድ እርምጃ ለሚያከናውነው የማንጻት ሥራ ራሳቸውን ካስገዙ እንዲሁም ቅዱስ ሆነው ለመቀጠል ከጣሩ መለኮታዊ ጥበቃ በሚያገኙበት “ዳስ” ውስጥ ያሉ ያህል አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይቆያሉ።

23. ይሖዋ ቅቡዓን ቀሪዎቹንና ተባባሪዎቻቸውን የባረካቸው ለምንድን ነው?

23 መጀመሪያ የሚቀድመው መንጻቱ እንደሆነና ቀጥሎ በረከቱ እንደሚከተል ልብ በል። ይህ በዘመናችንም ተፈጽሟል። በ1919 ቅቡዓን ቀሪዎቹ ለማጥራቱ ሂደት ራሳቸውን በትህትና አስገዝተው ነበር። ይሖዋም እድፋቸውን ‘አጥቦላቸዋል።’ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ከሌሎች በጎች ወገን የሆኑ ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ ይሖዋ እንዲያጠራቸው ፈቅደዋል። (ራእይ 7:​9) በዚህ መንገድ የነጹት ቀሪዎችና ጓደኞቻቸው ተባርከዋል። በይሖዋ እቅፍ ውስጥ ገብተዋል። የስደት ትኩሳትና የተቃውሞ ነፋስ እንዳይገጥማቸው በተዓምራዊ መንገድ አይከላከልላቸውም። ይሁን እንጂ ‘ከኃይለኛ ውሽንፍር መሸሸጊያ የሚሆን የዳስ ጥላ’ በላያቸው የተከለ ያህል ይጠብቃቸዋል። እንዴት?

24. ይሖዋ ሕዝቡን በድርጅት መልክ እንደባረካቸው የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

24 አንድ ነገር ልብ በል። በዓለም ታሪክ በጣም ኃያላን ከነበሩት መንግሥታት መካከል አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮችን የስብከት ሥራ አግደዋል ወይም እነርሱን ጨርሶ ለማጥፋት ሞክረዋል። ይሁንና ምሥክሮቹ ከመጽናታቸውም ሌላ ያላንዳች ማሰለስ ምሥራቹን መስበካቸውን ቀጥለዋል! ኃያላን መንግሥታት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የሆነውንና ምንም ራሱን መከላከል የማይችል መስሎ የሚታየውን የዚህን ቡድን ሥራ ማስቆም ሳይችሉ የቀሩት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ንጹሕ የሆነውን ሕዝቡን ያስቀመጠው ማንም ሰው ሊያፈርሰው በማይችል “ዳስ” ውስጥ ነው!

25. ይሖዋ ጠባቂያችን መሆኑ ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ያለው ትርጉም ምንድን ነው?

25 ስለ እኛስ በግለሰብ ደረጃ ምን ለማለት ይቻላል? ይሖዋ ጠባቂያችን ነው ማለት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንመራለን ማለት አይደለም። ብዙ የታመኑ ክርስቲያኖች እንደ ድህነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ጦርነት፣ ሕመም እና ሞት ያሉ ከባድ መከራዎች ይደርሱባቸዋል። እንዲህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ሲገጥመን አምላክ ከእኛ ጋር እንደሆነ ፈጽሞ አንዘንጋ። በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልገንን በመስጠት ይጠብቀናል። ፈተናዎችን የታመንን ሆነን በጽናት መቋቋም እንድንችል ‘ከወትሮው የተለየ ኃይልም’ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) እርሱ እያለ ምንም የሚያሰጋን ነገር ስለማይኖር የምንፈራበት ምክንያት የለም። ደግሞስ በእርሱ ዓይን ቅዱስ ሆነን ለመገኘት የቻልነውን ያህል እስከጣርን ድረስ ‘ከአምላክ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማን ነው?’​—⁠ሮሜ 8:​38, 39

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አንዳንድ ምሁራን “የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ” የሚለው ሐረግ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚናገረው ከኢየሩሳሌም መልሶ መቋቋም በኋላ ስለሚገለጠው መሲሕ ነው ይላሉ። ይህ አገላለጽ በአረማይኩ ትርጉም ውስጥ “የይሖዋ መሲህ [ክርስቶስ]” በሚል ተብራርቶ ተቀምጧል። የሚያስገርመው ከጊዜ በኋላ ኤርምያስ መሲሁ ከዳዊት ዘር የተገኘ “ጻድቅ ቁጥቋጥ” መሆኑን ሲገልጽ የተጠቀመበት የዕብራይስጥ ስም (ጼማክ) ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ነው።​—⁠ኤርምያስ 23:​5፤ 33:​15

^ አን.9 “ያመለጡ” የተባሉት ሰዎች በግዞት እያሉ የተወለዱትንም ይጨምራሉ። ወላጆቻቸው ከጥፋቱ ባይተርፉ ኖሮ ሊወለዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ስላልነበረ እነርሱም ‘እንዳመለጡ’ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ።​—⁠ዕዝራ 9:​13-15፤ ከ⁠ዕብራውያን 7:​9, 10 ጋር አወዳድር።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሁዳ የመለኮታዊ ፍርድ ዓውሎ ነፋስ እያንዣበበባት ነው