በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል

ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል

ምዕራፍ ስምንት

ይሖዋ አምላክ ቅዱስ በሆነው መቅደሱ ተቀምጧል

ኢሳይያስ 6:​1-13

1, 2. (ሀ) ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ቤተ መቅደሱ ራእይ ያየው መቼ ነበር? (ለ) ንጉሥ ዖዝያን የይሖዋን ሞገስ ያጣው ለምንድን ነው?

“ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፣ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።” (ኢሳይያስ 6:​1) የኢሳይያስ መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ የሚጀምረው በእነዚህ የነቢዩ ቃላት ነው። ዘመኑ 778 ከዘአበ ነበር።

2 ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ ሆኖ በሥልጣን ላይ ከቆየባቸው 52 ዓመታት መካከል አብዛኛዎቹ ከፍተኛ ስኬት ያገኘባቸው ነበሩ። ‘በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር በማድረጉ’ በውትድርናው፣ በግንባታውና በእርሻው መስክ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የአምላክ ድጋፍ አልተለየውም ነበር። ይሁን እንጂ ያገኘው ስኬት ለውድቀቱም ምክንያት ሆኗል። ከጊዜ በኋላ ልቡ በመታበዩ ‘ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ በማጠን አምላኩን ይሖዋን በድሏል።’ ይህን የትዕቢት ድርጊት በመፈጸሙና በተቃወሙት ካህናት ላይ በመቆጣቱ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ሆኖ ኖሯል። (2 ዜና መዋዕል 26:​3-22) ኢሳይያስም የነቢይነት አገልግሎቱን የጀመረው በዚህ ጊዜ ገደማ ነበር።

3. (ሀ) ኢሳይያስ በእርግጥ ይሖዋን አይቶታልን? አብራራ። (ለ) ኢሳይያስ የተመለከተው ነገር ምንድን ነው? ያየበትስ ዓላማ ምን ነበር?

3 ኢሳይያስ ራእዩን ባየበት ጊዜ የት እንደነበረ ምንም የተገለጸልን ነገር የለም። ይሁን እንጂ በሰብዓዊ ዓይኑ ያየው ነገር ራእይ እንደነበር ምንም አያጠያይቅም። ‘ሰው አይቶት አይድንምና’ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ በዓይኑ አላየም። (ዮሐንስ 1:​18፤ ዘጸአት 33:​20) በራእይም እንኳ ቢሆን ፈጣሪን፣ ይሖዋን ማየት መቻል እጅግ ድንቅ ነገር ነው። ዘላለማዊ ንጉሥና ዳኛ መሆኑን በሚያመለክተው ከፍ ያለ ዙፋን ላይ የተቀመጠው አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ ገዥና ፍጹም ሕጋዊ የሆነው መስተዳድር ምንጭ ነው! ረጅም የሆነው ልብሱ ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶታል። ኢሳይያስ የይሖዋን ሉዓላዊ ሥልጣንና ፍትሕ የሚያጎላ የነቢይነት አገልግሎት እንዲያከናውን ጥሪ እየቀረበለት ነው። ለዚህ አገልግሎት እንዲዘጋጅ ሲባል ስለ አምላክ ቅድስና የሚገልጽ ራእይ እንዲያይ ይደረጋል።

4. (ሀ) ስለ ይሖዋ በራእይ የታየውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ነገር ምሳሌያዊ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ ካየው ራእይ ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን?

4 ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል እና ዮሐንስ እንዳደረጉት ኢሳይያስ በራእይው ውስጥ ስለ ይሖዋ ገጽታ ምንም መግለጫ አልሰጠም። ሌሎቹም ዘገባዎች ቢሆኑ በሰማይ ስለታየው ነገር የጠቀሱት አንዱ ከሌላው የተለያየ ነው። (ሕዝቅኤል 1:​26-28፤ ዳንኤል 7:​9, 10፤ ራእይ 4:​2, 3) ይሁን እንጂ የእነዚህ ራእይዎች ባሕርይና ዓላማ ሊዘነጋ አይገባም። ይሖዋ ቃል በቃል በአካል ስለ መገኘቱ የተሰጡ መግለጫዎች አይደሉም። መንፈሳዊ የሆነውን ነገር በሰብዓዊ ዓይን ማየት አይቻልም። ውስን የሆነው የሰው ልጅ አእምሮም ቢሆን መንፈሳዊውን ዓለም ሙሉ በሙሉ መረዳት አይችልም። በመሆኑም ራእይዎቹ እንዲተላለፍ የተፈለገውን መልእክት በሰብዓዊ አእምሮ ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ አቅርበዋል። (ከ⁠ራእይ 1:​1 NW ጋር አወዳድር።) በኢሳይያስ ራእይ ውስጥ ስለ ይሖዋ ገጽታ መግለጫ መስጠት አስፈላጊ አልነበረም። ይሖዋ በመቅደሱ እንደተቀመጠና እርሱ ቅዱስ ፍርዶቹም ንጹሕ መሆናቸውን ኢሳይያስ ከራእይው መገንዘብ ችሏል።

ሱራፌል

5. (ሀ) ሱራፌል እነማን ናቸው? የቃሉ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ሱራፌል ፊታቸውንና እግራቸውን የሚሸፍኑት ለምንድን ነው?

5 ኢሳይያስ ምን በማለት እንደሚቀጥል አዳምጥ:- “ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፣ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።” (ኢሳይያስ 6:​2) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሱራፌል ተጠቅሶ የምናገኘው በኢሳይያስ ምዕራፍ 6 ላይ ብቻ ነው። በይሖዋ አገልግሎት ከፍተኛ መብትና ክብር ያላቸው እንዲሁም በይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን አጠገብ የሚገኙ መላእክታዊ ፍጥረታት እንደሆኑ ግልጽ ነው። ኩሩ ከነበረው ንጉሥ ዖዝያን በተለየ መልኩ በትሕትና ቦታቸውን ጠብቀው ያገለግላሉ። በሰማያዊው ሉዓላዊ ጌታ ፊት የሚቆሙ በመሆናቸው በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን ይሸፍናሉ። እንዲሁም ለዚያ ቅዱስ ስፍራ ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት በሌላው ሁለት ክንፋቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ። ይበልጡኑ ደግሞ ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ቅርብ በመሆናቸው ለአምላክ ሊሰጠው ከሚገባው ክብር ትኩረት ላለመሳብ ራሳቸውን ይሸሽጋሉ። “ሱራፌል” የሚለው ቃል “እሳት የሚያመነጭ” ወይም “የሚቃጠል” ማለት ሲሆን ብርሃን እንደሚያፈልቁ የሚጠቁም መጠሪያ ነው። ይሁንና ከታላቁ የይሖዋ ነፀብራቅና ክብር ፊታቸውን ይሸፍናሉ።

6. ሱራፌል በይሖዋ ፊት ያላቸው ቦታ ምንድን ነው?

6 ሱራፌል ሦስተኛውን ጥንድ ክንፋቸውን የሚጠቀሙበት ለመብረር እንዲሁም በተሰጣቸው ቦታ ለማንዣበብ ወይም ‘ለመቆም’ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (ከ⁠ዘዳግም 31:​15 ጋር አወዳድር።) የሱራፌል ቦታ በተመለከተ ፕሮፌሰር ፍራንዝ ዴሊትሽ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “እርግጥ ሱራፌል በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው በላይ ልቀው ይታያሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መቅደሱን ሞልቶት ከነበረው ልብሱ በላይ ያንዣብባሉ።” (ኮሜንታሪ ኦን ዘ ኦልድ ቴስታመንት) ደግሞም ይህ ምክንያታዊ ይመስላል። ‘ከበላዩ ይቆማሉ’ ሲባል ከይሖዋ የበላይ ናቸው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እርሱን የሚጠባበቁ ታዛዥና ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

7. (ሀ) ሱራፌል የሚያከናውኑት ሥራ ምንድን ነው? (ለ) ሱራፌል የአምላክን ቅድስና ሦስት ጊዜ ደጋግመው የተናገሩት ለምንድን ነው?

7 አሁን ደግሞ እነዚህ ልዩ መብት ያገኙት ሱራፌል የሚናገሩትን አድምጥ! “አንዱም ለአንዱ:- ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።” (ኢሳይያስ 6:3) ሥራቸው ምድርን ጨምሮ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ የይሖዋ ቅድስና መታወጁንና ለእርሱ ክብር መሰጠቱን መከታተል ነው። የፍጥረት ሥራዎቹ ሁሉ የእርሱን ክብር የሚያንጸባርቁ ሲሆኑ በቅርቡም መላው የምድር ነዋሪ ይህን ክብሩን የሚያስተውልበት ጊዜ ይመጣል። (ዘኍልቁ 14:​21፤ መዝሙር 19:​1-3፤ ዕንባቆም 2:​14) “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” የሚለው መግለጫ ሦስት ጊዜ መጠራቱ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ የሚያረጋግጥ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ መጠራቱ የአምላክን ቅድስና ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነው። (ከ⁠ራእይ 4:​8 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ቅድስና አቻ የለውም።

8. የሱራፌል እወጃ ውጤቱ ምን ሆነ?

8 ምንም እንኳ የሱራፌል ቁጥር ባይጠቀስም በዙፋኑ አቅራቢያ በርካታ ሱራፌል ሳይኖሩ አይቀሩም። በዜማ እየተቀባበሉ የአምላክን ቅድስናና ክብር ያውጃሉ። ታዲያ ውጤቱ ምን ይሆናል? ኢሳይያስ ቀጥሎ ምን እንዳለ አዳምጥ:- “የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፣ ቤቱንም ጢስ ሞላበት።” (ኢሳይያስ 6:​4) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ጢስ ወይም ዳመና የአምላክን መገኘት የሚያረጋግጥ የሚታይ ማስረጃ ነው። (ዘጸአት 19:​18፤ 40:​34, 35፤ 1 ነገሥት 8:​10, 11፤ ራእይ 15:​5-8) ሰብዓዊ ፍጥረታት የሆንነው ሰዎች ልንቀርበው የማንችለውን ክብር የሚያመለክት ነው።

የማይገባው ሰው ቢሆንም ነጽቷል

9. (ሀ) ራእይው በኢሳይያስ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? (ለ) በኢሳይያስና በንጉሥ ዖዝያን መካከል ምን ልዩነት በግልጽ ይታያል?

9 ይህ ስለ ይሖዋ ዙፋን የሚገልጸው ራእይ በኢሳይያስ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል አልነበረም። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔም:- ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፣ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ።” (ኢሳይያስ 6:​5) በኢሳይያስና በንጉሥ ዖዝያን መካከል ያለው ልዩነት እንዴት የሚያስገርም ነው! ዖዝያን የተቀቡ ካህናቱን ቦታ አላግባብ በመንጠቅ በማናለብኝነት ወደ ቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ገብቷል። ዖዝያን የወርቅ መቅረዙን፣ ከወርቅ የተሠራውን የዕጣን መሠዊያ እና “የመገኘቱ ኅብስት” የነበረበትን ገበታ ቢመለከትም የይሖዋን ሞገስ እንዳገኝ የሚያረጋግጥ ነገር አላየም ወይም ከእርሱ ልዩ ተልዕኮ አልተሰጠውም። (1 ነገሥት 7:​48-50 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በሌላ በኩል ደግሞ ኢሳይያስ የካህናቱን ቦታ አልተጋፋም ወይም ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ የማይገባውን ነገር አላደረገም። ይሁንና ይሖዋን በቅዱስ መቅደሱ ሆኖ በራእይ ከመመልከቱም ሌላ ከአምላክ በቀጥታ ተልዕኮ መቀበልን የመሰለ ልዩ ክብር አግኝቷል። ሱራፌል እንኳ በዙፋን ላይ የተቀመጠውን የመቅደሱን ጌታ ትክ ብለው የማይመለከቱ ቢሆንም ኢሳይያስ ግን በራእዩ ውስጥ “የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን” እንዲያይ ተፈቅዶለታል!

10. ኢሳይያስ ራእይውን ሲያይ ፍርሃት የተሰማው ለምንድን ነው?

10 ኢሳይያስ በአምላክ ቅድስና እና በእርሱ ኃጢአተኛነት መካከል ያለውን ልዩነት ሲያስተውል ርኩስ እንደሆነ ተሰምቶታል። በፍርሃት ተውጦ እሞታለሁ ብሎ አስቦ ነበር። (ዘጸአት 33:​20) ሱራፌል በንጹሕ ከንፈሮቻቸው አምላክን ሲያወድሱ ሰምቷል። ይሁን እንጂ የእርሱ ከንፈሮች የረከሱ ከመሆናቸውም ሌላ የሚኖረውም ከንፈሮቻቸው በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመሆኑ የሚናገሩትን ይሰማ ስለነበር ይበልጥ ረክሶ ነበር። ይሖዋ ቅዱስ ነው። አገልጋዮቹም ይህንኑ ባሕርይ ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:​15, 16) ኢሳይያስ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ እንዲያገለግል ተመርጦ የነበረ ቢሆንም ኃጢአተኛ መሆኑንና ለክብራማውና ቅዱስ ለሆነው ንጉሥ ቃል አቀባይ ለመሆን የሚበቃ ንጹህ አንደበት እንደሌለው ሲገነዘብ በጣም ተሰምቶታል። ከሰማይ የሚያገኘው ምላሽ ምን ይሆን?

11. (ሀ) ከሱራፌል አንዱ ምን አደረገ? ይህስ ምን ያመለክታል? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች በመሆናችን የማንረባ እንደሆንን ሲሰማን ሱራፊው ለኢሳይያስ በነገረው ነገር ላይ ማሰላሰላችን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

11 ሱራፌል ዝቅተኛ ደረጃ የነበረውን ኢሳይያስን ከይሖዋ ፊት እንዲርቅ ከማድረግ ይልቅ ረዱት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፣ በእጁም ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና:- እነሆ፣ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።” (ኢሳይያስ 6:​6, 7) በምሳሌያዊ ሁኔታ ሲታይ እሳት የማንጻት ኃይል አለው። ሱራፊው ከመሠዊያው ላይ በወሰደው እሳት የኢሳይያስን ከንፈር በመዳሰስ የአምላክን ሞገስ ለማግኘትና ተልዕኮ ለመቀበል በሚያስችለው መጠን ኃጢአቱ እንደተሠረየለት አረጋግጦለታል። ይህ ለእኛ እንዴት የሚያጽናና ነው! እኛም ብንሆን ኃጢአተኞችና በአምላክ ፊት መቅረብ የማይገባን ሰዎች ነን። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ተዋጅተን የአምላክን ሞገስ ለማግኘትና ወደ እርሱ በጸሎት ለመቅረብ ችለናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:​18, 21፤ 1 ዮሐንስ 4:​10

12. ኢሳይያስ ያየው መሠዊያ ምንድን ነው? እሳት ምን ውጤት አለው?

12 ኢሳይያስ ያየው ነገር ራእይ መሆኑን በድጋሚ የሚያስታውሰን “መሠዊያ” መጠቀሱ ነው። (ከ⁠ራእይ 8:​3፤ 9:​13 ጋር አወዳድር።) በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሁለት መሠዊያዎች ነበሩ። ከቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ በፊት ያለው የዕጣን መሠዊያ አንዱ ሲሆን ከቤተ መቅደሱ መግቢያ ፊት ለፊት የነበረው መሥዋዕት የሚቀርብበት ትልቅ መሠዊያ ደግሞ ሁለተኛው ነው። የዚህ መሠዊያ እሳት ሁልጊዜም አይጠፋም ነበር። (ዘሌዋውያን 6:​12, 13፤ 16:​12, 13) ይሁን እንጂ እነዚህ ምድራዊ መሠዊያዎች የሚበልጠውን ነገር የሚወክሉ ምሳሌያዊ ነገሮች ነበሩ። (ዕብራውያን 8:​5፤ 9:​23፤ 10:​5-10) ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መርቆ በከፈተበት ጊዜ በመሠዊያው ላይ የነበረውን መሥዋዕት የበላው ከሰማይ የወረደ እሳት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 7:​1-3) አሁንም የኢሳይያስን የረከሱ ከንፈሮች ያነጻለት ከእውነተኛው ሰማያዊ መሠዊያ የተወሰደ እሳት ነው።

13. ይሖዋ ምን ጥያቄ አቅርቧል? ‘እኛ’ ብሎ ሲናገር ማንን መጨመሩ ነበር?

13 እስቲ አሁን ደግሞ ከኢሳይያስ ጋር ሆነን እናዳምጥ። “የጌታንም ድምፅ:- ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም:- እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ አልሁ።” (ኢሳይያስ 6:​8) በራእይው ውስጥ የተካፈለ ሌላ ሰው ስለሌለ ይሖዋ ያቀረበው ጥያቄ ኢሳይያስ ራሱ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅ እንደነበር ግልጽ ነው። ኢሳይያስ የይሖዋ መልእክተኛ እንዲሆን የቀረበ ግብዣ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ማንስ ይሄድልናል?” ሲል የጠየቀው ለምንድን ነው? ይሖዋ ‘እኔ’ ከሚለው ነጠላ ተውላጠ ስም ‘እኛ’ ወደሚለው የብዙ ቁጥር ተውላጠ ስም በመሻገር ከራሱ ጋር ቢያንስ ሌላ አንድ አካል እንዳለ አመልክቷል። ይህ ማን ነው? ከጊዜ በኋላ ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ማለትም የእርሱ አንድያ ልጅ አይደለምን? አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት የተናገረውም ለዚሁ ልጁ ነበር። (ዘፍጥረት 1:​26፤ ምሳሌ 8:​30, 31) አዎን፣ በሰማያዊው መቅደስ ከይሖዋ ጋር ያለው አንድያ ልጁ ነው።​—⁠ዮሐንስ 1:​14

14. ኢሳይያስ ለይሖዋ ጥሪ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለእኛስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

14 ኢሳይያስ ምላሽ ለመስጠት አላመነታም! መልእክቱ ምንም ይሁን ምን ኢሳይያስ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል። ይህንን ሥራ ብቀበል ምን አገኛለሁ ብሎም አልጠየቀም። የእርሱ የፈቃደኛነት መንፈስ በዛሬው ጊዜ ‘በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ’ ተልእኮ ለተሰጣቸው የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ነው። (ማቴዎስ 24:​14) ለመልእክቱ ምላሽ የማይሰጡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክርነት’ የመስጠት ሥራቸውን ልክ እንደ ኢሳይያስ በታማኝነት ያከናውናሉ። ተልእኳቸውን የተቀበሉት ከታላቁ ባለሥልጣን መሆኑን ስለሚገነዘቡ ልክ እንደ ኢሳይያስ በትምክህት ወደፊት ይገፋሉ።

ለኢሳይያስ የተሰጠው ተልእኮ

15, 16. (ሀ) ኢሳይያስ ‘ለዚህ ሕዝብ’ ምን የሚናገረው ነገር አለ? የእነርሱስ ምላሽ ምን ይሆናል? (ለ) ሕዝቡ ለሚሰጠው ምላሽ ጥፋቱ የኢሳይያስ ነውን? አብራራ።

15 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ኢሳይያስ ምን እንደሚናገርና የሰዎቹ ምላሽ ምን እንደሚሆን ይጠቅሳል:- “ሂድ፣ ይህን ሕዝብ:- መስማትን [“ደጋግማችሁ” NW] ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፣ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፣ ጆሮአቸውንም አደንቁር፣ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።” (ኢሳይያስ 6:​9, 10) ይህ ማለት ግን ኢሳይያስ አሳቢነትና ጥበብ በጎደለው መንገድ ሊናገራቸውና አይሁዳውያኑን ከአምላክ ሊያቃቅራቸው ነው ማለት ነውን? በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም! እነዚህ እንደወገኑ የሚያያቸው የገዛ አገሩ ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ የቱንም ያህል ተግባሩን በታማኝነት ቢያከናውን ሕዝቡ የሚሰጡትን ምላሽ ይሖዋ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት እንችላለን።

16 ችግሩ ከሕዝቡ ነው! ኢሳይያስ ‘ደግሞ ደጋግሞ’ ቢነግራቸውም መልእክቱን አይቀበሉም ወይም አያስተውሉም። አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ማየትና መስማት የተሳናቸው ያህል እልከኛና ልበ ደንዳኖች ይሆናሉ። ኢሳይያስ ደጋግሞ ‘ወደዚህ ሕዝብ’ በመሄድ ማስተዋል እንዳልፈለጉ ያረጋግጥላቸዋል። ኢሳይያስ የሚናገረውን የአምላክ መልእክት ላለመቀበል አእምሮና ልባቸውን እንደዘጉ ያሳያሉ። ይህ አባባል ዛሬ ላሉት ሰዎች ምንኛ ተስማሚ ነው! ብዙዎቹ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጪው የአምላክ መንግሥት የሚሰብኩትን ምሥራች ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም።

17. ኢሳይያስ “እስከ መቼ ድረስ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ስለምን መናገሩ ነበር?

17 ኢሳይያስን ያሳሰበው አንድ ነገር አለ:- “እኔም:- ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ:- ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፣ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፣ እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፣ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው።” (ኢሳይያስ 6:11, 12) ኢሳይያስ “እስከ መቼ ድረስ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ለእነዚህ ልበ ደንዳና ሰዎች መስበኩን የሚቀጥለው እስከ መቼ እንደሆነ መጠየቁ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እርሱን ያሳሰበው ሕዝቡ በዚህ መጥፎ መንፈሳዊ ሁኔታው እስከ መቼ ድረስ ይቀጥላል? ደግሞስ የይሖዋ ስም በምድር ላይ ሳይከበር የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው የሚለው ጉዳይ ነው። (መዝሙር 74:​9-11ን ተመልከት።) ታዲያ ይህ አጉል አካሄድ የሚቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ነው?

18. የሕዝቡ የተበላሸ መንፈሳዊ ሁኔታ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? ኢሳይያስ ትንቢቱ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ በሕይወት ቆይቷልን?

18 ወዮ! ይሖዋ የሰጠው መልስ ብልሹ የሆነው የሕዝቡ መንፈሳዊ ሁኔታ የሚቀጥለው በቃል ኪዳኑ ላይ እንደተጠቀሰው አምላክን አለመታዘዝ የሚያስከትለው ውጤት ሙሉ በሙሉ እስኪታይ ድረስ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። (ዘሌዋውያን 26:​21-33፤ ዘዳግም 28:​49-68) ብሔሩ ለጥፋት ይዳረጋል፣ ሕዝቡ ይጋዛል፣ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች። ኢሳይያስ የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ ልጅ እስከሆነው ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ድረስ ለ40 ዓመታት ትንቢት መናገሩን የሚቀጥል ቢሆንም ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በ607 በባቢሎናውያን ሠራዊት እስከሚጠፉ ድረስ በሕይወት አይቆይም። ያም ሆኖ ግን ኢሳይያስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ወይም በብሔሩ ላይ የሚመጣው ጥፋት ከ100 የሚበልጡ ዓመታት እስኪቀረው ድረስ የታመነ ሆኖ ተልዕኮውን ፈጽሟል።

19. ሕዝቡ እንደ ወደቀ ዛፍ ቢሆንም ይሖዋ ለኢሳይያስ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶታል?

19 ይሁዳ “ፈጽሞ ባድማ” የምትሆንበት ጥፋት መምጣቱ የማይቀር ቢሆንም ሁኔታው ጭራሽ ተስፋ አስቆራጭ አልነበረም። (2 ነገሥት 25:​1-26) ይሖዋ እንዲህ ሲል ለኢሳይያስ ማረጋገጫ ሰጥቶታል:- “በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፣ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል።” (ኢሳይያስ 6:​13) አዎን፣ ተቆርጦ እንደ ወደቀ ትልቅ ዛፍ ጉቶ ሆኖ ‘አንድ አሥረኛ የተቀደሰ ዘር’ ይቀራል። በሕዝቡ መካከል የሚቀሩ ቅዱሳን እንደሚኖሩ የሚገልጸው ይህ ማረጋገጫ ኢሳይያስን እንዳጽናናው ምንም ጥርጥር የለውም። ብሔሩ ለማገዶ እንደተቆረጠ ዛፍ በተደጋጋሚ ጊዜ ለእሳት ቢዳረግም የምሳሌያዊ ዛፍ የእስራኤል ብሔር ጉቶ ግን አይጠፋም። ለይሖዋ ቅዱስ የሆነ ዘር ይሆናል። ከጊዜ በኋላም እንደገና ያቆጠቁጥና ዛፉ መልሶ ያድጋል።​—⁠ከ⁠ኢዮብ 14:​7-9፤ ዳንኤል 4:​26 ጋር አወዳድር።

20. የኢሳይያስ ትንቢት የመጨረሻ ክፍል የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

20 እነዚህ የትንቢቱ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል? አዎን፣ አግኝተዋል። የይሁዳ ምድር ለሰባ ዓመት ባድማ ሆና ከቆየች በኋላ አምላክን የሚፈሩ ቀሪዎች ከባቢሎን ግዞት ተመልሰዋል። ከተማዋንና ቤተ መቅደሷንም መልሰው በመገንባት በምድሪቱ እውነተኛውን አምልኮ መልሰው አቋቁመዋል። አይሁዳውያን አምላክ ወደሰጣቸው ምድር ተመልሰው መቋቋማቸው ይሖዋ ለኢሳይያስ የሰጠው ትንቢት ሁለተኛ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስችሏል። ይህስ ምን ነበር?​—⁠ዕዝራ 1:​1-4

ሌሎች ፍጻሜዎች

21-23. (ሀ) የኢሳይያስ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው በእነማን ላይ ነው? እንዴትስ? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ‘የተቀደሰ ዘር’ ማን ነው? ከጥፋት የተረፈውስ እንዴት ነው?

21 የኢሳይያስ የነቢይነት ተግባር መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ800 ዓመታት በኋላ ለሚያከናውነው ነገር ጥላ ነበር። (ኢሳይያስ 8:​18፤ 61:​1, 2፤ ሉቃስ 4:​16-21፤ ዕብራውያን 2:​13, 14) ኢየሱስ ከኢሳይያስ የሚበልጥ ቢሆንም “እነሆ፣ . . . ፈቃድህን ላደርግ መጥቻለሁ” በማለት እንደ ኢሳይያስ ለመላክ ፈቃደኛ ነበር።​—⁠ዕብራውያን 10:​5-9፤ መዝሙር 40:​6-8

22 ልክ እንደ ኢሳይያስ ኢየሱስም የተሰጠውን ሥራ በታማኝነት ያከናወነ ሲሆን ከሕዝቡ የገጠመውም ምላሽ ተመሳሳይ ነበር። በኢየሱስ ዘመን የኖሩትም አይሁዳውያን በኢሳይያስ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ኢሳይያስ 1:​4) ምሳሌዎችን መጠቀም የኢየሱስ አገልግሎት ክፍል ነበር። ከዚህ የተነሣ ደቀ መዛሙርቱ “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” ብለው ጠይቀዋል። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፣ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጀሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጀሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።”​—⁠ማቴዎስ 13:​10, 11, 13-15፤ ማርቆስ 4:​10-12፤ ሉቃስ 8:​9, 10

23 ኢየሱስ ከኢሳይያስ ትንቢት መጥቀሱ ትንቢቱ በእርሱም ዘመን ተፈጻሚነት እንዳለው ማመልከቱ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ የነበረው የልብ ዝንባሌ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ካሳዩት የተለየ አልነበረም። መልእክቱን ላለመቀበል ዓይናቸውን ጨፍነውና ጆሮአቸውን ደፍነው ስለነበር ተመሳሳይ ጥፋት ገጥሟቸዋል። (ማቴዎስ 23:​35-38፤ 24:​1, 2) ይህ የሆነው በጄኔራል ቲቶ የሚመራው የሮማውያን ሠራዊት በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ በዘመተና ከተማዋንና ቤተ መቅደሷን ባጠፋ ጊዜ ነው። ይሁንና አንዳንዶች ኢየሱስን በመስማት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ደስተኞች” [NW] ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 13:​16-23, 51) “ኢየሩሳሌም በጭፍራ ተከባ” ሲያዩ ‘ወደ ተራሮች መሸሽ እንዲጀምሩ’ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:​20-22) እምነት እንዳለው ያሳየውና መንፈሳዊ ብሔር ሆኖ የተቋቋመው ‘የተቀደሰ ዘር’ ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ በዚህ መንገድ ሊድን ችሏል። *​—⁠ገላትያ 6:​16

24. ጳውሎስ የኢሳይያስን ትንቢት የተጠቀመበት እንዴት ነው? ይህስ ምን ይጠቁማል?

24 በ60 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም በቁም እስር ላይ ነበር። እዚያ እያለ “የአይሁድን ታላላቆችና” ሌሎችንም ጨምሮ ስብሰባ በማድረግ ‘ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መሠከረላቸው።’ ብዙዎች መልእክቱን ሳይቀበሉ በቀሩ ጊዜ ጳውሎስ ይህ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ተናግሯል። (ሥራ 28:​17-27፤ ኢሳይያስ 6:​9, 10) በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የፈጸሙት ተልዕኮ ከኢሳይያስ ጋር የሚመሳሰል ነበር።

25. በዘመናችን ያሉ የአምላክ ምሥክሮች ያስተዋሉት ነገር ምንድን ነው? ምንስ ምላሽ ይሰጣሉ?

25 ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋ በቅዱስ መቅደሱ እንዳለ ያስተውላሉ። (ሚልክያስ 3:​1) ልክ እንደ ኢሳይያስ እነርሱም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ይላሉ! እየቀረበ ስላለው የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የሚገልጸውን መልእክት በቅንዓት ያውጃሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ለማየትና ለመስማት ዓይናቸውንና ጆሮአቸውን ክፍት የሚያደርጉና ለመዳን የሚበቁት ጥቂቶች ናቸው። (ማቴዎስ 7:​13, 14) ለመስማት ልባቸውን የሚያዘነብሉና ‘ፈውስ’ የሚያገኙ በእርግጥም ደስተኞች ናቸው።​—⁠ኢሳይያስ 6:​8, 10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.23 በ66 እዘአ የአይሁዳውያኑን ዓመፅ ተከትሎ በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራ የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በመክበብ ወደ ከተማዋ ዘልቆ ገብቶ እስከ መቅደሱ ግድግዳ ድረስ ተጠግቶ ነበር። ከዚያም የሮማ ሠራዊት ወደ ኋላ በመመለሱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሮማውያን በ70 እዘአ ተመልሰው ከመምጣታቸው በፊት ለመሸሽ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 94 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ”

[በገጽ 97 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ከተሞች የሚኖርባቸው አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ’