በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የጢሮስን ትዕቢት ይሽራል

ይሖዋ የጢሮስን ትዕቢት ይሽራል

ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ

ይሖዋ የጢሮስን ትዕቢት ይሽራል

ኢሳይያስ 23:​1-​18

1, 2. (ሀ) የጥንቷ ጢሮስ ምን ዓይነት ከተማ ነበረች? (ለ) ኢሳይያስ ስለ ጢሮስ ምን ትንቢት ተናግሯል?

ውበቷ ፍጹም” “የሀብቷም ዓይነት” ስፍር ቁጥር የሌለው ነበር። (ሕዝቅኤል 27:​4, 12 አን አሜሪካን ትራንስሌሽን) ግዙፍ የነበረው የባሕር ኃይሏ በጣም ሰፊ የሆነ የባሕር ክልል ይቆጣጠር ነበር። ‘በባሕርም ውስጥ እጅግ ከብራና’ ‘በብልጥግናዋም’ ‘የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርጋ’ ነበር። (ሕዝቅኤል 27:​25, 33) በሜዲትራኒያን ምሥራቃዊ ጫፍ የምትገኘው የፊንቄዋ ከተማ ጢሮስ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበራት ሁኔታ ይህንን የሚመስል ነበር።

2 ይሁንና ጢሮስ ከፊቷ ጥፋት ይጠብቃት ነበር። ሕዝቅኤል ስለ እርሷ ይህንን መግለጫ ከመስጠቱ ከ100 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ይህቺ የፊንቄ ምሽግ እንደምትፈርስና በእርሷ ይተማመኑ የነበሩ ወገኖችም እንደሚያዝኑ ትንቢት ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ አምላክ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ፊቱን ወደዚች ከተማ እንደሚመልስና እንደገና ብልጥግናን እንደሚያላብሳትም ተንብዮአል። የነቢዩ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው? በጢሮስ ላይ ከደረሰው ነገርስ እኛ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጢሮስ ምን እንደገጠማትና ይህ ነገር የደረሰባት ለምን እንደሆነ በግልጽ መረዳታችን በይሖዋና በተስፋዎቹ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ይሆናል።

“የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ አልቅሱ”

3, 4. (ሀ) ተርሴስ የምትገኘው የት ነበር? በጢሮስና በተርሴስ መካከል የነበረው ዝምድና ምንድን ነው? (ለ) ከተርሴስ ጋር የሚነግዱት መርከበኞች ‘የሚያለቅሱበት’ ምክንያት አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

3 ኢሳይያስ “ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም” የሚል ርዕስ ሰጥቶ ከጀመረ በኋላ እንዲህ ይላል:- “የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት [“ወደብ፣” NW] የለም፣ መግባትም የለም።” (ኢሳይያስ 23:​1ሀ) ተርሴስ በሜዲትራኒያን ምሥራቃዊ ክፍል ካለችው ጢሮስ ርቃ የምትገኝ የስፔይን አካል እንደነበረች ይታመናል። * ያም ሆኖ ግን የፊንቄ ሰዎች የተዋጣላቸው ባሕረተኞች የነበሩ ሲሆን መርከቦቻቸውም ትላልቅና አስተማማኝ ነበሩ። አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በጨረቃና በማዕበል መካከል ያለውን ትስስር በማስተዋልና የሰማይን ምልክት ለባሕር ላይ ጉዞ እንደ መረጃ አድርገው በመጠቀም ረገድ የመጀመሪያ የሆኑት የፊንቄ ሰዎች እንደሆኑ ያምናሉ። በመሆኑም ከጢሮስ እስከ ተርሴስ ያለው ረጅም ርቀት እንቅፋት አልሆነባቸውም።

4 በኢሳይያስ ዘመን ተርሴስ ለጢሮስ ጥሩ የሸቀጥ ማራገፊያ የነበረች ሲሆን ምናልባትም ለብዙ ዘመናት ዋነኛ የብልጽግናዋ ምንጭ ሳትሆንላት አልቀረችም። ስፔይን የብር፣ የብረት፣ የቆርቆሮ እና የሌሎች የብረት ማዕድናት ከፍተኛ ክምችት ነበራት። (ከ⁠ኤርምያስ 10:​9፤ ሕዝቅኤል 27:​12 ጋር አወዳድር።) “የተርሴስ መርከቦች” ማለትም ለንግድ ወደ ተርሴስ የሚመጡ የጢሮስ መርከቦች ሳይሆኑ አይቀሩም ማረፊያ ወደብ ሆናላቸው የነበረችው ጢሮስ በመጥፋቷ ‘ማልቀሳቸው’ ምንም አያስገርምም።

5. ከተርሴስ የሚመጡት መርከበኞች የጢሮስን መውደቅ የሚሰሙት የት ነው?

5 በባሕር ላይ ያሉት መርከበኞች የጢሮስን መውደቅ የሚያውቁት እንዴት ነው? ኢሳይያስ “ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል” በማለት መልሱን ይሰጣል። (ኢሳይያስ 23:​1ለ) ‘የኪቲም አገር’ የተባለችው ከፊንቄ የባሕር ዳርቻ በስተ ምዕራብ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው የቆጵሮስ ደሴት ሳትሆን አትቀርም። ከተርሴስ ተነስተው ወደ ምሥራቅ ለሚያቀኑት መርከቦች ይህ ጢሮስ ከመድረሳቸው በፊት የሚቆሙበት የመጨረሻ ማረፊያቸው ነው። በመሆኑም መርከበኞቹ በቆጵሮስ በሚያደርጉት ቆይታ ወቅት ማረፊያ ወደባቸው መውደቋን የሚገልጽ ወሬ ይሰማሉ። ይህ ለእነርሱ እንዴት አስደንጋጭ ነው! የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ‘ያለቅሳሉ።’

6. በጢሮስና በሲዶና መካከል የነበረውን ግንኙነት ግለጽ።

6 በፊንቄ የባሕር ዳርቻ ያሉትም ሰዎች እንዲሁ በግራ መጋባት ስሜት ይዋጣሉ። ነቢዩ እንዲህ ይላል:- “እናንተ በደሴት [“በባሕር ዳርቻ፣” NW] የምትኖሩ በባሕርም የሚሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች ንግድ የሞሉባችሁ ሆይ፣ ጸጥ በሉ። የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች።” (ኢሳይያስ 23:​2, 3) ‘በባሕር ዳርቻ የሚኖሩት’ ማለትም የጢሮስ አጎራባቾች እንደ መቅሰፍት ባለው የጢሮስ ውድቀት ተገርመው ጸጥ ይላሉ። እነዚህን ነዋሪዎች ‘የሞሉባቸውና’ ባለጠጋ ያደረጓቸው “የሲዶና ነጋዴዎች” እነማን ናቸው? ጢሮስ በመጀመሪያ በስተ ሰሜን በኩል 35 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘውና የወደብ ከተማ የሆነችው የሲዶና ቅኝ ግዛት ነበረች። ሲዶና በሳንቲሞቿ ላይ ሳይቀር የጢሮስ እናት መሆኗን ገልጻለች። ጢሮስ በብልጽግናዋ ሲዶናን ያስናቀች ቢሆንም አሁንም ‘የሲዶና ልጅ’ ናት። ነዋሪዎቿም ቢሆኑ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ራሳቸውን የሚጠሩት ሲዶናውያን ብለው ነበር። (ኢሳይያስ 23:​12) በመሆኑም “የሲዶና ነጋዴዎች” የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው የጢሮስ ነዋሪ የሆኑ ነጋዴዎችን ሳይሆን አይቀርም።

7. የሲዶና ነጋዴዎች ብልጽግናን ያስፋፉት እንዴት ነው?

7 በንግድ ሥራ የተሠማሩት የሲዶና ባለጠጋ ነጋዴዎች የሜዲትራኒያንን ባሕር ይሻገራሉ። በግብጽ ደል [delta] ክልል የሚገኘውንና የዓባይ ወንዝ ምሥራቃዊ ቅርንጫፍ የሆነውን የሺሖርን ዘር ወይም ጥራጥሬ ወደ ብዙ ቦታዎች ይዘው ይሄዳሉ። (ከ⁠ኤርምያስ 2:​18 ጋር አወዳድር።) “የአባይ ወንዝ መከር” ከግብጽ የሚገኙትን ሌሎች የምርት ውጤቶችንም ይጨምራል። እነዚህን ሸቀጦች መነገድም ሆነ መለወጥ በባሕር ላይ ለሚጓዙት ነጋዴዎችም ሆነ ከእነርሱ ጋር ለሚነግዱት ብሔራት ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ነገር ነበር። የሲዶና ነጋዴዎች ጢሮስን በገቢ ሞልተዋት ነበር። በእርግጥም ጢሮስ በመጥፋቷ እጅግ ያዝናሉ!

8. የጢሮስ መጥፋት በሲዶና ላይ የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው?

8 ቀጥሎ ኢሳይያስ ሲዶናን እንደሚከተለው ይላታል:- “ሲዶና ሆይ፣ ባሕር፣ የባሕር ምሽግ:- አላማጥሁም፣ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፣ ደናግልንም አላሳደግሁም ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ።” (ኢሳይያስ 23:​4) ጢሮስ ከጠፋች በኋላ ከተማዋ የነበረችበት ዳርቻ ባድማና ምድረ በዳ ሆኖ ይታያል። ባሕሩ ልጆቿን እንዳጣችና እጅግ ከመጨነቋ የተነሣ ጭራሽ አልወለድኳቸውም ብላ እንደምትናገር እናት በጭንቀት ይጮኻል። ሲዶና በልጅዋ ላይ በደረሰባት ነገር ታፍራለች።

9. የጢሮስ መውደቅ በሕዝቡ ላይ የሚያስከትለው ኃዘን ከየትኞቹ ሌሎች ክስተቶች በኋላ ከታየው ድንጋጤ ጋር የሚመሳሰል ይሆናል?

9 አዎን፣ ጢሮስ ጠፋች የሚለው ወሬ ብዙዎችን ያሳዝናል። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “ስለ ግብጽ በተነገረው ወሬ እንደሆነው ሁሉ በጢሮስም ወሬ እንዲሁ ምጥ ይይዛቸዋል።” (ኢሳይያስ 23:​5 NW) በኃዘን የሚዋጡት ሰዎች ስቃይ ስለ ግብጽ ወሬ በተሰማ ጊዜ የነበረውን ያህል ይሆናል። ነቢዩ የትኛውን ወሬ ማለቱ ነው? ምናልባት ቀደም ሲል ‘ስለ ግብጽ የተናገረውን ሸክም’ ፍጻሜ ማለቱ ሊሆን ይችላል። * (ኢሳይያስ 19:​1-25) ወይም ደግሞ በሙሴ ዘመን ስለጠፋው የፈርዖን ሠራዊት የተነገረውን ወሬ ማለቱም ሊሆን ይችላል። ይህ ወሬ በብዙ ቦታዎች ድንጋጤን ፈጥሯል። (ዘጸአት 15:​4, 5, 14-16፤ ኢያሱ 2:​9-11) ያም ሆነ ይህ ስለ ጢሮስ መጥፋት የሚሰሙት ሁሉ ከባድ ምጥ ይይዛቸዋል። ርቃ ወደምትገኘው ተርሴስ ሄደው እንዲሸሸጉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል። እንዲሁም ከፍ ባለ ድምፅ ኃዘናቸውን እንዲገልጹ ታዝዘዋል:- “ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ።”​—⁠ኢሳይያስ 23:​6

‘ከቀድሞ ዘመን’ አንስቶ ደስተኛ የሆነች

10-12. የጢሮስን ብልጽግና፣ ጥንታዊነት እንዲሁም የነበራትን ተጽዕኖ ግለጽ።

10 ኢሳይያስ እንደሚከተለው ብሎ በጠየቀ ጊዜ እንደሚጠቁመን ጢሮስ ጥንታዊ ከተማ ነች:- “በቀድሞ ዘመን ተመሥርታ የነበረችው . . . የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን?” (ኢሳይያስ 23:​7) የጢሮስ የብልጽግና ታሪክ ወደኋላ ቢያንስ እስከ ኢያሱ ዘመን ድረስ ይሄዳል። (ኢያሱ 19:​29) በእነዚህ ዓመታት የብረታ ብረትና የመስታወት ሥራዎች እንዲሁም ወይን ጠጅ ቀለም በማምረት የታወቀች ሆናለች። የጢሮስ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ካባ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ሲሆን ውድ ዋጋ ያላቸውን የጢሮስ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች የሚገዙት ታላላቅ ሰዎች ናቸው። (ከ⁠ሕዝቅኤል 27:​7, 24 ጋር አወዳድር።) ከዚህም ሌላ ጢሮስ በየብስ ላይ የሚጓዙ ነጋዴዎች መናኸሪያና ከፍተኛ የአስመጪና ላኪዎች ማዕከል ነበረች።

11 ከዚህም በተጨማሪ ከተማዋ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ነበራት። ኤል ስፕራግ ዴ ካምፕ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የጦርነት ሰዎች ባይሆኑም ማለትም ንግድ እንጂ ውትድርና የማይቀናቸው ሰዎች ቢሆኑም ፊንቄያውያን ከተሞቻቸውን የመከላከል ጠንካራ ወኔና አትንኩኝ ባይነት ነበራቸው። ይህ ባሕሪያቸው በባሕር ላይ ከነበራቸው የበላይነት ጋር ተዳምሮ የጢሮስ ሰዎች በወቅቱ እጅግ ጠንካራ የነበረውን የአሦራውያን ሠራዊት ለመቋቋም አስችሏቸዋል።”

12 በእርግጥም ጢሮስ በሜዲትራኒያኑ ዓለም ታሪኳን ጽፋ አልፋለች። ‘በዚያም እንደ እንግዳ ሆና ትኖር ዘንድ እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈልሱዋት ነበር።’ (ኢሳይያስ 23:​7) ፊንቄያውያን በየስፈራው የንግድ ማዕከሎችና ጊዜያዊ ማረፊያ ወደቦች በማቋቋም ሩቅ ቦታዎች ሁሉ ይሄዱ ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ከጊዜ በኋላ በቅኝ ግዛትነት ይዘዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ ሰሜናዊ ዳርቻ የምትገኘው ካርቴጅ የጢሮስ ቅኝ ግዛት ነች። ከጊዜ በኋላ ከጢሮስ በላይ ገናና በመሆን በሜዲትራኒያኑ ዓለም የበላይነትን ለመያዝ ከሮም ጋር መቀናቀን ትጀምራለች።

ትዕቢቷ ይሻራል

13. በጢሮስ ላይ የፍርድን መልእክት ሊናገር የሚደፍር ማን ነው የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?

13 ከጢሮስ ጥንታዊነትና ብልጽግና አንጻር ሲታይ ቀጥሎ ያለው ጥያቄ መቅረቡ ተገቢ ይሆናል:- “አክሊል ባስጫነች ከተማ በጢሮስ ላይ ይህን የወሰነ ማን ነው? ነጋዴዎችዋ አለቆች ናቸው፣ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን ናቸው።” (ኢሳይያስ 23:​8) በየአካባቢው ባሉት ቅኝ ግዛቶቿ ላይ ኃያላን ሰዎችን ከፍተኛ ሥልጣን ሰጥታ የሰየመችውንና በዚህም ምክንያት ‘አክሊል ያስጫነች’ ተብላ የተጠራችውን ጢሮስን ደፍሮ የሚናገር ማን ነው? ነጋዴዎቿ አለቆች በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን የሆኑትን ይህችን ትልቅ ከተማ ለመናገር የሚደፍር ማን አለ? በሊባኖስ ቤይሩት የሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም የጥንታዊ ቅርሶች ዲሬክተር የነበሩት ሞሪስ ሼሃብ እንዲህ ብለዋል:- “ጢሮስ ከዘጠነኛው እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ድረስ ገናና ሆና የኖረች ሲሆን ይህ ጉዳይ ለለንደን የተገለጠላት በሃያኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።” ታዲያ ይህችን ከተማ ደፍሮ የሚናገር ማን ነው?

14. በጢሮስ ላይ የፍርድ ውሳኔ ያስተላለፈው ማን ነው? ለምንስ?

14 በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠው ምላሽ በጢሮስ ላይ ድንጋጤን የሚፈጥር ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል።” (ኢሳይያስ 23:​9) ይሖዋ በዚህች ባለጠጋና ጥንታዊ ከተማ ላይ የፍርድ ውሳኔ ያስተላለፈው ለምንድን ነው? ነዋሪዎቿ የሐሰት አምላክ የሆነውን በኣልን ስለሚያመልኩ ነውን? ጢሮስ፣ አክዓብ የተባለውን የእስራኤል ንጉሥ አግብታ የይሖዋን ነቢያት ካስጨፈጨፈችውና የሲዶናና የጢሮስ ንጉሥ የኤትበኣል ሴት ልጅ ከሆነችው ከኤልዛቤል ጋር ግንኙነት ስላላት ነውን? (1 ነገሥት 16:​29, 31፤ 18:​4, 13, 19) የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አይደለም የሚል ነው። ጢሮስ የተወገዘችው እስራኤላውያንን ጨምሮ በሌሎች ሕዝቦች ትከሻ ስለበለጸገችበት የማን አለብኝነት ኩራቷ ነው። ይሖዋ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በነቢዩ ኢዩኤል አማካኝነት ለጢሮስና ለሌሎችም ከተሞች እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና።” (ኢዩኤል 3:​6) ጢሮስ በአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደ ሸቀጥ ስትነግድ ይሖዋ ዝም ብሎ ያያልን?

15. ኢየሩሳሌም በናቡከደነፆር እጅ ስትወድቅ የጢሮስ ምላሽ ምን ይሆናል?

15 አንድ መቶ ዓመት ቢያልፍም ጢሮስ አትቀየርም። የንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊት በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋ ጢሮስ ደስ ይላታል:- “እሰይ፣ የአሕዛብ በር የነበረች [ኢየሩሳሌም] ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፤ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለች።” (ሕዝቅኤል 26:​2) ጢሮስ ኢየሩሳሌም በመጥፋቷ እርሷ ትርፍ እንደምታገኝ በማሰብ ደስ ይላታል። የይሁዳ ዋና ከተማ ከእንግዲህ የእርሷ ተፎካካሪ ስለማትሆን የበለጠ የንግድ እንቅስቃሴ ይኖረኛል ብላ ጠብቃለች። ይሖዋ ራሳቸውን “ክቡራን” አድርገው የሚቀማጠሉትን ማለትም በትዕቢት ከአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ጎን የሚሰለፉትን ያዋርዳል።

16, 17. ከተማዋ ስትወድቅ የጢሮስ ነዋሪዎች ምን ይሆናሉ? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

16 ይሖዋ ስለ ጢሮስ የተናገረውን የውግዘት ቃል በመቀጠል ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “የተርሴስ ልጅ ሆይ፣ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ ጐርፈሽ እለፊ። በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን [“ፊንቄ፣” NW] አገር አዘዘ። እርሱም:- አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፣ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ።”​—⁠ኢሳይያስ 23:​10-12

17 ጢሮስ “የተርሴስ ልጅ ሆይ” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው? ምናልባት ጢሮስ ድል ከተነሳች በኋላ ከሁለቱ ይበልጥ ኃያል የምትሆነው ተርሴስ ስለሆነች ይሆናል። * የወደመችው ጢሮስ ነዋሪዎች በኃይል እንደሚጎርፍ ወንዝ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ይበተናሉ። ሞልቶ አካባቢውን እንደሚያጥለቀልቅ ወንዝ ወደ አጎራባች ሜዳዎች ሁሉ ይፈስሳሉ። ኢሳይያስ ስለ “ተርሴስ ልጅ” የተናገረው መልእክት በጢሮስ ላይ የሚደርሰው ነገር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ አበክሮ የሚገልጽ ነው። እጁን ዘርግቶ ትእዛዝ የሚያስተላልፈው ይሖዋ ራሱ ነው። ይህን ውጤት ሊያስቀር የሚችል የለም።

18. ጢሮስ “የሲዶና ድንግል ልጅ” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው? ያለችበት ሁኔታስ የሚለወጠው እንዴት ነው?

18 ኢሳይያስ ጢሮስን “የሲዶና ድንግል ልጅ” ሲልም ጠርቷታል። ይህም ከዚህ ቀደም በባዕድ ወራሪዎች ተይዛና ተበዝብዛ እንደማታውቅ አሁንም ቢሆን ነፃ ግዛት መሆኗን የሚጠቁም ነው። (ከ⁠2 ነገሥት 19:​21፤ ኢሳይያስ 47:​1፤ ኤርምያስ 46:​11 ጋር አወዳድር።) ይሁንና፣ አሁን ግን ጢሮስ ትጠፋለች። አንዳንዶቹ ነዋሪዎቿም ልክ እንደ ስደተኛ የፊንቄ ቅኝ ግዛት ወደ ሆነችው ኪቲም ይሻገራሉ። ሆኖም ኢኮኖሚያዊ ኃይላቸው ስለተሟጠጠ በኪቲም እረፍት አያገኙም።

ከለዳውያን ይበዘብዟታል

19, 20. ጢሮስን እንደሚያንበረክክ ትንቢት የተነገረለት ማን ነው? ይህስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ በጢሮስ ላይ ያሳለፈውን የፍርድ ውሳኔ የሚያስፈጽመው የፖለቲካ ኃይል የትኛው ይሆን? ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፣ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፣ ባድማም አደረጓት። እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ።” (ኢሳይያስ 23:​13, 14) ጢሮስን የሚያንበረክኳት አሦራውያን ሳይሆኑ ከለዳውያን ናቸው። ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችላቸውን ግንብ በማቆም ጢሮስን እንዳልነበረች ያደርጓታል። የተርሴስ መርከቦች ምሽግ የነበረችው ከተማ የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።

20 ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ልክ በትንቢቱ መሠረት ጢሮስ በባቢሎን ላይ በማመፅዋ ናቡከደነፆር ከተማዋን ከበበ። ጢሮስ እንደማትበገር በማሰብ ወረራውን መክታለች። በከበባው ወቅት የባቢሎን ወታደሮች ከራስ ቁሩ መፈጋፈግ የተነሣ ፀጉራቸው ‘ተመልጦና’ ለከበባው የሚያስፈልገውን ግንባታ ሲያከናውኑ ከተሸከሙት ዕቃ የተነሳ ትከሻቸው ‘ተልጦ’ ነበር። (ሕዝቅኤል 29:​18) ከበባው ናቡከደነፆርን ከባድ ወጪ ጠይቆበታል። ከባሕሩ ዳርቻ የነበረው የጢሮስ ከተማ ወደመ። ይሁን እንጂ ብዝበዛ አላገኙም። አብዛኛውን የጢሮስ ሀብት ከባሕሩ ዳርቻ 800 ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ትንሽ ደሴት አሽሽተው ነበር። የከለዳውያኑ ንጉሥ የባሕር ኃይል ስላልነበረው ደሴቲቱን መቆጣጠር አልቻለም። ከ13 ዓመታት በኋላ ጢሮስ እጅዋን ብትሰጥም ሕልውናዋን ጨርሳ ስለማታጣ ተጨማሪ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ትመለከታለች።

“ወደ ዋጋዋም ትመለሳለች”

21. ጢሮስ ‘የተረሳች የሆነችው’ በምን መንገድ ነው? ደግሞስ ለምን ያህል ጊዜ?

21 ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት ትንቢት መናገሩን ይቀጥላል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች።” (ኢሳይያስ 23:​15ሀ) ባቢሎናውያን በባሕሩ ዳርቻ ያለውን ከተማ ካጠፉ በኋላ በደሴት ላይ ያለችው የጢሮስ ከተማ “የተረሳች ትሆናለች።” ልክ በትንቢቱ መሠረት “እንደ አንድ ንጉሥ” ማለትም የባቢሎናውያን ግዛት ዘመን ያህል የደሴቲቱ የጢሮስ ከተማ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ኃይል ያላት ከተማ መሆኗ ይቀራል። ይሖዋ በኤርምያስ በኩል እንደተናገረው የእርሱን የቁጣ ጽዋ ከሚጠጡት ብሔራት መካከል ጢሮስ አንዷ ትሆናለች። “እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ” ብሏል። (ኤርምያስ 25:​8-17, 22, 27) እርግጥ የባቢሎናውያን ግዛት በ539 ከዘአበ ስለወደቀ የጢሮስ የደሴት ከተማ ለባቢሎን ሙሉ 70 ዓመት አልተገዛችም። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው 70ዎቹ ዓመታት ባቢሎናውያን ገናና የነበሩበትን ማለትም የባቢሎናውያን ንጉሣዊ ሥርወ መንግሥት ዙፋኑ “ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ” ከፍ ያለ እንደሆነ አድርጎ በማሰብ የተኩራራበትን ዘመን የሚያመለክቱ ነበሩ። (ኢሳይያስ 14:​13) የተለያዩ አሕዛብ በተለያየ ጊዜ በባቢሎናውያን ቀንበር ሥር ገብተዋል። ይሁን እንጂ በ70ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ይህ የበላይነት ይንኮታኮታል። በዚህ ጊዜ የጢሮስ ዕጣ ምን ይሆናል?

22, 23. ጢሮስ ከባቢሎናውያን የበላይነት ነፃ ስትወጣ ምን ትሆናለች?

22 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፣ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፣ ወደ ዋጋዋም ትመለሳለች፣ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች።”​—⁠ኢሳይያስ 23:​15ለ-17

23 ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከወደቀች በኋላ ፊንቄ የሜዶ ፋርስ የግዛት ክልል ሆናለች። የፋርሱ ንጉሠ ነገሥት ታላቁ ቂሮስ ጠባብ አመለካከት ያለው ሰው አልነበረም። ደንበኞቿ የሸሿት የተረሳች ጋለሞታ በከተማ ውስጥ እየተዘዋወረች በገና በመደርደርና ዘፈን በማንጎራጎር አዲስ ደንበኞችን ለመማረክ እንደምትጥር ሁሉ ጢሮስም በዚህ አዲስ አስተዳደር ሥር የቀድሞ እንቅስቃሴዋን በመቀጠል የዓለም የንግድ ማዕከል ሆና እውቅና ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች። ጢሮስ ይሳካላት ይሆን? አዎን፣ ይሖዋ ስኬት ይሰጣታል። ከጊዜ በኋላ የደሴቲቷ ከተማ በጣም ስለምትበለጽግ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ገደማ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ይላል:- “ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፣ ብሩንም እንደ አፈር ጥሩውንም ወርቅ እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች።”​—⁠ዘካርያስ 9:​3

‘ዋጋዋ የተቀደሰ ይሆናል’

24, 25. (ሀ) የጢሮስ ትርፍ ለይሖዋ የተቀደሰ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) ጢሮስ የአምላክን ሕዝብ ብትረዳም ይሖዋ እርሷን በተመለከተ ምን ትንቢት አስነግሯል?

24 ቀጥሎ ያሉት ትንቢታዊ ቃላት ምንኛ አስገራሚ ናቸው! “ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።” (ኢሳይያስ 23:​18) ጢሮስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ያገኘችው ትርፍ የተቀደሰ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ሕዝቡ በልተው ይጠግቡና ይለብሱ ዘንድ ነገሮች ከዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲፈጸሙ ያደርጋል። ይህ የሆነው የእስራኤላውያኑን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ መውጣት ተከትሎ ነው። የጢሮስ ሕዝብ ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚያስችል የዝግባ ዛፍ በመስጠት ተባብሯቸዋል። ከኢየሩሳሌምም ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን ቀጥለዋል።​—⁠ዕዝራ 3:​7፤ ነህምያ 13:​16

25 ይህ ሁሉ ቢሆንም ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት ስለ ጢሮስ ተጨማሪ መልእክት እንዲነገር አድርጓል። ዘካርያስ አሁን ባለ ጠጋ ስለሆነችው የደሴት ከተማ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ ጌታ ይገፍፋታል፣ በባሕርም ላይ ያለውን ብርታትዋን ይመታል፤ እርስዋም በእሳት ትበላለች።” (ዘካርያስ 9:​4) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ332 ከዘአበ ሐምሌ ወር ታላቁ እስክንድር ያቺን ኩሩ የባሕር ላይ እመቤት ባጠፋት ጊዜ ነው።

ከፍቅረ ነዋይና ከትዕቢት ራቁ

26. አምላክ ጢሮስን ያወገዛት ለምንድን ነው?

26 ይሖዋ ጢሮስን ስለ ትዕቢቷ አውግዟታል። ይህ ይሖዋ የማይወደው ባሕርይ ነው። “ትዕቢተኛ ዓይን” ይሖዋ ከሚጠላቸው ሰባት ነገሮች መካከል አንዱ ነው። (ምሳሌ 6:​16-19) ጳውሎስ ኩራትን ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር አያይዞ የገለጸው ሲሆን ሕዝቅኤል ኩራተኛ ስለነበረችው ጢሮስ የሰጠው መግለጫ ለሰይጣንም የሚሠራ እውነታ አለው። (ሕዝቅኤል 28:​13-15፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​6) ጢሮስ ኩራተኛ የሆነችው ለምንድን ነበር? ሕዝቅኤል ስለ ጢሮስ ሲናገር “በብልጥግናህም ልብህ ኰርቶአል” ብሏል። (ሕዝቅኤል 28:​5) ከተማዋ ለንግድና ገንዘብ ለማካበት ያደረች ነበረች። ጢሮስ በዚህ ረገድ ያገኘችው ስኬት ደግሞ ከልክ በላይ እንድትታበይ አድርጓታል። ይሖዋ “ለጢሮስ ገዥ” “ልብህ ኰርቶአል አንተም:- እኔ አምላክ ነኝ፣ በእግዚአብሔር ወንበር . . . ተቀምጫለሁ ብለሃል” ሲል በሕዝቅኤል አማካኝነት ተናግሮታል።​—⁠ሕዝቅኤል 28:​2

27, 28. ሰዎች በምን ወጥመድ ሊያዙ ይችላሉ? ኢየሱስ ይህንን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

27 ብሔራት በትዕቢት እንዲሁም ለሀብት የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ወጥመድ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሁሉ ግለሰቦችም ከዚህ አደጋ ነፃ አይደሉም። ኢየሱስ ይህ ወጥመድ ምን ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል በምሳሌ አስረድቷል። እርሻው ጥሩ ፍሬ ስላፈራለት አንድ ሀብታም ገበሬ ተናግሯል። ሰውዬው በጣም ደስ ብሎት ለምርቱ ማከማቻ የሚሆን ትልቅ ጎተራ ለማሠራት እቅድ አወጣ። ወደፊት ድሎት የሞላበት ረጅም ሕይወት ሲኖር ታየው። ይሁን እንጂ የተፈጸመው ነገር ከዚህ የተለየ ነበር። አምላክ “አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?” አለው። አዎን ሰውዬው ሲሞት ሀብቱ ምንም አልፈየደለትም።​—⁠ሉቃስ 12:​16-20

28 ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።” (ሉቃስ 12:​21) ሃብታም መሆን በራሱ ስህተት አልነበረም። ወይም ጥሩ መከር መሰብሰብም ኃጢአት ሆኖ አይደለም። የሰውዬው ጥፋት እነዚህን ነገሮች የሕይወቱ ዋነኛ ግብ ማድረጉ ነው። ትምክህቱ በሙሉ ያረፈው ሀብቱ ላይ ነበር። የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ ሲመለከት ይሖዋ አምላክን ከግምት ውስጥ አላስገባም።

29, 30. ያዕቆብ በራስ ከመታመን እንድንጠበቅ ያስጠነቀቀው እንዴት ነው?

29 ያዕቆብም ይህንኑ ነጥብ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ብሏል:- “አሁንም:- ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፣ ተመልከቱ፣ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። በዚህ ፈንታ:- ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።” (ያዕቆብ 4:​13-15) ከዚያም ያዕቆብ “አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው” ብሎ በተናገረ ጊዜ በሀብትና በትዕቢት መካከል ያለውን ተዛማጅነት ገልጿል።​—⁠ያዕቆብ 4:​16

30 አሁንም ቢሆን የንግድ ሥራ ኃጢአት ነው ማለት አይደለም። ኃጢአቱ ብልጽግናን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ትዕቢት፣ እብሪትና በራስ መመካት ነው። አንድ ጥንታዊ ምሳሌ “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ” በማለት ጥበብ ያለበት ሀሳብ ይሰነዝራል። ድህነት ሕይወትን መራራ ሊያደርገው ይችላል። ይሁን እንጂ ብልጽግና አንድን ሰው “እግዚአብሔርስ ማን ነው?” እስከ ማለት ሊያደርሰው ይችላል።​—⁠ምሳሌ 30:​8, 9

31. አንድ ክርስቲያን ራሱን ምን ብሎ ቢጠይቅ ጥሩ ይሆናል?

31 ዛሬ የምንኖረው ብዙዎች በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት ወጥመድ በወደቁበት ጊዜ ውስጥ ነው። አመቺ የንግድ እንቅስቃሴ የተስፋፋበት ዘመን በመሆኑ ብልጽግና ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶታል። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን የንግድ ከተማ የነበረችው ጢሮስ በወደቀችበት ወጥመድ እንዳይወድቅ ራሱን መመርመሩ ተገቢ ይሆናል። የሀብት ባሪያ እስኪሆን ድረስ አብዛኛውን ጊዜውንና ጉልበቱን የሚያውለው ቁሳዊ ነገር ለማከማቸት ነውን? (ማቴዎስ 6:​24) እርሱ ካለው የበለጠ ወይም የተሻለ ነገር ባላቸው ሰዎች ይቀናልን? (ገላትያ 5:​26) ሀብታም ከሆነ ደግሞ ከሌሎች የበለጠ ክብርና መብት ሊያገኝ እንደሚገባው አድርጎ ያስባልን? (ከ⁠ያዕቆብ 2:​1-9 ጋር አወዳድር።) ሀብታም ካልሆነ ደግሞ የከፈለውን ዓይነት መሥዋዕትነት ከፍሎ ‘ባለጠጋ ለመሆን ይፈልጋልን?’ (1 ጢሞቴዎስ 6:​9) በሥራ ጉዳይ በጣም ከመወጠሩ የተነሣ በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት የሚሰጠው ቦታ እጅግ አነስተኛ ነውን? (2 ጢሞቴዎስ 2:​4) በንግድ ሥራው ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ቸል እስኪል ድረስ ሃብትን በማሳደድ ተጠምዷልን?​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​10

32. ዮሐንስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ይህንንስ ሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?

32 ያለንበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ መያዝ ያለበት የአምላክ መንግሥት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገራቸውን ቃላት ሁል ጊዜ ልናስብባቸው ይገባል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ . . . ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐንስ 2:​15, 16) ሕልውናችንን ለመጠበቅ ስንል በዓለም ኢኮኖሚያዊ ዝግጅቶች መጠቀም እንዳለብን አይካድም። (2 ተሰሎንቄ 3:​10) ከዚህ አንጻር ‘ዓለምን እንጠቀምበታለን።’ ይሁን እንጂ ‘ሙሉ በሙሉ አንጠቀምበትም።’ (1 ቆሮንቶስ 7:​31 NW) ለቁሳዊ ነገሮች ማለትም በዓለም ውስጥ ላሉት ነገሮች ከልክ ያለፈ ፍቅር ካደረብን ለይሖዋ ፍቅር የለንም ማለት ነው። ‘የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮትን እንዲሁም የይታይልኝ ባይነት መንፈስን’ መከታተል የአምላክን ፈቃድ ከመፈጸም ጋር የሚጣጣም ነገር አይደለም። * ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ነው።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​16, 17 NW

33. ክርስቲያኖች ጢሮስ በወደቀችበት ወጥመድ ከመያዝ ሊርቁ የሚችሉት እንዴት ነው?

33 ጢሮስን ወጥመድ የሆነባት ከምንም ነገር በላይ ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ነው። በቁሳዊ ነገሮች አንጻር ሲታይ ተሳክቶላት ነበር። ትዕቢተኛ ሆነች ከዚያም ለትዕቢቷ ቅጣት ተቀበለች። የእርሷ ምሳሌ ዛሬ ላሉ ብሔራትም ሆነ ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ ይሆናል። የሐዋርያው ጳውሎስን ማሳሰቢያ መከተሉ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ክርስቲያኖች “የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ” አጥብቆ አሳስቧል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንድ ምሁራን ተርሴስ በሜዲትራኒያን በስተ ምዕራብ የምትገኘው ሰርዲኒያ ነች ይላሉ። ሰርዲኒያም ቢሆን የምትገኘው ከጢሮስ በጣም ርቃ ነበር።

^ አን.9 የዚህን መጽሐፍ 15ኛ ምዕራፍ ገጽ 200-207 ተመልከት።

^ አን.17 “የተርሴስ ልጅ” የሚለው መግለጫ የተርሴስን ነዋሪዎችም ሊያመለክት ይችል ይሆናል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የተርሴስ ተወላጅ የሆኑት ሰዎች አባይ ሲሞላ በየአቅጣጫው እንደሚፈስስ ሁሉ በየአቅጣጫው ሄደው ለመነገድ ነፃ ሆነዋል።” በዚህም መልኩ ቢሆን አጽዕኖት የተሰጠው ነገር የጢሮስ ውድቀት የሚያስከትለው መዘዝ ነው።

^ አን.32 “የይታይልኝ ባይነት መንፈስ” የሚለው መግለጫ አላዞኒያ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን “በምድራዊ ነገሮች ምቾት የሚተማመን ከንቱና ባዶ ትዕቢት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል።​—⁠ዘ ኒው ቴየርስ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲከን

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 256 ላይ የሚገኝ ካርታ]

[መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት]

አውሮፓ

ስፔይን (ተርሴስ ነበረችበት ተብሎ የሚታሰበው አካባቢ)

የሜዲትራኒያን ባሕር

ሳርዲኒያ

ቆጵሮስ

እስያ

ሲዶና

ጢሮስ

አፍሪካ

ግብጽ

[በገጽ 250 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ጢሮስ የምትንበረከከው በባቢሎን እንጂ በአሦር አይደለም

[በገጽ 256 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

የጢሮስ ዋነኛ አምላክ የሆነው የሜልካርት ምስል የተቀረጸበት ሳንቲም

[በገጽ 256 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

የፊንቄን መርከብ የሚያሳይ ናሙና