በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰው ዘር ብርሃን የፈነጠቀ የአምላክ ነቢይ

ለሰው ዘር ብርሃን የፈነጠቀ የአምላክ ነቢይ

ምዕራፍ አንድ

ለሰው ዘር ብርሃን የፈነጠቀ የአምላክ ነቢይ

1, 2. በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹን ሰዎች የሚያስጨንቋቸው የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?

ዛሬ ሁሉም ነገር በሰው እጅ ያለ ይመስላል። ወደ ሕዋ የሚደረግ ጉዞ፣ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ፣ ጀነቲካዊ ምሕንድስና እና ሌሎችም ሳይንሳዊ ግኝቶች የሰው ዘር የተሻለ እንዲያውም ረጅም ሕይወት አገኛለሁ ብሎ ተስፋ እንዲያደርግ የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

2 እንዲህ ያሉት እድገቶች በርህን ሳትቆልፍ ያለ ስጋት እንድትቀመጥ አስችለውሃል? የጦርነት ደመና እንዲገፈፍ ማድረግ ችለዋል? በሽታን ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘንስ አስቀርተዋል? በፍጹም! የሰው ልጅ የደረሰበት የእድገት ደረጃ የቱንም ያህል ድንቅ ቢሆን አቅሙ ውስን ነው! ወርልድዋች የተባለው ተቋም ያወጣው አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እንዴት ወደ ጨረቃ መጓዝ እንደምንችል አውቀናል፣ በጣም ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የኮምፒውተር ክፍሎች ሠርተናል እንዲሁም በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትን ጂኖች በሌላ ጂን መተካት ችለናል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን አንድ ቢልዮን ለሚያክሉ ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ፣ እየጠፉ ያሉትን በሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ ዝርያዎች መታደግ ወይም ከባቢ አየራችንን ሳናዛባ የኃይል ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻልንም።” ብዙ ሰዎች ማጽናኛና ተስፋ ለማግኘት ወደ ማን ዘወር ማለት እንዳለባቸው ስለማያውቁ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ መጨነቃቸው ምንም አያስደንቅም።

3. በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በይሁዳ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

3 ዛሬ እኛን የገጠመን ሁኔታ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረው የአምላክ ሕዝብ ከገጠመው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። በወቅቱ የይሁዳ ነዋሪዎች ማጽናኛ ያስፈልጋቸው ስለነበር አምላክ ነቢዩ ኢሳይያስ ለሕዝቡ አጽናኝ መልእክት እንዲያደርስ ተልዕኮ ሰጠው። የብሔሩን ሰላም ያናጉ ሁኔታዎች ተከስተው ነበር። ጨካኝ የሆነው የአሦር ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ምድሪቱን ስጋት ላይ በመጣል ብዙዎችን የሚያሸብርበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። የአምላክ ሕዝብ መዳን ለማግኘት በማን ሊታመን ይችላል? አምላካቸው ይሖዋ መሆኑን ይናገሩ እንጂ ትምክህታቸውን የጣሉት በሰዎች ላይ ነበር።​—⁠2 ነገሥት 16:​7፤ 18:​21

በጨለማ ውስጥ የሚበራ ብርሃን

4. ኢሳይያስ እንዲያውጅ የተነገረው ሁለት ዓይነት ይዘት ያለው መልእክት ምንድን ነው?

4 ይሁዳ በተከተለችው የዓመፀኝነት ጎዳና ምክንያት ኢየሩሳሌም ልትጠፋና የይሁዳም ነዋሪዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ሊወሰዱ ነው። አዎን፣ የጨለማ ዘመን እየመጣ ነበር። ይሖዋ ለነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ የጥፋት ዘመን ትንቢት የመናገር ተልዕኮ ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ምሥራችም እንዲያውጅ ነግሮታል። ከ70 ዓመት ግዞት በኋላ አይሁዳውያኑ ከባቢሎን ነፃ ይወጣሉ! በደስታ የተሞሉ ቀሪዎች ወደ ጽዮን ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ በዚያ መልሰው የማቋቋም መብት ያገኛሉ። ይህ አስደሳች መልእክት እንዲነገር በማድረግ ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት በጨለማ ውስጥ ብርሃን ፈንጥቋል።

5. ይሖዋ ዓላማውን ከረጅም ጊዜ በፊት የገለጸው ለምንድን ነው?

5 ይሁዳ የጠፋችው ኢሳይያስ ትንቢቱን ከመዘገበ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ቆይታ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ይህን ከሚያክል ረጅም ጊዜ በፊት ዓላማውን የገለጸው ለምንድን ነው? ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኘው ኢሳይያስ ትንቢቱን ሲናገር በጆሮአቸው የሰሙት ሰዎች ከሞቱ ከብዙ ጊዜ በኋላ አይደለምን? ይህ እውነት ነው። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ይህን ምሥጢር ለኢሳይያስ በመግለጡ ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ስትጠፋ በወቅቱ የሚኖሩት ሰዎች ኢሳይያስ በጽሑፍ ያሰፈረው ትንቢታዊ መልእክት ይኖራቸዋል። ይህም ይሖዋ “በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን” የሚናገር አምላክ መሆኑን በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሆናል።​—⁠ኢሳይያስ 46:​10፤ 55:​10, 11

6. ይሖዋ ከማንኛውም ሰብዓዊ ትንቢት ተናጋሪ የላቀ ነው የምንልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

6 እንዲህ ብሎ ሊናገር የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። አንድ ሰው በጊዜው ያለውን ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ አዝማሚያ በማገናዘብ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሆነውን ነገር መተንበይ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በየትኛውም ወቅት ላይ አልፎ ተርፎም ከረጅም ጊዜ በኋላ ምን ነገር እንደሚከናወን በፍጹም እርግጠኝነት ትንቢት ሊናገር የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። አገልጋዮቹም አንዳንድ ነገሮች ከመከናወናቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ትንቢት የመናገር ችሎታ እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።”​—⁠አሞጽ 3:​7

ስንት “ኢሳይያሶች”?

7. ብዙ ምሁራን የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ምን የተቃውሞ ሐሳብ ሰንዝረዋል? ለምንስ?

7 ብዙ ምሁራን መጽሐፉን የጻፈው ኢሳይያስ መሆኑን እንዲጠራጠሩ ምክንያት ከሆኗቸው ነገሮች አንዱ የትንቢት ጉዳይ ነው። እነዚህ ተቺዎች የኋለኛው የመጽሐፉ ክፍል የተጻፈው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማለትም በባቢሎን ግዞት ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ በኖረ ሌላ ሰው መሆን አለበት በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። እንደ እነርሱ አባባል ከሆነ ስለ ይሁዳ ጥፋት የሚናገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ የተጻፉ በመሆናቸው ጨርሶ ትንቢት አይደሉም። እነዚሁ ተቺዎች የኢሳይያስ መጽሐፍ ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 40 በኋላ ባቢሎን ኃያል መንግሥት እንደሆነችና እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ ሥር እንዳሉ አድርጎ ይናገራል ይላሉ። ከዚህ በመነሣት ይህንን የኋለኛውን ክፍል ማንም ይጻፈው ማን የተጻፈው በዚያው ዘመን ማለትም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በነበረ ሰው ነው ብለው ይከራከራሉ። እንዲህ ያለው የመከራከሪያ ነጥብ ተጨባጭ ማስረጃ አለውን? በፍጹም የለውም!

8. ምሁራን የኢሳይያስን ጸሐፊነት መጠራጠር የጀመሩት መቼ ነው? ይህ ጥርጣሬ እየተስፋፋ የሄደውስ እንዴት ነው?

8 የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ የመሆኑ ጉዳይ እስከ 12ኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ክርክር ተነስቶበት አያውቅም ነበር። በዚህ ወቅት ክርክሩን ያስነሱት አይሁዳዊው ተንታኝ አብርሃም ኢበኔዝራ ናቸው። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ እንዳሰፈረው “[አብርሃም ኢበኔዝራ] ስለ ኢሳይያስ መጽሐፍ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 40 በኋላ ያለው የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል በባቢሎን ምርኮ ወቅትና ወደ ጽዮን በተመለሱባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ላይ በኖረ አንድ ነቢይ የተጻፉ ናቸው ብለዋል።” በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን በርከት ያሉ ምሁራን የኢበኔዝራን አመለካከት ተቀብለው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በ1775 የኢሳይያስን መጽሐፍ የሚተነትን ጽሑፍ ያዘጋጁትና በ1789 ይህን ጽሑፍ ዳግመኛ ያሳተሙት ጀርመናዊው የሃይማኖት ምሁር ዮሃን ክሪስቶፍ ዶይደርላይን ይገኙበታል። ኒው ሴንቸሪ ባይብል ኮሜንታሪ የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 40-66 ያሉት ትንቢቶች በስምንተኛው መቶ ዘመን በኖረው ነቢይ በኢሳይያስ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ የተጻፉ ናቸው . . . የሚለው የዶይደርላይን መላምት ወግ አጥባቂ በሆኑት ምሁራን ዘንድ ካልሆነ በስተቀር በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።”

9. (ሀ) ምሁራን የኢሳይያስን መጽሐፍ የከፋፈሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ ስለመሆኑ የተነሣውን ውዝግብ ጠቅለል አድርገው የገለጹት እንዴት ነው?

9 ይሁን እንጂ የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ ስለመሆኑ የሚነሡት ጥያቄዎች በዚህ ብቻ አያበቁም። ሁለተኛ ወይም ዳግማዊ ኢሳይያስ አለ የሚለው ንድፈ ሐሳብ ሦስተኛም ጸሐፊ ሳይኖር አይቀርም የሚል ሐሳብ እንዲፀነስ በር ከፍቷል። * አንድ ምሁር ኢሳ. ምዕራፍ 15 እና 16 አንድ ያልታወቀ ነቢይ የጻፋቸው ናቸው ሲሉ ሌላው ደግሞ ከ⁠ኢሳ. 23 እስከ 27 ያሉት ምዕራፎች ጸሐፊ ማንነት አጠያያቂ ነው በማለታቸው የኢሳይያስ መጽሐፍ በሌሎች ተጨማሪ ክፍሎች ተከፋፍሏል። አንድ ሌላ ምሁር ደግሞ በ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 34 እና 35 ውስጥ ያሉትን ቃላት የጻፋቸው ኢሳይያስ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ለምን? ምክንያቱም የእነዚህ ምዕራፎች ይዘት ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 40 እስከ 66 ካለው ጋር ስለሚመሳሰል ነው። እነዚህ ምዕራፎች ደግሞ በስምንተኛው መቶ ዘመን በኖረው በኢሳይያስ ሳይሆን በሌላ ሰው የተጻፉ ናቸው ተብለዋል! የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ቻርልስ ሲ ቶሪ ይህ አስተሳሰብ ያስከተለውን ውጤት እንዲህ ሲሉ ጠቅለል አድርገው ገልጸውታል:- “በአንድ ወቅት ታላቅ ክብር የነበረው ‘ስለ ግዞት የተናገረው ነቢይ’ በመጽሐፉ ቁርጥራጮች የተቀበረ ያህል የተረሳ ሰው ሆኗል።” ይሁን እንጂ መጽሐፉ በዚህ መልክ መከፋፈሉን የማይደግፉ ምሁራን አሉ።

ጸሐፊው አንድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ

10. በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት አገላለጾች ተመሳሳይነት መጽሐፉ አንድ ጸሐፊ ብቻ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

10 የኢሳይያስን መጽሐፍ የጻፈው አንድ ሰው ነው ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ ጠንካራ ምክንያት አለ። አንደኛው ማስረጃ በመጽሐፉ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ተመሳሳይ አገላለጽ የሚገኝ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል “የእስራኤል ቅዱስ” የሚለው ሐረግ ከ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 1 እስከ 39 ድረስ 12 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ከ⁠ኢሳ. 40 እስከ 66 ድረስ ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ደግሞ 13 ጊዜ ተጠቅሷል። ይሁንና ለይሖዋ የተሰጠው ይህ መግለጫ በቀሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው 6 ጊዜ ያህል ብቻ ነው። በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የማይገኘው ይህ መግለጫ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ በብዛት መገኘቱ መጽሐፉ ኢሳይያስ የጻፈው አንድ ወጥ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

11. ከ⁠ኢሳ. 1 እስከ 39 እና ከ⁠ኢሳ. 40 እስከ 66 ድረስ ባሉት የኢሳይያስ ምዕራፎች መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

11 ከ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 1 እስከ 39 እና ከ⁠ኢሳ. 40 እስከ 66 ባሉት ምዕ​ራፎች መካከል ሌላም ተመሳሳይነት አለ። ምጥ የያዛት ሴት፣ “መንገድ” ወይም “ጎዳና” የሚሉትን የመሳሰሉ ለየት ያሉ ምሳሌያዊ መግለጫዎች በሁለቱም ክፍሎች ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሰው ይገኛሉ። * ከዚህም በተጨማሪ ስለ “ጽዮን” በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ሲሆን ከ⁠ኢሳ. 1 እስከ 39 ድረስ ባሉት ምዕራፎች ውስጥ 29 ጊዜ ከ⁠ኢሳ. 40 እስከ 66 ባሉት ምዕራፎች ደግሞ 18 ጊዜ ተጠቅሷል። እንዲያውም ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይበልጥ ስለ ጽዮን ብዙ ጊዜ የተጠቀ​ሰው በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ነው! ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ያሉት ማስረጃዎች መጽሐፉ በሁለት፣ በሦስት ወይም ከዚያ በሚበልጡ ሰዎች ተጽፎ ቢሆን ኖሮ “ሊገኙ የማይችሉ የመጽሐፉ ለየት ያሉ ገጽታዎች” መሆናቸውን ገልጿል።

12, 13. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የኢሳይያስ መጽሐፍ በአንድ ሰው የተጻፈ እንደሆነ የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

12 የኢሳይያስ መጽሐፍ ጸሐፊ አንድ ብቻ መሆኑን የሚያረጋግጠው ከሁሉ የበለጠው ጠንካራ ማስረጃ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የኢሳይያስ መጽሐፍ ጸሐፊ አንድ ብቻ ነው ብለው ያምኑ እንደነበር በግልጽ የሚያመለክቱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ሉቃስ በአሁኑ ጊዜ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ውስጥ የሚገኘውን ምንባብ ያነብ ስለነበር አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን ጠቅሷል። ይህ ደግሞ ተቺዎቹ በዳግማዊው ኢሳይያስ የተጻፈ ነው የሚሉት ክፍል ነው። ይሁን እንጂ ሉቃስ የጠቀሰው ኢትዮጵያዊው ሰው “የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ” እንደነበር ነው።​—⁠ሥራ 8:​26-28

13 ከዚህም በተጨማሪ የአጥማቂው ዮሐንስ አገልግሎት በዛሬው ጊዜ በ⁠ኢሳይያስ 40:​3 ላይ የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜ እንደሆነ የጠቀሰው ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ ምን እንዳለ ልብ በል። ማቴዎስ የትንቢቱ ጸሐፊ አድርጎ የጠቀሰው ማንን ነው? በውል የማይታወቅን ዳግማዊ ኢሳይያስ? በፍጹም፣ ‘ነቢዩ ኢሳይያስ’ በማለት ብቻ ነው የገለጸው። * (ማቴዎስ 3:​1-3) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ በ⁠ኢሳይያስ 61:​1, 2 ላይ ያሉት ቃላት የሚገኙበትን ጥቅልል አንብቧል። ሉቃስ ስለ ሁኔታው ሲዘግብ “የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት” ብሏል። (ሉቃስ 4:​17) ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ከፊተኛውም ሆነ ከኋለኛው የኢሳይያስ መጽሐፍ ክፍል የጠቀሰ ቢሆንም ጸሐፊው ያው ኢሳይያስ መሆኑን ከመግለጽ በቀር ሌላ ጸሐፊ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነገር እንኳ አልተናገረም። (ሮሜ 10:​16, 20፤ 15:​12) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የኢሳይያስ መጽሐፍ የሁለት፣ የሦስት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ጸሐፊዎች የሥራ ውጤት ነው የሚል እምነት አልነበራቸውም።

14. የሙት ባሕር ጥቅልሎች የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ መሆኑን የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

14 ከዚህም ሌላ የሙት ባሕር ጥቅልሎች የሚሰጡትን ምሥክርነት ተመልከት። ከእነዚህ ጥንታዊ መዛግብት መካከል ብዙዎቹ የተዘጋጁት ከኢየሱስ ዘመን በፊት ነው። የኢሳይያስ ጥቅልል በመባል የሚታወቀው በእጅ የተገለበጠ የኢሳይያስ መጽሐፍ ጥንታዊ ቅጂ የተዘጋጀው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው። ይህ ቅጂ ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 40 አንስቶ ያለውን የመጽሐፉን ክፍል የጻፈው ዳግማዊ ኢሳይያስ ነው የሚለውን የተቺዎቹን ሐሳብ ውድቅ የሚያደርግ ነው። እንዴት? በዚህ ጥንታዊ ቅጂ ላይ ዛሬ ኢሳ. ምዕራፍ 40 የሚባለው ክፍል የሚጀምረው በአንድ ዓምድ የመጨረሻ መስመር ላይ ሲሆን ይኸው የመክፈቻ ዓረፍተ ነገር የሚጠናቀቀው በቀጣዩ ዓምድ መጀመሪያ ላይ ነው። ገልባጩ እዚህ ቦታ ላይ የጸሐፊ ለውጥ ተደርጓል ወይም ሌላ ክፍል ይጀምራል ስለሚለው ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር እንዳልነበር ግልጽ ነው።

15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍሌቪየስ ጆሴፈስ ኢሳይያስ ቂሮስን አስመልክቶ ስለተናገረው ትንቢት ምን ብሏል?

15 በመጨረሻም፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍሌቪየስ ጆሴፈስ የሰጠውን ምሥክርነት ልብ በል። ጆሴፈስ ስለ ቂሮስ የተነገሩት የኢሳይያስ ትንቢቶች በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጻፋቸውን ብቻ ሳይሆን ቂሮስ ስለ እነዚህ ትንቢቶች ያውቅ እንደነበረም አመልክቷል። “ቂሮስ ስለ እነዚህ ነገሮች ሊያውቅ የቻለው ኢሳይያስ ከሁለት መቶ አሥር ዓመታት ቀደም ብሎ የጻፈውን የትንቢት መጽሐፍ በማንበቡ ነበር” ሲል ጽፏል። እንደ ጆሴፈስ ገለጻ ከሆነ ቂሮስ ስለ እነዚህ ትንቢቶች ማወቁ አይሁዳውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ እንዲነሳሳ አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ቂሮስ “አስቀድሞ የተጻፈውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት ነበረው።”​—⁠ጁዊሽ አንቲክዊቲስ፣ 11ኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 1 አንቀጽ 2

16. ተቺዎቹ ባቢሎን በኋለኞቹ የኢሳይያስ ምዕራፎች ውስጥ ኃያል መንግሥት ተደርጋ መገለጿን በመጥቀስ ስለሚያነሱት ክርክር ምን ማለት ይቻላል?

16 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ብዙ ተቺዎች ከኢሳይያስ ምዕራፍ 40 ጀምሮ ባለው ክፍል ውስጥ ባቢሎን ኃያል መንግሥት እንደሆነችና እስራኤላውያንም በምርኮ እንዳሉ ሆኖ መገለጹን ይናገራሉ። ታዲያ እንዲህ ያለው መግለጫ ጸሐፊው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደኖረ የሚጠቁም አይሆንምን? እንደዚያ ማለት አይቻልም። ከ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 40 በፊትም ባቢሎን ኃያል መንግሥት እንደሆነች ተደርጋ የተጠቀሰችበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል በ⁠ኢሳይያስ 13:​19 ላይ “የመንግሥታት ክብር” ወይም እንደ 1980 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አገላለጽ “ከመንግሥታት ሁሉ እጅግ የተዋበች” ተብላ ተጠርታለች። ባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችው ከአንድ ምዕተ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ስለነበር እነዚህ ቃላት ትንቢታዊ እንደሆኑ በግልጽ መረዳት ይቻላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺ ይህንን ሐሳብ “ለማስታረቅ” ሲሉ ብቻ ኢሳይያስ 13⁠ን የጻፈው ሌላ ሰው ነው ብለዋል! ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ ገና ወደፊት የሚከናወኑ ነገሮችን እንደተፈጸሙ አድርጎ መግለጽ የተለመደ ነው። ይህ የአጻጻፍ ስልት ትንቢቱ ፍጻሜውን ማግኘቱ የማይቀር መሆኑን የሚያስረግጥ ነው። (ራእይ 21:​5, 6) በእርግጥም “አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ” ብሎ ሊናገር የሚችለው የእውነተኛ ትንቢት ምንጭ የሆነው አምላክ ብቻ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 42:​9

አስተማማኝ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ

17. ከ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 40 በኋላ ስላለው የአጻጻፍ ለውጥ ምን ማለት ይቻላል?

17 እንግዲያው ማስረጃው ወደ ምን መደምደሚያ ያደርሳል? የኢሳይያስ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በአንድ ሰው ብቻ የተጻፈ መሆኑን ያረጋግጥልናል። መላው መጽሐፍ በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ሲተላለፍ የኖረው አንድ ወጥ ሥራ ሆኖ እንጂ ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቁጥር ባላቸው ሰዎች እንደተጻፈ ተደርጎ አይደለም። እርግጥ አንዳንድ ሰዎች የኢሳይያስ መጽሐፍ ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 40 በኋላ የአጻጻፍ ስልቱ ትንሽ ይቀየራል ይሉ ይሆናል። ሆኖም ኢሳይያስ የአምላክ ነቢይ ሆኖ ያገለገለው ከ46 ለማያንሱ ዓመታት እንደሆነ አስታውስ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመልእክቱ ይዘትና መልእክቱን የገለጸበት መንገድ ሊለወጥ እንደሚችል የታወቀ ነው። ደግሞም ኢሳይያስ ከአምላክ የተቀበለው ተልዕኮ ከባድ የፍርድ ማስጠንቀቂያ ማስታወቅ ብቻ አልነበረም። “አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ” የሚሉትንም የይሖዋ ቃላት ማሰማት ነበረበት። (ኢሳይያስ 40:​1) አይሁዳውያን ከ70 ዓመት ግዞት በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው እንደሚመጡ የሚገልጸው ተስፋ የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ በእጅጉ የሚያጽናና ነበር።

18. በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚብራራው የትኛው የኢሳይያስ መጽሐፍ ጭብጥ ነው?

18 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተብራሩት የኢሳይያስ ምዕራፎች መካከል አብዛኛዎቹ የአይሁዳውያንን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ መውጣት የሚገልጽ ጭብጥ የያዙ ናቸው። * ወደፊት እንደምናየው ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ብዙዎቹ ዘመናዊ ፍጻሜ አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ከአምላክ አንድያ ልጅ ሕይወትና ሞት ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አስገራሚ ትንቢቶችም ተመዝግበው ይገኛሉ። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን በጣም አስፈላጊ ትንቢቶች ማጥናት ለአምላክ አገልጋዮችም ሆነ በምድር ዙሪያ ላሉ ሌሎች ሰዎች ጠቃሚ እንደሆነ አያጠራጥርም። በእርግጥም እነዚህ ትንቢቶች ለመላው የሰው ዘር ብርሃን ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በዚህ መላ ምት መሠረት ከ⁠ኢሳ. 56 እስከ 66 ያሉትን ምዕራፎች ጽፏል ተብሎ የሚገመተውን ሦስተኛ ጸሐፊ ምሁራን ሳልሳዊ ኢሳይያስ ብለው ይጠሩታል።

^ አን.13 ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስም ስለዚሁ ጉዳይ ሲዘግቡ የተጠቀሙበት ሐረግ ተመሳሳይ ነው።​—⁠ማርቆስ 1:​2፤ ሉቃስ 3:​3፤ ዮሐንስ 1:​23

^ አን.18 የመጀመሪያዎቹ 40 ምዕራፎች በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የኢሳይያስ ትንቢት​—⁠ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1 በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ተብራርተዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከዳያክሮኒክ ግምገማ የተገኘ ማስረጃ

በብዙ ዓመታት ሂደት በቋንቋ ላይ የሚካሄደውን ለውጥ በተመለከተ ምርምር የሚደረግበት የዳያክሮኒክ የጥናት መስክ የኢሳይያስ መጽሐፍ አንድ ሰው ብቻ የጻፈው መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጠናል። የተወሰነው የኢሳይያስ መጽሐፍ ክፍል በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈና የቀረው ክፍል ደግሞ ከ200 ዓመታት በኋላ የተጻፈ ቢሆን ኖሮ በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ በተሠራበት የዕብራይስጥ ቋንቋ መካከል ልዩነት ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ ዌስትሚንስተር ቲዎሎጂካል ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ከዳያክሮኒክ ግምገማ የተገኘው ማስረጃ ከ⁠ኢሳይያስ 40-66 ያሉት ምዕራፎች ከግዞት በፊት የተጻፉ መሆናቸውን በእጅጉ የሚያረጋግጥ ነው።” የጥናቱን ሪፖርት የጻፉት ሰው እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “አሁንም ኢሳይያስ የተጻፈው በግዞት ዘመን ወይም ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ነው ብለው የሚተቹ ምሁራን ካሉ ይህን የሚሉት ከዳያክሮኒክ ግምገማዎች የተገኘውን ማረጋገጫ ላለማየት ዓይናቸውን ጨፍነው መሆን አለበት።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢሳይያስ መጽሐፍ የሙት ባሕር ጥቅልል የተወሰነ ክፍል። የኢሳ. ምዕራፍ 39 መጨረሻ በቀስት ተመልክቷል

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት አስቀድሞ ስለ አይሁዳውያን ነፃ መውጣት ተናግሯል