በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሐሰት ሃይማኖት ላይ ድንገተኛ ጥፋት እንደሚደርስ ተተነበየ

በሐሰት ሃይማኖት ላይ ድንገተኛ ጥፋት እንደሚደርስ ተተነበየ

ምዕራፍ ስምንት

በሐሰት ሃይማኖት ላይ ድንገተኛ ጥፋት እንደሚደርስ ተተነበየ

ኢሳይያስ 47:​1-15

1, 2. (ሀ) አንዳንዶች በዓለም ላይ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ በቅርቡ ሥር ነቀል ለውጥ ይገጥመዋል ብለው ለማመን የሚቸገሩት ለምንድን ነው? (ለ) በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 47 ላይ የሚገኙት ቃላት ወደፊትም ፍጻሜ እንደሚኖራቸው እንዴት እናውቃለን? (ሐ) የዓለም የሐሰት ሃይማኖት በጠቅላላ ‘ታላቂቱ ባቢሎን’ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

በአንድ ወቅት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት “ሃይማኖት ዳግም አንሰራራ” የሚል ጭብጥ ያለው ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር። ዘገባው እንደሚለው ሃይማኖት ዛሬም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብና አእምሮ የገዛ ይመስላል። በመሆኑም በዓለም ላይ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ በቅርቡ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ይገጥመዋል ብሎ ለማመን ሊከብድ ይችላል። ሆኖም የኢሳይያስ መጽሐፍ 47ኛ ምዕራፍ እንዲህ ያለ ለውጥ እንደሚከሰት ያመለክታል።

2 ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ከ2, 500 ዓመታት በፊት ተፈጽመዋል። ይሁን እንጂ በኢሳይያስ 47:​8 ላይ የሚገኙት ቃላት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከመጠቀሳቸውም በላይ ወደፊት ሌላ ፍጻሜ እንደሚኖራቸው ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ መጽሐፍ ላይ በጋለሞታ የተመሰለችውና ‘ታላቂቱ ባቢሎን’ በመባል የምትታወቀው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ጥፋት እንደሚጠብቃት አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 16:​19) የሐሰት ሃይማኖት ያቆጠቆጠው በጥንቷ ባቢሎን ውስጥ በመሆኑ የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች “ባቢሎን” ተብለው መጠራታቸው ተገቢ ነው። የሐሰት ሃይማኖት ከዚያ በመነሳት በአራቱም የምድር ማዕዘናት ተሰራጨ። (ዘፍጥረት 11:​1-9) ነፍስ አትሞትም፣ ሲኦል መቃጠያ ሥፍራ ነው እንዲሁም አምላክ አንድም ሦስትም ነው የሚሉትን የመሳሰሉ በባቢሎን የተፈለሰፉ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ የሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ እምነቶች ሆነዋል ማለት ይቻላል። * የኢሳይያስ ትንቢት የሃይማኖትን የወደፊት ዕጣ በተመለከተ የሚያስገነዝበን ነገር ይኖራል?

ባቢሎን ትቢያ ላይ ትጣላለች

3. የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችው ባቢሎን ምን ያህል ታላቅ እንደነበረች ግለጽ።

3 የሚከተለውን ስሜት ቀስቃሽ የሆነ መለኮታዊ መግለጫ ተመልከት:- “አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፣ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ቅልጣናምና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ።” (ኢሳይያስ 47:1) ባቢሎን ለበርካታ ዓመታት የዓለም ኃያል መንግሥት በመሆን በዙፋን ላይ ተቀምጣ ቆይታለች። “የመንግሥታት ክብር” ማለትም ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት፣ የንግድና የጦር ሠራዊት እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ማዕከል ሆና ነበር። (ኢሳይያስ 13:​19) የባቢሎን ግዛት በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድረስ ተስፋፍቶ ነበር። በተጨማሪም በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ስትቆጣጠር በድል አድራጊነት የምታደርገውን ግስጋሴ አምላክ እንኳን ሊገታው የቻለ አይመስልም ነበር! በመሆኑም ራሷን በማንኛውም የጠላት ኃይል የማትደፈር ‘ድንግል ልጅ’ አድርጋ ቆጥራለች። *

4. ባቢሎን ምን ይደርስባታል?

4 ይሁን እንጂ ይህች ኩሩ “ድንግል” ዓለምን ያላንዳች ተቀናቃኝ የገዛችበት ዘመን አክትሞ ከዙፋን የምትወርድበትና የኀፍረት ማቅ ተከናንባ ‘ትቢያ ላይ የምትቀመጥበት’ ጊዜ ተቃርቦ ነበር። (ኢሳይያስ 26:​5) እንደ “ቅልጣናምና ቅምጥል” ንግሥት የሚያሞላቅቃት አይኖርም። በመሆኑም ይሖዋ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷል:- “ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፤ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣዪው፤ ባትሽን ግለጪ፣ ወንዙን ተሻገሪ።” (ኢሳይያስ 47:2) መላውን የይሁዳ ብሔር ባሪያ አድርጋ ስትገዛ የኖረችው ባቢሎን አሁን እሷ ራሷ እንደ ባሪያ ትገዛለች! ከመንበሯ የሚያወርዷት ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ክብርን ዝቅ የሚያደርግ የጉልበት ሥራ እንድትሠራላቸው ያስገድዷታል።

5. (ሀ) ባቢሎን ‘መሸፈኛዋንና ረጅሙን ልብሷን’ የምትገፈፈው እንዴት ነው? (ለ) ‘ወንዙን እንድትሻገር’ መታዘዟ ምን ሊያመለክት ይችላል?

5 በዚህ መንገድ ባቢሎን የቀድሞ ክብሯንና ታላቅነቷን ሙሉ በሙሉ በማጣት ‘መሸፈኛዋንና ረጅሙን ልብሷን’ ትገፈፋለች። አስገባሪዎቿ ‘ወንዙን እንድትሻገር’ ያዝዟታል። አንዳንድ ባቢሎናውያን፣ ባሪያዎች የሚሠሩትን ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ይታዘዙ ይሆናል። አለዚያም ደግሞ ትንቢቱ አንዳንድ ባቢሎናውያን ተማርከው ቃል በቃል በወንዝ መካከል እየተጎተቱ እንደሚወሰዱ ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ባቢሎን በሰረገላ አስቀምጠው ወይም በወንበር ተሸክመው ወንዝ እንደሚያሻግሯት ንግሥት ተንፈላስሳ መጓዝ አትችልም። ከዚህ ይልቅ ኃፍረቱን ለመጣል እንደተገደደ ባሪያ ልብሷን ከፍ አድርጋ ባቷን በመግለጥ ወንዝ ትሻገራለች። እንዴት ያለ ውርደት ነው!

6. (ሀ) የባቢሎን ኃፍረተ ሥጋ የሚገለጠው በምን መንገድ ነው? (ለ) አምላክ ‘ለማንም የማይራራው’ እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 ይሖዋ በመቀጠል እንዲህ ሲል በባቢሎን ላይ ይሳለቃል:- “ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፤ እኔ እበቀላለሁ፣ ለማንም አልራራም።” (ኢሳይያስ 47:3) * አዎን፣ ባቢሎን ኃፍረትና ውርደት ትከናነባለች። በአምላክ ሕዝቦች ላይ የፈጸመችው ግፍና ጭካኔ ሁሉ አደባባይ ይወጣል። የአምላክን የበቀል እርምጃ ሊያስቀር የሚችል ሰው አይኖርም!

7. (ሀ) በግዞት ያሉ አይሁዳውያን ባቢሎን ስትወድቅ ምን ይሰማቸዋል? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡን የሚቤዠው በምን መንገድ ነው?

7 የአምላክ ሕዝቦች ለ70 ዓመታት በግዞት አስቀምጣ ስትገዛቸው የኖረችው ኃያሏ ባቢሎን ስትወድቅ እጅግ ሐሴት ያደርጋሉ። እንዲህ ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይናገራሉ:- “ታዳጊያችን፣ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ቅዱስ ነው።” (ኢሳይያስ 47:4) በሙሴ ሕግ አንድ እስራኤላዊ ዕዳውን ለመክፈል ሲል ራሱን ለባርነት ቢሸጥ የሥጋ ዘመዱ ከባርነት ሊታደገው ወይም ሊቤዠው ይችል ነበር። (ዘሌዋውያን 25:​47-54) አይሁዳውያን ለባቢሎን ባሪያዎች ሆነው ስለተሸጡ መቤዠት ወይም ነፃ መውጣት ያስፈልጋቸዋል። አንድ ወራሪ ኃይል ድል በሚያደርግበት ጊዜ በአብዛኛው ባሮች ጌቶቻቸው ከመለወጣቸው በቀር የሚያገኙት ነፃነት አይኖርም። ሆኖም ይሖዋ ድል አድራጊው ንጉሥ ቂሮስ አይሁዳውያንን ከባርነት ነፃ እንዲያወጣቸው ያነሳሳዋል። ቂሮስ በአይሁዳውያን ፋንታ ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሳባ “ቤዛ” ሆነው ይሰጡታል። (ኢሳይያስ 43:​3) የእስራኤል ታዳጊ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ነው መባሉ ተገቢ ነው። እጅግ ኃያል ተደርጎ ይቆጠር የነበረው የባቢሎን ጦር ሠራዊት በዓይን ከማይታዩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው የይሖዋ መላእክት ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር የሚገባ አይደለም።

የጭካኔ ድርጊት የሚያስከትለው መዘዝ

8. ባቢሎን ‘ጨለማ ውስጥ መግባቷ’ ምን ያመለክታል?

8 ይሖዋ በባቢሎን ላይ ትንቢታዊ ውግዘት መሰንዘሩን ቀጠለ:- “የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ:- የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ።” (ኢሳይያስ 47:5) ባቢሎን ጨለማና ጭጋግ ይውጣታል። ከዚህ በኋላ እንደ ጨካኝ እመቤት በሌሎች መንግሥታት ላይ መሰልጠን አትችልም።​—⁠ኢሳይያስ 14:​4

9. ይሖዋ በአይሁዳውያን ላይ የተቆጣው ለምንድን ነው?

9 ባቢሎን መጀመሪያውኑ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጉዳት እንድታደርስ የተፈቀደላት ለምንድን ነው? ይሖዋ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር ርስቴንም አረከስሁ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው።” (ኢሳይያስ 47:​6ሀ) ይሖዋ በአይሁዳውያን ላይ መቆጣቱ ተገቢ ነበር። ሕጉን ካላከበሩ ከምድሪቱ የመፈናቀል ዕጣ እንደሚገጥማቸው አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል። (ዘዳግም 28:​64) ሕጉን በመተላለፍ ጣዖት ማምለክና የፆታ ብልግና መፈጸም ሲጀምሩ ይሖዋ በፍቅር በመገፋፋት ወደ ንጹሕ አምልኮ እንዲመልሷቸው ነቢያቱን ይልክ ነበር። “እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 36:16) በዚህ ምክንያት አምላክ ባቢሎናውያን ምድሪቱን በወረሩና ቅዱስ ቤተ መቅደሱን ባጎደፉ ጊዜ ርስቱ የሆነችው ይሁዳ እንድትረክስ ፈቅዷል።​—⁠መዝሙር 79:​1፤ ሕዝቅኤል 24:​21

10, 11. ይሖዋ ባቢሎን ሕዝቡን ድል አድርጋ እንድትይዝ የፈቀደ ቢሆንም እንኳ በፈጸመችው ድርጊት የተቆጣው ለምንድን ነው?

10 ከዚህ አንጻር ሲታይ ባቢሎን አይሁዳውያንን በባርነት መግዛቷ የአምላክን ፈቃድ እንደመፈጸም ተደርጎ ሊቆጠር አይችልምን? በፍጹም! አምላክ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፣ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል። አንቺም:- እኔ ለዘላለም እመቤት እሆናለሁ ብለሻል፤ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም።” (ኢሳይያስ 47:6ለ, 7) አምላክ፣ ባቢሎን ‘ለሽማግሌዎቹ’ እንኳን ሳትራራ ከልክ ያለፈ የጭካኔ ድርጊት እንድትፈጽምባቸው አላዘዘም። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 4:​16፤ 5:​12) በተጨማሪም በማረኳቸው አይሁዳውያን ላይ በማላገጥ በእነሱ ሥቃይ እንዲደሰቱ የማድረግ ዓላማም አልነበረውም።​—⁠መዝሙር 137:​3

11 ባቢሎን አይሁዳውያንን በግዞት ማቆየት የምትችለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆኑን ዘንግታ ነበር። ኢሳይያስ ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ እንደሚያወጣ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብላለች። አይሁዳውያንን ለዘላለም የመግዛት መብት እንዳገኘችና ቅኝ ግዛቶቿ በሆኑት አገሮች ላይ ለዘላለም እመቤት ሆና እንደምትኖር ተሰምቷት ነበር። ጨቋኝ አገዛዟ ‘የሚያከትምበት’ ጊዜ እንደሚመጣ የተነገረውን ቃል ሳታስተውል ቀርታለች።

ባቢሎን እንደምትወድቅ ተተነበየ

12. ባቢሎን “ቅምጥል” ተብላ የተጠራችው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ እንዲህ ሲል አስታወቀ:- “አሁንም አንቺ ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጪ፣ በልብሽም:- እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ መበለትም ሆኜ አልኖርም የወላድ መካንነትንም አላውቅም የምትዪ ይህን ስሚ።” (ኢሳይያስ 47:8) ባቢሎናውያን ለሥጋዊ ምኞቶቻቸው ያደሩ ቅምጥሎች ነበሩ። በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ታሪክ ጸሐፊው ሂሮዶተስ ባቢሎናውያን “እጅግ አሳፋሪ የሆነ ልማድ” እንደነበራቸው ገልጿል። ሁሉም ሴቶች ለፍቅር የሴት አምላካቸው ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ዝሙት መፈጸም ይጠበቅባቸው ነበር። በተመሳሳይም ጥንታዊው ታሪክ ጸሐፊ ኩርቲየስ እንዲህ ብሏል:- “የከተማይቱ የሥነ ምግባር ደረጃ በእጅጉ ያዘቀጠ ነበር። በዚያ የነበረውን ያህል ወራዳ ለሆነ የብልግና ድርጊት የሚጋብዝና የሚያነሳሳ ብልሹ ሥርዓት የለም።”

13. ባቢሎን ለሥጋዊ ነገሮች ያደረች መሆኗ ውድቀቷን የሚያፋጥነው እንዴት ነው?

13 ባቢሎን ለሥጋዊ ነገሮች ያደረች መሆኗ ውድቀቷን ይበልጥ ያፋጥነዋል። በውድቀቷ ዋዜማ ንጉሷና መኳንንቱ በታላቅ ድግስ በመታደም አቅላቸውን እስኪስቱ ይጠጣሉ። በመሆኑም የሜዶ ፋርስ ሠራዊት ከተማይቱን ሲወርር አንዳች የሚያውቁት ነገር አይኖርም። (ዳንኤል 5:​1-4) ባቢሎን የማይደፈሩ የሚመስሉት ግንቦቿና በከ​ተማይቱ ዙሪያ ያለው ውኃ ከወራሪ ኃይል እንደሚጠብቋት በመ​ተማመን ‘ተዘልላ ትቀመጣለች።’ በልቧም ሥልጣኗን ሊወስድ የሚችል ‘እንደሌለ’ አድርጋ ታስባለች። ንጉሠ ነገሥቷንም ሆነ ‘ልጆችዋን’ ወይም ሕዝቧን በማጣት “መበለት” ልትሆን እንደምትችል አይታያትም። ይሁን እንጂ ከይሖዋ አምላክ የበቀል እርምጃ ሊያድናት የሚችል ግንብ ሊኖር አይችልም! ይሖዋ ቆየት ብሎ “ባቢሎን ምንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፣ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጸና፣ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል” ሲል ተናግሯል።​—⁠ኤርምያስ 51:53

14. ባቢሎን ‘የወላድ መካንና መበለት’ የምትሆነው በምን መንገዶች ነው?

14 ባቢሎን ምን ይደርስባታል? ይሖዋ በመቀጠል እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች፣ የወላድ መካንነትና መበለትነት፣ በድንገት ይመጡብሻል፤ ስለ መተቶችሽ ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል።” (ኢሳይያስ 47:9) አዎን፣ ባቢሎን በዓለም ላይ የተቆናጠጠችውን ታላቅ ሥልጣን በድንገት ታጣለች። በጥንቶቹ ምሥራቃውያን አገሮች መበለትና የወላድ መካን የሆነች ሴት ከሁሉ የከፋ መቅሰፍት እንደደረሰባት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ባቢሎን በወደቀችበት ሌሊት ምን ያህል ‘ልጆች’ እንዳጣች የምናውቀው ነገር የለም። * ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ከተማዋ ከናካቴው ሰው አልባ እንደምትሆን ተተንብዮ ነበር። (ኤርምያስ 51:​29) በተጨማሪም ነገሥታቷ ከዙፋን የሚወርዱ በመሆኑ መበለት ትሆናለች።

15. ባቢሎን በአይሁዳውያን ላይ ከፈጸመችው ግፍ በተጨማሪ ይሖዋን ያስቆጣው ነገር ምንድን ነው?

15 ይሁን እንጂ ይሖዋ በባቢሎን ላይ የተቆጣው በአይሁዳውያን ላይ በፈጸመችው ግፍ ብቻ አይደለም። ‘የመተትዋ ብዛትም’ አስቆጥቶታል። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ መናፍስታዊ እምነቶችን የሚያወግዝ ቢሆንም ባቢሎን በአስማት ድርጊቶች የተሞላች ነበረች። (ዘዳግም 18:​10–12፤ ሕዝቅኤል 21:​21) ሶሻል ላይፍ አማንግ ዚ አሲሪያንስ ኤንድ ባቢሎኒያንስ የተባለው መጽሐፍ ባቢሎናውያን “ሥፍር ቁጥር በሌላቸው አጋንንት እንደተከበቡ አድርገው በማሰብ በከፍተኛ ፍርሃት ተውጠው ይኖሩ” እንደነበረ ይገልጻል።

በክፋት መታመን

16, 17. (ሀ) ባቢሎን ‘በክፋቷ የምትታመነው’ እንዴት ነው? (ለ) በባቢሎን ላይ የሚደርሰው ጥፋት ሊቀለበስ የማይችለው ለምንድን ነው?

16 የባቢሎን መጽሐፍ ገላጮች ከጥፋት ይታደጓት ይሆን? ይሖዋ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል:- “በክፋትሽ ታምነሻል፤ የሚያየኝ የለም ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፣ በልብሽም:- እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል።” (ኢሳይያስ 47:10) ባቢሎን በዓለማዊና በሃይማኖታዊ ጥበቧ፣ በወታደራዊ ኃይሏና በረቀቀ አረመኔያዊ ድርጊቷ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆና መዝለቅ እንደምትችል አድርጋ ታስባለች። በእሷ አስተሳሰብ ማንም ‘አያያትም’ ወይም ለምትፈጽማቸው የክፋት ድርጊቶች ተጠያቂ የሚያደርጋት የለም። በተጨማሪም ሥልጣኗን ሊቀናቀን የሚችል ኃይል እንዳለ ሆኖ አይሰማትም። በልብዋ “እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ትላለች።

17 ይሁን እንጂ ይሖዋ በሌላው ነቢይ በኩል “ሰው በስውር ቢሸሸግ፣ እኔ አላየውምን?” ሲል አስጠንቅቋል። (ኤርምያስ 23:​24፤ ዕብራውያን 4:​13) በመሆኑም ይሖዋ የሚከተለውን መግለጫ ሰጠ:- “ስለዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፣ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤ ጉዳት ይወድቅብሻል ታስወግጅውም ዘንድ አይቻልሽም፤ የማታውቂያትም ጉስቁልና ድንገት ትመጣብሻለች።” (ኢሳይያስ 47:11) የባቢሎን ጠንቋዮች የሚፈጽሙት ‘ምዋርትም’ ሆነ አማልክቷ በከተማይቱ ላይ የሚመጣውን በታሪኳ ታይቶ የማያውቅ ክፉ ነገር ሊቀለብሱ አይችሉም!

የባቢሎን አማካሪዎች አይሳካላቸውም

18, 19. ባቢሎን በአማካሪዎቿ መታመኗ አስከፊ ውድቀት የሚያስከትልባት እንዴት ነው?

18 ይሖዋ ወጋ በሚያደርግ የምጸት አነጋገር የሚከተለውን ትእዛዝ አስተላለፈ:- “ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደ ሆነ፣ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ።” (ኢሳይያስ 47:12) ባቢሎን ባለችበት ‘እንድትቆም’ ወይም ምንም ለውጥ ሳታደርግ በአስማቷ እንደታመነች እንድትቀጥል ታዝዛለች። በብሔር ደረጃ ‘ከሕፃንነቷ’ ጀምሮ አስማታዊ ድርጊቶች እንዲስፋፉ ብዙ ደክማለች።

19 ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ሲል ያላግጥባታል:- “በምክርሽ [“በአማካሪዎችሽ፣” NW ] ብዛት ደክመሻል፤ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፣ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፣ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ።” (ኢሳይያስ 47:13) * ባቢሎን አማካሪዎቿ ለውድቀት ይዳርጓታል። እርግጥ ነው፣ ባቢሎናውያን ለብዙ መቶ ዘመናት በከዋክብት ላይ ያካሄዱት ጥናት የኮከብ ቆጠራ ትንበያ እንዲፈለሰፍ አድርጓል። ሆኖም ባቢሎን በምትወድቅበት ሌሊት ኮከብ ቆጣሪዎቹ የሚደርስባቸው አሳዛኝ ሽንፈት ጥንቆላ ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጥ ይሆናል።​—⁠ዳንኤል 5:​7, 8

20. የባቢሎን አማካሪዎች ምን ይደርስባቸዋል?

20 ይሖዋ ይህን የትንቢቱን ክፍል እንዲህ ሲል ይደመድማል:- “እነሆ፣ እንደ እብቅ ይሆናሉ፣ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፤ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፍም፣ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ያለ አይደለም። የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፣ የሚያድንሽም የለም።” (ኢሳይያስ 47:14, 15) አዎን፣ የባቢሎን ሐሰተኛ አማካሪዎች እሳት ይጠብቃቸዋል። ይህ እሳት ሰዎች ለመሞቅ የሚጠቀሙበት ፍም ሳይሆን የባቢሎንን ሐሰተኛ አማካሪዎች ለምንም እንደማይጠቅም እብቅ የሚያደርግ አጥፊና አውዳሚ የሆነ እሳት ነው። እንግዲያው የባቢሎን አማካሪዎች ተደናግጠው መሸሻቸው ምንም አያስደንቅም! ባቢሎን ትተማመንባቸው የነበሩ ሁሉ ጥለዋት ስለሚሄዱ የሚያድናት አይኖርም። በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሰችው መከራ በእሷም ላይ ይደርሳል።​—⁠ኤርምያስ 11:​12

21. የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት እውነተኛ መሆናቸው የተረጋገጠው መቼና እንዴት ነው?

21 እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት በ539 ከዘአበ መፈጸም ጀመሩ። በቂሮስ የሚመራው የሜዶንና የፋርስ ሠራዊት ከተማይቱን ተቆጣጠረና የባቢሎንን ንጉሥ ብልጣሶርን ገደለ። (ዳንኤል 5:​1-4, 30) ባቢሎን በዓለም ላይ የነበራትን ሥልጣን በአንድ ሌሊት አጣች። በዚህ መንገድ ለብዙ መቶ ዘመናት የዘለቀው የሴማውያን የበላይነት አበቃና ዓለም በአሪያን ቁጥጥር ሥር ወደቀ። ባቢሎን በዘመናት ሂደት እየቆረቆዘች በመሄድ በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ “የድንጋይ ቁልል” ሆና ቀርታለች። (ኤርምያስ 51:​37) በመሆኑም የኢሳይያስ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን አግኝቷል።

ዘመናዊቷ ባቢሎን

22. በባቢሎን ላይ የደረሰው ውድቀት ኩራትን በተመለከተ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

22 የኢሳይያስ ትንቢት ቆም ብለን ልናስብባቸው የሚገቡ በርካታ ትምህርቶች ይዟል። በመጀመሪያ ደረጃ ኩራትና እብሪት የሚያስከትለውን አደጋ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በኩሩዋ ባቢሎን ላይ የደረሰው ውድቀት “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 16:18) ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ጊዜ ኩራት ሊያሸንፈን ቢችልም ‘በትዕቢት የተነፉ’ መሆን “በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድ” እንድንወድቅ ሊያደርገን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:​6, 7) እንግዲያው “በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል” የሚለውን የያዕቆብ ምክር መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ያዕቆብ 4:10

23. የኢሳይያስ ትንቢት ምን ዓይነት እምነት እንዲያድርብን ይረዳናል?

23 በተጨማሪም እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ከተቃዋሚዎቹ ሁሉ የላቀ ኃይል ባለው በይሖዋ እንድንተማመን ያደርጉናል። (መዝሙር 24:​8፤ 34:​7፤ 50:​15፤ 91:​14, 15) ይህ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት እጅግ የሚያጽናና ማሳሰቢያ ነው። በይሖዋ መተማመናችን “[ንጹሕ] ሰው ተስፋ” እንዳለው በመገንዘብ በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነን ለመኖር የወሰድነውን ቁርጥ አቋም ያጠናክርልናል። (መዝሙር 37:​37, 38 አ.መ.ት ) የሰይጣንን “አታላይ ዘዴዎች” በራሳችን ጥበብና ችሎታ ለመወጣት ከመሞከር ይልቅ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጣራችን እጅግ የተሻለ ነው።​—⁠ኤፌሶን 6:​10-13 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

24, 25. (ሀ) ኮከብ ቆጠራ መሠረተ ቢስ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ሆኖም ብዙዎች በኮከብ ቆጠራ የሚያምኑት ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች አጉል እምነቶችን የማይከተሉት ለምንድን ነው?

24 ከዚህም ሌላ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች በተለይም ደግሞ ከኮከብ ቆጠራ እንድንጠበቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። (ገላትያ 5:​20, 21) ባቢሎን ብትወድቅም ኮከብ ቆጠራ በሰዎች ዘንድ ያለውን ተቀባይነት አላጣም። ግሬት ሲቲስ ኦቭ ዚ ኤንሸንት ወርልድ የተባለው መጽሐፍ ባቢሎናውያን በካርታ ከፋፍለው ያስቀመጧቸው ሕብረ ከዋክብት የቀድሞ ቦታቸው “የተለወጠ” መሆኑ “[የኮከብ ቆጠራ] ጽንሰ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ከንቱ” እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲል ገልጿል። ያም ሆኖ ኮከብ ቆጠራ በእጅጉ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ብዙ ጋዜጦች የሆሮስኮፕ አምዶችን ይዘው ይወጣሉ።

25 የተማሩ ሰዎች ሳይቀሩ የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎችን የሚከታተሉት ወይም ደግሞ ተጨባጭ ማስረጃ በሌላቸውና በአጉል እምነት ላይ በተመሠረቱ ልማዶች የሚካፈሉት ለምንድን ነው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች እርስ በርስ መተማመን እስካልቻሉና ስለወደፊቱ ጊዜ መጨነቃቸውን እስካልተዉ ድረስ አጉል እምነቶች ይወገዳሉ ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል።” ሰዎች ስጋት ካለባቸውና ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚጨነቁ ከሆነ ለአጉል እምነቶች ሊገዙ ይችላሉ። ክርስቲያኖች ግን አጉል እምነቶችን አይከተሉም። በይሖዋ ስለሚመኩ ሰውን አይፈሩም። (መዝሙር 6:​4-10) ስለወደፊቱ ጊዜም አይጨነቁም። ይሖዋ በመንፈሱ የገለጣቸውን ዓላማዎች የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ ‘የይሖዋ ምክር ለዘላለም እንደሚኖር’ እርግጠኞች ናቸው። (መዝሙር 33:​11) ከይሖዋ ምክር ጋር ተስማምተን መኖራችን አስደሳችና ዘላቂ የሆነ ሕይወት ያስገኝልናል።

26. ‘የጥበበኞች አሳብ ከንቱ’ መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?

26 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንዶች ይበልጥ “ሳይንሳዊ” በሆነ መንገድ ስለወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። እንዲያውም ፊውቸሮሎጂ የሚባል የጥናት መስክ የተከፈተ ሲሆን ይህም “ባሉት ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ ወደፊት ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች ለመተንበይ የሚደረግ ምርምር” ነው። ለምሳሌ ያህል በ1972 የሮም ክለብ በመባል የሚታወቅ ምሁራንንና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን በመላው ዓለም የሚገኘው የወርቅ፣ የሜርኩሪ፣ የዚንክና የነዳጅ ዘይት ክምችት በ1992 እንደሚሟጠጥ ተንብዮ ነበር። ከ1972 ወዲህ በዓለማችን ላይ የተለያዩ አስከፊ ችግሮች የደረሱ ቢሆንም ይህ ትንበያ ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል። ምድር አሁንም ድረስ የወርቅ፣ የሜርኩሪ፣ የዚንክና የነዳጅ ዘይት ክምችት አላት። የሰው ልጅ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ብዙ ቢደክምም መላ ምቶቹ ሁሉ አስተማማኝ ሊሆኑ አልቻሉም። በእርግጥም ‘የጥበበኞች አሳብ ከንቱ ነው!’​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​20

በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚመጣው ጥፋት

27. ታላቂቱ ባቢሎን በ539 ከዘአበ በባቢሎን ላይ የደረሰው ዓይነት ውድቀት የደረሰባት መቼ ነው? በምንስ መንገድ?

27 በዘመናችን ያሉት ሃይማኖቶች የሚከተሏቸው ብዙዎቹ ትምህርቶች በጥንቷ ባቢሎን የነበሩ ናቸው። በመሆኑም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ መጠራቷ ተገቢ ነው። (ራእይ 17:​5) በርካታ የእምነት ተቋማትን ያቀፈችው ይህች የሃይማኖት ድርጅት በ539 ከዘአበ በጥንቷ ባቢሎን ላይ የደረሰው ዓይነት ውድቀት ደርሶባታል። (ራእይ 14:​8፤ 18:​2) በ1919 ቀሪዎቹ የክርስቶስ ወንድሞች ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ በመውጣት የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ አካል ከሆነችው ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ተላቅቀዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሕዝበ ክርስትና ከፍተኛ ተጽዕኖ ታሳድርባቸው በነበሩ በርካታ አገሮች የነበራትን ተሰሚነት በእጅጉ አጥታለች።

28. ባቢሎን ምን በማለት ትኩራራለች? ሆኖም ምን ይደርስባታል?

28 ይሁን እንጂ ይህ ውድቀት ወደፊት በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚመጣውን ታላቅ ጥፋት የሚያመላክት ነበር። የራእይ መጽሐፍ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚደርሰውን ጥፋት አስመልክቶ የሚናገረው ትንቢት በ⁠ኢሳይያስ 47:​8, 9 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ትንቢታዊ ቃላት ያስታውሰናል። እንደ ጥንቷ ባቢሎን ሁሉ ዘመናዊቷ ታላቂቱ ባቢሎንም “ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንንም ከቶ አላይም” ትላለች። ይሁን እንጂ “በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጣሉ፣ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ስለዚህ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 47 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት አሁንም በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ላሉ ሰዎች ትልቅ ማስጠንቀቂያ ይሆናሉ። በእሷ ላይ የሚመጣው ጥፋት በእነርሱም ላይ እንዳይደርስ “ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚለውን መለኮታዊ ትእዛዝ መከተል ይኖርባቸዋል።​—⁠ራእይ 18:​4, 7, 8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 የሐሰት ሃይማኖቶች እንዴት እየተስፋፉ እንደመጡ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

^ አን.3 በዕብራይስጥ “ድንግል የባቢሎን ልጅ” የሚለው አገላለጽ ፈሊጣዊ አነጋገር ሲሆን ባቢሎንን ወይም የባቢሎንን ነዋሪዎች ያመለክታል። ባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ አገሪቷን መበዝበዝ የቻለ አንድም የጠላት ኃይል ባለመኖሩ “ድንግል” ነበረች።

^ አን.6 ምሁራን “ለማንም አልራራም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ አገላለጽ ለመተርጎም “እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሐረግ” እንደሆነ ይናገራሉ። “አልራራም” የሚለው ቃል የገባው ይሖዋ ባቢሎንን እንዳያጠፋ ማንም ሰው ቢለምነው የማይሰማ መሆኑን ለማመልከት ነው። የአይሁድ የኅትመት ማኅበር ያዘጋጀው ትርጉም ይህን ሐረግ “ማንም ሰው ጣልቃ ገብቶ እንዲማልድ . . . አልሻም” ሲል ተርጉሞታል።

^ አን.14 በሬይመንድ ፊሊፕ ዶውረቲ የተዘጋጀው ናቦኒደስ ኤንድ ቤልሻዘር የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው የናቦኒደስ ዜና መዋዕል ባቢሎንን የወረረው ሠራዊት “ያላንዳች ውጊያ” ወደከተማይቱ እንደዘለቀ ቢናገርም ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዜኖፎን ግን ከፍተኛ የሆነ እልቂት ደርሶ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።

^ አን.19 አንዳንዶች “የሰማይን ከዋክብት የሚቆጥሩ” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ሐረግ “ሰማያትን የሚከፋፍሉ” በማለት ተርጉመውታል። ይህ አገላለጽ ሰማያትን በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል ስለወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን የኮከብ ቆጠራ ትንበያ የሚያመለክት ነው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ደግሞ ይህን ሐረግ “ሰማያትን የሚያመልኩ” ሲል ተርጉሞታል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 111 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ቅምጥሏ ባቢሎን ትቢያ ላይ ትጣላለች

[በገጽ 114 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የባቢሎን ኮከብ ቆጣሪዎች የሚደርስባትን ውድቀት መተንበይ አይችሉም

[በገጽ 116 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው ሺህ ዓመት ከዘአበ ባቢሎናውያን ለኮከብ ቆጠራ ይጠቀሙበት የነበረ ቀን መቁጠሪያ

[በገጽ 119 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዘመናዊቷ ባቢሎን በቅርቡ ትጠፋለች