በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በአንድነት ዘምሩ!’

‘በአንድነት ዘምሩ!’

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

‘በአንድነት ዘምሩ!’

ኢሳይያስ 52:​1-12

1. በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 52 ላይ የሰፈሩት ትንቢታዊ ቃላት አስደሳች የሆኑት ለምንድን ነው? ሁለት ዓይነት ፍጻሜ አላቸው የምንለውስ ለምንድን ነው?

በግዞት የሚኖሩ ሰዎችን ነፃ ከመውጣት የበለጠ ሊያስደስታቸው የሚችል ምን ነገር ይኖራል? የኢሳይያስ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ነፃነት እንደሚያገኙና ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ በስፋት የሚያወሳ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመዝሙረ ዳዊት ቀጥሎ በርካታ የደስታ መግለጫዎች የሚገኙበት መጽሐፍ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። በተለይ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 52 ላይ የሰፈረው መልእክት የአምላክን ሕዝቦች በእጅጉ የሚያስደስት ነው። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት በ537 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ በእናትና በሚስት ተመስላ በተገለጸችውና መንፈሳዊ ፍጥረታትን ባቀፈችው የይሖዋ ሰማያዊት ድርጅት ማለትም በ“ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ላይ የላቀ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።​—⁠ገላትያ 4:​26፤ ራእይ 12:​1

‘ጽዮን ሆይ፣ ኃይልሽን ልበሺ!’

2. ጽዮን የምትነሳው መቼ ነው? ይህ የሚፈጸመውስ እንዴት ነው?

2 ይሖዋ እጅግ ለሚወድዳት የጽዮን ከተማ በኢሳይያስ በኩል የሚከተለውን ጥሪ አሰማ:- “ጽዮን ሆይ፣ ተነሺ፣ ተነሺ፣ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ። ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፣ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ የአንገትሽን እስራት ፍቺ።” (ኢሳይያስ 52:1, 2) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ይሖዋን በማስቆጣታቸው ከተማይቱ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና ቆይታለች። (2 ነገሥት 24:​4፤ 2 ዜና መዋዕል 36:​15–21፤ ኤርምያስ 25:​8-11፤ ዳንኤል 9:​2) አሁን ግን በድን ሆና የቆየችበት ረጅም ዘመን አብቅቶ የምትነሳበትና ጌጠኛውን የነፃነት ልብሷን የምትጎናጸፍበት ጊዜ ደርሷል። ይሖዋ የኢየሩሳሌም የቀድሞ ነዋሪዎችና ልጆቻቸው ባቢሎንን ለቅቀው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እውነተኛውን አምልኮ ማቋቋም እንዲችሉ ‘ምርኮኛይቱን የጽዮን ልጅ’ ነፃ እንዲያወጣ የቂሮስን ልብ አነሳስቷል። ያልተገረዘና ርኩስ የሆነ ሰው በኢየሩሳሌም መገኘት የለበትም።​—⁠ዕዝራ 1:​1-4

3. የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ “የጽዮን ልጅ” ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? ነፃ የወጡትስ በምን መንገድ ነው?

3 ኢሳይያስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በክርስቲያን ጉባኤ ላይም ተፈጻሚነት አላቸው። “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” እናታቸው እንደመሆኗ መጠን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ዘመናዊው “የጽዮን ልጅ” እንደሆነ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። * ከአረማውያንና ከከሃዲዎች ትምህርት የተላቀቁት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሥጋ በመገረዝ ሳይሆን ልባቸውን በመገረዝ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ይዘው መኖር አለባቸው። (ኤርምያስ 31:​33፤ ሮሜ 2:​25-29) ይህም በይሖዋ ፊት መንፈሳዊ፣ አእምሯዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ይጠይቃል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 7:​19፤ ኤፌሶን 2:​3

4. “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” በይሖዋ ላይ ዓምፃ ባታውቅም እንኳ በምድር ያሉት ወኪሎቿ በጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ ከደረሰው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ምን ነገር ደርሶባቸዋል?

4 እርግጥ ነው፣ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” በይሖዋ ላይ ዓምፃ አታውቅም። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት በምድር ላይ ያሉት ወኪሎቿ ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች እውነተኛ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ምን ማድረግ እንደሚጠይቅ በትክክል ባለመገንዘባቸው የይሖዋን ሕግ ጥሰው ነበር። ከዚህም የተነሳ መለኮታዊ ሞገስ በማጣታቸው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ መንፈሳዊ የባርነት ቀንበር ሥር ወደቁ። (ራእይ 17:​5) ይባስ ብሎ ደግሞ ሰኔ 1918 ስምንት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አባላት ሴራ ጠንስሳችኋል የሚለውን ውንጀላ ጨምሮ የተለያዩ የሐሰት ክሶች ቀርበውባቸው ወኅኒ ወረዱ። በዚህ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ ይካሄድ የነበረው የምሥራቹ ስብከት ሥራ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ በ1919 ከመንፈሳዊ እንቅልፍ እንዲነቁ የሚያሳስብ ቀስቃሽ ጥሪ ቀረበ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ርኩሰት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ማንጻት ጀመሩ። ከግዞት ተላቅቀው ከትቢያ በመነሳታቸው “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” መንፈሳዊ ርኩሰት ከቶ የማይገኝባት ‘ቅድስት ከተማ’ ሊኖራት የሚገባውን ግርማና ውበት ልትላበስ ችላለች።

5. ይሖዋ ሕዝቡን ለያዟቸው ሰዎች ካሳ ሳይከፍል የመቤዠት መብት አለው የምንለው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ በ537 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊትም ሆነ በ1919 እዘአ ሕዝቡን ነፃ የማውጣት ሙሉ መብት ነበረው። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፣ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ።” (ኢሳይያስ 52:3) የጥንቷ ባቢሎንም ሆነች ታላቂቱ ባቢሎን የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ ባሪያ አድርገው ሲወስዱ የከፈሉት ነገር የለም። ሕዝቡን በገንዘብ ተዋውለው ስላልወሰዷቸው ሕጋዊው ባለቤት ይሖዋ ነው። ዕዳ እንዳለበት ሆኖ ሊሰማው ይገባልን? በጭራሽ። የጥንቶቹንም ሆነ ዘመናዊዎቹን ሕዝቦቹን ለያዟቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ካሳ ሳይከፍል አገልጋዮቹን መቤዠት ይችላል።​—⁠ኢሳይያስ 45:​13

6. የይሖዋ ጠላቶች ከታሪክ ሳይማሩ የቀሩት ነገር ምንድን ነው?

6 የይሖዋ ጠላቶች ከታሪክ ሊማሩ ይገባቸው ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፣ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው።” (ኢሳይያስ 52:4) የግብጹ ፈርዖን በአገሩ በእንግድነት እንዲቀመጡ ግብዣ ቀርቦላቸው የመጡትን እስራኤላውያን ባሪያ አድርጎ ገዝቷቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ውስጥ አሰጠማቸው። (ዘጸአት 1:​11-14፤ 14:​27, 28) የአሦሩ ንጉሥ ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ በዛተ ጊዜ የይሖዋ መልአክ የንጉሡን 185,000 ወታደሮች ገድሏቸዋል። (ኢሳይያስ 37:​33-​37) በተመሳሳይ የጥንቷ ባቢሎንም ሆነች ታላቂቱ ባቢሎን በአ​ምላክ ሕዝቦች ላይ ግፍ በመ​ፈጸማቸው ከቅጣት ሊያ​መልጡ አይችሉም።

“ወገኔ ስሜን ያውቃል”

7. የይሖዋ ሕዝቦች ተማርከው መወሰዳቸው በይሖዋ ስም ላይ ምን አስከትሏል?

7 ትንቢቱ እንደሚያመለክተው የይሖዋ ሕዝቦች በግዞት መኖራቸው በይሖዋ ስም ላይ የሚያስከትለው ነገር አለ:- “ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ስሜም ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ይሰደባል። ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፣ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፤ እነሆ፣ እኔ ነኝ።” (ኢሳይያስ 52:​5, 6) ይህ ሁኔታ ይሖዋን የሚመለከተው እንዴት ነው? እስራኤል በባቢሎን የባርነት ቀንበር ሥር መውደቋ እሱን ለምን ያሳስበዋል? ባቢሎን ሕዝቡን ማርካ በመውሰድ በእስራኤላውያን ላይ በድል አድራጊነት ስሜት በመፈንጠዟ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። እንዲህ ያለው ዕብሪት ባቢሎን የይሖዋን ስም እንድታቃልል አድርጓታል። (ሕዝቅኤል 36:​20, 21) ባቢሎን ኢየሩሳሌም ባድማ ልትሆን የቻለችው ይሖዋ በሕዝቡ ድርጊት በማዘኑ ምክንያት እንደሆነ ሳታስተውል ቀርታለች። ከዚህ ይልቅ አይሁዳውያን በባርነት ቀንበር ሥር ሊወድቁ የቻሉት አምላካቸው እነሱን ማዳን ስለተሳነው እንደሆነ አድርጋ አስባለች። እንዲያውም የባቢሎን ምክትል ገዥ የነበረው ብልጣሶር ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን ዕቃዎች ለባቢሎን አማልክት ክብር ባዘጋጀው ግብዣ ላይ በመጠቀም በይሖዋ ላይ ተሳልቋል።​—⁠ዳንኤል 5:​1-4

8. ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በይሖዋ ስም ላይ ምን ተፈጽሟል?

8 ይህ ‘በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው? የክህደት ትምህርት ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ‘በእነዚህ ሰዎች ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል እየተሰደበ ነው።’ (ሮሜ 2:​24፤ ሥራ 20:​29, 30) ለምሳሌ ያህል አይሁዳውያን ያዳበሩት አጉል እምነት ውሎ አድሮ በመለኮታዊው ስም መጠቀም እንዲተዉ አድርጓቸዋል። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሃዲ ክርስቲያኖች የእነዚህን አይሁዳውያን ፈለግ በመከተል በአምላክ የግል ስም መጠቀም አቆሙ። ይህ ሃይማኖታዊ ክህደት ከጊዜ በኋላ የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና እንድትቋቋም በር ከፍቷል። (2 ተሰሎንቄ 2:​3, 7፤ ራእይ 17:​5) ሕዝበ ክርስትና የምትፈጽመው መረን የለቀቀ የጾታ ብልግናና ዓይን ያወጣ የደም አፍሳሽነት ተግባር የይሖዋን ስም አሰድቧል።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​1, 2

9, 10. በዘመናችን ያሉት የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ይሖዋ የሚጠይቃቸውን ብቃቶችና ስሙን በተመለከተ ምን ጠለቅ ያለ ግንዛቤ አግኝተዋል?

9 ታላቁ ቂሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ በ1919 የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ነፃ ባወጣበት ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ ምን ዓይነት ብቃት እንደሚጠብቅባቸው ይበልጥ ተገነዘቡ። ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ አረማውያን ያምኑባቸው የነበሩትን እንደ ሥላሴ፣ ነፍስ አትሞትም እንዲሁም በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም ትሰቃያለች የሚሉትን የመሳሰሉ በርካታ የሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች ቀደም ሲል አስወግደው ነበር። ከግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ደግሞ የቀሩትን የባቢሎን እምነት ርዝራዦች ጠራርገው ለማስወገድ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ። በተጨማሪም ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት ተገነዘቡ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ምሥክሮች ፈጽመውት ሊሆን ከሚችል ከማንኛውም በደም ባለዕዳነት ከሚያስጠይቅ ድርጊት ራሳቸውን ለማንጻት እርምጃ ወስደዋል።

10 ከዚህም ሌላ በዘመናችን ያሉት የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ ስም የመጠቀምን አስፈላጊነት ይበልጥ በመገንዘባቸው ከ1931 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስያሜ መጠራት ጀመሩ። በዚህ መንገድ ይሖዋንና ስሙን የሚደግፉ መሆናቸውን በይፋ አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከ1950 አንስቶ ባዘጋጁት የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም አማካኝነት መለኮታዊውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀድሞ ወደነበረበት ትክክለኛ ቦታ መልሰዋል። በይሖዋ ስም የመጠቀምን አስፈላጊነት በመገንዘብ ስሙን እስከ ምድር ዳር ድረስ በማስታወቅ ላይ ናቸው።

“የምስራች የሚናገር”

11. በ537 ከዘአበ ከተከናወኑት ሁኔታዎች አንጻር “አምላክሽ ነግሦአል” መባሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

11 አሁን ትኩረታችንን ጽዮን ባድማ ወደነበረችበት ጊዜ መለስ እናድርግ። አንድ መልእክተኛ የምሥራች ይዞ ብቅ ይላል:- “የምስራች የሚናገር [“ይዞ የሚመጣ፣” NW ]፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም:- አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።” (ኢሳይያስ 52:7) በ537 ከዘአበ የጽዮን አምላክ ነገሠ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምንጊዜም ንጉሥ አይደለምን? አዎን፣ ይሖዋ “የዘመናት ንጉሥ” ነው! (ራእይ 15:​3 አ.መ.ት ) ይሁን እንጂ በባቢሎን ላይ የደረሰው ውድቀት እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ዳግመኛ እንዲገነባና ንጹሕ አምልኮ እንደገና እንዲቋቋም የወጣው ንጉሣዊ አዋጅ የይሖዋ ንግሥና አዲስ መገለጫ በመሆኑ “አምላክሽ ነግሦአል” መባሉ የተገባ ነው።​—⁠መዝሙር 97:​1

12. ‘የምስራች ይዞ በመምጣት’ ግንባር ቀደም የሆነው ማን ነው? እንዴትስ?

12 በኢሳይያስ ዘመን “የምስራች ይዞ የሚመጣ” ተብሎ ተለይቶ የተጠቀሰ ግለሰብ ወይም ቡድን አልነበረም። በዘመናችን ግን የምስራቹን የያዘው ማን እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል። ዋነኛው የይሖዋ የሰላም መልእክተኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምድር ላይ በኖረበት ዘመን የሰው ልጆች በሽታንና ሞትን ጨምሮ ከአዳም የወረሱት ኃጢአት ካስከተለባቸው ችግሮች በሙሉ የሚላቀቁበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸውን ምስራች ሰብኳል። (ማቴዎስ 9:​35) ኢየሱስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት በማስተማር ይህን የመልካም ወሬ ምስራች በቅንዓት በማወጅ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። (ማቴዎስ 5:​1, 2፤ ማርቆስ 6:​34፤ ሉቃስ 19:​1-10፤ ዮሐንስ 4:​5-26) ደቀ መዛሙርቱም የእሱን ምሳሌ ተከትለዋል።

13. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የምስራች ይዞ የሚመጣ እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው’ የሚለውን መግለጫ ሰፋ ያለ ትርጉም የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) የመልእክተኞቹ እግሮች “ያማሩ” ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

13 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ላይ ኢሳይያስ 52:​7ን በመጥቀስ የምስራቹ ስብከት ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ‘ሰዎች ያለ ሰባኪ እንዴት ይሰማሉ?’ የሚለውን ጥያቄ ጨምሮ አንባቢዎቹ ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ ተከታታይ ጥያቄዎችን አቅርቧል። አክሎም “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ [ተጽፏል]” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 10:14, 15) ጳውሎስ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ በነጠላ ቁጥር የተጠቀሰውን “ሰው” በብዙ ቁጥር በመተካት ኢሳይያስ 52:​7 ላይ የገባውን ቃል ሰፋ ያለ ትርጉም ሰጥቶታል። ሁሉም ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ የሰላሙ ምስራች መልእክተኞች ሆነው ያገለግላሉ። እግሮቻቸው “ያማሩ” የሆኑት እንዴት ነው? ኢሳይያስ የተናገረው መልእክተኛው በይሁዳ አቅራቢያ ካሉ ተራሮች ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ እንዳለ አድርጎ ነው። ከርቀት የመልእክተኛውን እግር ማየት የማይቻል ነገር ነው። እዚህ ላይ ኢሳይያስ በዋነኛነት መናገር የፈለገው ስለ እግሩ ሳይሆን ስለ መልእክተኛው ነው። እግሩ የሚወክለው ራሱን መልእክተኛውን ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ፊት ያማሩ እንደነበሩ ሁሉ በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮችም ሕይወት አድን የሆነውን ምስራች ሰምተው እርምጃ በሚወስዱ ትሑታን ሰዎች ፊት ያማሩ ናቸው።

14. በዘመናችን ይሖዋ የነገሠው እንዴት ነው? ይህ ለሰው ዘሮች መታወጅ የጀመረው ከመቼ አንስቶ ነው?

14 በዘመናችን “አምላክሽ ነግሦአል” የሚለው አዋጅ መሰማት የጀመረው ከመቼ አንስቶ ነው? ከ1919 ጀምሮ ነው። በዚያ ዓመት በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ “ለረዳት ሠራተኞች የቀረበ ጥሪ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር በማቅረብ የአድማጮቹን ስሜት ቀስቅሶ ነበር። በ⁠ኢሳይያስ 52:​7 እና በ⁠ራእይ 15:​2 ላይ የተመሠረተው ይህ ንግግር በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ አነሳስቷል። በዚህ መንገድ ‘ያማሩ እግሮች’ “በተራሮች” ላይ ብቅ ማለት ጀመሩ። በመጀመሪያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በኋላ ደግሞ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ አጋሮቻቸው ይሖዋ እንደነገሠ የሚገልጸውን ምስራች በቅንዓት ሲያውጁ ቆይተዋል። (ዮሐንስ 10:​16) ይሖዋ የነገሠው እንዴት ነው? በ1914 ባቋቋመው አዲስ ሰማያዊ መንግሥት ላይ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ በመሾም ንግሥናውን በአዲስ መልክ አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በ1919 ‘የአምላክ እስራኤልን’ ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ በማውጣት ንግሥናውን በሌላ መልክ ግልጽ አድርጓል።​—⁠ገላትያ 6:​16፤ መዝሙር 47:​8፤ ራእይ 11:​15, 17፤ 19:​6

“ጉበኞችሽ ጮኸዋል”

15. በ537 ከዘአበ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የጮኹት “ጉበኞች” እነማን ናቸው?

15 “አምላክሽ ነግሦአል” የሚለው አዋጅ በጎ ምላሽ አግኝቷልን? አዎን። የኢሳይያስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ ጉበኞችሽ ጮኸዋል፤ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፣ በአንድነትም ይዘምራሉ።” (ኢሳይያስ 52:8) በ537 ከዘአበ ከግዞት ነፃ የወጡትን የመጀመሪያዎቹን ተመላሾች ለመቀበል በኢየሩሳሌም ውስጥ ቃል በቃል በቦታቸው ላይ የተሰየሙ ጉበኞች አልነበሩም። ከተማይቱ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና ቆይታለች። (ኤርምያስ 25:​11, 12) ስለዚህ የሚጮኹት “ጉበኞች” ጽዮን ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ የምትመለስበት ጊዜ እንደደረሰ የሚያበስረውን ዜና ቀድመው የሚሰሙና ለተቀሩት የጽዮን ልጆች ዜናውን የሚያሰሙ እስራኤላውያን መሆን አለባቸው። እነዚህ ጉበኞች በ539 ከዘአበ ይሖዋ ባቢሎንን ለቂሮስ አሳልፎ ሲሰጥ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እንደሚያስተውሉ ጥርጥር የለውም። ጉበኞቹ ጥሪያቸውን ከሚቀበሉ የእስራኤል ልጆች ጋር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአንድነት በመዘመር ምስራቹን ለሌሎች ያሰማሉ።

16. ጉበኞቹ “ዓይን በዓይን” የሚያዩት ማንን ነው? ይህስ ምን ያመለክታል?

16 ንቁ የሆኑት ጉበኞች “ዓይን በዓይን” ወይም ፊት ለፊት የመተያየት ያህል ከይሖዋ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና ይመሠርታሉ። (ዘኍልቁ 14:​14) ከይሖዋ ጋርም ሆነ እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት በመካከላቸው አንድነት እንዳለና መልእክታቸው እጅግ አስደሳች መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:​10

17, 18. (ሀ) በዘመናችን ያለው ጉበኛ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማው እንዴት ነው? (ለ) የጉበኛው ክፍል በአንድነት ጥሪ ያሰማው በምን መንገድ ነው?

17 በትንቢቱ ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት የጉበኛው ክፍል ማለትም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚታየው የአምላክ ድርጅት ውስጥ ለሚገኙት ብቻ ሳይሆን በውጭ ላሉትም ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማል። (ማቴዎስ 24:​45-47) በ1919 ቀሪዎቹን የቅቡዓን ክርስቲያኖች አባላት ለመሰብሰብ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የቀረበው “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚለው ማሳሰቢያ ይህን ጥሪ ይበልጥ አጠናክሮታል። ከ1935 አንስቶ ደግሞ በግ መሰል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ተጀመረ። (ራእይ 7:​9, 10) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የይሖዋን ንግሥና የማስታወቁ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ተፋፍሟል። እንዴት? በ2000 ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የይሖዋን ንግሥና ከ230 በሚበልጡ አገሮችና የምድር ክፍሎች አውጀዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጉበኛው ክፍል ዋነኛ መሣሪያ የሆነው መጠበቂያ ግንብ ይህን አስደሳች መልእክት ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች በማስታወቅ ላይ ነው።

18 እንዲህ ባለው አንድነት የሚጠይቅ ሥራ ለመካፈል ትሕትናና የወንድማማች ፍቅር ማሳየት ያስፈልጋል። በዚህ ሥራ የሚካፈሉ ሰዎች በሙሉ የሚያሰሙት ጥሪ ውጤታማ እንዲሆን ስለ ይሖዋ ስም፣ በቤዛው አማካኝነት ስላደረገው ዝግጅት፣ ስለ ጥበቡ፣ ስለ ፍቅሩና ስለ መንግሥቱ በመናገር አንድ ዓይነት መልእክት መስበክ አለባቸው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲያገለግሉ ከይሖዋ ጋር ያላቸው የግል ዝምድና ምስራቹን በአንድነት ለመናገር በሚያስችል ሁኔታ ይጠናከራል።

19. (ሀ) “የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች” የሚደሰቱት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ‘የተቀደሰውን ክንዱን መግለጡ’ ምን ያመለክታል?

19 የአምላክ ሕዝቦች በደስታ ስለሚጮኹ የሚኖሩበት ሥፍራ ሳይቀር ሐሴት ያደርጋል። ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፣ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፣ በአንድነትም ዘምሩ። እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፣ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ።” (ኢሳይያስ 52:9, 10) እስራኤላውያን ከባቢሎን ሲመለሱ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ዳግመኛ ስለሚቋቋም ባድማ ሆና የልቅሶና የዋይታ ሥፍራ ትመስል የነበረችው ኢየሩሳሌም አስደሳች ገጽታ ትላበሳለች። (ኢሳይያስ 35:​1, 2) በእርግጥም ይህ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ግልጽ ነው። ሕዝቡን የማዳን እርምጃ ለመውሰድ በመዘጋጀት እጅጌውን የጠቀለለ ያህል ‘የተቀደሰውን ክንዱን ገልጧል።’​—⁠ዕዝራ 1:​2, 3

20. በዘመናችን ይሖዋ የተቀደሰውን ክንዱን በመግለጡ ምን ውጤት ተገኝቷል? ወደፊትስ ምን ይከናወናል?

20 አሁን ባለንበት ‘የመጨረሻ ቀን’ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ‘ሁለት ምሥክሮች’ ማለትም ቅቡዓን ቀሪዎች እንደገና ሕያው እንዲሆኑ ለማድረግ የተቀደሰውን ክንዱን ገልጧል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1፤ ራእይ 11:​3, 7-13) እነዚህ ቅቡዓን ቀሪዎች ከ1919 አንስቶ ወደ መንፈሳዊ ገነት የገቡ ሲሆን ይህም በአሁኑ ጊዜ አጋሮቻቸው ከሆኑት በሚልዮን የሚቆጠሩ የሌሎች በጎች አባላት ጋር ያሉበትን መንፈሳዊ ርስት ያመለክታል። በመጨረሻም ይሖዋ ‘በአርማጌዶን’ ሕዝቡን ለማዳን የተቀደሰውን ክንዱን ይገልጣል። (ራእይ 16:​14, 16) በዚያን ጊዜ “በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ።”

አጣዳፊ እርምጃ

21. (ሀ) ‘የይሖዋን ዕቃ የሚሸከሙት’ ሰዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) ከባቢሎን የሚወጡት አይሁዳውያን ተጣድፈው መሸሽ የማያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

21 ከባቢሎን ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም የሚመለሱት እስራኤላውያን ሊወስዱት የሚገባ እርምጃ አለ። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩስን ነገር አትንኩ፣ ከመካከልዋ ውጡ፣ ንጹሐን ሁኑ። እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፣ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም።” (ኢሳይያስ 52:11, 12) ባቢሎንን ለቅቀው የሚወጡት እስራኤላውያን ከባቢሎን የሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ያለውን ነገር በሙሉ ትተው መውጣት አለባቸው። ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ተወስዶ የነበረውን የይሖዋ ዕቃ የሚሸከሙ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ ከውጪ የሚታይ የአምልኮ ሥርዓት በመፈጸም ከመንጻት በበለጠ ልባቸውን ማጥራት ይጠበቅባቸው ነበር። (2 ነገሥት 24:​11-13፤ ዕዝራ 1:​7) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ከፊታቸው የሚሄድ በመሆኑ ደም የተጠሙ አሳዳጆች እግር በእግር የሚከታተሏቸው ይመስል በፍርሃት ተጣድፈው የሚሸሹበት ወይም እግሬ አውጪኝ ብለው የሚፈረጥጡበት ምክንያት አይኖርም። የእስራኤል አምላክ ደጀን ይሆንላቸዋል።​—⁠ዕዝራ 8:​21-23

22. ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

22 ኢሳይያስ ንጽሕናን የመጠበቅን አስፈላጊነት አስመልክቶ የተናገራቸው ቃላት ‘በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ልጆች ላይ ከፍተኛ ተፈጻሚነት አለው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ከማያምኑ ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ እንዳይጠመዱ ባሳሰባቸው ጊዜ ኢሳይያስ 52:​11ን በመጥቀስ “ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል” ብሏቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 6:​14-17) ከባቢሎን ወጥተው ወደ ትውልድ አገራቸው እንደተመለሱት እስራኤላውያን ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖችም ከባቢሎናዊ የሐሰት አምልኮ ሙሉ በሙሉ መራቅ አለባቸው።

23. ዛሬ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ የሚጥሩት በምን መንገዶች ነው?

23 በተለይ በ1919 ከታላቂቱ ባቢሎን የወጡት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ይህን እርምጃ ወስደዋል። በመካከላቸው የነበረውን የሐሰት አምልኮ ርዝራዥ ደረጃ በደረጃ አስወግደዋል። (ኢሳይያስ 8:​19, 20፤ ሮሜ 15:​4) ከዚህም በተጨማሪ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ይበልጥ እየተገነዘቡ መጡ። ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የሥነ ምግባር መስፈርቶችን ሲጠብቁ የኖሩ ቢሆንም በ1952 የታተመው መጠበቂያ ግንብ የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ብልሹ ሥነ ምግባር ባላቸው ሰዎች ላይ የተግሳጽና የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠበቅ አድርገው የሚገልጹ ትምህርቶችን ይዞ ወጥቶ ነበር። እንዲህ ያለው እርምጃ ኃጢአት የሠራውም ሰው ልባዊ ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልገው እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:​6, 7, 9-13፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​8-10፤ 2 ዮሐንስ 10, 11

24. (ሀ) በዘመናችን ‘የይሖዋን ዕቃ’ የሚወክሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ይሖዋ ከፊታቸው እንደሚሄድና ደጀን እንደሚሆንላቸው እርግጠኞች የሚሆኑት ለምንድን ነው?

24 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ ርኩስ የሆነ ምንም ነገር ላለመንካት ቁርጥ አቋም ወስደዋል። ንጹሕና የጠሩ መሆናቸው ‘የይሖዋን ዕቃ ለመሸከም’ የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል። ይህም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናትም ሆነ በሌሎች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ ይሖዋ ያደረጋቸውን ውድ ዝግጅቶች ያመለክታል። ዛሬ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ አቋም ይዘው እስከኖሩ ድረስ ይሖዋ ከፊታቸው እንደሚሄድ እንዲሁም ደጀን እንደሚሆንላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። የአምላክ ንጹሕ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን ‘በአንድነት ለመዘመር’ የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶች አሏቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ‘በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ እና ምድር ላይ ባሉት ቅቡዓን ልጆቿ መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ 15ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 183 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጽዮን ከግዞት ነፃ ትወጣለች

[በገጽ 186 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ1919 አንስቶ ‘ያማሩ እግሮች’ “በተራሮች” ላይ እንደገና ብቅ ብለዋል

[በገጽ 189 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ድምፅ ያስተጋባሉ

[በገጽ 192 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የይሖዋን ዕቃ የሚሸከሙ’ ሰዎች በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሖች መሆን አለባቸው