በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ!’

‘ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ!’

ምዕራፍ ሦስት

‘ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ!’

ኢሳይያስ 42:​1-25

1, 2. የኢሳይያስ መጽሐፍ 42⁠ኛ ምዕራፍ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 43:​10) ነቢዩ ኢሳይያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመዘገባቸው እነዚህ ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት የጥንቱ የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ስለ እርሱ የሚመሠክር ብሔር እንደነበረ የሚያሳዩ ናቸው። የተመረጡ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። ከ2, 600 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1931 ቅቡዓን ክርስቲያኖች እነዚህ ቃላት እነርሱንም እንደሚያመለክቱ በይፋ አውጀዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ በመቀበል የአምላክ ምድራዊ አገልጋይ መሆን የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመሸከም በሙሉ ልብ ራሳቸውን አቅርበዋል።

2 የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ከዚህም የተነሣ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ስላገኘ አንድ አገልጋይና የእርሱን ሞገስ ስላጣ ሌላ አገልጋይ የሚናገረው የኢሳይያስ መጽሐፍ 42ኛ ምዕራፍ የእያንዳንዱን የይሖዋ ምሥክር ትኩረት በእጅጉ የሚስብ ይሆናል። ይህን ትንቢትና የትንቢቱን አፈጻጸም መመርመራችን በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት የሚረዳንንም ሆነ ሞገሱን እንድናጣ የሚያደርገንን ነገር ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል።

“መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ”

3. ይሖዋ “አገልጋዬ” ስላለው ሰው በኢሳይያስ አማካኝነት ምን ትንቢት ተናግሯል?

3 ይሖዋ እርሱ ራሱ የሚመርጠው አንድ አገልጋይ እንደሚመጣ በኢሳይያስ አማካኝነት ትንቢት ተናግሯል። “ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ [“ነፍሴ የተቀበለችው፣” NW ] ምርጤ ይህ ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል። አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም። የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል። ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ አይደክምም፤ ተስፋም አይቆርጥም፤ ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:​1-4 አ.መ.ት

4. “ምርጤ” ተብሎ የተጠቀሰው ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

4 እዚህ ላይ የተጠቀሰው አገልጋይ ማን ነው? እነዚሁ ቃላት በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመልከት የተጠቀሱ በመሆኑ የዚህ አገልጋይ ማንነት ግራ ሊያጋባን አይገባም። (ማቴዎስ 12:​15-21) ‘የተመረጠው’ የተወደደ አገልጋይ ኢየሱስ ነው። ይሖዋ መንፈሱን በኢየሱስ ላይ ያደረገው መቼ ነው? በ29 እዘአ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ነበር። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ስለ ጥምቀቱ ከገለጸ በኋላ ኢየሱስ ከውኃ ሲወጣ የሆነውን ነገር በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።” በዚህ መንገድ ይሖዋ ራሱ የሚወድደውን አገልጋዩን ማንነት ገልጿል። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ያከናወነው አገልግሎትና የፈጸማቸው ተአምራት የይሖዋ መንፈስ በእርሱ ላይ እንደነበረ አረጋግጠዋል።​​—⁠⁠ሉቃስ 3:​21, 22፤ 4:​14-21፤ ማቴዎስ 3:​16, 17

‘ለአሕዛብ ፍትሕን ያመጣል’

5. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለ ፍትሕ ግልጽ ማብራሪያ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው?

5 ይሖዋ የመረጠው አገልጋይ እውነተኛ ፍትሕን “ያመጣል” ወይም ይገልጣል። “ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።” (ማቴዎስ 12:​18 አ.መ.ት ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ እውነተኛ ፍትሕን የሚያውጅ ሰው በእጅጉ ያስፈልግ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ስለ ፍትሕና ጽድቅ የሚያስተምሩት ትምህርት የተዛባ ነበር። ድርቅ ያሉ ሕጎችን በመከተል ጽድቅን ለማግኘት ይጥሩ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ሕጎች መካከል ብዙዎቹም ራሳቸው ያወጧቸው ነበሩ። ጥብቅ በሆኑ ሕጎች ላይ የተመሠረተው የፍትሕ ሥርዓታቸው ምሕረትና ርኅራኄ የሌለው ነበር።

6. ኢየሱስ እውነተኛው ፍትሕ ግልጽ ሆኖ እንዲታወቅ ያደረገው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ግን አምላክ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት በግልጽ አስታውቋል። ያስተማረው ትምህርትም ሆነ አኗኗሩ እውነተኛው ፍትሕ በርኅራኄና በምሕረት ላይ የተመሠረተ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ዝነኛ የተራራ ስብከቱን ብቻ እንኳን ተመልከት። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) ፍትሕንና ጽድቅን እንዴት ማሳየት እንደሚገባ የሚጠቁም ድንቅ ማብራሪያ ነው! የወንጌል ዘገባዎችን ስናነብ ኢየሱስ ለድሆችና ለችግረኞች ያሳየው ርኅራኄ ልባችንን አይነካውምን? (ማቴዎስ 20:​34፤ ማርቆስ 1:​41፤ 6:​34፤ ሉቃስ 7:​13) እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ ጎብጠውና ደቅቀው ለነበሩት ሰዎች የሚያጽናና መልእክቱን አድርሶላቸዋል። እነዚህ ሰዎች የመኖር ተስፋቸው ሊጠፋ እንደተቃረበ የሚጤስ የጧፍ ክር ሆኖ ነበር። ኢየሱስ ‘የተቀጠቀጠን ሸንበቆ’ አልሰበረም፤ ‘የሚጤስንም የጧፍ ክር’ አላጠፋም። ይልቁንም ፍቅርና ርኅራኄ የተንጸባረቀበት ንግግሩና ድርጊቱ የዋህ የሆኑ ሰዎችን መንፈስ አነቃቅቶ ነበር።​​—⁠⁠ማቴዎስ 11:​28-30

7. ትንቢቱ ኢየሱስ ‘እንደማይጮኽ ወይም ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል እንደማያሰማ’ የተናገረው ለምንድን ነው?

7 ይሁንና ትንቢቱ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “አይጮኽም፣ ቃሉንም ከፍ አያደርግም፤ ድምፁንም በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም” የሚለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዘመኑ እንደነበሩት ብዙ ሰዎች ልታይ ልታይ የሚል ስላልነበረ ነው። (ማቴዎስ 6:​5) የሥጋ ደዌ የነበረበትን አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ “ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ” ብሎታል። (ማርቆስ 1:​40-44) ኢየሱስ የሰዎችን ትኩረት ከመሳብና ሰዎች በስሚ ስሚ ከደረሳቸው ወሬ ተነሥተው አንድ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ከማድረግ ይልቅ እርሱ ክርስቶስ ማለትም የተቀባ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን ራሳቸው በተጨባጭ ማስረጃ እንዲያስተውሉ ይፈልግ ነበር።

8. (ሀ) ኢየሱስ ‘ለአሕዛብ ፍትሕን’ ያመጣው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ስለ ፍትሕ ምን ያስተምረናል?

8 ይህ የተመረጠ አገልጋይ ‘ለአሕዛብ ፍትሕን እንደሚያመጣ’ ተነግሯል። ኢየሱስም ቢሆን ያደረገው ይህንኑ ነው። በአምላካዊው ፍትሕ ላይ የሚንጸባረቀውን የርኅራኄ ባሕርይ ጎላ አድርጎ ከማሳየቱም በተጨማሪ ይህ ፍትሕ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የሚያቅፍ መሆን እንዳለበት አስተምሯል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሕጉን ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው አምላክንና ባልንጀራውን መውደድ እንዳለበት ሲያሳስበው ሰውዬው “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ምናልባት ሰውዬው “አይሁዳዊ ወንድምህ” የሚል መልስ ይሰጠኛል ብሎ ጠብቆ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ ነገረው። በዚህ ምሳሌ ውስጥ በወንበዴዎች ጉዳት የደረሰበትን ሰው አንድ ሌዋዊና አንድ ካህን ለመርዳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው እንዳለፉና አንድ ሳምራዊ እንደረዳው ተጠቅሷል። ጥያቄውን ያነሳው ሰው በዚህ ጊዜ ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የተናቀው ሳምራዊ እንጂ ሌዋዊው ወይም ካህኑ እንዳልሆኑ አምኖ ለመቀበል ተገድዷል። ኢየሱስ “አንተም እንዲሁ አድርግ” የሚል ምክር በመስጠት ምሳሌውን ደመደመ።​​—⁠⁠ሉቃስ 10:​25-37፤ ዘሌዋውያን 19:​18

“አይደክምም፤ ተስፋም አይቆርጥም”

9. እውነተኛ ፍትሕን ጠንቅቀን መረዳታችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

9 ኢየሱስ እውነተኛ ፍትሕ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ስላሳየ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅን ተምረዋል። እኛም እንዲሁ ማድረግ ይገባናል። በመጀመሪያ ደረጃ ትክክለኛና ጽድቅ የሆነውን ነገር የመወሰን መብት ያለው አምላክ በመሆኑ በጎና መጥፎ የሆነውን ነገር በተመለከተ አምላክ ያወጣቸውን ደንቦች መቀበል ይኖርብናል። በሕይወታችን ውስጥ የምናከናውናቸውን ነገሮች ከይሖዋ አቋም ጋር ለማስማማት ስንጥር ቀና የሆነው ምግባራችን እውነተኛ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ በጉልህ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።​​—⁠⁠1 ጴጥሮስ 2:​12

10. በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ መካፈል ፍትሕን ከምናንጸባርቅባቸው መንገዶች አንዱ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በትጋት ስንካፈልም እውነተኛ ፍትሕ እናንጸባርቃለን። ይሖዋ ስለ ራሱ፣ ስለ ልጁና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጽ ሕይወት አድን የሆነ እውቀት አትረፍርፎ ሰጥቶናል። (ዮሐንስ 17:​3) ይህንን እውቀት ለራሳችን ብቻ ሸሽገን መያዛችን ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊ አይሆንም። ሰሎሞን “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትከልክል” ብሏል። (ምሳሌ 3:​27 አ.መ.ት ) ዘራቸው፣ ጎሳቸው ወይም ብሔራቸው ምንም ይሁን ምን ስለ አምላክ የምናውቀውን ነገር ለሁሉም ሰዎች በሙሉ ልብ እናካፍል።​​—⁠⁠ሥራ 10:​34, 35

11. የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ምን ለማድረግ መጣር ይገባናል?

11 በተጨማሪም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ኢየሱስ ለሰዎች የነበረውን ዓይነት ስሜት በመኮረጅ ሌሎችን ለመርዳት ይጥራል። ዛሬ ብዙ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች ስለሚገጥሟቸው ርኅራኄና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሳይቀሩ በተለያዩ ችግሮች ከመደቆሳቸው የተነሣ ከተቀጠቀጠ ሸንበቆ ወይም ከሚጤስ የጧፍ ክር ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ይገኙ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የእኛ እርዳታ አያስፈልጋቸውምን? (ሉቃስ 22:​32፤ ሥራ 11:​23) ፍትሕን በማሳየት በኩል የኢየሱስን ምሳሌ ለመኮረጅ ከሚጥሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል መቆጠር ምንኛ የሚያስደስት ነው!

12. በቅርቡ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

12 ሁሉም ሰው ፍትሕ የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎን፣ ይመጣል። ይሖዋ የመረጠው አገልጋይ “ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ አይደክምም፤ ተስፋም አይቆርጥም።” ትንሣኤ ያገኘውና በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ንጉሡ ክርስቶስ ኢየሱስ በቅርቡ ‘አምላክን በማያውቁ ሰዎች ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።’ (2 ተሰሎንቄ 1:​6-9፤ ራእይ 16:​14-16) ሰብዓዊው አገዛዝ በአምላክ መንግሥት ይተካል። ፍትሕና ጽድቅም ይሰፍናል። (ምሳሌ 2:​21, 22፤ ኢሳይያስ 11:​3-5፤ ዳንኤል 2:​44፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13) ርቀው በሚገኙት “ደሴቶች” ያሉትን ጨምሮ በየትኛውም የምድር ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ያንን ቀን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

‘ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጠዋለሁ’

13. ይሖዋ ስለተመረጠ አገልጋዩ ምን ትንቢት ተናግሯል?

13 ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ዘገባውን ይቀጥላል:- “ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፣ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፣ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።” (ኢሳይያስ 42:5) ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋን በተመለከተ የተሰጠ እንዴት ያለ ድንቅ መግለጫ ነው! ስለ ይሖዋ ኃይል የተሰጠው ይህ ማሳሰቢያ ከአፉ የሚወጣው ቃል ትልቅ ክብደት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፣ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፣ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:​6, 7

14. (ሀ) ይሖዋ የመረጠውን አገልጋዩን እጅ እንደሚይዝ መናገሩ ምን ያመለክታል? (ለ) የተመረጠው አገልጋዩ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?

14 ሕይወትንና ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የሰጠን ታላቁ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የመረጠውን አገልጋዩን እጅ እንደሚይዝና የማያቋርጥ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጠው ቃል ገብቷል። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ከዚህም በላይ ይሖዋ “ለሕዝብ ቃል ኪዳን” አድርጎ ስለሚሰጠው ይጠብቀዋል። ቃል ኪዳን ማለት ውል፣ ስምምነት ወይም ቃለ መሃላ መፈጸም ማለት ነው። ቃል ኪዳን የማይታጠፍ ቃል ነው። አዎን፣ ይሖዋ አገልጋዩን “ለሕዝቡ የጸና ውል” አድርጎ ሰጥቶታል።​​—⁠⁠አን አሜሪካን ትራንስሌሽን

15, 16. ኢየሱስ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ ሆኖ ያገለገለው በምን መንገድ ነው?

15 ተስፋ የተሰጠበት ይህ አገልጋይ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ እንደመሆኑ መጠን ‘የታወሩትን ዓይን ያበራል፣’ ‘በጨለማ የተቀመጡትንም’ ነፃ ያወጣል። ኢየሱስ ያደረገው ይህንኑ ነው። ስለ እውነት በመመሥከር የሰማያዊ አባቱን ስም አክብሯል። (ዮሐንስ 17:​4, 6) የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አጋልጧል፣ የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል እንዲሁም በሃይማኖታዊ ግዞት የነበሩት ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት የሚያገኙበትን በር ከፍቷል። (ማቴዎስ 15:​3-9፤ ሉቃስ 4:​43፤ ዮሐንስ 18:​37) የጨለማ ሥራን ከመሥራት እንዲርቁ ከማስጠንቀቁም ሌላ ሰይጣን ‘የሐሰት አባት’ እንዲሁም “የዚህ ዓለም ገዥ” መሆኑን አጋልጧል።​​—⁠⁠ዮሐንስ 3:​19-21፤ 8:​44፤ 16:​11

16 ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:​12) ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ባቀረበ ጊዜ የዓለም ብርሃን መሆኑን ድንቅ በሆነ መንገድ አረጋግጧል። ይህን ቤዛ በመክፈሉም እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት፣ ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና መመሥረትና የዘላለም ሕይወት ተስፋን መጠባበቅ የሚችሉበትን በር ከፍቷል። (ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 3:​16) ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ፍጹም ለአምላክ ያደረ መሆኑን በሚያሳይ መንገድ በመመላለስ የይሖዋን ሉዓላዊነት ሲያስከብር ዲያብሎስ ሐሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል። በእርግጥም ኢየሱስ ለታወሩ ብርሃን የሚሰጥና በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ የታሠሩትን ነፃ የሚያወጣ ነው።

17. ብርሃን አብሪዎች ሆነን የምናገለግለው በምን መንገዶች ነው?

17 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:​14) ታዲያ እኛስ ብርሃን አብሪዎች አይደለንምን? በአኗኗራችንና በስብከት ሥራችን አማካኝነት ሌሎች ሰዎች የእውነተኛ ብርሃን ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ እንዲመጡ የመርዳት መብት አግኝተናል። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የይሖዋን ስም እናሳውቃለን፣ ሉዓላዊነቱን እናስከብራለን እንዲሁም የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን እናውጃለን። ከዚህም በላይ ብርሃን አብሪዎች እንደመሆናችን መጠን የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን እናጋልጣለን፣ ርኩስ ከሆኑ የጨለማ ሥራዎች እንዲርቁ ሰዎችን እናስጠነቅቃለን እንዲሁም ክፉውን ሰይጣንን እናጋልጣለን።​​—⁠⁠ሥራ 1:​8፤ 1 ዮሐንስ 5:​19

‘ለይሖዋ አዲስ መዝሙር ዘምሩ’

18. ይሖዋ ሕዝቡ ስለ ምን ነገር እንዲያውቁ ያደርጋል?

18 አሁን ደግሞ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ ራሱ ሕዝብ በመመለስ እንዲህ ይላል:- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፣ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፣ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።” (ኢሳይያስ 42:​8, 9) “አገልጋዬ” ሲል ስለጠራው ሰው ትንቢት የተናገረው ብቸኛው ሕያውና እውነተኛ አምላክ እንጂ ከንቱ ከሆኑት አማልክት አንዱ አይደለም። ይህ ትንቢት መፈጸሙ አጠያያቂ አልነበረም። ደግሞም ተፈጽሟል። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ የአዳዲስ ነገሮች ምንጭ ሲሆን እነዚህን ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ለሕዝቡ ያስታውቃል። ታዲያ ይህ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

19, 20. (ሀ) መዘመር ያለበት መዝሙር የትኛው ነው? (ለ) ዛሬ ለይሖዋ የምስጋና መዝሙር እየዘመሩ ያሉት እነማን ናቸው?

19 ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፣ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፣ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:10-12

20 በከተሞች፣ በምድረ በዳ መሃል በሚገኙ መንደሮች፣ በደሴቶችና ‘በቄዳር’ ማለትም በበረሃ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ በአጠቃላይ በየትኛውም ስፍራ ያሉ ሰዎች ለይሖዋ የምስጋና መዝሙር እንዲዘምሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ትንቢታዊ ጥሪ መቀበላቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት በመቀበል ይሖዋን ለማምለክ መርጠዋል። የይሖዋ ሕዝብ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይህንን አዲስ መዝሙር በመዘመር ይሖዋን በማክበር ላይ ናቸው። ከተለያየ ባሕል፣ ቋንቋና ዘር የተውጣጡ ሰዎች አንድ ላይ በሚያሰሙት በዚህ ዝማሬ መካፈል መቻል እንዴት የሚያስደስት ነው!

21. የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ለይሖዋ የሚቀርበውን የምስጋና መዝሙር ማስቆም የማይችሉት ለምንድን ነው?

21 ተቃዋሚዎች አምላክን በመቃወም ይህን የምስጋና መዝሙር ማስቆም ይችላሉን? በፍጹም! “እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል።” (ኢሳይያስ 42:13) ይሖዋን ሊቋቋም የሚችል ምን ኃይል ይኖራል? ከ3, 500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ሙሴና የእስራኤል ልጆች እንደሚከተለው ሲሉ ዘምረዋል:- “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፣ ስሙ እግዚአብሔር ነው፣ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ።” (ዘጸአት 15:​3, 4) ይሖዋ የዘመኑን ታላቅ ወታደራዊ ኃይል ድል አድርጓል። እንደ ኃያል ተዋጊ ሆኖ ሲወጣ የትኛውም የአምላክ ሕዝብ ጠላት አንዳች ሊያደርግ አይችልም።

“ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ”

22, 23. ይሖዋ ‘ለረጅም ዘመን ዝም ብሎ’ የሚቆየው ለምንድን ነው?

22 ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የሚበይነው ፍርድ እንኳ ሳይቀር አድልዎ የሌለበትና ፍትሐዊ ነው። እንዲህ ይላል:- “ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፣ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፣ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፣ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:14, 15

23 ይሖዋ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ኃጢአተኛ ሰዎች ከመጥፎ ሥራቸው እንዲመለሱ አጋጣሚ ለመስጠት ሲል ለተወሰነ ጊዜ ይታገሳል። (ኤርምያስ 18:​7–10፤ 2 ጴጥሮስ 3:​9) ብርቱ የዓለም ኃይል የነበሩትንና በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ያወደሙትን ባቢሎናውያን አስታውስ። ይሖዋ እስራኤላውያን ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምክንያት እነርሱን ለመቅጣት ሲል ይህ ሁኔታ እንዲደርስ ፈቅዷል። ይሁን እንጂ ባቢሎናውያን የእነርሱ ሚና ምን እንደሆነ ሳይገነዘቡ ቀርተዋል። የአምላክ ፍርድ ከሚጠይቀው በላይ በአምላክ ሕዝብ ላይ የከፋ ጭካኔ ፈጽመዋል። (ኢሳይያስ 47:​6, 7፤ ዘካርያስ 1:​15) እውነተኛው አምላክ ሕዝቡ ያን ያህል ሲሰቃይ መመልከቱ ምንኛ አሳዝኖት ይሆን! ይሁን እንጂ አስቀድሞ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እርምጃ ከመውሰድ ይታቀባል። ወቅቱ ሲደርስ ግን ምጥ እንደያዛት ሴት በመቃተት የቃል ኪዳን ሕዝቡን ነፃ አውጥቶ ራሱን የቻለ ብሔር ሆኖ እንዲቋቋም ያደርጋል። ይህን ዳር ለማድረስ በ539 ከዘአበ ባቢሎንንና መከላከያዎቿን ያደርቃል ብሎም ያጠፋል።

24. ይሖዋ ለሕዝቡ ለእስራኤል ምን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል?

24 ከእነዚያ ሁሉ የግዞት ዓመታት በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ የሚችሉበት መንገድ ሲከፈትላቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! (2 ዜና መዋዕል 36:​22, 23) ቀጥሎ የተገለጸው የይሖዋ የተስፋ ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ በማየታቸው እጅግ ተደስተው መሆን አለበት:- “ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፣ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፣ ጠማማውንም አቀናለሁ [“ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ፣” አ.መ.ት ]ይህን አደርግላቸዋለሁ፣ አልተዋቸውምም።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:16

25. (ሀ) በዘመናችን የይሖዋ ሕዝብ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

25 እነዚህ ቃላት ዛሬ ምን ትርጉም አላቸው? ይሖዋ ለረጅም ዓመታት ማለትም ለብዙ መቶ ዘመናት ብሔራት በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቅዶላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ሁኔታ የሚቋጭበት ጊዜ ተቃርቧል። በዘመናችን ስለ ስሙ የሚመሠክር ሕዝብ አስነሥቷል። በእርሱ ላይ የሚነሡትን ተቃውሞዎች ሁሉ በማፍረስ እርሱን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ የሚችሉበትን መንገድ አስተካክሎላቸዋል። (ዮሐንስ 4:​24) “አልተዋቸውም” ሲል የገባውን ቃል ጠብቋል። የሐሰት አማልክትን ማምለካቸውን ስለሚቀጥሉ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፣ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች:- አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።” (ኢሳይያስ 42:17) የተመረጠው የይሖዋ አገልጋይ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ታማኝ ሆነን መቀጠላችን ምንኛ አንገብጋቢ ነው!

‘ደንቆሮና ዕውር አገልጋይ’

26, 27. እስራኤል ‘እንደ ደንቆሮና ዕውር አገልጋይ’ የሆነችው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?

26 የተመረጠው የአምላክ አገልጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል። ይሁንና የይሖዋ ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን ከዳተኞች ከመሆናቸውም ሌላ በመንፈሳዊ ሁኔታ ደንቆሮና ዕውር ሆነው ነበር። ይሖዋ አምላክ እነርሱን በተመለከተ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እናንተ ደንቆሮች፣ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፣ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ። ከባሪያዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹሙ ወይስ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ ዕውር የሆነ ማን ነው? ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፣ ነገር ግን አትሰሙም። እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:18-21

27 እስራኤል እንዴት ያለች ማፈሪያ ናት! ሕዝቡ ብሔራት ወደሚያመልኳቸው አጋንንታዊ አማልክት በተደጋጋሚ ጊዜ ዘወር ብለዋል። ይሖዋ መልእክተኞቹን ደጋግሞ ቢልክም አልሰሙም። (2 ዜና መዋዕል 36:​14-16) ይህ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ኢሳይያስ በትንቢት እንደሚከተለው ብሏል:- “ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁላቸው በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ብዝበዛ ሆነዋል የሚያድንም የለም፣ ምርኮም ሆነዋል፣ ማንም:- መልሱ አይልም። ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፣ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው? ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፣ እነርሱም በመንገዱ ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት ለሕጉም ያልታዘዙለት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን? ስለዚህ የቁጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰበት፤ በዙሪያም አነደደው እርሱ ግን አላወቀም፣ አቃጠለውም እርሱ ግን ልብ አላደረገም።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 42:22-25

28. (ሀ) ከይሁዳ ነዋሪዎች ምሳሌ ምን እንማራለን? (ለ) በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት መጣር የምንችለው እንዴት ነው?

28 ነዋሪዎቿ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምክንያት ይሖዋ የይሁዳ ምድር በ607 ከዘአበ እንድትበዘበዝና እንድትዘረፍ ፈቅዷል። ባቢሎናውያን የይሖዋን ቤተ መቅደስ በማቃጠል ኢየሩሳሌምን ያወደሙ ሲሆን አይሁዳውያንንም በምርኮ አግዘዋል። (2 ዜና መዋዕል 36:​17-21) እኛም ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት በማግኘት ይሖዋ ለሚሰጠው ማሳሰቢያ ጆሮአችንን እንዳንደፍን ወይም ደግሞ ቃሉን ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይገባናል። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ሞገስ ያገኘውን አገልጋይ ማለትም የክርስቶስ ኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት መጣር ይኖርብናል። ልክ እንደ ኢየሱስ በምንናገረውና በምናደርገው ነገር እውነተኛውን ፍትሕ ለሌሎች የምናንጸባርቅ እንሁን። በዚህ መንገድ እውነተኛውን አምላክ በማወደስ ክብር ከሚሰጡትና ብርሃን አብሪ ሆነው ከሚያገለግሉት ሕዝቡ መካከል ሆነን መቀጠል እንችላለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 33 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እውነተኛ ፍትሕ በርኅራኄና በምሕረት ላይ የተመሠረተ ነው

[በገጽ 34 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ እውነተኛ ፍትሕ ሁሉንም ሰው እንደሚያቅፍ አሳይቷል

[በገጽ 36 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሌሎችን የምናበረታታና ደጎች በመሆን አምላካዊ ፍትሕ እናሳያለን

[በገጽ 39 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በስብከት ሥራችን አምላካዊ ፍትሕ እናሳያለን

[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያገኘው አገልጋይ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ እንዲሆን ተሰጥቷል