በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አምላክ በጎ ፈቃድ ያሳየበት ዘመን’

‘አምላክ በጎ ፈቃድ ያሳየበት ዘመን’

ምዕራፍ አሥር

‘አምላክ በጎ ፈቃድ ያሳየበት ዘመን’

ኢሳይያስ 49:​1-26

1, 2. (ሀ) ኢሳይያስ ምን በረከት አግኝቷል? (ለ) በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 የመጀመሪያ ክፍል ላይ የሠፈሩት ትንቢታዊ ቃላት እነማንን ያመለክታሉ?

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የአምላክን ሞገስና ጥበቃ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በጎ ፈቃድ የሚያሳየው ለሁሉም ሰው አይደለም። አንድ ሰው ይህን ተወዳዳሪ የሌለው በረከት ለማግኘት ሊያሟላው የሚገባው ብቃት አለ። ኢሳይያስ እንዲህ ያለውን ብቃት ያሟላ ሰው ስለነበር አምላክ ሞገሱን ያሳየው ከመሆኑም በላይ ፈቃዱን ለሌሎች ለማስታወቅ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 የመጀመሪያ ክፍል ላይ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ዘገባ ሰፍሮ እናገኛለን።

2 እነዚህ ቃላት በትንቢት የተነገሩት ለአብርሃም ዘር ነው። በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት ይህ ዘር ከአብርሃም የተገኘው የእስራኤል ብሔር ነው። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ በአብዛኛው የሚያመለክተው ለረጅም ጊዜ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረውን የአብርሃም ዘር ማለትም አስቀድሞ የተነገረለትን መሲሕ ነው። እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት የአብርሃም መንፈሳዊ ዘርና ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት የሆኑትን የመሲሑ መንፈሳዊ ወንድሞችም ያመለክታሉ። (ገላትያ 3:​7, 16, 29፤ 6:​16) በይበልጥ ደግሞ ይህ የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል በይሖዋና በተወደደው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ልዩ ዝምድና ይገልጻል።​—⁠ኢሳይያስ 49:​26

በይሖዋ የተሾመና ጥበቃ ያገኘ

3, 4. (ሀ) መሲሑ ምን ድጋፍ አለው? (ለ) መሲሑ የተናገረው ለእነማን ነው?

3 መሲሑ የአምላክን በጎ ፈቃድ ወይም ተቀባይነት አግኝቷል። ይሖዋ ተልዕኮውን ለመፈጸም የሚያስችል ሥልጣንና ሙሉ ድጋፍ ሰጥቶታል። በመሆኑም መሲሑ እንዲህ ሲል መናገሩ የተገባ ነው:- “ደሴቶች ሆይ፣ ስሙኝ፣ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፣ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ከማኅፀን ጠርቶኛል፣ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንሥቶአል።”​—⁠ኢሳይያስ 49:1

4 መሲሑ የተናገረው ‘በሩቅ ላሉ’ አሕዛብ ነው። ይሖዋ መሲሕ እንደሚያስነሳ ቃል የገባው ለአይሁዳውያን ቢሆንም አገልግሎቱ ለአሕዛብ ሁሉ በረከት ያስገኛል። (ማቴዎስ 25:​31-33) “ደሴቶች” እና “አሕዛብ” ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን የገቡ ባይሆንም እንኳ የእስራኤል መሲሕ መላውን የሰው ዘር ለማዳን የተላከ በመሆኑ ሊያደምጡት ይገባል።

5. መሲሑ ገና ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በስም የተጠራው እንዴት ነው?

5 ትንቢቱ እንደሚናገረው ይሖዋ ለመሲሑ ስም የሚሰጠው ገና ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ነው። (ማቴዎስ 1:​21፤ ሉቃስ 1:​31) ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ ዓመታት በፊት “ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኢሳይያስ 9:​6) የኢሳይያስ ልጅ ስም እንደሆነ የሚታመነው አማኑኤል የሚለው መጠሪያም የመሲሑ ትንቢታዊ ስም ሆኖ አገልግሏል። (ኢሳይያስ 7:​14፤ ማቴዎስ 1:​21-23) መሲሑ ሲወለድ የተሰጠውና በስፋት ተለይቶ የሚታወቅበት ኢየሱስ የሚለው ስምም እንኳ ሳይቀር ከመወለዱ በፊት ተነግሯል። (ሉቃስ 1:​30, 31) ይህ ስም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። ኢየሱስ ራሱን በራሱ የሾመ መሲሕ አለመሆኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል።

6. የመሲሑ አፍ በስለታም ሰይፍ መመሰሉ ምን ያመለክታል? የተሸሸገው ወይም የተሰወረውስ እንዴት ነው?

6 መሲሑ በመቀጠል የሚከተሉትን ትንቢታዊ ቃላት ተናገረ:- “አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፣ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፤ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፣ በሰገባውም ውስጥ ሸሽጎኛል።” (ኢሳይያስ 49:2) ይሖዋ የሚልከው መሲሕ ማለትም ኢየሱስ በ29 እዘአ ምድራዊ አገልግሎቱን የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ የሚናገራቸው ቃላትም ሆኑ የሚያደርጋቸው ነገሮች እንደተሳለ መሣሪያ የአድማጮቹን ልብ ሰርስረው የሚገቡ ይሆናሉ። (ሉቃስ 4:​31, 32) የሚናገረው ቃልና የሚያደርጋቸው ነገሮች የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን የሰይጣንንና የወኪሎቹን ቁጣ ይቀሰቅሳሉ። ሰይጣን፣ ኢየሱስን ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ለማጥፋት ቢሞክርም ኢየሱስ በይሖዋ ሰገባ ውስጥ እንደተሸሸገ ፍላጻ ይሆናል። * አባቱ ጥበቃ እንደሚያደርግለት ሙሉ በሙሉ መተማመን ይችላል። (መዝሙር 91:​1፤ ሉቃስ 1:​35) የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ሕይወቱን ለሰው ልጆች አሳልፎ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከዚህ ፍጹም በተለየ ሁኔታ ከአፉ የሚወጣ ስለታም ሰይፍ በመታጠቅ ኃያል ሰማያዊ ተዋጊ ሆኖ ብቅ የሚልበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ወቅት ከአፉ የሚወጣው ስለታም ሰይፍ ኢየሱስ በይሖዋ ጠላቶች ላይ ፍርድ የመበየንና የማስፈጸም ሥልጣን ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው።​—⁠ራእይ 1:​16

የአምላክ አገልጋይ ድካም ከንቱ ሆኖ አይቀርም

7. በ⁠ኢሳይያስ 49:​3 ላይ የተጠቀሱት ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በይበልጥ የሚያመለክቱት ማንን ነው? ለምንስ?

7 በመቀጠል ይሖዋ የሚከተሉትን ትንቢታዊ ቃላት ተናገረ:- “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ።” (ኢሳይያስ 49:3) ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር እንደ አገልጋዩ አድርጎ ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 41:​8) ከሁሉ የላቀው የአምላክ አገልጋይ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሥራ 3:​13 NW ) ከኢየሱስ ይበልጥ የይሖዋን ‘ክብር’ ሊያንጸባርቅ የሚችል የአምላክ ፍጥረት የለም። ስለዚህ እነዚህ ቃላት በቀጥታ የተነገሩት ለእስራኤል ቢሆንም በይበልጥ የሚያመለክቱት ኢየሱስን ነው።​—⁠ዮሐንስ 14:​9፤ ቆላስይስ 1:​15

8. የገዛ አገሩ ሰዎች ለመሲሑ የሚኖራቸው አመለካከት ምን ይመስላል? ሆኖም መሲሑ ስኬታማነቱ የሚመዘነው በማን ነው?

8 ይሁን እንጂ ከገዛ አገሩ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢየሱስን በመናቅ ፊታቸውን አዙረውበት የለምን? አዎን፣ በጥቅሉ ሲታይ የእስራኤል ሕዝብ ኢየሱስን በአምላክ የተቀባ አገልጋይ አድርገው አይቀበሉትም። (ዮሐንስ 1:​11) ኢየሱስ በምድር ላይ የሚያከናውናቸው ነገሮች በሙሉ በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ዓይን ከንቱና ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ተደርገው ይታያሉ። መሲሑ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት አገልግሎቱ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደሚገጥመው የሚጠቁሙ ናቸው:- “በከንቱ ደከምሁ፣ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጉልበቴን ፈጀሁ።” (ኢሳይያስ 49:4ሀ) መሲሑ እነዚህን ቃላት የተናገረው የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮበት አይደለም። ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በል:- “ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፣ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው።” (ኢሳይያስ 49:4ለ) የመሲሑ ስኬታማነት የሚመዘነው በሰዎች ሳይሆን በአምላክ ነው።

9, 10. (ሀ) ይሖዋ ለመሲሑ የሰጠው ተልዕኮ ምንድን ነው? የሚያገኘው ውጤትስ ምን ይሆናል? (ለ) በዘመናችን ያሉት ክርስቲያኖች መሲሑ የገጠመው ሁኔታ ጥሩ ማበረታቻ ሊሆናቸው የሚችለው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በዋነኛነት የሚያሳስበው የአምላክን ሞገስ ወይም በጎ ፈቃድ ማግኘቱ ነው። መሲሑ በትንቢቱ ላይ እንዲህ ይላል:- “አሁንም በእግዚአብሔር ዓይን ከብሬአለሁና፣ አምላኬም ጉልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ የሠራኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።” (ኢሳይያስ 49:5) መሲሑ የሚመጣው የእስራኤልን ልጆች ልብ ወደ ሰማያዊ አባታቸው ለመመለስ ነው። አብዛኞቹ አሻፈረን የሚሉ ቢሆንም እንኳ አንዳንዶቹ ልባቸውን ይመልሳሉ። ይሁን እንጂ መሲሑ እውነተኛውን ዋጋ የሚያገኘው ከይሖዋ አምላክ ነው። ስኬቱ የሚለካው በሰው ሳይሆን በራሱ በይሖዋ መስፈርት ነው።

10 በዘመናችን ያሉት የኢየሱስ ተከታዮች አንዳንድ ጊዜ በከንቱ እየደከሙ እንዳሉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። በአንዳንድ ቦታዎች በአገልግሎት የሚያገኙት ውጤት ከሥራቸውና ከድካማቸው ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር የማይገባ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመኮረጅ በአገልግሎታቸው ይጸናሉ። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸው የሚከተሉት ቃላት ጥሩ ማበረታቻ ይሆኑላቸዋል:- “ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:58

“ለአሕዛብ ብርሃን”

11, 12. መሲሑ “ለአሕዛብ ብርሃን” ሆኖ ሊያገለግል የቻለው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የአምላክ አገልጋይ መሆን “ታላቅ ሥራ [የ1980 ትርጉም ]እንደሆነ በማሳሰብ መሲሑን አበረታቶታል። ኢየሱስ ‘የያዕቆብን ነገዶች እንዲያስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንዲመልስ’ ተልዕኮ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ።” (ኢሳይያስ 49:6) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱ በእስራኤል ምድር ብቻ የተወሰነ ሆኖ ሳለ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ላሉ ሕዝቦች መንፈሳዊ ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችለው እንዴት ነው?

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያመለክተው አምላክ ‘ለአሕዛብ የሰጠው ብርሃን’ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን አጠናቅቆ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም አልጠፋም። ኢየሱስ ከሞተ ከ15 ዓመት ገደማ በኋላ ሚስዮናውያን ሆነው ያገለገሉት ጳውሎስና በርናባስ ኢሳይያስ 49:​6 ላይ የሚገኘውን ቃል በመጥቀስ ትንቢቱ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማለትም በመንፈሳዊ ወንድሞቹም ላይ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ አመልክተዋል። “እንዲሁ ጌታ:- እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናል” ሲሉ ተናግረዋል። (ሥራ 13:47) ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት መዳን የሚያስገኘው የምሥራች ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” እንደተሰበከ ተገንዝቦ ነበር። (ቆላስይስ 1:​6, 23) በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ይህን ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው። በሚልዮን በሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመታገዝ በዓለም ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ “ለአሕዛብ ብርሃን” ሆነው እያገለገሉ ነው።​—⁠ራእይ 7:​9

13, 14. (ሀ) መሲሑና ተከታዮቹ የስብከቱን ሥራ ሲያካሂዱ ምን ገጥሟቸዋል? (ለ) ሁኔታዎች መልካቸውን የለወጡት እንዴት ነው?

13 ይሖዋ መሲሕ አድርጎ ለላከው አገልጋዩ፣ ለመሲሑ ቅቡዓን ወንድሞችና ከእነርሱ ጋር ሆነው የምሥራቹን ስብከት ሥራ እያካሄዱ ላሉት እጅግ ብዙ ሰዎች በሙሉ የብርታት ምንጭ ሆኖላቸዋል። ልክ እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱም ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። (ዮሐንስ 15:​20) ይሁን እንጂ ይሖዋ እሱ በወሰነው ጊዜ ታማኝ አገልጋዮቹን ለመታደግና ለመካስ ሲል ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ እንዲለወጡ ያደርጋል። ይሖዋ “ሰዎች ለሚንቁት” እና “ሕዝብም ለሚጠላው” መሲሕ የሚከተለውን ቃል ገብቷል:- “ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፣ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 49:7

14 ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በትንቢት በተነገረው መሠረት ሁኔታዎች እንዴት እንደተለወጡ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ጽፎ ነበር። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ቢዋረድም አምላክ ከፍ ከፍ እንዳደረገው ገልጿል። ይሖዋ ለአገልጋዩ ‘ከሁሉ የላቀ ቦታ እንዲሁም ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም ጉልበት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ ነው።’ (ፊልጵስዩስ 2:8-11) የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች በእነሱም ላይ ስደት እንደሚደርስ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ልክ እንደ መሲሑ እነርሱም የይሖዋን በጎ ፈቃድ እንደሚያገኙ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 5:​10-12፤ 24:​9-13፤ ማርቆስ 10:​29, 30

“የተወደደው ሰዓት”

15. በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ ምን ለየት ያለ “ዘመን” ተጠቅሷል? ይህስ ምን ያመለክታል?

15 የኢሳይያስ ትንቢት በመቀጠል አንድ ትልቅ ትርጉም ያዘለ መግለጫ ይሰጣል። ይሖዋ መሲሑን እንዲህ አለው:- “በተወደደ ጊዜ [“በበጎ ፈቃድ ዘመን፣” NW ] ሰምቼሃለሁ፣ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፣ . . . ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ።” (ኢሳይያስ 49:8ሀ, 9) ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ትንቢት በ⁠መዝሙር 69:​13-18 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። መዝሙራዊው፣ አምላክ ‘በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዘመን’ “መልካሙ ጊዜ” ሲል ጠቅሶታል። እነዚህ አገላለጾች ይሖዋ ለየት ባለ ሁኔታ በጎ ፈቃድ እንደሚያሳይና ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያመለክቱ ከመሆናቸውም በላይ ይህን የሚያደርገው ለተወሰነ ጊዜ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

16. ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በጎ ፈቃዱን ያሳየው መቼ ነው?

16 አምላክ በጎ ፈቃዱን ያሳየው መቼ ነው? ትንቢቱ መጀመሪያ ላይ የተነገረበት ሁኔታ እንደሚያመለክተው እነዚህ ቃላት አይሁዳውያን ከግዞት ነፃ ወጥተው ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ በሚገልጸው ትንቢት ውስጥ የተካተቱ ናቸው። እስራኤላውያን ‘ምድሩን ማቅናት’ እና “ውድማ የሆኑትን ርስቶች” ዳግመኛ መውረስ መቻላቸው ይሖዋ በጎ ፈቃዱን እንዳሳያቸው የሚያረጋግጥ ነው። (ኢሳይያስ 49:​8ለ) ከባቢሎን ‘ግዞት’ ነፃ ወጥተዋል። ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ይሖዋ ‘እንዳይራቡና እንዳይጠሙ’ እንዲሁም ‘ትኩሳት ወይም ፀሐይ እንዳይጎዳቸው’ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ አድርጎላቸዋል። ተበታትነው የነበሩት እስራኤላውያን “ከሩቅ . . . ከሰሜንና ከምዕራብ” ተሰባስበው ወደ ትውልድ አገራቸው ይመለሳሉ። (ኢሳይያስ 49:​9-12) ይህ ትንቢት እጅግ አስገራሚ በሆነ መንገድ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቱ በሌሎች ሁኔታዎችም ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ያመለክታል።

17, 18. ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በጎ ፈቃድ ያሳየበት ጊዜ የትኛው ነው?

17 በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት መላእክት ሰላምን ያወጁ ከመሆኑም በላይ አምላክ ለሰዎች በጎ ፈቃድ ወይም ሞገስ እንደሚያሳይ አስታውቀዋል። (ሉቃስ 2:​13, 14) አምላክ በጎ ፈቃዱን የሚያሳየው ለሰው ዘር በጠቅላላ ሳይሆን በኢየሱስ ለሚያምኑ ሰዎች ብቻ ነው። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ኢሳይያስ 61:​1, 2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት በሕዝብ ፊት በማንበብ “የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት” እንዲያውጅ የተላከው እሱ መሆኑን ገልጿል። (ሉቃስ 4:​17-21) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ በሥጋ በኖረበት ዘመን የይሖዋን ልዩ ጥበቃ እንዳገኘ ተናግሯል። (ዕብራውያን 5:​7-9) ስለዚህ ይህ የበጎ ፈቃድ ዘመን ኢየሱስ ሰው ሆኖ በኖረበት ዘመን ሁሉ አምላክ ያሳየውን ሞገስ የሚያመለክት ነው።

18 ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት ሌላም ፍጻሜ አለው። ጳውሎስ አምላክ በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዘመን አስመልክቶ ኢሳይያስ የተናገራቸውን ቃላት ከጠቀሰ በኋላ “እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው” ሲል ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 6:​2) ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው ኢየሱስ ከሞተ ከ22 ዓመታት በኋላ ነው። በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ በመቋቋሙ ይሖዋ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮችም ከዚህ ልዩ ዝግጅት እንዲጠቀሙ በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዓመት እንዳራዘመ በግልጽ መረዳት ይቻላል።

19. በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ይሖዋ ባዘጋጀው የበጎ ፈቃድ ዘመን መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?

19 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ወራሾች ያልሆኑት በዘመናችን ያሉ የኢየሱስ ተከታዮችስ? ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎችም በተወደደው ሰዓት ከተደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ? አዎን። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ይሖዋ “ከታላቁ መከራ” ተርፈው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ላላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች በጎ ፈቃድ ባሳየበት ዘመን ውስጥ እንዳለን ያመለክታል። (ራእይ 7:​13-17) ስለዚህ ሁሉም ክርስቲያኖች ይሖዋ ፍጽምና ለጎደላቸው ሰዎች በጎ ፈቃዱን እያሳየ ባለበት በዚህ አጭር ጊዜ በሚገባ መጠቀም ይችላሉ።

20. ክርስቲያኖች የይሖዋን ጸጋ አላግባብ ከመጠቀም መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

20 ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ስላዘጋጀው የተወደደ ሰዓት ከመናገሩ በፊት አንድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ክርስቲያኖች ‘የተቀበሉትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳያደርጉት’ ተማጽኗቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:​1 አ.መ.ት ) ስለዚህ ክርስቲያኖች የሚያገኙትን ማንኛውንም አጋጣሚ አምላክን ለማስደሰትና ፈቃዱን ለማድረግ ይጠቀሙበታል። (ኤፌሶን 5:​15, 16) የሚከተለውን የጳውሎስ ማሳሰቢያ መከተላቸው በጣም ጠቃሚ ነው:- “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ።”​—⁠ዕብራውያን 3:12, 13

21. የ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 የመጀመሪያ ክፍል የሚደመደመው በየትኛው የደስታ መግለጫ ነው?

21 ይሖዋና መሲሑ የተለዋወጧቸው ትንቢታዊ ቃላት ሲጠናቀቁ ኢሳይያስ የሚከተለውን የደስታ መግለጫ አሰማ:- “እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፣ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፣ ዘምሩ፣ ምድር ሆይ፣ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፣ እልል በሉ።” (ኢሳይያስ 49:13) የጥንቶቹን እስራኤላውያንም ሆነ ታላቁን የይሖዋ አገልጋይ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሁም የይሖዋን ቅቡዓን አገልጋዮችና ከጎናቸው የተሰለፉትን በዘመናችን ያሉ “ሌሎች በጎች” የሚያጽናኑ እንዴት ያሉ ግሩም ቃላት ናቸው!​—⁠ዮሐንስ 10:​16

ይሖዋ ሕዝቡን አይረሳም

22. ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይረሳ ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

22 ኢሳይያስ አሁን የይሖዋን ቃል ማሰማቱን ይቀጥላል። በግዞት የሚኖሩት እስራኤላውያን የመታከትና ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው በመግለጽ እንዲህ ሲል ተነበየ:- “ጽዮን ግን:- እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች።” (ኢሳይያስ 49:14) ይህ እውነት ነውን? ይሖዋ ሕዝቡን እርግፍ አድርጎ በመተው ከናካቴው ረስቷቸዋልን? ኢሳይያስ የይሖዋ ቃል አቀባይ በመሆን እንዲህ ሲል መናገሩን ቀጠለ:- “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም።” (ኢሳይያስ 49:15) ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምላሽ ነው! አምላክ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር እናት ለልጅዋ ካላት ፍቅር የላቀ ነው። ታማኝ የሆኑትን አገልጋዮቹን ዘወትር ያስባል። ስማቸው በእጁ ላይ የተቀረጸ ያህል ያስታውሳቸዋል:- “እነሆ፣ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፣ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።”​—⁠ኢሳይያስ 49:16

23. ጳውሎስ፣ ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይረሳቸው ሙሉ እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ክርስቲያኖችን ያሳሰበው እንዴት ነው?

23 ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” ሲል ክርስቲያኖችን አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ገላትያ 6:9) ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደግሞ የሚከተሉትን አበረታች ቃላት ጽፎላቸዋል:- “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ ሕዝቡን እንደረሳ ሆኖ ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። ልክ እንደ ጥንቷ ጽዮን ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም የሚደሰቱበትና ይሖዋን በትዕግሥት የሚጠባበቁበት በቂ ምክንያት አላቸው። ይሖዋ ቃል ኪዳኑንም ሆነ የሰጠውን ተስፋ መፈጸሙ አይቀርም።

24. ጽዮን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ የምትመለሰው እንዴት ነው? ምን ጥያቄዎችንስ ታነሳለች?

24 ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ሌላ ማጽናኛም ሰጥቷል። ‘ጽዮንን ያፈረሷት’ ባቢሎናውያንም ሆኑ ከሃዲ አይሁዶች እንደ ቀድሞው በከተማይቱ ላይ የሚፈጥሩት ስጋት አይኖርም። የጽዮን “ልጆች” ማለትም ከይሖዋ ጎን በታማኝነት የቆሙ በግዞት የሚኖሩ አይሁዳውያን “ይፈጥናሉ፤ ” ‘በአንድነትም ይሰበሰባሉ። ’ ‘ሙሽራ በጌጥ እንደምትሸለም’ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም በፍጥነት የተመለሱት አይሁዳውያንም ለዋና ከተማቸው ጌጥ ይሆናሉ። (ኢሳይያስ 49:​17, 18) የጽዮን ምድር “ባድማ ” ሆኖ ነበር። ጽዮን ባዶ የነበረው መኖሪያዋ በድንገት በሚያጥለቀልቋት በርካታ ነዋሪዎች ሲጨናነቅ ምን ያህል እንደምትገረም አስበው! (ኢሳይያስ 49:​19, 20ን አንብብ።) እነዚህ ሁሉ ልጆች ከየት እንደመጡ መጠየቋ አይቀርም:- “አንቺም በልብሽ:- የወላድ መካን ሆኛለሁና፣ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝብዤአለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፣ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ።” (ኢሳይያስ 49:21) ባድማ ሆና ለቆየችው ለጽዮን ይህ ምንኛ አስደሳች ይሆናል!

25. በዘመናችን መንፈሳዊ እስራኤል ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ የተመለሰችው እንዴት ነው?

25 እነዚህ ቃላት በዘመናችንም ተፈጽመዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበሩት አስቸጋሪ ዓመታት መንፈሳዊ እስራኤል ተማርካና ውድማ ሆና ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ በመመለስ መንፈሳዊ ገነት ሆናለች። (ኢሳይያስ 35:​1-10) ኢሳይያስ እንደጠቀሳት በአንድ ወቅት ባድማ ሆና እንደነበረችው ከተማ ደስተኛና ትጉ በሆኑ የይሖዋ አምላኪዎች በመጥለቅለቋ ሐሴት አድርጋለች።

“ለአሕዛብ ምልክት”

26. ይሖዋ ነፃ ለወጡት ሕዝቦቹ ምን አመራር ሰጥቷል?

26 ከዚህ በመቀጠል ይሖዋ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ሕዝቡ ከባቢሎን ነፃ ስለሚወጡበት ጊዜ እንዲተነብይ አደረገው። በዚያ ወቅት ሕዝቡ መለኮታዊ አመራር ያገኙ ይሆን? ይሖዋ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል:- “እነሆ፣ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፣ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል።” (ኢሳይያስ 49:22) በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት ቀደም ሲል የመንግሥት መቀመጫ የነበረችውና የይሖዋ ቤተ መቅደስ ይገኝባት የነበረችው የኢየሩሳሌም ከተማ የይሖዋ “ዓላማ” ወይም ምልክት ሆናለች። እንደ “ነገሥታት” እና ‘እቴጌዎች ’ ያሉ ስመጥርና ገናና የሆኑ የሌሎች ብሔራት ሰዎች ሳይቀሩ ወደ ትውልድ አገራቸው ለሚመለሱት እስራኤላውያን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጉላቸዋል። (ኢሳይያስ 49:​23ሀ) ለእስራኤላውያን እርዳታ ካደረጉት ሰዎች መካከል የፋርስ ነገሥታት የሆኑት ቂሮስና አርጤክስስ ሎንጊማነስ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ይገኙበታል። (ዕዝራ 5:​13፤ 7:​11-26) ይሁንና ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ሌላም ፍጻሜ አላቸው።

27. (ሀ) በትንቢቱ የላቀ ፍጻሜ መሠረት አሕዛብ የሚጎርፉት ወደየትኛው “ምልክት” ነው? (ለ) ብሔራት በሙሉ ለመሲሑ አገዛዝ በሚንበረከኩበት ጊዜ ምን ውጤት ይገኛል?

27 ኢሳይያስ 11:​10 “ለአሕዛብ ምልክት” ሆኖ የሚቆም እንደሚኖር ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ቃላት ክርስቶስ ኢየሱስን እንደሚያመለክቱ ጠቁሟል። (ሮሜ 15:​8-12) በመሆኑም በትንቢቱ የላቀ ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ ኢየሱስንና ከእርሱ ጋር አብረው የሚገዙትን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች “ምልክት” አድርጎ ያቆማቸው ሲሆን አሕዛብ ወደ እነርሱ ይጎርፋሉ። (ራእይ 14:​1) ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን የገዢ መደቦች ጨምሮ የምድር አሕዛብ ሁሉ ለመሲሑ አገዛዝ ይንበረከካሉ። (መዝሙር 2:​10, 11፤ ዳንኤል 2:​44) ውጤቱስ ምን ይሆናል? ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፣ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም።”​—⁠ኢሳይያስ 49:23ለ

“መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአል”

28. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቡ ነፃ እንደሚወጡ በድጋሚ ያረጋገጠው ምን በማለት ነው? (ለ) ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቡን በተመለከተ የትኛውን ቃሉን ይጠብቃል?

28 በባቢሎን በግዞት ከሚኖሩት መካከል አንዳንዶቹ ‘እውን እስራኤል ነፃ ልትወጣ ትችላለች?’ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። ይሖዋ ይህን ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ ሲል ይጠይቃል:- “በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን?” (ኢሳይያስ 49:24) መልሱ አዎን፣ የሚል ነው። ይሖዋ እንዲህ ሲል ያረጋግጥላቸዋል:- “በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፣ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል።” (ኢሳይያስ 49:​25ሀ) ይህ እንዴት ያለ የሚያጽናና ዋስትና ነው! ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሕዝቡ በጎ ፈቃድ ለማሳየት ብቻ ሳይሆን ጥበቃም ለማድረግ ቃል ገብቷል። በማያሻማ ቃል እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፣ ልጆችሽንም አድናለሁ።” (ኢሳይያስ 49:25ለ) ይህ ቃል ዛሬም እንደተጠበቀ ነው። በ⁠ዘካርያስ 2:​8 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ‘የሚነካችሁ የዓይኔን ብሌን የሚነካ ነውና’ ሲል ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ዛሬ አምላክ በጎ ፈቃዱን እያሳየ ባለበት ዘመን ላይ የምንገኝ በመሆኑ በምድር ዙሪያ ያሉ ሰዎች ወደ መንፈሳዊቷ ጽዮን መጉረፍ የሚችሉበት አጋጣሚ አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ የበጎ ፈቃድ ዘመን የሚያከትምበት ጊዜ ይመጣል።

29. ይሖዋን ለመታዘዝ አሻፈረን የሚሉ ሰዎች ምን አስፈሪ ዕጣ ይጠብቃቸዋል?

29 ይሖዋን ለመታዘዝ አሻፈረን የሚሉ አልፎ ተርፎም በአምላኪዎቹ ላይ ስደት የሚያመጡ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፣ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ።” (ኢሳይያስ 49:​26ሀ) ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ጊዜ እጅግ አስፈሪ ነው! እንዲህ ያሉት እምቢተኛ የሆኑ ተቃዋሚዎች የሚጠብቃቸው ዕጣ ጥፋት ነው። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን በማዳንና ጠላቶቻቸውን በማጥፋት አዳኝ መሆኑን ያስመሰክራል። “ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፣ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።”​—⁠ኢሳይያስ 49:26ለ

30. ይሖዋ ሕዝቡን ለማዳን ምን እርምጃዎችን ወስዷል? ወደፊትስ ምን እርምጃ ይወስዳል?

30 እነዚህ ቃላት የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ይሖዋ ቂሮስን በመጠቀም ሕዝቡን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ባወጣቸው ጊዜ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በ1919 ይሖዋ በዙፋን ላይ የተቀመጠውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመጠቀም ሕዝቡን ከመንፈሳዊ ባርነት ባላቀቀበት ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ አዳኝ እንደሆኑ ይናገራል። (ቲቶ 2:​11-13፤ 3:​4-6) ይሖዋ አዳኛችን ሲሆን መሲሑ ኢየሱስ ደግሞ ‘ዋነኛ ወኪሉ [NW ]’ ነው። (ሥራ 5:​31) በእርግጥም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የወሰዳቸው የማዳን እርምጃዎች እጅግ አስደናቂ ናቸው። ይሖዋ በምሥራቹ አማካኝነት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት ባርነት ነፃ ያወጣል። በቤዛው መሥዋዕት አማካኝነት ደግሞ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ያላቅቃቸዋል። በ1919 የኢየሱስን ወንድሞች ከመንፈሳዊ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። በጣም እየቀረበ ባለው የአርማጌዶን ጦርነት ደግሞ እጅግ ብዙ የሆኑ ታማኝ ሰዎችን በኃጢአተኞች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ያድናቸዋል።

31. ክርስቲያኖች የአምላክን በጎ ፈቃድ ማግኘታቸው ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል?

31 እንግዲያው የአምላክን በጎ ፈቃድ ማግኘት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሁላችንም ይህን የተወደደ ሰዓት በጥበብ እንጠቀምበት። በተጨማሪም ያለንበት ጊዜ አጣዳፊ መሆኑን በመገንዘብ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች የጻፈውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናድርግ:- “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፣ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፣ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።”​—⁠ሮሜ 13:11-14

32. የአምላክ ሕዝቦች ምን ዋስትና ተሰጥቷቸዋል?

32 ይሖዋ አሁንም ቢሆን ምክሩን ለሚከተሉ ሰዎች ሞገሱን ያሳያል። የምሥራቹን ስብከት ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ብርታትና ችሎታ ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) ይሖዋ የሕዝቡ መሪ የሆነውን ኢየሱስን እንደተጠቀመበት ሁሉ አገልጋዮቹንም ይጠቀምባቸዋል። በምሥራቹ መልእክት አማካኝነት ቅን የሆኑ ሰዎችን ልብ መንካት እንዲችሉ አፋቸውን “እንደ ተሳለ ሰይፍ” ያደርገዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ሕዝቡን “በእጁ ጥላ” ይጠብቃቸዋል። “እንደ ተሳለ ፍላጻ” ‘በሰገባው ውስጥ ይሸሽጋቸዋል።’ በእርግጥም ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም!​—⁠መዝሙር 94:​14፤ ኢሳይያስ 49:​2, 15

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 “ሰይጣን፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው መሠረት ራሱን እንደሚቀጠቅጠው (ዘፍ 3:​15) በመገንዘብ ኢየሱስን ለማጥፋት ያልሸረበው ሴራ የለም። ይሁን እንጂ መልአኩ ገብርኤል ማርያም ኢየሱስን እንደምትጸንስ ባስታወቃት ጊዜ እንዲህ ብሏት ነበር:- ‘መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።’ (ሉቃስ 1:35) ይሖዋ ልጁን ጠብቆታል። ኢየሱስን በሕፃንነቱ ለመግደል የተደረገው ሙከራ ሁሉ ሳይሳካ ቀርቷል።”​—⁠ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 868፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሲሑ በይሖዋ ሰገባ ውስጥ እንዳለ ‘የተሳለ ፍላጻ’ ነው

[በገጽ 141 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሲሑ “ለአሕዛብ ብርሃን” ሆኖ አገልግሏል

[በገጽ 147 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር እናት ለልጅዋ ካላት ፍቅር የላቀ ነው