በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”!

“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”!

ምዕራፍ አራት

“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”!

ኢሳይያስ 43:​1-28

1. ይሖዋ ትንቢት የሚናገረው ለምን ዓላማ ነው? ሕዝቡስ ፍጻሜ ያገኙትን ትንቢቶች በተመለከተ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

እውነተኛውን አምላክ ከሌሎች የሐሰት አማልክት የሚለየው አንዱ ነገር ስለ ወደፊቱ ጊዜ የመተንበይ ችሎታው ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ትንቢት የሚናገረው አምላክነቱን ለማረጋገጥ በማሰብ ብቻ አይደለም። በኢሳይያስ ምዕራፍ 43 ላይ በግልጽ እንደተንጸባረቀው አምላክነቱንና ለቃል ኪዳን ሕዝቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽም ይጠቀምበታል። ሕዝቡም የትንቢቶቹን ፍጻሜ ካስተዋሉ በኋላ ዝም ማለት የለባቸውም። ስላዩት ነገር መመሥከር ይጠበቅባቸዋል። አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች መሆን አለባቸው!

2. (ሀ) በኢሳይያስ ዘመን የእስራኤላውያን መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ይሖዋ የሕዝቡን ዓይን የሚከፍተው እንዴት ነው?

2 የሚያሳዝነው ግን በኢሳይያስ ዘመን እስራኤላውያን የነበሩበት ሁኔታ በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሣ ይሖዋ ሕዝቡን መንፈሳዊ እክል እንዳለበት አድርጎ ተመልክቶታል። “ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፣ ጆሮችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ።” (ኢሳይያስ 43:8) በመንፈሳዊ ዕውርና ደንቆሮ የሆነ ሕዝብ እንዴት ለይሖዋ ሕያው ምሥክር ሆኖ ሊያገለግል ይችላል? ይህ ሊሆን የሚችለው ዓይኖቻቸውና ጆሮዎቻቸው በተአምራዊ ሁኔታ ከተከፈቱ ብቻ ነው። ደግሞም ይሖዋ ይከፍትላቸዋል! እንዴት? በመጀመሪያ ይሖዋ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ይሰጣቸዋል። የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ነዋሪዎች በ740 ከዘአበ የይሁዳ ነዋሪዎች ደግሞ በ607 ከዘአበ በምርኮ ተግዘዋል። ከዚያ በኋላ ይሖዋ መንፈሳዊ ኃይላቸው የታደሰና ንስሐ የገቡ ቀሪዎች በ537 ከዘአበ ነፃ ወጥተው ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል የኃይል እርምጃ ይወስዳል። እንዲያውም ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለው ዓላማ ፍጻሜውን ስለ ማግኘቱ ፍጹም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሣ የእስራኤልን ነፃ መውጣት በተመለከተ ከ200 ዓመታት በፊት ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ ተናግሯል።

3. ይሖዋ ወደፊት ግዞተኛ ለሚሆኑት ሰዎች ምን ማበረታቻ ሰጥቷል?

3 “ያዕቆብ ሆይ፣ የፈጠረህ፣ እስራኤልም ሆይ፣ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፣ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፣ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፣ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:1-3ሀ

4. ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር መገኘት ምክንያት የሆነው እንዴት ነው? ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በተመለከተስ ለሕዝቡ ምን ዋስትና ሰጥቷል?

4 ይሖዋ የእስራኤል ብሔር የእርሱ ንብረት ስለሆነ ለዚህ ብሔር ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣል። ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ይህ ብሔር እንዲገኝ ያደረገው ይሖዋ ራሱ ነው። (ዘፍጥረት 12:​1-3) በመሆኑም መዝሙር 100:​3 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።” ይሖዋ እስራኤልን የፈጠረና የተቤዠ አምላክ በመሆኑ ወደ ትውልድ አገራቸው በደህና እንዲመለሱ ያደርጋል። እንደ ውኃ፣ ኃይለኛ ወንዝና ንዳድ የሆነ በረሃ ያሉት እንቅፋቶች አይገቷቸውም ወይም ጉዳት አያደርሱባቸውም። ከአንድ ሺህ ዓመት በፊትም ቢሆን እንዲህ ያሉት ነገሮች ቅድመ አያቶቻቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረጉትን ጉዞ አልገቱትም።

5. (ሀ) ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት መንፈሳዊ እስራኤላውያንን የሚያጽናኑት እንዴት ነው? (ለ) ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የሚተባበሩት እነማን ናቸው? በእነማንስ ተመስለዋል?

5 ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን ላሉት በመንፈስ የተወለዱና “አዲስ ፍጥረት” የሆኑ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችም ማጽናኛ ይሆናሉ። (2 ቆሮንቶስ 5:​17) “በውኃ” የተመሰለውን የሰው ዘር በድፍረት በተጋፈጡ ጊዜ አምላክ ከምሳሌያዊው ጎርፍ ልዩ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ጠላቶቻቸው የለኮሱትም እሳት እንዲጠሩ አደረጋቸው እንጂ አልጎዳቸውም። (ዘካርያስ 13:​9፤ ራእይ 12:​15-17) ከአምላክ መንፈሳዊ ብሔር ጋር የተባበሩት ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑት ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ የይሖዋን ጥበቃና እንክብካቤ አግኝተዋል። (ራእይ 7:​9፤ ዮሐንስ 10:​16) እነዚህ ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር ከግብጽ በወጡት “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እና ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከወጡት አይሁዳውያን ጋር በተመለሱት አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ተመስለዋል።​​—⁠⁠ዘጸአት 12:​38፤ ዕዝራ 2:​1, 43, 55, 58

6. ይሖዋ (ሀ) ሥጋዊ እስራኤላውያንን (ለ) መንፈሳዊ እስራኤላውያንን በመቤዠት በኩል የፍትሕ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ የሜዶንንና የፋርስን ሠራዊት በመጠቀም ሕዝቡን ከባቢሎን ነፃ እንደሚያወጣ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 13:​17-19፤ 21:​2, 9፤ 44:​28፤ ዳንኤል 5:​28) ይሖዋ የፍትሕ አምላክ እንደመሆኑ መጠን “ላገለገሉት” ሜዶ ፋርሳውያን በእስራኤል ፋንታ ተገቢውን ቤዛ ይከፍላቸዋል። “ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፣ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፣ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ።” (ኢሳይያስ 43:​3ለ, 4) የፋርስ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ አምላክ በትንቢት ባስነገረው መሠረት ግብጽን፣ ኢትዮጵያንና በአቅራቢያው የነበረችውን የሳባን ግዛት በቁጥጥሩ ሥር አስገብቶ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። (ምሳሌ 21:​18) በተመሳሳይም በ1919 ይሖዋ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለዚህ አገልግሎቱ ወሮታ አላስፈለገውም። እርሱ አረማዊ ገዥ አይደለም። ደግሞም ነፃ ያወጣው የገዛ መንፈሳዊ ወንድሞቹን ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ በ1914 ‘አሕዛብን ለርስቱ፣ የምድርንም ዳርቻ ለግዛቱ ሰጥቶታል።’​​—⁠⁠መዝሙር 2:​8

7. ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ ስላሉት ሕዝቦቹ ምን ይሰማዋል?

7 ይሖዋ ከምርኮ ስለተቤዣቸው ሰዎች የሚሰማውን ፍቅራዊ ስሜት እንዴት በግልጽ እንዳስቀመጠ ልብ በል። በፊቱ ‘የከበሩና’ ‘የተመሰገኑ’ እንደሆኑ እንዲሁም ‘እንደሚወዳቸው’ ነግሯቸዋል። (ኤርምያስ 31:​3) ዛሬ ላሉት ታማኝ አገልጋዮቹ የሚኖረውም ስሜት ከዚህ የላቀ እንጂ ያነሰ አይደለም። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የተዛመዱት በዘር ሐረጋቸው ሳይሆን ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው ከወሰኑ በኋላ ባገኙት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ነው። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ወደ ልጁና ወደ ራሱ በመሳብ ሕጎቹንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን እሺ ባይ በሆነው ልባቸው ላይ ጽፏል።​​—⁠⁠ኤርምያስ 31:​31-34፤ ዮሐንስ 6:​44

8. ይሖዋ ለግዞተኞቹ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷል? የሚያገኙትን ነፃነት በተመለከተስ ምን ይሰማቸዋል?

8 ይሖዋ ለግዞተኞቹ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፣ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን:- መልሰህ አምጣ፣ ደቡብንም:- አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፣ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።” (ኢሳይያስ 43:​5-7 ) ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ነፃ በማውጣት ወደ ተወደደች ትውልድ አገራቸው የሚመልስበት ጊዜ ሲደርስ ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች ያሉት ሕዝቦቹ እንኳ ለእርሱ ሩቅ አይሆኑበትም። (ኤርምያስ 30:​10, 11) በዚህ ጊዜ የሚያገኙትን ነፃነት ብሔሩ ቀደም ሲል ከግብጽ ባርነት በተላቀቀበት ወቅት ካገኘው ነፃነት አስበልጠው እንደሚያዩት ምንም ጥርጥር የለውም።​​—⁠⁠ኤርምያስ 16:​14, 15

9. ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት የሚወስደውን እርምጃ ከስሙ ጋር ያያያዘው በምን ሁለት መንገዶች ነው?

9 ይሖዋ በስሙ የተጠሩ መሆናቸውን ለሕዝቡ በማስታወስ እስራኤልን ነፃ ለማውጣት የገባውን ቃል በድጋሚ ያረጋግጣል። (ኢሳይያስ 54:​5, 6) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ እነርሱን ነፃ ለማውጣት የገባውን ቃል ከስሙ ጋር አያይዞታል። ይህን ያደረገው ትንቢታዊው ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ክብሩ ለእርሱ እንዲሰጥ ነው። በባቢሎን ላይ ድል የተቀዳጀው ተዋጊ እንኳ ሕያው ለሆነው አንድ አምላክ ሊሰጥ የሚገባው ክብር ለእኔ መሰጠት አለበት ብሎ ሊከራከር አይችልም።

አማልክት በችሎት ፊት

10. ይሖዋ በብሔራትና በአማልክታቸው ፊት ያቀረበው ፈተና ምንድን ነው?

10 ይሖዋ እስራኤልን ነፃ ለማውጣት የገባውን ቃል መሠረት በማድረግ የአሕዛብ አማልክትን በአንድ አጽናፈ ዓለማዊ ችሎት ፊት ያቀርባቸዋል። ዘገባው እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው [ከአማልክታቸው መካከል] ይህን የሚናገር፣ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? [አማልክታቸው] ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፣ ሰምተውም:- እውነት ነው ይበሉ።” (ኢሳይያስ 43:​9 ) ይሖዋ ለዓለም ብሔራት ያቀረበው ጥያቄ እንዲህ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም። በሌላ አባባል ‘አማልክታችሁ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል በመተንበይ አማልክት መሆናቸውን ያረጋግጡ’ እያላቸው ነበር። ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ሊተነብይ የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ በመሆኑ ይህ ፈተና አስመሳዮችን ሁሉ የሚያጋልጥ ነው። (ኢሳይያስ 48:​5) ይሁን እንጂ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሌላም ሕጋዊ መሠረት ያለው የመከራከሪያ ነጥብ አቅርቧል። እውነተኛ አምላክ ነን የሚሉ ሁሉ ስለተናገሯቸው ትንቢቶችና እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ስለማግኘታቸው ምሥክር እንዲያቀርቡ ጠይቋል። ይሖዋ ራሱንም ቢሆን ከዚህ ሕጋዊ መስፈርት ነፃ አላደረገም።

11. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሰጠው ተልዕኮ ምንድን ነው? ስለ አምላክነቱስ ምን ነገር ገልጧል?

11 የሐሰት አማልክት ምንም ነገር የማድረግ ችሎታ ስለሌላቸው ምሥክሮች ማቅረብ አይችሉም። በመሆኑም ምሥክር ሆኖ የሚቀርብ አንድም ሰው በመጥፋቱ ያፍራሉ። አሁን ደግሞ ይሖዋ በተራው አምላክነቱን የሚያስመሰክርበት ጊዜ ደርሷል። ወደ ሕዝቡ በመመልከት እንዲህ ይላል:- “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፣ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ . . .፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፣ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣ . . . እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፣ [እጄን] የሚከለክልስ ማን ነው?”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:10-13

12, 13. (ሀ) የይሖዋ ሕዝብ ምን ምሥክርነት መስጠት ይጠበቅበታል? (ለ) በዘመናችን የይሖዋ ስም የገነነው እንዴት ነው?

12 ለዚህ የይሖዋ ቃል ምላሽ በመስጠት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደስተኛ የሆኑ ምሥክሮች የምሥክርነት ቃል መስጫ ቦታውን ያጥለቀልቁታል። የሚሰጡት ምሥክርነት ግልጽና የማይታበል ነው። እንደ ኢያሱ ሁሉ እነርሱም ‘ይሖዋ የተናገረው በሙሉ እንደተፈጸመና ከቃሉ አንዳች እንዳልቀረ’ ይመሠክራሉ። (ኢያሱ 23:​14) በይሖዋ ሕዝብ ጆሮ የሚያቃጭለው ነገር ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ሌሎችም ነቢያት እንደ አንድ ሰው ሆነው ስለ አይሁዳውያን ግዞትና በተአምራዊ መንገድ ነፃ ስለሚወጡበት ሁኔታ የተናገሩት ትንቢት ነው። (ኤርምያስ 25:​11, 12) አይሁዳውያንን ነፃ ያወጣው ቂሮስ በስም የተጠቀሰው ገና ከመወለዱ በፊት ነው!​—⁠ኢሳይያስ 44:​26 – 45:1

13 ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን ማን ሊክድ ይችላል? ይሖዋ እንደ አረማዊ አማልክት ፍጡር አይደለም። * ከዚህ የተነሣ የይሖዋን ስም የተሸከሙት ሰዎች ስለ እርሱ ድንቅ ሥራዎች ወደፊት ለሚመጡት ትውልዶችም ሆነ ለሚጠይቋቸው ሁሉ የመንገር ልዩና አስደሳች መብት አግኝተዋል። (መዝሙር 78:​5-7) ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በተመሳሳይ በምድር ዙሪያ የይሖዋን ስም የማወጅ መብት አግኝተዋል። በ1920ዎቹ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ያለውን ጥልቅ ትርጉም ተገነዘቡ። ከዚያም በሐምሌ 26, 1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ “አዲስ ስም” የሚል ርዕስ ያለው የአቋም መግለጫ አቀረበ። “የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መታወቅና በዚህ ስም መጠራት እንፈልጋለን” የሚሉት ቃላት የስብሰባውን ተካፋዮች በሙሉ ያስደሰቱ ሲሆን በሚያስተጋባ ድምፅ “አዎን!” በማለት የአቋም መግለጫውን መደገፋቸውን አሳይተዋል። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ስም በዓለም ዙሪያ በሰፊው ሊታወቅ ችሏል።​​—⁠⁠መዝሙር 83:​18 NW

14. ይሖዋ፣ እስራኤላውያን የትኛውን ጉዳይ መለስ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል? ይህ ማሳሰቢያ ወቅታዊ የነበረውስ ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ስሙን በክብር የተሸከሙትን ሰዎች ‘እንደ ዓይኑ ብሌን’ ይንከባከባቸዋል። ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውና በምድረ በዳ እንዴት ተንከባክቦ እንደመራቸው በመግለጽ እስራኤላውያን ይህን ጉዳይ መለስ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። (ዘዳግም 32:​10, 12) በዚያ ወቅት የግብጻውያን አማልክት በሙሉ እንዴት እንደተዋረዱ በገዛ ዓይናቸው አይተው ስለነበር በመካከላቸው ባዕድ አማልክት አልነበሩም። አዎን፣ የግብጻውያን አማልክት ግብጽን መከላከልም ሆነ እስራኤላውያን እንዳይሄዱ ማገድ ሳይችሉ ቀርተዋል። (ዘጸአት 12:​12) በተመሳሳይም ኃያሏ ባቢሎን በትንሹ እስከ 50 የሚደርሱ የሐሰት አማልክት ቤተ መቅደሶች ቢኖሯትም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕዝቡን ነፃ በሚያወጣበት ጊዜ እጁን መከልከል አትችልም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ከይሖዋ በቀር “የሚያድን የለም።”

የጦር ፈረሶች ይወድቃሉ፣ የእስር ቤት በሮችም ይከፈታሉ

15. ይሖዋ ባቢሎንን በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?

15 “የእስራኤል ቅዱስ፣ የሚቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፣ [“የእስር ቤት መዝጊያዎችንም እሰባብራለሁ፣” NW ] ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፣ የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ፣ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፣ አይነሡም፤ ቀርተዋል፣ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:14-17

16. ባቢሎን፣ የከለዳውያን ነጋዴዎችና ባቢሎንን ከወራሪው ኃይል ለመታደግ የሚቃጡ ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል?

16 ባቢሎን በግዞት የወሰደቻቸው ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይመለሱ በመከልከሏ ልክ እንደ እስር ቤት ሆናባቸው ነበር። ይሁን እንጂ “በባሕር [በቀይ ባሕር] ውስጥ መንገድን በኃይለኛ ውኃ ውስጥ [በዮርዳኖስ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም] መተላለፊያን” ላደረገው ሁሉን ቻይ አምላክ የባቢሎን መከላከያዎች እንቅፋት አይሆኑበትም። (ዘጸአት 14:​16፤ ኢያሱ 3:​13) የይሖዋ ወኪል የሆነው ቂሮስ ታላቁን የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ተዋጊዎቹ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ያደርጋል። በሺህ የሚቆጠሩ የንግድ ጀልባዎችና የባቢሎናውያንን አማልክት የያዙ ታንኳዎች ይመላለሱባቸው በነበሩት የባቢሎን ውኃዎች ላይ የሚቀዝፉት የከለዳውያን ነጋዴዎች ታላቋ ከተማቸው በምትወድቅበት ጊዜ በኃዘን ይዋጣሉ። በቀይ ባሕር እንደሰጠሙት የፈርዖን ሰረገሎች ሁሉ ፈጣኖቹ የባቢሎን ሠረገላዎችም ምንም የማይፈይዱ ይሆናሉ። ባቢሎንን ሊያድኗት አይችሉም። ወራሪው ሠራዊት የጧፍ ኩስታሪን ማጥፋት ቀላል የሆነውን ያህል የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ የሚቃጣውን ማንኛውንም ኃይል ወዲያውኑ ይደመስሳል።

ይሖዋ ሕዝቡን በሰላም ወደ አገራቸው ይመልሳል

17, 18. (ሀ) ይሖዋ ምን “አዲስ” ነገር እንደሚያከናውን ተንብዮአል? (ለ) ይሖዋ ሕዝቦቹን “የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

17 ይሖዋ ቀደም ሲል ሕዝቡን ለማዳን የወሰዳቸውን እርምጃዎች አሁን ሊያደርግ ካለው ነገር ጋር በማወዳደር እንዲህ ይላል:- “የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፣ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፣ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፣ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ። ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፣ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፣ ቀበሮችና ሰጎኖች፣ ያከብሩኛል።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:18-21

18 ይሖዋ “የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ” በማለት ሲናገር አገልጋዮቹ በፊት የወሰደውን የማዳን እርምጃ ከአእምሮአቸው እንዲያወጡት መናገሩ አልነበረም። እንዲያውም ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ብዙዎቹ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ይሖዋም ከግብጽ ነፃ የወጡበት ጊዜ በየዓመቱ የማለፍ በዓል ተብሎ እንዲከበር አዝዞ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:​5፤ ዘዳግም 16:​1-4) ይሁን እንጂ አሁን ይሖዋ የፈለገው በሚያከናውነው “አዲስ ነገር” ማለትም ሕዝቡ ራሳቸው በዓይናቸው በሚያዩት ክስተት እንዲያከብሩት ነው። ይህ ደግሞ ከባቢሎን ነፃ መውጣታቸውን ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ቀጥተኛ በሆነው በረሃማ መንገድ በኩል አልፈው ወደ ትውልድ አገራቸው የሚያደርጉትን ተአምራዊ ጉዞ ጭምር የሚያካትት ነው። በዚያ ጠፍ ምድር ይሖዋ “መንገድን” ያዘጋጅላቸዋል። እንዲሁም በሙሴ ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያን ያደረገላቸውን ነገር የሚያስታውስ ድንቅ ሥራ ያከናውናል። ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱትን ሰዎች በበረሃ እንደሚመግባቸውና ወንዞችን በማፍሰስ ጥማቸውን እንደሚያረካላቸው ምንም አያጠራጥርም። የይሖዋ ዝግጅቶች እጅግ የተትረፈረፉ ከመሆናቸው የተነሣ የዱር አራዊት ሳይቀሩ አምላክን በማክበር ሕዝቡ ላይ ጉዳት ከማድረስ ይታቀባሉ።

19. የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችና ተባባሪዎቻቸው ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ የሚጓዙት እንዴት ነው?

19 የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎችም በ1919 ከባቢሎናዊ ምርኮ ነፃ ወጥተው ይሖዋ ባዘጋጀላቸው “የተቀደሰ መንገድ” ተጉዘዋል። (ኢሳይያስ 35:​8) እነርሱ እንደ እስራኤላውያን ቃል በቃል በሚያቃጥል በረሃ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ አላስፈለጋቸውም። ጉዟቸውም ከጥቂት ወራት መንገድ በኋላ ኢየሩሳሌም በመድረስ የሚጠናቀቅ ዓይነት አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ “የተቀደሰ መንገድ” ቀሪዎቹን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ መንፈሳዊ ገነት መርቷቸዋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያደርጉት ጉዞ ገና ያላበቃ በመሆኑ አሁንም ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ በመጓዝ ላይ ናቸው። በዚህ ጎዳና ላይ መጓዛቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ወይም በሌላ አባባል ይሖዋ ያወጣውን የንጽሕናና የቅድስና መስፈርት እስከጠበቁ ድረስ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይኖራሉ። ከዚህም በተጨማሪ “እስራኤላዊ ያልሆኑ” እጅግ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጋር በመተባበራቸው በጣም ተደስተዋል! እምነታቸውን በሰይጣን ሥርዓት ላይ የጣሉ ሰዎች በመንፈሳዊ ሲራቡ ቅቡዓኑና ተባባሪዎቻቸው ግን ከይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ማዕድ እየተቋደሱ ነው። (ኢሳይያስ 25:​6፤ 65:​13, 14) እንደ አውሬ ያለ ጠባይ የነበራቸው ብዙ ሰዎች ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ያፈሰሰውን በረከት በማስተዋልና መንገዳቸውን በመለወጥ እውነተኛውን አምላክ አክብረዋል።​​—⁠⁠ኢሳይያስ 11:​6-9

ይሖዋ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ

20. በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋን ያሳዘኑት እንዴት ነው?

20 በጥንት ዘመን ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት የእስራኤል ቀሪዎች በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው ክፉ ትውልድ አንጻር ሲታይ በሕይወታቸው ጥሩ ለውጥ ያደረጉ ሰዎች ነበሩ። ይሖዋ በኢሳይያስ ዘመን የነበረውን ክፉ ትውልድ በተመለከተ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ያዕቆብ ሆይ፣ አንተ ግን አልጠራኸኝም፣ አንተም እስራኤል ሆይ፣ በእኔ ዘንድ ደክመሃል [“የእኔ ነገር ታክቶሃል፣” አ.መ.ት ]። ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቁርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም አላደከምሁህም። ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ [“እንዳገለግልህ አደረግኸኝ፣” NW ]፣ በበደልህም አደከምኸኝ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:22-24

21, 22. (ሀ) ይሖዋ የሚጠይቀው ነገር ሸክም አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሕዝቡ ይሖዋ እንዲያገለግላቸው ያደረጉት ያህል ነበር ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

21 ይሖዋ “በእህልም ቁርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም [“በነጭ ዕጣንም፣” NW ] አላደከምሁህም” ሲል መሥዋዕትና ነጭ ዕጣን (በቅዱስ ዕጣን ውስጥ የሚጨመር ነው) አያስፈልጉም ማለቱ አልነበረም። እነዚህ ነገሮች በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ይከናወን የነበረው እውነተኛ አምልኮ አብይ ክፍል ናቸው። በቁጥር 24 ላይ “ዕጣን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የሚሾሙ ሰዎችን ለመቀባት የሚያገለግለው ቅዱስ ዘይት ጣፋጭ መዓዛ እንዲኖረው የሚጨመረውን ጥሩ ሽታ ያለውን ቅመም የሚያመለክት ሲሆን ይህም ቢሆን የእውነተኛው አምልኮ አብይ ክፍል ነበር። እስራኤላውያን በቤተ መቅደሱ አገልግሎት እነዚህን ነገሮች መጠቀምን ቸል ብለው ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ደንቦች ሸክም ነበሩን? በፍጹም! ይሖዋ የሚጠይቀው ነገር የሐሰት አማልክት ከሚጠይቁት ነገር ጋር ሲወዳደር በጣም ቀላል ነበር። ለምሳሌ ያህል የሐሰት አምላክ የሆነው ሞሎክ እንደሚያደርገው ይሖዋ ልጆቻቸውን መሥዋዕት እንዲያደርጉ ፈጽሞ ጠይቆ አያውቅም!​​—⁠⁠ዘዳግም 30:​11፤ ሚክያስ 6:​3, 4, 8

22 እስራኤላውያን መንፈሳዊ ማስተዋል ቢኖራቸው ኖሮ ‘የይሖዋ ነገር ባልታከታቸው’ ነበር። በሕጉ ላይ የተንጸባረቀውን ይሖዋ ለእነርሱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በማስተዋል ‘ስቡን’ ማለትም ምርጥ የሆነውን መሥዋዕታቸውን በደስታ ያቀርቡለት ነበር። ሆኖም እንደዚህ በማድረግ ፋንታ በስስት ስቡን ለራሳቸው አስቀርተዋል። (ዘሌዋውያን 3:​9-11, 16) ይህ ክፉ ብሔር በኃጢአቱ ብዛት ይሖዋን በእጅጉ አሳዝኖት ነበር። በሌላ አባባል ይሖዋ እንዲያገለግላቸው ያደረጉት ያህል ነበር!​​—⁠⁠ነህምያ 9:​28-30

ተግሣጽ ፍሬ አለው

23. (ሀ) ይሖዋ ተግሣጽ መስጠቱ የተገባ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ለእስራኤል የሰጠው ተግሣጽ ምን ነገርን ይጨምራል?

23 ይሖዋ ከባድ ተግሣጽ መስጠቱ የተገባ ነው። ይህ ተግሣጽ ተፈላጊውን ፍሬ የሚያፈራ ከመሆኑም በላይ ምሕረት ሊያስገኝ የሚችል ነው። “መተላለፍህን:- ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም። አሳስበኝ፣ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር። ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፣ መምህሮችህም [“ተርጓሚዎችህም፣” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] በድለውኛል። ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስሁ፣ ያዕቆብንም እርግማን [‘ለጥፋት እዳርጋለሁ፣’ አ.መ.ት ]፣ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።” (ኢሳይያስ 43:25-28) በዓለም ላይ እንዳሉት ሌሎች ብሔራት ሁሉ እስራኤልም የተገኘው ‘ከፊተኛው አባት’ ማለትም ከአዳም ነው። በመሆኑም የትኛውም እስራኤላዊ ቢሆን ‘ጻድቅ ነኝ’ ሊል አይችልም። የእስራኤል “መምህሮች” ማለትም የሕጉ አስተማሪዎች ወይም ተርጓሚዎች እንኳ ሳይቀሩ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሰርተዋል፤ ሐሰትንም አስተምረዋል። ከዚህ የተነሣ ይሖዋ ብሔሩን “ለጥፋት” እና ‘ለስድብ’ አሳልፎ ይሰጣል። ‘በመቅደሱ’ የሚያገለግሉትንም ሁሉ ያረክሳል።

24. ይሖዋ ጥንት የነበረውንም ሆነ ዛሬ ያለውን ሕዝቡን ይቅር የሚልበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? ሆኖም ለሕዝቡ ምን ዓይነት ስሜት አለው?

24 ይሁንና እስራኤላውያን መለኮታዊ ምሕረት የሚያገኙት እንዲሁ ንስሐ በመግባታቸው ሳይሆን ይሖዋ ለራሱ ሲል የሚያደርገው ነገር እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። አዎን፣ ጉዳዩ የእርሱን ስም የሚነካ ነው። እስራኤላውያንን እስከ መጨረሻ ድረስ በግዞት እንዳሉ ቢተዋቸው ይህን የሚመለከቱ ሰዎች በስሙ ላይ ነቀፋ ሊሰነዝሩ ይችላሉ። (መዝሙር 79:​9፤ ሕዝቅኤል 20:​8-10) ዛሬም በተመሳሳይ ቅድሚያ የሚሰጠው የይሖዋ ስም መቀደስና የሉዓላዊነቱ መረጋገጥ እንጂ የግለሰቦች መዳን አይደለም። ያም ሆኖ ይሖዋ የእርሱን ተግሣጽ ያላንዳች ማንገራገር የሚቀበሉትንና እርሱን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩትን ሰዎች ይወድዳል። እነዚህ ሰዎች ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች የፈጸሙትን መተላለፍና በደል በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር በማለት ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ያሳያል።​​—⁠⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 4:​23, 24

25. በቅርቡ ይሖዋ የሚያከናውነው ታላቅ ሥራ ምንድን ነው? ለዚህ ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?

25 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በቅርቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ከታላቁ መከራ’ በሕይወት አልፈው በጸዳች “አዲስ ምድር” ላይ እንዲኖሩ የሚያስችል አዲስ ነገር በማከናወን ለታማኝ አምላኪዎቹ ያለውን ፍቅር ያሳያል። (ራእይ 7:​14፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13) የይሖዋ ኃይል በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ በማያውቅ መንገድ ሲገለጥ የዓይን ምሥክር ለመሆን ይበቃሉ። ይህ አስተማማኝ ተስፋ ቅቡዓን ቀሪዎችንም ሆነ እጅግ ብዙ ሰዎችን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’ በማለት ከሰጣቸው ታላቅ ተልዕኮ ጋር በየዕለቱ ተስማምተው እንዲመላለሱ የሚያነሳሳቸው ይሆናል!​​—⁠⁠ኢሳይያስ 43:​10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 በብሔራት አፈ ታሪክ ውስጥ ብዙ አማልክት “እንደተወለዱ” እና “ልጆችንም” እንደወለዱ ይነገራል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 48 እና 49 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግላቸዋል

[በገጽ 52 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ይሖዋ ብሔራት ለአምላኮቻቸው ምሥክር እንዲያቀርቡ ጠይቋል

1. ከነሐስ የተሠራ የበኣል ሐውልት 2. ከሸክላ የተሠሩ የአስታሮት ምስሎች 3. ሆረስ፣ ኦሳይረስና አይሲስ የተባሉት የግብጻውያን ሦስት ጥምር አማልክት 4. አቴና (በስተግራ ) እና አፍሮዳይት የተባሉት የግሪክ አማልክት

[በገጽ 58 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’—ኢሳይያስ 43:​10