በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው አምላክ ሕዝቡን ነፃ እንደሚያወጣ ትንቢት ተናገረ

እውነተኛው አምላክ ሕዝቡን ነፃ እንደሚያወጣ ትንቢት ተናገረ

ምዕራፍ አምስት

እውነተኛው አምላክ ሕዝቡን ነፃ እንደሚያወጣ ትንቢት ተናገረ

ኢሳይያስ 44:​1-28

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ምን ጥያቄ አንስቷል? (ለ) ይሖዋ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

‘እውነተኛው አምላክ ማን ነው?’ ይህ በየዘመናቱ ሲነሣ የኖረ ጥያቄ ነው። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ ራሱ ይህን ጥያቄ ማንሳቱ የሚያስገርም ነው! ሰዎች ‘እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው? ወይስ የእርሱን ሥልጣን ሊገዳደር የሚችል ሌላ አምላክ ይኖራል?’ የሚለውን ጉዳይ በጥሞና እንዲመረምሩ ይጋብዛቸዋል። ይሖዋ የውይይት መድረኩን ከከፈተ በኋላ አምላክነትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የሚያስችል ምክንያታዊ የሆነ መመዘኛ ያቀርባል። የቀረበው የመከራከሪያ ነጥብ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ አንድ የማያሻማ መደምደሚያ የሚመራ ነው።

2 በኢሳይያስ ዘመን የተቀረጹ ምስሎችን ማምለክ በሰፊው የተለመደ ነበር። በትንቢታዊው የኢሳይያስ መጽሐፍ 44ኛ ምዕራፍ ውስጥ ሰፍሮ በሚገኘው ግልጽና ቀጥተኛ ማብራሪያ ላይ የተቀረጹ ምስሎችን ማምለክ ከንቱ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል! ይሁንና የአምላክ ሕዝብ ሳይቀር በጣዖት አምልኮ ወጥመድ ወድቋል። ከዚህም የተነሣ ቀደም ባሉት የኢሳይያስ ምዕራፎች ውስጥ እንደተመለከትነው እስራኤላውያን ጠንከር ያለ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ ሕዝቡን ለባቢሎናውያን አሳልፎ የሚሰጣቸው ቢሆንም እንኳ እርሱ ራሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ነፃ እንደሚያወጣቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ከምርኮ ነፃ ስለ መውጣታቸውና ንጹሕ አምልኮ እንደገና ስለሚቋቋምበት ሁኔታ የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል። ይህ ደግሞ በድን የሆኑትን የአሕዛብ አማልክት የሚያገለግሉትን ሰዎች ሁሉ ኃፍረት የሚያከናንብ ይሆናል።

3. የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች የሚጠቅሙት እንዴት ነው?

3 በዚህኛው የኢሳይያስ ምዕራፍ ውስጥ ያሉት ትንቢቶችና በጥንት ዘመን ያገኙት ፍጻሜ ዛሬ ያሉትን ክርስቲያኖች እምነት የሚያጠነክር ነው። ከዚህም በላይ ኢሳይያስ የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት በዘመናችን አልፎ ተርፎም ወደፊት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። በዚህ ጊዜ የሚገለጠው ነፃ አውጪም ሆነ የሚገኘው ነፃነት በጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ዘመን ከተነሳው ነፃ አውጪና ከተገኘው ነፃነት እጅግ የላቀ ነው።

ለይሖዋ ሕዝብ የተዘረጋ ተስፋ

4. ይሖዋ እስራኤላውያንን ያበረታታው እንዴት ነው?

4 በምዕራፍ 44 የመግቢያ ቁጥሮች ላይ እስራኤላውያን በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ የተለዩና የአምላክ አገልጋይ እንዲሆኑ የተመረጡ መሆናቸውን የሚያወሳ ገንቢ ሐሳብ ተጠቅሶ እናገኛለን። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፣ ስማ። የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፣ አትፍራ።” (ኢሳይያስ 44:1, 2) ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ወጥተው በብሔር ደረጃ ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ስለረዳቸው ከማኅፀን ጀምሮ የተንከባከባቸው ያህል ነበር። ሕዝቡን በጥቅሉ “ይሹሩን” በማለት ጠርቷቸዋል። ትርጉሙም “ቅን የሆነ” ማለት ሲሆን ፍቅርንና የጠበቀ የመውደድ ስሜትንም የሚያሳይ መግለጫ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ስም እስራኤላውያን ቅን ሆነው መመላለስ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነበር። እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲህ ካለው የሥነ ምግባር አቋም ፈቀቅ ብለዋል።

5, 6. ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገላቸው መንፈስን የሚያድስ ዝግጅት ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት ይኖረዋል?

5 ይሖዋ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ምንኛ የሚያስደስቱና መንፈስን የሚያድሱ ናቸው! እንዲህ ብሏል:- “በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፣ በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ።” (ኢሳይያስ 44:​3, 4) ሞቃታማና ደረቅ በሆነ ምድር እንኳ ሳይቀር በውኃ ፈሳሽ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሊያብቡ ይችላሉ። ይሖዋ ሕይወት ሰጭ የሆነውን የእውነት ውኃውንና መንፈስ ቅዱሱን ሲያፈስስ እስራኤል በመስኖ ቦይ አጠገብ እንዳሉ ዛፎች እጅግ ይለመልማል። (መዝሙር 1:​3፤ ኤርምያስ 17:​7, 8) ይሖዋ አገልጋዮቹ እውነተኛ አምላክ መሆኑን መመሥከር እንዲችሉ አስፈላጊውን ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።

6 ይሖዋ መንፈሱን በማፍሰሱ አንዳንድ ሰዎች የእስራኤል ሕዝብ ከእርሱ ጋር ያለውን ዝምድና እንደ አዲስ ማድነቅ ይጀምራሉ። በመሆኑም ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ይህ:- እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፣ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም:- እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል።” (ኢሳይያስ 44:​5) አዎን፣ እውነተኛ አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑ ስለሚረጋገጥ በእርሱ ስም መጠራት ክብር ይሆንላቸዋል።

ለአማልክቱ የቀረበ ፈተና

7, 8. ይሖዋ ለአሕዛብ አማልክት ምን ጥያቄ ያቀርብላቸዋል?

7 በሙሴ ሕግ አንድ ሰው በባርነት ቀንበር ሥር በሚወድቅበት ጊዜ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው ሊቤዠው ይችል ነበር። (ዘሌዋውያን 25:​47-54፤ ሩት 2:​20) አሁን ግን እስራኤልን የሚቤዠው ማለትም ብሔሩን አድኖ ባቢሎንንና የሐሰት አማልክቷን በጠቅላላ የኃፍረት ማቅ የሚያከናንበው ይሖዋ ራሱ እንደሆነ ተናግሯል። (ኤርምያስ 50:​34) የሐሰት አማልክቱንና አምላኪዎቻቸውን እንዲህ ይላቸዋል:- “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፣ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፣ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፣ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ። አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሮ አልነገርኋችሁምን ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ [“ዐለት፣” አ.መ.ት ] የለም፤ ማንንም አላውቅም።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:6-8

8 ይሖዋ አማልክቱ ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸዋል። ስለወደፊቱ ጊዜ ሊናገሩ ወይም ወደፊት የሚከናወነውን ነገር አሁን እየተፈጸመ ያለ እስኪመስል ድረስ በፍጹም ትክክለኝነት ሊተነብዩ ይችላሉን? ይህን ማድረግ የማይሳነው ‘ፊተኛና ኋለኛ’ የሆነው አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ የሐሰት አማልክት ገና ሳይታሰቡ በፊት የነበረ ከመሆኑም በላይ እነዚህ አማልክት ፈጽሞ ከተረሱም በኋላ ይኖራል። እንደማይነቃነቅ ትልቅ ዐለት የሆነው ይሖዋ አስፈላጊውን ድጋፍ ስለሚሰጣቸው የአምላክ አገልጋዮች ስለዚህ እውነት ከመመሥከር ወደኋላ የሚሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም!​​—⁠⁠ዘዳግም 32:​4 አ.መ.ት፤ 2 ሳሙኤል 22:​31, 32 አ.መ.ት

የተቀረጹ ምስሎች አምልኮ ከንቱነት

9. እስራኤላውያን ማንኛውንም ዓይነት የሕያዋን ፍጥረታት ምስል እንዳይሠሩ ተከልክለው ነበርን? አብራራ።

9 ይሖዋ ለሐሰት አማልክቱ ያቀረበው ፈተና ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ሁለተኛውን ያስታውሰናል። ይህ ትእዛዝ “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዘጸአት 20:4, 5) እርግጥ ይህ እስራኤላውያን የተለያዩ ምስሎችንና ቅርጾችን ለጌጥነት መጠቀም አይችሉም ማለት አልነበረም። ይሖዋ ራሱ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ የዕፅዋትና የኪሩቤል ምስሎች ተሠርተው እንዲቀመጡ መመሪያ ሰጥቷል። (ዘጸአት 25:​18, 33፤ 26:​31) ይሁን እንጂ እነዚህ ምስሎች ልዩ ክብር የሚሰጣቸው ወይም የሚመለኩ አልነበሩም። ለእነዚህ ምስሎች የሚጸልይም ሆነ መሥዋዕት የሚያቀርብ አልነበረም። መለኮታዊው ትእዛዝ ማንኛውም የተቀረጸ ምስል ለአምልኮ እንዳይውል ይከለክል ነበር። የተቀረጹ ምስሎችን ማምለክ ወይም ለእነርሱ መስገድ የጣዖት አምልኮ ነው።​​—⁠⁠1 ዮሐንስ 5:​21

10, 11. ይሖዋ የተቀረጹ ምስሎችን አሳፋሪ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸው ለምንድን ነው?

10 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ የተቀረጹ በድን ምስሎችን ከንቱነትና እነርሱን የሚሠሩ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ኃፍረት ይገልጻል:- “የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፣ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ ያፍራሉ። አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፣ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፣ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፤ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:9-11

11 አምላክ እነዚህን የተቀረጹ ምስሎች ይህን ያህል አሳፋሪ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ በቁሳዊ ነገሮች መመሰል ፈጽሞ አይቻልም። (ሥራ 17:​29) ከዚህም በላይ ፈጣሪ እያለ የተፈጠረን ነገር ማምለክ የይሖዋን አምላክነት ማቃለል ነው። ደግሞስ ‘በአምላክ መልክ’ የተፈጠረውን ሰው ክብር ዝቅ የሚያደርግ አይሆንምን?​​—⁠⁠ዘፍጥረት 1:​27፤ ሮሜ 1:​23, 25

12, 13. የሰው ልጅ፣ ሊመለክ የሚገባው ምስል ሊሠራ አይችልም የምንለው ለምንድን ነው?

12 አንድ ምስል ለአምልኮ እንዲያገለግል ተብሎ ስለ ተቀረጸ ብቻ ቅድስና ሊላበስ ይችላልን? ኢሳይያስ የተቀረጸ ምስል የሰው እጅ ሥራ እንደሆነ ያሳስበናል። የተቀረጸ ምስል የሚሠራው ሰው የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎችም ሆኑ ዘዴዎች ማንኛውም የእጅ ባለሙያ ከሚጠቀምባቸው የተለዩ አይደሉም:- “ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፣ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፣ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፣ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፣ እርሱም ይራባል ይደክምማል፣ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለካዋል፤ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:12, 13

13 የሰውን ልጅ ጨምሮ በዚህ ምድር ላይ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ የፈጠረው እውነተኛው አምላክ ነው። የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ለይሖዋ አምላክነት ድንቅ ማስረጃዎች ናቸው። ይሁንና አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ ከእርሱ ጋር አይተካከሉም። ታዲያ የሰው ልጅ ከይሖዋ የበለጠ ጥበብና ችሎታ ኖሮት እንደ አምላክ ሊመለክ የሚችል ከራሱ ከሰው የተሻለ ነገር መሥራት ይችላልን? አንድ ሰው ምስል ሲቀርጽ ይደክመዋል፣ ይርበዋል እንዲሁም ይጠማዋል። ይህ ሁኔታ የሰው ልጅ የአቅም ገደብ እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ይሁንና ሌላው ቢቀር የሰው ልጅ ሕያው መሆኑን ያረጋግጣሉ። ባለሙያው የሚያበጀው ቅርጽ የሰው ምስል ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ውብ አድርጎ ይሠራው ይሆናል። ሆኖም ምስሉ ሕይወት ሊኖረው አይችልም። የተቀረጹ ምስሎች በምንም ዓይነት አማልክት ሊሆኑ አይችሉም። ሟች የሆነው የሰው ልጅ ሥራ ውጤት አይደለም ሊባል የሚችል ‘ከሰማይ የወረደ’ ምስል ደግሞ የለም።​​—⁠⁠ሥራ 19:​35

14. ምስሎችን የሚሠሩ ሰዎች የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ የተመካ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

14 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ ምስሎችን የሚሠሩ ሰዎች የሚጠቀሙበት ቁሳቁስም ሆነ የሚሠሩት ነገር ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮችና በተፈጥሮ ሂደት ላይ የተመካ እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፣ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፣ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፣ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፣ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፣ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና:- እሰይ ሞቅሁ፣ እሳቱን አይቻለሁ ይላል። የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ:- አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:14-17

15. የተቀረጸ ምስል የሚሠራ ሰው ጨርሶ ማስተዋል የሌለው ነው የምንለው ለምንድን ነው?

15 የማገዶ እንጨት ሌሎችን ሊያድን ይችላልን? እንዴት አድርጎ! ሰዎችን ሊያድን የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። ሰዎች እንዴት ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች ያመልካሉ? ኢሳይያስ ችግሩ ያለው ሰዎቹ ልብ ላይ መሆኑን ገልጿል:- “አያውቁም፣ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፣ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። በልቡም ማንም አያስብም:- ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፣ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፣ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም። አመድ ይበላል፣ የተታለለ ልብ አስቶታል፣ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፣ ወይም:- በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም።” (ኢሳይያስ 44:​18-20) አዎን፣ የጣዖት አምልኮ የሚያስገኘው መንፈሳዊ ጥቅም ይኖራል ብሎ መጠበቅ ገንቢ የሆነውን ምግብ ትቶ አመድ ከመብላት ተለይቶ አይታይም።

16. የጣዖት አምልኮ የጀመረው እንዴት ነው? ወደዚህስ ሊመራ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

16 ጣዖት አምልኮ የጀመረው፣ ሰይጣን የሚል ስያሜ የተሰጠው ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር በሰማይ ሳለ ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ ለማድረግ በተመኘ ጊዜ ነበር። ያደረበት ምኞት እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ ከአምላክ ጋር አቆራርጦታል። ሐዋርያው ጳውሎስ መጎምጀት ጣዖትን ማምለክ እንደሆነ ስለ ገለጸ ጣዖት አምልኮ የጀመረው ያን ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። (ኢሳይያስ 14:​12-14፤ ሕዝቅኤል 28:​13-15, 17፤ ቆላስይስ 3:​5) ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በራስ ወዳድነት ላይ ብቻ ያተኮሩ ሐሳቦችን እንዲያውጠነጥኑ አድርጓቸዋል። ሔዋን ‘ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ፣ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ’ ሲላት እጅግ ጎመጀች። ኢየሱስ መጎምጀት ከልብ የሚወጣ ሐሳብ እንደሆነ ገልጿል። (ዘፍጥረት 3:​5፤ ማርቆስ 7:​20-23) በልብ ውስጥ ክፉ ሐሳብ ከበቀለ ወደ ጣዖት አምልኮ ሊመራ ይችላል። እንግዲያው ሁላችንም ይሖዋ በልባችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ ለማንም ወይም ለምንም አሳልፈን ላለመስጠት ስንል ‘ልባችንን መጠበቃችን’ ምንኛ አስፈላጊ ነው!​​—⁠⁠ምሳሌ 4:​23፤ ያዕቆብ 1:​14

ይሖዋ ልብ በሚነካ መንገድ ተናገረ

17. እስራኤላውያን ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

17 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ እስራኤላውያኑ ምሥክሮቹ እንደመሆናቸው መጠን ያገኙትን መብትና ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲያስቡ የሚያደርግ ነገር ይነግራቸዋል። እንዲህ ይላል:- “ያዕቆብ ሆይ፣ አንተም እስራኤል፣ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፣ በእኔ ዘንድ ያልተረሳ ትሆናለህ። መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። ሰማያት ሆይ፣ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፣ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፣ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፣ እልል በሉ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:21-23

18. (ሀ) የእስራኤል ሕዝብ የሚደሰትበት ምን ምክንያት ነበረው? (ለ) ዛሬ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች የእርሱን ምህረት መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ይሖዋ እስራኤላውያን የፈጠሩት አምላክ አይደለም። እርሱ የሰው እጅ ሥራ አይደለም። ይልቁንም እስራኤልን የእርሱ የተመረጠ አገልጋይ እንዲሆን የሠራው ይሖዋ ነው። አሁን ደግሞ ብሔሩን ነፃ በማውጣት አምላክነቱን በድጋሚ ያረጋግጣል። ንስሐ ከገቡ ኃጢአታቸውን ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፍንላቸውና መተላለፋቸውንም ጥቅጥቅ ባለ ደመና የተጋረደ ያህል እንደሚሰውርላቸው ማረጋገጫ በመስጠት ሕዝቡን ርኅራኄ በተሞላበት መንፈስ አነጋግሯቸዋል። ይህ የእስራኤልን ሕዝብ ምን ያህል ሊያስደስተው እንደሚችል መገመት ይቻላል! ይህ የይሖዋ ምሳሌ ዛሬ ያሉ አገልጋዮቹ የእርሱን ምሕረት እንዲኮርጁ የሚያነሳሳ ነው። የተሳሳተ ጎዳና የተከተሉትን ለማቅናት በመጣርና በተቻለ መጠን በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደገና በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ በመርዳት የእርሱን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።​​—⁠⁠ገላትያ 6:​1, 2

የክርክሩ መቋጫ

19, 20. (ሀ) ይሖዋ ክርክሩን የሚቋጨው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡን በሚመለከት ምን አስደሳች ትንቢት ተናግሯል? ይህንንስ ለማስፈጸም በማን ይጠቀማል?

19 አሁን ይሖዋ ክርክሩን እጅግ አሳማኝ በሆነ መንገድ ይቋጨዋል። እውነተኛውን አምላክ ለመለየት ለቀረበው ከባድ መመዘኛ የራሱን መልስ ሊሰጥ ነው። መመዘኛው ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል የመተንበይ ችሎታ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን የ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 44 አምስት ቁጥሮች አስመልክተው ሲናገሩ ሁሉን ስለፈጠረው፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በመተንበይ ተወዳዳሪ ስለማይገኝለትና የእስራኤል ብቸኛ የነፃነት ተስፋ ስለሆነው “አምላክ ታላቅነት የሚገልጹ የግጥም ስንኞች” እንደሆኑ ገልጸዋል። ምንባቡ የእስራኤልን ሕዝብ ከባቢሎን ነፃ የሚያወጣውን ሰው በስም በመጥቀስ በአስደናቂ ሁኔታ ይደመድማል።

20 “ከማኅፀን የሠራህ፣ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ሁሉን የፈጠርሁ፣ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፣ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፣ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤ የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፣ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን:- የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፣ የይሁዳንም ከተሞች:- ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ፤ ቀላዩንም:- ደረቅ ሁን፣ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤ ቂሮስንም:- እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን:- ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።”​​—⁠⁠ኢሳይያስ 44:24-28

21. የይሖዋ ቃል ምን ዋስትና ይሰጣል?

21 ይሖዋ ስለወደፊቱ ጊዜ መተንበይ ብቻ ሳይሆን ዓላማውን አንድም ሳይቀር ማስፈጸምም ይችላል። ይህ መግለጫ ለእስራኤላውያን ትልቅ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነበር። የባቢሎን ሠራዊት ምድሪቱን ባድማ ቢያደርጋትም ኢየሩሳሌምና በእርሷ ሥር ያሉት ከተሞች እንደገና እንደሚቆረቆሩና እውነተኛውም አምልኮ በዚያው ተመልሶ እንደሚቋቋም ዋስትና የሚሰጥ ነው። ግን እንዴት?

22. የኤፍራጥስ ወንዝ የደረቀው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

22 የአምላክ መንፈስ ድጋፍ የሌላቸው ምዋርተኞች ጊዜው ሲደርስ ልንጋለጥ እንችላለን ብለው ስለሚፈሩ ትንቢት በሚናገሩበት ጊዜ በዝርዝር ለመናገር አይደፍሩም። ይሖዋ ግን ሕዝቡ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲገነቡ ከምርኮ ነፃ ለማውጣት መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት ሰው ማን እንደሆነ ሳይቀር በኢሳይያስ አማካኝነት ለይቶ ጠቅሷል። ስሙ ቂሮስ ሲሆን የፋርሱ ታላቁ ቂሮስ በሚል ስያሜ ይታወቃል። ይሖዋ፣ ቂሮስ የባቢሎንን ግዙፍና ውስብስብ መከላከያ ጥሶ የሚገባበትን ስልት ሳይቀር በዝርዝር ተናግሯል። ባቢሎን በትላልቅ ቅጥሮች እንዲሁም በከተማዋ ውስጥና በዙሪያዋ በሚፈስሰው ውኃ የተከበበች ትሆናለች። ቂሮስ ለከተማዋ መከላከያ ቁልፍ ድርሻ ያለውን የኤፍራጥስ ወንዝ ለራሱ ዓላማ በሚበጅ መንገድ ይጠቀምበታል። የጥንቶቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ሂሮዶተስ እና ዜኖፎን እንደዘገቡት ቂሮስ ከባቢሎን ትንሽ እልፍ ብሎ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር የውኃው መጠን ወታደሮቹ በእግራቸው ሊሻገሩት እስኪችሉ ድረስ እንዲቀንስ አድርጓል። ባቢሎንን ከመከላከል አንጻር ሲታይ የኤፍራጥስ ወንዝ የደረቀ ያህል ነበር።

23. ቂሮስ እስራኤልን ነፃ እንደሚያወጣ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱን የሚያረጋግጥ ምን ዘገባ አለ?

23 ቂሮስ የአምላክን ሕዝብ እንደሚለቅቅና ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ተመልሰው እንዲገነቡ እንደሚያደርግ ስለተሰጠውስ ተስፋ ምን ማለት ይቻላል? ቂሮስ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኝ አንድ ኦፊሴላዊ አዋጅ እንደሚከተለው ብሏል:- “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል:- የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፣ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ።” (ዕዝራ 1:2, 3) ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት የተናገረው ቃል አንድም ሳይቀር ፍጻሜውን አግኝቷል!

ኢሳይያስ፣ ቂሮስና ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች

24. አርጤክስስ ስለ ‘ኢየሩሳሌም መጠገንና መሠራት’ ባወጣው ትእዛዝና በመሲሑ መምጣት መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

24 የኢሳይያስ መጽሐፍ 44ኛ ምዕራፍ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነና የጥንት ሕዝቦቹን ነፃ የሚያወጣ አምላክ እንደሆነ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ምዕራፍ ነው። ከዚህም በላይ ትንቢቱ ለዘመናችንም ጥልቅ ትርጉም አለው። ቂሮስ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንዲገነባ አዋጅ ካወጣበት ከ538/537 ከዘአበ ጀምሮ የተለያዩ ነገሮች ደረጃ በደረጃ ሲከናወኑ ቆይተው በስተመጨረሻ ላይ አንድ ሌላ አስገራሚ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። ከቂሮስ በኋላ የተነሳው አርጤክስስ የተባለው ገዥ ኢየሩሳሌም እንድትገነባ ሌላ አዋጅ አስነግሯል። የዳንኤል መጽሐፍ “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ [ከ455 ከዘአበ] እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ” እያንዳንዳቸው የ7 ዓመት ርዝማኔ ያላቸው 69 ‘ሣምንታት’ እንደሚያልፉ ይናገራል። (ዳንኤል 9:24, 25) ይህም ትንቢት ቢሆን ፍጻሜውን አግኝቷል። አርጤክስስ ያወጣው አዋጅ በተስፋይቱ ምድር ተግባራዊ ከሆነ ከ483 ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ልክ በታቀደለት ጊዜ ማለትም በ29 እዘአ ተጠምቆ ምድራዊ አገልግሎቱን ጀምሯል። *

25. ባቢሎን በቂሮስ እጅ መውደቋ በዘመናችን ምን ነገር እንደሚከናወን የሚያመለክት ነው?

25 ባቢሎን ስትወድቅ ታማኝ አይሁዳውያን ያገኙት ነፃነት በ1919 ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ለወጡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንቢታዊ ጥላ ሆኖ አገልግሏል። ቅቡዓኑ ነፃ መውጣታቸው ጋለሞታ ተብላ የተገለጸች ሌላ ባቢሎን ማለትም የሐሰት ሃይማኖትን በጥቅሉ የምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን እንደወደቀች የሚያሳይ ነበር። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ዮሐንስ ውድቀቷን አስቀድሞ ተመልክቷል። (ራእይ 14:​8) ድንገተኛ ጥፋት እንደሚመጣባትም በራእይ አይቷል። ዮሐንስ በጣዖት በተሞላችው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የሰጠው መግለጫ ኢሳይያስ፣ ቂሮስ በጥንቷ የባቢሎን ከተማ ላይ ስለሚቀዳጀው ድል ከሰጠው መግለጫ ጋር በአንዳንድ መልኩ ተመሳሳይነት አለው። ባቢሎንን ከጠላት ኃይል ለመጠበቅ እንደ አጥር ሆኖ ያገለግል የነበረው ውኃ ከተማይቱን ከቂሮስ እጅ ሊያስጥላት እንዳልቻለ ሁሉ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚደግፋትና የሚጠብቃት የሰው ዘር ‘ውኃም’ ቢሆን እርሷ ከመጥፋቷ ቀደም ብሎ ‘ይደርቃል።’​​—⁠⁠ራእይ 16:​12 *

26. የኢሳይያስ ትንቢትና ያገኘው ፍጻሜ እምነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?

26 ኢሳይያስ ትንቢቱን ከተናገረ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ካለፉ በኋላም ዛሬ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት በእርግጥም አምላክ ‘የመልእክተኞቹን ምክር እንደሚፈጽም’ እናስተውላለን። (ኢሳይያስ 44:​26) እንግዲያው የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በሙሉ አስተማማኝ መሆናቸውን የሚጠቁም ግሩም ምሳሌ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማገዶ እንጨት ሌሎችን ሊያድን ይችላልን?

[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቂሮስ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ትንቢቱን ፈጽሟል