በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው አምልኮ በዓለም ዙሪያ ይስፋፋል

እውነተኛው አምልኮ በዓለም ዙሪያ ይስፋፋል

ምዕራፍ ሃያ አንድ

እውነተኛው አምልኮ በዓለም ዙሪያ ይስፋፋል

ኢሳይያስ 60:​1-22

1. ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ምን አበረታች መልእክት ይዟል?

የኢሳይያስ መጽሐፍ 60ኛ ምዕራፍ የተጻፈው ስሜት ቀስቃሽ በሆነ ድራማ መልክ ነው። በምዕራፉ የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ የተገለጸው ልብ የሚነካ ትዕይንት ትኩረታችንን ይማርከዋል። ከዚያ ቀጥሎ የተዘረዘሩት እርስ በርሳቸው እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ክንውኖች እጅግ አስደሳች ወደሆነ መደምደሚያ ያደርሱናል። በዚህ ምዕራፍ ላይ የሰፈረው ዘገባ እውነተኛው አምልኮ በጥንቷ ኢየሩሳሌም ዳግመኛ የሚቋቋምበትንና በዘመናችን በዓለም ዙሪያ የሚስፋፋበትን ሁኔታ ውብ በሆነ መንገድ ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ታማኝ አምላኪዎች በሙሉ የሚያገኟቸውን ዘላለማዊ በረከቶች ይጠቁማል። እያንዳንዳችን አስደሳች በሆነው በዚህ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ የበኩላችንን ድርሻ ልናበረክት እንችላለን። እንግዲያው እስቲ ትንቢቱን በጥሞና እንመርምር።

በጨለማ ሥፍራ ብርሃን ፈነጠቀ

2. ጨለማው ውስጥ ለተኛችው ሴት ምን ትእዛዝ ተላልፏል? ይህን ትእዛዝ ማክበሯ አጣዳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

2 በዚህ ምዕራፍ መክፈቻ ላይ የሚገኙት ቃላት እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ላይ ለምትገኝ ሴት የተነገሩ ናቸው። በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠ ሥፍራ መሬት ላይ ደፍት ብላ ተኝታለች። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የሚከተለውን ጥሪ ሲያስተላልፍ በድንገት የበራው ብርሃን ጨለማውን ገፈፈው:- “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፣ አብሪ።” (ኢሳይያስ 60:1) አዎን፣ ‘ሴቲቱ’ መነሳትና የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ይኖርባታል! ይህ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።” (ኢሳይያስ 60:2) ‘ሴቲቱ’ በዙሪያዋ ላሉት በጨለማ የሚደናበሩ ሕዝቦች ጥቅም ስትል ‘ብርሃን ማብራት’ ይኖርባታል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።” (ኢሳይያስ 60:3) በምዕራፉ መግቢያ ላይ የሚገኙት እነዚህ ቃላት በቀጣዮቹ ቁጥሮች ላይ በዝርዝር የሚብራራውን ነጥብ ይኸውም እውነተኛው አምልኮ በዓለም ዙሪያ መስፋፋት እንዳለበት የሚጠቁመውን መሠረታዊ ሐሳብ እንድናስተውል ይረዱናል።

3. (ሀ) ‘ሴቲቱ’ ማን ናት? (ለ) ጨለማ ውስጥ የተኛችው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ እየተናገረ ያለው ወደፊት ስለሚከናወኑ ሁኔታዎች ቢሆንም እንኳ ብርሃኗ ‘እንደመጣ’ ‘ለሴቲቱ’ ገልጾላታል። ይሖዋ እንዲህ ብሎ መናገሩ ትንቢቱ ፍጻሜውን ማግኘቱ እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሰችው ‘ሴት’ የምታመለክተው የይሁዳ መዲና የሆነችውን ጽዮንን ወይም ኢየሩሳሌምን ነው። (ኢሳይያስ 52:​1, 2፤ 60:​14) ከተማዋ ሕዝቡን በጠቅላላ ትወክላለች። ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ባገኘበት ወቅት ‘ሴቲቱ’ በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌም ከጠፋችበት ጊዜ አንስቶ በጨለማ ውስጥ ተኝታ ቆይታለች። ይሁን እንጂ በ537 ከዘአበ ወደ ግዞት ተወስደው የነበሩ ታማኝ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ንጹሕ አምልኮን ዳግመኛ አቋቋሙ። በመጨረሻ ይሖዋ ‘በሴቲቱ’ ላይ ብርሃን በማብራቱ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት ሕዝቦቹ በዙሪያቸው ላሉት መንፈሳዊ ጨለማ የዋጣቸው አሕዛብ የብርሃን ምንጭ ሆነዋል።

የላቀ ፍጻሜ

4. በዛሬው ጊዜ ‘ሴቲቱን’ በምድር ላይ የሚወክሉት እነማን ናቸው? እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት እነማንንም ጭምር ይመለከታሉ?

4 እነዚህን ትንቢታዊ ቃላት የምንመረምረው በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸሙበትን ሁኔታ ለማጤን ብቻ አይደለም። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሰማያዊት ‘ሴት’ በምድር ላይ “በእግዚአብሔር እስራኤል” ተወክላለች። (ገላትያ 6:​16) ይህ መንፈሳዊ ብሔር በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ወደ ሕልውና ከመጣበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ሥልጣን የሚሰጣቸውን ‘ከምድር የተዋጁ’ 144, 000 በመንፈስ የተቀቡ አባላት አጠቃላይ ቁጥር ያቀፈ ሆኗል። (ራእይ 14:​1, 3) ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ዘመናዊ ፍጻሜውን የሚያገኘው “በመጨረሻው ቀን” በምድር ላይ በሚኖሩ የ144, 000 አባላት ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ከዚህም በተጨማሪ ትንቢቱ የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አጋሮች የሆኑትንና ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይመለከታል።​—⁠ራእይ 7:​9፤ ዮሐንስ 10:​11, 16

5. በምድር ላይ ያሉት የአምላክ እስራኤል አባላት በጨለማ ውስጥ የተኙት መቼ ነበር? የይሖዋ ብርሃን በእነሱ ላይ የበራውስ መቼ ነው?

5 በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በምድር ላይ የነበሩት የአምላክ እስራኤል አባላት ለአጭር ጊዜ ጨለማ ውስጥ ተኝተው ነበር ለማለት ይቻላል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተገለጸው በድናቸው ‘በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ በተባለችው በታላቂቱ ከተማ አደባባይ’ ተኝቶ ነበር። (ራእይ 11:​8) ይሁን እንጂ በ1919 ይሖዋ ብርሃኑን በእነሱ ላይ አበራ። በዚህ ጊዜ ተነስተው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ያላንዳች ፍርሃት በማወጅ የአምላክን ብርሃን አንጸባረቁ።​—⁠ማቴዎስ 5:​14-16፤ 24:​14

6. በጥቅሉ ሲታይ ዓለም ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን እንደተረከበ ለሚገልጸው አዋጅ ምን ምላሽ ሰጥቷል? ይሁንና ወደ ይሖዋ ብርሃን ተስበው የመጡት እነማን ናቸው?

6 የሰው ዘር በጥቅሉ ‘የጨለማው ዓለም ገዦች’ አለቃ የሆነው ሰይጣን ባሳደረበት ተጽዕኖ የተነሳ “የዓለም ብርሃን” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን እንደተረከበ የሚገልጸውን አዋጅ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። (ኤፌሶን 6:​12፤ ዮሐንስ 8:​12፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​3, 4) ያም ሆኖ ‘ነገሥታትን’ (የሰማያዊው መንግሥት ቅቡዓን ወራሾች የሆኑትን) እና ‘አሕዛብን’ (የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎችን) ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ ብርሃን ተስበው መጥተዋል።

ጭማሪው ታላቅ ደስታ ያስገኛል

7. ‘ሴቲቱ’ የምትመለከተው አስደሳች ነገር ምንድን ነው?

7 ይሖዋ በኢሳይያስ 60:​3 ላይ የተጠቀሰውን ጭብጥ ይበልጥ ግልጽ በማድረግ “ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ ” የሚል ትእዛዝ ‘ለሴቲቱ’ አስተላለፈ። ‘ሴቲቱ’ እንደተባለችው ዓይኗን አቅንታ ስታይ ልጆቿ ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ ስለምትመለከት እጅግ ትደሰታለች! “እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል።” (ኢሳይያስ 60:4) ከ1919 አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግሥቱን የማወጅ ሥራ በመካሄድ ላይ በመሆኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ቅቡዓን “ወንዶች ልጆች” እና “ሴቶች ልጆች” የአምላክ እስራኤልን ተቀላቅለዋል። በዚህ መንገድ ይሖዋ በትንቢቱ መሠረት ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን 144, 000 ሰዎች ቁጥር ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዷል።​—⁠ራእይ 5:​9, 10

8. ከ1919 ወዲህ የአምላክ እስራኤል አባላት እንዲደሰቱ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?

8 ይህ ጭማሪ ታላቅ ደስታ አስገኝቷል። “በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፣ አይተሽ ደስ ይልሻል፣ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል።” (ኢሳይያስ 60:5) በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት የተካሄደው ቅቡዓኑን የመሰብሰቡ ሥራ የአምላክ እስራኤል አባላትን በእጅጉ አስደስቷቸዋል። ይሁን እንጂ የተደሰቱት በዚህ ብቻ አልነበረም። በተለይ ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡና ከአምላክ የራቀው የሰው ዘር “ባሕር” ክፍል የነበሩ ሰዎች ከአምላክ እስራኤል ጋር ሆነው ይሖዋን ለማምለክ ተሰብስበዋል። (ኢሳይያስ 57:​20፤ ሐጌ 2:​7) እነዚህ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት እያንዳንዳቸው በመሰላቸው መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ‘ሴት’ ጎን በመሰባሰብ አንድ ከሆነው የአምላክ መንጋ ጋር ይቀላቀላሉ። በመሆኑም እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋቱ ሥራ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይካፈላሉ።

አሕዛብ ወደ ኢየሩሳሌም ይጎርፋሉ

9, 10. ወደ ኢየሩሳሌም ሲጎርፉ የታዩት እነማን ናቸው? ይሖዋስ የሚቀበላቸው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ በኢሳይያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ጠንቅቀው የሚያውቋቸውን ምሳሌዎች በመጠቀም ወደፊት የሚገኘውን እድገትና ጭማሪ ገለጸ። ‘ሴቲቱ’ በጽዮን ተራራ ላይ ቆማ በመጀመሪያ በስተምሥራቅ ወዳለው አድማስ ዓይኗን አቅንታ ትመለከታለች። የምታየው ነገር ምንድን ነው? “የግመሎች ብዛት፣ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፣ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፣ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።” (ኢሳይያስ 60:6) ከተለያዩ ነገዶች የመጡ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚሸቅጡ ነጋዴዎች የግመል ቅፍለቶቻቸውን እየነዱ ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስዱት መንገዶች ላይ ይተምማሉ። (ዘፍጥረት 37:​25, 28፤ መሳፍንት 6:​1, 5፤ 1 ነገሥት 10:​1, 2) ግመሎቹ ምድሪቱን እንደ ጎርፍ አጥለቅልቀዋታል! ቅፍለቶቹ ውድ ዋጋ ያላቸውን ስጦታዎች የጫኑ መሆናቸው ነጋዴዎቹ የመጡት ሰላማዊ የሆነ ጉዳይ ለማከናወን እንደሆነ ይጠቁማል። ወደ ኢየሩሳሌም ያቀኑት ይሖዋን ለማምለክና ካላቸው ንብረት መካከል ምርጡን ለእርሱ ለመስጠት ነው።

10 ይሁን እንጂ ወደ ኢየሩሳሌም በመትመም ላይ ያሉት እነዚህ ነጋዴዎች ብቻ አይደሉም። “የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል።” አዎን፣ ከብት አርቢ የሆኑ ነገዶችም ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ነው። በጣም ውድ የሆኑ ንብረቶቻቸውን ማለትም የበግ መንጎቻቸውን ስጦታ አድርገው ያመጡ ሲሆን ራሳቸውንም አገልጋዮች አድርገው አቅርበዋል። ይሖዋ እንዴት ይቀበላቸው ይሆን? እንዲህ አለ:- “እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፣ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ።” (ኢሳይያስ 60:7) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ የሚውለውን ስጦታቸውን ይቀበለዋል።​—⁠ኢሳይያስ 56:​7፤ ኤርምያስ 49:​28, 29

11, 12. (ሀ) ‘ሴቲቱ’ በስተምዕራብ በኩል ዓይኗን ስታቀና ምን ትመለከታለች? (ለ) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እየተቻኮሉ ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ላይ ያሉት ለምንድን ነው?

11 ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ‘ሴቲቱ’ በስተምዕራብ ወዳለው አድማስ እንድትመለከት ካደረገ በኋላ “ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፣ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ይሖዋ ራሱ እንዲህ በማለት መልስ ሰጠ:- “እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።”​—⁠ኢሳይያስ 60:8, 9

12 ‘ከሴቲቱ’ ጋር አብረህ ቆመህ በስተምዕራብ በኩል ከታላቁ ባሕር ባሻገር እየተመለከትክ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ምን ታያለህ? እንደ ደመና ያሉ ነጫጭ ነቁጦች በባሕሩ ላይ እየተንሳሰፉ ሲተሙ ከሩቅ ይታያሉ። ከሩቅ ሲታዩ ርግቦች ቢመስሉም እንኳ እየቀረቡ ሲመጡ ሸራቸውን የዘረጉ መርከቦች እንደሆኑ ትገነዘባለህ። “ከሩቅ” የመጡ ናቸው። * (ኢሳይያስ 49:​12) መርከቦቹ በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ በከፍተኛ ፍጥነት እየቀዘፉ ወደ ጽዮን ሲመጡ ወደ ቤታቸው የሚበርሩ ርግቦች ይመስላሉ። መርከቦቹ ይህን ያህል የተጣደፉት ለምንድን ነው? ርቀው ከሚገኙ ወደቦች የጫኗቸውን የይሖዋን አምላኪዎች ለማድረስ ስለጓጉ ነው። ከምሥራቅም ሆነ ከምዕራብ እንዲሁም ከሩቅም ሆነ ከቅርብ በመምጣት ላይ ያሉት እስራኤላውያንና የባዕድ አገር ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ራሳቸውንም ሆነ ያላቸውን ነገር ሁሉ ለአምላካቸው ለይሖዋ ስም ለማዋል እየተጣደፉ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 55:​5

13. በዘመናችን ‘ወንዶቹና ሴቶቹ ልጆች’ እነማን ናቸው? ‘የአሕዛብ ብልጥግና’ የተባሉትስ እነማን ናቸው?

13 ኢሳይያስ 60:​4-9 ላይ የሰፈረው ዘገባ የይሖዋ ‘ሴት’ ጨለማ በዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ብርሃን ከፈነጠቀችበት ጊዜ አንስቶ በዓለም ዙሪያ የተገኘውን ጭማሪ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሕያው መግለጫ ነው! በመጀመሪያ የተሰበሰቡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሆኑት የሰማያዊቷ ጽዮን “ወንዶች ልጆች” እና “ሴቶች ልጆች” ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በይፋ አሳውቀዋል። ከዚያም ‘የአሕዛብ ብልጥግና’ እና “የባሕሩ በረከት” ማለትም እንደ ደመና ያሉ በርካታ ቅን ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት ከቀሪዎቹ የክርስቶስ ወንድሞች ጋር ተቀላቅለዋል። * በዛሬው ጊዜ ከአራቱም የምድር ማዕዘናትና ከሁሉም የኑሮ ደረጃዎች የተውጣጡት እነዚህ አገልጋዮች ከአምላክ እስራኤል ጎን በመሰለፍ ሉዓላዊ ጌታቸውን ይሖዋን እያወደሱ ከመሆኑም በላይ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ታላቅ ስም ያለው መሆኑን በማስታወቅ ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

14. ከአሕዛብ የመጡት ሰዎች ‘በአምላክ መሠዊያ ላይ የሚወጡት’ በምን መንገድ ነው?

14 ይሁንና እነዚህ ከአሕዛብ የመጡ ሰዎች ‘በአምላክ መሠዊያ ላይ ይወጣሉ’ የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? መሥዋዕት የሚቀርበው በመሠዊያ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ መሥዋዕትንም የሚመለከት ሐሳብ ሰንዝሮ ነበር:- “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ . . . እለምናችኋለሁ።” (ሮሜ 12:1) እውነተኛ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው። (ሉቃስ 9:​23, 24) ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሙያቸውን ይሠዋሉ። (ሮሜ 6:​13) በዚህ መንገድ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው የምስጋና መሥዋዕት ያቀርባሉ። (ዕብራውያን 13:​15) በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ የይሖዋ አምላኪዎች ከግል ፍላጎቶቻቸው ይልቅ የአምላክን መንግሥት ማስቀደማቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከልብ የመነጨ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያሳያሉ።​—⁠ማቴዎስ 6:​33፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​15

ከአሕዛብ የመጡት ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋቱ ሥራ ይካፈላሉ

15. (ሀ) በጥንት ዘመን ከመጻተኞች ጋር በተያያዘ የይሖዋ ምሕረት የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን “መጻተኞች” እውነተኛውን አምልኮ በመገንባቱ ሥራ የተካፈሉት እንዴት ነው?

15 እነዚህ ከአሕዛብ የመጡ ሰዎች ንብረታቸውንና ጉልበታቸውን የይሖዋን ‘ሴት’ ለመርዳት ይጠቀሙበታል። “በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፣ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል።” (ኢሳይያስ 60:10) በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጻተኞች በኢየሩሳሌም የግንባታ ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ባደረጉ ጊዜ የይሖዋ ምሕረት በግልጽ ታይቷል። (ዕዝራ 3:​7፤ ነህምያ 3:​26) በዘመናችን ደግሞ በትንቢቱ የላቀ ፍጻሜ መሠረት “መጻተኞች” ማለትም እጅግ ብዙ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ የግንባታ ሥራ ቅቡዓን ቀሪዎችን ይረዳሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ በመርዳት ክርስቲያን ጉባኤን በመገንባቱ ሥራ የበኩላቸውን ድርሻ የሚወጡ ከመሆናቸውም በላይ በከተማ የተመሰለው የይሖዋ ድርጅት ‘ቅጥሮች’ እንዲጠናከሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። (1 ቆሮንቶስ 3:​10-15) የመንግሥት አዳራሾች፣ የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾችና የቤቴል ሕንፃዎች ግንባታ በማካሄድ ቃል በቃል በሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎችም በትጋት ይካፈላሉ። በዚህ መንገድ እያደገ ያለው የይሖዋ ድርጅት የሚያስፈልጉትን ነገሮች በማሟላቱ ሥራ ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጎን ተሰልፈው ያገለግላሉ።​—⁠ኢሳይያስ 61:​5

16, 17. (ሀ) የአምላክ ድርጅት “በሮች” ክፍት ሆነው ሊቆዩ የቻሉት እንዴት ነው? (ለ) “ነገሥታት” ጽዮንን ያገለገሏት እንዴት ነው? (ሐ) ይሖዋ ተከፍተው እንዲቆዩ የሚፈልጋቸውን “በሮች” ለመዝጋት የሚሞክሩ ሁሉ ምን ይደርስባቸዋል?

16 በዚህ መንፈሳዊ ግንባታ ፕሮግራም በመጠቀም በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ “መጻተኞች” ወደ ይሖዋ ድርጅት እየጎረፉ ሲሆን በሩ አሁንም ክፍት ነው። ይሖዋ እንዲህ አለ:- “የአሕዛብ ነገሥታት ሀብታቸውን ያስገቡልሽ ዘንድ፣ የቅጽር በሮችሽ ቀንና ሌሊት ክፍት ይሆናሉ።” (ኢሳይያስ 60:​11 የ1980 ትርጉም ) የአሕዛብን ሀብት ወደ ጽዮን ያመጡት “ነገሥታት” እነማን ናቸው? በጥንት ዘመን ይሖዋ አንዳንድ ገዥዎች ጽዮንን ‘እንዲያገለግሏት’ ልባቸውን አነሳስቷል። ለምሳሌ ያህል ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንዲገነቡ ትእዛዝ አስተላልፏል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አርጤክስስ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ እንዲገነባ ነህምያን የላከው ከመሆኑም በላይ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ሰጥቷል። (ዕዝራ 1:​2, 3፤ ነህምያ 2:​1-8) በእርግጥም “የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው።” (ምሳሌ 21:1) አምላካችን ኃያል የሆኑ መሪዎችን እንኳ ሳይቀር ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ ሊገፋፋቸው ይችላል።

17 በዘመናችን ብዙ “ነገሥታት” ወይም ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት የይሖዋን ድርጅት “በሮች” ለመዝጋት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ባለ ሥልጣናት እነዚህ “በሮች” እንዳይዘጉ የሚከላከሉ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ጽዮንን አገልግለዋታል። (ሮሜ 13:​4) በ1919 ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድና አጋሮቹ አላግባብ ከተበየነባቸው እስር ነፃ እንዲለቀቁ አድርገዋል። (ራእይ 11:​13) ሰብዓዊ መንግሥታት ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለ በኋላ ያመጣውን የስደት ጎርፍ ‘ውጠውታል።’ (ራእይ 12:​16) አንዳንድ መንግሥታት ሃይማኖታዊ ነፃነትን የሚያስከብር ሥርዓት እንዲሰፍን ያደረጉ ሲሆን አንዳንዶቹ እንዲህ ያለ እርምጃ የወሰዱት ለይሖዋ ምሥክሮች ሲሉ ነው። ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲህ ያለ አገልግሎት መስጠታቸው ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች በተከፈቱት “በሮች” በኩል ወደ ይሖዋ ድርጅት እንዲዘልቁ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። እነዚህን “በሮች” ለመዝጋት የሚሞክሩትን ተቃዋሚዎች በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? መቼም ቢሆን አይሳካላቸውም። እነሱን አስመልክቶ ይሖዋ እንዲህ አለ:- “ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፣ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።” (ኢሳይያስ 60:12) የአምላክን ‘ሴት’ የሚጻረሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በሙሉ በቅርቡ ከሚካሄደው የአርማጌዶን ጦርነት አያመልጡም።​—⁠ራእይ 16:​14, 16

18. (ሀ) በእስራኤል ምድር ዛፎች እንደሚለመልሙ የተነገረው ተስፋ ምን ትርጉም አለው? (ለ) በዘመናችን ‘የይሖዋ እግር ስፍራ’ ምንድን ነው?

18 ትንቢቱ ይህን የፍርድ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ የክብርና የብልጽግና ዘመን እንደሚመጣ ይገልጻል። ይሖዋ ‘ሴቲቱን’ እንዲህ አላት:- “የመቅደሴንም ስፍራ ያስጌጡ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፣ ጥዱና አስታው ባርሰነቱም፣ ወደ አንቺ ይመጣሉ፣ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ።” (ኢሳይያስ 60:13) የለመለሙ ዛፎች ውበትንና ፍሬያማነትን ያመለክታሉ። (ኢሳይያስ 41:​19፤ 55:​13) በዚህ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ‘መቅደስ’ እና ‘የእግሬን ስፍራ’ የሚሉት አገላለጾች የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ያመለክታሉ። (1 ዜና መዋዕል 28:​2፤ መዝሙር 99:​5) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት በአምልኮ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበትን ዝግጅት የሚያመለክት ዓይነተኛ ተምሳሌት እንደሆነ ገልጿል። (ዕብራውያን 8:​1-5፤ 9:​2-10, 23) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ‘የእግሩን ስፍራ’ ማለትም የዚህን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባዮች ያከብራል። እነዚህ አደባባዮች በጣም የሚማርኩ ከመሆናቸው የተነሳ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ ለመካፈል ወደዚህ ስፍራ ይጎርፋሉ።​—⁠ኢሳይያስ 2:​1-4፤ ሐጌ 2:​7

19. ተቃዋሚዎች አምነው ለመቀበል የሚገደዱት ነገር ምንድን ነው? ይህ የሚሆነውስ መቼ ነው?

19 በመቀጠል ይሖዋ ትኩረቱን እንደገና ወደ ተቃዋሚዎቹ በማዞር እንዲህ አለ:- “የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፣ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።” (ኢሳይያስ 60:14) አዎን፣ በአምላክ በረከት የተነሳ ሕዝቡ የሚያገኘውን ከፍተኛ ጭማሪና እጅግ የተሻለ የሕይወት መንገድ በማየት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ‘ለሴቲቱ’ ለመስገድ ይገደዳሉ። በሌላ አባባል ቅቡዓን ቀሪዎችና አጋሮቻቸው ‘የእግዚአብሔር ከተማ፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን’ የተባለችውን የአምላክ ሰማያዊት ድርጅት በትክክል እንደሚወክሉ እስከ አርማጌዶን ባለው ጊዜ ውስጥ አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ።

ባሉት ቁሳዊ ነገሮች መጠቀም

20. ‘ሴቲቱ’ ምን ዓይነት ታላቅ ለውጥ ይጠብቃታል?

20 የይሖዋ ‘ሴት’ ያለችበት ሁኔታ በእጅጉ ይለወጣል! ይሖዋ እንዲህ አለ:- “ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ። የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የያዕቆብ ኃያል፣ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።”​—⁠ኢሳይያስ 60:15, 16

21. (ሀ) የጥንቷ ኢየሩሳሌም ‘መመኪያ’ የሆነችው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ከ1919 አንስቶ ምን በረከቶች አግኝተዋል? ‘የአሕዛብን ወተት’ የጠጡትስ እንዴት ነው?

21 የጥንቷ ኢየሩሳሌም ለ70 ዓመታት ከካርታ ላይ የተፋቀች ያህል ሆና ቆይታለች። ‘ማንም አያልፍባትም ነበር።’ ይሁን እንጂ ከ537 ከዘአበ አንስቶ ይሖዋ ከተማዋ እንደገና በሰዎች እንድትሞላ በማድረግ ‘መመኪያ’ እንድትሆን አደረጋት። በተመሳሳይም በአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ የአምላክ እስራኤል አባላት ‘እንደተተዉ’ እስኪሰማቸው ድረስ ከባድ የመከራ ጊዜ አሳልፈዋል። ሆኖም በ1919 ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹን ከግዞት የተቤዣቸው ሲሆን ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ ጭማሪና መንፈሳዊ ብልጽግና እንዲያገኙ በማድረግ ባርኳቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች የአሕዛብን ቁሳዊ ነገሮች እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት መሣሪያ አድርገው በመጠቀም ‘የአሕዛብን ወተት’ ጠጥተዋል። ለምሳሌ ያህል ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ በጥበብ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች መተርጎምና ማተም ችለዋል። በዚህም ሳቢያ በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋ በክርስቶስ በኩል እንደሚያድናቸውና እንደሚቤዣቸው በመማር ላይ ናቸው።​—⁠ሥራ 5:​31፤ 1 ዮሐንስ 4:​14

ድርጅታዊ ማሻሻያዎች

22. ይሖዋ ምን ዓይነት ለየት ያለ ለውጥ እንደሚኖር ቃል ገብቷል?

22 ከይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር ጭማሪ ጎን ለጎን ድርጅቱም እያደገና እየተሻሻለ ሄዷል። ይሖዋ እንዲህ አለ:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:17) ናሱ በወርቅ መተካቱም ሆነ እዚህ ላይ በተጠቀሱት ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ የተደረገው ለውጥ መሻሻልን የሚያሳይ ነው። ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ የይሖዋ ሕዝቦች በመጨረሻዎቹ ቀናት በርካታ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

23, 24. የይሖዋ ሕዝቦች ከ1919 ወዲህ ምን ድርጅታዊ ማሻሻያዎች አድርገዋል?

23 ከ1919 በፊት በነበሩት ዓመታት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በጉባኤዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ይሾሙ ነበር። ከዚያ ዓመት አንስቶ ግን የጉባኤውን የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ የሚከታተል የአገልግሎት ዲሬክተር ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሾም የጀመረ ቢሆንም በምርጫ የተሾሙ አንዳንድ ሽማግሌዎች የአገልግሎት ዲሬክተሩን የተቃወሙባቸው ጊዜያት ነበሩ። በ1932 ሌላ ማሻሻያ ተደረገ። ጉባኤዎች ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን መምረጥ እንዲያቆሙ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በኩል መመሪያ ተሰጣቸው። በዚያ ፋንታ ከአገልግሎት ዲሬክተሩ ጋር ተባብሮ የሚሠራ የአገልግሎት ኮሚቴ እንዲመርጡ ተደረገ። ይህ ትልቅ ማሻሻያ ነበር።

24 በ1938 በጉባኤ ውስጥ የሚሠሩ አገልጋዮች በሙሉ ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚሾሙበት ዝግጅት በመደረጉ ተጨማሪ “ወርቅ” ሊገኝ ችሏል። ጉባኤን የማስተዳደር ኃላፊነት ለአንድ የቡድን አገልጋይ (በኋላ የጉባኤ አገልጋይ ተብሏል) እና የእርሱ ረዳት ሆነው ለሚሠሩ አገልጋዮች የተሰጠ ሲሆን ሁሉም የሚሾሙት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አመራር ሰጪነት ነበር። * (ማቴዎስ 24:​45-47) ይሁን እንጂ በ1972 በቅዱስ ጽሑፋዊው አሠራር መሠረት ጉባኤዎችን በበላይነት መምራት ያለበት አንድ ሰው ሳይሆን የሽማግሌዎች አካል መሆን እንዳለበት ግልጽ ሆነ። (ፊልጵስዩስ 1:​1) ከዚህም በተጨማሪ በጉባኤም ሆነ በአስተዳደር አካል ውስጥ ሌሎች ለውጦች ተደርገዋል። ከአስተዳደር አካል ጋር በተያያዘ ከተደረጉት ማሻሻያዎች አንዱ ጥቅምት 7, 2000 የተካሄደው ለውጥ ሲሆን የፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና የማኅበሩ ኮርፖሬሽኖች ዲሬክተሮች ሆነው ያገለግሉ የነበሩ የአስተዳደር አካል አባላት ይህን ኃላፊነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለሌሎች ሰጥተዋል። ይህም ታማኝና ልባም ባሪያን የሚወክለው የአስተዳደር አካል ‘ለእግዚአብሔር ጉባኤ’ አባላትና አጋሮቻቸው ለሆኑት ሌሎች በጎች መንፈሳዊ አመራር የመስጠት ኃላፊነቱን በተሻለ ብቃት ለማከናወን አስችሎታል። (ሥራ 20:​28) እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች በየጊዜው የተደረጉ ማሻሻያዎች ናቸው። የይሖዋ ድርጅት እንዲጠናከር ከማድረጋቸውም በላይ አምላኪዎቹም እንዲባረኩ በር ከፍተዋል።

25. የይሖዋ ሕዝቦች ድርጅታዊ ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ የረዳቸው ማን ነው? ይህስ ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል?

25 እነዚህን ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ የረዳቸው ማን ነው? እነዚህ ማሻሻያዎች በተወሰኑ ሰዎች የማደራጀት ችሎታ ወይም የመጠቀ አስተሳሰብ የተገኙ ናቸውን? በፍጹም፤ ምክንያቱም ‘ወርቅ አመጣለሁ’ ሲል የተናገረው ይሖዋ ነው። ይህ ሁሉ ማሻሻያ ሊደረግ የቻለው በመለኮታዊ አመራር ነው። የይሖዋ ሕዝቦች ለአመራሩ በመገዛት ማስተካከያዎች ሲያደርጉ በእጅጉ ይጠቀማሉ። በመካከላቸው ሰላም የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ ለጽድቅ ያላቸው ፍቅር አምላካቸውን እንዲያገለግሉ ይገፋፋቸዋል።

26. ተቃዋሚዎች እንኳ ሳይቀሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች በየትኛው ባሕርያቸው ተለይተው እንደሚታወቁ አይክዱም?

26 አምላክ የሚሰጠው ሰላም ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው። ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገባ:- “ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ።” (ኢሳይያስ 60:18) ይህ ፈጽሞ የማይታበል ሐቅ ነው! እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰላማዊ መሆናቸውን ተቃዋሚዎች እንኳን አይክዱም። (ሚክያስ 4:​3) የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ሁከት በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባ የሚደረግበት እያንዳንዱ ቦታ ልክ በበረሃ እንዳለ ገነት መንፈስን የሚያድስ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:​17) ይህም ሁሉም የምድር ነዋሪዎች “ከእግዚአብሔር የተማሩ” በሚሆኑበት ጊዜ የሚያገኙትን የተትረፈረፈ ሰላም ከወዲሁ የሚያመላክት ነው።​—⁠ኢሳይያስ 11:​9፤ 54:​13

መለኮታዊ ተቀባይነትን የሚያመለክት ታላቅ ብርሃን

27. በይሖዋ ‘ሴት’ ላይ የበራው የማይቋረጥ ብርሃን ምንድን ነው?

27 ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ የሚፈነጥቀው ብርሃን ምን ያህል ደማቅ እንደሆነ አመልክቷል:- “ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ፣ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም፣ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያበራልሽም። እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፣ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም ጨረቃሽም አይቋረጥም።” (ኢሳይያስ 60:19, 20) ይሖዋ ‘ለሴቲቱ’ “የዘላለም ብርሃን” ይሆንላታል። እንደ ፀሐይ ‘አይጠልቅም፣’ እንደ ጨረቃም ብርሃኑ “አይቋረጥም።” * ሞገሱን የሚያሳይበት ዘላለማዊ ብርሃኑ የአምላክ ‘ሴት’ ሰብዓዊ ወኪሎች በሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ በርቷል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች በዓለም የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ያለው ጨለማ ሊውጠው የማይችል ደማቅ መንፈሳዊ ብርሃን ፈንጥቆላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ቃል በገባላቸው ብሩህ ተስፋ ሙሉ ትምክህት አላቸው።​—⁠ሮሜ 2:​7፤ ራእይ 21:​3-5

28. (ሀ) ወደ ኢየሩሳሌም የሚመለሱትን ነዋሪዎች በተመለከተ ምን ተስፋ ተሰጥቶ ነበር? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 የወረሱት ምንድን ነው? (ሐ) ጻድቃን ምድርን የሚወርሱት ለምን ያህል ጊዜ ነው?

28 በመቀጠል ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አስመልክቶ እንዲህ አለ:- “ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፣ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ።” (ኢሳይያስ 60:21) ሥጋዊ እስራኤላውያን ከባቢሎን በተመለሱበት ወቅት ‘ምድሪቱን ወርሰዋል።’ ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በምድሪቱ ላይ “ለዘላለም” ሊቆዩ አልቻሉም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምንም ሆነ የአይሁድን ብሔር ደምስሷል። በ1919 በምድር ላይ የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ወጥተው መንፈሳዊ ምድር ወርሰዋል። (ኢሳይያስ 66:​8) ይህ ምድር ወይም የሥራ መስክ እንደ ገነት ባለ ፈጽሞ በማይጠፋ መንፈሳዊ ብልጽግና የተሞላ ነው። በቡድን ደረጃ መንፈሳዊው እስራኤል እንደ ጥንቷ እስራኤል ታማኝነቱን አያጓድልም። ከዚህም በተጨማሪ ምድር ‘ሰላም የሞላባት’ ገነት በምትሆንበት ጊዜ የኢሳይያስ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜውን ያገኛል። በዚያን ጊዜ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ጻድቃን ምድርን ለዘላለም ይወርሳሉ።​—⁠መዝሙር 37:​11, 29

29, 30. “ታናሹ ለሺህ” የሆነው እንዴት ነው?

29 በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 መደምደሚያ ላይ ይሖዋ በራሱ ስም ዋስትና የሰጠበትን የማይታጠፍ ቃል እናገኛለን። እንዲህ አለ:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:​22) ተበታትነው የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 እንደገና ተሰባስበው ሥራቸውን ማከናወን ሲጀምሩ ‘አነስተኛ’ ነበሩ። * የተቀሩት መንፈሳዊ እስራኤላውያን ሲሰበሰቡ ግን ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ። እጅግ ብዙ ሰዎች መሰብሰብ ሲጀምሩ ደግሞ ቁጥራቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ እየጨመረ ሄደ።

30 ብዙም ሳይቆይ በአምላክ ሕዝብ መካከል ያለው ሰላምና ጽድቅ ቅን ልብ ያላቸውን በርካታ ሰዎች በመሳቡ ቃል በቃል “ታናሹ” “ብርቱ ሕዝብ” ሆነ። በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው በዓለም ላይ ካሉት በርካታ ሉዓላዊ መንግሥታት የሕዝብ ቁጥር ይበልጣል። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመንግሥቱን ሥራ ከመምራቱም በላይ በእጅጉ እንዳፋጠነው በግልጽ መረዳት ይቻላል። እውነተኛው አምልኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ ማየትና የዚህ እድገት አካል መሆን መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው! አዎን፣ ይህ ጭማሪ እነዚህን ትንቢቶች ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገረውን አምላክ ይሖዋን እንደሚያስከብረው ማወቃችን በእጅጉ ያስደስተናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ተርሴስ በዛሬው ጊዜ ስፔይን በመባል በሚታወቀው የምድር ክፍል ትገኝ እንደነበር ይታመናል። ይሁንና አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች እንደሚሉት “የተርሴስ መርከቦች” የሚለው አገላለጽ የመርከቦቹን ዓይነት ማለትም “ወደ ተርሴስ ለመጓዝ አመቺ” የሆኑትን በሌላ አባባል ርቀው ወደሚገኙ ወደቦች ረጅም ጉዞ ለማድረግ ተስማሚ የሆኑትን “ረጃጅም ተራዳ ያላቸው በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ መርከቦች” ያመለክታል።​—⁠1 ነገሥት 22:​48

^ አን.13 ከ1930 በፊትም ከአምላክ እስራኤል ጋር የተባበሩ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ቀናተኛ ክርስቲያኖች የነበሩ ቢሆንም ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው ከ1930ዎቹ ዓመታት ወዲህ ነው።

^ አን.24 በዚያ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎች ቡድኖች በመባል ይታወቁ ነበር።

^ አን.27 ሐዋርያው ዮሐንስ “አዲሲቱን ኢየሩሳሌም” ማለትም ሰማያዊ ክብር የተጎናጸፉትን 144, 000ዎች አስመልክቶ ሲናገር ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ራእይ 3:​12፤ 21:​10, 22-26) ‘አዲሲቷ ኢየሩሳሌም’ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ያገኙትንና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የአምላክ ‘ሴት’ ማለትም ‘የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ዋነኛ አካል የሚሆኑትን የአምላክ እስራኤል አባላት በሙሉ የምታመለክት በመሆኑ ይህ አገላለጽ ተስማሚ ነው።​—⁠ገላትያ 4:​26

^ አን.29 በ1918 ቃሉን በመስበኩ ሥራ በየወሩ ይካፈሉ የነበሩት ሰዎች አማካይ ቁጥር ከ4, 000 አይበልጥም ነበር።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 305 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ሴቲቱ እንድትነሳ’ ትእዛዝ ተሰጥቷታል

[በገጽ 312, 313 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የተርሴስ መርከቦች” የይሖዋን አምላኪዎች ጭነው ይመጣሉ