በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ይሖዋ አምልኮ ተመለሱ

ወደ ይሖዋ አምልኮ ተመለሱ

ምዕራፍ ሰባት

ወደ ይሖዋ አምልኮ ተመለሱ

ኢሳይያስ 46:​1-13

1. ከባቢሎን ዋና ዋና አማልክት መካከል ሁለቱ ምን በመባል ይታወቃሉ? እነሱን በተመለከተስ ምን ትንቢት ተነግሯል?

እስራኤላውያን በምርኮ የሚጋዙባት ባቢሎን በሐሰት አምልኮ የተሞላች ናት። ኢሳይያስ በሕይወት በነበረበት ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች ገና በትውልድ አገራቸው የነበሩ ሲሆን ቤተ መቅደሱም ሆነ የክህነት አገልግሎቱ አልጠፋም ነበር። ይሁን እንጂ ራሱን ለአምላክ ከወሰነው ብሔር መካከል ብዙዎቹ በጣዖት አምልኮ ተሸንፈዋል። በመሆኑም ለባቢሎን የሐሰት አማልክት አምልኮታዊ ፍርሃት እንዳያድርባቸው ወይም እነሱን ለማገልገል እንዳይፈተኑ ከወዲሁ ማሳሰቢያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ የተነሳ ኢሳይያስ ሁለቱን የባቢሎን ዋና ዋና አማልክት አስመልክቶ እንዲህ ሲል በትንቢት ተናገረ:- “ቤል ተዋረደ፣ ናባው ተሰባበረ [“አጎነበሰ፣” NW ]፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል።” (ኢሳይያስ 46:1) ቤል የከለዳውያን ዋነኛ አምላክ ነው። ናባው ደግሞ የጥበብና የእውቀት አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ይመለክ ነበር። በርካታ ባቢሎናውያን ስማቸው የእነዚህን አማልክት ስም የያዘ መሆኑ ለአማልክቱ ልዩ አክብሮት እንደነበራቸው ያሳያል። ከእነዚህም መካከል ብልጣሶር፣ ናቦፖላሳር፣ ናቡ ከደነፆርና ናቡ ዘረዳን የሚሉት ስሞች ይገኙበታል።

2. የባቢሎን አማልክት አንዳች ማድረግ የማይችሉ መሆናቸው ጎላ ተደርጎ የተገለጸው እንዴት ነው?

2 ኢሳይያስ ቤል “ተዋረደ፣” ናባው ደግሞ “አጎነበሰ” ሲል ተናግሯል። እነዚህ የሐሰት አማልክት ይሖዋ በባቢሎን ላይ የፍርድ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ አምላኪዎቻቸውን ሊያስጥሉ ይቅርና ራሳቸውን እንኳን ማዳን ስለማይችሉ ይዋረዳሉ! ባቢሎናውያን እንደ ቀድሞው ቤልንና ናባውን እንደ ዘመን መለወጫ ባሉ ክብረ በዓሎቻቸው በክብር ተሸክመውና በደመቀ የሰልፍ ሥነ ሥርዓት አጅበው ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ መውሰዳቸው ያበቃል። ሲያመልኳቸው የኖሩትን አማልክት እንደ ተራ ዕቃ በእንስሳት በሚጎተት ጋሪ ጭነው ይወስዷቸዋል። አማልክቱ ቀድሞ ያገኙት የነበረው ውዳሴና ከበሬታ ሁሉ ቀርቶ ማፌዣና መሳለቂያ ይሆናሉ።

3. (ሀ) ባቢሎናውያንን በኀፍረት የሚያሸማቅቃቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በባቢሎናውያን አማልክት ላይ ከደረሰው ሁኔታ ዛሬ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

3 ባቢሎናውያን በአንድ ወቅት ከፍ አድርገው ይመለከቷቸው የነበሩት ጣዖቶቻቸው በደካማ እንስሳት የሚጫኑ ተራ ኮተቶች መሆናቸውን ሲገነዘቡ ምን ያህል በኀፍረት እንደሚሸማቀቁ አስበው! ዛሬም በተመሳሳይ የዚህ ዓለም አማልክት ማለትም ሰዎች እምነታቸውን የሚጥሉባቸው እንዲሁም ጉልበታቸውን የሚያፈስሱላቸውና ሕይወታቸውን ሳይቀር የሚሠዉላቸው ነገሮች ከንቱ ማታለያዎች ናቸው። ሀብት፣ የጦር መሣሪያ፣ ሥጋዊ ምኞቶች፣ ገዥዎች፣ እናት አገር ወይም እነዚህን ነገሮች የሚወክሉ ምስሎች እንደ ጣዖት ይመለካሉ። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እነዚህ እንደ አምላክ የሚመለኩ ነገሮች ዋጋቢስ መሆናቸው በሚገባ ይረጋገጣል።​—⁠ዳንኤል 11:​38፤ ማቴዎስ 6:​24፤ ሥራ 12:​22፤ ፊልጵስዩስ 3:​19፤ ቆላስይስ 3:​5፤ ራእይ 13:​14, 15

4. የባቢሎን አማልክት ‘ይጎነበሳሉ’ እንዲሁም “ዝቅ ይላሉ” የሚለው አባባል ምን ያመለክታል?

4 ትንቢቱ በመቀጠል የባቢሎን አማልክት የሚደርስባቸውን ታላቅ ውድቀት እንዲህ ሲል ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- “ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ [“ዝቅ ይላሉ፣” አ.መ.ት ]፤ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፣ ራሳቸው ግን ተማረኩ።” (ኢሳይያስ 46:2) የባቢሎን አማልክት በጦር ሜዳ እንደቆሰለ ወይም እርጅና እንደተጫጫነው ሰው ‘ይጎነበሳሉ’ እንዲሁም “ዝቅ ይላሉ።” ለተሸከሟቸው ዝቅተኛ እንስሳት ሸክሙን ማቅለል ወይም እንስሳቱን ማዳን እንኳን አይችሉም። ታዲያ የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝቦች በባቢሎን ቢማረኩም እንኳ ለእነዚህ አማልክት ክብር መስጠት ይገባቸዋልን? በፍጹም! በተመሳሳይም የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች በመንፈሳዊ ግዞት በነበሩበት ጊዜም እንኳ ‘ለታላቂቱ ባቢሎን’ የሐሰት አማልክት ምንም ዓይነት ክብር አልሰጡም። እነዚህ አማልክት ታላቂቱ ባቢሎንን በ1919 ከደረሰባት ውድቀት መታደግ እንዳልቻሉ ሁሉ ‘በታላቁ መከራ’ ከሚደርስባት ጥፋትም ሊያድኗት አይችሉም።​—⁠ራእይ 18:​2, 21፤ ማቴዎስ 24:​21

5. በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ጣዖት አምላኪ የሆኑት ባቢሎናውያን የሠሩትን ስህተት ዳግመኛ ከመፈጸም የተቆጠቡት እንዴት ነው?

5 በዘመናችን ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ለማንኛውም ዓይነት ጣዖት አይሰግዱም። (1 ዮሐንስ 5:​21) መስቀል፣ መቁጠሪያና የቅዱሳን ሰዎች ምስሎች ወደ ፈጣሪ ሊያቀርቡን ወይም ሊያማልዱን አይችሉም። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ደቀ መዛሙርት “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” በማለት አምላክን ማምለክ የሚቻልበትን ትክክለኛ መንገድ አስተምሯቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:6, 14

“ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ”

6. ይሖዋ ከአሕዛብ አማልክት የሚለየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ የባቢሎንን የጣዖት አማልክት ማምለክ ከንቱ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ሕዝቡን እንዲህ አለ:- “እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፣ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ፣ ስሙኝ።” (ኢሳይያስ 46:3) በይሖዋና በባቢሎን የተቀረጹ ምስሎች መካከል እጅግ ከፍተኛ ልዩነት አለ! የባቢሎን አማልክት ለአምላኪዎቻቸው አንዳች ማድረግ አይችሉም። በእንስሳት ተጭነው ካልሆነ በስተቀር ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ እንኳ አይችሉም። በአንጻሩ ግን ይሖዋ ሕዝቡን ተሸክሟል። “ከማኅፀን” ማለትም የእስራኤል ብሔር ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ አድርጎላቸዋል። አይሁዳውያን ቀደም ባሉት ዘመናት ይሖዋ እነሱን በመሸከሙ ያገኟቸው ጥቅሞች ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁና ይሖዋን እንደ አባታቸውና እንደ ወዳጃቸው አድርገው በመመልከት እምነታቸውን እንዲጥሉበት ሊገፋፏቸው ይገባል።

7. ይሖዋ ለአምላኪዎቹ የሚያደርገው እንክብካቤ ሰብዓዊ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሚያደርጉት እንክብካቤ የሚበልጠው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅርና አሳቢነት እንዲህ ሲል አክሎ ገልጿል:- “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ።” (ኢሳይያስ 46:4) ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያደርገው እንክብካቤ አንድ እጅግ አሳቢ የሆነ ሰብዓዊ ወላጅ ለልጁ ከሚያደርገው እንክብካቤ በጣም የላቀ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ ያለባቸው ኃላፊነት እየቀነሰ እንደሚሄድ ሊሰማቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ሲያረጁ ልጆቻቸው ይጦሯቸዋል። ይሖዋ ግን እንደዚያ አይደለም። ሰብዓዊ ልጆቹን ምንጊዜም መንከባከቡን አያቆምም፤ ቢያረጁም እንኳን አይተዋቸውም። በዘመናችን ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ፈጣሪያቸውን የሚወዱና በእሱ የሚታመኑ ሲሆን ከላይ በኢሳይያስ ትንቢት የተጠቀሱት ቃላት በእጅጉ ያጽናኗቸዋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያሳልፉት ቀሪ የሕይወት ዘመናቸው አያስጨንቃቸውም። ይሖዋ በዕድሜ የገፉ አገልጋዮቹን በታማኝነት እንዲጸኑ አስፈላጊውን ብርታት በመስጠት ‘እንደሚሸከማቸው’ ቃል ገብቷል። ይሸከማቸዋል፣ ያበረታቸዋል እንዲሁም ያድናቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

ከዘመናዊ ጣዖታት ተጠበቁ

8. አንዳንድ እስራኤላውያን የፈጸሙት ትልቅ ኃጢአት ምን ነበር?

8 ባቢሎናውያን የሚታመኑባቸው ጣዖታት ምንም ዋጋ የሌላቸው መሆኑን ሲመለከቱ ምን ያህል ቅስማቸው እንደሚሰበር ልትገምት ትችላለህ! እስራኤላውያን እነዚህ አማልክት ከይሖዋ ጋር ሊወዳደሩ እንደሚችሉ አድርገው ማሰብ ይገባቸዋልን? በፍጹም! ይሖዋ እንዲህ ሲል መጠየቁ የተገባ ነው:- “በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?” (ኢሳይያስ 46:5) አንዳንድ እስራኤላውያን መናገርም ሆነ አንዳች ማድረግ የማይችሉ በድን ምስሎችን ማምለክ መጀመራቸው ትልቅ ስህተት ነበር! ይሖዋን የሚያውቅ ብሔር በሰው እጅ በተሠሩና ራሳቸውን እንኳ መከላከል በማይችሉ በድን ምስሎች መታመኑ ትልቅ ሞኝነት ነው።

9. አንዳንድ ጣዖት አምላኪዎች ምን ያህል ማስተዋል የጎደላቸው እንደሆኑ ግለጽ።

9 እነዚህ ጣዖት አምላኪዎች ምን ያህል ማስተዋል የጎደላቸው እንደነበሩ ተመልከት። ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ወርቁን ከኮረጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፣ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል።” (ኢሳይያስ 46:6) እነዚህ አምላኪዎች በጣም ውድ ከሆነ ነገር የተሠራ ጣዖት ከእንጨት ከተሠራው የበለጠ የማዳን ኃይል ያለው ይመስል ከፍተኛ ወጪ አፍስሰው ጣዖት ከማሠራት ወደኋላ አይሉም። ሆኖም አንድ ጣዖት ምንም ያህል ቢደከምለት ወይም ምንም ያህል ወጪ ቢፈስለት የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። በድን የሆነ ጣዖት ምንጊዜም ያው በድን ነው።

10. ጣዖት ማምለክ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌለው የተገለጸው እንዴት ነው?

10 ትንቢቱ በመቀጠል ጣዖት ማምለክ ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል:- “በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፣ በዚያም ይቆማል፣ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም።” (ኢሳይያስ 46:7) መስማትም ሆነ አንዳች ነገር ማድረግ የማይችልን ምስል መለመን እንዴት ያለ ቂልነት ነው! መዝሙራዊው እንዲህ ያሉ ጣዖታት ከንቱ መሆናቸውን ጥሩ አድርጎ ገልጿል:- “የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው አያዩምም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱምም፤ እግር አላቸው አይሄዱምም፤ በጕሮሮአቸውም አይናገሩም። የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።”​—⁠መዝሙር 115:4-8

‘ደፋሮች ሁኑ’

11. ቆራጥ አቋም ለመውሰድ የተቸገሩ ሰዎች ‘ድፍረት ማግኘት’ እንዲችሉ የሚረዳቸው ምንድን ነው?

11 ይሖዋ ጣዖት ማምለክ ከንቱ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ሕዝቡ እሱን ማገልገላቸው ተገቢ የሆነበትን ምክንያት አመልክቷል:- “ይህን አስቡና አልቅሱ [“ድፍረት ማግኘት እንድትችሉ ይህን አስታውሱ፣” NW ]፤ ተላላፊዎች ሆይ፣ ንስሐ ግቡ፣ ልባችሁንም መልሱ። እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።” (ኢሳይያስ 46:8, 9) በእውነተኛ አምልኮና በጣዖት አምልኮ መካከል የሚዋልሉ ሰዎች የቀድሞውን ታሪክ መለስ ብለው ማሰብ አለባቸው። ይሖዋ ያደረጋቸውን ነገሮች ማስታወስ ይገባቸዋል። ይህም ድፍረት እንዲያገኙና ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ እንዲሁም ወደ ይሖዋ አምልኮ እንዲመለሱ ይረዳቸዋል።

12, 13. ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ትግል አለባቸው? ድል አድራጊዎች መሆን የሚችሉትስ እንዴት ነው?

12 ይህ ማበረታቻ ዛሬም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ልክ እንደ እስራኤላውያን በዘመናችን የሚገኙ ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖችም ከራሳቸው አለፍጽምና ጋርም ሆነ መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ከሚገፋፏቸው ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ጋር መታገል አለባቸው። (ሮሜ 7:​21-24) ከዚህም በተጨማሪ በዓይን ከማይታይ እጅግ ኃይለኛ የሆነ ጠላት ጋር ከፍተኛ መንፈሳዊ ትግል ያደርጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።”​—⁠ኤፌሶን 6:12

13 ሰይጣንና አጋንንቱ ክርስቲያኖችን ከእውነተኛው አምልኮ ለማራቅ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም። ክርስቲያኖች በውጊያው ድል እንዲቀናቸው የይሖዋን ምክር መከተልና ድፍረት ማግኘት ይኖርባቸዋል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።” ይሖዋ አገልጋዮቹን በሚገባ ሳያስታጥቅ ወደ ውጊያ አይልክም። የክርስቲያኖች መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ‘የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ሊያጠፉ የሚችሉበትን የእምነትን ጋሻ’ ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:11, 16) እስራኤላውያን ይሖዋ ያዘጋጀላቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ችላ በማለታቸው ሕጉን ተላልፈዋል። ይሖዋ ለእነሱ ሲል በተደጋጋሚ ጊዜያት የፈጸማቸውን ተአምራት ቢያሰላስሉ ኖሮ አስጸያፊ ወደሆነ የጣዖት አምልኮ ዘወር አይሉም ነበር። እንግዲያው ከእነሱ ምሳሌ በመማር ትክክል የሆነውን ለማድረግ በምናካሂደው ትግል ያላንዳች ማመንታት ወደፊት ለመግፋት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​11

14. ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እሱ ብቻ መሆኑን ለማመልከት ምን የማድረግ ችሎታ እንዳለው ጠቅሷል?

14 ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።” (ኢሳይያስ 46:10) በዚህ ረገድ ከይሖዋ ጋር ሊወዳደር የሚችል አምላክ ይኖራል? ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ መቻሉ የፈጣሪን እውነተኛ አምላክነት የሚያረጋግጥ ጉልህ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ የተነገሩት ትንቢቶች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። “ምክሬ ትጸናለች” የሚለው መግለጫ ይሖዋ ያወጣው ዓላማ የማይለወጥ መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል። ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ታላቅ ኃይል ያለው በመሆኑ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ፈቃዱን ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል ነገር የለም። (ዳንኤል 4:​35) ስለዚህ ገና ያልተፈጸሙት ትንቢቶችም አምላክ በወሰነው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 55:​11

15. ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በመተንበይ ረገድ ያለውን ችሎታ የሚያሳይ ምን አስደናቂ ምሳሌ ተጠቅሶልናል?

15 የኢሳይያስ ትንቢት በመቀጠል ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በመተንበይና የተናገረውን ቃል በመፈጸም ረገድ ያለውን ችሎታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ይጠቅስልናል:- “ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፣ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራዋለሁ። ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።” (ኢሳይያስ 46:11) ይሖዋ አምላክ ‘በመጀመሪያ መጨረሻውን የሚናገር’ በመሆኑ ምክሩን ዳር ለማድረስ ሲል ከሰው ልጅ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች እሱ ባሰበው መንገድ እንዲፈጸሙ ያደርጋል። ቂሮስን “ከምሥራቅ” ማለትም የቂሮስ ተወዳጅ ዋና ከተማ የሆነችው ፓሳርጋዲ ከምትገኝበት ከፋርስ ይጠራዋል። ቂሮስ እንደ “ነጣቂ ወፍ” ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ባቢሎንን ይይዛል።

16. ይሖዋ ባቢሎንን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ እንደማይቀር ያረጋገጠው እንዴት ነው?

16 “ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ” የሚሉት ቃላት ይሖዋ ባቢሎንን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚያረጋግጥ ነው። ፍጽምና የጎደለው የሰው ልጅ በግብታዊነት ቃል መግባት የሚቀናው ሲሆን ፈጣሪ የሚናገረው ቃል ግን መሬት ጠብ አይልም። ይሖዋ “የማይዋሽ” አምላክ በመሆኑ ‘ካሰበ እንደሚያደርገው’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ቲቶ 1:​2

እምነት የሌላቸው ልቦች

17, 18. (ሀ) በጥንት ዘመን (ለ) በዘመናችን “እልከኞች” የሆኑት እነማን ናቸው?

17 ይሖዋ እንደገና ትኩረቱን ወደ ባቢሎናውያን በማዞር እንዲህ አለ:- “እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፣ ስሙኝ።” (ኢሳይያስ 46:12) “እልከኞች” የሚለው አባባል ግትር የሆኑትንና የአምላክን ፈቃድ በመቃወም በአቋማቸው የገፉትን ሰዎች ያመለክታል። ባቢሎናውያን ከአምላክ በጣም ርቀው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ለይሖዋና ለሕዝቡ የነበራቸው ጥላቻ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፉና ነዋሪዎቿን ማርከው እንዲወስዱ ይገፋፋቸዋል።

18 በዘመናችን ተጠራጣሪና የማያምን ልብ ያላቸው ሰዎች በምድር ዙሪያ እየተሰበከ ያለውን የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት አሻፈረን በማለት እልከኞች ሆነዋል። (ማቴዎስ 24:​14) ይሖዋ የመግዛት መብት ያለው ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን አምነው ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። (መዝሙር 83:​18፤ ራእይ 4:​11) ልባቸው ‘ከጽድቅ የራቀ’ በመሆኑ የይሖዋን ፈቃድ አጥብቀው ይቃወማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ልክ እንደ ባቢሎናውያን ይሖዋን መስማት አይፈልጉም።

አምላክ የሚወስደው የማዳን እርምጃ አይዘገይም

19. ይሖዋ ለእስራኤል ሲል የጽድቅ እርምጃ የሚወስደው በምን መንገድ ነው?

19 የኢሳይያስ ምዕራፍ 46 የመደምደሚያ ቃላት የይሖዋን ሁለንተናዊ ባሕርይ አንዳንድ ገጽታዎች ጎላ አድርገው ይገልጻሉ:- “ጽድቄን አቀርባለሁ፣ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።” (ኢሳይያስ 46:13) አምላክ እስራኤልን ነፃ በማውጣት የጽድቅ እርምጃ ይወስዳል። ሕዝቡ ለዘመናት በግዞት እየማቀቁ እንዲኖሩ አይሻም። ጽዮንን ለማዳን በተገቢው ጊዜ ላይ እርምጃ ይወስዳል፣ ፈጽሞ “አይዘገይም።” የእስራኤላውያን ከግዞት ነፃ መውጣት በአካባቢው ያሉ ብሔራትን ትኩረት ይስባል። ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት የሚወስደው እርምጃ የማዳን ኃይል ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሆናል። የባቢሎን አማልክት ቤል እና ናባው አንዳች ማድረግ የማይችሉ ከንቱ አማልክት መሆናቸውን ሁሉም ሰው ይገነዘባል።​—⁠1 ነገሥት 18:​39, 40

20. ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚወስደው የማዳን እርምጃ ‘እንደማይዘገይ’ እርግጠኞች መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

20 በ1919 ይሖዋ ሕዝቡን ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ያወጣ ሲሆን ይህን እርምጃ ለመውሰድ ከቶ አልዘገየም። ይህ ክንውንም ሆነ ባቢሎን በቂሮስ እጅ በወደቀችበት ጊዜ የተፈጸሙት ሁኔታዎች ዛሬ ጥሩ ማበረታቻ ይሆኑናል። ይሖዋ የሐሰት አምልኮን ጨምሮ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት ቃል ገብቷል። (ራእይ 19:​1, 2, 17-21) አንዳንድ ክርስቲያኖች በሰብዓዊ ዓይን ሲመለከቱት መዳናቸው እንደዘገየ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን ቃል ለመፈጸም የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ መታገሱ የጽድቅ እርምጃ ነው። ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ (2 ጴጥሮስ 3:​9) እንግዲያው በጥንት እስራኤል ዘመን እንደሆነው ሁሉ አሁንም የይሖዋ የማዳን እርምጃ ‘እንደማይዘገይ’ እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ ይህን የማዳን እርምጃ የሚወስድበት ቀን እየቀረበ በመጣ መጠን በፍቅር ተገፋፍቶ የሚከተለውን ጥሪ ማሰማቱን ቀጥሏል:- “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”​—⁠ኢሳይያስ 55:6, 7

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 94 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የባቢሎን አማልክት ከጥፋት አያድኗትም

[በገጽ 98 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ከዘመናዊ ጣዖታት መጠበቅ አለባቸው

[በገጽ 101 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ትክክል የሆነውን ለማድረግ ድፍረት ይኑራችሁ