በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የንስሐ ጸሎት

የንስሐ ጸሎት

ምዕራፍ ሃያ አምስት

የንስሐ ጸሎት

ኢሳይያስ 63:​15–64:​12

1, 2. (ሀ) መለኮታዊ ቅጣት ዓላማው ምንድን ነው? (ለ) አይሁዳውያን የይሖዋን ቅጣት ከተቀበሉ በኋላ ምን ምርጫ ይቀርብላቸዋል?

በ607 ከዘአበ በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሷ ላይ የደረሰው ጥፋት ከይሖዋ የመጣ ቅጣት ነበር። ይህም ይሖዋ በሕዝቡ እጅግ ማዘኑን የሚያሳይ ነው። ዓመፀኛ የሆነው የይሁዳ ሕዝብ ከባድ ቅጣት መቀበሉ የተገባ ነው። ይሁንና ይሖዋ ይህን እርምጃ የወሰደው አይሁዳውያን ከናካቴው ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ ለማድረግ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ይሖዋ ሰዎችን የሚቀጣው ለምን እንደሆነ ጠቁሟል:- “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።”​—⁠ዕብራውያን 12:11

2 አይሁዳውያን እንዲህ ያለ ከባድ ቅጣት ሲደርስባቸው ምን ይሰማቸው ይሆን? የይሖዋን ተግሣጽ ይጠሉ ይሆን? (መዝሙር 50:​16, 17) ወይስ ተግሣጹን እንደ ጥሩ ማሰልጠኛ አድርገው በመመልከት ይቀበሉታል? ንስሐ ገብተው ፈውስ ያገኙ ይሆን? (ኢሳይያስ 57:​18፤ ሕዝቅኤል 18:​23) የኢሳይያስ ትንቢት ከቀድሞው የይሁዳ ነዋሪዎች መካከል ቢያንስ የተወሰኑት ተግሣጹን ተቀብለው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠቁማል። ከ⁠ኢሳ. ምዕራፍ 63 ቁጥር 15-19 የመጨረሻ ቁጥሮች አንስቶ እስከ ኢሳ. ምዕራፍ 64 በሚዘልቀው የኢሳይያስ ትንቢት ላይ የይሁዳ ብሔር በጥፋቱ ተጸጽቶ ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ልመና እንዳቀረበ ተደርጎ ተገልጿል። ነቢዩ ኢሳይያስ ግዞተኛ የሚሆኑትን የአገሩን ሰዎች ወክሎ የንስሐ ጸሎት አቅርቧል። ጸሎቱን ያቀረበው ወደፊት የሚከናወኑት ነገሮች በፊቱ እየተፈጸሙ እንዳሉ ያህል አድርጎ ነው።

ርኅሩኅ አባት

3. (ሀ) ኢሳይያስ ያቀረበው ትንቢታዊ ጸሎት ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል ያቀረበው ጸሎት የኢሳይያስ ትንቢታዊ ጸሎት በባቢሎን የነበሩትን ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ሐሳብ እንደሚያንጸባርቅ የሚጠቁመው እንዴት ነው? (ገጽ 362 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

3 ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ወደ ይሖዋ ጸለየ:- “ከሰማይ ተመልከት፣ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ።” ነቢዩ እየተናገረ ያለው ይሖዋና የማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታቱ ስለሚኖሩበት መንፈሳዊ ሰማይ ነው። ኢሳይያስ በመቀጠል በግዞት የሚኖሩትን አይሁዳውያን ሐሳብ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ።” (ኢሳይያስ 63:15) ይሖዋ ኃይሉን ከመግለጥ የታቀበ ከመሆኑም በላይ ለሕዝቡ የነበረውን ጥልቅ ስሜት ማለትም ‘የልቡን ናፍቆትና ርኅራኄውን’ ተቆጣጥሮታል። ያም ሆኖ ይሖዋ የአይሁድ ሕዝብ ‘አባት’ ነው። የአይሁዳውያን ሥጋዊ አባቶች የሆኑት አብርሃምና እስራኤል (ያዕቆብ) ዳግም ሕያው ቢሆኑ ኖሮ ከሃዲ የሆኑ ዝርያዎቻቸውን እርግፍ አድርገው ለመተው ሊፈተኑ ይችሉ ነበር። ይሖዋ ግን ከእነሱ የላቀ ርኅራኄ አለው። (መዝሙር 27:​10) በመሆኑም ኢሳይያስ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “አቤቱ፣ አንተ አባታችን ነህ፣ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።”​—⁠ኢሳይያስ 63:16

4, 5.(ሀ) ይሖዋ ሕዝቡ መንገዱን እንዲስቱ አድርጓል ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ይሖዋ የሚፈልገው ምን ዓይነት አምልኮ ነው?

4 ኢሳይያስ በመቀጠል የሚከተለውን ከልብ የመነጨ ቃል ተናገረ:- “አቤቱ፣ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ።” (ኢሳይያስ 63:17) አዎን፣ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ አገልጋዮቹ እንዲመልስ ኢሳይያስ ተማጽኗል። ይሁንና ይሖዋ አይሁዳውያን መንገዱን እንዲስቱ አድርጓል ሲባል ምን ማለት ነው? ልባቸው ደንድኖ ለእሱ የነበራቸው ፍርሃት እንዲጠፋ ያደረገው ይሖዋ ነው ማለት ነውን? በፍጹም፤ ሆኖም ይህ ሲሆን ዝም ብሎ ተመልክቷል። በመሆኑም አይሁዳውያን እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ከመውደቃቸው የተነሳ ይሖዋ እንዲህ ያለ ነፃነት ባልሰጠን ኖሮ እስከማለት ደርሰዋል። (ዘጸአት 4:​21፤ ነህምያ 9:​16) ይሖዋ እጁን ጣልቃ አስገብቶ ስህተት የሆነ ነገር እንዳንሠራ በከለከለን ኖሮ ሲሉ ተመኝተዋል።

5 ይሁንና አምላክ እንዲህ አያደርግም። ይሖዋ ሲፈጥረን ነፃ ምርጫ የሰጠን ከመሆኑም በላይ እርሱን የመታዘዝም ሆነ ያለመታዘዙ ጉዳይ ለእያንዳንዳችን የተተወ የግል ውሳኔ ነው። (ዘዳግም 30:​15-19) ይሖዋ ከልብ በመነጨ እውነተኛ ፍቅር ተገፋፍተን እንድናመልከው ይፈልጋል። በመሆኑም አይሁዳውያን ይሖዋ የሰጣቸው መብት በእሱ ላይ እንዲያምፁ በር የከፈተላቸው ቢሆንም እንኳ በራሳቸው ነፃ ምርጫ እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸዋል። ልባቸው እንዲደነድን ያደረገው በዚህ መንገድ ነው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 36:​14-21

6, 7. (ሀ) አይሁዳውያን የይሖዋን መንገዶች መተዋቸው ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) አይሁዳውያን ምን ከንቱ ምኞት ተመኝተዋል? ይደረግልናል ብለው ሊጠብቁት የማይችሉትስ ነገር ምንድን ነው?

6 ውጤቱ ምን ሆነ? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል በትንቢት ገለጸ:- “የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል። ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል።” (ኢሳይያስ 63:18, 19) የይሖዋ ሕዝቦች ለተወሰነ ጊዜ መቅደሱን ወርሰው ነበር። በኋላ ግን ይሖዋ መቅደሱ እንዲወድምና ሕዝቡ ተማርከው እንዲወሰዱ ፈቅዷል። በዚያን ጊዜ በእርሱና በአብርሃም ዘሮች መካከል ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን እንዳልነበረና ስሙም በእነሱ እንዳልተጠራ ያህል ሆኖ ነበር። አይሁዳውያን በባቢሎን ግዞተኞች ሆነው በተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚከተለውን ልመና ያሰማሉ:- “ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፣ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፣ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፣ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ።” (ኢሳይያስ 64:1, 2) በእርግጥም ይሖዋ ለማዳን የሚያስችል ኃይል አለው። እንደ ሰማይ ያሉ መስተዳድሮችን በመበታተንና እንደ ተራራ ያሉ ግዛቶችን በማናወጥ ለሕዝቡ መዋጋት ይችላል። ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል እንደ እሳት የሚያቃጥለውን ቅንዓቱን በመግለጥ ስሙ እንዲታወቅ ማድረግ ይችላል።

7 ቀደም ባሉት ዘመናት ይሖዋ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ፈጽሞ ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፣ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ።” (ኢሳይያስ 64:3) እነዚህ ታላላቅ ሥራዎች የይሖዋን ኃይልና አምላክነት በግልጽ አንጸባርቀዋል። ይሁን እንጂ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ከሃዲ አይሁዳውያን ይሖዋ ለእነሱም እንዲህ ያለ ድንቅ ሥራ እንዲያከናውንላቸው ሊጠብቁ አይችሉም።

ማዳን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው

8. (ሀ) ይሖዋ አሕዛብ ከሚያመልኳቸው የሐሰት አማልክት የሚለይበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡን ማዳን ቢችልም እንኳ እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ያልፈለገው ለምንድን ነው? (ሐ) ጳውሎስ ኢሳይያስ 64:​4ን በመጥቀስ የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ገጽ 366 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

8 የሐሰት አማልክት ለአምላኪዎቻቸው ድንቅ የማዳን ሥራዎች ሊፈጽሙ አይችሉም። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም። ጽድቅን የሚያደርገውን በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ።” (ኢሳይያስ 64:4, 5ሀ) ‘ለሚፈልጉት ዋጋ የሚሰጠው’ ይሖዋ ብቻ ነው። (ዕብራውያን 11:​6) ጽድቅን የሚያደርጉትንና እሱን የሚያስቡትን ሁሉ ይጠብቃል። (ኢሳይያስ 30:​18) አይሁዳውያን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሆነው ተገኝተዋልን? በፍጹም። ኢሳይያስ ለይሖዋ እንዲህ አለ:- “እኛ ግን በእነርሱ ላይ ሳናቋርጥ ኀጢአት በመሥራታችን፣ እነሆ፣ ተቈጣህ፤ ታዲያ እንዴት መዳን እንችላለን?” (ኢሳይያስ 64:5ለ አ.መ.ት ) የአምላክ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜያት በኃጢአት ጎዳና በመመላለሳቸው ይሖዋ ከቁጣ የሚታቀብበትና እነሱን ለማዳን እርምጃ የሚወስድበት ምንም ምክንያት የለም።

9. ንስሐ የገቡ አይሁዶች በተስፋ ሊጠብቁት የሚችሉት ነገር ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

9 አይሁዳውያን ቀደም ሲል የሠሩትን ስህተት መፋቅ አይችሉም። ሆኖም ንስሐ ከገቡና ወደ ንጹሕ አምልኮ ከተመለሱ ይቅርታና በረከት እናገኛለን ብለው በተስፋ ሊጠባበቁ ይችላሉ። ይሖዋ ራሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ንስሐ የገቡ አይሁዶችን ከባቢሎን ግዞት ነፃ በማውጣት ይባርካቸዋል። ይሁንና በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርባቸዋል። ንስሐ ቢገቡም እንኳ ይሖዋ ፕሮግራሙን አይለውጥም። ይሁን እንጂ ነቅተው የሚጠባበቁና ለይሖዋ ፈቃድ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ውሎ አድሮ ነፃ መውጣታቸው አይቀርም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ይሖዋን በትዕግሥት ይጠባበቃሉ። (2 ጴጥሮስ 3:​11, 12) “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ተግባራዊ እናደርጋለን።​—⁠ገላትያ 6:9

10. የ⁠ኢሳይያስ ጸሎት የትኛውን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል?

10 ኢሳይያስ ያቀረበው ትንቢታዊ ጸሎት እንዲሁ የተለመደ ዓይነት የኃጢአት ኑዛዜ ብቻ አልነበረም። ሕዝቡ ራሱን ማዳን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ አምኖ መቀበሉን የሚያሳይ ጭምር ነው። ነቢዩ እንዲህ አለ:- “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፣ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፣ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።” (ኢሳይያስ 64:6) ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን ይከተሉት የነበረውን የክህደት ጎዳና በግዞት ዘመናቸው መገባደጃ ላይ እርግፍ አድርገው ትተውት ይሆናል። የጽድቅ ሥራዎች በመሥራት ወደ ይሖዋ ተመልሰው ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ነበሩ። መልካም ተግባሮቻቸው የሚያስመሰግኗቸው ቢሆኑም እንኳ ኃጢአትን ከማስተሰረይ አኳያ ሲታዩ ካደፈ ጨርቅ የማይሻሉ ነበሩ። የይሖዋ ይቅርታ በምሕረቱ ተገፋፍቶ የሚያደርገው የጸጋ ስጦታ ነው። በሥራ ሊገኝ የሚችል ነገር አይደለም።​—⁠ሮሜ 3:​23, 24

11. (ሀ) አብዛኞቹ አይሁዳውያን ግዞተኞች በምን ዓይነት መጥፎ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር? ይህ የሆነውስ ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) አይሁዳውያን በግዞት በነበሩበት ዘመን በጠንካራ እምነታቸው ግሩም ምሳሌ የሆኑት እነማን ናቸው?

11 ኢሳይያስ ወደፊት የሚሆነውን ሁኔታ አሻግሮ ሲመለከት ያስተዋለው ነገር ምንድን ነው? ነቢዩ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “ስምህንም የሚጠራ፣ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፣ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል።” (ኢሳይያስ 64:7) የሕዝቡ መንፈሳዊ ሁኔታ በእጅጉ አዝቅጧል። የአምላክን ስም በጸሎት አይጠሩም። ከባድ ኃጢአት በሆነው የጣዖት አምልኮ መካፈላቸውን ትተው የነበረ ቢሆንም አምልኳቸውን ቸል ብለው እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሖዋን “ሊይዝ የሚያስብ የለም።” ከፈጣሪያቸው ጋር ጤናማ ግንኙነት እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ምናልባትም አንዳንዶቹ ይሖዋን በጸሎት ለማነጋገር ብቁ እንዳልሆኑ ተሰምቷቸው ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ ለይሖዋ ምንም ቦታ ሳይሰጡ በዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸው ተጠምደው ሊሆን ይችላል። እርግጥ እንደ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤል፣ አዛርያና ሕዝቅኤል ያሉ በጠንካራ እምነታቸው ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች በግዞተኞቹ መካከል ይገኙ ነበር። (ዕብራውያን 11:​33, 34) በግዞት ያሳለፏቸው 70 ዓመታት እየተገባደዱ በመጡበት ወቅት እንደ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ያሉ ሰዎች የይሖዋን ስም በመጥራት ረገድ ግሩም አመራር ለመስጠት ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው አቅርበዋል። ያም ሆኖ የኢሳይያስ ትንቢታዊ ጸሎት በአብዛኞቹ ግዞተኞች ላይ የሚንጸባረቀውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚገልጽ ይመስላል።

‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’

12. ኢሳይያስ ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን ምግባራቸውን ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጸው እንዴት ነው?

12 ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን ለመለወጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። ኢሳይያስ እነሱን በመወከል እንዲህ ሲል ለይሖዋ ጸለየ:- “አሁን ግን፣ አቤቱ፣ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፣ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን።” (ኢሳይያስ 64:8) እነዚህም ቃላት ቢሆኑ ይሖዋ የአባትነት ሥልጣን እንዳለው ወይም ሕይወት ሰጪ እንደሆነ አምነው መቀበላቸውን የሚያሳዩ ናቸው። (ኢዮብ 10:​9) ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን በተፈለገው መንገድ ሊቀረጽ በሚችል የሸክላ ጭቃ ተመስለዋል። የይሖዋን ተግሣጽ የሚቀበሉ ሰዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ ከአምላክ መስፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሊቀረጹ ይችላሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በሸክላ ሠሪ የተመሰለው ይሖዋ የምሕረት እጁን ከዘረጋ ብቻ ነው። በመሆኑም ኢሳይያስ አይሁዳውያን ሕዝቡ መሆናቸውን እንዲያስብ ይሖዋን በድጋሚ ተማጽኗል:- “አቤቱ፣ እጅግ አትቈጣ፣ ለዘላለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፣ እባክህ፣ ተመልከት፣ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን።”​—⁠ኢሳይያስ 64:9

13. የአምላክ ሕዝቦች በግዞት በነበሩበት ወቅት የእስራኤል ምድር በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር?

13 አይሁዳውያን ከተማረኩ በኋላ በአረማውያን አገር በግዞት መኖር ከሚያስከትለው ችግር በተጨማሪ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ መውደማቸው በእነሱም ሆነ በአምላካቸው ላይ የሚያመጣውን ነቀፋ ተሸክመው ለመኖር ይገደዳሉ። ኢሳይያስ ያቀረበው የንስሐ ጸሎት ለዚህ ነቀፋ መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ይዘረዝራል:- “የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፣ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል።”​—⁠ኢሳይያስ 64:10, 11

14. (ሀ) ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰውን ሁኔታ አስቀድሞ ያስጠነቀቀው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በቤተ መቅደሱና ለእርሱ ይቀርቡ በነበሩት መሥዋዕቶች ቢደሰትም እንኳ ከዚያ የላቀ ዋጋ የነበረው ነገር ምንድን ነው?

14 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ከአባቶቻቸው በወረሱት ምድር ላይ የደረሰውን ሁኔታ ጠንቅቆ ያውቃል። ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ከ420 ዓመታት ገደማ በፊት ሕዝቡ ትእዛዛቱን ችላ ካሉና ሌሎች አማልክትን ካመለኩ ‘ከሰጣቸው ምድር እንደሚያጠፋቸው’ እና የተዋበውን ቤተ መቅደስ “ባድማ” እንደሚያደርገው አስጠንቅቋቸው ነበር። (1 ነገሥት 9:​6-9) ይሖዋ ለሕዝቡ በሰጠው ምድር፣ ለክብሩ በተገነባው ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስና ለእርሱ ይቀርቡ በነበሩት መሥዋዕቶች ይደሰት እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ታማኝነትና ታዛዥነት ከመሥዋዕትም ሆነ ከሌላ ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር የላቀ ዋጋ አላቸው። ነቢዩ ሳሙኤል ለንጉሥ ሳኦል እንዲህ ሲል መናገሩ ተገቢ ነው:- “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።”​—⁠1 ሳሙኤል 15:22

15. (ሀ) ኢሳይያስ በትንቢት ለይሖዋ ምን ልመና አቀረበ? ይሖዋስ መልስ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ እርግፍ አድርጎ እንዲተው ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

15 ይሁንና የእስራኤል አምላክ ንስሐ በገቡ ሕዝቦቹ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እያየ በቸልታ ሊያልፍ ይችላልን? ኢሳይያስ ትንቢታዊውን ጸሎት የደመደመው ይህን ጥያቄ በማቅረብ ነው። ግዞተኞቹን አይሁዳውያን በመወከል የሚከተለውን ልመና አቀረበ:- “አቤቱ፣ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን?” (ኢሳይያስ 64:12) በእርግጥም ይሖዋ በስተመጨረሻ ሕዝቡን ይቅር በማለት በ537 ከዘአበ ነፃ አውጥቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ንጹሕ አምልኮን መልሰው እንዲያቋቁሙ አድርጓል። (ኢዩኤል 2:​13) ይሁን እንጂ በርከት ያሉ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ዳግመኛ ከመጥፋታቸውም በላይ አምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቡን እርግፍ አድርጎ ትቷቸዋል። ለምን? የይሖዋ ሕዝቦች ትእዛዛቱን ቸል በማለታቸውና መሲሑን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። (ዮሐንስ 1:​11፤ 3:​19, 20) ይህ ከሆነ በኋላ ይሖዋ እስራኤልን በአዲስ መንፈሳዊ ሕዝብ ማለትም “በእግዚአብሔር እስራኤል” ተካው።​—⁠ገላትያ 6:​16፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9

‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው ይሖዋ

16. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ይቅር ባይነት በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

16 በእስራኤል ላይ ከደረሰው ሁኔታ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች ማግኘት ይቻላል። ይሖዋ “መሓሪና ይቅር ባይ” እንደሆነ እንረዳለን። (መዝሙር 86:​5) ፍጽምና የጎደለን ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን መዳን ማግኘታችን የተመካው በእሱ ምሕረትና ይቅር ባይነት ላይ ነው። እንዲህ ያለውን በረከት በራሳችን ጥረት ብቻ ልናገኘው አንችልም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እገሌ ከእገሌ ሳይል ሁሉንም ሰው ይቅር ይላል ማለት አይደለም። መለኮታዊ ይቅርታ የሚያገኙት ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው የሚመለሱ ሰዎች ብቻ ናቸው።​—⁠ሥራ 3:​19

17, 18. (ሀ) ይሖዋ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ስንገልጽለት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰማን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? (ለ) ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ትዕግሥት የሚያሳየው ለምንድን ነው?

17 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት ሐሳባችንንና ስሜታችንን ስንገልጽለት ጆሮውን ሰጥቶ እንደሚሰማን መረዳት እንችላለን። ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ ነው። (መዝሙር 65:​2, 3) ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 3:12) በተጨማሪም የንስሐ ጸሎት ራስን ዝቅ አድርጎ ኃጢአትን መናዘዝን እንደሚጨምር እንማራለን። (ምሳሌ 28:​13) እንዲህ ሲባል ግን የአምላክን ምሕረት አላግባብ ልንጠቀምበት እንችላለን ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘የእግዚአብ​ሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳያደርጉት’ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​1

18 በመጨረሻም፣ አምላክ ኃጢአተኛ የሆኑ ሕዝቦቹን የሚታገሰው ለምን እንደሆነ እንማራለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ የሚታገሰው “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ” እንደሆነ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:​9) ይሁንና የአምላክን ትዕግሥት አላግባብ ከመጠቀም የማይመለሱ ሰዎች ውሎ አድሮ መቀጣታቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “[ይሖዋ] ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቊጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።”​—⁠ሮሜ 2:6-8

19. ይሖዋ ምንጊዜም የማይለወጡ ምን ባሕርያት አሉት?

19 ይሖዋ ከጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ጋር ግንኙነት ያደርግ የነበረው በዚህ መንገድ ነው። ይሖዋ የማይለወጥ በመሆኑ ዛሬም ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና በእነዚሁ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመረኮዘ ነው። ተገቢውን ቅጣት ከመስጠት ወደ ኋላ የማይል ቢሆንም እንኳ ምንጊዜም “እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” አምላክ ነው።​—⁠ዘጸአት 34:6, 7

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 362 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ዳንኤል ያቀረበው የንስሐ ጸሎት

ነቢዩ ዳንኤል አይሁዳውያን በግዞት ባሳለፏቸው 70 ዓመታት በሙሉ በባቢሎን ኖሯል። በ68ኛው የግዞት ዓመት ገደማ ላይ ዳንኤል የእስራኤላውያን የግዞት ኑሮ እየተገባደደ እንዳለ ከኤርምያስ ትንቢት ተረዳ። (ኤርምያስ 25:​11፤ 29:​10፤ ዳንኤል 9:​1, 2) በመሆኑም መላውን የአይሁድ ብሔር በመወከል ለይሖዋ የንስሐ ጸሎት አቀረበ። ዳንኤል እንዲህ ሲል ገልጿል:- ‘ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ። ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፣ ተናዘዝሁም።’​—⁠ዳንኤል 9:3, 4

ዳንኤል ጸሎቱን ያቀረበው ኢሳይያስ በምዕራፍ 63 እና 64 ላይ የሚገኘውን ትንቢታዊ ጸሎት ከጻፈ ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ቅን ልብ ያላቸው ብዙዎቹ አይሁዶች በግዞት ባሳለፏቸው አስቸጋሪ ዓመታት ወደ ይሖዋ ጸልየው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የብዙዎቹን ታማኝ አይሁዳውያን ስሜት እንደሚወክል የሚታመነውን የዳንኤል ጸሎት ጎላ አድርጎ ይገልጸዋል። በመሆኑም የዳንኤል ጸሎት በኢሳይያስ ትንቢታዊ ጸሎት ላይ የተገለጸው ሐሳብ በባቢሎን የኖሩትን ታማኝ አይሁዳውያን ስሜት እንደሚያንጸባርቅ ይጠቁማል።

በዳንኤልና በኢሳይያስ ጸሎት መካከል ያሉትን አንዳንድ ተመሳሳይ ሐሳቦች ተመልከት።

ኢሳይያስ 63:​16 ዳንኤል 9:​15

ኢሳይያስ 63:​18 ዳንኤል 9:​17

ኢሳይያስ 64:​1-3 ዳንኤል 9:​15

ኢሳይያስ 64:​4-7 ዳንኤል 9:​4-7

ኢሳይያስ 64:​6 ዳንኤል 9:​9, 10

ኢሳይያስ 64:​10, 11 ዳንኤል 9:​16-18

[በገጽ 366 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ዓይንም አላየችም”

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የኢሳይያስን መጽሐፍ በመጥቀስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እንዲህ እንናገራለን።” (1 ቆሮንቶስ 2:9) * ጳውሎስ የተናገረው ቃልም ሆነ ኢሳይያስ የተጠቀመባቸው አገላለጾች ይሖዋ ሰማያዊ ውርሻ ላላቸውም ሆነ ምድራዊቷን ገነት ለሚወርሱት ሕዝቦቹ ያዘጋጃቸውን ነገሮች አያመለክቱም። ጳውሎስ የኢሳይያስን ቃላት የጠቀሰው የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መረዳትንና ይሖዋ የሚፈነጥቀውን መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ማግኘትን ጨምሮ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ያገኟቸውን በረከቶች ለማመልከት ነው።

ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስተዋል የምንችለው ይሖዋ ራሱ በወሰነው ጊዜ ሲገልጥልን ነው። ይህን መብት ማግኘት የምንችለው ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ያለን መንፈሳዊ ሰዎች ከሆን ብቻ ነው። የጳውሎስ ቃላት በጣም ደካማ የሆነ መንፈሳዊ አቋም ያላቸውን ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት የሌላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። ዓይኖቻቸው መንፈሳዊ እውነቶችን ማየት ወይም ማስተዋል አይችሉም፤ ጆሮቻቸውም እንዲህ ያሉ ነገሮችን መስማት ወይም መረዳት አይችሉም። አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ስላዘጋጃቸው ነገሮች የሚገልጸው እውቀት ወደ ልባቸው ጠልቆ አይገባም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህን ነገሮች እንደ ጳውሎስ ላሉ ራሳቸውን ለአምላክ ለወሰኑ ሰዎች በመንፈሱ በኩል ገልጦላቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​1-16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.56 ጳውሎስ የጠቀሳቸው ቃላት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቃል በቃል ሰፍረው አይገኙም። በ⁠ኢሳይያስ 52:​15፤ 64:​4 እና ኢሳ. 65:​17 ላይ ያሉትን ሐሳቦች አንድ ላይ አጣምሮ የጠቀሰ ይመስላል።

[በገጽ 367 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ሕዝቦች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ‘ለጥቂት ጊዜ’ ወርሰው ነበር