በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብዝነታቸው ተጋለጠ!

ግብዝነታቸው ተጋለጠ!

ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ

ግብዝነታቸው ተጋለጠ!

ኢሳይያስ 58:​1-14

1. ኢየሱስም ሆነ ይሖዋ ግብዝነትን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ይህ ባሕርይ በኢሳይያስ ዘመን ተስፋፍቶ የነበረውስ እንዴት ነው?

ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፣ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:28) ኢየሱስ ግብዝነትን በማውገዝ የሰጠው አስተያየት የሰማያዊ አባቱን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። የኢሳይያስ ትንቢት ኢሳ. 58⁠ኛ ምዕራፍ በዋነኛነት የሚናገረው በይሁዳ ተስፋፍቶ ስለነበረው የግብዝነት አኗኗር ነው። ምድሪቱ በጠብ፣ በግፍና በአመፅ ተሞልታ የነበረ ከመሆኑም በላይ የሰንበትንም ሕግ የሚጠብቁት እንዲሁ ለወጉ ያህል ብቻ ነበር። ሕዝቡ ለይሖዋ የይስሙላ አገልግሎት ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ለደንቡ ያህል በመጾም ለአምልኳቸው ያደሩ መስለው ለመታየት ይሞክሩ ነበር። ይሖዋ ማንነታቸውን ማጋለጡ ምንም አያስደንቅም!

‘ለሕዝቡ ኃጢአታቸውን ንገር’

2. ኢሳይያስ የይሖዋን መልእክት ሲያውጅ ምን ዓይነት መንፈስ አሳይቷል? ዛሬስ በተመሳሳይ የተሰጣቸውን ተልእኮ እየተወጡ ያሉት እነማን ናቸው?

2 ይሖዋ፣ ይሁዳ በፈጸመችው ድርጊት የተንገሸገሸ ቢሆንም የተናገራቸው ቃላት ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ ያስተላለፈውን ከልብ የመነጨ ልመናም ያዘሉ ናቸው። ያም ሆኖ ይሖዋ ቀጥተኛ ወቀሳ መስጠቱ አልቀረም። በመሆኑም ኢሳይያስን እንዲህ ሲል አዘዘው:- “በኃይልህ ጩኽ፣ አትቈጥብ፣ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፣ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።” (ኢሳይያስ 58:1) ኢሳይያስ የይሖዋን ቃል በድፍረት ማወጁ በሕዝቡ ዘንድ ጥላቻ እንዲያተርፍ ሊያደርገው ቢችልም መልእክቱን ከማወጅ ወደ ኋላ አላለም። በዚህም ጊዜ ቢሆን “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ሲል በተናገረ ጊዜ ያሳየው ዓይነት ለአምላክ የማደር መንፈስ ነበረው። (ኢሳይያስ 6:​8) ኢሳይያስ በዘመናችን ላሉት የአምላክን ቃል የመስበክና ሃይማኖታዊ ግብዝነትን የማጋለጥ ተልእኮ ለተሰጣቸው የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት ያለ ግሩም የጽናት ምሳሌ ነው!​—⁠መዝሙር 118:​6፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​1-5

3, 4. (ሀ) በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ያልሆኑትን መስለው ለመቅረብ የሞከሩት እንዴት ነው? (ለ) በይሁዳ ምን ዓይነት ሁኔታ ሰፍኖ ነበር?

3 በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ከላይ ሲታዩ ይሖዋን የሚፈልጉና የጽድቅ ፍርዶቹን የሚወድዱ ይመስላሉ። ይሖዋ በመቀጠል ምን እንዳለ ተመልከት:- “ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ።” (ኢሳይያስ 58:2) የይሖዋን መንገዶች የሚወድዱት ከልባቸው ነበርን? በፍጹም። ‘ጽድቅን ያደረገ ሕዝብ’ መስለው ቢታዩም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ እንዲሁ ለታይታ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ‘የአምላካቸውን ፍርድ ትተው ነበር።’

4 በዘመኑ የነበረው ሁኔታ ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለነቢዩ ሕዝቅኤል ከገለጠለት ሁኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። ይሖዋ አይሁዳውያን እርስ በርሳቸው “እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ” እንደሚባባሉ ለሕዝቅኤል ነግሮታል። ሆኖም እንዲህ የሚያደርጉት ከልባቸው እንዳልሆነ በመግለጽ እንደሚከተለው ሲል አስጠንቅቆታል:- “ወደ አንተ ይመጣሉ፣ . . . ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፣ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች። እነሆ፣ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም።” (ሕዝቅኤል 33:​30-32) በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎችም ይሖዋን ዘወትር እንደሚፈልጉ ቢናገሩም ቃሉን ግን አልታዘዙም።

የይስሙላ ጾም

5. አይሁዳውያን መለኮታዊ ሞገስ ለማግኘት የሞከሩት እንዴት ነው? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጣቸው?

5 አይሁዳውያን መለኮታዊ ሞገስ ለማግኘት በሚል ለወጉ ያህል ይጾሙ ነበር። ሆኖም ይህ ለይስሙላ ያደርጉት የነበረው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከይሖዋ ጋር እንዲራራቁ ከማድረግ በቀር የፈየደላቸው ነገር የለም። ግራ በመጋባት መንፈስ እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ:- “ስለ ምን ጾምን፣ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፣ አንተም አላወቅህም?” ይሖዋ እንዲህ ሲል በግልጽ ይመልስላቸዋል:- “እነሆ፣ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፣ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?”​—⁠ኢሳይያስ 58:3-5

6. አይሁዳውያን የይስሙላ ጾም ይጾሙ እንደነበረ የሚያሳየው የትኛው ድርጊታቸው ነው?

6 ሕዝቡ በአንድ በኩል እየጾሙ፣ ለታይታ የሚደረግ ጽድቅ እየሠሩና አልፎ ተርፎም የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ እየጠየቁ በሌላ በኩል የራሳቸውን ተድላና ቁሳዊ ጥቅም ያሳድዱ ነበር። ድርጊታቸው ሁሉ ጠብ፣ ግፍና አመፅ የሞላበት ነበር። ይህን ምግባራቸውን ለመሸፋፈን ሲሉ ለታይታ የሚደረጉ የሐዘን መግለጫዎችን በመፈጸም ማለትም ራሳቸውን እንደ እንግጫ ዝቅ በማድረግና ማቅ ለብሰው አመድ ላይ በመቀመጥ ከኃጢአታቸው ንስሐ እንደገቡ ለማስመሰል ይሞክራሉ። ይሁንና ከአመፅ ድርጊታቸው ካልተመለሱ ይህ ሁሉ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ከእውነተኛ ጾም ጋር ሊታይ የሚገባውን አምላክ የሚፈልገውን ዓይነት ጸጸትና የንስሐ ፍሬ አላሳዩም። ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ዋይታቸውን ቢያቀልጡትም በሰማይ ተሰሚነት አላገኙም።

7. በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ግብዝ የሆኑት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎችም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸሙ ያሉት እንዴት ነው?

7 በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም እንደዚሁ ለታይታ የሚደረግ የጾም ሥርዓት ነበራቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይጾሙ ነበር! (ማቴዎስ 6:​16-18፤ ሉቃስ 18:​11, 12) ብዙዎቹ ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢሳይያስ ዘመን እንደነበረው ትውልድ ክፉና ጨቋኝ ነበሩ። በመሆኑም ኢየሱስ የአምልኮ ሥርዓታቸው ከንቱ እንደሆነ በመግለጽ እነዚህን ግብዝ ሃይማኖታዊ መሪዎች በድፍረት አጋልጧቸዋል። (ማቴዎስ 15:​7-9) በዛሬው ጊዜም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፣ በሥራቸው ይክዱታል።” (ቲቶ 1:16) እንዲህ ያሉ ሰዎች አምላክ ምሕረት እንደሚያሳያቸው አድርገው ሊያስቡ ቢችሉም ሥራቸው ግን ግብዞች መሆናቸውን በግልጽ ይመሰክራል። በአንጻሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደሩ ከመሆናቸውም በላይ እውነተኛ የሆነ የወንድማማችነት ፍቅር አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 13:​35

እውነተኛ ንስሐ ምን ማድረግን ይጨምራል?

8, 9. እውነተኛ ንስሐ በምን አዎንታዊ ተግባራት መደገፍ ይኖርበታል?

8 ይሖዋ ሕዝቡ ለሠሩት ኃጢአት እንዲጾሙ ብቻ ሳይሆን ንስሐ እንዲገቡም ይፈልጋል። እንዲህ ካደረጉ ሞገሱን ያገኛሉ። (ሕዝቅኤል 18:​23, 32) ይሖዋ አንድ ሰው መጾሙ ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ቀደም ሲል የፈጸማቸውን የኃጢአት ድርጊቶች እስከተወ ድረስ ብቻ እንደሆነ ገልጿል። ይሖዋ በመቀጠል ያቀረባቸውን እውነተኛ ዝንባሌን ለመመርመር የሚያስችሉ ጥያቄዎች ተመልከት:- “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት [“ሰንሰለት፣” አ.መ.ት] ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?”​—⁠ኢሳይያስ 58:6

9 ሰንሰለትና ቀንበር ጨቋኝ የሆነን የባርነት አገዛዝ ጥሩ አድርገው የሚገልጹ ተስማሚ ተምሳሌቶች ናቸው። ስለዚህ ሕዝቡ በአንድ በኩል እየጾሙ በሌላ በኩል እንደነሱው ያሉ አማኞችን ከመጨቆን ይልቅ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ ማክበር ይኖርባቸዋል። (ዘሌዋውያን 19:​18) በደል እየፈጸሙባቸው ያሉትንና አላግባብ በባርነት ቀንበር የያዟቸውን ሰዎች መልቀቅ አለባቸው። * ከልብ የመነጨ ለአምላክ የማደር መንፈስ ሳያሳዩና ለወንድሞቻቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ሳይገልጹ እንደ ጾም ያሉትን ለታይታ የሚደረጉ ሃይማኖታዊ ተግባራት ቢፈጽሙ ዋጋ አይኖረውም። በኢሳይያስ ዘመን ይኖር የነበረው ነቢዩ ሚክያስ “ይሖዋ ከአንተ የሚሻው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ደግነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ አይደለምን?” ሲል ጽፏል።​—⁠ሚክያስ 6:​8 NW

10, 11. (ሀ) አይሁዳውያን ከመጾም ይልቅ ምን ቢያደርጉ የተሻለ ነበር? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ይሖዋ ለአይሁዶች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ፍትሕ፣ ደግነትና ልክን ማወቅ ለሌሎች መልካም ማድረግን የሚጠይቁ ባሕርያት ናቸው። ይህ ደግሞ የይሖዋ ሕግ መሠረታዊ ገጽታ ነው። (ማቴዎስ 7:​12) አይሁዳውያን ከመጾም ይልቅ ያላቸውን ቁሳዊ ነገር ለተቸገሩ ሰዎች ቢያካፍሉ የተሻለ ነበር። ይሖዋ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- [እኔ የመረጥሁት ጾም ] እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?” (ኢሳይያስ 58:7) አዎን፣ ለታይታ ከመጾም ይልቅ አቅሙ ያላቸው ሰዎች የሥጋ ዘመዶቻቸው ለሆኑት የተቸገሩ የይሁዳ ነዋሪዎች ምግብ፣ ልብስ ወይም መጠለያ መስጠት ይኖርባቸዋል።

11 ወንድማዊ ፍቅርና ርኅራኄ ማሳየትን አስመልክቶ ይሖዋ የገለጻቸው እነዚህ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች በኢሳይያስ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖችም ጥሩ መመሪያ ሆነው ያገለግላሉ። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:10) በተለይ ዛሬ የምንኖርበት ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ አስጨናቂ እየሆነ በመምጣቱ የክርስቲያን ጉባኤ ፍቅርና የመዋደድ መንፈስ የሰፈነበት ቦታ ሊሆን ይገባዋል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1፤ ያዕቆብ 1:​27

ታዛዥነት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል

12. ይሖዋ ሕዝቡ ከታዘዙት ምን ያደርግላቸዋል?

12 የይሖዋ ሕዝቦች የሰጣቸውን ፍቅራዊ ወቀሳ ሰምተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ጥሩ ማስተዋል ቢኖራቸው ኖሮ ምንኛ በተጠቀሙ ነበር! ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፣ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፣ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፣ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም:- እነሆኝ ይላል።” (ኢሳይያስ 58:8, 9ሀ) እንዴት ያሉ ልብ የሚነኩ አስደሳች ቃላት ናቸው! ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትንና ጽድቅን የሚወድዱ ሰዎችን ይባርካል እንዲሁም ይጠብቃል። የይሖዋ ሕዝቦች በሌሎች ላይ የሚፈጽሙትን በደልና የግብዝነት ድርጊታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው እሱን ከታዘዙት የወደፊት ሕይወታቸው ብሩህ ይሆናል። ይሖዋ ሕዝቡ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ በማድረግ ‘ይፈውሳቸዋል።’ የቀድሞ አባቶቻቸው ግብጽን ለቅቀው ሲወጡ ጥበቃ እንዳደረገላቸው ሁሉ ለእነሱም ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ልመናቸውንም ፈጥኖ ይሰማል።​—⁠ዘጸአት 14:​19, 20, 31

13. አይሁዳውያን የይሖዋን ማሳሰቢያ ሰምተው ተግባራዊ ካደረጉ ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል?

13 ይሖዋ በመቀጠል ተጨማሪ ማሳሰቢያ ሰጠ:- “ከመካከልህ [ጨቋኝና ኢፍትሐዊ የሆነ የባርነት] ቀንበርን ብታርቅ፣ ጣትህንም [በንቀት ወይም በሐሰት ውንጀላ ሳይሆን አይቀርም] መጥቀስ ብትተው፣ ባታንጐራጉርም፣ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፣ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፣ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።” (ኢሳይያስ 58:9ለ, 10) ራስ ወዳድነትና በደል ራስን የሚጎዱ ባሕርያት ከመሆናቸውም በላይ ይሖዋን ያስቆጣሉ። በአንጻሩ ግን በተለይ ለተራቡና ለተቸገሩ ደግነትና ልግስና ማሳየት የአምላክን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። አይሁዳውያን እነዚህን እውነታዎች አስተውለው ተግባራዊ ቢያደርጉ መንፈሳዊ ብርሃናቸውና ብልጽግናቸው ማንኛውንም ዓይነት ጨለማ በመግፈፍ እንደ ቀትር ፀሐይ ሙሉ በሙሉ እንዲያበሩ ያደርጋቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሞገሳቸውና የበረከታቸው ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ያስከብራሉ እንዲሁም ያስመሰግናሉ።​—⁠1 ነገሥት 8:​41-43

ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ የተመለሰ ሕዝብ

14. (ሀ) በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ነቢዩ ለተናገራቸው ቃላት የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ በዚህም ጊዜ ቢሆን ምን ከማድረግ አልታቀበም?

14 የሚያሳዝነው ሕዝቡ የይሖዋን ልመና ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ በክፋት ድርጊቶች ተዘፈቁ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ አስቀድሞ ባስጠነቀቀው መሠረት ለምርኮ አሳልፎ ሰጣቸው። (ዘዳግም 28:​15, 36, 37, 64, 65) ያም ሆኖ ይሖዋ በመቀጠል በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸው ቃላት ተስፋ የሚፈነጥቁ ናቸው። አምላክ ቅጣቱን ተቀብለው የሚስተካከሉና ንስሐ የሚገቡ አይሁዳውያን ቀሪዎች ባድማ ሆኖ ወደቆየው ምድራቸው በደስታ እንደሚመለሱ ተንብዮአል።

15. ይሖዋ አይሁዳውያን ወደ ምድራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በማስመልከት ምን አስደሳች ትንቢት ተናገረ?

15 ይሖዋ ሕዝቡ በ537 ከዘአበ ወደ ምድራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ አሻግሮ በመመልከት በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናገረ:- “እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።” (ኢሳይያስ 58:11 አ.መ.ት ) ይሖዋ በፀሐይ ክው ብሎ የደረቀውን የእስራኤል ምድር እንደገና እንዲያብብና ፍሬያማ እንዲሆን በማድረግ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ይመልሰዋል። ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ በመንፈሳዊ በድን ሆኖ የነበረውን ‘አጥንታቸውን’ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ በማድረግና በማበርታት ንስሐ የገቡ ሕዝቦቹን ይባርካል። (ሕዝቅኤል 37:​1-14) ሕዝቡ ራሳቸው “በውሃ እንደ ረካ” እና በመንፈሳዊ ፍሬ እንደተሞላ የአትክልት ቦታ ይሆናሉ።

16. ምድሪቱ ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ የምትመለሰው እንዴት ነው?

16 ተሃድሶው የባቢሎን ወራሪዎች በ607 ከዘአበ ያወደሟቸውን ከተሞች መልሶ መገንባትን ይጨምራል። “ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፣ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም:- ሰባራውን ጠጋኝ፣ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ።” (ኢሳይያስ 58:12) “ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች” እና “የብዙ ትውልድም መሠረት” (ወይም ለብዙ ትውልዶች ፈርሰው የቆዩት መሠረቶች) የሚሉት ተመሳሳይ መግለጫዎች ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት ቀሪዎች የፈረሱትን የይሁዳ ከተሞች በተለይ ደግሞ ኢየሩሳሌምን መልሰው እንደሚገነቡ ያመለክታሉ። (ነህምያ 2:​5፤ 12:​27፤ ኢሳይያስ 44:​28) “ሰባራውን” ሁሉ የሚጠግኑ ሲሆን ይህ ቃል በኢየሩሳሌምም ሆነ በሌሎች ከተሞች ግንቦች ላይ የተፈጠሩትን ክፍተቶች በጠቅላላ የሚያመለክት ነው።​—⁠ኤርምያስ 31:​38-40፤ አሞጽ 9:​14

ሰንበትን በታማኝነት መጠበቅ የሚያስገኛቸው በረከቶች

17. ይሖዋ ሕዝቡ የሰንበት ሕጎችን እንዲጠብቁ የተማጸነው እንዴት ነው?

17 የሰንበት ሕግ አምላክ ለሕዝቡ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደህንነት ያለውን አሳቢነት የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 2:​27) ይሖዋ የቀደሰው ይህ ቀን እስራኤላውያን ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት የሚችሉበት ልዩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። የሚያሳዝነው ግን በኢሳይያስ ዘመን ሰንበት ከንቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚፈጸሙበትና ሰዎች የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን የሚያረኩበት ዕለት ሆኖ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን ዳግመኛ መውቀስ አስፈልጎታል። አሁንም እንደገና ልባቸውን ለመንካት በመጣር እንዲህ አለ:- “ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ ሰንበትንም ደስታ፣ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፣ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፣ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፣ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፣ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።”​—⁠ኢሳይያስ 58:13, 14

18. ይሁዳ ሰንበትን ባለማክበሯ ምን አደጋ ተጋርጦባታል?

18 ሰንበት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል፣ ለመጸለይና በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆኖ ይሖዋን ለማምለክ የሚያስችል ዕለት ነው። አይሁዳውያን ይሖዋ ለእነሱ ሲል ባከናወናቸው ድንቅ ሥራዎች ላይ እንዲሁም በሕጉ ላይ በተንጸባረቀው ፍትሕና ፍቅር ላይ እንዲያሰላስሉ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። ስለዚህ ሕዝቡ ይህን ቅዱስ ቀን በታማኝነት ማክበራቸው ከአምላካቸው ጋር ይበልጥ እንዲቀራረቡ ሊረዳቸው ይገባ ነበር። ይሁንና አይሁዳውያን ሰንበትን አላግባብ እየተጠቀሙበት ስለነበር የይሖዋን በረከት የማጣት አደጋ ሊጋረጥባቸው ችሏል።​—⁠ዘሌዋውያን 26:​34፤ 2 ዜና መዋዕል 36:​21

19. የአምላክ ሕዝቦች የሰንበትን ሕግ ካከበሩ ምን የተትረፈረፉ በረከቶች ያገኛሉ?

19 ያም ሆኖ አይሁዳውያን ከቅጣቱ ተምረው የሰንበትን ዝግጅት ካከበሩ የተትረፈረፉ በረከቶች የማግኘት አጋጣሚ አላቸው። እውነተኛውን አምልኮ ከተከተሉና የሰንበትን ሕግ ካከበሩ በመላ ሕይወታቸው ይባረካሉ። (ዘዳግም 28:​1-13፤ መዝሙር 19:​7-11) ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ሕዝቡን ‘በምድር ከፍታዎች ላይ ያወጣቸዋል።’ ይህ አገላለጽ ጥበቃ ማግኘትንና በጠላቶች ላይ ድል መቀዳጀትን ያመለክታል። ከፍታ ቦታዎችን ማለትም ኮረብታዎችንና ተራሮችን መቆጣጠር የቻለ ምድሩን ሁሉ መቆጣጠር ይችላል። (ዘዳግም 32:​13፤ 33:​29) እስራኤል ይሖዋን ትታዘዝ በነበረበት ዘመን ሕዝቡ የእሱን ጥበቃ ከማግኘቱም በላይ በሌሎች ብሔራት ይከበርና አልፎ ተርፎም ይፈራ ነበር። (ኢያሱ 2:​9-11፤ 1 ነገሥት 4:​20, 21) አሁንም ይሖዋን ከታዘዙ የቀድሞ ክብራቸውን መልሰው ማግኘት ይችላሉ። ይሖዋ በቀድሞ አባቶቻቸው በኩል ቃል የገባቸውን በረከቶች በተለይ ደግሞ የተስፋይቱን ምድር ቋሚ ይዞታ አድርጎ እንደሚሰጣቸው የገባውን ቃል በመፈጸም “የያዕቆብን ርስት” ሙሉ ድርሻ ይሰጣቸዋል።​—⁠መዝሙር 105:​8-11

20. ለክርስቲያኖች የቀረላቸው “የሰንበት ዕረፍት” ምንድን ነው?

20 ይህ ለክርስቲያኖች የሚሆን ትምህርት ይዟልን? ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሞት የሰንበትን ድንጋጌዎች ጨምሮ የሙሴ ሕግ ቀርቷል። (ቆላስይስ 2:​16, 17) ይሁን እንጂ አይሁዳውያን መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲያስቀድሙና ከይሖዋ ጋር እንዲቀራረቡ የሚያደርገው የሰንበት ሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዛሬ ላሉት የይሖዋ አምላኪዎችም በጣም ጠቃሚ ነው። (ማቴዎስ 6:​33፤ ያዕቆብ 4:​8) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ላይ “የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል” ሲል ተናግሯል። ክርስቲያኖች ወደዚህ “የሰንበት ዕረፍት” የሚገቡት ይሖዋን በመታዘዝና በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ላይ ባላቸው እምነት ተመርኩዘው ጽድቅን በመከታተል ነው። (ዕብራውያን 3:​12, 18, 19፤ 4:​6, 9-11, 14-16) ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የሰንበት ሥርዓት የሚጠብቁት በሳምንት አንድ ቀን ሳይሆን በየዕለቱ ነው።​—⁠ቆላስይስ 3:​23, 24

መንፈሳዊ እስራኤል ‘በምድር ከፍታዎች ላይ ይወጣል’

21, 22. ይሖዋ የአምላክ እስራኤልን ‘በምድር ከፍታዎች ላይ ያወጣው’ በምን መንገድ ነው?

21 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ከባቢሎናዊ ግዞት ነፃ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ የሰንበትን ሕግ መሠረታዊ ዓላማ በታማኝነት አክብረዋል። በመሆኑም ይሖዋ ‘በምድር ከፍታዎች ላይ አውጥቷቸዋል።’ በምን መንገድ? በ1513 ከዘአበ ይሖዋ የአብርሃም ዘሮች ትእዛዙን ከጠበቁ የካህናት መንግሥትና የተቀደሰ ሕዝብ እንደሚሆኑ ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘጸአት 19:​5, 6) በምድረ በዳ ባሳለፏቸው 40 ዓመታት ንስር ጫጩቶቿን እንደምትሸከም ይሖዋም ሕዝቡን በመሸከም ጥበቃ ያደረገላቸው ከመሆኑም በላይ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አትረፍርፎ በመስጠት ባርኳቸዋል። (ዘዳግም 32:​10-12) ይሁን እንጂ ሕዝቡ እምነት በማጣቱ ሊያገኝ ይችል የነበረውን መብት ሁሉ አጥቷል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የካህናት መንግሥት አለው። ይህ መንግሥት መንፈሳዊው የአምላክ እስራኤል ነው።​—⁠ገላትያ 6:​16፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9

22 ‘በፍጻሜው ዘመን’ ይህ መንፈሳዊ ብሔር በይሖዋ በማመን የጥንቷ እስራኤል ሳታሳየው የቀረችውን እምነት አሳይቷል። (ዳንኤል 8:​17) የዚህ ብሔር አባላት አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎችና መንገዶች አጥብቀው በመከተላቸው በመንፈሳዊ ሁኔታ ይሖዋ ወደ ከፍታ ቦታ አውጥቷቸዋል። (ምሳሌ 4:​4, 5, 8፤ ራእይ 11:​12) የአኗኗር ዘይቤያቸው በዙሪያቸው ካለው ርኩሰት የጸዳና ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ደንቦችን የተከተለ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸውን መንገድ ከመከተል ይልቅ በይሖዋና በቃሉ ‘ይደሰታሉ።’ (መዝሙር 37:​4) በዓለም ዙሪያ ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ይሖዋ በመንፈሳዊ ፍንክች ሳይሉ ጸንተው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። ከ1919 ወዲህ መንፈሳዊ ‘አገራቸው’ አልተደፈረም። (ኢሳይያስ 66:​8) ከፍ ያለውን ስሙን በዓለም ዙሪያ በደስታ በማወጅ ለስሙ የቆሙ ሕዝቦች ሆነው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። (ዘዳግም 32:​3፤ ሥራ 15:​14) በተጨማሪም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ቅን ሰዎች ከእነሱ ጋር አብረው የይሖዋን መንገዶች የመማርና በጎዳናው የመመላለስ ታላቅ መብት አግኝተዋል።

23. ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹ ‘ከያዕቆብ ርስት እንዲበሉ’ ያደረጋቸው እንዴት ነው?

23 ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹ ‘ከያዕቆብ ርስት እንዲበሉ’ አድርጓቸዋል። የዕብራውያን አባት የሆነው ይስሐቅ በኤሳው ፋንታ ያዕቆብን በባረከበት ጊዜ ተስፋ በተሰጠበት የአብርሃም ዘር የሚያምኑ ሁሉ እንደሚባረኩ ተንብዮአል። (ዘፍጥረት 27:​27-29፤ ገላትያ 3:​16, 17) ከኤሳው በተለየ ሁኔታ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው ልክ እንደ ያዕቆብ “ቅዱሳን ነገሮችን” በተለይ ደግሞ አምላክ አትረፍርፎ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ምግብ ‘ያደንቃሉ።’ (ዕብራውያን 12:​16, 17 NW ፤ ማቴዎስ 4:​4) ይሖዋ ተስፋ በተሰጠበት ዘርና በዘሩ ተባባሪዎች አማካኝነት እያከናወነ ያለውን ነገር የሚገልጸውን እውቀት አካትቶ የያዘው ይህ መንፈሳዊ ምግብ የሚያጠነክርና ኃይልን የሚያድስ ከመሆኑም ሌላ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው እጅግ ወሳኝ ነው። በመሆኑም የአምላክን ቃል በማንበብና በቃሉ ላይ በማሰላሰል ይህን መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረው መመገባቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 1:​1-3) እንደነሱው ካሉ አማኞች ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ይህን ምግብ በደስታ ለሌሎች በሚያካፍሉበት ጊዜ የእውነተኛ አምልኮን ላቅ ያሉ መስፈርቶች መጠበቅ አለባቸው።

24. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

24 እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ ማንኛውንም ዓይነት የግብዝነት መንፈስ አጥብቀው መዋጋት ይኖርባቸዋል። “የያዕቆብን ርስት” በመመገብ ‘በምድር ከፍታዎች’ ላይ መንፈሳዊ ጥበቃ አግኝተው ይኖሩ ዘንድ ምኞታችን ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ይሖዋ ዕዳ ውስጥ የገቡ ሰዎች ራሳቸውን ለባርነት በመሸጥ በሌላ አባባል ተቀጥረው በመሥራት ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:​39-43) ይሁን እንጂ ሕጉ ባሪያዎች በርኅራኄ መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ግፍ የተፈጸመባቸው ባሮች በነፃ እንዲለቀቁ ይደረጋል።​—⁠ዘጸአት 21:​2, 3, 26, 27፤ ዘዳግም 15:​12-15

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 278 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይሁዳውያን ለወጉ ያህል ቢጾሙና ራሳቸውን ዝቅ ቢያደርጉም አካሄዳቸውን አላስተካከሉም

[በገጽ 283 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቅሙ ያላቸው ሰዎች ለተቸገሩ መጠለያ፣ ልብስ ወይም ምግብ ይሰጣሉ

[በገጽ 286 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሁዳ ንስሐ ከገባች የፈራረሱ ከተሞቿን መልሳ ትገነባለች