ለተሰብሳቢዎች የቀረበ መረጃ
ለየት ያለ ስብሰባ
የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት አገልግሎታቸውን የማስፋት ፍላጎት ያላቸው ከ23 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አቅኚዎች፣ ለመንግሥቱ ወንጌላውያን በተዘጋጀው ትምህርት ቤት መካፈል ከሚፈልጉ አመልካቾች ጋር እሁድ ከሰዓት በኋላ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል። ይህ ስብሰባ የሚደረግበት ቦታና ሰዓት አስቀድሞ በማስታወቂያ ይገለጻል።
“ደፋር ሁኑ”! የ2018 የይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የተዘጋጀለተሰብሳቢዎች የቀረበ መረጃ
መዋጮዎች ስብሰባው አስደሳች ብሎም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዲሆን ለማድረግ ሲባል ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ በቂ ወንበሮች እንዲሁም የድምፅ መሣሪያዎችና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶች እንዲኖሩ ዝግጅት ተደርጓል። በፈቃደኝነት የምታደርጉት መዋጮ እነዚህን ወጪዎች ለመሸፈን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወነውን ሥራ ለመደገፍ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የመዋጮ ሣጥን የሚል ምልክት በግልጽ የተጻፈባቸው ሣጥኖች በስብሰባው ቦታ አመቺ በሆኑ ስፍራዎች ላይ ተቀምጠዋል። የምታደርጉትን መዋጮ ሁሉ ከልብ እናደንቃለን። የበላይ አካሉ የአምላክን መንግሥት ዓላማ ለማራመድ በልግስና ለምታደርጉት ድጋፍ ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ይገልጻል።
አስተናጋጆች አስተናጋጆች የተመደቡት እናንተን ለመርዳት ነው። ስለዚህ መኪና ማቆምን፣ በመተላለፊያዎች ላይ መቆምን፣ ወንበር መያዝንና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ የሚሰጧችሁን መመሪያ በመከተል እባካችሁ ሙሉ በሙሉ ተባበሯቸው።
ወንበር እባካችሁ ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ። ወንበር መያዝ የሚቻለው ለቤተሰባችሁ አባላት፣ ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ አብረዋችሁ ለሚኖሩ ወይም በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለምታስጠኗቸው ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ። እባካችሁ በአጠገባችሁ ባሉት ወንበሮች ላይ ዕቃዎቻችሁን አታስቀምጡ።
የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ይህ ዝግጅት የተደረገው ድንገት ለሚያጋጥም የጤና ችግር ብቻ እንደሆነ እባካችሁ አስታውሱ።
የፈቃደኛ አገልግሎት ከክልል ስብሰባው ጋር በተያያዘ በሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች መካፈል ከፈለጋችሁ እባካችሁ ለፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል አመልክቱ።
ጠፍተው የተገኙ ዕቃዎች የሚቀመጡበት ቦታ ጠፍተው የተገኙ ዕቃዎች ሁሉ ወደዚህ ክፍል መምጣት አለባቸው። ዕቃ ከጠፋባችሁ ወደዚህ ክፍል በመሄድ ንብረታችሁን ጠይቃችሁ መውሰድ ትችላላችሁ። ከወላጆቻቸው የጠፉ ልጆች ወደዚህ ክፍል መወሰድ አለባቸው። ሆኖም በማንም ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዳይፈጠር እባካችሁ ልጆቻችሁን በቅርብ ተከታተሏቸው እንዲሁም ከአጠገባችሁ እንዳይርቁ ጠብቋቸው።
ጥምቀት የተለየ ዝግጅት ካልተደረገ በቀር ተጠማቂዎቹ የሚቀመጡት ከመድረኩ ፊት ለፊት ባለው ቦታ ላይ ይሆናል። የጥምቀት እጩዎች ቅዳሜ ጠዋት የሚቀርበው የጥምቀት ንግግር ከመጀመሩ በፊት በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ መገኘት አለባቸው። እያንዳንዱ ተጠማቂ ለጥምቀት ተስማሚ የሆነ ልብስና ፎጣ ይዞ መምጣት አለበት።
በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የተዘጋጀ