በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በሙሉ ፍጹም የተለየ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት መሥርተዋል። ብዙውን ጊዜ ስለ እኛ የተሳሳቱ ወሬዎች ስለሚነገሩ ያለ ምክንያት በሩቁ ከሚጠሉን ምንጮች ስለእኛ እውነቱን ለማወቅ መጠበቁ ስህተት ይሆናል። ስለዚህ ከዋና ዋናዎቹ እምነቶቻችን መካከል አንዳንዶቹን ስንገልጽልህ ደስ ይለናል።

አምላክ፣ መጽሐፍ ቅዱስና መሲሑ

አምላክ የግል መጠሪያ ስም አለው። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች እርሱን የሚያመልኩ ሰዎች በዚህ ስም መጠቀም እንዳለባቸው ያምናሉ። ሁሉን የሚችለው አምላክ ስሙ “ይሖዋ” እንደሆነ ለሙሴ ነግሮታል። (ዘጸአት 6:3 የ1879 እትም፤ መዝሙር 83:18 NW) ሙሴ፣ አብርሃምና ሌሎች በጥንት ጊዜ የነበሩ የታመኑ ሰዎች በዚህ የአምላክ ስም ተጠቅመዋል። (ዘፍጥረት 12:8 NWሩት 2:4, 12 NW) እንዲያውም ይሖዋ የሚለው ስም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ሺህ ጊዜ ይገኛል። ስለዚህ በጥንት ጊዜ እንደነበሩት የታመኑ ሰዎች በአምላክ ስም እንጠቀማለን እንዲሁም በስሙ እናገለግላለን።—ኢሳይያስ 43:10

የይሖዋ ምሥክሮች ቅዱስ ጽሑፉ በሌላ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና በዛሬው ጊዜ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት ብቸኛው የመገናኛ መሥመር እንደሆነ ያምናሉ። ንጉሥ ዳዊት ይህን ጉዳይ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ” በማለት ገልጾታል። (2 ሳሙኤል 23:2) ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያብራሩ በማድረግ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥብቅ እንከተላለን።

የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚታወቀው ክፍል ከታናክ ወይም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚቀጥልና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ይቀበላሉ። በመጀመሪያ በግሪክኛ የተጠናቀረውን የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ማለትም “አዲስ ኪዳንን” የጻፉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ናቸው። እነዚህ ሰዎች እንደ ሙሴ፣ ኢሳይያስና ዳንኤል ያሉ ዕብራውያን ነቢያት መሲሑን በማስመልከት የመዘገቧቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተዋል። በዘፍጥረት 49:10፤ በኢሳይያስ 52:13–53:12 እና በዳንኤል 9:24-27 ላይ የሚገኙትን የመሰሉ ትንቢቶች በዘመናቸው ድንቅ አስተማሪ በነበረው በኢየሱስ ላይ ሲፈጸሙ አይተዋል።

ከዚህም የተነሳ አምላክ የሰውን ዘር የአዳም ኃጢአት ካስከተለበት መዘዝ ለማዳን ሕጋዊ መንገድ አድርጎ የተጠቀመበት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን የይሖዋ ምሥክሮች አምነው ይቀበላሉ። ስርየት ለማግኘት መሥዋዕት መቅረብ እንዳለበት የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ያሳያል። (ዘሌዋውያን 6:6, 11, 15, 30፤ ዘኁልቁ 15:22-29) ይሁን እንጂ የሙሴ ቃል ኪዳን በሁኔታዎች ላይ የተመካና ጊዜያዊ ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6) ነቢዩ ኤርምያስ የተሟላና ዘላቂ የኃጢአት ይቅርታ ስለሚያስገኝ “አዲስ ቃል ኪዳን” ተናግሯል። (ኤርምያስ 31:31-34) ፍጹም በሆነ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተው ይህ “አዲስ ቃል ኪዳን” ታማኝ ሰዎች ቃል የተገባላቸውን ምድራዊ ገነት እንዲወርሱ መንገድ ይጠርጋል።—ኢሳይያስ 53:4-6, 10-12፤ 65:21-25

የይሖዋ ምሥክሮች የሕዝበ ክርስትና ክፍል አይደሉም። ሕዝበ ክርስትና የተመሠረተችው ኢየሱስ ከሞተ ከ300 ዓመት አካባቢ በኋላ ሲሆን እምነቷም ኢየሱስ ካስተማረው ትምህርት በጣም የራቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ራሱ አምላክ ነው የሚለውን የሕዝበ ክርስትናን የሥላሴ እምነት አንቀበልም። ይህ አምላክን የማያስከብር ትምህርት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በአንድም ቦታ ላይ ተጠቅሶ አይገኝም። (ዘዳግም 6:4፤ ማርቆስ 12:29፤ ዮሐንስ 14:28) መስቀልን እንደ ምልክት አድርገን አንጠቀምም። እንደ ሐውልት ሠርተን ለአምልኮታችን የምንገለገልበትም ቅርፅ የለም። እነዚህ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዙ ተግባሮች ናቸው።—ዘጸአት 20:3-5፤ 1 ዮሐንስ 5:21

የአምላክ መንግሥት

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአምላክ መንግሥት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ጎላ ተደርጎ የተገለጸ ጭብጥ ነው። ነቢዩ ዳንኤል መሲሑን በተመለከተ ሲናገር “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” ብሎ ተናግሯል። (ዳንኤል 7:13, 14) የይሖዋ ምሥክሮች በመሲሑ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነና የዚህ መስተዳድር አገዛዝ በምድር ላይ እውነተኛ ሰላም እንደሚያሰፍን ያምናሉ።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ መዝሙር 46:8, 9፤ 72:7

ቅዱሳን ጽሑፎች የዚህ መስተዳድር መቀመጫ በሰማይ እንደሆነና ከሞት ተነስቶ በአምላክ ቀኝ የተቀመጠው መሲሕ የዚህ መስተዳድር ገዥ እንደሆነ ይገልጻሉ። (መዝሙር 110:1, 2) የይሖዋ ምሥክሮች ውሎ አድሮ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመሲሐዊው አገዛዝ ተገዥዎች በመሆን በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ያምናሉ። ስለዚህ ምድር ፈጽሞ እንደማትጠፋና “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ጽኑ እምነት አለን።—መዝሙር 37:29

ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት የሚመጣው እንዴት ነው? መንግሥቱ ሲመጣ አምላክ በምድር ጉዳዮች በቀጥታ እጁን እንዲያስገባ መጽሐፍ ቅዱስ ተጨባጭ ማስረጃ ያቀርባል። “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል፤ . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው? በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜያቸውን በማግኘት ላይ ከሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ በእኛ ትውልድ እንደሚመጣ ያምናሉ። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የዚህን የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ዘመን” ገጽታ በዝርዝር ለይተው የሚያሳውቁ ትንቢቶችን ይዘዋል። በማቴዎስ 24:3-14፤ በሉቃስ 21:7-13, 25-32 እና በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ ከተመዘገቡት ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

ይሖዋ አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አሳባችንና ኃይላችን ስለምንወድና ጎረቤቶቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን የምንወድ በመሆናችን በብሔር፣ በዘር ወይም በኑሮ ደረጃ የተከፋፈልን አይደለንም። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 6:4, 5፤ ማርቆስ 12:30, 31) በየአገሩ በሚገኙ መንፈሳዊ ወንድማማቾቻችን መካከል በሚታየው ፍቅርና አንድነት በሰፊው ተለይተን እንታወቃለን። ይህም ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው አምላክን እንደሚያመልኩና ‘ጦርነት እንደማይማሩ’ ከሚናገረው ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ሶፎንያስ 3:9፤ ዮሐንስ 13:35) ከዚህም የተነሳ ከብሔራት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ አቋም እንይዛለን። አምላክን በተገቢው መንገድ ማምለክ ማለት መዋሸትን፣ መስረቅን፣ ዝሙትን፣ ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ደምን አላግባብ መጠቀምን፣ ጣዖት ማምለክንና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተወገዙ ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ጨምሮ ሥነ ምግባር ከጎደለው አኗኗር መራቅ ማለት እንደሆነ እናምናለን።—ዘጸአት 20:3-5, 13-17፤ ዘሌዋውያን 17:10፤ 20:13፤ መዝሙር 15:1-5፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11

የወደፊቱ ተስፋ

የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ማለት በዚህ የነገሮች ስርዓት እንደሚታየው መወለድ፣ ማደግና መሞት ማለት ብቻ እንዳልሆነ ያምናሉ። በአምላክ መንግሥት የሚከናወነውን የሙታንን ትንሣኤ ጨምሮ ወደፊት ስለሚመጣው ሕይወት ሙሉ ትምክህት አለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን እናምናለን። (መዝሙር 146:3, 4፤ መክብብ 9:5፤ ሕዝቅኤል 18:4) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የማትሞት ነፍስ አለች የሚለውን ወይም የሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ አያስተምርም። ከዚያ ይልቅ ሙታን ወደፊት ሕይወት ሊያገኙ የሚችሉት አምላክ በትንሣኤ ካሰባቸው ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 25:8፤ ዳንኤል 12:1, 2, 13

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት ዛሬ ያሉትን መስተዳድሮች በሚያጠፋበት ወቅት በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በሕይወት እንደሚተርፉ ያምናሉ። ከዚያም ኖኅና ቤተሰቡ ከውኃ ጥፋቱ እንደዳኑ ሁሉ እነዚህ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በጸዳች ምድር ላይ በደስታ ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 11:1-9፤ 65:17፤ ማቴዎስ 24:36-39) መጽሐፍ ቅዱስ “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ” ስለሚል አንድ ሰው ይህ ዓለም ሲጠፋ በሕይወት ለመትረፍ ከፈለገ አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላት አለበት።—ምሳሌ 2:20-22፤ መዝሙር 37:9-11, 29

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት “በ1993 ዓ.ም ከታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። አንዳንዶቹን ጥቅሶች በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።