በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹን ለማካፈል የሚጠቀሙባቸው መንገዶች

ምሥራቹን ለማካፈል የሚጠቀሙባቸው መንገዶች

ምሥራቹን ለማካፈል የሚጠቀሙባቸው መንገዶች

ክርስቲያኖች ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ታዘዋል፤ እንዲህ ሲባል ግን ሌሎችን በመጫን ወይም በማስገደድ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ኢየሱስ ‘ለድኾች ምሥራቹን የመስበክ፣ ልባቸው የተሰበረባቸውን የመጠገን እንዲሁም የሚያለቅሱትን የማጽናናት’ ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር። (ማቴዎስ 28:19፤ ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:18, 19) የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች በማወጅ ይህን ተልእኮ መፈጸም ይፈልጋሉ። በጥንት ዘመን ይኖር እንደነበረው እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ‘በሚሠራው ጸያፍ ተግባር የሚያዝኑና የሚያለቅሱ’ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።—ሕዝቅኤል 9:4

በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ባሉት ነገሮች የሚጨነቁ ሰዎችን ለማግኘት የሚጠቀሙበት በብዙዎች ዘንድ በጣም የታወቀው ዘዴ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ ነው። ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ” እንደነበር ሁሉ እነሱም ሰዎችን ለማግኘት ተመሳሳይ ጥረት ያደርጋሉ። የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ቢሆኑ እንዲሁ አድርገዋል። (ሉቃስ 8:1፤ 9:1-6፤ 10:1-9) ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ማድረግ በሚቻልባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰዎችን በአካባቢያቸውም ሆነ በዓለም ላይ እየተከናወኑ ስላሉ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ወይም አሳሳቢ ሁኔታዎች ለጥቂት ደቂቃዎች ለማነጋገር በዓመቱ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ እያንዳንዱ ሰው ቤት ለመሄድ ጥረት ያደርጋሉ። አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ጠቅሰው በዚያ ላይ ከተወያዩ በኋላ የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየ አመቺ በሆነ ጊዜ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ይይዛሉ። የቤቱ ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን ወስዶ እንዲያነብ ግብዣ ይቀርብለታል፤ እንዲሁም ፈቃደኛ ከሆነ ያለምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ይደረግለታል። በዚህ መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦችንም ሆነ ቤተሰቦችን በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” የሚሰብኩበት ሌላው መንገድ በየአካባቢው ባሉ ‘የመንግሥት አዳራሽ’ ብለው በሚጠሯቸው ቦታዎች የሚያደርጉት ስብሰባ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አዳራሾች ሳምንታዊ ስብሰባዎች ያደርጋሉ። ከእነዚህ ስብሰባዎች አንዱ ወቅታዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚቀርብ ሕዝባዊ ንግግር ሲሆን ከዚህ ንግግር ቀጥሎ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አማካኝነት በአንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ ወይም ትንቢት ላይ ውይይት ይደረጋል። በሌላ ቀን ደግሞ ሦስት ክፍሎች ያሉት ፕሮግራም ለማካሄድ በመንግሥት አዳራሹ ይሰበሰባሉ። በመጀመሪያ፣ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀ መጽሐፍ ወይም ብሮሹር አማካኝነት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ይደረጋል። በመቀጠል፣ የይሖዋ ምሥክሮች የተሻሉ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንዲሆኑ ሥልጠና የሚያገኙበት ትምህርት ቤት ይካሄዳል። በመጨረሻም፣ በአካባቢው በሚደረገው የምሥክርነት ሥራ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ክፍል ይቀርባል።

ማንኛውም ሰው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላል። በስብሰባው ወቅት ምንም ዓይነት ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም። እነዚህ ስብሰባዎች ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።” በግል ማጥናትና ምርምር ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ከሌሎች ጋር መሰብሰብ ለተግባር ያነሳሳል፦ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል።”—ዕብራውያን 10:24, 25፤ ምሳሌ 27:17

በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች የዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸውን በሚያከናውኑባቸው ጊዜያት ከሰዎች ጋር ሲገናኙ አጋጣሚውን ተጠቅመው ምሥራቹን ለመናገር ጥረት ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ከጎረቤቶቻቸው አሊያም በአውቶቡስ ወይም በአውሮፕላን ላይ ካገኙት ሰው ጋር አጠር ያለ ውይይት በማድረግ፣ ከወዳጅ ወይም ከዘመድ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው በመጫወት አለዚያም በእረፍት ሰዓት ላይ ከሥራ ባልደረባቸው ጋር በመወያየት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በአብዛኛው ምሥክርነት የሚሰጠው እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ነበር፤ ለምሳሌ በኮረብታ ላይ አረፍ ብሎ ሳለ፣ በባሕር ዳርቻ ሲያልፍ፣ ሰው ቤት ተጋብዞ በመመገብ ላይ እያለ፣ ሠርግ ላይ ሲገኝ ወይም በገሊላ ባሕር ላይ በዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ሲጓዝ አጋጣሚዎቹን ለመመሥከር ተጠቅሞባቸዋል። በምኩራቦችና በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ አስተምሯል። በሄደበት ቦታ ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልግ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድም የእሱን ፈለግ ለመከተል ይጥራሉ።—1 ጴጥሮስ 2:21

በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም መስበክ

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩትን ትምህርት በተግባር የማያውሉት ከሆነ ከላይ በተዘረዘሩት መንገዶች ተጠቅመው ምሥራቹን ለአንተ መስበካቸው ምንም ፋይዳ አይኖረውም። አንድ ሰው የሚያስተምረውን ነገር ሥራ ላይ የማያውል ከሆነ ግብዝነት ይሆንበታል፤ ደግሞም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሃይማኖታዊ ግብዝነት የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን ከመከተል ወደኋላ ብለዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ተወቃሽ ሊሆን አይችልም። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ነበሯቸው፤ ያም ሆኖ ኢየሱስ ግብዞች በማለት አውግዟቸዋል። እነዚህ ሰዎች የሙሴን ሕግ እንደሚያነቡ ከተናገረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፣ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ።” (ማቴዎስ 23:3) አንድ ክርስቲያን በአኗኗሩ ጥሩ ምሳሌ መሆኑ ከረጅም ሰዓት ስብከት የበለጠ ሰዎችን የማሳመን ኃይል አለው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ባል ያላቸው ክርስቲያን ሚስቶች ይህን ነጥብ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ምክር ተሰጥቷቸዋል፦ “ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:1, 2

ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች በሚያስተምሯቸው ክርስቲያናዊ ባሕርያት ረገድ ጥሩ ምሳሌ በመሆንም ምሥራቹ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይጥራሉ። ‘ሰዎች እንዲያደርጉላቸው የሚፈልጉትን ነገር እነሱም ለሌሎች ለማድረግ’ ይጥራሉ። (ማቴዎስ 7:12) እንዲህ ለማድረግ የሚጥሩት ለእምነት ባልንጀሮቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች ነው። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን በዚህ ረገድ ሙሉ በሙሉ ይሳካላቸዋል ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ምሥራቹን በመናገር ብቻ ሳይሆን በሚችሉበት ጊዜ ሁሉ የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት ጭምር ለሰው ሁሉ በጎ ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት አላቸው።—ያዕቆብ 2:14-17

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃዋይ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቬነዝዌላ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩጎዝላቪያ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ተስማሚ በሆነ መንገድ የተሠሩት የመንግሥት አዳራሾች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት የሚደረግባቸው ቦታዎች ናቸው

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የይሖዋ ምሥክሮች በቤተሰብ ኑሯቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚያስተምሩትን ትምህርት ሥራ ላይ ለማዋል ይጥራሉ