በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እነማን ናቸው?

እነማን ናቸው?

እነማን ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች በደንብ እንድታውቃቸው ይፈልጋሉ። ምናልባት ጎረቤቶችህ ወይም የሥራ ባልደረቦችህ የይሖዋ ምሥክሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም በሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከእነሱ ጋር ትገናኝ ይሆናል። መንገድ ላይ ለሰዎች መጽሔቶቻቸውን ሲሰጡ አይተሃቸው ሊሆን ይችላል። አለዚያም ቤትህ መጥተው ለጥቂት ደቂቃዎች አነጋግረሃቸው ይሆናል።

እውነቱን ለመናገር፣ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አንተ ያስባሉ፤ ጥሩ ሕይወት እንድትመራም ይፈልጋሉ። ወዳጆችህ ሊሆኑ ብሎም ስለ ራሳቸው፣ ስለ እምነታቸውና ስለ ድርጅታቸው ሊነግሩህ ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም ስለ ሌሎች ሰዎችና ሁላችንም ስለምንኖርበት ዓለም ምን አመለካከት እንዳላቸው ሊገልጹልህ ይሻሉ። የዚህ ብሮሹር ዓላማም ይህ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ መንገዶች እንደ ማንኛውም ሰው ናቸው። እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ችግሮች እንዲሁም ስሜታቸውን የሚደቁሱ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ፍጹም ስላልሆኑ ስህተት የሚሠሩባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ ከስህተታቸው ለመማር ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠናሉ። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን ለእሱ ለመስጠት የወሰኑ ሲሆን ከዚህ ውሳኔያቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። በሁሉም እንቅስቃሴዎቻቸው በአምላክ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ይፈልጋሉ።

የሚያምኑባቸው ነገሮች በሰዎች አስተሳሰብ ወይም በሃይማኖታዊ ቀኖና ላይ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ነው። “ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ አምላክ እውነተኛ ሆኖ እንዲገኝ አድርጉ” በማለት በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ስሜት ይጋራሉ። (ሮም 3:4) የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆኑ ተደርገው በሚቀርቡ ትምህርቶች ረገድ የቤርያ ሰዎች የወሰዱትን ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ፤ እነዚህ ሰዎች የሐዋርያው ጳውሎስን ስብከት ካዳመጡ በኋላ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” (የሐዋርያት ሥራ 17:11) የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች የሚያስተምሯቸው ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በሙሉ በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን መመርመር አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። ከእነሱ ጋር በምታደርገው ውይይትም ይህን እንድታደርግ አጥብቀው ይመክራሉ።

ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያምናሉ። እንዲሁም 66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት እንደተጻፉና ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ እንደሆኑ አድርገው ይቀበሏቸዋል። በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለው የሚጠሩት ሲሆን ብሉይ ኪዳንን ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ብለው ይጠሩታል። የግሪክኛውንም ሆነ የዕብራይስጡን ቅዱሳን መጻሕፍት እንደ አምላክ ቃል አድርገው የሚቀበሏቸው ሲሆን በአንድ ጥቅስ ላይ የተሠራበት አገላለጽ ወይም መቼት ጥቅሱ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው በግልጽ የሚጠቁም እስካልሆኑ ድረስ ጥቅሱን ቃል በቃል ይወስዱታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ትንቢቶች መካከል ብዙዎቹ እንደተፈጸሙ፣ አንዳንዶቹ በመፈጸም ላይ እንዳሉና ሌሎቹ ደግሞ ወደፊት እንደሚፈጸሙ ይገነዘባሉ።

የሚጠሩበት ስም

የይሖዋ ምሥክሮች? አዎን፣ ራሳቸውን የሚጠሩት እንዲህ ብለው ነው። ስማቸው ስለ ይሖዋ፣ ስለ እሱ አምላክነትና ስለ ዓላማዎቹ እንደሚመሠክሩ የሚገልጽ ነው። “አምላክ፣” “ጌታ” እና “ፈጣሪ” የሚሉት መጠሪያዎች “ፕሬዚዳንት፣” “ንጉሥ” እና “ጄኔራል” እንደሚሉት መጠሪያዎች ሁሉ የማዕረግ ስሞች ሲሆኑ ትልቅ ሥልጣን ያላቸውን የተለያዩ አካላት ለማመልከት ሊያገለግሉ ይችላሉ። “ይሖዋ” ግን የግል ስም ሲሆን የሚያመለክተው ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክና የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ ነው። የአምላክን ስም በተመለከተ ዘፀአት 6:3 በ1879 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።”

ይሖዋ (ወይም በሮም ካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል ላይ እንደተቀመጠውና አንዳንድ ምሑራን እንደሚመርጡት ያህዌህ) የሚለው ስም በዕብራይስጥ በተጻፉት በመጀመሪያዎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ግን ስሙን በዚህ መንገድ ከማስቀመጥ ይልቅ “አምላክ” ወይም “ጌታ” በሚሉት ቃላት ተክተውታል። የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “እግዚአብሔር” የሚለውን መጠሪያ ይጠቀማል። ይሁን እንጂ በእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ እንኳ የመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅጂ ይሖዋ የሚለውን ስም የሚጠቀምባቸውን ቦታዎች አብዛኛውን ጊዜ ማወቅ ይቻላል፤ ለምሳሌ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ይሖዋ” የሚለው ስም “እግዚአብሔር” በሚለው መጠሪያ በተተካበት ስፍራ ለየት ባለ የሆሄ ቅርጽ ወይም አጣጣል በሚከተለው መንገድ እንዲጻፍ ተደርጓል፦ እግዚአብሔር (ያህዌ)። አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ ወይም ያህዌ የሚሉትን ስሞች ይጠቀማሉ። ለምሳሌ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በ⁠ዘፀአት 15:3 ላይ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው” ይላል።

የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ስያሜ መጠራት የጀመሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 43 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ መሠረት አድርገው ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ የዓለማችን ትዕይንት በፍርድ ቤት ውስጥ ከሚከናወነው ሁኔታ ጋር ተመሳስሏል፤ ጻድቅ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡት የአሕዛብ አማልክት ይህን ለማረጋገጥ ምሥክሮቻቸውን እንዲያቀርቡ አሊያም ከይሖዋ ጎን የቆሙትን ሰዎች ምሥክርነት አዳምጠው እውነቱን እንዲቀበሉ ተጋብዘዋል። በዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “‘ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]። ‘ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም።’”—ኢሳይያስ 43:10, 11

ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት በነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት በምድር ላይ ምሥክሮች ነበሩት። ከእነዚህ የእምነት ሰዎች አንዳንዶቹ በ⁠ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተዘረዘሩ በኋላ በ⁠ዕብራውያን 12:1 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን፦ “እንግዲህ እጅግ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።” ኢየሱስ በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ “እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት እንድመሠክር ነው” ብሏል። እንዲሁም “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 18:37፤ ራእይ 3:14) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8

በዛሬው ጊዜ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከ7,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በክርስቶስ ኢየሱስ ስለሚተዳደረው የይሖዋ መንግሥት ምሥራች ይሰብካሉ፤ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ብለው መጥራታቸው ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን ለእሱ ወስነዋል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያምናሉ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች ስም በፍርድ ቤት ውስጥ ከሚከናወነው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተገልጿል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ከ7,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ አንተ ያስባሉ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ የግል ስም በጥንታዊ ዕብራይስጥ