በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ

ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ

ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ

ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ከጀመረ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በ1870ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አንድ አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ በአሌጌኒ (በአሁኑ ጊዜ የፒትስበርግ ክፍል ናት)፣ ፔንሲልቬንያ ውስጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ። የቡድኑ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ቻርልስ ቴዝ ራስል ነበር። የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለው መጽሔት የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 1879 ወጣ። እስከ 1880 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከዚህ አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ቡድን የወጡ በርካታ ጉባኤዎች በአቅራቢያው ባሉ ግዛቶች ተቋቋሙ። በ1881 ዛዮንስ ዎች ታወር ትራክት ሶሳይቲ የተቋቋመ ሲሆን በ1884 ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ተመዘገበ፤ በዚህ ወቅት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ራስል ነበር። ከጊዜ በኋላ ማኅበሩ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የሚል ስያሜ አግኝቷል። ብዙዎች ከቤት ወደ ቤት እየመሠከሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያበረክቱ ነበር። በ1888 ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚህ ሥራ ያውሉ የነበሩት ሰዎች ብዛት 50 ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን በመላው ዓለም ከ800,000 የሚበልጡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚህ ሥራ ያዋሉ ሰዎች አሉ።

በ1909 ሥራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሆነ፤ የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤትም አሁን ወደሚገኝበት ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ተዛወረ። በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የስብከት ዓምዶች ይወጡ ነበር፤ እነዚህ የስብከት ዓምዶች በ1913 በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳና በአውሮፓ በአራት የተለያዩ ቋንቋዎች በሺዎች በሚቆጠሩ ጋዜጦች ላይ ይወጡ ነበር። በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት፣ ቡክሌቶችና ትራክቶች ተሰራጭተዋል።

በ1912 “የፍጥረት ፎቶ ድራማን” የማዘጋጀት ሥራ ተጀመረ። ይህ ፊልም በድምፅ በተቀናበሩ ስላይዶችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች አማካኝነት ከምድር አፈጣጠር አንስቶ እስከ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያሳይ ነበር። ፊልሙን ማሳየት የተጀመረው በ1914 ሲሆን በየቀኑ 35,000 ሰዎች ይመለከቱት ነበር። ይህ ፊልም በድምፅ ለተቀናበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እድገት ፈር ቀዳጅ ነበር።

1914 ዓመተ ምህረት

በጣም ወሳኝ የሆነ ጊዜ በመቃረብ ላይ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1876 በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚታተም ባይብል ኤግዛምነር በተባለ መጽሔት ላይ “የአሕዛብ ዘመናት የሚያበቁት መቼ ነው?” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ይህ መጽሔት በጥቅምት እትሙ በገጽ 27 ላይ የአሕዛብ ዘመናት በ1914 ዓ.ም. እንደሚያበቁ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 21:24) በ1914 ይፈጸማሉ ተብለው የተጠበቁት ነገሮች ሁሉ ባይፈጸሙም እንኳ ይህ ዓመት የአሕዛብ ዘመን ያበቃበት ጊዜ ከመሆኑም ሌላ ልዩ ትርጉም ያለው ዓመት ነው። በርካታ የታሪክ ሊቃውንትና ተንታኞች 1914 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት እንደሆነ ይስማማሉ። የሚከተሉት አስተያየቶች ለዚህ እንደ ምሳሌ ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ፦

“በታሪክ ዘመናት ውስጥ ከነበሩት የተለየ ክስተት ያልታየባቸው ዓመታት መካከል የመጨረሻው ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በፊት የነበረው 1913 ነው።”—በዋሽንግተን ዲሲው ታይምስ-ሄራልድ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ፣ መጋቢት 13, 1949

“ሁለቱን የዓለም ጦርነቶችና ቀዝቃዛውን ጦርነት ያካተተው ከ1914 እስከ 1989 ያለው የ75 ዓመት ዘመን፣ አብዛኛው የዓለም ክፍል በጦርነት፣ ከጦርነት በማገገም ወይም ለጦርነት በመዘጋጀት ያሳለፈው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሆነ የታሪክ ሊቃውንት ይናገራሉ።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ግንቦት 7, 1995

“መላው ዓለም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ፍርስርሱ ወጣ፤ ለምን እንዲህ እንደሆነ ግን እስከ ዛሬ ድረስ ማወቅ አልቻልንም። ከዚያ በፊት፣ ሰዎች የሚያልሙትን ነገር ሁሉ የሚያገኙበት ፍጹም የሆነ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ አድርገው ያስቡ ነበር። ሰላምና ብልጽግና ሰፍኖ ነበር። ወዲያው ሁሉ ነገር እንዳልነበረ ሆነ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ነገር ቀጥ ብሎ የቆመ ይመስላል። . . . በዚህ ምዕተ ዓመት የተገደሉት ሰዎች ብዛት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከተገደሉት ይበልጣል።”—ዶክተር ዎከር ፐርሲ፣ አሜሪካን ሜዲካል ኒውስ፣ ኅዳር 21, 1977

አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ኮንራት አደናወር የተባሉት የጀርመን መሪ “ከ1914 ወዲህ የሰው ልጆች ሰላምና መረጋጋት የሚባል ነገር አጥተዋል” ብለዋል።—ዘ ዌስት ፓርከር፣ ክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ጥር 20, 1966

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1916 ሞተ፤ በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በቦታው ተተካ። ብዙ ለውጦች ተደረጉ። ከመጠበቂያ ግንብ በተጨማሪ ዘ ጎልደን ኤጅ የተባለ መጽሔት መታተም ጀመረ። (በአሁኑ ጊዜ ንቁ! ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከ80 በሚበልጡ የተለያዩ ቋንቋዎች ወደ 40,000,000 በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል።) ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው የስብከት ሥራ የበለጠ ትኩረት ተሰጠ። በ1931 እነዚህ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ቡድኖች ለመለየት ሲሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ ተቀበሉ። ይህ መጠሪያ በ⁠ኢሳይያስ 43:10-12 ላይ የተመሠረተ ነው።

በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት በሬዲዮ አማካኝነት ሰፊ ምሥክርነት ተሰጥቶ ነበር። ማኅበሩ በ1933 የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ለማስተላለፍ በ403 የሬዲዮ ጣቢያዎች ይጠቀም ነበር። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሬዲዮ ስርጭት ከመጠቀም ይልቅ በአብዛኛው ራሳቸው ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ በተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ማሰማት ጀመሩ። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያለው ሰው ሲያገኙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያስጀምሩታል።

በፍርድ ቤት የተገኙ ድሎች

በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት በርካታ ምሥክሮች ይህን ሥራ በመሥራታቸው ይታሠሩ ስለነበረ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና የማምለክ ነፃነትን ለማስከበር ሲባል በፍርድ ቤት መሟገት አስፈልጎ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የበታች ፍርድ ቤቶች ባስተላለፉት ውሳኔ ላይ ይግባኝ ተጠይቆ ለዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡ ወደ 50 የሚጠጉ ክሶች የይሖዋ ምሥክሮች ረትተዋል። በሌሎች አገሮች በሚገኙ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ተመሳሳይ ድሎች ተገኝተዋል። ፕሮፌሰር ሲ ኤስ ብሬደን ዚስ ኦልሶ ብሊቭ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እነዚህን የፍርድ ቤት ድሎች አስመልክተው ሲጽፉ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ብለዋል፦ “የዜግነት መብታቸውን ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ የእነሱ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ የሚኖሩ የሁሉም አናሳ ቡድኖች መብት እንዲከበር ስላደረጉ ለዲሞክራሲ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።”

ልዩ የሥልጠና ፕሮግራሞች

በ1942 ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ሲሞት በኤን ኤች ኖር ተተካ። የተቀናጀ የሥልጠና ፕሮግራም መካሄድ ጀመረ። በ1943 ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተባለ ሚስዮናውያን ልዩ ሥልጠና የሚያገኙበት ትምህርት ቤት ተቋቋመ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዚህ ትምህርት ቤት ምሩቃን በመላው ዓለም ወደሚገኙ የተለያዩ አገሮች ተልከዋል። አንድም ጉባኤ ባልነበረባቸው በርካታ አገሮች አዳዲስ ጉባኤዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከ100 በላይ የሚሆኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይገኛሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችና ሙሉ ጊዜያቸውን ለስብከቱ ሥራ የሚያውሉ ክርስቲያኖች (አቅኚዎች ይባላሉ) የሚሠለጥኑባቸው ልዩ ኮርሶች በየጊዜው ይሰጣሉ። በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የትምህርት ማዕከል ለአምላክ አገልጋዮች የሚሰጡ ለየት ያሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ኤን ኤች ኖር በ1977 ሞተ። ከመሞቱ በፊት ከተካሄዱት ድርጅታዊ ለውጦች አንዱ በብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ያለው የበላይ አካል አባላት ቁጥር እንዲጨምር መደረጉ ነበር። በ1976 የአስተዳደር ኃላፊነቶች በበላይ አካሉ አባላት ለተዋቀሩ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተከፋፈሉ፤ እነዚህ የበላይ አካል አባላት ለበርካታ ዓመታት አምላክን በማገልገል ተሞክሮ ያካበቱ ናቸው።

የኅትመት ሥራው ተስፋፋ

ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ በጣም አስደናቂ በሆኑ ክንውኖች የተሞላ ነው። በ1870 በፔንሲልቬንያ የነበረው አንድ የይሖዋ ምሥክሮች አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን እያደገ ሄዶ በ2010 በመላው ዓለም ከ100,000 የሚበልጡ ጉባኤዎችን ማፍራት ችሏል። መጀመሪያ ላይ ሁሉም ጽሑፎች ይታተሙ የነበረው በንግድ ማተሚያ ቤቶች ሲሆን በ1920 የይሖዋ ምሥክሮች በተከራዩአቸው የፋብሪካ ሕንፃዎች ውስጥ የተወሰኑ ጽሑፎችን ማተም ጀመሩ። ከ1927 ጀምሮ ግን አብዛኞቹ ጽሑፎች የዎችታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ንብረት በሆነውና በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ ውስጥ መታተም ጀመሩ። ይህ የኅትመት ሥራ በመስፋፋቱ ሌሎች የፋብሪካና የአስተዳደር ሕንፃዎች ለዚህ አገልግሎት ውለው ነበር። ሥራውን በተቀናጀ ሁኔታ የሚያካሂዱ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚኖሩባቸው ተጨማሪ ሕንፃዎች በብሩክሊን አቅራቢያ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክፍል ዎልኪል በሚባል አካባቢ የግብርናና የኅትመት ሥራ ይከናወናል። በዚህ ስፍራ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች የሚታተሙ ከመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ለሚሠሩ አገልጋዮች የሚሆን ምግብ ይመረታል። እያንዳንዱ ፈቃደኛ ሠራተኛ ለአነስተኛ የግል ወጪዎች መሸፈኛ የሚሆን ትንሽ ገንዘብ በየወሩ ይሰጠዋል።

ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች

በ1893 በቺካጎ፣ ኢሊኖይ ዩ ኤስ ኤ የመጀመሪያው ትልቅ ስብሰባ ተደረገ። በስብሰባው ላይ 360 ሰዎች የተገኙ ሲሆን 70 አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። በአንድ ቦታ ላይ ከተካሄዱ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች መካከል የመጨረሻው ትልቅ ስብሰባ የተካሄደው በ1958 በኒው ዮርክ ሲቲ ነበር። ስብሰባው የተካሄደው በያንኪ ስታዲየምና በወቅቱ በነበረው በፖሎ ግራውንድስ ነበር። ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 253,922 የነበረ ሲሆን 7,136 አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በርካታ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች በተለያዩ አገሮች በተከታታይ ተካሂደዋል። እንደነዚህ ያሉት ተከታታይ ስብሰባዎች በመላው ዓለም በሚገኙ አገሮች ውስጥ የሚደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ ትላልቅ ስብሰባዎችን ሊያጠቃልሉ ይችላሉ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የዜግነት መብትን ለማስከበር የተካሄደ ከፍተኛ ተጋድሎ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ ቋንቋ በ6,000 ቅጂዎች ይታተም የነበረው “መጠበቂያ ግንብ” በአሁኑ ጊዜ ከ180 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ከ42,000,000 በሚበልጡ ቅጂዎች እየታተመ ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]