በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች

ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች

ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች

አምላክ ፍቅር ከሆነ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደ ሲሆን በመላው ምድር የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው የክፋት ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ለምሳሌ ጦርነት ያውጃሉ፣ በሕፃናት ላይ ቦምብ ይጥላሉ፣ ምድርን ያበላሻሉ እንዲሁም ብዙ ሰዎች ለረሃብ እንዲጋለጡ ምክንያት ይሆናሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለሚያጨሱ የሳንባ ካንሰር ይይዛቸዋል፤ ምንዝር ስለሚፈጽሙ በአባለዘር በሽታዎች ይያዛሉ፤ በተጨማሪም ከልክ በላይ መጠጥ ስለሚጠጡ የጉበት በሽታ ይይዛቸዋል፤ በዚህ ረገድ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ክፋት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ልባዊ ፍላጎት የላቸውም። እነሱ የሚፈልጉት፣ ክፉ ድርጊት በመፈጸማቸው የሚደርስባቸው ቅጣት እንዲቀርላቸው ብቻ ነው። የዘሩትን በሚያጭዱበት ጊዜ “ይህ ለምን በእኔ ላይ ይደርሳል?” ብለው ይጮኻሉ። አምላክንም ተወቃሽ ያደርጋሉ፤ ምሳሌ 19:3 እንደሚለው “ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤ በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል።” አምላክ ክፉ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ቢያደርግ ደግሞ ነፃነት ተነፈግን ብለው ይቃወማሉ!

ይሖዋ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበት ዋነኛ ምክንያት ለሰይጣን ግድድር ምላሽ ለመስጠት ነው። ሰይጣን ዲያብሎስ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ አይሆኑም በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-10) ይሖዋ፣ ሰይጣን የተናገረው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲያገኝ በማሰብ በሕይወት እንዲቀጥል ፈቅዶለታል። (ዘፀአት 9:16) ሰይጣን የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል ዛሬም በሰዎች ላይ መከራ በማምጣት በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ለማድረግ እየሞከረ ነው። (ራእይ 12:12) ይሁን እንጂ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። ኢየሱስም እንዲሁ አድርጓል። ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች ንጹሕ አቋማቸውን ይጠብቃሉ።—ኢዮብ 27:5 NW፤ 31:6 NW፤ ማቴዎስ 4:1-11፤ 1 ጴጥሮስ 1:6, 7

ወደፊት ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ ብሎ ማመን አስደሳች ነው፤ ግን ይህ በእርግጥ ሊሆን የሚችል ነገር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ በእርግጥ እንደሚፈጸም ይናገራል። የሰው ልጆች ለበርካታ መቶ ዓመታት መጥፎ ነገር እያዩ ስለኖሩ ይህ ይሆናል ብለው ማመን ይከብዳቸዋል። ይሖዋ ምድርን ከፈጠረ በኋላ የሰው ልጆች ምድርን ጻድቅ በሆኑ ወንዶችና ሴቶች እንዲሞሏት አዝዞ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ምድርን ከማበላሸት ይልቅ በላይዋ ላይ የሚገኙትን ዕፅዋትና እንስሳት መንከባከብ እንዲሁም የምድርን ውበት መጠበቅ ይገባቸው ነበር። (ገጽ 12⁠ን እና 17⁠ን ተመልከት።) አምላክ ቃል የገባልን የገነት ተስፋ እውን መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ ይልቁንም ይህ አሁን የምናየው አሳዛኝ ሁኔታ እንዲሁ ሊቀጥል አይችልም። ይህ ሁኔታ ይወገድና ምድር ገነት ትሆናለች።

መጽሐፍ ቅዱስን ለሚተቹ እንዲሁም ተረትና ኢሳይንሳዊ ነው ለሚሉ ምን መልስ መስጠት እችላለሁ?

በእነዚህ ተስፋዎች የምናምነው እንዲሁ በጭፍን አይደለም። “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።” የአምላክን ቃል የምናጠና ከሆነ በውስጡ የተንጸባረቀው ጥበብ ግልጽ ሆኖ ይታየናል፤ እምነታችንም እያደገ ይሄዳል።—ሮም 10:17፤ ዕብራውያን 11:1

ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር በተያያዘ የሚካሄደው የአርኪኦሎጂ ምርምር አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። እውነተኛ ሳይንስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል። ዓለማዊ ምሑራን የሚከተሉትን ሐቆች ከመገንዘባቸው ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን እውነታዎች በግልጽ አስፍሯል፦ የምድር አፈጣጠር ቅደም ተከተል፣ ምድር ክብ መሆኗ፣ ያለምንም ድጋፍ በሕዋ ውስጥ ተንጠልጥላ የምትኖር መሆኗ፣ ወፎች ከአንደኛው የዓለም ክፍል ወደ ሌላኛው መፍለሳቸው።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 1፤ ኢሳይያስ 40:22፤ ኢዮብ 26:7፤ ኤርምያስ 8:7

ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ዳንኤል የዓለም ኃያላን መንግሥታትን መነሳትና መውደቅ እንዲሁም መሲሑ የሚመጣበትንና የሚገደልበትን ጊዜ ተንብዮአል። (ዳንኤል ምዕራፍ 2, 8፤ 9:24-27) ዛሬ የምንኖርበት ጊዜ ‘የመጨረሻው ቀን’ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች ትንቢቶች በመፈጸም ላይ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ ምዕራፍ 24) የሰው ልጅ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ የለውም። (ኢሳይያስ 41:23) ተጨማሪ ማስረጃዎች ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? እንዲሁም የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባሉትን መጻሕፍት ተመልከት።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ባጠናኸው ነገር ላይ ማሰላሰል አለብህ፤ በተጨማሪም ይህን ስታደርግ የአምላክ መንፈስ እንዲመራህ መጸለይ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 15:28፤ ሉቃስ 11:9-13) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) በተጨማሪም ልትመረምራቸው የሚገቡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች አሉ። ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንደረዳው ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ የሌሎች ሰዎችን እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-35) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ቤታቸው ሄደው ያለምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኗቸዋል። አንተም በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የምትፈልግ ከሆነ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትበል።

ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወሙትና ከእነሱ ጋር ማጥናት እንደሌለብኝ የሚነግሩኝ ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ምሥራቹን ሲሰብክ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ሲሆን ተከታዮቹም ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው ተናግሯል። አንዳንድ ሰዎች በኢየሱስ ትምህርት በተደነቁ ጊዜ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች “እናንተም ደግሞ ተታለላችሁ እንዴ? ከገዥዎች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእሱ ያመነ አንድም የለም፤ አለ እንዴ?” በማለት በቁጣ ተናግረው ነበር። (ዮሐንስ 7:46-48፤ 15:20) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዳታጠና የሚመክሩህ አብዛኞቹ ሰዎች ወይ በቂ ግንዛቤ የላቸውም አሊያም መሠረተ ቢስ ጥላቻ አድሮባቸዋል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጥናና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለህ ግንዛቤ ይጨምር እንደሆነና እንዳልሆነ አንተው ራስህ ለማየት ሞክር።—ማቴዎስ 7:17-20

የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸው ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች የሚሰብኩት ለምንድን ነው?

ይህን የሚያደርጉት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ስለሚፈልጉ ነው። ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ይሰብክ ነበር። አይሁዳውያን የራሳቸው ሃይማኖት የነበራቸው ቢሆንም ሃይማኖታቸው በብዙ መንገዶች ከአምላክ ቃል ጋር የማይስማማ ነበር። (ማቴዎስ 15:1-9) ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ይሁኑም አይሁኑ፣ ሁሉም ሕዝቦች የራሳቸው ሃይማኖት አላቸው። ሰዎች ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ እምነት መከተላቸው በጣም አስፈላጊ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሰዎችን ለመርዳት የሚያደርጉት ጥረት ለሰው ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የእነሱ ሃይማኖት ብቻ ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ?

ሃይማኖቱን በቁም ነገር የሚመለከት ማንኛውም ሰው ‘የራሴ ሃይማኖት ትክክል ነው’ ብሎ እንደሚያስብ የታወቀ ነው። እንዲህ ባይሆንማ ኖሮ ሃይማኖቱን ለምን ይከተል ነበር? ክርስቲያኖች “ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) አንድ ሰው የሚያምንበት ነገር ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፤ ምክንያቱም እውነተኛው እምነት አንድ ብቻ ነው። ኤፌሶን 4:5 “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ” በማለት ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ወደ መዳን የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች ማለትም ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ከሚለው በዘመናችን ካለው ልል አመለካከት ጋር አይስማማም። እንዲያውም ኢየሱስ “ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ሲል ተናግሯል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መንገድ እንዳገኙ ያምናሉ። ይህ ባይሆንማ ኖሮ ሌላ ሃይማኖት ይፈልጉ ነበር።—ማቴዎስ 7:14

የሚድኑት እነሱ ብቻ እንደሆኑ አድርገው ያምናሉ?

በፍጹም። ባለፉት መቶ ዘመናት የኖሩና የይሖዋ ምሥክር ያልነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በትንሣኤ ተነስተው ዳግመኛ በሕይወት የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። አሁን በሕይወት ያሉ በርካታ ሰዎችም ቢሆኑ ከመጪው “ታላቅ መከራ” በፊት ከእውነትና ከጽድቅ ጎን ሊሰለፉና መዳን ሊያገኙ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ አንዳችን በሌላው ላይ መፍረድ እንደማይገባን ተናግሯል። እኛ የምናየው ውጫዊውን ገጽታ ሲሆን አምላክ ግን ልብን ይመለከታል። አምላክ በትክክል አይቶ ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይፈርዳል። የመፍረድ ሥልጣን የሰጠው ለኢየሱስ እንጂ ለእኛ አይደለም።—ማቴዎስ 7:1-5፤ 24:21፤ 25:31

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ የሚገኙ ሰዎች የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

ሐዋርያ ጳውሎስ የገንዘብ መዋጮ ማድረግን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።” (2 ቆሮንቶስ 9:7) በመንግሥት አዳራሾችም ሆነ በይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም። የመዋጮ ሣጥኖች አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ ሲሆን መዋጮ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መዋጮ ማድረግ ይችላል። ማን መዋጮ እንዳደረገም ሆነ ምን ያህል መዋጮ እንዳደረገ የሚያውቅ ሰው አይኖርም። አንዳንዶች ከሌሎች የበለጠ ሊሰጡ ይችላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ መዋጮ ለማድረግ አቅማቸው ላይፈቅድ ይችላል። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የነበረውን የመዋጮ ሣጥንና በዚያ ገንዘብ ይጨምሩ የነበሩትን ሰዎች በተመለከተ የሰጠው አስተያየት በዚህ ረገድ ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ይጠቁማል፤ አስፈላጊው ነገር የገንዘቡ መጠን ሳይሆን የሰጪው አቅምና የተሰጠበት መንፈስ ነው።—ሉቃስ 21:1-4

የይሖዋ ምሥክር ብሆን እንደ እነሱ እንድሰብክ ይጠበቅብኛል?

አንድ ሰው በክርስቶስ መንግሥት ስለሚተዳደረው ምድራዊ ገነት ያለው እውቀት እያደገ ሲሄድ ይህን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል እንደሚነሳሳ ጥርጥር የለውም። አንተም እንዲሁ ማድረግህ አይቀርም። ደግሞም ይህ ሊነገር የሚገባው ምሥራች ነው!—የሐዋርያት ሥራ 5:41, 42

እንዲህ ማድረግህ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆንህን ከምታሳይባቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል። ምድር ላይ በነበረ ጊዜ “መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል” እያለ ሰብኳል፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ልኳቸዋል። (ራእይ 3:14፤ ማቴዎስ 4:17፤ 10:7) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እንዲሁም አስተምሯቸው’ ሲል አዟል። በተጨማሪም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

ይህ የምሥራች የሚነገርባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ብዙ ጊዜ ከወዳጆቻችንና ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር የምናደርገው ጭውውት ምሥራቹን ለመናገር የሚያስችል መንገድ ይከፍትልናል። ደብዳቤ በመጻፍ አሊያም ስልክ በመደወል የሚሰብኩ አሉ። ሌሎች ደግሞ ለሚያውቁት ሰው ይበልጥ ትኩረቱን ሊስበው ይችላል ብለው ያመኑበትን ጽሑፍ በፖስታ ይልካሉ። የይሖዋ ምሥክሮች መልእክቱን ለእያንዳንዱ ሰው ማዳረስ ስለሚፈልጉ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ይሰብካሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ፍቅር የተንጸባረቀበት ግብዣ ያቀርባል፦ “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው። የሚሰማም ሁሉ ‘ና!’ ይበል። የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።” (ራእይ 22:17) ገነት ስለምትሆነው ምድርና በዚያ ስለሚገኙት በረከቶች ለሌሎች የምንናገረው በፈቃደኝነትና ይህን የምሥራች ለሌሎች ለመናገር ባለን ልባዊ ፍላጎት ተነሳስተን መሆን ይኖርበታል።

ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ሌሎች ጥያቄዎችም እንደሚኖሩህ እርግጠኞች ነን። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ብዙ የሚያወያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለጥያቄዎችህ መልስ ብንሰጥህ ደስ ይለናል። በዚህ ብሮሹር ላይ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ መስጠት ስለማንችል በአካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች እንድትጠይቅ እናበረታታሃለን። ስብሰባ ወደሚያደርጉባቸው የመንግሥት አዳራሾች ሄደህ ወይም ወደ ቤትህ ሲመጡ ልታነጋግራቸው ትችላለህ። አለዚያም ከታች በሚገኙት አድራሻዎች ተጠቅመህ ጥያቄዎችህን ለይሖዋ ምሥክሮች መላክ ትችላለህ።