በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ እውነተኛ ክርስቲያናዊ መመሪያዎችን ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ

ሊከበሩ የሚገባቸው ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች

ሊከበሩ የሚገባቸው ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች

በታሪክ ዘመናት ሁሉ ደፋር ወንዶችና ሴቶች በዘመናቸው በሰፊው ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ አቋም ወስደዋል። የደረሰባቸውን የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የዘር ጭቆና የተቋቋሙ ሲሆን ብዙዎቹ ለቆሙለት ዓላማ ሕይወታቸውን ሠውተዋል።

በተለይ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ደፋሮች ነበሩ። ከባድ ስደት በነበረባቸው በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት፣ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱን ለማምለክ አሻፈረኝ በማለታቸው አረማውያን በነበሩት ሮማውያን ተገድለዋል። አንዳንድ ጊዜ በስፖርት መወዳደሪያ ሥፍራዎች መሠዊያ እንዲቆም ይደረግ ነበር። ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱ የመለኮትነት ባሕርይ እንዳለው አምነው እንደተቀበሉ ለማሳየት ትንሽ ዕጣን ቆንጠር አድርገው መሠዊያው ላይ በማጨስ ብቻ ነፃ መውጣት ይችሉ ነበር። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ አቋማቸውን ቢያላሉም አብዛኞቹ ግን እምነታቸውን ከመካድ ይልቅ ሞትን መርጠዋል።

በዘመናችን ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆንን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በናዚ አገዛዝ ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም የጸና አቋም መያዛቸውን የታሪክ መዛግብት ይመሠክራሉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትም ሆነ በዚያ ወቅት 25 በመቶ የሚሆኑ ጀርመናውያን የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን አብዛኞቹ የሞቱት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ነው፤ ይህም የሆነው ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች በመሆናቸውና “ሃይል ሂትለር” ለማለት ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረታቸው ነው። ልጆች፣ የይሖዋ ምሥክር ከሆኑት ወላጆቻቸው ጉያ እየተነጠቁ ይወሰዱ ነበር። እነዚህ ልጆች ብዙ ተጽዕኖ ይደርስባቸው የነበረ ቢሆንም በአቋማቸው የጸኑ ከመሆናቸውም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን እንዲቀበሉ የሚደረግባቸውን ጫና ተቋቁመዋል።

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት

በጥቅሉ ሲታይ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ አስከፊ ስደት አይደርስባቸውም። ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች ከሕሊናቸው የተነሳ ለባንዲራ ሰላምታ እንደ መስጠት ባሉ ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ አቋማቸው የተሳሳተ ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል።

“የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ”—​ማቴዎስ 22:21

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች ሌሎች ለባንዲራ ሰላምታ እንዳይሰጡ ጫና ለማሳደር አይሞክሩም፤ ይህ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው አቋም የማያወላውል ነው፤ ለማንኛውም አገር ባንዲራ ሰላምታ አይሰጡም። ይህን የሚያደርጉት ግን አክብሮት ስለሌላቸው አይደለም። የሚኖሩት የትም ይሁን የት ለሚኖሩበት አገር ባንዲራ አክብሮት ያላቸው ሲሆን አክብሮታቸውንም የአገሪቱን ሕግ በመታዘዝ ያሳያሉ። በየትኛውም ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ ፈጽሞ አይካፈሉም። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች፣ አሁን ያሉት ሰብዓዊ መንግሥታት አምላክ በዚህ ሥርዓት እንዲኖር የፈቀደው “ዝግጅት” አካል እንደሆኑ ያምናሉ። በመሆኑም ቀረጥ እንዲከፍሉና “ለበላይ ባለሥልጣናት” አክብሮት እንዲያሳዩ የተሰጣቸውን መለኮታዊ መመሪያ ይታዘዛሉ። (ሮም 13:1-7) ይህ ደግሞ ክርስቶስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ማቴዎስ 22:21

አንዳንዶች ‘ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ለባንዲራ ያላቸውን አክብሮት ሰላምታ በመስጠት የማያሳዩት ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል። ይህን የማያደርጉት ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትን እንደ አምልኮ ስለሚቆጥሩት ነው፤ አምልኮ የሚገባው ደግሞ አምላክ ብቻ ነው። ከአምላክ በስተቀር ማንንም ሆነ የትኛውንም ነገር አያመልኩም። (ማቴዎስ 4:10፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29) ስለሆነም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች ያላቸውን አቋምም ሆነ ከእምነታቸው ጋር ተስማምተው ለመኖር ያደረጉትን ውሳኔ አስተማሪዎች ሲያከብሩላቸው ደስ ይላቸዋል።

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት ከአምልኮ ጋር የተያያዘ ነው ብለው የሚያምኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንዳልሆኑ የሚከተሉት አስተያየቶች ያሳያሉ፦

“የጥንቶቹ ሰንደቅ ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ የሆነ ባሕርይ ነበራቸው ለማለት ይቻላል። . . . የብሔራት ባንዲራዎች ቅዱስ ተደርገው እንዲታዩ ለማድረግ ሁልጊዜ የሃይማኖት እርዳታ ያስፈልግ የነበረ ይመስላል።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ

“ባንዲራ እንደ መስቀል ቅዱስ ነው። . . . ሰዎች ለብሔራዊ አርማዎች ካላቸው አመለካከት ጋር በተያያዘ የወጡት ደንቦችና መመሪያዎች ‘ባንዲራን ማገልገል’ . . . ‘ለባንዲራ አምልኮታዊ አክብሮት መስጠት፣’ ‘ለባንዲራ ያደሩ መሆን’ እንደሚሉት ያሉ ኃይለኛና ገላጭ ቃላትን ይጠቀማሉ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)—ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና

“ክርስቲያኖች [ለሮም] ንጉሠ ነገሥት ውቃቢ መሥዋዕት ለማቅረብ . . . ፈቃደኞች አልነበሩም። ይህም በዛሬው ጊዜ ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ወይም የታማኝነት ቃለ መሐላ ለመግባት እምቢተኛ ከመሆን ጋር የሚመሳሰል ነው።”—በዳንኤል ማኒክስ የተዘጋጀው፣ ዞስ አባውት ቱ ዳይ (1958) ገጽ 135

ሦስቱ ወጣት ዕብራውያን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆኑም

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኞች የማይሆኑት ለማንኛውም መንግሥት ሆነ ለባለሥልጣናቱ አክብሮት ስለሌላቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ አገርን ለሚወክል ምስል በመስገድ ወይም ሰላምታ በመስጠት አምልኮ ማቅረብ ስለማይፈልጉ ነው። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በዱራ ሜዳ ላቆመው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ ያልሆኑት ሦስቱ ወጣት ዕብራውያን ከወሰዱት አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዳንኤል ምዕራፍ 3) ስለሆነም ሌሎች ለባንዲራው ሰላምታ ሲሰጡና ታማኝ ለመሆን ቃል ሲገቡ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናቸውን ይከተላሉ። በዚህም የተነሳ ሥነ ሥርዓቱን የሚያውክና የሚያቃልል ነገር ባይፈጽሙም በሥነ ሥርዓቱ ላይ አይካፈሉም። ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወይም ሙዚቃው በሚሰማበት ጊዜ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች ምንም ዓይነት ተሳትፎ አያደርጉም።

የወላጆች መብት

በዛሬው ጊዜ፣ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች ከእነሱ እምነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት የመስጠት ሕጋዊ መብት አላቸው። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሁንም ድረስ የሚሠራበት የሚከተለው ቀኖና ሁሉም ሃይማኖቶች ይህን መብት እንደሚደግፉ ያሳያል፦ “ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሕይወት የሰጧቸው እነሱ እንደመሆናቸው መጠን ልጆቻቸውን የማስተማር ግዴታ የተጣለባቸው ከመሆኑም ሌላ እንዲህ የማድረግ መብት አላቸው። ወላጆች በዋነኝነት ከቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ የክርስትና ትምህርት ለልጆቻቸው ማስተማራቸው እጅግ አስፈላጊ የሆነው ከዚህ የተነሳ ነው።”—ቀኖና 226

ልጆች ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳዩ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል

የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ የተለየ ነገር አያደርጉም። ለልጆቻቸው የሚያስቡ በመሆናቸው እውነተኛ ክርስቲያናዊ መመሪያዎችን በልባቸው ውስጥ ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ለሌሎች ፍቅር እንዲኖራቸውና ለሰዎች ንብረት አክብሮት እንዲያሳዩ ያሠለጥኗቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁን የሚያስቆጣ ነገር አታድርጉ። ከዚህ ይልቅ በክርስቲያናዊ ተግሣጽና ትምህርት ኮትኩታችሁ አሳድጓቸው” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋሉ።—ኤፌሶን 6:4 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

በሃይማኖት የተከፋፈሉ ቤተሰቦች

በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የይሖዋ ምሥክር የሆነው አንደኛው ወላጅ ብቻ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወላጅ እምነቱን የማይጋራው የትዳር ጓደኛ የራሱን ሃይማኖታዊ እምነት ለልጆቹ የማስተማር መብት እንዳለው ይገነዘባል። ልጆች የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን መቅሰማቸው እምብዛም ጉዳት አያስከትልባቸውም። * የትኛውን ሃይማኖት መከተል እንዳለባቸው ልጆቹ ራሳቸው ይወስናሉ። ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑም አልሆኑ ሁሉም ልጆች የወላጆቻቸውን ሃይማኖት ይከተላሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ልጆች ከሕሊና ነፃነት ጋር በተያያዘ ያላቸው መብት

የይሖዋ ምሥክሮች ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕሊና ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። (ሮም ምዕራፍ 14) በ1989 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የልጆችን መብት በተመለከተ ያጸደቀው ስምምነት ልጆች “የሐሳብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት” እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳላቸውና የሚሰጡት ሐሳብ ከእነሱ ጋር በተያያዘ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ይገልጻል።

ሁሉም ልጆች አንድ አይደሉም። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆችም ሆኑ ሌሎች ተማሪዎች በትምህርት ቤት ከሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ወይም ከቤት ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚወስዱት አቋም በተወሰነ ደረጃ ሊለያይ ይችላል። አንተም፣ ልጆች የሕሊና ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል በሚለው ሐሳብ እንደምትስማማ ተስፋ እናደርጋለን።

^ አን.18 በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆችን በተመለከተ ዶክተር ስቲቨን ካር ሩበን፣ ሬይዚንግ ጁዊሽ ችልድረን ኢን ኤ ከንቴምፐራሪ ወርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ወላጆች እውነተኛ ማንነታቸውን ሲደብቁ፣ ግራ የሚያጋባና ሚስጥራዊ የሆነ ሕይወት ሲመሩ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ገሸሽ ሲያደርጉ ልጆች ግራ ይጋባሉ። ወላጆች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች፣ ስለሚመሩባቸው ደንቦችና ስለሚያከብሯቸው በዓላት ግልጽና ሐቀኛ ሲሆኑ ልጆች ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የደኅንነት ስሜት ተሰምቷቸውና ለራሳቸው ጥሩ ግምት ኖሯቸው ያድጋሉ፤ ይህ ደግሞ በራሳቸው እንዲተማመኑና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዲገነዘቡ ትልቅ ሚና ይጫወታል።”