ወላጆች የሚጫወቱት ሚና
በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ ልጆችን የተረጋጉና ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያላቸው አድርጎ ማሳደግ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አይካድም።
የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም፣ ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ ስኬታማ በሆኑ ወላጆች ላይ የተደረገን ጥናት አስመልክቶ አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር። ይህ ዘገባ፣ ከ21 ዓመት በላይ የሆኑት ልጆቻቸው “በሙሉ ከኅብረተሰቡ ጋር ራሳቸውን በጥሩ ሁኔታ አስማምተው የሚኖሩ ጠቃሚ ዜጎች” እንደሆኑ ገልጿል። እነዚህ ወላጆች፣ ‘ከራሳችሁ ተሞክሮ በመነሳት ለሌሎች ወላጆች ምን ምክር ትሰጣላችሁ?’ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው
ነበር። አብዛኞቹ ወላጆች ከሰጧቸው መልሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ‘አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው፣’ ‘ገንቢ በሆነ መንገድ ተግሣጽ ስጧቸው፣’ ‘አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ፣’ ‘ልጆቻችሁን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ አሠልጥኗቸው፣’ ‘እርስ በርስ ተከባበሩ፣’ ‘በጥሞና አዳምጧቸው፣’ ‘ዲስኩር ከመስጠት ይልቅ ማድረግ ያለባቸውን ጠቁሟቸው’ እንዲሁም ‘ምክንያታዊ ሁኑ።’ይሁንና ልጆች አድገው የበሰሉ ወጣቶች እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ከወላጆች በተጨማሪ አስተማሪዎችም ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ተሞክሮ ያካበተ አንድ የትምህርት ቤት አማካሪ “የመደበኛ ትምህርት ዋነኛ ዓላማ ወላጆች በአስተሳሰብ፣ በአካልና በስሜት የበሰሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወጣቶችን ማፍራት እንዲችሉ መርዳት ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
በመሆኑም ወላጆችና አስተማሪዎች ግባቸው ተመሳሳይ ነው፤ ይኸውም የበሰሉና የተረጋጉ እንዲሁም በሕይወታቸው ደስተኞች የሆኑና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚገነዘቡ ወጣቶች ማፍራት ነው።
ተባብረው ይሠራሉ እንጂ አይፎካከሩም
ወላጆች ከአስተማሪዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች ሳይሆኑ ሲቀሩ ግን ችግሮች ይከሰታሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ምንም ትኩረት አይሰጡም፤ ሌሎቹ ደግሞ ከአስተማሪዎች ጋር ለመፎካከር ይጥራሉ። አንድ የፈረንሳይ መጽሔት ይህን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚከታተለው አስተማሪ ብቻ መሆኑ ቀርቷል። የልጆቻቸው ስኬት ከልክ በላይ የሚያስጨንቃቸው ወላጆች መማሪያ መጻሕፍትን አንድ በአንድ ይመረምራሉ፣ የማስተማሪያ ዘዴዎቹን ይተቻሉ እንዲሁም ይነቅፋሉ፤ ከዚህም ሌላ ልጆቻቸው ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጡ በጣም ቅር ይሰኛሉ።” እንዲህ ያሉ ነገሮች የአስተማሪን መብት ሊጋፉ ይችላሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለልጆቻቸው ትምህርት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከአስተማሪዎች ጋር ተባብረው ሲሠሩ ልጆቻቸው ይበልጥ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ይሰማቸዋል። የማስተማር ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝ እየሆነ በመሄዱ ወላጆች እንዲህ ያለ የትብብር መንፈስ ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ።
በዛሬው ጊዜ በትምህርት ቤት ያሉ ችግሮች
ትምህርት ቤቶች የኅብረተሰቡ ነጸብራቅ እንደመሆናቸው መጠን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ችግሮች በትምህርት ቤትም መታየታቸው አይቀርም። ማኅበራዊ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየተባባሱ ሄደዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ይተኛሉ፣ ዛቻ የተሞላባቸውን ቃላት በየግድግዳዎች ላይ በመጻፍ አንዳቸው ሌላውን ያስፈራራሉ፣ ጎበዝ ተማሪዎችን ያንኳስሳሉ። . . . ሁሉም ተማሪዎች ለማለት ይቻላል፣ ሕፃናትን መንከባከብ፣ በእስር ላይ ያሉ ወላጆችን መጠየቅ እንዲሁም የዱርዬዎችን ጥቃት የመሳሰሉ ችግሮችን መቋቋም ይጠበቅባቸዋል። በየቀኑ 25 በመቶ የሚያህሉ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።”
በዓለም አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እየጨመረ የሄደው ዓመጽ በጣም አሳሳቢ ሆኗል። ቀደም ሲል ተማሪዎች
በመገፈታተርና በመደባደብ አልፎ አልፎ ይጣሉ የነበሩ ሲሆን ዛሬ ዛሬ ግን ጥይት ሲታኮሱና ስለት ባላቸው ነገሮች ሲደባደቡ ማየት የተለመደ ነው። ብዙ ተማሪዎች መሣሪያ የሚይዙ ከመሆኑም በላይ በልጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እጅግ አስከፊ እየሆነ መጥቷል፤ ከዚህም በተጨማሪ ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለድብድብ ሲጋበዙ ይታያሉ።እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉ አስከፊ ሁኔታዎች በሁሉም አገሮች ይታያሉ ማለት አይደለም። ይሁንና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አስተማሪዎች፣ ለ ፕዋ የተባለው የፈረንሳይ ሳምንታዊ መጽሔት፣ “አስተማሪ መከበሩ ቀርቷል፤ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለውም” በማለት የገለጸው ዓይነት ችግር ያጋጥማቸዋል።
እንዲህ ያለው ለሥልጣን አክብሮት ያለማሳየት መንፈስ በሁሉም ልጆች ላይ ከባድ መዘዝ ያስከትላል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ቤት ውስጥ እምብዛም የማይታዩትን ባሕርያት እንዲያፈሩ ማለትም ለሥልጣን ታዛዦች እንዲሆኑና አክብሮት እንዲያሳዩ ልጆቻቸውን ያሠለጥኗቸዋል።