የተለያዩ ሃይማኖቶች መኖራቸው የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ
አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን የተለያዩ ሃይማኖቶች መኖራቸው ፈታኝ ሁኔታ ሊያስከትልብህ የሚችል ሲሆን ይህ ባለፉት መቶ ዘመናት የነበሩ አስተማሪዎች እምብዛም ያላጋጠማቸው ችግር ነው።
በመካከለኛው ዘመን፣ የአንድ አገር ዜጎች አንድ ዓይነት ሃይማኖት መከተላቸው የተለመደ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይም እንኳ አውሮፓ ውስጥ ብዙ ተከታይ የነበራቸው ሃይማኖቶች ጥቂቶች ሲሆኑ እነሱም በምዕራብ አውሮፓ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት፣ በምሥራቅ ደግሞ ኦርቶዶክስና እስልምና እንዲሁም የአይሁድ ሃይማኖት ናቸው። በዛሬው ጊዜ ግን በአውሮፓም ሆነ በመላው ዓለም በርካታ ሃይማኖቶች ይገኛሉ። ብዙም የማይታወቁ ሃይማኖቶች በራሱ በአገሬው ሰው ወይም ከሌላ አካባቢ በመጡ ስደተኞች አማካኝነት እየተስፋፉ መጥተዋል።
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ እንደ ብሪታንያ፣ አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ በርካታ ሙስሊሞች፣ ቡዲስቶችና ሂንዱዎች ይገኛሉ። ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮችም በ239 አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። በ14 አገሮች ውስጥ የአባሎቻቸው ብዛት ከ150,000 በላይ ሆኗል።—“ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፋዊ ሃይማኖት የሚለውን ሣጥን ተመልከት።”
ተማሪዎች የተለያዩ ሃይማኖታዊ ልማዶች ያሏቸው መሆኑ ለአስተማሪዎች ፈታኝ ሁኔታ ይፈጥርባቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ከሆኑ ክብረ በዓላት ጋር በተያያዘ እንደሚከተሉት ያሉ ትኩረት የሚሹ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፦ አንድ ተማሪ ሃይማኖቱ ምንም ይሁን ምን ሁሉንም በዓላት እንዲያከብር ጫና ሊደረግበት ይገባል? አብዛኞቹ ተማሪዎች እንዲህ ያሉ በዓላትን ማክበር ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከብዙሃኑ የተለየ ሃይማኖት የሚከተሉ ቤተሰቦች ያላቸው አመለካከትስ ሊከበር አይገባውም? ሊታሰብበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ፤ ሃይማኖት ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደማይገባ የሚደነግግ ሕግ ባላቸውና የሃይማኖት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማይካተትባቸው አገሮች ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን እንዲህ ያሉ ክብረ በዓላትን እንዲያከብሩ ማስገደድ ተገቢ ነው?
የልደት ቀን
በበርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከበሩትን የልደት ቀናት ጨምሮ ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ የሌላቸው ከሚመስሉ በዓላት ጋር በተያያዘም እንኳ የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች የልደት ቀናቸውን የማክበር መብት እንዳላቸው ቢገነዘቡም እነሱ እንዲህ ባሉ ሥነ ሥርዓቶች ላይ እንደማይካፈሉ ሳታስተውል አትቀርም። ይሁን እንጂ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው እንዲህ ባሉ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የማይካፈሉበትን ምክንያት አታውቅ ይሆናል።
በፈረንሳይ አገር በብዛት የተሰራጨው ለ ሊቭር ዴ ሬሊዦን (የሃይማኖቶች መጽሐፍ) የተባለ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ይህን ልማድ የራሱ የሆነ ደንብ ያለው ሥነ ሥርዓት ብሎ የጠራው ሲሆን “ሃይማኖታዊ ካልሆኑ ሥርዓቶች” መካከል ፈርጆታል። በዛሬው ጊዜ የልደት ክብረ በዓል ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የሌለው ልማድ ተደርጎ ቢታይም ከአረማውያን የመጣ ነው።
ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና (የ1991 እትም) እንዲህ ይላል፦ “የጥንቶቹ ግብጻውያን፣ ግሪካውያን፣ ሮማውያንና ፋርሳውያን የአማልክትን፣ የነገሥታትንና የታወቁ ሰዎችን የልደት ቀን ያከብሩ ነበር።” ራልፍ እና አደሊን ሊንተን የተባሉ ደራሲዎች ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “መስጴጦምያና ግብጽ፣ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ ከመሆናቸውም ባሻገር የልደት ቀንን ማሰብና ማክበር የተጀመረባቸው አገሮች ናቸው። በጥንት ጊዜ ሰዎች የልደት ቀናቸውን የሚመዘግቡበት ዋነኛ ምክንያት በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት የሰውን የወደፊት ዕጣ ለማወቅ የልደት ቀን በጣም አስፈላጊ ስለነበር ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ኮከብ ቆጠራን አስመልክቶ የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች የልደት ቀን ከኮከብ ቆጠራ ጋር እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑ በእጅጉ ያሳስባቸዋል።—ኢሳይያስ 47:13-15
ስለሆነም ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ
“የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የማንኛውንም ሰው የልደት በዓል ማክበርን አረማዊ ልማድ አድርገው ይመለከቱት ስለነበር [የክርስቶስን] ልደት አላከበሩም” በማለት መናገሩ አያስገርምም።—ጥራዝ 3 ገጽ 416የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ ባሉት ምክንያቶች የተነሳ በልደት በዓላት ላይ አይካፈሉም። እርግጥ ነው፣ ልጅ መውለድ በጣም አስደሳች እንደሆነ አይካድም። ዓመታት ባለፉ ቁጥር ልጆች እያደጉና እየበሰሉ መሄዳቸው ማንኛውንም ወላጅ እንደሚያስደስት ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ለቤተሰባቸውና ለጓደኞቻቸው ስጦታ በመስጠትና ከእነሱ ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ፍቅራቸውን መግለጽ በጣም ያስደስታቸዋል። ይሁንና የልደት በዓል ከአረማውያን የመጣ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉት በሌሎች ጊዜያት ነው።—ሉቃስ 15:22-25፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35
የገና በዓል
የገና በዓል ክርስቲያን ያልሆኑ በርካታ አገሮችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ይከበራል። አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የገናን በዓል ስለሚያከብሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በዓል አለማክበራቸው በሰዎች አእምሮ ውስጥ
ጥያቄ ሊፈጥር ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች የገናን በዓል የማያከብሩት ለምንድን ነው?በርካታ ኢንሳይክሎፒዲያዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት የኢየሱስ ልደት ታኅሣሥ 25 * ላይ የሚከበረው ከሮም የአረማውያን በዓል ጋር እንዲገጥም ስለተፈለገ ነው። ከተለያዩ የማመሳከሪያ ጽሑፎች የተወሰዱትን የሚከተሉትን መግለጫዎች ተመልከት፦
“ክርስቶስ የተወለደበት ቀን አይታወቅም። ወንጌሎች የተወለደበትን ቀንም ሆነ ወር አይገልጹም።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ጥራዝ 3 ገጽ 656
“በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ተስፋፍተው የሚገኙት ወይም ቀደም ባሉት ዘመናት በጽሑፍ ሰፍረው የምናገኛቸው የገና በዓል ልማዶች እውነተኛ የክርስትና ልማዶች ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸው ወይም ያላወገዘቻቸው አረማዊ ልማዶች ናቸው። . . . በሮም ይከበር የነበረው የሳተርኔሊያ በዓል፣ ገና በሚከበርበት ወቅት ለሚታዩት ለአብዛኞቹ ፈንጠዝያዎች ሞዴል ሆኖ አገልግሏል።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ (ኤድንበር 1910) በጄምስ ሃስቲንግስ የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 3 ገጽ 608-609
“የገና በዓል ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ታኅሣሥ 25 ላይ ሲከበር ቆይቷል። በዚያን ዘመን አረማውያን የፀሐይን በዓል የሚያከብሩት በዚህ ዕለት ነበር። . . . በሮም፣ ቤተ ክርስቲያን በጣም ተወዳጅ የሆነውን ይህን ልማድ . . . አዲስ ትርጓሜ በመስጠት [የክርስትና በዓል አድርጋ] ተቀበለችው።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ዩኒቨርሳሊስ፣ 1968 (ፈረንሳይኛ) ጥራዝ 19 ገጽ 1375
አንዳንዶች ስለ ገና በዓል እውነታውን ሲያውቁ ምን አደረጉ? ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በ1644 በእንግሊዝ ይኖሩ የነበሩ የፕሮቴስታንት የተሐድሶ አራማጆች [ገና] የአረማውያን በዓል ነው በሚል ከዚህ በዓል ጋር የተያያዙ ፈንጠዝያዎችም ሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በፓርላማ እንዲታገዱና ቀኑ በጾም ታስቦ እንዲውል ትእዛዝ አስተላለፉ። ዳግማዊ ቻርልስ ከዚህ በዓል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ልማዶች እንዲያንሠራሩ ያደረገ ቢሆንም ስኮትላንዳውያን፣ የፕሮቴስታንት የተሐድሶ አራማጆችን አመለካከት በጥብቅ መከተላቸውን ቀጥለዋል።” የጥንቶቹ
ክርስቲያኖች የገና በዓልን አላከበሩም፤ በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በዓል አያከብሩም ወይም ከዚህ በዓል ጋር በተያያዙ ሥነ ሥርዓቶች ላይ አይካፈሉም።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ጊዜያት ስጦታ መስጠትን እንዲሁም ከወዳጅ ዘመዶች ጋር መገባበዝን አያወግዝም። ልጆች፣ ሌሎች ሰዎች ስለሚጠብቁባቸው ብቻ ስጦታ ከመስጠት ይልቅ ከልብ ተነሳስተው የልግስና መንፈስ እንዲያሳዩ ወላጆች አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲሰጧቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታል። (ማቴዎስ 6:2, 3) የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች የሌሎችን አመለካከት ማክበር እንዳለባቸው ይማራሉ፤ ይህ ደግሞ ሌሎች የገና በዓልን የማክበር መብት እንዳላቸው መገንዘብን ይጨምራል። እነሱም በገና በዓል ላይ ላለመካፈል ያደረጉትን ውሳኔ ሌሎች ሲያከብሩላቸው ደስ ይላቸዋል።
ሌሎች ክብረ በዓላት
የይሖዋ ምሥክሮች በትምህርት ወቅት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ የሆኑ ወይም በተወሰነ ደረጃ ከሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸው በዓላትን በተመለከተም ቢሆን ተመሳሳይ አቋም አላቸው፤ ከእነዚህ በዓላት መካከል በብራዚል የሚከበረው ጁን ፌስቲቫል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚከበረው ሃሎዊን፣ በጀርመን የሚከበረው ካርኒቫል፣ በጃፓን የሚከበረው ሴትስበንና በፈረንሳይ የሚከበረው ጥምቀት ይገኙበታል። የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ ልጆቻቸው እነዚህንና እዚህ ላይ ያልተጠቀሱ ሌሎች ክብረ በዓላትን አስመልክቶ ለሚኖርህ ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው።
^ አን.14 በአገራችን የገና በዓል የሚከበረው እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 ሲሆን ይህ ቀን በጎርጎርዮስ የዘመን አቆጣጠር ጥር 7 በጁልየስ የዘመን አቆጣጠር ደግሞ ታኅሣሥ 25 ላይ ይውላል።