በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትምህርት መርሐ ግብር

የትምህርት መርሐ ግብር

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራቸው ይታወቃሉ።

አንዳንድ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራቸውን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ ለሰብዓዊ ትምህርት ትኩረት እንደማይሰጡ ይሰማቸዋል። ሆኖም እውነታው ይህ አይደለም። አንድ አስተማሪ ሌሎችን ለማስተማር በቅድሚያ እሱ መማር ይኖርበታል፤ ይህ ደግሞ ተገቢ ሥልጠና እና ትምህርት ማግኘት ይጠይቃል። የይሖዋ ምሥክሮች ሰብዓዊ ትምህርታቸውን በሚገባ የሚከታተሉ ከመሆናቸውም ባሻገር የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ባዘጋጃቸው የተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮችና ባቋቋማቸው ትምህርት ቤቶች ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙ ኖረዋል። እነዚህ ሥልጠናዎች የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በአእምሮ እንዲበስሉ፣ በሥነ ምግባር እንዲታነጹና በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ረድተዋቸዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በብዙ አገሮች ውስጥ መደበኛ ትምህርት የመማር አጋጣሚ ባለማግኘታቸው የተነሳ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ሰዎች የማስተማር ለየት ያለ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ይህን ችግር ለመወጣት የመሠረተ ትምህርት መርሐ ግብር ነድፏል።

ለአብነት ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች በናይጄሪያ ከ1949 ጀምሮ መሠረተ ትምህርት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በዚህ የትምህርት መርሐ ግብር አማካኝነት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ማንበብ ተምረዋል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በናይጄሪያ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማንበብና መጻፍ ይችላሉ፤ በአንጻሩ ግን በአገሪቱ ካለው ሕዝብ መካከል ማንበብና መጻፍ የሚችለው ከ50 በመቶ ያነሰ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሜክሲኮ ከ1946 አንስቶ የመሠረተ ትምህርት መርሐ ግብርን ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአንድ ዓመት ውስጥ ከ6,500 ሰዎች በላይ ማንበብና መጻፍ ተምረዋል። እንዲያውም ከ100,000 የሚበልጡ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ችለዋል። እንደ ቦሊቪያ፣ ኔፓል፣ ካሜሮንና ዛምቢያ ባሉ በርካታ አገሮች ውስጥም የመሠረተ ትምህርት መርሐ ግብር ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ማንበብና መጻፍ መማር (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን ብሮሹር ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያዘጋጁ ሲሆን ከሰባት ሚሊዮን በላይ ቅጂዎችን አትመዋል።

እንዲህ ያሉ የመሠረተ ትምህርት መርሐ ግብሮች ተግባራዊ በሚደረጉባቸው አገሮች የሚገኙ የትምህርት ባለሥልጣናት ለዚህ የማስተማር ሥራ ዕውቅና ሰጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሜክሲኮ የሚኖር አንድ የመንግሥት ሠራተኛ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለምታሳዩት የትብብር መንፈስ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፤ ሰዎች ከመሃይምነት ጨለማ እንዲላቀቁ እያከናወናችሁ ላላችሁት ድንቅ ሥራ የግዛቱ መስተዳድር ልባዊ አድናቆት እንዳለው በመስተዳድሩ ስም ስገልጽላችሁ ደስ ይለኛል። . . . የማስተማር ሥራችሁ ስኬታማ እንዲሆን እመኛለሁ።”

ተጨማሪ ሥልጠና

ተማሪዎች በሰዎች ፊት የማንበብና የመናገር ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ሥልጠና ይሰጣቸዋል

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራቸውን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን የማስተማር ችሎታቸውን ለማሻሻል ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ119,000 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ ተማሪዎች በሰዎች ፊት የማንበብና የመናገር ክህሎታቸውን ማሻሻል እንዲችሉ የሚረዳ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ትናንሽ ልጆችም እንኳ ማንበብ እንደቻሉ በዚህ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ሥልጠና ማግኘት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ በሰብዓዊ ትምህርታቸውም ሆነ በሌሎች መስኮች በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎች ሐሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ መግለጽ እንደሚችሉ በርካታ መምህራን አስተያየት ሰጥተዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የማንበብ ልማድ እንዲያዳብሩ በጉባኤ ምክር የሚሰጣቸው ሲሆን እያንዳንዱ ቤተሰብም የተለያዩ ጽሑፎችን የያዘ ቤተ መጻሕፍት እንዲኖረው ይበረታታል

ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በመንግሥት አዳራሹ ወይም በመሰብሰቢያ ቦታው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን፣ መዝገበ ቃላትንና ሌሎች የማመሳከሪያ ጽሑፎችን የያዘ ቤተ መጻሕፍት ይኖረዋል። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሚሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ በዚህ ቤተ መጻሕፍት መጠቀም ይችላሉ። የማንበብ ልማድ እንዲያዳብሩ በጉባኤ ምክር የሚሰጣቸው ሲሆን እያንዳንዱ ቤተሰብ ለልጆችም ሆነ ለአዋቂዎች የሚጠቅሙ የተለያዩ ጽሑፎችን የያዘ ቤተ መጻሕፍት እንዲኖረው ይበረታታል።

ከፍተኛ ሥልጠና

የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት፣ ወንዶችና ሴቶች ሚስዮናውያንን እንዲሁም በየአካባቢው ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሚያገለግሉ ወንዶችን የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶችንም አቋቁሟል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለትምህርት ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጡ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው።