በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዚህ ብሮሹር ዓላማ

የዚህ ብሮሹር ዓላማ

የደች ተወላጅ የሆነው ስፒኖዛ የተባለ ፈላስፋ “በሰው ድርጊት ከመሳቅና ከማዘን ብሎም ድርጊታቸውን ከመጸየፍ ይልቅ ሁኔታውን ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ” ሲል ጽፏል። አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች የሆኑትን ጨምሮ የተማሪዎችህን አመለካከት፣ አስተዳደግና እምነት መረዳት ፈታኝ ሊሆንብህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎች በተወሰኑ ጉዳዮች ከብዙሃኑ የተለየ አቋም ይወስዱ ይሆናል። ይሁንና አንድ ተማሪ እንዲህ ዓይነት አቋም የሚወስደው በሃይማኖታዊና በሥነ ምግባራዊ አመለካከቱ የተነሳ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳዩን በቁም ነገር ልታስብበት ይገባል። ይህ ብሮሹር የታተመው በመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር (የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት የኅትመት ዋና ክፍል) ሲሆን የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎችን አቋም በተሻለ ሁኔታ መገንዘብ እንድትችል ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም ጊዜ ወስደህ በደንብ እንደምታነበው ተስፋ እናደርጋለን።

የሌላን ሰው ሃይማኖታዊ እምነት መረዳት የዚያን ሰው እምነት መቀበል ወይም መከተል አይጠይቅም፤ እንዲሁም እምነትን የሚመለከቱ መረጃዎች መስጠት ሃይማኖትን ለማስቀየር እንደሚደረግ ሙከራ ተደርጎ መታየት የለበትም። ይህ ብሮሹር አንተም ሆንክ ተማሪዎችህ የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ አመለካከት እንድትቀበሉ ጫና ለማሳደር ተብሎ የተዘጋጀ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማችን፣ ከተማሪዎችህ መካከል አንዳንዶቹ ከወላጆቻቸው የተማሯቸውን መሠረታዊ መመሪያዎችና ሃይማኖታዊ አመለካከቶች እንድታውቅ መርዳት ነው፤ ይህም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆችን አቋም ለመረዳትና ከእነሱ ጋር ተግባብተህ ለመሥራት ያስችልሃል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ልጅ የራሱን ሕሊና ማሠልጠን የሚችልበትን መንገድ ገና በመማር ላይ በመሆኑ ልጆች የተማሩትና የሚያደርጉት ነገር አንዳንድ ጊዜ ላይጣጣም ይችላል።

እንደ ብዙዎቹ ወላጆች፣ የይሖዋ ምሥክሮችም ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ከሚገበዩት እውቀት በሚገባ እንዲጠቀሙ ይፈልጋሉ። ከዚህም የተነሳ ልጆቻቸው አስተማሪዎቻቸውን እንዲሰሙና የሚሰጧቸውን መመሪያ እንዲያከብሩ ያሠለጥኗቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆችና ልጆቻቸው፣ አስተማሪዎች አቋማቸውን ሲረዱላቸውና በአክብሮት ሲይዟቸው ይደሰታሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚታወቁ ክርስቲያኖች ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ስለ እነሱ የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ስለሆነም ይህ ብሮሹር የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎችህ ያላቸውን አቋም በተሻለ ሁኔታ እንድትገነዘብ ይረዳሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በተለይም ደግሞ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተለየ አቋም የመያዝ መብት እንዳላቸው የሚናገሩት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችልሃል።