በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ለትምህርት ያላቸው አመለካከት

የይሖዋ ምሥክሮች ለትምህርት ያላቸው አመለካከት

እንደ ማንኛውም ወላጅ፣ የይሖዋ ምሥክሮችም የልጆቻቸው የወደፊት ሕይወት ያሳስባቸዋል። በመሆኑም ለትምህርት ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። “ትምህርት፣ ሰዎች ጠቃሚ ዜጎች እንዲሆኑ መርዳት መቻል ይኖርበታል። በተጨማሪም ባሕላዊ ቅርሶቻቸውን እንዲያደንቁና ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲኖሩ ሊረዳቸው ይገባል።”

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ከተባለው የማመሳከሪያ ጽሑፍ ላይ የተወሰደው ይህ ሐሳብ እንደሚያመለክተው ከትምህርት ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ልጆችን ለዕለት ተዕለት ሕይወት ማሠልጠን ነው፤ ይህም ልጆቹ አድገው ቤተሰባቸው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ መርዳትን ይጨምራል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቤተሰብን መንከባከብ ቅዱስ የሆነ ኃላፊነት እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚከተለው ይላል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ልጆች በትምህርት ቤት የሚያገኙት ሥልጠና በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶችን መሸከም እንዲችሉ ከወዲሁ ያዘጋጃቸዋል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት በቁም ነገር ሊታይ እንደሚገባው ያምናሉ።

“ትምህርት፣ ሰዎች ጠቃሚ ዜጎች እንዲሆኑ መርዳት መቻል ይኖርበታል። በተጨማሪም ባሕላዊ ቅርሶቻቸውን እንዲያደንቁና ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲኖሩ ሊረዳቸው ይገባል።”​ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ

የይሖዋ ምሥክሮች፣ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ጋር ተስማምተው ለመኖር ይጥራሉ። (ቈላስይስ 3:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይህ መሠረታዊ መመሪያ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በሁሉም የኑሮ መስክ ይሠራል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች፣ ልጆቻቸው በትጋት እንዲያጠኑና በትምህርት ቤት የሚሰጧቸውን የክፍልና የቤት ሥራዎች በሚገባ እንዲሠሩ ያበረታቷቸዋል።

“የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት።”​ቈላስይስ 3:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው ለሚኖርበት አገር ሕግ መገዛት እንዳለበት ያስተምራል። ስለዚህ ሕጉ አንድ ሰው እስከተወሰነ ዓመት ድረስ እንዲማር የሚያስገድድ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሕግ ይታዘዛሉ።—ሮም 13:1-7

ጤናማ መዝናኛ፣ ሙዚቃ፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም ቤተ መጻሕፍትንና ቤተ መዘክሮችን መጎብኘትን የመሳሰሉ ነገሮች አንድ ልጅ ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ

ትምህርት ለዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጠቅም ሥልጠና እንደሚሰጥ አይካድም፤ ሆኖም ይህ የትምህርት ብቸኛም ሆነ ዋነኛ ዓላማ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ጥሩ ትምህርት፣ ልጆች በሕይወታቸው ደስተኞች እንዲሆኑ ብሎም የተረጋጉና በአእምሮ የበሰሉ ዜጎች መሆን እንዲችሉ ሊረዳቸው ይገባል። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች ከመደበኛው ትምህርት ውጭ ባሉ እንቅስቃሴዎች ረገድ የሚደረጉ ምርጫዎች ወሳኝ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ጤናማ መዝናኛ፣ ሙዚቃ፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም ቤተ መጻሕፍትንና ቤተ መዘክሮችን መጎብኘትን የመሳሰሉ ነገሮች አንድ ልጅ ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቻቸው ትልልቅ ሰዎችን እንዲያከብሩና ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እነሱን ለመርዳት ጥረት እንዲያደርጉ ያሠለጥኗቸዋል።

ስለ ተጨማሪ ትምህርትስ ምን ማለት ይቻላል?

በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተነሳ በሥራው ዓለም ያለው ሁኔታ በየጊዜው ይለዋወጣል። በዚህም ምክንያት ብዙ ወጣቶች ሥልጠና ባላገኙባቸው የሥራ መስኮች ወይም ሞያዎች መሠማራት ግድ ሆኖባቸዋል። በመሆኑም የሥራ ልማዳቸው፣ በግል ያገኙት ሥልጠና በተለይም ደግሞ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን አስማምተው የመሥራት ችሎታቸው የበለጠ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። ሥነ ጥበብ ባንሰራራበት ዘመን ይኖር የነበረው ሞንቴን የተባለ ደራሲ እንደገለጸው ተማሪዎች ‘በደንብ ከተሞላ አእምሮ ይልቅ በደንብ የታነጸ አእምሮ’ ያላቸው ሆነው ቢያድጉ የተሻለ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ፣ በቂ ሥልጠና ያላገኙ ወጣቶች የሀብታም አገሮችም ሆነ የድሃ አገሮች ችግር ለሆነው ሥራ አጥነት የተጋለጡ ናቸው። ስለዚህ አንድ ሰው ሥራ ለማግኘት ሕጉ ከሚጠይቀው የትምህርት ደረጃ በተጨማሪ ሌላ ሥልጠና መውሰድ የሚያስፈልገው ከሆነ ወላጆች ተጨማሪ ትምህርት መከታተልን በተመለከተ ጥቅሙንና ጉዳቱን በማመዛዘን ልጆቻቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርጉ የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው።

ይሁን እንጂ ስኬት የሚለካው በቁሳዊ ብልጽግና ብቻ እንዳልሆነ ሳትገነዘብ አትቀርም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በሥራ የተጠመዱ ወንዶችና ሴቶች ከሥራ ገበታቸው በሚፈናቀሉበት ጊዜ መላ ሕይወታቸው ባዶ ሲሆንባቸው ይታያል። አንዳንድ ወላጆች የሥራ ሱስ የተጠናወታቸው ከመሆኑ የተነሳ የቤተሰባቸውን ሕይወትና ከልጆቻቸው ጋር ሊያሳልፉት የሚችሉትን ጊዜ መሥዋዕት ያደርጋሉ፤ በመሆኑም ልጆቻቸው እንዲበስሉና እንዲጎለምሱ መርዳት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቁሳዊ ብልጽግና ብቻውን እውነተኛ ደስታ ስለማያስገኝ ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት ይህን ሐቅ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ጥሩ የሆኑ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ባሕርያትን ማፍራት ብሎም ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያስችል ሥልጠና መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ።