በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት

ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት

1, 2. በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ ያለውን ትንቢት በትኩረት ልንከታተል የሚገባን ለምንድን ነው?

ሁለት ተጻራሪ ነገሥታት አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት የሞት ሽረት ትግል ገጥመዋል። በዘመናት ሂደት ውስጥ ተራ በተራ እየተፈራረቁ የበላይነትን ሲቀዳጁ ኖረዋል። አንዱ አደብ ሲገዛ ሌላው የገነነባቸው ወቅቶች የነበሩ ሲሆን ምንም ዓይነት ግጭት ያልተከሰተባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ይሁንና ድንገት ሌላ ውጊያ ይጫርና ሽኩቻው ይቀጥላል። የዚህ ድራማ ተዋናያን ከሆኑት መካከል የሶርያው ንጉሥ ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር፣ የግብፁ ንጉሥ ቶሌሚ ላገስ፣ የሶርያ ልዕልት የነበረችውና በኋላም የግብፅ ንግሥት የሆነችው ቀዳማዊት ክሊዮፓትራ፣ የሮማዎቹ ንጉሠ ነገሥታት አውግስጦስና ጢባርዮስ እንዲሁም የፓልሚራዋ ንግሥት ዘኖቢያ ይገኙበታል። ሽኩቻው ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲመጣ ደግሞ ናዚ ጀርመን፣ የኮሚንስቱ ጎራ አባል አገራት፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል፣ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተጨምረዋል። ከእነዚህ ፖለቲካዊ ወገኖች መካከል ማናቸውም ቢሆኑ የመጨረሻው ምዕራፍ ምን እንደሚሆን ሊተነብዩ አይችሉም። የይሖዋ መልአክ ይህንን አስገራሚ ትንቢት ለነቢዩ ዳንኤል የገለጠለት ከ2,500 ዓመታት በፊት ነበር።—ዳንኤል ምዕራፍ 11

2 መልአኩ ወደፊት በሚነሱት ሁለት ነገሥታት መካከል ስለሚኖረው ፉክክር በዝርዝር ሲያስረዳው ዳንኤል ምንኛ ተደንቆ ይሆን! በሁለቱ ነገሥታት መካከል የሚደረገው ትግል እስከ ዘመናችን ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ ድራማው የእኛንም ትኩረት የሚስብ ነው። የትንቢቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ፍጻሜውን ማግኘቱ በታሪክ የተረጋገጠው እንዴት እንደሆነ ስንመለከት የትንቢታዊው ዘገባ የኋለኛው ክፍልም ፍጻሜውን ማግኘቱ እንደማይቀር ያለን እምነትና ትምክህት ይጠነክራል። ይህን ትንቢት በትኩረት መከታተላችን በጊዜ ሂደት ውስጥ የትኛው ነጥብ ላይ እንደቆምን በግልጽ እንድናስተውል ይረዳናል። አምላክ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ጊዜ ከግጭቱ ገለልተኛ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነውንም ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። (መዝሙር 146:3, 5) እንግዲያውስ የይሖዋ መልአክ ለዳንኤል የሚነግረውን ነገር በጉጉት እንከታተል።

በግሪክ መንግሥት ላይ ይነሣል

3. መልአኩ ‘በሜዶናዊው ዳርዮስ የመጀመሪያ ዓመት’ የደገፈው ማንን ነው?

3 መልአኩ “እኔም በሜዶናዊው በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት [539/538 ከዘአበ] አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር” ብሏል። (ዳንኤል 11:1) በዚህ ጊዜ ዳርዮስ በሕይወት ባይኖርም መልአኩ የእርሱን ግዛት የትንቢታዊው መልእክት መጀመሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ዳንኤል ከአንበሶች ጉድጓድ እንዲወጣ ትእዛዝ የሰጠው ይህ ንጉሥ ነበር። በተጨማሪም ዳርዮስ ተገዥዎቹ በሙሉ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈሩ የሚያዝዝ ድንጋጌ አውጥቶ ነበር። (ዳንኤል 6:21-27) ይሁን እንጂ መልአኩ ደጋፊ ሆኖ የቆመው ለሜዶናዊው ዳርዮስ ሳይሆን የዳንኤል ሕዝቦች አለቃ ለሆነውና ለባልደረባው ለሚካኤል ነው። (ከዳንኤል 10:12-14 ጋር አወዳድር።) የአምላክ መልአክ ይህንን ድጋፍ የሰጠው ሚካኤል የሜዶ ፋርስን ጋኔናዊ አለቃ በተቋቋመበት ጊዜ ነበር።

4, 5. በትንቢት የተነገረላቸው አራቱ የፋርስ ነገሥታት እነማን ናቸው?

4 የአምላክ መልአክ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እነሆ፣ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፤ ባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል።” (ዳንኤል 11:2) ታዲያ እነዚህ የፋርስ ገዥዎች እነማን ነበሩ?

5 የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ነገሥታት ታላቁ ቂሮስ፣ ዳግማዊ ካምቢሰስ እና ቀዳማዊ ዳርዮስ ናቸው። ባርዲያ (ምናልባትም ባርዲያ ነኝ ብሎ የተነሣው ጋውማታ በሚባል ስም የሚታወቀው ሰው) የገዛው ለሰባት ወር ስለነበር ትንቢቱ የእርሱን አጭር የግዛት ዘመን ግምት ውስጥ አላስገባም። በ490 ከዘአበ ሦስተኛው ንጉሥ ቀዳማዊ ዳርዮስ ግሪክን ለሁለተኛ ጊዜ ለመውረር ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ፋርሳውያኑ ማራቶን ላይ ክፉኛ ተመትተው ወደ ትንሿ እስያ ሸሹ። ዳርዮስ በግሪክ ላይ ተጨማሪ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት ቢያደርግም ከአራት ዓመት በኋላ በሞት በመቀጨቱ ዘመቻውን ማስፈጸም ሳይችል ቀርቷል። ዘመቻው ዙፋኑን ለወረሰው ልጁ ማለትም ‘ለአራተኛው ንጉሥ’ ለቀዳማዊ ለዜርሰስ ተላለፈ። ዜርሰስ አስቴርን ያገባው አሕሻዊሮስ ነው።—አስቴር 1:1 NW2:15-17

6, 7. (ሀ) አራተኛው ንጉሥ ‘በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣው’ እንዴት ነው? (ለ) ዜርሰስ በግሪክ ላይ የከፈተው ዘመቻ ውጤቱ ምን ነበር?

6 በእርግጥም ቀዳማዊ ዜርሰስ ‘በግሪክ መንግሥት’ ማለትም በቡድን ባሉት የግሪክ ነፃ ግዛቶች ላይ ‘ሁሉን አስነስቶ ነበር።’ ዘ ሜደስ ኤንድ ፐርሺያንስ—ኮንከረርስ ኤንድ ዲፕሎማትስ የተባለው መጽሐፍ “ዜርሰስ ልባቸው ትልቅ በሆነው ባለሟሎቹ ጎትጓችነት በምድርና በባሕር ጥቃት ሰንዝሯል” ብሏል። በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረው ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ “ከዚህ የዜርሰስ ዘመቻ ጋር የሚወዳደር ጥቃት አይኖርም” ሲል ዘግቧል። እንዲህ ብሏል:- የባሕር ኃይሉ ሠራዊት “እስከ 517,610 ይደርስ ነበር። 1,700,000 እግረኛ ወታደርና 80,000 ፈረሰኛ ሠራዊት የነበረው ሲሆን፤ ይህ ሁሉ ደግሞ ግመል ይጋልቡ የነበሩት አረቦችና ሠረገለኞቹ ሊቢያውያን ሳይታሰቡ ነው። እነርሱ ብቻቸውን 20,000 የሚሆኑ ይመስለኛል። በመሆኑም የምድርና የባሕር ኃይሉ ወታደሮች ቁጥር በአጠቃላይ ሲደመር 2,317,610 ይደርሳል።”

7 ቀዳማዊ ዜርሰስ በ480 ከዘአበ ይህን ግዙፍ ሠራዊት በግሪክ ላይ ሲያዘምት ዓላማው ሙሉ በሙሉ ድል አድርጎ መያዝ እንጂ ሌላ አልነበረም። ግሪካውያኑ በተርሞፕሊ ዘመቻውን ለማዘግየት የተጠቀሙበትን የጦር ስልት አክሽፈው ፋርሳውያኑ አቴንስን ዶግ አመድ አደረጓት። ይሁንና በሳለመስ ፋርሳውያኑ ራሳቸው ትልቅ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ግሪካውያን በ479 ከዘአበ በፕለቴ ሌላ ድል ተቀዳጁ። ከዚያ በኋላ በነበሩት 143 ዓመታት ውስጥ በዜርሰስ ፋንታ በፋርስ ግዛት ዙፋን ላይ ከተቀመጡት ሰባት ነገሥታት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከግሪክ ጋር ጦርነት አልገጠሙም። በዚህ ጊዜ ግን በግሪክ አንድ ኃያል ንጉሥ ተነሣ።

ታላቁ መንግሥት ለአራት ተከፋፈለ

8. የተነሣው ‘ኃያል ንጉሥ’ የትኛው ነው? ‘በትልቅ አገዛዝስ የገዛው’ እንዴት ነው?

8 መልአኩ “ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፣ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፣ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 11:3) የሃያ ዓመቱ እስክንድር በ336 ከዘአበ የመቄዶንያ ንጉሥ ሆኖ ‘ተነሣ።’ ታላቁ እስክንድር እስኪባል ድረስ በእርግጥም ‘ኃያል ንጉሥ’ ሆኗል። በአባቱ በዳግማዊ ፊሊፕ ዕቅድ ተነሳስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘውን የፋርሳውያን ክፍለ ግዛት ተቆጣጠረ። አርባ ሰባት ሺህ የሚያክለው ሠራዊቱ የኤፍራጥስንና የጤግሮስን ወንዞች ተሻግሮ የሳልሳዊ ዳርዮስን 250,000 ሠራዊት በጋውጋሜላ ብትንትኑን አወጣው። ዳርዮስ ከሸሸ በኋላ ስለተገደለ የፋርስ ሥርወ መንግሥት አክትሟል። በዚህ ጊዜ ግሪክ የዓለም ኃያል ሆነች። እስክንድርም ‘በትልቅ አገዛዝ ይገዛ እንደ ፈቃዱም ያደርግ ጀመር።’

9, 10. የእስክንድር መንግሥት ለዘሩ እንደማይከፋፈል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

9 የአምላክ መልአክ እንደሚከተለው ብሎ ስለነበር የእስክንድር የዓለም አገዛዝ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አልነበረም:- “እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፣ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።” (ዳንኤል 11:4) እስክንድር በድንገተኛ ሕመም በ323 ከዘአበ በባቢሎን ሕይወቱ ሲቀጭ ገና 33 ዓመት እንኳ አልሞላውም ነበር።

10 ሰፊው የእስክንድር ግዛት ‘ለዘሩ’ አልተከፋፈለም። ወንድሙ ሳልሳዊ ፊሊፕ አርዴስ ከሰባት ላነሱ ዓመታት ከገዛ በኋላ በእስክንድር እናት በኦሊምፒየስ ጥያቄ በ317 ከዘአበ ተገደለ። የእስክንድር ልጅ የሆነው እስክንድር አራተኛ እስከ 311 ከዘአበ ድረስ ከገዛ በኋላ ከአባቱ ጄኔራሎች አንዱ በነበረው በካሳንደር ተገደለ። ከሕጋዊ ሚስቱ ያልተወለደው የእስክንድር ልጅ ሄራክለስ በአባቱ ስም ለመግዛት ፈልጎ የነበረ ቢሆንም በ309 ከዘአበ ተገድሏል። በዚህ መልኩ የእስክንድር የዘር መስመር ተቋረጠ፤ ‘ግዛቱም’ ከቤተሰቡ ተወሰደ።

11. የእስክንድር መንግሥት ‘ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የተከፋፈለው’ እንዴት ነበር?

11 ከእስክንድር ሞት በኋላ መንግሥቱ ‘ወደ አራቱ የምድር ነፋሳት’ ተከፋፍሏል። በቁጥር ብዙ የነበሩት ጄኔራሎቹ የግዛት ክልሉን ሲቀራመቱ እርስ በርሳቸው ተጋጭተው ነበር። አንድ ዓይናው ጄኔራል ቀዳማዊ አንቲጎነስ መላውን የእስክንድር ግዛት በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ሆኖም በፍርግያ በምትገኘው ኢፕሰስ በዋለው አውደ ግንባር ተገደለ። በ301 ከዘአበ አራቱ የእስክንድር ጄኔራሎች አዛዣቸው ድል አድርጎ በተቆጣጠረው ሰፊ ግዛት ላይ ሥልጣን ጨበጡ። ካሳንደር መቄዶንያንና ግሪክን ይገዛ ጀመር። ላይሲመከስ ትንሿን እስያንና ትሬስን ተቆጣጠረ። ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር መሶጴጣምያንና ሶርያን በእጁ አስገባ። ቶሌሚ ላገስ ደግሞ ግብጽንና ፍልስጤምን ያዘ። ልክ በትንቢታዊው ቃል መሠረት የእስክንድር ታላቅ ግዛት ለአራት ሄለናዊ መንግሥታት ተከፋፈለ።

ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት ብቅ አሉ

12, 13. (ሀ) አራቱ ሄለናዊ መንግሥታት ወደ ሁለት የታጠፉት እንዴት ነው? (ለ) ሰሉከስ በሶርያ ያቋቋመው ሥርወ መንግሥት የትኛው ነው?

12 ካሳንደር ወደ ሥልጣን ከወጣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመሞቱ በ285 ከዘአበ ላይሲመከስ የግሪክ ግዛት የነበረውን የአውሮፓ ክልል ተቆጣጠረ። በ281 ከዘአበ ላይሲመከስ ከቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ጋር ሲዋጋ ስለወደቀ ሰሉከስ አብዛኛውን የእስያ ክልል መቆጣጠር ጀመረ። ከእስክንድር ጄኔራሎች መካከል የአንዱ የልጅ ልጅ የሆነው ዳግማዊ አንቲጎነስ ጋንተስ በ276 ከዘአበ በመቄዶንያ ዙፋን ላይ ወጣ። ከጊዜ በኋላ መቄዶንያ የሮማ ጥገኛ ሆና ቆይታ በ146 ከዘአበ አንደኛውኑ የሮማ ክፍለ ግዛት በመሆን ተጠቃልላለች።

13 ከአራቱ ሄለናዊ መንግሥታት ገናና ሆነው የቀጠሉት ሁለቱ የቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተርና የቶሌሚ ላገስ መንግሥታት ነበሩ። ሰሉከስ በሶርያ የሰሉሲድን ሥርወ መንግሥት መሠረተ። ከቆረቆራቸው ከተሞች መካከል አዲሷ የሶርያ መዲና አንጾኪያና የሴሌውቅያ የወደብ ከተማ ይገኙበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው በተጠሩባት በአንጾኪያ አስተምሯል። (ሥራ 11:25, 26፤ 13:1-4) ሰሉከስ በ281 ከዘአበ ቢገደልም ሥርወ መንግሥቱ የሮማው ጄኔራል ኒየስ ፖምፒ፣ ሶርያ የሮማ ክፍለ ግዛት እንድትሆን እስካደረገበት እስከ 64 ከዘአበ ድረስ ቀጥሎ ነበር።

14. የቶሌሚ ሥርወ መንግሥት በግብጽ የተቋቋመው መቼ ነበር?

14 ከአራቱ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ሄለናዊ መንግሥት በ305 ከዘአበ ንጉሥ የሚል ማዕረግ ያገኘው ቶሌሚ ላገስ ወይም ቀዳማዊ ቶሌሚ የሚመራው መንግሥት ነበር። እርሱ የመሠረተው የቶሌሚ ሥርወ መንግሥት እስከ 30 ከዘአበ ድረስ በግብጽ መግዛቱን ቀጥሏል።

15. ከአራቱ ሄለናዊ መንግሥታት የወጡት ሁለት ጠንካራ ነገሥታት የትኞቹ ናቸው? ምንስ ትግል ጀመሩ?

15 በዚህ መንገድ ከአራቱ ሄለናዊ መንግሥታት መካከል ሁለት ጠንካራ ነገሥታት ብቅ አሉ። እነርሱም በሶርያ የነገሠው ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተርና በግብጽ የነገሠው ቀዳማዊ ቶሌሚ ናቸው። በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የተገለጸው ‘በሰሜን ንጉሥና’ ‘በደቡብ ንጉሥ’ መካከል የሚደረገው ረጅም ትግል የጀመረው ከእነዚህ ነገሥታት ነው። የእነዚህ ሁለት ነገሥታት ማንነትና አገር በየዘመናቱ ስለሚለዋወጥ የይሖዋ መልአክ ስማቸውን ሳይጠቅስ ቀርቷል። መልአኩ አላስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን በማስቀረት በዚህ ሽኩቻ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸውን ገዥዎችና ክንውኖች ብቻ ጠቅሷል።

ሽኩቻው ጀመረ

16. (ሀ) ሁለቱ ነገሥታት የነበሩት ከማን በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ ነው? (ለ) የመጀመሪያዎቹ ‘የሰሜን ንጉሥ’ እና ‘የደቡብ ንጉሥ’ የነበሩት ነገሥታት እነማን ናቸው?

16 አዳምጥ! የይሖዋ መልአክ የዚህን አስገራሚ ሽኩቻ አጀማመር ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም [ከእስክንድር አለቆች] አንዱ ይበረታሉ፤ እርሱም [የሰሜን ንጉሥም] ይበረታበታል ይሠለጥንማል፤ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል።” (ዳንኤል 11:5) ‘የሰሜን ንጉሥ’ እና ‘የደቡብ ንጉሥ’ የሚለው ስያሜ የሚያመለክተው በወቅቱ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተው ወደ ምድራቸው ወደ ይሁዳ ከተመለሱት የዳንኤል ሕዝብ በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ የነበሩትን ነገሥታት ነው። የመጀመሪያው ‘የደቡብ ንጉሥ’ የግብጹ ቀዳማዊ ቶሌሚ ነው። ከእስክንድር ጄኔራሎች መካከል አንዱ የሆነውና በቀዳማዊ ቶሌሚ ላይ ‘የበረታው’ እንዲሁም ‘ግዛቱም ታላቅ የሆነው’ የሶርያው ንጉሥ ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ነበር። ‘የሰሜን ንጉሥ’ ሆኖ ብቅ ያለው እርሱ ነው።

17. በሰሜኑና በደቡቡ ንጉሥ መካከል ሽኩቻ ሲጀመር የይሁዳ ምድር በማን ቁጥጥር ሥር ነበረች?

17 ሽኩቻው ሲጀመር ይሁዳ በደቡቡ ንጉሥ ቁጥጥር ሥር ነበረች። ከ320 ከዘአበ አንስቶ ቀዳማዊ ቶሌሚ አይሁዳውያን በቅኝ ተገዥነት መልክ ወደ ግብጽ እንዲሄዱ አድርጓል። ቀዳማዊ ቶሌሚ፣ ዕውቅ ቤተ መጻሕፍት በከፈተባት በእስክንድርያ የአይሁዳውያኑ ማኅበረሰብ ቁጥር እያደገ ሄደ። በይሁዳ ያሉትም አይሁዳውያን እስከ 198 ከዘአበ ድረስ በደቡብ ንጉሥ ማለትም በግብጹ ቶሌሚ አስተዳደር ሥር ቆይተዋል።

18, 19. በጊዜ ሂደት ሁለቱ ተጻራሪ ነገሥታት ‘የጋራ ስምምነት ያደረጉት’ እንዴት ነው?

18 ሁለቱን ነገሥታት በሚመለከት መልአኩ እንደሚከተለው ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ [“ያብራሉ፣” NW]፤ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን [“የጋራ ስምምነት፣” NW] ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፤ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፣ እርሱና ክንዱም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ።” (ዳንኤል 11:6) ይህ የተፈጸመው እንዴት ነው?

19 የቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ልጅና የዙፋኑ ወራሽ የነበረው ቀዳማዊ አንታይከስ ከደቡቡ ንጉሥ ጋር የገጠመው ወሳኝ ጦርነት ስላልነበረ ትንቢቱ እርሱን ግምት ውስጥ አላስገባም። ይሁን እንጂ የእርሱን ዙፋን የወረሰው ዳግማዊ አንታይከስ የቀዳማዊ ቶሌሚ ልጅ ከሆነው ከዳግማዊ ቶሌሚ ጋር ረጅም ጦርነት አካሂዷል። ዳግማዊ አንታይከስ የሰሜን ንጉሥ ዳግማዊ ቶሌሚ ደግሞ የደቡብ ንጉሥ ሆነው ነበር። ዳግማዊ አንታይከስ፣ ላድሴን አግብቶ ዳግማዊ ሰሉከስን ሲወልድ ዳግማዊ ቶሌሚ ደግሞ ቤረኒስ የተባለች ሴት ልጅ ነበረችው። በ250 ከዘአበ እነዚህ ሁለት ነገሥታት ‘የጋራ ስምምነት’ አድርገዋል። ይህን አጋርነት ለማጠናከር ሲባል ዳግማዊ አንታይከስ ሚስቱን ላድሴን ፈትቶ ‘የደቡቡን ንጉሥ ሴት ልጅ’ ቤረኒስን አገባ። የዙፋኑ ወራሽ ያደረገውም ከቤረኒስ የወለደውን ልጅ እንጂ ከላድሴ የወለዳቸውን ልጆች አልነበረም።

20. (ሀ) የቤረኒስ ‘ክንድ’ ሳይጸና የቀረው እንዴት ነው? (ለ) ቤረኒስ እንዲሁም እርስዋን ‘ያመጧትና’ ‘ያጸኗት’ ሁሉ አልፈው የተሰጡት እንዴት ነው? (ሐ) ዳግማዊ አንታይከስ ‘ክንዱን’ ወይም ኃይሉን ካጣ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ሆኖ የተነሣው ማን ነው?

20 የቤረኒስ ‘ክንድ’ ወይም ደጋፊ አባቷ ዳግማዊ ቶሌሚ ነበር። በ246 ከዘአበ ሲሞት ግን ‘የክንዷ ኃይል’ ከባሏ ጋር ‘አልጸናም።’ ዳግማዊ አንታይከስ እርሷን ትቶ ላድሴን እንደገና በማግባት የእርሷ ልጅ ዙፋኑን እንዲወርስ አደረገ። በላድሴ ዕቅድ መሠረት ቤረኒስና ልጅዋ ተገደሉ። ከማስረጃዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው “እርስዋን ያመጡ” ተብለው የተገለጹት ቤረኒስን ከግብጽ ወደ ሶርያ ያመጧት አጃቢዎቿም መጨረሻቸው ከዚህ የተለየ አልነበረም። ላድሴ፣ ዳግማዊ አንታይከስንም ቢሆን መድኃኒት አብልታው ስለነበር የእርሱም ‘ክንድ’ ወይም ኃይል እንዲሁ ‘አልጸናም።’ በመሆኑም የቤረኒስ አባት ማለትም ‘የወለዳት’ እና ለጊዜውም ቢሆን “ያጸናት” ሶርያዊ ባሏ ሁለቱም ሞቱ። ይህም የላድሴ ልጅ የሆነው ዳግማዊ ሰሉከስ የሶርያ ንጉሥ እንዲሆን አስችሎታል። ቀጣዩ ቶሌሚያዊ ንጉሥስ በአጸፋው ምን ያደርግ ይሆን?

የእህቱን ደም የተበቀለ ንጉሥ

21. (ሀ) ከቤረኒስ ‘ሥር’ የተገኘው ‘አንዱ ቁጥቋጥ’ ማን ነበር? ‘የተነሣውስ’ እንዴት ነው? (ለ) ሳልሳዊ ቶሌሚ ‘በሰሜን ንጉሥ አምባ’ ላይ የዘመተውና ያሸነፈውስ እንዴት ነው?

21 መልአኩ እንዲህ ብሏል:- “ከሥርዋ ቁጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፣ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፣ በላያቸውም ያደርጋል፣ ያሸንፍማል።” (ዳንኤል 11:7) የቤረኒስ ‘ሥር’ ተደርገው የተገለጹት ወላጆቿ ሲሆኑ ከእነርሱ የወጣው ‘ከቁጥቋጡ አንዱ’ ደግሞ ወንድሟ ነው። አባቱ ሲሞት የግብጹ ፈርዖን ሳልሳዊ ቶሌሚ በሚል ስያሜ የደቡብ ንጉሥ ሆኖ ‘ተነሣ።’ ወዲያውኑም የእህቱን ደም መበቀሉን ተያያዘው። ላድሴ ቤረኒስንና ልጅዋን ለማስገደል በተጠቀመችበት በሶርያው ንጉሥ በዳግማዊ ሰሉከስ ላይ በመዝመት ‘ወደ ሰሜን ንጉሥ አምባ መጣ።’ ሳልሳዊ ቶሌሚ የተመሸገችውን የአንጾኪያ ክፍል በመቆጣጠር ላድሴን ገደለ። በሰሜኑ ንጉሥ ግዛት በስተ ምሥራቅ በኩል በመገስገስም ባቢሎንያን በዝብዞ ወደ ሕንድ አቀና።

22. ሳልሳዊ ቶሌሚ ወደ ግብጽ መልሶ ያመጣው ምንድን ነው? ‘ለጥቂት ዓመታት ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ የተቀመጠውስ’ ለምንድን ነው?

22 ከዚያስ ምን ሆነ? የአምላክ መልአክ እንዲህ ይለናል:- “አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅ የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፤ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል።” (ዳንኤል 11:8) ከ200 ዓመታት ቀደም ብሎ የፋርሱ ንጉሥ ዳግማዊ ካምቢሰስ፣ ግብጽን ድል በማድረግ የግብጻውያንን አማልክት ማለትም “ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን” ወደ አገሩ አግዞ ነበር። ሳልሳዊ ቶሌሚ የጥንቷን የፋርስ ንጉሣዊ መዲና ሱሳን በመበዝበዝ እነዚህን አማልክት አስመልሶ ወደ ግብጽ ‘ማርኳል።’ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ‘ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎች’ ዘርፎ ወስዷል። ሳልሳዊ ቶሌሚ በአገሩ የተነሣውን ዓመፅ ለማብረድ ሲል መመለስ ግድ ስለሆነበት ‘ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ’ ቀርቷል፤ ይህም በሰሜኑ ንጉሥ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስበት ገትቶታል።

የሶርያው ንጉሥ የበቀል እርምጃ ወሰደ

23. የሰሜን ንጉሥ ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ከመጣ በኋላ ‘ወደ ምድሩ የተመለሰው’ ለምን ነበር?

23 የሰሜኑ ንጉሥ ምን ምላሽ ሰጠ? ዳንኤል “ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፣ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል” የሚል ቃል ተነግሮታል። (ዳንኤል 11:9) የሰሜን ንጉሥ የሆነው የሶርያ ንጉሥ ዳግማዊ ሰሉከስ መልሶ የማጥቃት እርምጃ በመውሰድ ወደ ግብጹ የደቡብ ንጉሥ “መንግሥት” ወይም ግዛት ቢገባም ሽንፈት ገጥሞታል። ዳግማዊ ሰሉከስ በ242 ከዘአበ ወደ ሶርያዋ መዲና አንጾኪያ አፈግፍጎ ‘ወደ ምድሩ የተመለሰው’ ከቀሪዎቹ ጥቂት ወታደሮች ጋር ነበር። እርሱ ሲሞት ልጁ ሳልሳዊ ሰሉከስ በፋንታው ነገሠ።

24. (ሀ) ሳልሳዊ ሰሉከስ ምን ገጠመው? (ለ) የሶርያው ንጉሥ ሳልሳዊ አንታይከስ በደቡቡ ንጉሥ ግዛት ላይ ‘እንደ ጎርፍ የመጣውና ያለፈው’ እንዴት ነው?

24 የሶርያውን ንጉሥ የዳግማዊ ሰሉከስን ልጆች በሚመለከት ምን ትንቢት ተነግሯል? መልአኩ ለዳንኤል እንዲህ ብሎታል:- “ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፤ እርሱም ይመጣል፣ ይጎርፍማል፣ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል።” (ዳንኤል 11:10) ሳልሳዊ ሰሉከስ በመገደሉ ግዛቱ ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አከተመ። ወንድሙ ሳልሳዊ አንታይከስ በእርሱ ፋንታ በሶርያ ዙፋን ላይ ተቀመጠ። ይህ የዳግማዊ ሰሉከስ ልጅ ግዙፍ ሠራዊት በማደራጀት በወቅቱ የደቡብ ንጉሥ በነበረው ቶሌሚ አራተኛ ላይ ለመዝመት ተዘጋጀ። አዲሱ የሶርያ የሰሜን ንጉሥ ከግብጽ ጋር የተሳካ ውጊያ በማድረግ የሴሌውቅያን የወደብ ከተማ፣ የኮይሌ-ሶርያን ክፍለ ግዛት፣ የጢሮስን ከተማና ታልማስን ጨምሮ በአቅራቢያው ያሉ ከተሞችን መልሶ ተቆጣጠረ። የንጉሥ ቶሌሚ አራተኛን ሠራዊት በማፍረክረክ የይሁዳን ብዙ ከተሞች ተቆጣጠረ። በ217 ከዘአበ የፀደይ ወራት ሳልሳዊ አንታይከስ ከታልማስ ተነሥቶ በስተ ሰሜን በኩል በሶርያ እስካለው ‘እስከ አምባው ድረስ ሄደ።’ ይሁን እንጂ ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም።

የሞገዱ አቅጣጫ ተቀየረ

25. ቶሌሚ አራተኛ፣ ሳልሳዊ አንታይከስን በጦርነት የገጠመው የት ነው? በግብጹ የደቡብ ንጉሥ ‘እጅ አልፎ የተሰጠውስ’ ምንድን ነው?

25 የይሖዋ መልአክ የሚከተለውን ትንቢት ሲናገር እኛም እንደ ዳንኤል በጉጉት እናዳምጥ:- “የደቡብም ንጉሥ ይቆጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፣ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል።” (ዳንኤል 11:11) የደቡቡ ንጉሥ ቶሌሚ አራተኛ 75,000 ሠራዊት አሰልፎ በስተ ሰሜን ወደ ጠላቱ ዘመተ። የሶርያው የሰሜን ንጉሥ ሳልሳዊ አንታይከስ 68,000 የሚያህል “ብዙ ሕዝብ” አሰልፎ በእርሱ ላይ ተነሥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ‘ብዙ ሕዝብ’ ከግብጽ ድንበር ብዙም በማትርቀው የድንበር ከተማ በራፋይ በተደረገው ውጊያ በደቡብ ንጉሥ ‘እጅ አልፎ ተሰጠ።’

26. (ሀ) በራፋይ በተደረገው ውጊያ በደቡብ ንጉሥ የተወሰደው “ብዙ ሕዝብ” ምንድን ነው? በዚያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ውሎችስ ምንድን ናቸው? (ለ) ቶሌሚ አራተኛ ‘ብርቱ ኃይሉን ሳይጠቀም የቀረው’ እንዴት ነው? (ሐ) ቀጣዩ የደቡብ ንጉሥ ማን ነበር?

26 ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፤ ነገር ግን አያሸንፍም [“ኃይሉን አይጠቀምም፣” NW]።” (ዳንኤል 11:12) የደቡቡ ንጉሥ ቶሌሚ አራተኛ የሶርያን 10,000 እግረኛ ሠራዊትና 300 ፈረሰኞች በሞት ‘ሲወስድ’ 4,000 የሚያህሉትን ደግሞ በምርኮ አግዟል። ከዚያም ነገሥታቱ፣ ሳልሳዊ አንታይከስ የሶርያዋ የወደብ ከተማውን ሴሌውቅያን አስቀርቶ ፊኒሺየንና ኮይሌ-ሶርያን እንዲያስረክብ ተስማሙ። የግብጹ የደቡብ ንጉሥ በዚህ ድል ‘ልቡ ታበየ፤’ በተለይ በይሖዋ ላይ። ይሁዳ በቶሌሚ አራተኛ ግዛት ሥር እንደሆነች ቆየች። ይሁን እንጂ በሶርያው የሰሜን ንጉሥ ላይ ባገኘው ድል ለመግፋት ‘ኃይሉን አልተጠቀመም።’ ይልቁንም ቶሌሚ አራተኛ አኗኗሩ ብልሹ እየሆነ በመሄዱ የአምስት ዓመት ልጁ ቶሌሚ አምስተኛ፣ ሳልሳዊ አንታይከስ ከመሞቱ ትንሽ ዓመታት ቀደም ብሎ ቀጣዩ የደቡብ ንጉሥ ሆኗል።

ጀብደኛው ተመለሰ

27. የሰሜኑ ንጉሥ ‘በዘመን ፍጻሜ ላይ’ የግዛት ክልል ከግብጽ ለማስመለስ የመጣው እንዴት ነበር?

27 ሳልሳዊ አንታይከስ ከፈጸማቸው ጀብዱዎች የተነሣ ታላቁ አንታይከስ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። እርሱን በሚመለከት መልአኩ እንዲህ ብሏል:- “የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፣ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ይቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል።” (ዳንኤል 11:13) እነዚህ “ዘመናት” ግብጻውያን ሶርያውያኑን በራፋይ ድል ካደረጉ በኋላ የነበሩት 16 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዓመታት ናቸው። ወጣቱ ቶሌሚ አምስተኛ የደቡብ ንጉሥ በሆነ ጊዜ ሳልሳዊ አንታይከስ ለግብጹ የደቡብ ንጉሥ ለመተው የተገደደባቸውን ክልሎች ለማስመለስ “ከቀደመው የበለጠ ብዙ ሕዝብ” አደራጀ። ይህን ዓላማውንም ከግብ ለማድረስ ኃይሉን ከመቄዶንያው ንጉሥ ፊሊፕ አምስተኛ ጋር አጣመረ።

28. ወጣቱ የደቡቡ ንጉሥ ምን ችግሮች ገጥመውት ነበር?

28 የደቡቡ መንግሥት በራሱ መንግሥት ውስጥም ችግር ነበረበት። መልአኩ “በዚያ ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ” ብሏል። (ዳንኤል 11:14ሀ) በእርግጥም ደግሞ ‘ብዙዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ተነሥተዋል።’ ወጣቱ የደቡብ ንጉሥ፣ ሳልሳዊ አንታይከስን እና መቄዶናዊውን አጋሩን ብቻ ሳይሆን በውስጥ ማለትም በግብጽ የገጠሙትንም ችግሮች ጭምር መጋፈጥ ነበረበት። በስሙ ያስተዳድር የነበረው ባለሟሉ ጋትክሌዝ ግብጻውያኑን አላግባብ ስለያዛቸው ብዙዎች ዓምፀው ነበር። መልአኩ እንዲህ ሲል ጨምሮ ተናግሯል:- “ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።” (ዳንኤል 11:14ለ) ከዳንኤል ሕዝብ እንኳ ሳይቀር አንዳንዶቹ ‘የዓመፅ ልጆች’ ወይም አብዮተኞች ሆነው ነበር። ይሁን እንጂ በትውልድ አገራችን ያለው የአሕዛብ የበላይነት የሚያከትምበት ጊዜ ቀርቧል የሚለው የእነዚህ አይሁዳውያን ወንዶች ራእይ ሐሰት ነበር። ‘ይወድቃሉ’ ወይም በሌላ አባባል አይሳካላቸውም።

29, 30. (ሀ) ‘የደቡቡ ክንድ’ ከሰሜን ለተሰነዘረበት ጥቃት እጁን የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) የሰሜኑ ንጉሥ ‘በጌጡ ምድር’ ላይ የቆመው እንዴት ነው?

29 የይሖዋ መልአክ በመቀጠል እንደሚከተለው ብሏል:- “የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፣ አፈርንም ይደለድላል፣ [“የወረራ ምሽግ በፍጥነት ይገነባል፣” NW] የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፤ የደቡብም ሠራዊት [“ክንድ፣” NW] የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም። በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፣ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር [“በጌጧ ምድር፣” NW] ይቆማል፣ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል።”—ዳንኤል 11:15, 16

30 በቶሌሚ አምስተኛ ሥር የነበረው የጦር ሠራዊት ወይም ‘የደቡብ ክንድ’ ከሰሜን ለተሰነዘረበት ጥቃት እጁን ሰጠ። ሳልሳዊ አንታይከስ በፕኔዝ (ፊልጶስ ቂሣርያ) የግብጹን ጄኔራል ስኮፓስን ‘ከተመረጡ’ 10,000 ወታደሮች ጋር እየነዳ ‘ወደ ተመሸገችው ከተማ’ ወደ ሲዶና ወሰዳቸው። በዚያም ሳልሳዊ አንታይከስ በ198 ከዘአበ ‘በፍጥነት በገነባው የከበባ ምሽግ’ የወደብ ከተማ የሆነችውን ፊኒሺየን ያዛት። የግብጹ የደቡብ ንጉሥ ኃይሎች በፊቱ ሊቆሙ ስላልቻሉ ‘እንደ ፈቃዱ አድርጓል።’ ከዚያም ሳልሳዊ አንታይከስ ‘የጌጡ ምድር’ ማለትም የይሁዳ መዲና በሆነችው በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። በ198 ከዘአበ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ በግብጹ የደቡብ ንጉሥ ሥር መሆናቸው ቀርቶ በሶርያዊው የሰሜን ንጉሥ እጅ ወደቁ። የሰሜን ንጉሥ የሆነው ሳልሳዊ አንታይከስም ‘በጌጡ ምድር ላይ ቆመ።’ ለሚቃወሙት አይሁዳውያንና ግብጻውያን ሁሉ ‘በእጁ ውስጥ ጥፋት’ ነበር። ይህ የሰሜን ንጉሥ እንደ ፈቃዱ እያደረገ የሚቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ነው?

ሮም ጀብደኛውን ንጉሥ ገታች

31, 32. የሰሜኑ ንጉሥ ከደቡቡ ንጉሥ ጋር ‘አንድነት’ ለመፍጠር የተገደደው ለምንድን ነበር?

31 የይሖዋ መልአክ የሚከተለውን መልስ ይሰጠናል:- “[የሰሜኑ ንጉሥ] ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፣ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፤ እርስዋም አትጸናም፤ ለእርሱም አትሆንም።”—ዳንኤል 11:17

32 የሰሜኑ ንጉሥ ሳልሳዊ አንታይከስ ግብጽን ‘በመንግሥቱ ኃይል’ ለመቆጣጠር “ፊቱን ያቀናል።” ይሁን እንጂ ከደቡቡ ንጉሥ ቶሌሚ አምስተኛ ጋር ‘አንድነት’ ለመፍጠር ተስማሙ። ሮም የጠየቀቻቸው ነገሮች ሳልሳዊ አንታይከስ ሐሳቡን እንዲቀይር አድርገውታል። እርሱና የመቄዶንያው ንጉሥ ፊሊፕ አምስተኛ በወጣቱ የግብጽ ንጉሥ ላይ ለመዝመትና ግዛቱን ለመንጠቅ ሕብረት በፈጠሩ ጊዜ የቶሌሚ አምስተኛ ሞግዚቶች የሮምን ከለላ ለማግኘት እርዳታ ጠየቁ። ሮም ጡንቻዋን በማሳየት ይህን አጋጣሚ የገናናነቷን አድማስ ለማስፋት ተጠቅማበታለች።

33. (ሀ) በሳልሳዊ አንታይከስና በቶሌሚ አምስተኛ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ምን ነበር? (ለ) በቀዳማዊት ክሊዮፓትራና በቶሌሚ አምስተኛ መካከል የተመሠረተው ጋብቻ ዓላማው ምን ነበር? ግቡን ሳይመታ የቀረውስ ለምንድን ነው?

33 ሳልሳዊ አንታይከስ በሮም አስገዳጅነት ከደቡቡ ንጉሥ ጋር የሰላም ስምምነት አደረገ። ሳልሳዊ አንታይከስ እንደ ሮም ጥያቄ ድል የተደረጉትን ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ከማስረከብ ይልቅ ‘ሴት ልጁን’ ቀዳማዊት ክሊዮፓትራን ለቶሌሚ አምስተኛ በመዳር ለይስሙላ ያክል ክልሎቹን ለማዛወር አቀደ። ‘ጌጥ ምድር’ የሆነችውን ይሁዳን የሚጨምረው ክልል እንደ ጥሎሽ ሆኖ መሰጠት ነበረበት። ይሁን እንጂ በ193 ከዘአበ ጋብቻው ሲፈጸም የሶርያው ንጉሥ እነዚህን ክፍለ ግዛቶች ለቶሌሚ አምስተኛ ሳይሰጥ ቀረ። ይህ ግብጽ ለሶርያ እንድትገዛ ለማድረግ የታቀደ ፖለቲካዊ ጋብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ቀዳማዊት ክሊዮፓትራ ‘የእርሱ ሆና ስላልቀጠለችና’ ከባሏ ጋር ስለወገነች ውጥኑ አልተሳካለትም። በሳልሳዊ አንታይከስና በሮማውያኑ መካከል ጦርነት በፈነዳ ጊዜ ግብጽ ከሮም ጎን ተሰልፋለች።

34, 35. (ሀ) የሰሜኑ ንጉሥ ፊቱን ያዞረው ወደ የትኞቹ ‘የባሕር ዳርቻዎች’ ነው? (ለ) ሮም የሰሜኑን ንጉሥ “ስድብ” ወደ ፍጻሜው ያመጣችው እንዴት ነው? (ሐ) ሳልሳዊ አንታይከስ የሞተው እንዴት ነው? ቀጣዩ የሰሜን ንጉሥስ ማን ነበር?

34 መልአኩ የሰሜኑ ንጉሥ ስለገጠመው ሽንፈት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ከዚህም በኋላ [ሳልሳዊ አንታይከስ ] ፊቱን ወደ ባሕር ዳርቻዎች ይመልሳል፣ ብዙዎችንም ይማርካል፤ አንድ አለቃ [ሮም] ግን ስድቡን [የሳልሳዊ አንታይከስን ስድብ] ለራሱ ሲል ይሽራል፣ ስድቡንም [የሳልሳዊ አንታይከስን] ያስቀራል። እርሱም [ሮም] ስድቡን በራሱ ላይ ይመልስበታል። [ሳልሳዊ አንታይከስ] ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አንባዎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፣ አይገኝምም።”—ዳንኤል 11:18, 19 NW

35 ‘የባሕር ዳርቻዎች’ የተባሉት መቄዶንያ፣ ግሪክና ትንሿ እስያ ናቸው። በ192 ከዘአበ በግሪክ ጦርነት በመፈንዳቱ ሳልሳዊ አንታይከስ ወደዚያው ለመሄድ ተነሣሣ። የሶርያው ንጉሥ በዚያ አካባቢ ተጨማሪ ግዛት ለመያዝ ያደረገው ሙከራ ያበሳጫት ሮም በይፋ ጦርነት አወጀችበት። በተርሞፕሊ በሮማውያኑ ድል ተነሣ። በ190 ከዘአበ በማግኔዣ በተደረገው ውጊያ ከተሸነፈ በኋላ በግሪክ፣ በትንሿ እስያና ከታውሩስ ተራሮች በስተ ምዕራብ ስላለው ነገር ማሰብን በሚመለከት እርሙን ማውጣት ነበረበት። ሮም ከፍተኛ ግብር በመጫን በሶርያው የሰሜን ንጉሥ ላይ የበላይነቷን አረጋገጠች። ከግሪክና ከትንሿ እስያ የተባረረውና ሁሉንም ሠራዊቱን ለማለት ይቻላል ያጣው ሳልሳዊ አንታይከስ ‘ፊቱን ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች’ መለሰ። ሮማውያን ‘በእነርሱ ላይ የሰነዘረውን ስድብ አዙረው ለራሱ እንዲሆን አድርገዋል።’ ሳልሳዊ አንታይከስ በ187 ከዘአበ በፋርስ ኤልማስ የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ሊዘርፍ ሲሞክር ተገድሏል። በዚህ መንገድ በሞት ‘ሲወድቅ’ ልጁ ሰሉከስ አራተኛ ቀጣዩ የሰሜን ንጉሥ በመሆን ተክቶታል።

ሽኩቻው ቀጠለ

36. (ሀ) የደቡብ ንጉሥ ትግሉን ለመቀጠል የሞከረው እንዴት ነው? ምንስ ገጠመው? (ለ) ሰሉከስ አራተኛ የወደቀው እንዴት ነው? እርሱንስ የተካው ማን ነበር?

36 የደቡብ ንጉሥ የሆነው ቶሌሚ አምስተኛ ለክሊዮፓትራ እንደ ጥሎሽ ሆኖ ለእርሱ መሰጠት የነበረበትን ክፍለ ግዛት ለማግኘት ቢሞክርም በመርዝ በመገደሉ ጥረቱ ዳር አልደረሰም። በእርሱ ፋንታ የተነሳው ቶሌሚ ስድስተኛ ነበር። ስለ ሰሉከስ አራተኛስ ምን ማለት ይቻላል? ለሮም መክፈል የነበረበትን ከባድ ግብር ለመክፈል ገንዘብ ያስፈልገው ስለነበር የግምጃ ቤት ኃላፊ የሆነው ሄሌዎዶረስ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውድ የሆኑ ንብረቶችን እንዲያመጣ ልኮት ነበር። ሄሌዎዶረስ የሰሉከስ አራተኛን ሥልጣን በመመኘት ሰሉከስን ገደለው። ይሁን እንጂ የጴርጋሞኑ ንጉሥ ዩመኔዝና ወንድሙ አታለስ የሟቹን ንጉሥ ወንድም አንታይከስ አራተኛን ሥልጣን ላይ አወጡት።

37. (ሀ) አንታይከስ አራተኛ ከይሖዋ ይበልጥ ኃያል እንደሆነ ለማሳየት የሞከረው እንዴት ነው? (ለ) አንታይከስ አራተኛ፣ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ የወሰደው እርምጃ ወደ ምን አምርቷል?

37 አዲሱ የሰሜን ንጉሥ አንታይከስ አራተኛ የይሖዋን የአምልኮ ዝግጅት ለማጥፋት በመፈለጉ ከአምላክ በላይ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል። ይሖዋን በመዳፈር በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለዙስ ወይም ለጁፒተር አገልግሎት እንዲውል አደረገ። በታኅሣሥ 167 ከዘአበ አንድ የአረማውያን መሠዊያ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚገኘውና ለይሖዋ በየዕለቱ የሚቃጠል መሥዋዕት ይቀርብበት በነበረው ታላቅ መሠዊያ አናት ላይ ተተከለ። ከአሥር ቀናት በኋላ በአረማውያኑ መሠዊያ ላይ ለዙስ መሥዋዕት እንዲቀርብ ተደረገ። ይህ ርኩሰት አይሁዶች በመቃብያን አመራር ሥር ሆነው ለዓመፅ እንዲነሱ አድርጓቸዋል። አንታይከስ አራተኛ ለሦስት ዓመታት ያህል ተዋጋቸው። በ164 ከዘአበ በርኩሰት ድርጊቱ ዓመታዊ በዓል ወቅት ጁዳ መቃብ ቤተ መቅደሱ በድጋሚ ለይሖዋ አገልግሎት እንዲወሰን ያደረገ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ለአምላክ አገልግሎት መወሰኑ የሚከበርበትን የሃኑካ በዓል አቋቋመ።—ዮሐንስ 10:22 NW

38. የመቃብያን አገዛዝ ወደ ፍጻሜው የመጣው እንዴት ነው?

38 መቃብያን በ161 ከዘአበ ከሮም ጋር ስምምነት አድርገው ሳይሆን አይቀርም በ104 ከዘአበ መንግሥት መሠረቱ። ይሁን እንጂ በእነርሱና በሶርያው የሰሜኑ ንጉሥ መካከል ያለው ግጭት ቀጥሎ ነበር። በመጨረሻም ሮም ጣልቃ እንድትገባ ተጠየቀች። የሮማው ጄኔራል ኒየስ ፖምፒ ከሦስት ወር ከበባ በኋላ ኢየሩሳሌምን በ63 ከዘአበ ላይ ጠቀለላት። በ39 ከዘአበ የሮማ ሴኔት ኤዶማዊውን ሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ሄሮድስ በ37 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ሲቆጣጠር የመቃብያን አገዛዝ አከተመ።

39. ዳንኤል 11:1-19⁠ን በመመርመርህ የተጠቀምከው እንዴት ነው?

39 እርስ በርሳቸው የሚሻኮቱትን ሁለት ነገሥታት በሚመለከት የተነገረው የትንቢቱ የመጀመሪያ ክፍል በዝርዝር ፍጻሜውን እንዳገኘ መመልከት እንዴት የሚያስደንቅ ነው! መልእክቱ ለዳንኤል ከተነገረ ከ500 ዓመታት በኋላ የተፈጸመውን ታሪክ መመርመርና የሰሜንና የደቡብ ንጉሥ በመሆን ሚና የተጫወቱትን ነገሥታት ለይቶ ማወቅ መቻል በእርግጥም እንዴት የሚመስጥ ነገር ነው! ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንዲሁም በእኛ ዘመን በእነዚህ ሁለት ነገሥታት መካከል የሚደረገው ሽኩቻ በቀጠለ መጠን ፖለቲካዊ ማንነታቸውም እንዲሁ ይቀያየራል። ታሪካዊ ክንውኖችን ልብ ከሚመስጡት የዚህ ትንቢት ዝርዝር ጉዳዮች ጋር በማዛመድ የእነዚህን ሁለት ተጻራሪ ነገሥታት ማንነት ማወቅ እንችላለን።

ምን አስተውለሃል?

• ከሄለናዊ መንግሥታቱ የወጡት ሁለት የጠንካራ መንግሥታት መሥመሮች የትኞቹ ናቸው? ነገሥታቱስ ምን ዓይነት ትግል ጀምረዋል?

• በ⁠ዳንኤል 11:6 ላይ በተነገረው መሠረት ሁለቱ ነገሥታት ‘የጋራ ስምምነት ያደረጉት’ እንዴት ነው?

• ቀጥሎ በተዘረዘሩት ነገሥታት መካከል ቅራኔው የቀጠለው እንዴት ነው?

በዳግማዊ ሰሉከስና በሳልሳዊ ቶሌሚ (ዳንኤል 11:7-9)

በሳልሳዊ አንታይከስና በቶሌሚ አራተኛ (ዳንኤል 11:10-12)

በሳልሳዊ አንታይከስና በቶሌሚ አምስተኛ (ዳንኤል 11:13-16)

• በቀዳማዊት ክሊዮፓትራና በቶሌሚ አምስተኛ መካከል የተፈጸመው ጋብቻ ዓላማው ምን ነበር? ግቡን ሳይመታ የቀረውስ ለምንድን ነው (ዳንኤል 11:17-19)?

ዳንኤል 11:1-19⁠ን በትኩረት መከታተልህ የጠቀመህ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 228 ላይ የሚገኝ ቻርት/ሥዕል]

በ⁠ዳንኤል 11:5-19 ላይ የተጠቀሱት ነገሥታት

የሰሜን ንጉሥ የደቡብ ንጉሥ

ዳንኤል 11:5 ቀዳማዊ ሰሉከስ ቀዳማዊ ቶሌሚ

ዳንኤል 11:6 ዳግማዊ አንታይከስ ዳግማዊ ቶሌሚ

ዳንኤል 11:7-9 ዳግማዊ ሰሉከስ ሳልሳዊ ቶሌሚ

ዳንኤል 11:10-12 ሳልሳዊ አንታይከስ ቶሌሚ አራተኛ

ዳንኤል 11:13-19 ሳልሳዊ አንታይከስ ቶሌሚ አምስተኛ

ወራሽ:-

ወራሾች:- ቶሌሚ ስድስተኛ

ሰሉከስ አራተኛ እንዲሁም

አንታይከስ አራተኛ

[ሥዕል]

የዳግማዊ ቶሌሚንና የባለቤቱን ምስል የያዘ ሳንቲም

[ሥዕል]

ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር

[ሥዕል]

ሳልሳዊ አንታይከስ

[ሥዕል]

ቶሌሚ ስድስተኛ

[ሥዕል]

ሳልሳዊ ቶሌሚና ወራሾቹ በላይኛው ግብጽ ባለችው ኢድፉ ይህን የሆረስ ቤተ መቅደስ ገንብተዋል

[በገጽ 216 እና 217 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

“የሰሜን ንጉሥ” እና “የደቡብ ንጉሥ” የሚሉት ስያሜዎች ከዳንኤል ሕዝብ በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ ያሉትን ነገሥታት የሚያመለክቱ ናቸው

መቄዶንያ

ግሪክ

ትንሿ እስያ

እስራኤል

ሊቢያ

ግብጽ

ኢትዮጵያ

ሶርያ

ባቢሎን

የአረብ ምድር

[ሥዕል]

ዳግማዊ ቶሌሚ

[ሥዕል]

ታላቁ አንታይከስ

[ሥዕል]

ታላቁ አንታይከስ ያወጣውን የመንግሥት ድንጋጌ የያዘ ጥርብ ድንጋይ

[ሥዕል]

የቶሌሚ አምስተኛን ምስል የሚያሳይ ሳንቲም

[ሥዕል]

በካርናክ ግብጽ የሚገኘው የሳልሳዊ ቶሌሚ በር

[በገጽ 210 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 215 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር

[በገጽ 218 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀዳማዊ ቶሌሚ