በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍጻሜው ዘመን ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎች ለይቶ ማወቅ

በፍጻሜው ዘመን ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎች ለይቶ ማወቅ

ምዕራፍ አሥራ ሰባት

በፍጻሜው ዘመን ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎች ለይቶ ማወቅ

1. በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 7 መሠረት በዘመናችን የሚኖር ምንም የመከላከል አቅም የሌለው አንድ አነስተኛ የሰዎች ቡድን ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት ነበር?

አንድ አነስተኛ የሆነና ምንም የመከላከል አቅም የሌለው የሰዎች ቡድን ብርቱ ከሆነ የዓለም ኃይል ከባድ ጥቃት ይሰነዘርበታል። ቡድኑ ለጥቃቱ አልተበገረም፤ እንዲያውም በአዲስ መልክ መንቀሳቀስ ጀመረ። ይህን ማድረግ የቻሉት ግን በራሳቸው ብርታት ሳይሆን ይሖዋ አምላክ ሞገሱን ስለሰጣቸው ነበር። በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተከናወኑት እነዚህ ክስተቶች በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ በትንቢት ተነግረዋል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ይኸው የዳንኤል መጽሐፍ 7ኛ ምዕራፍ ‘የልዑሉ’ የይሖዋ አምላክ ‘ቅዱሳን’ በማለት ይጠራቸዋል። እንዲሁም እነዚህ ግለሰቦች በመጨረሻ በመሲሐዊው መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች እንደሚሆኑ ይገልጻል!—ዳንኤል 7:13, 14, 18, 21, 22, 25-27

2. (ሀ) ይሖዋ ስለ ቅቡዓን አገልጋዮቹ ምን ይሰማዋል? (ለ) በእነዚህ ወቅቶች ጥበብ የሚሆነው ምን ዓይነት ጎዳና መከተል ነው?

2 በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ እንደተመለከትነው የሰሜን ንጉሥ ወደ ፍጻሜው የሚመጣው በእነዚህ የታመኑ ሰዎች የተረጋጋ መንፈሳዊ ምድር ላይ ስጋት እንዲያጠላ ሲያደርግ ነው። (ዳንኤል 11:45፤ ከ⁠ሕዝቅኤል 38:18-23 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ይሖዋ የታመኑ ቅቡዓኑን በሚገባ ይጠብቃቸዋል። መዝሙር 105:14, 15 “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፣ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፣ . . . ስለ እነርሱም [ይሖዋ] ነገሥታትን ገሠጸ” ይለናል። ታዲያ ሁከት በሞላበት በዛሬው ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የመጣው “እጅግ ብዙ ሰዎች” በተቻለ መጠን ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር በቅርብ ተባብረው መሥራታቸው ጥበብ ነው ቢባል አትስማማም? (ራእይ 7:9፤ ዘካርያስ 8:23) ኢየሱስ ክርስቶስም በግ መሰል ሰዎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ማለትም ቅቡዓኑን የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች በሥራቸው በመደገፍ ከእነርሱ ጋር እንዲተባበሩ መክሯል።—ማቴዎስ 25:31-46፤ ገላትያ 3:29

3. (ሀ) የተቀቡትን የኢየሱስ ተከታዮች ማግኘትና ከእነርሱም ጋር በቅርብ መተባበር ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ዳንኤል ምዕራፍ 12 በዚህ ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው?

3 ይሁን እንጂ የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን በቅቡዓኑ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል። የሐሰት ሃይማኖትን በማራመድ መላውን ዓለም በአስመሳይ ክርስትና ለመሙላት ያደረገው ጥረት ሰምሮለታል። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች ተታልለዋል። ሌሎች ደግሞ እውነተኛውን ሃይማኖት የሚወክሉ ሰዎች ማግኘት ይቻላል የሚለው ተስፋቸው ተሟጥጦባቸዋል። (ማቴዎስ 7:15, 21-23፤ ራእይ 12:9, 17) ይህ ዓለም እምነታችንን ለመሸርሸር ያላሰለሰ ጥረት ስለሚያደርግ ‘ታናሹን መንጋ’ ያገኙትና ከእነርሱ ጋር የሚተባበሩትም ቢሆኑ እምነታቸውን ለመጠበቅ መጋደል ይኖርባቸዋል። (ሉቃስ 12:32) አንተስ? ‘የልዑሉን ቅዱሳን’ አግኝተሃቸዋል? ከእነርሱስ ጋር እየተባበርህ ነው? አንተ ያገኘሃቸው ሰዎች በትክክል አምላክ የመረጣቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ምን እንደሆኑ ተገንዝበሃል? እንዲህ ያሉት ማስረጃዎች እምነትህን ሊያጠናክሩልህ ይችላሉ። ሌሎች ሰዎችም ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ የሚንጸባረቀው ሃይማኖታዊ ግራ መጋባት ግልጽ ሆኖ እንዲታያቸው ለመርዳት የሚያስችል ብቃት ታገኛለህ። ዳንኤል ምዕራፍ 12 በዚህ ሕይወት ሰጭ እውቀት የተሞላ ነው።

ታላቁ አለቃ ለእርምጃ ተንቀሳቀሰ

4. (ሀ) ዳንኤል 12:1 ስለ ሚካኤል የትኞቹን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ይተነብያል? (ለ) በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ስለ ንጉሠ ነገሥታት ‘መነሣት’ ሲናገር በአብዛኛው ምን ማለቱ ነው?

4 ዳንኤል 12:1 [NW] እንዲህ ይላል:- “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚነሣው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይቆማል።” ይህ ቁጥር ስለ ሚካኤል የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች ለይቶ በመጥቀስ ይተነብያል:- አንደኛ ‘መነሣቱ’ ሲሆን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚከናወንን ሁኔታ ያመለክታል። ሁለተኛው ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የሚፈጸምን ክንውን የሚያመለክተው ‘መቆሙ’ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ሚካኤል ‘[ለዳንኤል ሕዝብ] ልጆች የሚነሣበትን’ ጊዜ ማወቅ ይኖርብናል። ሚካኤል የሚለው ስም ኢየሱስ ሰማያዊ ገዥ በመሆን የሚጫወተውን ሚና የሚገልጽ ስያሜ መሆኑን አስታውስ። ስለ ‘መነሣቱ’ መጠቀሱ ይህ መግለጫ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ቦታዎች ላይ እንዴት እንደተሠራበት ያስታውሰናል። ብዙውን ጊዜ አንድ ንጉሥ ቤተ መንግሥታዊ ሥልጣኑን መያዙን የሚጠቁም ነው።—ዳንኤል 11:2-4, 7, 20, 21

5, 6. (ሀ) ሚካኤል የሚነሣው በየትኛው ወቅት ነው? (ለ) ሚካኤል ‘የሚቆመው’ መቼና እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?

5 እዚህ ላይ መልአኩ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ስለተጠቀሰ ጊዜ እየተናገረ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ይህንን ጊዜ ‘መገኘት’ (በግሪክኛ ፓሩሲያ) በማለት የጠራው ሲሆን በሰማይ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛበት ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 24:37-39) ይህ ጊዜ ‘የመጨረሻ ቀን’ እና ‘የፍጻሜ ዘመን’ ተብሎም ተጠርቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ዳንኤል 12:4, 9) ይህ ጊዜ ከጀመረበት ከ1914 አንስቶ ሚካኤል በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ተነሥቷል።—ከ⁠ኢሳይያስ 11:10፤ ራእይ 12:7-9 ጋር አወዳድር።

6 ይሁን እንጂ ሚካኤል ‘የሚቆመው’ መቼ ነው? ልዩ እርምጃ ለመውሰድ በሚነሳበት ጊዜ ነው። ኢየሱስ ይህንን የሚያደርገው ወደፊት ይሆናል። ራእይ 19:11-16 ኢየሱስ የመላእክትን ጭፍራ በመምራት የአምላክን ጠላቶች የሚያወድም ኃያል መሲሐዊ ንጉሥ መሆኑን በትንቢታዊ ሁኔታ ይገልጻል። ዳንኤል 12:1 እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል።” ክርስቶስ የይሖዋ ዋነኛ ፍርድ አስፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን አስቀድሞ በተነገረለት “ታላቅ መከራ” ወቅት መላውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል።—ማቴዎስ 24:21፤ ኤርምያስ 25:33፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ ራእይ 7:14፤ 16:14, 16

7. (ሀ) የታመኑ ሆነው የተገኙ ሁሉ በመጪው ‘የመከራ ጊዜ’ ምን ተስፋ አላቸው? (ለ) የይሖዋ መጽሐፍ የተባለው ምንድን ነው? በዚያ መጽሐፍ መጻፋችንስ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

7 እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች በዚህ የጨለማ ዘመን ምን ይሆኑ ይሆን? ለዳንኤል የሚከተለው ነገር ተነግሮታል:- “በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።” (ከ⁠ሉቃስ 21:34-36 ጋር አወዳድር።) ይህ መጽሐፍ ምንድን ነው? ይሖዋ ፈቃዱን የሚያደርጉትን ሰዎች እንደሚያስታውሳቸው የሚያመለክት ነው። (ሚልክያስ 3:16፤ ዕብራውያን 6:10) ስማቸው በዚህ የሕይወት መጽሐፍ ላይ የተጻፈ ሰዎች መለኮታዊ ከለላ ስለሚያገኙ በዓለም ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው። በእነርሱ ላይ የሚቃጣ ጎጂ ነገር ሁሉ ሊከሽፍ ይችላል፤ ደግሞም ይከሽፋል። ከዚህ “የመከራ ዘመን” በፊት ሞት ቢቀድማቸው እንኳ በማይሞላው የይሖዋ ዝክር ውስጥ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ይጻፋሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አስታውሶ ያስነሣቸዋል።—ሥራ 24:15፤ ራእይ 20:4-6

ቅዱሳን “ይነቃሉ”

8. ዳንኤል 12:2 ምን አስደሳች ተስፋ ይዟል?

8 በእርግጥም የትንሣኤ ተስፋ እጅግ የሚያጽናና ነው። ዳንኤል 12:2 ስለዚሁ ጉዳይ ሲጠቁም እንዲህ ይላል:- “በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኩሌቶቹም ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና።” (ከ⁠ኢሳይያስ 26:19 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አጠቃላይ ትንሣኤ የተናገረውን ስሜት ቀስቃሽ ተስፋ ያስታውሱን ይሆናል። (ዮሐንስ 5:28, 29) እንዴት የሚያስደስት ተስፋ ነው! እስቲ አስበው፣ ዛሬ ሞተው ያሉት የምታፈቅራቸው ወዳጆችህና የቤተሰብህ አባላት ወደፊት እንደገና የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ! ይሁን እንጂ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ በዋነኛነት የሚናገረው ጥቂት ቀደም ብሎ ፍጻሜውን ስላገኘ የትንሣኤ ዓይነት ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

9. (ሀ) ዳንኤል 12:2 ፍጻሜውን የሚያገኘው በመጨረሻው ዘመን ነው ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ትንቢቱ የሚገልጸው ስለ ምን ዓይነት ትንሣኤ ነው? እንዴትስ እናውቃለን?

9 በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ተመልከት። ቀደም ሲል እንዳየነው የምዕራፍ 12 የመጀመሪያ ቁጥር የሚያመለክተው የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን የመጨረሻ ዘመን ፍጻሜም ነው። እንዲያውም አብዛኛው የምዕራፉ ሐሳብ ፍጻሜውን የሚያገኘው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሳይሆን በፍጻሜው ዘመን ውስጥ ነው። በዚህ ጊዜ የተከናወነ ትንሣኤ ነበርን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ለክርስቶስ የሆኑት” የሚያገኙትን ትንሣኤ አስመልክቶ ሲናገር ‘በመገኘቱ ጊዜ ’ እንደሚሆን ጠቅሷል። ይሁን እንጂ ሰማያዊ ሕይወት አግኝተው ከሞት የተነሱት ሰዎች ያገኙት ‘የማይበሰብስ’ ሕይወት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:23, 52) ከእነርሱ መካከል በ⁠ዳንኤል 12:2 ላይ እንደተገለጸው ‘ለእፍረትና ለዘላለም ጉስቁልና’ የሚነሣ የለም። ሌላ ዓይነት ትንሣኤ ይኖር ይሆን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለትንሣኤ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጥበትም ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል የሕዝቅኤልና የራእይ መጻሕፍት መንፈሳዊ ማንሰራራትን ወይም ትንሣኤን የሚገልጹ ትንቢታዊ መልእክቶች ይዘዋል።—ሕዝቅኤል 37:1-14፤ ራእይ 11:3, 7, 11

10. (ሀ) በፍጻሜው ዘመን ቅቡዓኑ ትንሣኤ ያገኙት በምን መልኩ ነው? (ለ) እንደገና ካንሰራሩት ቅቡዓን መካከል አንዳንዶቹ የነቁት ‘ለእፍረትና ለዘላለም ጉስቁልና’ ነው ማለት የምንችለው እንዴት ነው?

10 በፍጻሜው ዘመን የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች በተመሳሳይ መንገድ በመንፈሳዊ አንሰራርተዋልን? አዎን! በ1918 የነበሩት ጥቂት የታመኑ ክርስቲያን ቀሪዎች በተደራጀ መልክ የሚያከናውኑትን ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያውክ ከባድ ጥቃት ተሠንዝሮባቸው የነበረ መሆኑ ታሪካዊ ሐቅ ነው። በወቅቱ የሚቻል ነገር መስሎ ባይታይም በ1919 በመንፈሳዊ አነጋገር ወደ ሕይወት ተመልሰዋል። እነዚህ እውነታዎች በ⁠ዳንኤል 12:2 ላይ አስቀድሞ ከተሰጠው የትንሣኤ መግለጫ ጋር ይስማማሉ። አንዳንዶች በመንፈሳዊ ‘የነቁት’ በዚህ ጊዜና ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። የሚያሳዝነው ግን በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው የቀጠሉት ሁሉም አይደሉም። አንድ ጊዜ ከነቁ በኋላ መሲሐዊውን ንጉሥ ላለመቀበል የመረጡትና የአምላክን አገልግሎት የተዉት ሰዎች በ⁠ዳንኤል 12:2 ላይ እንደተገለጸው በገዛ እጃቸው ‘እፍረትንና የዘላለምን ጉስቁልና’ አጭደዋል። (ዕብራውያን 6:4-6) ይሁን እንጂ ያገኙትን በመንፈሳዊ የማንሰራራት አጋጣሚ የተጠቀሙበት የታመኑ ቅቡዓን በታማኝነት መሲሐዊውን መንግሥት ደግፈዋል። በመጨረሻም ትንቢቱ እንደሚለው ታማኝነታቸው “ወደ ዘላለም ሕይወት” መርቷቸዋል። ተቃውሞ ሲገጥማቸው የሚያሳዩት መንፈሳዊ ጥንካሬ ዛሬ እነርሱን ለይተን እንድናውቃቸው ይረዳናል።

‘እንደ ከዋክብት ይደምቃሉ’

11. ዛሬ ‘ጥበበኞች’ የተባሉት እነማን ናቸው? እንደ ከዋክብትስ የሚያበሩት በምን መንገድ ነው?

11 የሚቀጥሉት የ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 12 ሁለት ቁጥሮች ‘የልዑሉን ቅዱሳን’ ለይተን እንድናውቅ የሚረዳ ተጨማሪ መረጃ ይሰጡናል። በቁጥር ሦስት ላይ መልአኩ ለዳንኤል እንዲህ ብሎታል:- “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፣ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።” ዛሬ እነዚህ ‘ጥበበኞች’ እነማን ናቸው? አሁንም ቢሆን ማስረጃው የሚያረጋግጠው ‘የልዑሉ ቅዱሳን’ መሆናቸውን ነው። ደግሞስ ታላቁ አለቃ ሚካኤል በ1914 ንጉሥ ሆኖ እንደተነሳ ከታመኑት ቅቡዓን ቀሪዎች ሌላ ያስተዋለ ማን አለ? እንዲህ ያሉትን እውነቶች በመስበክ እንዲሁም ክርስቲያናዊ አኗኗርን ተላብሶ በመመላለስ በመንፈሳዊ ድቅድቅ ጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ‘ብርሃን አብሪዎች’ ሆነዋል። (ፊልጵስዩስ 2:15፤ ዮሐንስ 8:12) እነርሱን በሚመለከት ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ተንብዮአል:- “በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።”—ማቴዎስ 13:43

12. (ሀ) በፍጻሜው ዘመን ቅቡዓኑ ‘ብዙዎችን ወደ ጽድቅ በመመለሱ’ ሥራ ሲካፈሉ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) ቅቡዓኑ በሺህ ዓመቱ የክርስቶስ ግዛት ወቅት ብዙዎችን ወደ ጽድቅ የሚመልሱትና ‘እንደ ከዋክብት የሚያበሩት’ እንዴት ነው?

12 ዳንኤል 12:3 በፍጻሜው ዘመን እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምን ሥራ እንደሚጠመዱ ሳይቀር ይነግረናል። ‘ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ ይመልሳሉ።’ ቅቡዓን ቀሪዎቹ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ወራሽ ከሚሆኑት 144,000 ሰዎች መካከል የቀሩትን መሰብሰቡን ተያያዙት። (ሮሜ 8:16, 17፤ ራእይ 7:3, 4) ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” መሰብሰብ ጀመሩ። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ የሆነው በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) እጅግ ብዙ ሰዎችም ቢሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። በመሆኑም በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም አላቸው። ዛሬ በሚልዮኖች የሚቆጠሩት እነዚህ ሰዎች በክፉው ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት የመትረፍ ተስፋቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አብረውት ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት 144,000ዎቹ በምድር ላይ ለሚኖሩት ታዛዥ የሰው ልጆች የቤዛውን ሙሉ ጥቅም በማዳረስ፣ እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ሰዎች ሁሉ ከአዳም የወረሱትን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ እንዲያራግፉ ይረዷቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 7:13, 14፤ 20:5, 6) ቅቡዓኑ ‘ብዙዎችን ወደ ጽድቅ በመመለሱ’ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚሳተፉበት በዚህ ጊዜ ‘እንደ ከዋክብት ያበራሉ።’ በክርስቶስና በተባባሪ ገዥዎቹ በሚመራው ክብራማ ሰማያዊ መስተዳድር ሥር በምድር ላይ የመኖርን ተስፋ ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህን? የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ‘ከቅዱሳኑ’ ጋር መካፈል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ማቴዎስ 24:14

“ይመረምራሉ”

13. በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ቃላት የታተሙትና ምሥጢር ሆነው የቆዩት በምን መልኩ ነው?

13 በ⁠ዳንኤል 10:20 ላይ የጀመረው መልአኩ ለዳንኤል የሚነግረው ነገር በሚከተሉት አስደሳች ቃላት ተደምድሟል:- “ዳንኤል ሆይ፣ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፣ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፣ እውቀትም ይበዛል።” (ዳንኤል 12:4) በእርግጥም ዳንኤል በመንፈስ ተነሳስቶ የጻፈው አብዛኛው ነገር ለሰው ልጅ አእምሮ ምሥጢር ሆኖ ታትሞ ቆይቷል። እንዲያውም ዳንኤል ራሱ “ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም” ሲል ጽፏል። (ዳንኤል 12:8) በዚህ መልኩ የዳንኤል መጽሐፍ ለዘመናት ታትሞ ቆይቷል። ዛሬስ ምን ማለት ይቻላል?

14. (ሀ) ‘በፍጻሜው ዘመን’ ‘ሲመረምሩ’ የነበሩት እነማን ናቸው? ደግሞስ ምኑን? (ለ) ይሖዋ ይህን ‘ምርምር’ እንደባረከው የሚያሳይ ምን ማረጋገጫ አለ?

14 ዛሬ እኛ የምንኖረው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት በተነገረለት ‘የፍጻሜ ዘመን ላይ’ በመሆኑ እድለኞች ነን። በትንቢት በተነገረው መሠረት ብዙ የታመኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ገጾች መርምረዋል። ውጤቱስ? በይሖዋ በረከት እውነተኛ እውቀት በዝቷል። የታመኑት ቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሰው ልጅ በ1914 መንገሡንና በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጹትን አራዊት ማንነት ለማወቅ እንዲሁም ስለ ‘ጥፋት ርኩሰት’ ለማስጠንቀቅ የሚያስችል ማስተዋል በማግኘት መባረካቸው ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። (ዳንኤል 11:31) ይህ የተትረፈረፈ እውቀትም ራሱ ‘የልዑሉን ቅዱሳን ለይቶ ለማወቅ’ የሚያስችል ሌላ ምልክት ነው። ይሁን እንጂ ዳንኤል ተጨማሪ ማስረጃዎችንም ተቀብሏል።

‘ተፈጩ’

15. አሁን አንድ መልአክ ምን ጥያቄ አነሣ? ይህስ ጥያቄ ስለማን ሊያስታውሰን ይችላል?

15 ዳንኤል በመልአክ አማካኝነት የተሰጠውን ይህን መልእክት የተቀበለው ጤግሮስ እየተባለ በሚታወቀው “በታላቁ ወንዝ” በሂዴኬል እንደነበር እናስታውሳለን። (ዳንኤል 10:4) አሁን ደግሞ በዚሁ ቦታ ሦስት መላእክታዊ ፍጥረታት ተመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እኔም ዳንኤል አየሁ፤ እነሆም፣ ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፣ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፣ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር። አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን:- የዚህ ድንቅ ፍጻሜ እስከ መቼ ነው? አለው።” (ዳንኤል 12:5, 6) እዚህ ላይ መልአኩ ያነሳው ጥያቄም ቢሆን ‘የልዑሉን ቅዱሳን’ እንድናስታውስ ያደርገን ይሆናል። ‘በፍጻሜው ዘመን’ መጀመሪያ ላይ ማለትም በ1914 አምላክ የሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ ምን ያህል ይቆይ ይሆን የሚለው ጉዳይ አስጨንቋቸው ነበር። ለጥያቄው የተሰጠው መልስ ይህ ትንቢት በእነርሱ ላይ ያተኮረ መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው።

16. መልአኩ ምን ትንቢት ተናገረ? የትንቢቱ ፍጻሜ እርግጠኛ መሆኑን ጎላ አድርጎ የገለጸውስ እንዴት ነው?

16 የዳንኤል ዘገባ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ:- ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኩሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን [“መፈጨት፣” NW] በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ።” (ዳንኤል 12:7) ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም። መልአኩ ሁለቱንም እጆቹን አንስቶ ምሏል። ምናልባትም ይህን ያደረገው ከሰፊው ወንዝ ማዶ ለማዶ ያሉት ሁለት መላእክት በግልጽ እንዲያዩት ሲል ይሆናል። እግረ መንገዱንም የዚህ ትንቢት ፍጻሜ በምንም ዓይነት የማይሻር መሆኑን ጠንከር አድርጎ ይገልጻል። ይሁንና እነዚህ የተወሰኑ ዘመናት ከመቼ እስከ መቼ ያለውን ጊዜ የሚያመለክቱ ናቸው? መልሱ የምታስበውን ያህል ከባድ አይሆንም።

17. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 7:25፣ 12:7 እና በ⁠ራእይ 11:3, 7, 9 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት ትንቢቶች መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? (ለ) የሦስት ተኩል ዘመናቱ ርዝማኔ ምን ያህል ነው?

17 ይህ ትንቢት ከሌሎች ሁለት ትንቢቶች ጋር አስገራሚ ተመሳሳይነት አለው። አንደኛው ትንቢት በዚህ መጽሐፍ 9ኛ ምዕራፍ ውስጥ የመረመርነውና በ⁠ዳንኤል 7:25 ላይ የሚገኘው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በ⁠ራእይ 11:3, 7, 9 ላይ የሚገኘው ነው። በእነዚህ ትንቢቶች መካከል ያሉትን አንዳንድ ተመሳሳይነቶች ልብ በል። እያንዳንዳቸው ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በፍጻሜው ዘመን ነው። ሁለቱም ትንቢቶች የአምላክ ቅዱሳን አገልጋዮች ስደት እንደሚደርስባቸው አልፎ ተርፎም ለአጭር ጊዜም ቢሆን በይፋ የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ መሥራት እንደማይችሉ የሚገልጹ ናቸው። ትንቢቶቹ የአምላክ አገልጋዮች እንደገና አንሠራርተው ሥራቸውን በመቀጠል በአሳዳጆቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ይገልጻሉ። እንዲሁም እነዚህ ቅቡዓን መከራ የሚቀበሉበትንም የጊዜ ርዝማኔ ይጠቅሳሉ። በ⁠ዳንኤል (7:25 እና 12:7) ላይ የሚገኙት ሁለቱም ትንቢቶች የሚጠቅሱት ስለ ‘ዘመን፣ ዘመናትና የዘመናት እኩሌታ’ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ምሁራን ይህ የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜን እንደሚያመለክት ይስማማሉ። የራእይ መጽሐፍም ይኸንኑ ጊዜ 42 ወር ወይም 1,260 ቀናት በማለት ይጠቅሰዋል። (ራእይ 11:2, 3) ይህም በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተገለጸው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ እያንዳንዳቸው 360 ቀናት ያላቸው ሦስት ሙሉ አንድ ሁለተኛ ዓመት ጊዜን የሚያመለክቱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ 1,260 ቀናት የጀመሩት መቼ ነው?

18. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 12:7 መሠረት የ1,260ዎቹ ቀናት ማብቂያ ምንድን ነው? (ለ) ‘የቅዱሳኑ ኃይል’ በመጨረሻ የተፈጨው መቼ ነው? ይህስ የሆነው እንዴት ነው? (ሐ) እነዚህ 1,260 ቀናት የጀመሩት መቼ ነው? በዚህ ወቅት ቅቡዓኑ ‘ማቅ ለብሰው’ ትንቢት የተናገሩት እንዴት ነው?

18 ትንቢቱ እነዚህ 1,260 ቀናት የሚያበቁት ‘የተቀደሰው ሕዝብ ኃይል መፈጨት ሲያበቃ ነው’ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል። በ1918 አጋማሽ ላይ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን ጄ ኤፍ ራዘርፎርድን ጨምሮ ሌሎች በአመራር ቦታ ላይ የነበሩ የማኅበሩ አባላት በሐሰት ክስ ተወንጅለው የረጅም ጊዜ እስር ተበይኖባቸው ወህኒ ወረዱ። በእርግጥም የአምላክ ቅዱሳን ሥራቸው ‘ሲፈጭ’ ማለትም ኃይላቸው ሲደቅቅ ተመልክተዋል። ከ1918 አጋማሽ ተነሥተን ወደ ኋላ ሦስት ዓመት ተኩል ስንቆጥር ወደ 1914 መጨረሻ ላይ እንደርሳለን። በዚህ ወቅት እፍኝ የማይሞሉት ቅቡዓን ራሳቸውን ለከባድ ስደት እያስታጠቁ ነበር። አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቶና በሥራቸው ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ ነበር። እንዲያውም የ1915 የዓመት ጥቅሳቸው የተመሠረተው ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ባቀረበው “እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ . . . ትችላላችሁን?” በሚለው ጥያቄ ላይ ነበር። (ማቴዎስ 20:22) በራእይ 11:3 ላይ አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው መሠረት ቀጣዩ የ1,260 ቀናት ጊዜ ለቅቡዓኑ የሐዘን ወቅት ነበር። ማቅ ለብሰው ትንቢት የሚናገሩ ያህል ሆኖ ነበር። ስደቱ ይበልጥ እየከፋ ሄደ። አንዳንዶቹ ታሥረዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ሕዝባዊ ዓመፅ ገጥሟቸዋል ሌሎቹም ተሠቃይተዋል። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1916 መሞቱ ብዙዎችን አደናግጧቸው ነበር። ይህ የጨለማ ዘመን የሰባኪ ድርጅት ሆነው ተደራጅተው በነበሩት ቅቡዓን መገደል ከተደመደመ በኋላ የሚቀጥለው ነገር ምን ይሆን?

19. በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ትንቢት ቅቡዓኑ ለረጅም ጊዜ ዝም ብለው እንደማይቆዩ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?

19 በራእይ 11:3, 9, 11 ላይ የሚገኘው ተመሳሳይ ትንቢት እንደሚያሳየው ሁለት ‘ምሥክሮች’ ከተገደሉ በኋላ እንደገና ሕይወት እስኪዘሩ ድረስ አስከሬናቸው ለአጭር ጊዜ ማለትም ለሦስት ቀን ተኩል ያህል ወድቆ ይቆያል። በተመሳሳይም በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘው ትንቢት ቅዱሳኑ ዝም ብለው እንደማይቀሩና ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ይጠቁማል።

‘ጠርተዋል፣ ነጥተዋል፣ ነጥረዋልም’

20. በ⁠ዳንኤል 12:10 መሠረት ቅቡዓኑ ከደረሰባቸው ከባድ መከራ በኋላ ምን በረከቶች ይገኛሉ?

20 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ዳንኤል እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ ያስፍራቸው እንጂ አልተገነዘባቸውም። ቅዱሳኑ ባሳዳጆቻቸው እጅ የሚጠፉ ከሆነ ‘የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድን ነው?’ ብሎ ተገርሞ መሆን አለበት። መልአኩ እንደሚከተለው ሲል መልሶለታል:- “ዳንኤል ሆይ፣ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤ ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል፣ ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፣ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ።” (ዳንኤል 12:8-10) ቅዱሳኑ የተረጋገጠ ተስፋ ነበራቸው! በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ አቋም በማግኘት ይጠራሉ እንጂ አይጠፉም። (ሚልክያስ 3:1-3) ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ያገኙት ማስተዋል በአምላክ ዓይን ንጹሕ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። ክፉዎች ግን መንፈሳዊ ነገሮችን ለመረዳት አሻፈረኝ ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር የሚከናወነው መቼ ነው?

21. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 12:11 ላይ በትንቢት የተገለጸው ጊዜ የሚጀምረው ምን ነገሮች ሲፈጸሙ ነው? (ለ) ‘የዘወትሩ መሥዋዕት’ ምን ነበር? የቀረውስ መቼ ነበር? (በገጽ 298 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

21 ዳንኤል እንደሚከተለው በማለት ተነግሮታል:- “የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፣ የጥፋትም ርኩሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል።” በመሆኑም ይህ ጊዜ የሚጀምረው አንድ ነገር ሲፈጸም ነው። “የዘወትሩ መሥዋዕት” መቅረት ነበረበት። * (ዳንኤል 12:11 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) መልአኩ የትኛውን መሥዋዕት ማለቱ ነው? በምድራዊ ቤተ መቅደስ ስለሚቀርበው የእንስሳ መሥዋዕት መናገሩ አልነበረም። በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም ቆሞ የነበረውም ቤተ መቅደስ ቢሆን ‘የእውነተኛው ነገር’ ማለትም ኢየሱስ በ29 እዘአ ሊቀ ካህናት ሆኖ ብቅ ሲል ወደ ሕልውና የመጣው የታላቁ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ‘ምሳሌ’ ነበር! ‘ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ስለተሠዋ’ የአምላክን ንጹሕ አምልኮ በሚወክለው በዚህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዘወትር የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልግም። (ዕብራውያን 9:24-28) ይሁን እንጂ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ መሥዋዕት ያቀርባሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ [በክርስቶስ] እናቅርብለት።” (ዕብራውያን 13:15) በመሆኑም ይህ የትንቢቱ የመጀመሪያ ሁኔታ ማለትም ‘የዘወትሩ መሥዋዕት መቅረት’ ፍጻሜውን ያገኘው የምሥራቹ ሥራ የቆመ መስሎ በታየበት በ1918 አጋማሽ ላይ ነበር።

22. (ሀ) የጥፋት ‘ርኩሰቱ’ ምንድን ነው? የቆመውስ መቼ ነው? (ለ) በ⁠ዳንኤል 12:11 ላይ በትንቢት የተነገረው ወቅት የሚጀምረው መቼ ነው? የሚያበቃውስ?

22 ይሁን እንጂ ‘የጥፋት ርኩሰት መቆሙ’ ወይም ስለ መተከሉስ ምን ማለት ይቻላል? ስለ ዳንኤል 11:31 ስንወያይ እንዳየነው ይህ ርኩሰት በመጀመሪያ የመንግሥታቱ ቃል ኪዳን ማኅበር የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተብሎ በአዲስ መልክ ብቅ ብሏል። ሁለቱም ቢሆኑ በምድር ላይ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ ብቸኛ ተስፋ እንደሆኑ አድርገው በማስለፈፋቸው ርኩስ ነገር ሆነዋል። በዚህ መንገድ እነዚህ ተቋማት በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የአምላክ መንግሥት መያዝ የሚገባውን ቦታ ይዘዋል! የቃል ኪዳኑ ማኅበር በኦፊሴል የተቋቋመው በጥር 1919 ነበር። በመሆኑም በዚያ ወቅት በ⁠ዳንኤል 12:11 ላይ ተጠቅሰው የሚገኙት ሁለቱም ሁኔታዎች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በመሆኑም 1,290ዎቹ ቀናት የሚጀምሩት በ1919 መጀመሪያ ላይ ሆኖ እስከ 1922 የበልግ ወቅት (በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ) ድረስ ይዘልቃሉ።

23. የአምላክ ቅዱሳን በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ በትንቢት በተነገረላቸው 1,290 ቀናት ውስጥ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ለማግኘት የቻሉት እንዴት ነው?

23 በዚህ ወቅት ቅዱሳኑ ለመጥራትና በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነው ለመታየት ያደረጉት ለውጥ ነበርን? እንዴታ! በመጋቢት 1919 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የቅርብ ረዳቶቹ ከወህኒ ተለቀቁ። ቆይቶም ከተሰነዘረባቸው የሐሰት ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኑ። ሥራቸው ሊያልቅ ይቅርና ገና እንዳልተነካ ስለተገነዘቡ ወዲያውኑ በመስከረም 1919 የሚደረግ አንድ የአውራጃ ስብሰባ በማዘጋጀት ሥራ ተጠመዱ። በዚያው ዓመት የመጠበቂያ ግንብ ተጓዳኝ የሆነ መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ወጣ። በመጀመሪያ ወርቃማው ዘመን የሚል ስያሜ የነበረው ይህ መጽሔት (ዛሬ ንቁ! ተብሏል) የዚህን ዓለም ብልሹነት ያለፍርሃት በማጋለጥና የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ ሆነው እንዲቀጥሉ በመርዳት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ተጓዳኝ ሆኖ ቆይቷል። በትንቢት በተነገሩት 1,290 ቀናት ማብቂያ ላይ ቅዱሳኑ ንጹሕና የተስተካከለ አቋም ለመያዝ የሚያስችላቸውን ብዙ ነገር አድርገው ነበር። ልክ ይህ ጊዜ ባበቃበት ወቅት ማለትም በመስከረም 1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ አንድ የላቀ ግምት የሚሰጠው የአውራጃ ስብሰባ አካሄዱ። ስብሰባው ለስብከቱ ሥራ በእጅጉ አነሳስቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላም ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህ ደግሞ የሚከናወነው ጉልህ ስፍራ ባለው በቀጣዩ ጊዜ ውስጥ ነበር።

የቅዱሳኑ ደስታ

24, 25. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 12:12 ላይ በትንቢት የተነገረለት ጊዜ የትኛው ነው? ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ጊዜ የጀመረውና ያበቃውስ መቼ ነው? (ለ) በ1,335ቱ ቀናት መጀመሪያ ላይ ቅቡዓን ቀሪዎቹ የነበራቸው መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

24 የይሖዋ መልአክ ስለ ቅዱሳኑ የተናገረውን ትንቢት በሚከተሉት ቃላት ደምድሟል:- “የሚታገሥ [“በጉጉት የሚጠባበቅ፣” NW]፣ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው።” (ዳንኤል 12:12) ይህ ጊዜ መቼ እንደሚጀምርም ሆነ መቼ እንደሚያበቃ መልአኩ ምንም የተናገረው ነገር የለም። ነገር ግን ይህ ጊዜ የመጀመሪያውን ጊዜ ተከትሎ ወዲያውኑ እንደጀመረ ታሪክ ይጠቁመናል። እንደዚያ ከሆነ ከ1922 መከር አንስቶ እስከ 1926 የፀደይ ወራት ድረስ (በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ) ይቆያል ማለት ነው። ቅዱሳኑ በዚህ ክፍለ ጊዜ ማብቂያ ላይ ተደስተው ነበርን? አዎን፣ በጣም ወሳኝ የሆነ መንፈሳዊ ደስታ አግኝተዋል።

25 በ1922 ከተደረገው (በገጽ 302 ላይ ከሚታየው) የአውራጃ ስብሰባም በኋላ አንዳንዶቹ የአምላክ ቅዱሳን ያለፈውን ጊዜ ይናፍቁ ነበር። በወቅቱ በስብሰባዎቻቸው ላይ የሚጠቀሙበት መሠረታዊ የማጥኛ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስና ሲ ቲ ራስል ያዘጋጀው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባለው መጽሐፍ ነበር። በወቅቱ በ1925 ትንሣኤ ይጀምርና ምድር ወደ ገነትነት ትመለሳለች የሚል አመለካከት በሰፊው ሰፍኖ ነበር። በመሆኑም ብዙዎቹ የሚያገለግሉት ቁርጥ ያለ ቀን በአእምሮአቸው በመያዝ ነበር። አንዳንዶችም ኩራት ይዟቸው ለሕዝብ በሚደረገው የስብከት ሥራ ለመካፈል እምቢተኞች ሆነው ነበር። ይህ ደስ የሚያሰኝ ነገር አልነበረም።

26. እነዚያ 1,335ቱ ቀናት እየገፉ ሲሄዱ የቅቡዓኑ መንፈሳዊ ሁኔታ የተለወጠው እንዴት ነው?

26 ይሁን እንጂ 1,335ቱ ቀናት እየገፉ ሲሄዱ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እየተለወጡ መጡ። የስብከቱ ሥራ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት እያንዳንዱ ሰው አዘውትሮ በመስክ አገልግሎት የሚካፈልበት ቋሚ ዝግጅት ተደረገ። መጠበቂያ ግንብ በየሳምንቱ የሚጠናበት የስብሰባ ፕሮግራም ተደረገ። የመጋቢት 1,1925 እትም “የብሔሩ መወለድ” የሚል ጭብጥ ያለው ታሪካዊ ርዕስ ይዞ የወጣ ሲሆን የአምላክ ሕዝቦች 1914-19 ባሉት ጊዜያት ምን ነገሮች እንደተከናወኑ እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። ከ1925 በኋላ ቅዱሳኑ ቁርጥ ያለ የቀን ቀጠሮ በአእምሮአቸው ይዘው አምላክን ማገልገላቸው አከተመ። እንዲያውም የይሖዋ ስም መቀደስ ዋነኛውን ቦታ ያዘ። ይህ በጣም ወሳኝ የሆነ እውነት በጥር 1,1926 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ይሖዋን የሚያከብር ማን ይሆን?” በሚል ርዕስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በግንቦት 1926 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ መዳን የተባለው መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ወጥቷል። (ገጽ 302⁠ን ተመልከት።) የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባለውን መጽሐፍ እንዲተኩ ከታሰቡት መካከል አንዱ ይህ መጽሐፍ ነበር። ቅዱሳኑ የኋላውን ጊዜ መናፈቃቸው አበቃ። ከፊታቸው ያለውን ጊዜና ሥራ በትምክህት መጠባበቅ ጀመሩ። በመሆኑም አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው መሠረት የ1,335ቱ ቀናት ማብቂያ ለቅቡዓኑ የደስታ ጊዜ ሆኖላቸዋል።

27. የ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 12⁠ን ይዘት መከለሳችን የይሖዋን ቅቡዓን ማንነት በሚመለከት መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚረዳን እንዴት ነው?

27 እርግጥ በዚህ ነውጥ የበዛበት ጊዜ ውስጥ የጸኑት ሁሉም አልነበሩም። መልአኩ ‘በጉጉት መጠባበቅን’ ጎላ አድርጎ የገለጸው ለዚያ ሳይሆን አይቀርም። የጸኑትና በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩት ሁሉ በእጅጉ ተባርከዋል። የ⁠ዳንኤል 12⁠ን ይዘት መከለሳችን ይህንን ሐሳብ ግልጽ ያደርገዋል። አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው ቅቡዓኑ እንደገና አንሠራርተዋል ወይም በመንፈሳዊ ሁኔታ ትንሣኤ አግኝተዋል። ስለ አምላክ ድንቅ ማስተዋል ስለተሰጣቸው ቃሉን ‘ለመመርመር’ የሚያስችል ኃይል አግኝተዋል፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ዘመናት ያስቆጠረውን ምሥጢር መፍታት ችለዋል። ይሖዋ አጥርቷቸዋል፤ በመንፈሳዊም እንደ ከዋክብት እንዲያበሩ አድርጓቸዋል። ከዚህም የተነሣ ብዙዎችን በይሖዋ አምላክ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ ረድተዋቸዋል።

28, 29. ‘የፍጻሜው ዘመን’ ወደ መደምደሚያው እየተቃረበ ሲሄድ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

28 ‘የልዑሉን ቅዱሳን’ ማንነት ለይተን እንድናውቅ የሚያስችሉን እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች እያሉ እነማን እንደሆኑ ስላላወቅሁ ከእነርሱ ጋር አልተባበርኩም ብሎ እንዴት ሰበብ ማቅረብ ይቻላል? ቁጥራቸው እየቀነሰ ካለው የቅቡዓን ክፍል ጋር ይሖዋን በማገልገል የሚካፈሉትን እጅግ ብዙ ሰዎች ድንቅ በረከቶች ይጠብቋቸዋል። ሁላችንም አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ፍጻሜ በጉጉት መጠባበቅ ይኖርብናል። (ዕንባቆም 2:3) በዚህ በእኛ ዘመን ታላቁ አለቃ ሚካኤል ለአምላክ ሕዝቦች ሲል ከተነሣ አሥርተ ዓመታት ተቆጥረዋል። በቅርቡም በመለኮታዊ አካል የተሾመ ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ እርምጃ ይወስዳል። እርሱ ይህን እርምጃ ሲወስድ እኛ የት እንቆም ይሆን?

29 የዚህ ጥያቄ መልስ ዛሬ ጽኑ አቋም ይዘን ለመኖር በምናደርገው ምርጫ ላይ የተመካ ነው። ‘የፍጻሜው ዘመን’ ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ ይህን ለማድረግ የደረስንበትን ቁርጥ ውሳኔ ለማጽናት የዳንኤልን መጽሐፍ የመጨረሻ ቁጥሮች እንመርምር። በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ በዚህ ቁጥር ላይ ስንወያይ ዳንኤል እንዴት በአምላኩ ፊት እንደቆመና ወደፊትም እንዴት በፊቱ እንደሚቆም እናስተውላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 በግሪክኛው ሰፕቱጀንት ውስጥ “መሥዋዕት” ብቻ ተብሎ ተተርጉሟል።

ምን አስተውለሃል?

• ሚካኤል ‘የተነሣው’ በየትኛው ወቅት ነው? ‘የሚቆመውስ’ መቼና እንዴት ነው?

ዳንኤል 12:2 የሚገልጸው ስለ ምን ዓይነት ትንሣኤ ነው?

• በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ የተጠቀሱት ወቅቶች የጀመሩባቸውንና ያበቁባቸውን ቀኖች ጥቀስ።

በ⁠ዳንኤል 12:7 ላይ የተጠቀሰው ሦስት ተኩል ዘመን?

በ⁠ዳንኤል 12:11 ላይ አስቀድመው የተነገሩት 1,290 ቀናት?

በ⁠ዳንኤል 12:12 ላይ በትንቢት የተነገሩት 1,335 ቀናት?

ዳንኤል ምዕራፍ 12⁠ን በትኩረት መከታተላችን የይሖዋን እውነተኛ አምላኪዎች ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 298 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዘወትሩ መሥዋዕት መቅረት

በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ‘የዘወትሩ መሥዋዕት’ የሚለው መግለጫ አምስት ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። አገልጋዮቹ ዘወትር ለይሖዋ አምላክ የሚያቀርቡትን የምሥጋና መሥዋዕት ማለትም ‘የከንፈሮችን ፍሬ’ የሚያመለክት ነው። (ዕብራውያን 13:15) ይህ መሥዋዕት እንደሚቀር የተነገረው ትንቢት በ⁠ዳንኤል 8:11፣ ዳንኤል 11:31 እና ዳንኤል 12:11 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።

በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች ‘በሰሜኑ ንጉሥና’ ‘በደቡቡ ንጉሥ’ ግዛት ሥር ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። (ዳንኤል 11:14, 15) ‘የዘወትሩ መሥዋዕት’ የቀረው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ገደማ የስብከቱ ሥራ በ1918 አጋማሽ እንደቆመ ያህል በሆነበት ጊዜ ነበር። (ዳንኤል 12:7) በተመሳሳይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ‘የዘወትሩ መሥዋዕት’ በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ለ2,300 ቀናት ያህል ‘ተወስዶ’ ነበር። (ዳንኤል 8:11-14፤ የዚህን መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ተመልከት።) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተለይቶ ባይጠቀስም በናዚ ‘ክንዶች’ አማካኝነትም ለተወሰነ ጊዜ ቀርቶ ነበር።—ዳንኤል 11:31፤ የዚህን መጽሐፍ 15ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

[በገጽ 301 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹ ትንቢታዊ ወቅቶች

ሰባት ዘመናት (2,520 ዓመታት):- ከጥቅምት 607 ከዘአበ እስከ

ዳንኤል 4:16, 25 ጥቅምት 1914 እዘአ

(የመሲሐዊው መንግሥት መቋቋም።

የዚህን መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ ተመልከት።)

ሦስት ዘመን ተኩል ከታኅሣሥ 1914 እስከ ሰኔ 1918

(1,260 ቀናት):- (ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተንገላትተዋል።

ዳንኤል 7:25፤ 12:7 የዚህን መጽሐፍ 9ኛ ምዕራፍ ተመልከት።)

2,300 ማታና ጥዋት:- ከሰኔ 1 ወይም 15, 1938 እስከ

ዳንኤል 8:14 ጥቅምት 8 ወይም 22, 1944

(“እጅግ ብዙ ሰዎች” ብቅ አሉ፣ ቁጥራቸውም እየጨመረ ሄደ።

የዚህን መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ተመልከት።)

70 ሳምንታት (490 ዓመታት):- ከ455 ከዘአበ እስከ 36 እዘአ

ዳንኤል 9:24-27 (የመሲሁ መምጣትና ምድራዊ አገልግሎቱ።

የዚህን መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ

ተመልከት።)

1,290 ቀናት:- ከጥር 1919 እስከ መስከረም 1922

ዳንኤል 12:11 (የቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ

መንቃትና መሻሻል።)

1,335 ቀናት:- ከመስከረም 1922 እስከ ግንቦት 1926

ዳንኤል 12:12 (ለቅቡዓን ክርስቲያኖች የደስታ ወቅት።)

[በገጽ 287 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው የይሖዋ አገልጋዮች በአትላንታ ጆርጂያ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው ወህኒ ቤት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ታስረዋል። ከግራ ወደ ቀኝ:- (የተቀመጡት) ኤ ኤች ማክሚላን፣ ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ፣ ደብልዩ ኢ ቫን አምበርግ፤ (የቆሙት) ጂ ኤች ፊሸር፣ አር ጄ ማርቲን፣ ጂ ዲሴካ፣ ኤፍ ኤች ሮቢንሰን እና ሲ ጄ ዉድዎርዝ

[በገጽ 299 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1919 (ከላይ) እና በ1922 (ከታች) በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ተደርገዋል

[በገጽ 302 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]