በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባላንጣዎቹ ነገሥታት ፍጻሜያቸው ቀርቧል

ባላንጣዎቹ ነገሥታት ፍጻሜያቸው ቀርቧል

ምዕራፍ አሥራ ስድስት

ባላንጣዎቹ ነገሥታት ፍጻሜያቸው ቀርቧል

1, 2. ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ማንነት የተለወጠው እንዴት ነው?

ፈረንሳዊው ፈላስፋና የታሪክ ሰው አሌክሲ ደ ቶክቪል የዩናይትድ ስቴትስንና የሩሲያን ፖለቲካዊ አዝማሚያ በመመልከት በ1835 እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈው ነበር:- “አንደኛው ነፃነትን ሌላው ደግሞ ባርነትን እንደ መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል። . . . ሁለቱም የሚከተሉት ጎዳና የተለያየ [ነው]፤ የሆነ ሆኖ አንድ ቀን ዓለምን ለሁለት ከፍለው ዕጣ ፋንታውን እንዲቆጣጠሩ በአንድ መለኮታዊ ኃይል ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ የተቀመጡ ይመስላል።” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ይህ ትንበያ ምን ደርሶ ይሆን? ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በእርግጥም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የዓለም ዕጣ ፋንታ ፈጽሞ በተለያዩ ሁለት ታላላቅ ኃያላን እጅ የወደቀ ይመስል ነበር። አንደኛው ኃይል የቀድሞዋን ሩሲያ ሌላኛው ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካን መሠረት ያደረገ ነበር።”

2 በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ወቅት ጀርመን የደቡቡ ንጉሥ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ዋነኛ ጠላት የነበረች ሲሆን የሰሜን ንጉሥነትን ቦታ ይዛ ነበር። ይሁን እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለሁለት ተከፈለች። ምዕራብ ጀርመን የደቡብ ንጉሥ አጋር ስትሆን ምሥራቅ ጀርመን ደግሞ ከሌላው ኃያል ወገን ማለትም በሶቪየት ኅብረት ከሚመራው የኮሚኒስቱ ጎራ ጋር ወገነች። ይህ ጎራ ወይም ፖለቲካዊ ኃይል የአንግሎ አሜሪካን ኅብረት በመቃወም የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ተነሣ። በሁለቱ ነገሥታት መካከል ያለውም ቅራኔ ከ1948 እስከ 1989 ድረስ ለዘለቀው ቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት ሆኗል። ቀደም ሲል የጀርመኑ የሰሜን ንጉሥ ‘የተቀደሰውን ቃል ኪዳን ተቃውሞ ነበር።’ (ዳንኤል 11:28, 30) የኮሚኒስቱ ጎራስ ይህን ቃል ኪዳን በሚመለከት ምን ያደርግ ይሆን?

እውነተኛ ክርስቲያኖች ቢወድቁም ይበረታሉ

3, 4. ‘ቃል ኪዳኑን የሚበድሉት’ እነማን ናቸው? ከሰሜኑ ንጉሥ ጋርስ ምን ዓይነት ግንኙነት ነበራቸው?

3 የአምላክ መልአክ “[የሰሜኑም ንጉሥ] ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል” ካለ በኋላ ጨምሮ እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፣ ያደርጋሉም። በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ።”—ዳንኤል 11:32, 33

4 ‘ቃል ኪዳኑን የሚበድሉት’ ክርስቲያን ነን እያሉ በድርጊታቸው የክርስትናን ስም ከሚያጎድፉት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ዎልተር ኮላረስ ሪሊጅን ኢን ዘ ሶቪየት ዩኒየን በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “[በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት] የሶቪየት መንግሥት እናት አገርን ለመከላከል እንዲያስችል አብያተ ክርስቲያናት ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማድረግ ጥሯል።” የሰሜን ንጉሥ የሆነው ኃይል፣ አምላክ የለሽ አቋም የሚያራምድ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላም አብያተ ክርስቲያናቱ ወዳጅነታቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ሞክረዋል። በዚህ መንገድ ሕዝበ ክርስትና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የዚህ ዓለም ክፍል በመሆን በይሖዋ ፊት አጸያፊ ክህደት መሆኗ ታይቷል።—ዮሐንስ 17:16፤ ያዕቆብ 4:4

5, 6. ‘አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ’ የተባሉት እነማን ናቸው? በሰሜኑ ንጉሥ ሥር ምን ዓይነት ሁኔታ አሳልፈዋል?

5 “አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ” እና “ጥበበኛ” ስለተባሉት እውነተኛ ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? በሰሜኑ ንጉሥ ግዛት ሥር የነበሩት ክርስቲያኖች ‘በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች ባግባቡ ይገዙ’ የነበረ ቢሆንም የዓለም ክፍል አልሆኑም። (ሮሜ 13:1፤ ዮሐንስ 18:36) “የቄሣርን ለቄሣር” በማስረከብ በኩል ጠንቃቆች የነበሩ ቢሆንም ‘የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር’ ከመስጠት ወደኋላ አላሉም። (ማቴዎስ 22:21) በዚህም ምክንያት ንጹህ አቋማቸውን ለመጠበቅ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:12

6 ከዚህ የተነሣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ወድቀዋልም፤’ ‘በርትተዋልም።’ እንደ ወደቁ ተደርገው የተገለጹት ከደረሰባቸው ከባድ ስደት የተነሣ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ተገድለዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው በርትተዋል። ልክ እንደ ኢየሱስ ዓለምን አሸንፈዋል። (ዮሐንስ 16:33) ከዚህም በላይ በእስር ቤቶች ወይም በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ቢጣሉም ፈጽሞ ስብከታቸውን አላቆሙም። በዚህ መንገድ ‘ብዙ ሰዎችን አስተምረዋል።’ በሰሜኑ ንጉሥ ቁጥጥር ሥር በነበሩት በአብዛኛዎቹ አገሮች ስደት የነበረ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ጨምሯል። ‘ጥበበኞች’ የተባሉት ሰዎች ላሳዩት ታማኝነት ምስጋና ይግባውና በእነዚህ አገሮች ውስጥ ቁጥሩ እያደገ የሚሄድ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ብቅ ብሏል።—ራእይ 7:9-14

የይሖዋ ሕዝቦች ተፈትነው ጠሩ

7. በሰሜኑ ንጉሥ ሥር የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ጥቂት እርዳታ’ ያገኙት እንዴት ነው?

7 መልአኩ “[የአምላክ ሕዝቦች] በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ” ብሏል። (ዳንኤል 11:34⁠ሀ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የደቡቡ ንጉሥ የተቀዳጀው ድል በተቀናቃኙ ንጉሥ ግዛት ሥር ለነበሩት ክርስቲያኖች በመጠኑም ቢሆን እፎይታ አምጥቶላቸዋል። (ከ⁠ራእይ 12:15, 16 ጋር አወዳድር።) በተተኪው የሰሜን ንጉሥ ሥር መከራ ይደርስባቸው የነበሩትም በተመሳሳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እረፍት እያገኙ መጥተዋል። ብዙ መሪዎች የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ሲቃረብ እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ምንም ስጋት የማይፈጥሩ ወገኖች መሆናቸውን በመገንዘብ ሕጋዊ እውቅና ሰጥተዋቸዋል። የታመኑትን ቅቡዓን ስብከት ተቀብለው ከጎናቸው ከተሰለፉትና ቁጥራቸው እያደገ ከመጣው እጅግ ብዙ ሰዎችም እርዳታ አግኝተዋል።—ማቴዎስ 25:34-40

8. አንዳንዶች ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ‘በግብዝነት’ የተቀላቀሉት እንዴት ነው?

8 በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አምላክን የማገልገል ፍላጎት አለን ይሉ የነበሩት ሁሉ በጥሩ ዝንባሌ የተነሳሱ ነበሩ ማለት አይደለም። መልአኩ “ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ” ብሏል። (ዳንኤል 11:34ለ) የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለእውነት ፍላጎት አሳይተው የነበረ ቢሆንም ለአምላክ ራሳቸውን ለመወሰን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ምሥራቹን የተቀበሉ ይመስሉ የነበሩት ሌሎች ደግሞ ለባለ ሥልጣኖች የሚሰልሉ ነበሩ። ከአንድ አገር የተላከው ሪፖርት እንደሚከተለው ይነበባል:- “ከእነዚህ ይሉኝታ የለሽ ሰዎች መካከል ወደ ጌታ ድርጅት ሾልከው ገብተው ከፍተኛ ቅንዓት ሲያሳዩ የነበሩትና ለከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ እስከመታጨት የደረሱት አንዳንዶች የወጣላቸው ኮሚኒስቶች ነበሩ።”

9. ይሖዋ አንዳንድ የታመኑ ክርስቲያኖች በሰርጎ ገቦች አማካኝነት ‘እንዲወድቁ’ የፈቀደው ለምንድን ነው?

9 መልአኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።” (ዳንኤል 11:35) እነዚህ ሰርጎ ገቦች አንዳንድ የታመኑ ወንድሞች በባለ ሥልጣኖች እጅ እንዲወድቁ አድርገዋል። ይሖዋ እንዲህ ያሉት ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደው ሕዝቦቹን ለማንጠርና ለማጥራት ነው። ኢየሱስ ‘ከተቀበለው መከራ መታዘዝን እንደተማረ’ ሁሉ እነዚህ የታመኑ ሰዎችም በእምነታቸው ላይ ከደረሰው ፈተና ጽናትን ተምረዋል። (ዕብራውያን 5:8፤ ያዕቆብ 1:2, 3፤ ከ⁠ሚልክያስ 3:3 ጋር አወዳድር።) በዚህ መልኩ ‘ነጥረዋል፣ ተጣርተዋል እንዲሁም ነጥተዋል።’

10. ‘እስከ ፍጻሜው ድረስ’ የሚለው መግለጫ ምን ያመለክታል?

10 የይሖዋ ሕዝቦች ‘እስከ ፍጻሜው ድረስ’ መውደቅና መጥራት ነበረባቸው። እርግጥ እስከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ስደት እንደሚደርስባቸው ይጠብቃሉ። ይሁን እንጂ በሰሜኑ ንጉሥ ምክንያት የተከናወነው የአምላክ ሕዝቦች መጥራትና መንጣት ‘እስከ ተወሰነው ጊዜ’ ነበር። በመሆኑም በ⁠ዳንኤል 11:35 ላይ የተጠቀሰው ‘የፍጻሜ ዘመን’ የአምላክ ሕዝቦች ከሰሜኑ ንጉሥ የሚደርስባቸውን ጥቃት ተቋቁመው በመጽናት ሊጠሩ ይገባቸው ከነበረበት ዘመን ፍጻሜ ጋር የሚዛመድ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው መውደቃቸው ይሖዋ በወሰነው ጊዜ አብቅቷል።

ንጉሡ ራሱን ታላቅ ያደርጋል

11. የሰሜኑ ንጉሥ የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚመለከት ያለውን አቋም አስመልክቶ መልአኩ ምን ብሏል?

11 የሰሜኑን ንጉሥ በሚመለከት መልአኩ እንዲህ ሲል ጨምሮ ተናገረ:- “ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፣ [የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት] በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቁጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፣ የተወሰነው ይደረጋልና። የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም።”—ዳንኤል 11:36, 37

12, 13. (ሀ) የሰሜኑ ንጉሥ ‘የአባቶቹን አምላክ’ ቸል ያለው በምን መንገድ ነው? (ለ) የሰሜኑ ንጉሥ ‘ምኞታቸውን’ ያልተመለከተላቸው ‘ሴቶች’ እነማን ናቸው? (ሐ) የሰሜኑ ንጉሥ ያከበረው የትኛውን ‘አምላክ’ ነው?

12 የሰሜኑ ንጉሥ ሕዝበ ክርስትና የምታመልከውን እንደ መለኮታዊ ሥላሴ ያለውን ‘የአባቶቹን አምላክ’ ቸል በማለት እነዚህን ትንቢታዊ ቃላት ፈጽሟል። የኮሚኒስቱ ጎራ ግልጽ የሆነ የአምላክ የለሽነት አቋም አራምዷል። በዚህ መንገድ የሰሜኑ ንጉሥ ‘ራሱን ከሁሉ በላይ ታላቅ በማድረግ’ ራሱን አምላክ አድርጓል። ንጉሡ ‘የሴቶችን ምኞት አይመለከትም’ በተባለው መሠረት እንደፈቃዱ አድርጓል። ሴቶች የተባሉት እንደ ሰሜን ቬትናም ያሉት እንደ ገረድ መጠቀሚያ ያደረጋቸው ለፈቃዱ ተገዥ የነበሩ አገሮች ናቸው።

13 መልአኩ ትንቢቱን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቁና በከበረ ነገር ያከብረዋል።” (ዳንኤል 11:38) እንዲያውም የሰሜኑ ንጉሥ ትምክህቱን የጣለው ዘመናዊ በሆነ በተራቀቀ የጦር ኃይል ማለትም ‘በአምባው አምላክ’ ላይ ነው። እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በዚህ ‘አምላኩ’ መሠዊያ ላይ በማቅረብ መዳን እንዲያስገኝለት ተማጽኖታል።

14. የሰሜኑ ንጉሥ ‘እንዳሻው ያደረገው’ እንዴት ነው?

14 “በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፣ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፣ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል።” (ዳንኤል 11:39) የሰሜኑ ንጉሥ በወታደራዊ ‘ባዕድ አምላኩ’ ታምኖ ያሻውን ‘በማድረግ’ በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ብርቱ ወታደራዊ ኃይል ለመሆን በቅቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የእርሱን ርዕዮተ ዓለም ለደገፉትም የፖለቲካ፣ የገንዘብና አንዳንዴም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥቷል።

በፍጻሜው ዘመን የሚታይ ግፊያ

15. የደቡቡ ንጉሥ ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ‘የተጋፋው’ እንዴት ነው?

15 መልአኩ “በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል [“ይጋፋል፣” NW]” ሲል ለዳንኤል ነግሮታል። (ዳንኤል 11:40ሀ) ‘በፍጻሜው ዘመን’ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜኑን ንጉሥ ‘ተጋፍቶታልን?’ (ዳንኤል 12:4, 9) አዎን፣ ተጋፍቶታል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በወቅቱ የሰሜን ንጉሥ በነበረችው ጀርመን ላይ የተጣለው ቅጣት አዘል የሰላም ስምምነት ለበቀል የሚያነሳሳ ‘የመጋፋት’ እርምጃ ነበር። የደቡቡ ንጉሥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድል ከተቀዳጀ በኋላ አስፈሪውን የኑክሌር ጦር መሣሪያውን በተቀናቃኙ ላይ ከማነጣጠሩም ሌላ እርሱን የሚቃወም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) የተባለ ኃያል ወታደራዊ ኅብረት አደራጅቷል። የኔቶን ተግባር በተመለከተ አንድ እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ለአውሮፓ ሰላም አስጊ እንደሆነች ተደርጋ የምትታሰበውን የሶቪየት ኅብረትን መስፋፋት ለመግታት የሚያገለግል ዋነኛ መሣሪያ ነው። ለ40 ዓመታት ያህል ተልእኮውን በተሳካ መንገድ አከናውኗል።” የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን እየቀጠለ ሲሄድ የደቡቡ ንጉሥ ‘ግፊያ’ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስለላ ማካሄድን እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ትንኮሳን የሚጨምር ሆኗል።

16. የሰሜኑ ንጉሥ ለደቡቡ ንጉሥ ግፊያ ምን ምላሽ ሰጠ?

16 የሰሜኑ ንጉሥ ምላሽ ምን ነበር? “የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፣ ይጎርፍማል፣ ያልፍማል።” (ዳንኤል 11:40ለ) የሰሜኑ ንጉሥ መስፋፋት በመጨረሻዎቹ ቀናት በጉልህ ተንጸባርቋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ “ንጉሥ” አዋሳኝ ወደሆኑት የአካባቢው አገሮች ዘምቷል። በጦርነቱ ማብቂያ ላይ ደግሞ በእርሱ ፋንታ የተነሣው “ንጉሥ” ጠንካራ ግዛት ገንብቷል። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሰሜን ንጉሥ ተቀናቃኙን በእጅ አዙር ጦርነትና በአፍሪካ፣ በእስያ እንዲሁም በላቲን አሜሪካ በተደረጉ ዓመፆች አማካኝነት ተዋግቶታል። በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ስደት በማድረስ ሥራቸውን ቢገድበውም ጨርሶ ማስቆም ሳይችል ቀርቷል። የወሰዳቸው ወታደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎች በርካታ አገሮችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ አስችሎታል። መልአኩም ስለዚሁ ጉዳይ በትክክል ተንብዮአል:- “ወደ መልካሚቱም [“ጌጧ፣” NW] ምድር [ወደ ይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ይዞታ] ይገባል፣ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ።”—ዳንኤል 11:41ሀ

17. የሰሜኑ ንጉሥ የመስፋፋት እንቅስቃሴ ተገድቦ ነበር ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

17 የሆነ ሆኖ የሰሜኑ ንጉሥ ዓለምን በሙሉ ድል አድርጎ አልተቆጣጠረም። መልአኩ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ።” (ዳንኤል 11:41ለ) በጥንት ዘመን ኤዶም፣ ሞዓብ እና አሞን በግብጹ የደቡብ ንጉሥና በሶርያው የሰሜን ንጉሥ መካከል ባለው ቦታ ሰፍረው የሚገኙ ወገኖች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ያነጣጠረባቸውን ነገር ግን በእርሱ ተጽዕኖ ሥር እንዲንበረከኩ ሊያደርጋቸው ያልቻላቸውን ብሔራትና ድርጅቶች ሊያመለክቱ ይችላሉ።

ግብጽ አላመለጠችም

18, 19. የደቡቡ ንጉሥ በተቀናቃኙ ተጽዕኖ የተነካው በምን መንገድ ነው?

18 የይሖዋ መልአክ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “[የሰሜኑ ንጉሥ] እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፣ የግብጽም ምድር አታመልጥም። በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፣ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል።” (ዳንኤል 11:42, 43) “ግብጽ” ማለትም የደቡብ ንጉሥ እንኳ ሳይቀር የሰሜኑ ንጉሥ የመስፋፋት ፖሊሲ ባሳደረው ተጽእኖ ተነክቷል። ለምሳሌ ያህል የደቡቡ ንጉሥ በቬትናም ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ስለ ‘ልብያውያንና ኢትዮጵያውያንስ’ ምን ማለት ይቻላል? የጥንቷ ግብጽ አጎራባች የነበሩት እነዚህ አገሮች ከመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር የዛሬዋ “ግብጽ” (የደቡብ ንጉሥ) አጎራባቾችን ሊያመለክቱ ይችላሉ። እነዚህ አገሮች የሰሜኑን ንጉሥ ጎዳና ‘የተከተሉባቸው’ ጊዜያት ነበሩ።

19 የሰሜን ንጉሥ ‘በከበረው የግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ’ ሰልጥኗልን? በእርግጥም በደቡብ ንጉሥ የፋይናንስ አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። የደቡቡ ንጉሥ ተቀናቃኙን በመፍራት ግዙፍ ሠራዊት፣ የባሕር ኃይል እና የአየር ኃይል ለመገንባት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አፍስሷል። በዚህ መልኩ የሰሜኑ ንጉሥ በደቡቡ ንጉሥ የሀብት አጠቃቀም ላይ ‘ሰልጥኖ’ ወይም ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር ማለት ነው።

የመጨረሻው ዘመቻ

20. መልአኩ የሰሜኑ ንጉሥ የሚያደርገውን የመጨረሻ ዘመቻ የገለጸው እንዴት ነው?

20 በሰሜኑና በደቡቡ ንጉሥ መካከል የሚደረጉት ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ሌላ ዓይነት ሽኩቻዎች ሁሉ የሚያበቁበት ጊዜ ቅርብ ነው። መልአኩ ገና ወደፊት ስለሚፈጠረው ቅራኔ ዝርዝር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “[የሰሜኑን ንጉሥ] ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱሱ ተራራ [“በታላቁ ባሕርና በጌጡ ቅዱስ ተራራ፣” NW] መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፣ ማንም አይረዳውም።”—ዳንኤል 11:44, 45

21. ስለ ሰሜኑ ንጉሥ ምን ገና ወደፊት የሚገለጥ ነገር አለ?

21 በታኅሣሥ 1991 ሶቪየት ኅብረት ስትበታተን የሰሜኑ ንጉሥ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ዳንኤል 11:44, 45 ፍጻሜውን ሲያገኝ የሰሜን ንጉሥ የሚሆነው ማን ይሆን? የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ክፍል ከነበሩት አገሮች መካከል አንዱ የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ ይል ይሆን? ወይስ እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው ማንነቱን ቀይሮ ብቅ ይላል? ተጨማሪ ብሔራት የኑክሌር መሣሪያዎችን መሥራታቸው ሌላ የጦር መሣሪያ እሽቅድድም እንዲጀመር ምክንያት ሆኖ በዚህ ንጉሥ ማንነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖር ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱን የሚሰጠን ጊዜ ብቻ ይሆናል። መልሱን ለመገመት አለመሞከራችን ጥበብ ነው። የሰሜን ንጉሥ የመጨረሻውን ዘመቻ ሲያደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ማስተዋል ያላቸው ሁሉ የትንቢቱን ፍጻሜ በግልጽ ማስተዋል ይችላሉ።—በገጽ 284 ላይ የሚገኘውን “በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት ነገሥታት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

22. የሰሜኑ ንጉሥ ስለሚሰነዝረው የመጨረሻ ጥቃት ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

22 ይሁን እንጂ የሰሜን ንጉሥ በቅርቡ ምን እርምጃ እንደሚወስድ እናውቃለን። “ከምሥራቅና ከሰሜንም” በሚያውከው ወሬ ተነሣስቶ ‘ብዙዎችን’ ለማጥፋት ዘመቻ ያካሂዳል። ይህ ዘመቻ ዒላማ ያደረገው ማንን ነው? እንዲህ ያለውን ጥቃት እንዲፈጽም የሚያነሳሳውስ “ወሬ” ምንድን ነው?

የሚያውክ ወሬ ይደርሰዋል

23. (ሀ) ከአርማጌዶን በፊት ምን ጉልህ ክንውን መፈጸም ይኖርበታል? (ለ) ‘ከፀሐይ መውጫ የሚመጡት ነገሥታት’ እነማን ናቸው?

23 የራእይ መጽሐፍ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት የሆነችውን የታላቂቱ ባቢሎንን ፍጻሜ በሚመለከት ምን እንደሚል ልብ በል። ከአርማጌዶን ማለትም ‘ሁሉን ከሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በፊት ይህቺ የእውነተኛው አምልኮ ቀንደኛ ጠላት ‘ሙሉ በሙሉ በእሳት ትቃጠላለች።’ (ራእይ 16:14, 16፤ 18:2-8) የሚደርስባት ጥፋት በምሳሌያዊው የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ በፈሰሰው ስድስተኛው የአምላክ የቁጣ ጽዋ ተገልጿል። ‘ከፀሐይ መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ ይሰናዳላቸው ዘንድ’ ወንዙ ደረቀ። (ራእይ 16:12) እነዚህ ነገሥታት እነማን ናቸው? ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም!—ከ⁠ኢሳይያስ 41:2፤ 46:10, 11 ጋር አወዳድር።

24. የሰሜኑን ንጉሥ የሚያውከው ይሖዋ የሚወስደው የትኛው እርምጃ ሊሆን ይችላል?

24 የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው ተደርጎ በሥዕላዊ መንገድ ተገልጿል:- “ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና [በፍጻሜው ዘመን የሚገዙት ነገሥታትና] አውሬው [የተባበሩት መንግሥታት] ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:16) ገዥዎቹ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፏት ለምንድን ነው? ‘አምላክ ሐሳቡን እንዲፈጽሙ ወደ ልባቸው ስለሚያገባው’ ነው። (ራእይ 17:17) ከእነዚህ ነገሥታት መካከል የሰሜኑ ንጉሥም ይገኝበታል። ‘ከምሥራቅ’ የሚሰማው ነገር ይሖዋ ታላቂቷን ሃይማኖታዊ ጋለሞታ ያጠፉ ዘንድ በገዥዎች ልብ ውስጥ ሐሳቡን በማስገባት የሚወስደውን እርምጃ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል።

25. (ሀ) የሰሜኑ ንጉሥ ልዩ ዒላማ ማን ነው? (ለ) የሰሜኑ ንጉሥ ‘ንጉሣዊ ድንኳኑን’ የሚተክለው የት ነው?

25 ይሁን እንጂ የሰሜኑ ንጉሥ ቁጣ የሚነድበት የተለየ ወገን አለ። ‘ንጉሣዊ ድንኳኑን በታላቁ ባሕርና በጌጡ ቅዱስ ተራራ መካከል’ እንደሚተክል መልአኩ ተናግሯል። በዳንኤል ዘመን ታላቅ ባሕር የተባለው የሜድትራንያን ባሕር ሲሆን ቅዱሱ ተራራ ደግሞ በአንድ ወቅት የአምላክ ቤተ መቅደስ መቀመጫ የነበረችው ጽዮን ናት። በመሆኑም በዚህ ትንቢት መሠረት የተቆጣው የሰሜን ንጉሥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ዘመቻ ያካሂዳል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘በታላቁ ባሕርና በቅዱሱ ተራራ መካከል ያለው ቦታ’ የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ያላቸውን መንፈሳዊ ርስት የሚያመለክት ነው። እንደ “ባሕር” ከተመሰለው ከአምላክ የራቀ የሰው ዘር መካከል ወጥተው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊቷ ጽዮን የመግዛት ተስፋ አግኝተዋል።—ኢሳይያስ 57:20፤ ዕብራውያን 12:22፤ ራእይ 14:1

26. በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ እንደተገለጸው ‘ከሰሜን የሚመጣው’ ዜና ምንጭ ማን ሊሆን ይችላል?

26 በዳንኤል ዘመን የኖረው ሕዝቅኤልም “በኋለኛው ዘመን” በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ተንብዮአል። ይህን ጥላቻ የሚቆሰቁሰው የማጎጉ ጎግ ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ገልጿል። (ሕዝቅኤል 38:14, 16) በምሳሌያዊ አነጋገር ጎግ የሚመጣው ከየት አቅጣጫ ነው? ይሖዋ በሕዝቅኤል አማካኝነት ‘በስተ ሰሜን በኩል ካለ ሩቅ ስፍራ’ መሆኑን ይነግረናል። (ሕዝቅኤል 38:151980 ትርጉም) ይህ ጥቃት የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆን የይሖዋን ሕዝቦች ጨርሶ የሚያጠፋ አይሆንም። ይህ አስገራሚ ክንውን ይሖዋ የጎግን ኃይሎች ለመደምሰስ የሚወስደው ስትራቴጃዊ እርምጃ ውጤት ነው። በመሆኑም ይሖዋ ሰይጣንን እንዲህ ይለዋል:- “በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ።” “ከሰሜን ዳርቻ እጎትትሃለሁ፣ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ።” (ሕዝቅኤል 38:4፤ 39:2) በመሆኑም “ከሰሜን” የሚመጣውና የሰሜኑን ንጉሥ የሚያስቆጣው ዜና የሚመነጨው ከይሖዋ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ “ከምሥራቅና ከሰሜን” የሚወጡት ወሬዎች በመጨረሻ ምን ይያዙ ምን የሚወስነው አምላክ ራሱ ሲሆን ለእኛም ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል።

27. (ሀ) ጎግ የሰሜኑን ንጉሥ ጨምሮ ሁሉም ብሔራት የይሖዋን ሕዝቦች እንዲያጠቁ የሚያነሳሳቸው ለምንድን ነው? (ለ) የጎግ ጥቃት መጨረሻው ምን ይሆናል?

27 ጎግ ግን የዓለም ክፍል ሳይሆኑ የሚመላለሱት ‘የእግዚአብሔር እስራኤልና’ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሚኖራቸው ብልጽግና ተነሣስቶ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይሰነዝራል። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16፤ 17:15, 16፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ጎግ ‘ከብሔራት ተውጣጥተው የተሰበሰቡትንና [መንፈሳዊ] ሀብትና ንብረት ያከማቹትን ሕዝቦች’ የሚያያቸው በክፉ ዓይን ነው። (ሕዝቅኤል 38:12 NW) የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ይዞታ በግላጭ እንደተገኘ ‘ቅጥር የሌለው መንደር’ በመቁጠር መላውን የሰው ዘር እንዳይቆጣጠር እንቅፋት የሆነበትን ነገር ጨርሶ ለማስወገድ በሙሉ ኃይሉ ይንቀሳቀሳል። ይሁን እንጂ አይሳካለትም። (ሕዝቅኤል 38:11, 18፤ 39:4) የሰሜኑን ንጉሥ ጨምሮ የምድር ነገሥታት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ‘ወደ ፍጻሜያቸው ይመጣሉ።’

‘ንጉሡ ወደ ፍጻሜው ይመጣል’

28. የሰሜኑንና የደቡቡን ነገሥታት የወደፊት ዕጣ በሚመለከት ምን የምናውቀው ነገር አለ?

28 የሰሜን ንጉሥ የሚያደርገው የመጨረሻ ዘመቻ በደቡብ ንጉሥ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በመሆኑም የሰሜን ንጉሥ ወደ ፍጻሜው የሚመጣው በዋነኛ ተቀናቃኙ እጅ አይደለም። በተመሳሳይም የደቡቡ ንጉሥ የሚጠፋው በሰሜኑ ንጉሥ አይደለም። የደቡቡ ንጉሥ የሚጠፋው ‘[በሰው] እጅ’ ሳይሆን በአምላክ መንግሥት ነው። * (ዳንኤል 8:25) እንዲያውም በአርማጌዶን ጦርነት ጊዜ ምድራዊ መንግሥታት በሙሉ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከሕልውና ውጭ ይሆናሉ። የሰሜኑ ንጉሥ ዕጣም ቢሆን ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ግልጽ ነው። (ዳንኤል 2:44) ዳንኤል 11:44, 45 የሚገልጸው ወደ መጨረሻው ውጊያ የሚያመሩትን ክንውኖች ነው። የሰሜኑ ንጉሥ ወደ ፍጻሜው ሲመጣ የሚረዳው አለመኖሩ ምንም አያስገርምም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 የዚህን መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

ምን አስተውለሃል?

• ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ማንነት የተቀየረው እንዴት ነው?

• የሰሜንና የደቡብ ንጉሥ የመጨረሻ ዕጣቸው ምን ይሆናል?

• የዳንኤል ትንቢት በሁለቱ ተቀናቃኝ ነገሥታት መካከል ስላለው ቅራኔ የሚናገረውን ነገር በትኩረት በመከታተልህ የተጠቀምከው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 284 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱ ነገሥታት

የሰሜን ንጉሥ የደቡብ ንጉሥ

ዳንኤል 11:5 ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ቀዳማዊ ቶሌሚ

ዳንኤል 11:6 ዳግማዊ አንታይከስ ዳግማዊ ቶሌሚ

(ሚስቱ ላድሴ) (ልጁ ቤረኒስ)

ዳንኤል 11:7-9 ዳግማዊ ሰሉከስ ሳልሳዊ ቶሌሚ

ዳንኤል 11:10-12 ሳልሳዊ አንታይከስ ቶሌሚ አራተኛ

ዳንኤል 11:13-19 ሳልሳዊ አንታይከስ ቶሌሚ አምስተኛ

(ልጁ ቀዳማዊት ክሊዮፓትራ) ወራሽ:- ቶሌሚ ስድስተኛ

ወራሾች:-

ሰሉከስ አራተኛና

አንታይከስ አራተኛ

ዳንኤል 11:20 አውግስጦስ

ዳንኤል 11:21-24 ጢባርዮስ

ዳንኤል 11:25, 26 ኦሬሊየን ንግሥት ዘኖቢያ

የሮማ ግዛት

መፈራረስ

ዳንኤል 11:27-30ሀ የጀርመን ግዛት የአንግሎ አሜሪካን የዓለም

(አንደኛው የዓለም ጦርነት) ኃይል አስከትላ

ብቅ ያለችው ብሪታንያ

ዳንኤል 11:30ለ, 31 የሂትለር ሦስተኛው ራይክ የአንግሎ አሜሪካ

(ሁለተኛው የዓለም ጦርነት) የዓለም ኃይል

ዳንኤል 11:32-43 የኮሚኒስቱ ጎራ የአንግሎ አሜሪካ

ቀዝቃዛው ጦርነት) የዓለም ኃይል

ዳንኤል 11:44, 45 ገና ወደፊት ይነሣል * የአንግሎ አሜሪካ

የዓለም ኃይል

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.83 በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት በተለያዩ ወቅቶች ላይ የሰሜንና የደቡብ ንጉሥ ሆነው የተነሱትን ፖለቲካዊ ኃይሎች ስም አይጠቅስም። ማንነታቸው ግልጽ የሚሆነው ክንውኖቹ መታየት ከጀመሩ በኋላ ነው። ከዚህም ሌላ ቅራኔው የራሱ ምዕራፎች ያሉት በመሆኑ ምንም ዓይነት ግጭት ያልታየባቸውና አንዱ ሲገንን ሌላው አደብ የገዛባቸው ወቅቶች ታይተዋል።

[በገጽ 271 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 279 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የደቡቡ ንጉሥ ‘ግፊያ ’ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስለላ ማካሄድንና ወታደራዊ ማስፈራሪያዎችን ያካትታል