በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነታቸው ከባዱን ፈተና ተቋቋመ

እምነታቸው ከባዱን ፈተና ተቋቋመ

ምዕራፍ አምስት

እምነታቸው ከባዱን ፈተና ተቋቋመ

1. አንዳንዶች ለአምላክና ለትውልድ አገራቸው ያደሩ ስለመሆን ምን ይሰማቸዋል?

አምልኮታዊ ፍቅር ማሳየት ያለብህ ለአምላክ ነው ወይስ ለምትኖርበት አገር? ብዙዎች ‘ለሁለቱም የመቆም ግዴታ አለብኝ። አምላክንም ሃይማኖቴ በሚያዝዘው መሠረት አመልከዋለሁ፤ ለትውልድ አገሬም ታማኝ ሆኜ መቆም አለብኝ’ ይላሉ።

2. የባቢሎን ንጉሥ የሃይማኖትም የፖለቲካም ሰው የነበረው በምን መልኩ ነው?

2 ዛሬ በሃይማኖታዊ ፍቅርና በአገር ፍቅር መካከል ያለው ልዩነት ደብዝዟል። በጥንቷ ባቢሎን ግን ጭራሽ ምንም ዓይነት ልዩነት አልነበረም ለማለት ይቻላል። እንዲያውም የአገር ጉዳይና ቅዱስ የሚባሉት ነገሮች እርስ በርሳቸው የተቆራኙ ከመሆናቸው የተነሣ አንዱን ከሌላው ነጥሎ ለማየት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ ነበር። ፕሮፌሰር ቻርለስ ኤፍ ፐፊፈር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጥንቷ ባቢሎን ንጉሡ ሊቀ ካህናትም የሕዝብ አስተዳዳሪም ነበር። መሥዋዕቶችን ያቀርብ የነበረ ሲሆን የተገዥዎቹንም ሃይማኖታዊ ሕይወት የመወሰን ሥልጣን ነበረው።”

3. ናቡከደነፆር በጣም ሃይማኖተኛ ሰው እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

3 የንጉሥ ናቡከደነፆርን ሁኔታ ተመልከት። ስሙ ራሱ “ነቦ ሆይ አልጋ ወራሹን ጠብቅ!” ማለት ነው። ነቦ የባቢሎናውያን የጥበብና የግብርና አምላክ ነው። ናቡከደነፆር እጅግ ሃይማኖተኛ ሰው ነበር። ቀደም ሲል እንደተገለጸው የበርካታ ባቢሎናውያን አማልክትን ቤተ መቅደስ የገነባና ያስዋበ ሲሆን በተለይ ደግሞ ወታደራዊ ድሎችን እንድጎናጸፍ ረድቶኛል ለሚለው ለማርዱክ ያደረ ሰው ነበር። * ናቡከደነፆር የውጊያ ስልቶቹን በመንደፍ ረገድ እጅጉን በጥንቆላ ይጠቀም የነበረ ይመስላል።—ሕዝቅኤል 21:18-23

4. በባቢሎን ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ ሁኔታ እንደነበር ግለጽ።

4 በእርግጥም በመላዋ ባቢሎን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ሰፍኖ ነበር። ከተማዋ የአኑን (የሰማይ አምላክ) የኤንሊልን (የምድር፣ የአየርና የማዕበል አምላክ) እና የኢአን (የውኃዎች አምላክ) የሦስት አምላኮች ጥምረት ጨምሮ ሌሎች በጣም ብዙ ወንድና ሴት አማልክት የሚመለኩባቸው ከ50 የሚበልጡ ቤተ መቅደሶች ነበሯት። ሌላው የሦስት አማልክት ጥምረት ደግሞ የሲን (የጨረቃ አምላክ)፣ የሻማሽ (የፀሐይ አምላክ) እንዲሁም የኢሽታር (የመራባት ሴት አምላክ) ጥምረት ነው። በባቢሎናውያን አምልኮ ውስጥ ጥንቆላ፣ አስማትና ኮከብ ቆጠራ ከፍተኛ ቦታ ነበራቸው።

5. የባቢሎን ሃይማኖታዊ ሁኔታ ለአይሁዳውያኑ ግዞተኞች ምን ፈታኝ ሁኔታ ጋርጦባቸዋል?

5 በምርኮ ለነበሩት አይሁዳውያን ብዙ አማልክት ባሏቸው ሰዎች መካከል መኖር እጅግ ፈታኝ ነበር። ከብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ሙሴ በታላቁ ሕግ ሰጭ ላይ ማመፅ የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት በሚመለከት እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸው ነበር። እንዲህ ብሏቸዋል:- “እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ።”—ዘዳግም 28:15, 36

6. ለዳንኤል፣ ለአናንያ፣ ለሚሳኤልና አዛርያ በባቢሎን መኖር ልዩ ፈተና የሆነባቸው እንዴት ነው?

6 አሁን አይሁዳውያን የገጠማቸው ልክ ይህንኑ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። በተለይ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ለይሖዋ ያላቸውን የጸና አቋም ለመጠበቅ የነበረባቸው ትግል ቀላል አልነበረም። እነዚህ አራት ወጣት ዕብራውያን ለመንግሥት አገልግሎት እንዲሠለጥኑ ተመርጠው ነበር። (ዳንኤል 1:3-5) ሌላው ቀርቶ ከአዲሱ አካባቢ ጋር እንዲስማሙ ተጽዕኖ ለማሳደር ተብሎ ሳይሆን አይቀርም ብልጣሶር፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚሉ ባቢሎናዊ ስሞችም ተሰጥተዋቸው እንደነበር አስታውስ። * በሕዝብ ፊት ጎላ ብለው እንዲታዩ የሚያደርግ ከፍተኛ ሥልጣን ስለ ነበራቸው የምድሪቱን አማልክት አናመልክም በማለት የሚወስዱት ማንኛውም እርምጃ ሊሰወር የማይችል ከመሆኑም ሌላ እንደ ክሕደት ሊቆጠርባቸው ይችላል።

አስጊ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ የወርቅ ምስል

7. (ሀ) ናቡከደነፆር ያቆመው ምስል ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ። (ለ) የምስሉ ዓላማ ምን ነበር?

7 ናቡከደነፆር የግዛቱን አንድነት ለማጠናከር በማሰብ ሳይሆን አይቀርም በዱራ ሜዳ አንድ የወርቅ ምስል አቆመ። የምስሉ ርዝመት 60 ክንድ (27 ሜትር) ወርዱ 6 ክንድ (2.7 ሜትር) ነበር። * አንዳንዶች ይህ ምስል እንዲሁ እንደ ዓምድ ያለ ነገር ወይም ሐውልት ነው ይላሉ። ምናልባትም ረጅም መቆሚያ ኖሮት እዚያ ላይ ናቡከደነፆርን ራሱን ወይም ነቦ የተባለውን አምላክ የሚያመለክት በሰው ምስል የተሠራ እጅግ ግዙፍ ሐውልት ቆሞም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የባቢሎናውያን ግዛት መለያ የሆነ ሐውልት ነበር። ሰው ሁሉ እንዲያየውና ልዩ ክብር እንዲሰጠው ታስቦ የቆመ ነው።—ዳንኤል 3:1

8. (ሀ) ወደ ምስሉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የተጠሩት እነማን ናቸው? በዚያ የተገኙት ሁሉስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? (ለ) በምስሉ ፊት ተደፍተው ሳይሰግዱ ቢቀሩ የሚወሰደው ቅጣት ምን ነበር?

8 ናቡከደነፆርም ለዚሁ ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት አዘጋጅቶ ነበር። በዚያም መሳፍንቱንና ሹማምንቶቹን፣ አገረ ገዥዎቹን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ የሕግ አዋቂዎችንና የአውራጃ አስተዳዳሪዎቹን ሁሉ ሰበሰበ። ከዚያም እንዲህ የሚል አዋጅ ተነገረ:- “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፣ የመለከትንና የእምቢልታን፣ የመሰንቆንና የክራርን፣ የበገናንና የዋሽንትን፣ የዘፈንንም ድምፅ ሁሉ በሰማችሁ ጊዜ፣ ተደፍታችሁ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል፤ ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”—ዳንኤል 3:2-6

9. ናቡከደነፆር ባቆመው ምስል ፊት ወድቀው እንዲሰግዱ የተደረገበት ዓላማ ምን ሊሆን ይችላል?

9 አንዳንዶች ናቡከደነፆር ይህንን ሥነ ሥርዓት ያዘጋጀው አይሁዳውያኑ ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲተዉ ለማድረግ አስቦ ነው ይላሉ። ወደዚህ ሥነ ሥርዓት የተጠሩት የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ብቻ ስለሆኑ ለዚያ ታስቦ የተደረገ ነው ማለት ያስቸግራል። ስለሆነም በዚህ ሥርዓት ላይ የተገኙት አይሁዳውያን የመንግሥት ሥልጣን የነበራቸው ብቻ ናቸው። በምስሉ ፊት ተደፍተው እንዲሰግዱ መደረጉ የገዥውን መደብ ኅብረትና አንድነት ለማጠናከር ታስቦ የተደረገ ሥነ ሥርዓት ይመስላል። ምሁሩ ጆን ኤፍ ዋልቮርድ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ባለ ሥልጣናቱ በዚህ መልክ ግልብጥ ብለው መውጣታቸው አንድም የናቡከደነፆር ግዛት ያለውን ኃይል የሚያንጸባርቅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ የድላችን ምንጮች ናቸው ብለው ለሚያስቧቸው ጣዖታት ክብር ነበር።”

የይሖዋ አገልጋዮች አቋማቸውን ለማላላት አልፈቀዱም

10. የናቡከደነፆርን ትእዛዝ ማክበር አይሁዳውያን ላልሆኑት ሰዎች ቀላል የነበረው ለምንድን ነው?

10 ናቡከደነፆር ካቆመው ምስል ፊት የተሰበሰቡት ሰዎች የየራሳቸው የሚለማመኗቸው አማልክት ቢኖሯቸውም አብዛኞቹ ሰዎች ለምስሉ በመስገዳቸው ምንም ቅር አይላቸውም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳሉት “ሁሉም የጣዖት አማልክትን ማምለክ የለመዱ ሲሆኑ የሚያመልኩት የራሳቸው አንድ አምላክ ያላቸው መሆኑ ለሌላው አምልኮታዊ ክብር እንዳይሰጡ አያግዳቸውም።” በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል:- “ብዙ አማልክት አሉ፤ . . . ለየትኛውም ሕዝብ ወይም አገር አማልክት አምልኮታዊ አክብሮት ማሳየት ደግሞ ስህተት አይደለም ከሚለው በእጅጉ ከተስፋፋው የጣዖት አምላኪዎቹ አመለካከት ጋር የሚስማማ ነበር።”

11. ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በምስሉ ፊት ወድቀው ለመስገድ አሻፈረን ያሉት ለምን ነበር?

11 ለአይሁዳውያኑ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነበር። አምላካቸው ይሖዋ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም . . . እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” (ዘጸአት 20:4, 5) በመሆኑም ሙዚቃው መሰማት ሲጀምርና በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ከምስሉ ፊት ተደፍተው ሲሰግዱ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉት ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ቀጥ ብለው እንደቆሙ ንቅንቅ አላሉም።—ዳንኤል 3:7

12. አንዳንድ ከለዳውያን ሦስቱን ዕብራውያን ምን ብለው ከሰሷቸው? ለምንስ?

12 እነዚህ ዕብራውያን ባለ ሥልጣኖች ለምስሉ አንሰግድም ማለታቸው አንዳንዶቹን ከለዳውያን እጅግ አስቆጣቸው። ወዲያውኑ ንጉሡ ዘንድ ሄደው ‘አይሁዳውያኑን ከሰሱ።’ * የእነርሱን ሐሳብ መስማት አልፈለጉም ነበር። ዕብራውያኑ ታማኝነት በማጉደልና አገርን በመክዳት ወንጀል እንዲቀጡላቸው በማሰብ ከሳሾቻቸው እንዲህ አሉ:- “በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እምቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም።”—ዳንኤል 3:8-12

13, 14. ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለወሰዱት እርምጃ የናቡከደነፆር ምላሽ ምን ነበር?

13 እነዚህ ሦስት ዕብራውያን ትእዛዙን ሳያከብሩ በመቅረታቸው ናቡከደነፆር ምንኛ ተበሳጭቶ ይሆን! ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የባቢሎን ግዛት ታማኝ ጠበቆች እንዲሆኑ ለመለወጥ ያደረገው ጥረት እንዳልሠመረለት ግልጽ ነበር። የከለዳውያንን ጥበብ አስተምሯቸው አልነበረምን? ስማቸውን ሳይቀር ለውጦት ነበር! ይሁን እንጂ ናቡከደነፆር ሰፊ ትምህርት እንዲሰጣቸው ስላደረገ ብቻ አዲስ ዓይነት አምልኮ አስተምራቸዋለሁ ወይም ስማቸውን ስለቀየረ ብቻ ማንነታቸውን እለውጠዋለሁ ብሎ አስቦ ከነበረ በእጅጉ ተሳስቷል። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ከመሆን ፍንክች አላሉም።

14 ንጉሥ ናቡከደነፆር በጣም ተቆጣ። ወዲያውኑም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን አስጠርቶ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፣ አምላኬን አለማምለካችሁ፣ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?” ናቡከደነፆር ይህን ያለው ጉዳዩን ለማመን ተቸግሮ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞስ ‘ጤናማ አእምሮ ያላቸው እነዚህ ሦስት ሰዎች እንዲህ ያለውን ግልጽ የሆነና ከባድ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ትእዛዝ እንዴት እምቢ ይላሉ’ ብሎ አስቦም ሊሆን ይችላል።—ዳንኤል 3:13, 14

15, 16. ናቡከደነፆር ለሦስቱ ዕብራውያን ምን ዕድል ሰጣቸው?

15 ናቡከደነፆር ለሦስቱ ዕብራውያን ሌላ አንድ ዕድል ሊሰጣቸው ፈልጎ እንዲህ አለ:- “አሁንም የመለከቱንና የእምቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚህ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?”—ዳንኤል 3:15

16 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ናቡከደነፆር (በዳንኤል ምዕራፍ 2 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው) በሕልም ካየው ምስል ባገኘው ትምህርት ልቡና አእምሮው አልተነካም። ለዳንኤል “አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ . . . ነው” እንዳለ ሳይረሳው አልቀረም። (ዳንኤል 2:47) በዚህ ጊዜ ናቡከደነፆር ዕብራውያኑን ከሚጠብቃቸው ጥፋት ሊያድናቸው የሚችል አምላክ እንደሌለ ሲናገር ይሖዋን ጭምር እየተገዳደረ ያለ ይመስላል።

17. ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ንጉሡ ላቀረበላቸው ሐሳብ የሰጡት መልስ ምንድን ነው?

17 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ጉዳዩን እንደገና ማጤን አላስፈለጋቸውም። ወዲያውኑ እንዲህ ሲሉ መለሱ:- “ናቡከደነፆር ሆይ፣ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፣ ንጉሥ ሆይ፣ እርሱ ባያድነን፣ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።”—ዳንኤል 3:16-18

በእሳቱ እቶን ውስጥ!

18, 19. ሦስቱ ዕብራውያን ወደ እሳቱ እቶን ሲጣሉ ምን ነገር ተፈጸመ?

18 ናቡከደነፆር እጅግ ተቆጥቶ እሳቱን ይነድድ ከነበረው ሰባት እጥፍ ያነዱት ዘንድ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም ‘ኃያላን ሰዎች’ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን አስረው ‘ወደሚነድደው እቶን እሳት’ ይጥሏቸው ዘንድ አዘዘ። የንጉሡን ትእዛዝ በመቀበል ሦስቱን ዕብራውያን አስረው ልብሶቻቸውን እንደለበሱ ወደ እሳቱ ጣሏቸው። ምናልባትም ከነልብሳቸው የጣሏቸው ቶሎ እንዲቃጠሉ ብለው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በእሳቱ የተበሉት የራሱ የናቡከደነፆር ባለሟሎች ነበሩ።—ዳንኤል 3:19-22

19 ሆኖም አንድ እንግዳ ክስተት ይታይ ነበር። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በእሳቱ እቶን ውስጥ ቢሆኑም እሳቱ አላቃጠላቸውም። ናቡከደነፆር ምን ያህል እንደሚገረም አስበው! ጥፍር አድርገው አስረው በሚንቀለቀለው እሳት ውስጥ ጥለዋቸው ነበር። ነገር ግን አሁንም በሕይወት አሉ። ይባስ ብሎ በእሳት ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይንቀሳቀሳሉ! ይሁን እንጂ ናቡከደነፆር ሌላም ነገር ተመለከተ። “አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን?” [የ1980 ትርጉም] ሲል የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣናቱን ጠየቀ። እነርሱም “ንጉሥ ሆይ፣ እውነት ነው” ብለው መለሱለት። ናቡከደነፆርም “እነሆ፣ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቆሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል” ሲል ተናገረ።—ዳንኤል 3:23-25

20, 21. (ሀ) ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎ ከእሳቱ ሲወጡ ናቡከደነፆር ምን አስተዋለ? (ለ) ናቡከደነፆር ምን ነገር አምኖ ለመቀበል ተገድዷል?

20 ናቡከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ “እናንተ የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች፣ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፣ ኑ ውጡ” ብሎ ጮኸ! ሦስቱም ዕብራውያን ከእሳቱ ውስጥ ወጡ። መሳፍንቱንና ሹማምንቱን፣ አገረ ገዥዎቹንና ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖቹን ጨምሮ ይህን ተዓምር በዓይናቸው የተመለከቱት ሁሉ ባሉበት በድን ሆነው እንደቀሩ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሦስት ወጣቶች ጭራሽ እሳት ውስጥ ገብተው የወጡ አይመስሉም! የእሳቱ ሽታ አልደረሰባቸውም፤ ከፀጉራቸው አንዷ እንኳ ቀለሟን አልቀየረችም።—ዳንኤል 3:26, 27

21 በዚህ ጊዜ ናቡከደነፆር ይሖዋ ልዑል አምላክ መሆኑን አምኖ ለመቀበል ተገድዷል። እንዲህ አለ:- “መልአኩን የላከ፣ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፣ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።” ከዚያም ንጉሡ በመቀጠል ይህን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈ:- “እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ፣ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ።” ከዚህ በኋላ ሦስቱ ዕብራውያን የቀድሞ የቤተ መንግሥት ክብራቸው ተመለሰላቸው፤ ‘በባቢሎን አውራጃ ውስጥም ከፍ ከፍ ተደረጉ።’—ዳንኤል 3:28-30

እምነትና ዛሬ ያለው ከባድ ፈተና

22. በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ከሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ጋር የሚመሳሰሉ ሁኔታዎች የሚገጥሟቸው እንዴት ነው?

22 ዛሬም የይሖዋ አምላኪዎች ከሲድራቅ፣ ከሚሳቅና አብደናጎ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ይገጥማቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል ግዞተኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንዳይደሉ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:14) በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎች፣ አመለካከቶችና ልማዶች ስለማይከተሉ “መጻተኞች” ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ክርስቲያኖች ‘ይህንን ዓለም አይመስሉም።’—ሮሜ 12:2

23. ሦስቱ ዕብራውያን ጽናታቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችስ የእነርሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

23 ሦስቱ ዕብራውያን የባቢሎናውያኑን ሥርዓት ላለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። የከለዳውያኑን ጥበብ በሰፊው እንዲማሩ መደረጋቸው እንኳን መስመራቸውን እንዲስቱ አላደረጋቸውም። አምልኳቸውን በሚመለከት ያላቸው አቋም ለድርድር የሚቀርብ አልነበረም። ታማኝነታቸው ለይሖዋ ነበር። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ጽኑዎች መሆን ያስፈልጋቸዋል። በዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች የተለዩ በመሆናቸው ሊያፍሩ አይገባም። “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ።” (1 ዮሐንስ 2:17) በመሆኑም እየሞተ ካለው ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ጋር መመሳሰል ከንቱና ሞኝነት ነው።

24. የእውነተኛ ክርስቲያኖች አቋም ከሦስቱ ዕብራውያን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

24 ክርስቲያኖች መሠሪ የሆኑትን የጣዖት ዓይነቶች ጨምሮ ከማንኛውም ጣዖት መራቅ አለባቸው። * (1 ዮሐንስ 5:21) ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በታዛዥነትና በአክብሮት ከወርቁ ምስል ፊት ቢቆሙም ለዚህ ምስል መስገድ ግን የአክብሮት መግለጫ እንደሆነ ብቻ ተደርጎ የሚታይ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል። እንደዚያ ማድረግ የአምልኮ ድርጊት ስለነበር በዚያ መካፈላቸው ይሖዋን የሚያስቆጣ ነገር ነበር። (ዘዳግም 5:8-10) ጆን ኤፍ ዋልቮርድ “ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ታማኝነት ከነበራቸው የጠበቀ ትስስር አንጻር ሃይማኖታዊ አንድምታ ይኑረው እንጂ ለባንዲራ ሰላምታ ከመስጠት ጋር የሚመሳሰል ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች ጣዖትን በሚመለከት የሚወስዱት አቋም ከዚህ የተለየ አይደለም።

25. ከሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

25 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ታሪክ ለይሖዋ ብቻ የተለየ አምልኮ ለመስጠት ቆርጠው ለተነሡ ሁሉ ትልቅ ትምህርት ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት ስላሳዩ ብዙ ሰዎች ሲዘረዝር ‘የእሳትን ኃይል ስላጠፉት ሰዎች’ ሲገልጽ እነዚህን ሦስት ዕብራውያን በአእምሮ ይዞ እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ዕብራውያን 11:33, 34) ይሖዋ ይህን የመሰለውን እምነት የሚያሳዩትን ሁሉ ይባርካቸዋል። ሦስቱን ዕብራውያን ከእሳቱ እቶን እንዳዳናቸው ሁሉ የጸና አቋማቸውን ጠብቀው ሕይወታቸውን ያጡትን ታማኞች በሙሉ ከሞት በማስነሣት በዘላለም ሕይወት እንደሚባርካቸው እርግጠኞች ነን። በየትኛውም መንገድ ቢሆን ይሖዋ “የቅዱሳኑን [“የታማኞቹን፣” NW] ነፍሶች ይጠብቃል፣ ከኀጥአንም እጅ ያድናቸዋል።”—መዝሙር 97:10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶች የባቢሎን ግዛት መስራች ነው ተብሎ የሚታመነው ማርዱክ እንደ አምላክ ይታይ የነበረውን ናምሩድን ያመለክታል ይላሉ። ይሁንና በእርግጠኝነት እንደዚያ ማለት አይቻልም።

^ አን.6 “ብልጣሶር” ማለት “የንጉሡን ሕይወት ጠብቅ” ማለት ነው። “ሲድራቅ” ማለት የሱሜሪያን የጨረቃ አምላክ የሆነው “የአኩ ትእዛዝ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። “ሚሳቅ” አንድን የሱሜሪያን አምላክ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። “አብደናጎ” ደግሞ “የናጎ [ወይም የናቦ] አገልጋይ” ማለት ነው።

^ አን.7 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ምስሉ የነበረውን ግዝፈት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከእንጨት የተሠራና ከላይ ብቻ በወርቅ የተለበጠ ነበር ብለው ያምናሉ።

^ አን.12 “ከሰሱ” ተብሎ የተተረጎመው የአረማይክ አገላለጽ ‘የሰውን ሥጋ የመቦጫጨቅ’ ያህል ስሙን እያነሱ በሐሜት ማኘክ የሚል መልእክት አለው።

^ አን.24 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ሆዳምነትንና መመኘትን ከጣዖት አምልኮ ጋር ያያይዘዋል።—ፊልጵስዩስ 3:18, 19፤ ቆላስይስ 3:5

ምን አስተውለሃል?

• ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ ያልሆኑት ለምንድን ነው?

• ናቡከደነፆር ሦስቱ ዕብራውያን ለወሰዱት አቋም የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?

• ይሖዋ ሦስቱን ዕብራውያን ላሳዩት እምነት የካሳቸው እንዴት ነው?

• የሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎን እውነተኛ የሕይወት ታሪክ በመመርመርህ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 68 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 70 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. በባቢሎን የሚገኘው የቤተ መቅደስ ማማ (ዚጉራት)

2. የማርዱክ ቤተ መቅደስ

3. ማርዱክን (በስተግራ) እና ናቦን (በስተቀኝ) በደራጎኖች ላይ ቆመው የሚያሳየው የነሐስ ሰሌዳ

4. በግንባታ ሥራዎቹ የሚታወቀው የናቡከደነፆር ምስል

[በገጽ 76 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]