በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን የሚገዛው ማን ይሆን?

ዓለምን የሚገዛው ማን ይሆን?

ምዕራፍ ዘጠኝ

ዓለምን የሚገዛው ማን ይሆን?

1-3. ዳንኤል በብልጣሶር የመጀመሪያ የግዛት ዘመን ያየው ሕልምና ራእይ ምን እንደሆነ ግለጽ።

ቀልብ የሚስበው የዳንኤል ትንቢት ወደ ባቢሎናዊው ንጉሥ ብልጣሶር የመጀመሪያ የግዛት ዘመን ይመልሰናል። ዳንኤል በባቢሎን ውስጥ ለረጅም ጊዜ በግዞት ቢቆይም ለይሖዋ ያለውን የጸና አቋም ፈጽሞ አላላላም። በዚህ ወቅት በ70ዎቹ ዓመት ዕድሜው ላይ የሚገኘው ይህ የታመነ ነቢይ “በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ።” እነዚህ ራእይዎች እጅግ አስፈርተውታል!—ዳንኤል 7:1, 15

2 ዳንኤል በመገረም እንዲህ ይላል:- “እነሆም፣ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር። አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፣ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች።” እንዴት የሚያስገርሙ አራዊት ናቸው! የመጀመሪያዋ ክንፍ ያላት አንበሳ ስትሆን ሁለተኛይቱ ደግሞ ድብ የምትመስል ናት። ከዚያም አራት ክንፎችና አራት ራሶች ያሏት ነብር መጣች! እጅግ የበረታችው አራተኛ አውሬ ደግሞ ታላላቅ የብረት ጥርሶችና አሥር ቀንዶች ያሏት ነበረች። ከእነዚህም ከአሥሩ ቀንዶች መካከል አንድ “ትንሽ” ቀንድ ወጣ። እርሱም “እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም [“ታላላቅ ነገሮችን፣” NW] የሚናገር አፍ ነበሩበት።”—ዳንኤል 7:2-8

3 ቀጥሎ የዳንኤል ራእይ ወደ ሰማያዊ ክንውኖች መለስ ይላል። በዘመናት የሸመገለው ታላቅ ክብር ተላብሶ በሰማያዊው ችሎት ለዳኝነት ተቀምጧል። ‘ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉታል፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመዋል።’ ከአራዊቱ ግዛትን በመንጠቅና አራተኛዋን አውሬ በማጥፋት ጠንከር ያለ ፍርድ ያስተላልፍባቸዋል። ‘የሰው ልጅ ለሚመስለውም ወገኖችና፣ አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ’ ይገዙለት ዘንድ ዘላቂ ግዛት ተሰጠው።—ዳንኤል 7:9-14

4. (ሀ) ዳንኤል እውነተኛውን ነገር ለማወቅ ዘወር ያለው ወደ ማን ነው? (ለ) ዳንኤል በዚያ ሌሊት ያየውና የሰማው ነገር ለእኛ ዐብይ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ዳንኤልም “በእኔም . . . በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ ደነገጠች፣ የራሴም ራእይ አስቸገረኝ” ብሏል። በመሆኑም አንድ መልአክ ‘ስለዚህ ሁሉ ነገር እውነቱን እንዲነግረው ጠይቋል።’ መልአኩም ‘የነገሩን ፍቺ አስታወቀው።’ (ዳንኤል 7:15-28) ዳንኤል ያን ዕለት ሌሊት ያየውና የሰማው ነገር የእኛንም ትኩረት የሚስብ ነው። ምክንያቱም ‘ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ’ ይገዙለት ዘንድ ሥልጣን የተሰጠው ‘የሰውን ልጅ የሚመስለው’ ሥልጣኑን እስከሚረከብበት እስከዚህ እስከ እኛ ዘመን ድረስ የሚከናወኑ ነገሮችን የሚዘረዝር ነው። በአምላክ ቃልና መንፈስ እርዳታ እኛም የእነዚህን ትንቢታዊ ራእይዎች ትርጉም መረዳት እንችላለን። *

ከባሕር የወጡ አራት አራዊት

5. በንፋስ የሚናወጠው ባሕር ምን ያመለክታል?

5 ዳንኤል “አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ” ብሏል። (ዳንኤል 7:3) በንፋስ የሚናጠው ባሕር ምን ያመለክታል? ከብዙ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ ሰባ⁠ት ራስ ያለው አውሬ “ከባሕር” ሲወጣ ተመልክቷል። ባሕሩ የሚያመለክተው ከአምላክ የራቀውን ሰፊ የሰው ዘር ወገን ማለትም ‘ወገኖችና ብዙ ሰዎችን፣ አሕዛብንም ቋንቋዎችንም’ ነው። እንግዲያው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ባሕርም ከአምላክ የራቀውን ሰፊውን ኅብረተሰብ የሚያመለክት መሆኑ ተገቢ ነው።—ራእይ 13:1, 2፤ 17:15፤ ኢሳይያስ 57:20

6. አራቱ አራዊት ምን ያመለክታሉ?

6 የአምላክ መልአክ “እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው” ብሏል። (ዳንኤል 7:17) በግልጽ እንደምንረዳው ዳንኤል ያያቸው አራት አራዊት “አራት ነገሥታት” መሆናቸውን መልአኩ ተናግሯል። በመሆኑም እነዚህ አራዊት የዓለምን ኃይላት የሚወክሉ ናቸው። ይሁን እንጂ የትኞቹን የዓለም ኃይላት?

7. (ሀ) ዳንኤል ስለ አራቱ አራዊት ስላየው ሕልምና ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ስላየው ግዙፍ ምስል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ምን ይላሉ? (ለ) በአራት የብረት ዓይነቶች የተገለጹት የምስሉ አካሎች እያንዳንዳቸው ምን ያመለክታሉ?

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ብዙውን ጊዜ ዳንኤል ስለ አራቱ አራዊት ያየውን የሕልም ራእይ ናቡከደነፆር በሕልሙ ካየው ግዙፍ ምስል ጋር ያያይዙታል። ለምሳሌ ያህል ዚ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ “[ዳንኤል] ምዕራፍ 7 ከምዕራፍ 2 ጋር ጎን ለጎን ይሄዳል” ይላል። ዘ ዊክሊፍ ባይብል ኮሜንታሪ ደግሞ እንዲህ ይላል:- “በዚህ [በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 7] እና [በዳንኤል] ምዕራፍ 2 ላይ በየተራ ስለተፈራረቁት አራት የአሕዛብ ኃይሎች የተሰጠው መግለጫ ተመሳሳይ . . . መሆኑ በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ ነገር ነው።” በናቡከደነፆር ሕልም ውስጥ በታዩት አራት የብረት ዓይነቶች የተወከሉት አራት የዓለም ኃይሎች የባቢሎን ግዛት (የወርቁ ራስ)፣ ሜዶ ፋርስ (የብር ደረቱና እጆቹ)፣ ግሪክ (የነሐስ ሆዱና ጭኖቹ) እንዲሁም የሮማ ግዛት (የብረት ቅልጥሞቹ) ናቸው። * (ዳንኤል 2:32, 33) እነዚህ አራት መንግሥታት ዳንኤል ካያቸው አራት ትላልቅ አራዊት ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

እንደ አንበሳ አስፈሪ፤ እንደ ንስር ፈጣን

8. (ሀ) ዳንኤል የመጀመሪያዋን አውሬ የገለጻት እንዴት ነበር? (ለ) የመጀመሪያዋ አውሬ የምታመለክተው የትኛውን ግዛት ነው? እንደ አንበሳስ የሆነችው በምን መንገድ ነው?

8 ዳንኤል የተመለከታቸው አራዊት እንዴት የሚያስገርሙ ናቸው! ስለ አንዲቷ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፣ የንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፣ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፣ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፣ የሰውም ልብ ተሰጣት።” (ዳንኤል 7:4) ይህች አውሬ የምታመለክተው በግዙፉ ምስል የወርቅ ራስ የተመሰለውን አገዛዝ ማለትም የባቢሎንን የዓለም ኃይል ነው (607-539 ከዘአበ)። ባቢሎን እያደነ እንደሚበላ “አንበሳ” የአምላክን ሕዝቦች ጨምሮ ብሔራትን በጭካኔ ስትበላ ቆይታለች። (ኤርምያስ 4:5-7፤ 50:17) ይህች “አንበሳ” የንስር ክንፍ ያላት ያህል በጦር ድልዋ በፍጥነት ወደፊት ገስግሳለች።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 4:19፤ ዕንባቆም 1:6-8

9. እንደ አንበሳ ያለችው አውሬ ምን ለውጥ አድርጋለች? ይህስ በእርሷ ላይ ምን ውጤት ነበረው?

9 ከጊዜ በኋላ ይህቺ ለየት ያለች ባለ ክንፍ አንበሳ ክንፎቿ ‘ተነቀሉ።’ ባቢሎን የንጉሥ ብልጣሶር አገዛዝ ማክተሚያ ሲቃረብ የድል ግስጋሴዋንና በብሔራት ላይ የነበራትን እንደ አንበሳ ያለ የበላይነት አጥታ ነበር። ፍጥነቷ በሁለት እግር ከቆመ ሰው ያልተሻለ ሆኖ ነበር። ‘የሰውም ልብ ስለተሰጣት’ ደካማ ሆነች። ባቢሎን ‘የአንበሳ ልቧ’ ስለጠፋ “በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ” ንጉሥ ልትሆን አልቻለችም። (ከ⁠2 ሳሙኤል 17:10፤ ሚክያስ 5:8 ጋር አወዳድር።) ሌላ ታላቅ አውሬ ድል አድርጓታል።

እንደ ድብ በልታ የማትጠግብ

10. ‘ድቧ’ የምታመለክተው የትኛውን የገዥዎች መስመር ነው?

10 ዳንኤል እንዲህ ይላል:- “እነሆም፣ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፣ በአንድ ወገንም ቆመች [“ተነሣች፣” NW]፣ ሦስትም የጎድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም:- ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት።” (ዳንኤል 7:5) በድብየተመሰለው ንጉሥ በታላቁ ምስል የብር ደረትና እጆች የተመሰለው መንግሥት ማለትም የሜዶ ፋርስ የገዥዎች መስመር ነው (539-331 ከዘአበ)። ግዛቱ የጀመረው ከሜዶናዊው ዳርዮስና ከታላቁ ቂሮስ ሲሆን በሳልሳዊ ዳርዮስ ጊዜ ተደምድሟል።

11. ምሳሌያዊቷ ድብ በአንድ ወገን መነሳቷ ምን ያመለክታል? በአፏ የያዘቻቸው ሦስት የጎድን አጥንቶችስ?

11 ምሳሌያዊቷ ድብ ‘በአንድ ወገን እንደተነሣች’ ተገልጿል። ምናልባትም ይህ በብሔራት ላይ ጥቃት ለመሰንዘርና ድል በማድረግ የዓለም የበላይነቷን ለማረጋገጥ ዝግጅት ማድረጓን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በአንድ በኩል እንደተነሣች መገለጹ የፋርሳውያን የገዥዎች መስመር በብቸኛው የሜዶናውያን ንጉሥ ዳርዮስ ላይ የበላይነት እንደሚቀዳጅ ለማሳየት የታሰበ ሊሆን ይችላል። በድቧ ጥርሶች መካከል የነበሩት ሦስቱ የጎድን አጥንቶች የድል ግስጋሴ ያደረገችባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ። የሜዶ ፋርስ “ድብ” በ539 ከዘአበ ባቢሎንን ለመያዝ በስተ ሰሜን አቀናች። ከዚያም በስተ ምዕራብ በትንሿ እስያ እንዲሁም በትሬስ ላይ ዘምታለች። በመጨረሻም ‘ድቧ’ ግብጽን ድል ለማድረግ ወደ ደቡብ ሄደች። ሦስት ቁጥር አንዳንድ ጊዜ ጉዳዩን ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ስለሚያገለግል ሦስቱ የጎድን አጥንቶች መጠቀሳቸው ምሳሌያዊቷ ድብ ድል ለማድረግ ያላትን ከፍተኛ ጉጉት ለማጋነን የገባም ሊሆን ይችላል።

12. ምሳሌያዊቷ ድብ “ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ” የሚለውን ትእዛዝ መስማቷ ምን አስከትሏል?

12 ድቧ በብሔራት ላይ ጥቃት የሰነዘረችው “ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ” በሚሉት ቃላት መሠረት ነው። ሜዶ ፋርስ በመለኮታዊ ፈቃድ ባቢሎንን በመብላት የይሖዋን ሕዝቦች የማገልገል አጋጣሚ አግኝታ ነበር። ደግሞም አገልግላለች! (በገጽ 149 ላይ የሚገኘውን “ሆደ ሰፊ ንጉሥ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ሜዶ ፋርስ በታላቁ ቂሮስ፣ በቀዳማዊ ዳርዮስ (ታላቁ ዳርዮስ) እንዲሁም በቀዳማዊ አርጤክስስ አማካኝነት በባቢሎን የነበሩት አይሁዳዊ ምርኮኞች ነፃ ወጥተው የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ መልሰው እንዲገነቡና ቅጥሯን እንዲያድሱ ረድታለች። የኋላ ኋላ ሜዶ ፋርስ በ127 ጠቅላይ ግዛቶች ላይ ትገዛ የነበረ ሲሆን የንግሥት አስቴር ባል አሕሻዊሮስ (ቀዳማዊ ዜርሰስ) “ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ” ነግሦ ነበር። (አስቴር 1:1) ይሁን እንጂ ሌላ አውሬ እየተነሣች ነበር።

ክንፍ እንዳላት ነብር ፈጣን የሆነች አውሬ!

13. (ሀ) ሦስተኛዋ አውሬ ምን ታመለክታለች? (ለ) የሦስተኛዋን አውሬ ፍጥነትና የተቆጣጠረችውን የግዛት ክልል በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል?

13 ሦስተኛዋ አውሬ “ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት” ነች። “ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፣ ግዛትም ተሰጣት።” (ዳንኤል 7:6) ናቡከደነፆር በሕልሙ ባየው ምስል ውስጥ እንዳለው የነሐስ ሆድና ጭን ሁሉ ይህች ባለ አራት ክንፍና ባለ አራት ራሶች ነብር የምታመለክተው ከታላቁ እስክንድር ጀምሮ የተነሡትን የመቄዶናውያን ወይም የግሪክ ገዥዎች መስመር ነው። እስክንድር እንደ ነብር ባለ ቅልጥፍናና ፍጥነት በትንሿ እስያ፣ በደቡብ ወደ ግብጽ እንዲሁም በምዕራብ እስከ ሕንድ ምዕራባዊ ድንበር ድረስ ተንቀሳቅሷል። (ከ⁠ዕንባቆም 1:8 ጋር አወዳድር።) ግዛቱ መቄዶንያን፣ ግሪክንና የፋርስን ግዛት የሚጨምር ስለነበር ‘ከድቧ’ የሚበልጥ ነበር።—በገጽ 153 ላይ የሚገኘውን “ዓለምን ድል አድርጎ የተቆጣጠረ ወጣት ንጉሥ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

14. ‘ነብሯ’ ባለ አራት ራስ የሆነችው እንዴት ነው?

14 እስክንድር በ323 ከዘአበ ከሞተ በኋላ ‘ነብሯ’ አራት ራሶች ያሏት ሆናለች። ከጊዜ በኋላ አራት ጄኔራሎቹ በእርሱ ፋንታ በተለያዩ የግዛቱ ክፍሎች ላይ ሥልጣን ጨብጠዋል። ሰሉከስ መሶጴጣሚያንና ሶርያን ያዘ። ቶሌሚ ግብጽንና ፍልስጤምን ያዘ። ላይሲመከስ በትንሿ እስያና በትሬስ ሲገዛ ካሳንደር መቄዶንያንና ግሪክን ይዞ ነበር። (በገጽ 162 ላይ የሚገኘውን “ሰፊ የነበረው ግዛት ተከፋፈለ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ከዚያም አንድ አዲስ አስጊ ሁኔታ ተፈጠረ።

አንዲት አስፈሪ አውሬ ከሌሎች የተለየች ሆና ተገኘች

15. (ሀ) አራተኛዋ አውሬ ምን እንደምትመስል ግለጽ። (ለ) አራተኛዋ አውሬ ማንን ትወክላለች? በመንገዷ ላይ ያገኘችውን ሁሉ ታደቅቅና ትበላ የነበረውስ እንዴት ነው?

15 ዳንኤል አራተኛዋ አውሬ “የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች” መሆኗን ገልጿል። በመቀጠልም “ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት . . . ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፣ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።” (ዳንኤል 7:7) ይህች አስፈሪ አውሬ እንቅስቃሴ የጀመረችው የሮም ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይል በመሆን ነበር። ቀስ በቀስ የግሪካውያኑን ግዛት አራት ሄለናዊ ክፍሎች የጠቀለለች ሲሆን በ30 ከዘአበ ሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ቀጣይዋ የዓለም ኃይል ሆና ብቅ ብላለች። የሮማ ግዛት በመንገዷ ላይ ያገኘችውን ሁሉ በጦር ኃይል በማንበርከክ በመጨረሻ ግዛቷን ከብሪታንያ ደሴቶች አንስቶ አውሮፓን ይዞ በሜድትራንያን በኩል በባቢሎን አልፎ እስከ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ድረስ አስፋፍታ ነበር።

16. መልአኩ ስለ አራተኛዋ አውሬ ምን መረጃ ሰጥቷል?

16 ዳንኤል “እጅግ ስለምታስፈራው” አውሬ ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን መልአኩ የሰጠውን የሚከተለውን ማብራሪያ በትኩረት ተከታትሏል:- “አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፣ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፣ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል።” (ዳንኤል 7:19, 20, 24) እነዚህ ‘አሥር ቀንዶች’ ወይም “አሥር ነገሥታት” ምንድን ናቸው?

17. የአራተኛዋ አውሬ “አሥር ቀንዶች” ምን ያመለክታሉ?

17 ሮም ይበልጥ እየበለጸገችና በገዥው መደብ ልቅ አኗኗር ምክንያት እያሽቆለቆለች ስትሄድ የጦር ኃይሏም እየተዳከመ መጣ። ከጊዜ በኋላ የሮማ ወታደራዊ ጥንካሬ እየተዳከመ መሄዱ ግልጽ ሆነ። በመጨረሻም ኃያሏ ግዛት በብዙ መንግሥታት ተከፋፈለች። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ አሥር ቁጥርን ሙላትን ለማመልከት ስለሚጠቀምበት የአራተኛዋ አውሬ “አሥር ቀንዶች” ከሮም መፈረካከስ በኋላ የተፈጠሩትን መንግሥታት በሙሉ የሚያመለክቱ ናቸው።—ከ⁠ዘዳግም 4:13፤ ሉቃስ 15:8፤ 19:13, 16, 17 ጋር አወዳድር።

18. ሮም የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥትዋ ከተወገደም በኋላ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት በአውሮፓ የበላይነቷን ይዛ የቀጠለችው እንዴት ነበር?

18 ይሁን እንጂ የሮማ የዓለም ኃይል ያከተመው የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት በ476 እዘአ ከሥልጣኑ በተወገደ ጊዜ አልነበረም። በሊቀ ጳጳሳት የምትመራው ሮም ለብዙ መቶ ዘመናት በአውሮፓ ፖለቲካዊ በተለይ ደግሞ ሃይማኖታዊ የበላይነቷን ጠብቃ ቆይታለች። ይህንንም ያደረገችው በአውሮፓ ብዙዎቹ ነዋሪዎች ለጌቶቻቸው ብሎም ለነገሥታት ተገዥ በነበሩበት የፊውዳል ሥርዓት አማካኝነት ነው። ሁሉም ነገሥታት ደግሞ ለሊቀ ጳጳሳቱ ሥልጣን እውቅና ሰጥተው ነበር። በዚህ መንገድ በሊቀ ጳጳሳት የምትተዳደረውን ሮምን ማዕከል ያደረገው የቅድስቲቱ ሮማ ግዛት የጨለማ ዘመን ተብሎ በሚታወቀው ረጅም የታሪክ ዘመን ሁሉ የዓለምን ጉዳይ በበላይነት ሲቆጣጠር ቆይቷል።

19. አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት ከሆነ ሮም ከዚያ ቀደም ከነበሩት ግዛቶች ጋር ስትነጻጸር ምን ዓይነት ሁኔታ ነበራት?

19 አራተኛዋ አውሬ ‘ከሌሎቹ አራዊት ሁሉ የተለየች’ መሆኗን የሚክድ ማን ይኖራል? (ዳንኤል 7:7, 19, 23) ይህን በሚመለከት ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ እንዲህ ሲሉ ዘግበዋል:- “ይህ አዲሱ የሮማ ኃይል . . . በሰለጠነው ዓለም እስከዚህ ጊዜ ድረስ ከተነሡት ታላላቅ ግዛቶች ሁሉ በብዙ ነገሮች የተለየ ነበር። . . . ግዛቱ በዓለም ያሉትን ግሪካውያን በሙሉ ለማለት ይቻላል አቅፎ የነበረ ሲሆን ከዚያ በፊት ከነበረው ከየትኛውም ግዛት ጋር ሲተያይ የሕዝቡ የሐማዊና ሴማዊ የዘር ግንድ እምብዛም ጠንካራ አልነበረም . . . እስከ አሁን ድረስ ይህ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል . . . የሮማ ግዛት ያልተጠበቀና ድንገት የተከሰተ ግዛት ነው፤ የሮማ ሰዎችም ሳያስቡት ሰፊ የአስተዳደር ሥራ ውስጥ ገብተዋል።” ይሁንና አራተኛዋ አውሬ ገና ሌላ ድንገተኛ ለውጥም ታሳያለች።

አንድ ትንሽ ቀንድ የበላይነትን ተቀዳጀ

20. በአራተኛዋ አውሬ ራስ ላይ ስላደገው ትንሽ ቀንድ መልአኩ ምን ብሏል?

20 ዳንኤል እንዲህ ብሏል:- “ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፣ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ።” (ዳንኤል 7:8) የዚህን ቀንድ መከሰት በተመለከተ መልአኩ ለዳንኤል እንዲህ ብሎታል:- “ከእነርሱም [ከአሥሩ ቀንዶች] በኋላ ሌላ ይነሣል፣ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፣ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል።” (ዳንኤል 7:24) ይህ ንጉሥ ማን ነው? መቼ ተነሣ? የሚያዋርዳቸው ሦስት ነገሥታትስ የትኞቹ ናቸው?

21. ብሪታንያ በአራተኛዋ አውሬ ራስ ላይ እንደ ወጣው ትንሽ ቀንድ የሆነችው እንዴት ነው?

21 የሚከተሉትን ክንውኖች ተመልከት። በ55 ከዘአበ የሮማ ጄኔራል የሆነው ጁሊየስ ቄሣር ብሪታንያን ወርሮ የነበረ ቢሆንም ቋሚ መቀመጫው ሊያደርጋት ሳይችል ቀርቷል። በ43 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ የደቡባዊ ብሪታንያን ግዛት ይበልጥ ዘለቄታ ባለው መንገድ ድል አድርጎ መቆጣጠር ጀምሮ ነበር። ከዚያም በ122 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ሃድሪያን ከታይን ወንዝ አንስቶ እስከ ሶልዌይ ፊርዝ ድረስ ግንብ በመገንባት የሮማን ግዛት ሰሜናዊ ድንበር ወሰነ። በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮማ ጭፍራ ደሴቲቷን ለቅቆ ሄደ። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዳብራሩት ደግሞ “በስድስተኛው መቶ ዘመን እንግሊዝ ሁለተኛ ደረጃ ያላት የዓለም ኃይል ሆና ነበር። ብልጽግናዋ ከኔዘርላንድ ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነበር። የሕዝቧም ብዛት ከፈረንሳይ በጣም ያነሰ ነበር። የጦር ኃይሏም ጥንካሬ (የባሕር ኃይሏን ጨምሮ) ከስፔይን ደከም ያለ ነበር።” በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ብሪታንያ በአራተኛዋ አውሬ ላይ እንደታየው ቀንድ በወቅቱ ይህን ያህልም ግምት የሚሰጣት አገር አልነበረችም። ይሁን እንጂ ሁኔታው በዚህ መልኩ አልቀጠለም።

22. (ሀ) ‘ትንሹ’ ቀንድ ድል ያደረጋቸው በአራተኛዋ አውሬ ራስ ላይ የነበሩት ሦስት ቀንዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በዚህ ጊዜ ብሪታንያ ምን ሆና ብቅ አለች?

22 በ1588 የስፔይኑ ዳግማዊ ፊሊፕ የስፔይንን የባሕር ኃይል በብሪታንያ ላይ አዘመተ። ሆኖም 130 መርከቦችንና 24,000 ወንዶችን ያቀፈው ይህ ሠራዊት በእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ በብሪታንያ የባሕር ኃይል ድል ተነስቶ ከየአቅጣጫው ለሚነፍሰው ነፋስና ለኃይለኛው የአትላንቲክ ማዕበል ሲሳይ ሆኗል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ ይህ ድል “የባሕር ኃይል የበላይነት ከስፔይን ወደ እንግሊዝ መሻገሩን የሚያመለክት ወሳኝ” ክንውን እንደነበር ገልጸዋል። በ17ኛው መቶ ዘመን በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነውን የባሕር ላይ ንግድ ያካሂዱ የነበሩት ዳቾች ነበሩ። ይሁን እንጂ ብሪታንያ በባሕር ማዶ ያሏት ቅኝ ግዛቶች ቁጥር እያደገ በመሄዱ ከዳች መንግሥት ልቃ ተገኝታለች። በ18ኛው መቶ ዘመን ብሪታንያና ፈረንሳይ በሰሜን አሜሪካና በሕንድ ምክንያት ጦርነት ገጥመው የነበረ ሲሆን ከዚህ የተነሣ በ1763 የፓሪሱን ስምምነት ፈርመዋል። ጸሐፊው ዊልያም ቢ ዊልኮክስ እንደሚሉት ከሆነ ይህ ስምምነት “ብሪታንያ በዓለም ላይ ገናና የሆነች ብቸኛ አውሮፓዊት አገር መሆኗን እውቅና የሰጠ” ነበር። ብሪታንያ በ1815 እዘአ በፈረንሳዩ ናፖሊዮን ላይ ትልቅ ድል በተቀዳጀች ጊዜ የበላይነቷ ተረጋግጧል። በመሆኑም ብሪታንያ ‘ያዋረደቻቸው’ “ሦስት ነገሥታት” ስፔይን፣ ኔዘርላንድስና ፈረንሳይ ናቸው። (ዳንኤል 7:24) በዚህ መንገድ ብሪታንያ በቅኝ ግዛትና በንግድ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናና ሆነች። አዎን ‘ትንሹ’ ቀንድ የዓለም ኃይል ለመሆን በቃ!

23. ምሳሌያዊው ትንሽ ቀንድ ‘ምድሪቱን ሁሉ የሚበላው’ በምን መንገድ ነው?

23 መልአኩ አራተኛዋ አውሬ ወይም አራተኛው መንግሥት ‘ምድሪቱን ሁሉ እንደሚበላ’ ነግሮታል። (ዳንኤል 7:23) ይህ ነገር በአንድ ወቅት ብሪታንያ እየተባለች ትጠራ በነበረችው የሮማ ክፍለ ግዛት ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል። የኋላ ኋላ የብሪታንያ ግዛት ተብላ ‘ምድርን ሁሉ በልታለች።’ የብሪታንያ ግዛት አንድ አራተኛ የሚያህለውን የምድር ክፍልና አንድ አራተኛ የሚሆነውን ነዋሪውን ያቀፈበትም ወቅት ነበር።

24. የብሪታንያ ግዛት የተለየ ስለመሆኑ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ምን ብለዋል?

24 የሮማ ግዛት ከዚያ ቀደም ከነበሩት መንግሥታት የተለየ እንደሆነ ሁሉ ‘በትንሹ’ ቀንድ የተወከለው ንጉሥም “ከፊተኞች የተለየ ይሆናል።” (ዳንኤል 7:24) ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ የብሪታንያን ግዛት በሚመለከት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “እንዲህ የመሰለ ነገር ከዚያ በፊት ሆኖ አያውቅም። የመላው ሥርዓት ዕምብርት የተባበረው የብሪታንያ መንግሥት ማለትም ‘ንጉሠ ነገሥታዊው ሪፐብሊክ’ ነበር። . . . መላውን የብሪታንያ ግዛት ከዳር እስከ ዳር አውቃለሁ የሚል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ሆነ ግለሰብ አልነበረም። ከዚያ ቀደም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ናቸው ከተባሉት ከማናቸውም ፍጹም በተለየ መልኩ የተለያዩ ድንገተኛ ለውጦች ጥምረት ነው።”

25. (ሀ) ከጊዜ በኋላ ምሳሌያዊው ትንሽ ቀንድ ማንን የሚጨምር ይሆናል? (ለ) ‘ትንሹ’ ቀንድ “እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች” ‘ታላቅም ነገር የሚናገር አፍ’ አለው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

25 ‘ትንሹ’ ቀንድ ግን ከብሪታንያ ግዛት ውጭም ሌላ ነገር ይጨምራል። በ1783 ብሪታንያ ቀድሞ በእርሷ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩት 13 የአሜሪካ ግዛቶች ላወጁት ነፃነት እውቅና ሰጠች። በመጨረሻም ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምድራችን ኃያል ብሔር ሆና ብቅ በማለት የብሪታንያ የቅርብ አጋር ሆናለች። ዛሬም ቢሆን ከብሪታንያ ጋር የጠበቀ ትስስር አላት። ‘ዓይን ያለው ቀንድ’ የሚያመለክተው የዚህ ውጤት የሆነውን የአንግሎ አሜሪካ ጥምር የዓለም ኃይል ነው። በእርግጥም ይህ የዓለም ኃይል አስተዋይና ብልህ ነው! ለአብዛኛው የዓለም ክፍል ፖሊሲ በመንደፍ እና እንደ አፈ ቀላጤ ወይም ‘ሐሰተኛ ነቢይ’ ሆኖ በማገልገል ‘ታላላቅ ነገሮችን’ ይናገራል።—ዳንኤል 7:8, 11, 20፤ ራእይ 16:13፤ 19:20

ትንሹ ቀንድ አምላክንና ቅዱሳኑን ይቃወማል

26. ምሳሌያዊው ቀንድ በይሖዋና በአገልጋዮቹ ስለሚናገረው ቃልና ስለሚያደርገው ነገር መልአኩ ምን ትንቢት ተናግሯል?

26 ዳንኤል እንደሚከተለው በማለት ስለ ራእይው ማብራራቱን ቀጥሏል:- “እነሆም ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ . . . አሸነፋቸውም።” (ዳንኤል 7:21, 22) ይህንን “ቀንድ” ወይም ንጉሥ በተመለከተ የአምላክ መልአክ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል:- “በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፣ የልዑሉንም ቅዱሳን ይሰብራል [“ያስጨንቃል፣” የ1980 ትርጉም ]፣ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።” (ዳንኤል 7:25) ይህ የትንቢቱ ክፍል ፍጻሜውን ያገኘው እንዴትና መቼ ነው?

27. (ሀ) ‘ትንሹ’ ቀንድ ስደት ያደረሰባቸው “ቅዱሳን” እነማን ናቸው? (ለ) ምሳሌያዊው ቀንድ ‘ዘመናትንና ሕግን’ ለመለወጥ ያሰበው እንዴት ነበር?

27 ‘ትንሹ’ ቀንድ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ስደት የሚያደርስባቸው ‘ቅዱሳን’ በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ተከታዮች ናቸው። (ሮሜ 1:7፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) በምድር የነበሩት ቅቡዓን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት አስቀድሞ ለበርካታ ዓመታት 1914 ‘የተቀጠሩት የአሕዛብ ዘመናት’ መደምደሚያ እንደሚሆን በይፋ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። (ሉቃስ 21:24 NW) በዚያ ዓመት ጦርነት ሲፈነዳ ‘ትንሹ’ ቀንድ ይህንን ማስጠንቀቂያ ቸል እንዳለው ግልጽ ነበር። ምክንያቱም ቅቡዕ የሆኑትን ‘ቅዱሳን’ ማስጨነቁን ቀጥሎ ነበር። የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ሳይቀር ተቃውሟል። ይህ ሥራ ደግሞ ይሖዋ በምሥክሮቹ አማካኝነት እንዲሠራ የሚፈልገው ነገር (ወይም “ሕግ”) ነው። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ መንገድ ‘ትንሹ’ ቀንድ ‘ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ’ ሞክሯል።

28. ‘ዘመን፣ ዘመናትና የዘመናት እኩሌታ’ ሲባል ምን ያህል ጊዜ ማለት ነው?

28 የይሖዋ መልአክ ትንቢታዊ ትርጉም ስላለው ወቅት ይኸውም ስለ ‘ዘመን፣ ዘመናትና የዘመናት እኩሌታ’ ጠቅሷል። የዚህ ጊዜ ርዝማኔ ምን ያህል ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህ መግለጫ ሦስት ዘመን ተኩል እንደሚያመለክት ማለትም የአንድ ዘመን፣ የሁለት ዘመናትና የግማሽ ዘመን ድምር እንደሆነ በሰፊው ይስማማሉ። ናቡከደነፆር ነፍሱን ስቶ ያሳለፋቸው “ሰባት ዘመናት” ሰባት ዓመታት ከሆኑ ሦስት ተኩሉ ዘመንም የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነው ማለት ነው። * (ዳንኤል 4:16, 25) አን አሜሪካን ትራንስሌሽን እንዲህ ይነበባል:- “እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።” የጄምስ ሞፋት ትርጉም “ለሦስት ዓመት ተኩል” ይላል። ራእይ 11:2-7 ስለ ተመሳሳይ ወቅት ሲናገር የአምላክ ምሥክሮች ማቅ ለብሰው ለ42 ወራት ወይም 1,260 ቀን እንደሚሰብኩና ከዚያ በኋላ እንደሚገደሉ ይገልጻል። ይህ ጊዜ የጀመረውና ያበቃው መቼ ነው?

29. ትንቢታዊው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ የጀመረው መቼና እንዴት ነው?

29 ለቅቡዓን ክርስቲያኖች አንደኛው የዓለም ጦርነት የፈተና ወቅት ነበር። በ1914 ማብቂያ ላይ ፈተና እንደሚደርስባቸው ይጠብቁ ነበር። እንዲያውም ለ1915 የተመረጠው የዓመት ጥቅስ “እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” የሚለው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበው ጥያቄ ነበር። ጥቅሱ በ⁠ማቴዎስ 20:22 ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም ከታኅሣሥ 1914 ጀምሮ እነዚያ ጥቂት ምሥክሮች “ማቅ ለብሰው” ሰብከዋል።

30. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል የተንገላቱት እንዴት ነበር?

30 ጦርነቱ እየተጋጋለ ሲመጣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። አንዳንዶቹ ወኅኒ ቤት ወርደዋል። በእንግሊዝ እንደነበረው ፍራንክ ፕላት እንዲሁም በካናዳ እንደነበረው ሮበርት ክሌግ ያሉ ግለሰቦች በጨካኝ ባለ ሥልጣኖች እጅ ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። ከየካቲት 12, 1918 ትንሽ ቀደም ብሎ የታተመው ያለቀለት ምሥጢር የተባለው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) ሰባተኛ ጥራዝ እንዲሁም ዘ ባይብል ስቱደንትስ መንዝሊ (እንግሊዝኛ) የተባለው ትራክት በዚህ ጊዜ በብሪቲሽ ዶሚኒየን ኦቭ ካናዳ በሕግ ታገደ። በቀጣዩ ወር የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ቢሮ የሰባተኛው ጥራዝ ሥርጭት ሕገ ወጥ ነው ሲል ውሳኔ አስተላለፈ። ውጤቱ ምን ነበር? መኖሪያ ቤቶች እየተበረበሩ ጽሑፎች ከመወረሳቸውም ሌላ የይሖዋ አገልጋዮች ታሠሩ!

31. ‘ዘመን፣ ዘመናትና የዘመን እኩሌታው’ የተፈጸመው መቼና እንዴት ነበር?

31 በአምላክ ቅቡዓን ላይ የሚፈጸመው በደል ሰኔ 21, 1918 ፕሬዚዳንት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ሌሎች በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ አባላት በሐሰት ክስ የረጅም ጊዜ እስር ተፈርዶባቸው ወኅኒ ሲወርዱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ‘ትንሹ ቀንድ’ “ዘመናትንና ሕግን” ለመለወጥ በማሰብ የተደራጀውን የስብከት ሥራ ገድሎት ነበር ለማለት ይቻላል። (ራእይ 11:7) በመሆኑም አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው ‘ዘመን፣ ዘመናትና የዘመናት እኩሌታ’ የተፈጸመው ሰኔ 1918 ነበር።

32. ‘ቅዱሳኑ’ በ‘ትንሹ ቀንድ’ ተጠራርገው አልጠፉም የምትለው ለምንድን ነው?

32 ይሁን እንጂ ‘ቅዱሳኑ’ ከ‘ትንሹ’ ቀንድ በደረሰባቸው መንገላታት ከምድር ገጽ አልጠፉም። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት እንደተነገረው ቅቡዓን ክርስቲያኖቹ ለጥቂት ጊዜ ያለ እንቅስቃሴ ከቆዩ በኋላ እንደገና ሕያው ሆነው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። (ራእይ 11:11-13) መጋቢት 26, 1919 የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንትና ባልደረቦቹ ከእስር ቤት የተለቀቁ ሲሆን ቆየት ብሎም ከቀረበባቸው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነዋል። ከዚያም ቅቡዓን ቀሪዎች ወዲያው ለተጨማሪ እንቅስቃሴ እንደገና ራሳቸውን ማደራጀት ጀመሩ። ይሁን እንጂ የ‘ትንሹ’ ቀንድ ዕጣ ምን ይሆን?

በዘመናት የሸመገለው፣ ችሎት ተቀምጧል

33. (ሀ) በዘመናት የሸመገለው ማን ነው? (ለ) በሰማያዊው ችሎት ‘የተከፈቱት መጻሕፍት’ ምንድን ናቸው?

33 ዳንኤል ስለ አራቱ አራዊት ከገለጸ በኋላ ዓይኑን ከአራተኛዋ አውሬ በሰማይ ወደሚደረገው ክንውን ይመልሳል። በዘመናት የሸመገለው በአንጸባራቂ ዙፋን ላይ ለዳኝነት ተቀምጦ ተመለከተ። በዘመናት የሸመገለ የተባለው ከይሖዋ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (መዝሙር 90:2) ሰማያዊው ችሎት ሲሰየም ዳንኤል ‘መጻሕፍት ተከፍተው’ አይቷል። (ዳንኤል 7:9, 10) ይሖዋ ከዘላለም ጀምሮ የነበረ በመሆኑ የሰውን ልጅ ታሪክ በመጽሐፍ የተጻፈ ያህል ጠንቅቆ ያውቃል። አራቱንም ምሳሌያዊ አራዊት በደንብ ያስተዋላቸው ሲሆን ራሱ ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ ፍርድ ሊሰጣቸው ይችላል።

34, 35. ‘ትንሹ ቀንድ’ እና በአራዊት የተመሰሉት ሌሎች ኃይሎች ምን ይጠብቃቸዋል?

34 ዳንኤል በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፤ አውሬይቱም እስክትገደል፣ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፣ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ።” (ዳንኤል 7:11, 12) መልአኩም ለዳንኤል “ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፣ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል” ሲል ነግሮታል።—ዳንኤል 7:26

35 ታላቁ ዳኛ ይሖዋ አምላክ በዚህ አምላክን በተሳደበውና ‘ቅዱሳኑን’ ባስጨነቀው ቀንድ ላይ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ያሳደደው የሮማ ግዛት የቀመሰው ዓይነት ፍርድ እንዲቀበል ያደርጋል። ግዛቱ አይቀጥልም። ከሮማ ግዛት የወጡት እንደ ቀንድ የተመሰሉት አነስተኛ ‘ነገሥታትም’ ቢሆኑ እንዲሁ አይቀጥሉም። ቀደም ሲል ከተነሡት እንደ አራዊት ካሉት ኃይሎች ስለወጡት አገዛዞችስ ምን ማለት ይቻላል? አስቀድሞ እንደተነገረው ዕድሜያቸው የሚረዝመው ‘እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ’ ድረስ ብቻ ነው። በግዛት ክልሎቻቸው እስከ ዛሬም ድረስ ሰዎች ይኖሩባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ኢራቅ የጥንቷን ባቢሎን ክልል ይዛለች። ፋርስ (ኢራን) እና ግሪክ ዛሬም አሉ። የእነዚያ የዓለም ኃይላት ቅሪቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ናቸው። እነዚህም መንግሥታት ቢሆኑ የመጨረሻው የዓለም ኃይል በሚጠፋበት ጊዜ አብረው ይደመሰሳሉ። ሁሉም ሰብዓዊ መስተዳድሮች ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ቀን በሚደረገው ታላቅ ጦርነት’ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። (ራእይ 16:14, 16) ታዲያ ዓለምን የሚገዛው ማን ይሆን?

ዘላቂ የሆነው አገዛዝ ቀርቧል!

36, 37. (ሀ) “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ማን ነው? በሰማያዊው ችሎት የታየውስ መቼና ለምን ዓላማ ነው? (ለ) በ1914 እዘአ ምን ተቋቁሟል?

36 ዳንኤል እንደሚከተለው ሲል በመገረም ተናግሯል:- “በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፣ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።” (ዳንኤል 7:13) ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ራሱን “የሰው ልጅ” ሲል ጠርቷል። ይህም ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ዝምድና የሚጠቁም ነበር። (ማቴዎስ 16:13፤ 25:31) ኢየሱስ በሳንሄድሪን ማለትም በአይሁዳውያኑ ከፍተኛ ሸንጎ ፊት ቀርቦ “ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:64) በመሆኑም በዳንኤል ራእይ ውስጥ ለሰው ዓይን በማይታይ መልክ እንደሚመጣና በይሖዋ ፊት የመቅረብ መብት እንዳለው ተደርጎ የተገለጸው፣ ትንሣኤ ያገኘውና ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ የሆነው መቼ ነው?

37 አምላክ ከንጉሥ ዳዊት ጋር ያደረገውን የመሰለ የመንግሥት ቃል ኪዳን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አድርጓል። (2 ሳሙኤል 7:11-16፤ ሉቃስ 22:28-30) በ1914 እዘአ ‘የተቀጠሩት የአሕዛብ ዘመናት’ ሲያበቁ ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ንግሥና ወራሽ እንደመሆኑ መጠን የመንግሥቱን ግዛት የመረከብ መብት ነበረው። የዳንኤል ትንቢታዊ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” (ዳንኤል 7:14) በዚህ መንገድ መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ በ1914 ተቋቋመ። ይሁን እንጂ የግዛቱ ተካፋይ የሆኑ ሌሎችም አሉ።

38, 39. የዓለምን ዘላለማዊ አገዛዝ የሚረከበው ማን ይሆናል?

38 መልአኩ “የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 7:18, 22, 27) ዋነኛው ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሥራ 3:14፤ 4:27, 30) በግዛቱ የሚካፈሉት ሌሎቹ ‘ቅዱሳን’ ደግሞ በመንፈስ የተቀቡት 144,000 የታመኑ ክርስቲያኖች ናቸው። እነዚህ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች ይሆናሉ። (ሮሜ 1:7፤ 8:17፤ 2 ተሰሎንቄ 1:5፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) በሰማያዊቷ ጽዮን ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት አግኝተው ከሞት ይነሣሉ። (ራእይ 2:10፤ 14:1፤ 20:6) በመሆኑም የሰውን ዘር ዓለም የሚገዙት ክርስቶስ ኢየሱስና ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው።

39 የሰው ልጅ የተባለውንና ትንሣኤ ያገኙትን የሌሎች ‘ቅዱሳን’ አገዛዝ በተመለከተ የአምላክ መልአክ እንዲህ ብሏል:- “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፣ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።” (ዳንኤል 7:27) ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በዚያች መንግሥት ሥር የሚያገኙት በረከት እንዴት ድንቅ ነው!

40. የዳንኤልን ሕልምና ራእይ በትኩረት በመከታተላችን ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

40 ዳንኤል፣ አምላክ ያሳየው ራእይ ድንቅ ፍጻሜ ምን እንደሚሆን የሚያውቀው ነገር አልነበረም። እንዲህ ብሏል:- “የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፣ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ።” (ዳንኤል 7:28) እኛ ግን የምንኖረው ዳንኤል የተመለከተው ነገር ፍጻሜ ምን እንደሆነ መረዳት በምንችልበት ዘመን ነው። ይህንን ትንቢት በትኩረት መከታተል እምነታችንን የሚያጠናክርልንና የይሖዋ መሲሐዊ መንግሥት ዓለምን እንደሚገዛ ያለንን ጽኑ እምነት የሚያሳድግልን ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ነጥቡ ግልጽ እንዲሆንና ድግግሞሽን ለማስወገድ ስንል ማብራሪያ የተሰጠባቸውን በ⁠ዳንኤል 7:15-28 ላይ የሚገኙትን ቁጥሮች በ⁠ዳንኤል 7:1-14 ላይ የሚገኙትን ራእይዎች አንድ በአንድ ስናብራራ አጣምረን እናቀርባቸዋለን።

^ አን.7 የዚህን መጽሐፍ 4ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

^ አን.28 የዚህን መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

ምን አስተውለሃል?

• ‘ከባሕር የሚወጡት አራቱ ግዙፍ አራዊት’ እያንዳንዳቸው ምን ያመለክታሉ?

• ‘ትንሹ’ ቀንድ ማንን ያቀፈ ነው?

• በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ‘ቅዱሳኑ’ በትንሹ ቀንድ መንገላታት የደረሰባቸው እንዴት ነው?

• ምሳሌያዊው ትንሽ ቀንድና ሌሎቹ አውሬ መሰል ኃይሎች ምን ይጠብቃቸዋል?

• ስለ ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት’ የሚናገረውን የዳንኤልን ሕልምና ራእይ በትኩረት በመከታተልህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 149-152 የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ታጋሽ ንጉሥ

በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረ አንድ ግሪካዊ ጸሐፊ ታጋሽ የሆነ የተዋጣለት ንጉሥ ነው ሲል አውስቶለታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ‘ቅቡዕ’ እንዲሁም ‘ከፀሐይ መውጫ’ የሚመጣ ‘ነጣቂ ወፍ’ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (ኢሳይያስ 45:1፤ 46:11 NW) ይህ የፋርሱ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ ነው።

ቂሮስ ስሙን የማስጠራት ግስጋሴውን የጀመረው በጥንቷ ፋርስ በምትገኘው አንሻን በተባለች ከተማ ወይም አውራጃ በ560/559 ከዘአበ በአባቱ በቀዳማዊ ካምቢሰስ ዙፋን ላይ በተቀመጠ ጊዜ ነበር። በወቅቱ አንሻን በሜዶናዊው ንጉሥ አስታይጂዝ የምትተዳደር ራስ ገዝ ከተማ ነበረች። ቂሮስ በሜዶናውያኑ አገዛዝ ላይ በማመፅ ሲነሣ የአስታይጂዝ ሠራዊት ከድቶ ከእርሱ ጋር ስለወገነ ፈጣን ድል ተቀዳጀ። ከዚያም ቂሮስ የሜዶናውያኑን ሙሉ ድጋፍ አገኘ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በእርሱ አመራር አንድ ላይ አብረው ሲዋጉ ቆይተዋል። በዚህ መንገድ ቀስ በቀስ ግዛቱን እያሰፋ ከኢጂያን ባሕር እስከ ኢንደስ ወንዝ ድረስ ያለውን ክልል የጠቀለለው የሜዶ ፋርስ ግዛት ተመሠረተ።—ካርታውን ተመልከት።

ቂሮስ የሜዶንና የፋርስን ጥምር ኃይል እየመራ አወዛጋቢ በነበረው ቦታ የበላይነቱን ለማረጋገጥ ተንቀሳቀሰ። ይህ ቦታ የልድያውያን ንጉሥ ክሬሰስ ወደ ሜዶናውያን ግዛት እየተስፋፋበት የነበረው የሜዶን ምዕራባዊ ክፍል ነው። በትንሿ እስያ ወደምትገኘው የልድያውያን ግዛት ምሥራቃዊ ድንበር በመግፋት ቂሮስ ክሬሰስን ድል አድርጎ መዲናውን ሳርዲስን ተቆጣጠረ። ከዚያም ቂሮስ የአይኦኒያን ከተሞችን በማንበርከክ ትንሿን እስያ በሙሉ በሜዶ ፋርስ ግዛት ሥር ጠቀለለ። በዚህ መንገድ የባቢሎንና የንጉሥዋ የናቦኒደስ ዋነኛ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ከዚያም ቂሮስ ከኃያሏ ባቢሎን ጋር ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ተዘጋጀ። ከዚህ ጊዜ አንስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ይሖዋ ወደ ሁለት መቶ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት በስሙ ጠርቶ ቂሮስ የሚባል ገዥ ባቢሎንን እንደሚገለብጥና አይሁዳውያንን ከምርኮ ነፃ እንደሚያወጣ ተናግሮ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎችም ቂሮስ በይሖዋ ‘የተቀባ’ መሆኑን የሚናገሩት በዚህ መንገድ አስቀድሞ መሾሙን ለማመልከት ነው።—ኢሳይያስ 44:26-28

ቂሮስ በ539 ከዘአበ በባቢሎን ላይ ሲዘምት ተልእኮው ቀላል አልነበረም። ዙሪያዋን ግዙፍ ቅጥር ያላትና ከኤፍራጥስ ወንዝ በሚፈስስ ውኃ በተሞላ ሰፊና ጥልቅ የውኃ ማውረጃ የተከበበችው ከተማ የምትደፈር አትመስልም ነበር። የኤፍራጥስ ወንዝ በባቢሎን መካከል በሚያልፍበት ዳርቻ ሁሉ ትላልቅ የነሐስ በሮች ያሉት እንደ ተራራ የተቆለለ ቅጥር ነበር። ታዲያ ቂሮስ ባቢሎንን ሊቆጣጠር የሚችለው እንዴት ነው?

ከአንድ መቶ ዘመን ከሚበልጥ ጊዜ ቀደም ብሎ ይሖዋ “ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ” ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 50:38) ልክ በዚህ ትንቢት መሠረት ቂሮስ የኤፍራጥስን ውኃ አቅጣጫ በማስቀየር ከባቢሎን በስተ ሰሜን ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኝ ቦታ እንዲፈስስ አደረገ። ሠራዊቱ ውኃው ተኝቶበት በነበረው ቦታ ላይ እየዳከረ ተዳፋቱን ወጥቶ ወደ ቅጥሩ ካመራ በኋላ የነሐስ በሮቿ ክፍት ተረስተው ስለነበር በቀላሉ ወደ ከተማይቱ ገባ። በሚፈልገው ነገር ላይ ድንገት ጉብ እንደሚል ‘ነጣቂ ወፍ’ ‘ከፀሐይ መውጫ’ ማለትም ከምሥራቅ የመጣው ይህ ገዥ ባቢሎንን በአንድ ሌሊት ተቆጣጠራት!

በባቢሎን ለነበሩት አይሁዳውያን የቂሮስ ድል ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረው ነፃ የሚወጡበት ጊዜ እንደደረሰና ትውልድ አገራቸው ባድማ ሆና የቆየችበት 70 ዓመት ማብቃቱን የሚያበስር ነበር። ቂሮስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ የሚፈቅድ ትእዛዝ ሲያወጣ ምንኛ ተደስተው ይሆን! ከዚህም በላይ ቂሮስ፣ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን አግዞት የነበረውን ውድ ንዋየ ቅድሳት የመለሰላቸው ሲሆን የግንባታ እንጨት ከሊባኖስ እንዲያስገቡ ንጉሣዊ ፈቃድ ሰጥቷቸውና የግንባታው ወጪም በንጉሡ ቤት እንዲሸፈን ፈቅዶ ነበር።—ዕዝራ 1:1-11፤ 6:3-5

በጥቅሉ ሲታይ ቂሮስ ድል ካደረጋቸው ሕዝቦች ጋር በነበረው ግንኙነት የሚመራበት ፖሊሲ ምሕረትና ሆደ ሰፊነት የተንጸባረቀበት ነበር። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንዲያንጸባርቅ ምክንያት የሆነው አንዱ ነገር ሃይማኖቱ ሊሆን ይችላል። ቂሮስ የፋርሳዊውን ነቢይ የዞራስተርን ትምህርት የሚከተልና የመልካም ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ነው የሚባለውን አምላክ አሁራ ማዝዳን የሚያመልክ ሰው እንደነበር ይታመናል። ዘ ዞራስተሪያን ትራዲሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ፋርሃ ሜር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ዞራስተር አምላክ የመልካም ምግባር ፍጹም ምሳሌ እንደሆነ ያስተምር ነበር። ለሕዝቡ የሚነግራቸው አሁራ ማዝዳ ተበቃይ ሳይሆን ፍትሐዊ ነው፤ በመሆኑም የሚወደድ እንጂ የሚፈራ አይደለም እያለ ነበር።” የሥነ ምግባር ፍጹም ምሳሌና ፍትሐዊ የሆነ አምላክ ማምለኩ በቂሮስ ግብረገብነት ላይ ተጽዕኖ ሳይኖረውና ለጋስ እንዲሆን እንዲሁም መልካም ሥራ እንዲሠራ ሳያበረታታው አልቀረም።

ይሁን እንጂ ንጉሡ የባቢሎንን የአየር ጠባይ አልቻለውም። የበጋው ንዳድ ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ሆኖበት ነበር። በመሆኑም ባቢሎን የግዛቱ ንጉሣዊ መቀመጫ እንዲሁም የሃይማኖታዊና ባሕላዊ ማዕከል ብትሆንም አልፎ አልፎ ብቻ የክረምት መቀመጫው ሆና ታገለግል ነበር። እንዲያውም ቂሮስ ባቢሎንን ድል ካደረገ በኋላ ወዲያውኑ ከአልዋንድ ተራራ ግርጌ ከባሕር ወለል በላይ 1,900 ሜትር ከፍታ ላይ ወደምትገኘው የበጋ መቀመጫው ወደሆነችው መዲና አሕምታ ተመልሷል። በዚያ ያለውን ቀዝቀዝ ያለ ክረምትና አስደሳች የበጋ ወቅት ይወደው ነበር። ከዚህም ሌላ ቂሮስ ከአሕምታ 650 ኪሎ ሜትር ርቃ (ፐርሴፐለስ አቅራቢያ) በምትገኘው በቀድሞዋ መዲናው በፐሰርገዲ ድንቅ ቤተ መንግሥት ገንብቷል። በዚያ ያለው መኖሪያ ከግርግር ነፃ ሆኖ ጊዜውን የሚያሳልፍበት ቦታ ሆኖለታል።

ቂሮስ ጀግና ድል አድራጊና ታጋሽ ንጉሥ የሚል ስም አትርፏል። በ530 ከዘአበ በወታደራዊ ዘመቻ ላይ እያለ ሲሞት የ30 ዓመት ግዛቱ አከተመ። ልጁ ዳግማዊ ካምቢሰስ በእርሱ ፋንታ በፋርስ ላይ ነግሷል።

ምን አስተውለሃል?

• የፋርሱ ቂሮስ በይሖዋ ‘የተቀባ’ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

• ቂሮስ ለይሖዋ ሕዝቦች ምን ጠቃሚ ነገር አከናውኗል?

• ቂሮስ ድል ያደረጋቸውን ሕዝቦች የሚይዝበት መንገድ ምን ይመስላል?

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሜዶ ፋርስ ግዛት

መቄዶንያ

ሜምፊስ

ግብጽ

ኢትዮጵያ

ኢየሩሳሌም

ባቢሎን

አሕምታ

ሱሳ

ፐርሴፐለስ

ሕንድ

[ሥዕል]

በፐሰርገዲ የሚገኘው የቂሮስ መቃብር

[ሥዕል]

በፐሰርገዲ የሚገኘው የቂሮስ ውቅር ምስል

[ከገጽ 153-161 የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዓለምን ድል አድርጎ የተቆጣጠረ ወጣት ንጉሥ

ወደ 2,300 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት ወርቃማ ፀጉር ያለውና ዕድሜው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ የጦር ጄኔራል በሜድትራንያን ባሕር ዳርቻ ቆሟል። ዓይኖቹ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ደሴት ላይ ተተክለዋል። ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ በመከልከሉ እጅግ የተቆጣው ጄኔራል ከተማይቱን በኃይል ለማንበርከክ ቆርጦ ተነሥቷል። ጥቃት ለመሰንዘር ያቀደው እንዴት ነው? ወደ ደሴቲቱ የሚያደርስ መተላለፊያ በመገንባት ጦሩን በከተማዋ ላይ በማዝመት ነው። የመተላለፊያው ግንባታ ተጀምሯል።

ይሁን እንጂ ከታላቁ የፋርስ ንጉሥ የመጣ መልእክት የወጣቱን ጄኔራል ትኩረት ሰረቀው። ሰላም ለመፍጠር የጓጓው የፋርስ ገዥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው እጅ መንሻ ለመስጠት ሐሳብ አቀረበ:- 10,000 ታላንት ወርቅ እንደሚሰጠው (ዛሬ ባለው ዋጋ ሲተመን ከ2 ቢልዮን ዶላር በላይ ነው)፣ ሴት ልጁን እንደሚድርለት እንዲሁም በፋርስ ግዛት ምዕራባዊ ክፍል ላይ በሙሉ ገዥ እንደሚያደርገው ቃል ገባ። ይህ ሁሉ ስጦታ የቀረበለት ጄኔራሉ ማርኮ የያዘውን የንጉሡን ቤተሰብ እንዲለቅ ነበር።

ይህን ስጦታ የመቀበልና ያለመቀበል ምርጫ ውስጥ የገባው የጦር መሪ የመቄዶንያው ሳልሳዊ እስክንድር ነበር። ስጦታውን መቀበል ይኖርበታልን? “ለጥንቱ ዓለም ይህ የማይገኝ አጋጣሚ ነበር” ሲሉ ታሪክ ጸሐፊው ኡልሪክ ቪልን ተናግረዋል። “ውሳኔው የሚኖረው ውጤት ከመካከለኛው ዘመን አልፎ እስከ እኛ ጊዜ ድረስ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ላይ ይንጸባረቃል።” እስክንድር ምን ምላሽ እንደሰጠ ከመመልከታችን በፊት ወደዚህ ወሳኝ ወቅት ያደረሰው ነገር ምን እንደሆነ እንመልከት።

ድል አድራጊ ንጉሥ እንዲሆን ያበቃው ነገር

እስክንድር የተወለደው በ356 ከዘአበ በፔላ መቄዶንያ ነበር። አባቱ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ ሲሆን እናቱ ደግሞ ኦሊምፒየስ ነበረች። ኦሊምፒየስ፣ የመቄዶንያ ነገሥታት የግሪክ አምላክ የሆነው የዙስ ልጅ የኸርኩለስ ዝርያዎች መሆናቸውን ለእስክንድር ታስተምረው ነበር። እንደ ኦሊምፒየስ አባባል ከሆነ የእስክንድር ቅድመ አያት ሊያድ በሚባለው የሆሜር ግጥም ውስጥ የተገለጸው ጀግና አኪሊዝ ነው። ወላጆቹ ድል የማድረግና ንጉሣዊ ክብር የመቀዳጀት ምኞት ስለቀረጹበት ወጣቱ እስክንድር ለሌሎች ነገሮች እምብዛም ፍላጎት አልነበረውም። በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ወቅት በሩጫ እንዲወዳደር ተጠይቆ ከነገሥታት ጋር እንዲሮጥ የሚደረግ ከሆነ ለመወዳደር ፈቃደኛ እንደሚሆን ተናግሯል። ምኞቱ ከአባቱ የበለጡ ነገሮችን ማከናወንና በሥራው ውጤት ከበሬታን ማትረፍ ነበር።

እስክንድር 13 ዓመት ሲሞላው ከግሪኩ ፈላስፋ አርስቶትል የመማር አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ሲሆን ከእርሱ መማሩ ስለ ፍልስፍና፣ ሕክምናና ሳይንስ ጉጉት እንዲያድርበት አድርጎታል። የአርስቶትል የፍልስፍና ትምህርቶች የእስክንድርን አስተሳሰብ የቀረጹት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው። የ20ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ የሆኑት በርትረንድ ራስል እንዳሉት ከሆነ “ሁለቱ ሰዎች የተስማሙባቸው ነገሮች ብዙም አይደሉም ማለቱ ሳይሻል አይቀርም። የአርስቶትል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የግሪክን ራስ ገዝ ከተሞች መሠረት ያደረገ ሲሆን ይህ ዓይነቱ አሠራር እየተዳከመ ሄዶ ነበር።” የትናንሽ ራስ ገዝ ከተሞች መስተዳድር የሚለው ንድፈ ሐሳብ የተማከለ ታላቅ ግዛት ለመመሥረት ለሚፈልገው መስፍን የሚዋጥለት ነገር አልነበረም። ከዚህም ሌላ እስክንድር ግሪካውያን ያልሆኑትን ሰዎች እንደ ባርያ መያዝ የሚለውን የአርስቶትል መርህ የሚያየው በጥርጣሬ ዓይን ነበር። ምክንያቱም እርሱ የሚያልመው በድል አድራጊዎቹና ድል በተነሱት ሰዎች መካከል ወዳጅነት የሰፈነበት ሰፊ ግዛት ለመመሥረት ነበር።

ይሁን እንጂ አርስቶትል የእስክንድርን የማንበብና የመማር ፍላጎት እንዳሳደገለት ምንም ጥርጥር የለውም። እስክንድር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማንበብ የሚወድ ሰው የነበረ ሲሆን በተለይ ለሆሜር ጽሑፎች ልዩ ፍቅር ነበረው። ሊያድን ማለትም 15,693 ስንኝ ያለውን ግጥም በቃሉ ይዞት እንደነበር ይነገርለታል።

በ340 ከዘአበ የ16 ዓመቱ መስፍን አባቱ ባለመኖሩ መቄዶንያን ለማስተዳደር ወደ ፔላ ሲሄድ ከአርስቶትል ያገኘው የነበረው ትምህርት ተቋረጠ። አልጋ ወራሹ መስፍን በወታደራዊ ጀብዱ ስሙን ለማስጠራት ብዙ ጊዜ አላጠፋም። ወዲያውኑ ዓመፀኛ የነበረውን ሜዴ የሚባለውን የትሬስ ጎሳ ፀጥ በማሰኘት ትልቋን ከተማቸውን በወረራ ይዞ በራሱ ስም አሌክሳንደሮፖሊስ ሲል ሰይሟታል። ይህም ፊሊፕን ደስ አሰኝቶት ነበር።

በኃይል ማንበርከኩን ቀጠለ

በ336 ከዘአበ ፊሊፕ በመገደሉ የ20 ዓመቱ እስክንድር የመቄዶንያን ዙፋን ወረሰ። እስክንድር በ334 ከዘአበ የጸደይ ወራት በሄለስፓንት (በዛሬዋ ዳርደኔልዝ) በኩል በቁጥር አነስተኛ የሆነ ነገር ግን ጥሩ የውጊያ ብቃት ያለው 30,000 እግረኛ ጦርና 5,000 ፈረሰኛ ይዞ ወደ እስያ በመግባት በኃይል የማንበርከክ ዘመቻውን ጀመረ። ከሠራዊቱ ጋር አብረው የሚጓዙ መሐንዲሶች፣ ቀያሾችና፣ የግንባታ ንድፍ አውጪዎች እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊዎች ነበሩ።

በትንሿ እስያ ሰሜን ምዕራብ ማዕዘን (በዛሬዋ ቱርክ) አካባቢ በሚገኘው የግረናይከስ ወንዝ እስክንድር ከፋርሳውያን ጋር የመጀመሪያውን ውጊያ በድል ተወጣ። በዚያ የበጋ ወቅት የትንሿን እስያ ምዕራባዊ ክፍል ድል አድርጎ ተቆጣጠረ። በሚቀጥለው የበልግ ወቅት በትንሿ እስያ ደቡብ ምሥራቅ ማዕዘን ላይ በምትገኘው በኢሰስ ከፋርሳውያን ጋር ሁለተኛውን ወሳኝ ውጊያ አደረገ። ታላቁ የፋርስ ንጉሥ ሳልሳዊ ዳርዮስ፣ ግማሽ ሚልዮን የሚያክል ሠራዊት ይዞ እስክንድርን ለመግጠም ወደዚያ ወርዶ ነበር። ዳርዮስ ድል እንደሚያደርግ ፍጹም እርግጠኛ ስለነበር እናቱ፣ ሚስቱና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ለሚቀዳጀው ታላቅ ድል የዓይን ምሥክር እንዲሆኑ ሲል እዚያ ድረስ ይዟቸው መጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ፋርሳውያን መቄዶናውያኑ ለሰነዘሩት ድንገተኛና ሞገደኛ ጥቃት አልተዘጋጁም ነበር። የፋርስ ሠራዊት በእስክንድር ሠራዊት ከፍተኛ ሽንፈት ገጠመው፤ ዳርዮስም ቤተሰቡን በእስክንድር እጅ ትቶ ሸሸ።

እስክንድር የሸሹትን ፋርሳውያን ከማሳደድ ይልቅ ብርቱ የሆነው የፋርስ ሠራዊት መቀመጫ የነበሩትን ቦታዎች ድል በማድረግ በስተ ደቡብ በኩል ወደ ሜድትራንያን ገሰገሰ። ይሁን እንጂ የደሴት ከተማ የሆነችው ጢሮስ ወረራውን ተቋቋመች። ከተማዋን ድል አድርጎ ለመያዝ ቆርጦ የተነሣው እስክንድር ለሰባት ወራት የዘለቀ ከበባ አካሄደ። ቀደም ሲል የተገለጸው የዳርዮስ የሰላም ድርድር የቀረበለት በዚህ ወቅት ነበር። የቀረበለት ነገር እጅግ የሚያባብል ከመሆኑ የተነሣ የታመነው የእስክንድር አማካሪ ፓርሜኒዮ ‘እኔ እስክንድርን ብሆን ኖሮ እሺ ብዬ እቀበል ነበር’ እንዳለ ይነገራል። ይሁን እንጂ ወጣቱ ጄኔራል ‘እኔም ፓርሜኒዮን ብሆን ኖሮ እቀበል ነበር’ በማለት መልሶለታል። እስክንድር ለመደራደር አሻፈረኝ ብሎ በከበባው በመግፋት በሐምሌ 332 ከዘአበ ላይ ያችን ኩሩ የባሕር ላይ እመቤት እንዳልነበረች አደረጋት።

እስክንድር በሰላም እጅዋን የሰጠችውን ኢየሩሳሌምን አልፎ በስተ ደቡብ ወደ ጋዛ ገሰገሰ። የፋርስ አገዛዝ ያንገፈገፋቸው ግብጻውያን እንደ ነፃ አውጪ አድርገው እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት። በሜምፊስ ተገኝቶ ኤፕስ ለሚባለው ጣዖት ኮርማ በመሠዋት ግብጻውያን ካህናትን ደስ አሰኝቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ በትምህርት ማዕከልነት አቴንስን መፎካከር የጀመረችውንና እስከዛሬም በእሱ ስም የምትጠራውን የእስክንድርያ ከተማንም ቆርቁሯል።

ከዚያም እስክንድር ወደ ሰሜን ምስራቅ በማቅናት በፍልስጤም ምድር አድርጎ ወደ ጤግሮስ ወንዝ አመራ። በ331 ከዘአበ ከፈራረሰችው ነነዌ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ጋውጋሜላ ከፋርሳውያን ጋር ሦስተኛውን ከባድ ጦርነት ገጠመ። በዚህ ወቅት 47,000 ወታደሮችን ያቀፈው የእስክንድር ሠራዊት ቢያንስ ቢያንስ 250,000 ወታደሮች ባሉት እንደገና በተደራጀው የፋርስ ሠራዊት ላይ የበላይነት አግኝቷል! ዳርዮስ ከዚህ ውጊያ ሸሽቶ ቢያመልጥም ከጊዜ በኋላ በራሱ ሰዎች ተገድሏል።

አንጸባራቂ ድል የተቀዳጀው እስክንድር ወደ ደቡብ ፊቱን በመመለስ የፋርሳውያን የክረምት መቀመጫ የሆነችውን የባቢሎን ከተማ ተቆጣጠረ። በሱሳና በፐርሴፐለስ የሚገኙትን ዋና ከተማዎች የያዘ ሲሆን ግዙፍ የሆነውን የፋርሳውያን የሀብት ማከማቻ በመያዝ ታላቁን የዜርሰስን ቤተ መንግሥት በእሳት አቃጥሏል። በመጨረሻም በአሕምታ ያለችው መዲና በእርሱ ቁጥጥር ሥር ወደቀች። ከዚያም ፈጣኑ ባለ ድል በምሥራቅ በኩል የዛሬዋ ፓኪስታን ባለችበት ቦታ እስከሚገኘው እስከ ኢንደስ ወንዝ ድረስ በመሄድ የቀረውን የፋርስ ግዛት በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር አደረገ።

እስክንድር የፋርስ ግዛት ክልል የሆነችውን ታክሲልን በሚያዋስነው አካባቢ የኢንደስን ወንዝ ሲሻገር የሕንዱ ንጉሥ ፖረስ በእጅጉ ተቋቋመው። እስክንድር ሰኔ 326 ከዘአበ ከእርሱ ጋር አራተኛውንና የመጨረሻውን ታላቅ ውጊያ አደረገ። የፖረስ ሠራዊት 35,000 ወታደሮችንና 200 ዝሆኖችን ያካተተ ሲሆን ዝሆኖቹ የመቄዶናውያኑን ፈረሶች አስደንብረዋቸው ነበር። ውጊያው በጣም ኃይለኛና አሰቃቂ ቢሆንም የእስክንድር ኃይሎች በድል ተወጡት። ፖረስ በሰላም እጁን በመስጠት የእስክንድር አጋር ሆነ።

የመቄዶናውያኑ ኃይል ወደ እስያ ከዘለቀ ስምንት ዓመታት አልፈዋል። ወታደሮቹም ዝለውና የትውልድ አገራቸው ናፍቋቸው ነበር። ከፖረስ ጋር በተደረገው ኃይለኛ ውጊያ ሃሞታቸው የፈሰሰው ወታደሮች ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ፈለጉ። እስክንድር በመጀመሪያ አመንትቶ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ቃላቸውን ሰማ። ግሪክ በእርግጥም የዓለም ኃይል ሆና ነበር። ድል በተደረጉት አካባቢዎች በሙሉ የግሪካውያን ማኅበረሰቦች ተቋቁመው ስለነበር የግሪክ ቋንቋና ባሕል በግዛቱ በሙሉ ተስፋፍቶ ነበር።

ከድሉ በስተጀርባ ያለው ሰው

ለእነዚሁ ሁሉ ዓመታት የመቄዶናውያኑን ሠራዊት አንድ አድርጎ ያቆየው ነገር የእስክንድር የግል ባሕርይ ነበር። እስክንድር ከውጊያ በኋላ ቁስለኞችን የመጎብኘትና የደረሰባቸውን ጉዳት መጠን የመመልከት እንዲሁም ለሠሩት ጀግንነት በማመስገን በፈጸሙት ጀብዱ መጠን የገንዘብ ሽልማት የመስጠት ልማድ ነበረው። በፍልሚያው መሀል የወደቁት ወታደሮች አስከሬን በክብር የሚያርፍበት ደማቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ይካሄድ ነበር። የተሰዉት ወንዶች ወላጆች እና ልጆች ከማንኛውም ዓይነት ቀረጥና አገልግሎት ነፃ ይደረጉ ነበር። እስክንድር ከውጊያ በኋላ ለለውጥ ያህል የተለያዩ ጨዋታዎችና ውድድሮች እንዲካሄዱ ያደርጋል። እንዲያውም በአንድ ወቅት በዚያው ሰሞን ላገቡት ወንዶች ከሚስቶቻቸው ጋር የበጋውን ወራት በመቄዶንያ እንዲያሳልፉ ፈቃድ ሰጥቷቸው ነበር። እንዲህ የመሳሰለው ድርጊቱ አብረውት በተሰለፉት ዘንድ ፍቅርንና አድናቆትን እንዲያተርፍ አስችሎታል።

እስክንድር የባክትሪያዋን ንግሥት ሮክሳናን ማግባቱን አስመልክተው ሲጽፉ አንድ ግሪካዊ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ጋብቻ ለመመሥረት ያበቃቸው ነገር ፍቅር እንደነበር ግልጽ ቢሆንም እግረ መንገዱን ከዓላማውም ጋር ተዛምዶ ነበረው። ምክንያቱም ከእነርሱ መካከል ሚስት መምረጡ ድል ለተደረጉት ሰዎች ትልቅ ክብር ከመሆኑም ሌላ ከሁሉ ይበልጥ ደርባባ የሆነው ይህ ሰው የተሸነፈበት ብቸኛ ፍቅር ይህ ሆኖ ሳለ በክብርና በሕጋዊ መንገድ እስኪያገኛት ድረስ ወደ እርሷ አለመድረሱ ለእርሱ እጅግ ጥልቅ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓል።”

እስክንድር የሌሎችንም ትዳር ያከብር ነበር። የዳርዮስ ሚስት የእርሱ ምርኮኛ ብትሆንም በክብር እንድትያዝ አድርጓል። በተመሳሳይም ሁለት የመቄዶንያ ወታደሮች የአንዳንድ እንግዶችን ሚስቶች ማማገጣቸውን ሲሰማ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በሞት እንዲቀጡ አዝዟል።

ልክ እንደ እናቱ እንደ ኦሊምፒየስ እስክንድርም እጅግ ሃይማኖተኛ ሰው ነበር። ከማንኛውም ውጊያ በፊትና በኋላ መሥዋዕት ያቀርብ የነበረ ሲሆን ስለ አንዳንድ የገድ ምልክቶችም ጠንቋዮቹን ያማክር ነበር። በተጨማሪም በሊቢያ ወደሚገኘው የአሞን መቅደስ ሄዶ ምክር ጠይቋል። በባቢሎንም እንዲሁ በተለይ ለባቢሎናውያኑ አምላክ ቤል (ማርዱክ) መሥዋዕትን ማቅረብን በተመለከተ ከለዳውያኑ የነበራቸውን መመሪያ ተከትሏል።

እስክንድር በአመጋገብ ልማዱ ረገድ ልከኛ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ከልክ በላይ መጠጣት ጀምሮ ነበር። እያንዳንዷን ብርጭቆ ጨብጦ ረጅም ታሪክ ያወራና ስላገኛቸው ድሎች ጉራውን ይነዛ ነበር። እስክንድር በታሪኩ ላይ ጥቁር ነጥብ ከጣሉበት ነገሮች መካከል አንዱ ወዳጁን ክሊተስን በመጠጥ ግፊት በቁጣ ገንፍሎ መግደሉ ነው። ይሁን እንጂ እስክንድር ራሱን እጅግ የሚኮንን ሰው ስለነበር ለሦስት ቀናት ምንም እህል ውኃ ሳይቀምስ አልጋ ውስጥ ቆይቷል። በመጨረሻም ምግብ እንዲበላ ያሳመኑት ጓደኞቹ ናቸው።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እስክንድር ክብር ለማግኘት የነበረው ከፍተኛ ጉጉት ሌሎች መጥፎ ባሕርያትን እንዲያሳይ አድርጎታል። የሐሰት ክሶችን እንዲሁ አምኖ በመቀበል አሰቃቂ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሮ ነበር። ለምሳሌ ያህል ፊሎትስ ሕይወትህን ለማጥፋት ሞክሯል የሚል ወሬ ስለሰማ እርሱንና አባቱን ፓርሜኒዮን ማለትም እጅግ ያምነው የነበረውን አማካሪውን አስገድሏል።

የእስክንድር ሽንፈት

እስክንድር ወደ ባቢሎን ከተመለሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የለከፈው የወባ በሽታ አልለቀቀውም ነበር። ለ32 ዓመታት ከ8 ወር ብቻ ከኖረ በኋላ ሰኔ 13 ቀን 323 ከዘአበ ለማይገፋው ባላጋራ ለሞት እጁን ሰጥቷል።

ሁኔታው አንዳንድ የሕንድ ጠቢባን እንዳሉት ነው:- “አቤቱ ንጉሥ እስክንድር ሆይ፣ እያንዳንዱ ሰው ከዚህች ከቆምንባት መሬት የበለጠ መሬት አይዝም። እዚህና እዚያ የምትባክንና እረፍት የሌለህ ሰው ሆነህ ከአገርህ ርቀህ ይህችን ምድር በማሰስ ራስህ ተቸግረህ ሌሎችን የምታስቸግር ከመሆንህ በቀር አንተም እንደ ሌላው ሰው ነህ። አንድ ቀን ስትሞት ግን የምትቀበረው ስንዝር በማትሞላ መሬት ላይ ይሆናል።”

ምን አስተውለሃል?

• የታላቁ እስክንድር አስተዳደግ ምን ይመስላል?

• እስክንድር የመቄዶንያን ዙፋን ከጨበጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ምን ዘመቻ ጀመረ?

• አንዳንዶቹን የእስክንድር ድሎች ግለጽ።

• ስለ እስክንድር የግል ባሕርይ ምን ማለት ይቻላል?

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

እስክንድር ድል አድርጎ የተቆጣጠራቸው ግዛቶች

መቄዶንያ

ግብጽ

ባቢሎን

የኢንደስ ወንዝ

[ሥዕል]

እስክንድር

[ሥዕል]

አርስቶትልና ተማሪው እስክንድር

[ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[ሥዕል]

የታላቁ እስክንድርን ምስል ይዟል የሚባልለት ሜዳልያ

[በገጽ 162 እና 163 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሰፊ የነበረው ግዛት ተከፋፈለ

መጽሐፍ ቅዱስ የታላቁ እስክንድር መንግሥት እንደሚከፋፈል ‘ለዘሩ ግን እንደማይሆን’ ትንቢት ተናግሯል። (ዳንኤል 11:3, 4) በዚህም መሠረት እስክንድር በ323 ከዘአበ በሞት ከተቀጨ በኋላ በነበሩት 14 ዓመታት ውስጥ ሕጋዊ ልጁ እስክንድር አራተኛና ከሕጋዊ ሚስቱ የማይወለደው ልጁ ሄራክለስ ተገድለዋል።

በ301 ከዘአበ አራት የእስክንድር ጄኔራሎች አዛዣቸው የገነባውን ሰፊ ግዛት ተከፋፍለው ሥልጣን ተቆናጠጡ። ጄኔራል ካሳንደር መቄዶንያንና ግሪክን ተቆጣጠረ። ጄኔራል ላይሲመከስ ትንሿን እስያንና ትሬስን ያዘ። ቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ደግሞ መሶጴጣሚያንና ሶርያን ወሰደ። እንዲሁም ቶሌሚ ላገስ ወይም ቀዳማዊ ቶሌሚ ግብጽንና ፍልስጤምን ይገዛ ነበር። በዚህ መንገድ ከእስክንድር ታላቅ መንግሥት 4 ሄለናዊ ወይም የግሪክ መንግሥታት ተነሡ።

ከአራቱ ሄለናዊ መንግሥታት መካከል ዕድሜው አጭር የነበረው የካሳንደር አገዛዝ ነው። ካሳንደር ወደ ሥልጣን ከወጣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዙፋኑን የሚረከቡ ወንዶች እየተመናመኑ ሄዱ። ከዚያም በ285 ከዘአበ ላይሲመከስ በአውሮፓ በኩል ያለውን የተወሰነ የግሪክ ግዛት ያዘ። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ ላይሲመከስ ከቀዳማዊ ሰሉከስ ናይኬተር ጋር ሲዋጋ በመሞቱ በእስያ የነበረውን አብዛኛውን የግዛቱን ክፍል አስረክቧል። ሰሉከስ በሶርያ የነገሡት የሰሉሲድ ነገሥታት የመጀመሪያው ሆኗል። የሶርያዋን አንጾኪያ በመቆርቆር አዲሷ መዲናው እንድትሆን አድርጓል። ሰሉከስ በ281 ከዘአበ ይገደል እንጂ ያቋቋመው ሥርወ መንግሥቱ የሮማው ጄኔራል ፖምፔ ሶርያን የሮማ ግዛት አድርጎ እስከ ጠቀለለበት እስከ 64 እዘአ ድረስ ቀጥሎ ነበር።

ለአራት ከተከፋፈለው የእስክንድር ግዛት መካከል ይበልጥ ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀው የቶሌሚ መንግሥት ነው። ቀዳማዊ ቶሌሚ፣ ንጉሥ የሚለውን ማዕረግ ያገኘው በ305 ከዘአበ ሲሆን የመጀመሪያው መቄዶናዊ የግብጽ ንጉሥ ወይም ፈርዖን ለመሆን በቅቷል። እስክንድርያን መዲናው በማድረግ ወዲያው የከተማ ልማት ፕሮግራም ጀመረ። ካከናወናቸው ታላላቅ የግንባታ ሥራዎች መካከል አንዱ የታወቀው የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት ነው። ቶሌሚ ይህንን ታላቅ ፕሮጄክት በበላይነት እንዲቆጣጠሩለት ሲል ከግሪክ የታወቀውን የአቴንስ ምሁር ሴሜትሬዎስ ፋሌሬፈስን አስመጥቷል። በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ቤተ መጻሕፍቱ አንድ ሚልዮን ጥቅልሎችን ይዞ እንደነበር ይነገራል። የቶሌሚ ሥርወ መንግሥት ግብጽ በ30 ከዘአበ በሮም እጅ እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ መግዛቱን ቀጥሏል። ከዚያ በኋላ ሮም የዓለም ኃያልነቱን ሥፍራ ከግሪክ ተረክባለች።

ምን አስተውለሃል?

• የእስክንድር ሰፊ ግዛት የተከፋፈለው እንዴት ነው?

• የሰሉሲድ ነገሥታት መሥመር በሶርያ መግዛቱን የቀጠለው እስከ መቼ ድረስ ነው?

• በግብጽ የነበረው የቶሌሚ መንግሥት ያከተመው መቼ ነው?

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የእስክንድር ግዛት መከፋፈል

ካሳንደር

ላይሲመከስ

ቀዳማዊ ቶሌሚ

ቀዳማዊ ሰሉከስ

[ሥዕል]

ቀዳማዊ ቶሌሚ

ቀዳማዊ ሰሉከስ

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጹት የዓለም ኃይሎች

ግዙፉ ምስል (ዳንኤል 2:31-45)

ከባሕር የወጡ አራት አራዊት (ዳንኤል 7:3-8, 17, 25)

ባቢሎኒያ ከ607 ከዘአበ ጀምሮ

ሜዶ ፋርስ ከ539 ከዘአበ ጀምሮ

ግሪክ ከ331 ከዘአበ ጀምሮ

ሮም ከ30 ከዘአበ ጀምሮ

የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ከ1763 እዘአ ጀምሮ

በፖለቲካ የተከፋፈለው ዓለም በፍጻሜው ዘመን

[በገጽ 128 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 147 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]