በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልዑላንን ልዑል ሊገዳደር የሚችል ማን ነው?

የልዑላንን ልዑል ሊገዳደር የሚችል ማን ነው?

ምዕራፍ አሥር

የልዑላንን ልዑል ሊገዳደር የሚችል ማን ነው?

1, 2. ዳንኤል በብልጣሶር ሦስተኛ የግዛት ዓመት ያየው ራእይ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በኢየሩሳሌም የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ከፈረሰ ሃምሳ ሰባት ዓመታት አልፈዋል። ብልጣሶርና አባቱ ናቦኒደስ ጣምራ ሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ሦስተኛ የዓለም ኃይል የሆነችውን የባቢሎንን ግዛት ያስተዳድራሉ። * የአምላክ ነቢይ የሆነው ዳንኤል አሁንም ባቢሎን ውስጥ በግዞት ይገኛል። “ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት” ይሖዋ የእውነተኛውን አምልኮ መልሶ መቋቋም በሚመለከት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ያቀፈ ራእይ ለዳንኤል አሳይቶታል።—ዳንኤል 8:1

2 ዳንኤል ባየው ትንቢታዊ ራእይ በጥልቅ ተነክቶ የነበረ ሲሆን ራእይው ‘በፍጻሜው ዘመን’ የምንኖረውን የእኛንም ትኩረት በእጅጉ የሚስብ ነው። መልአኩ ገብርኤል ለዳንኤል እንዲህ ብሎታል:- “እነሆ፣ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና።” (ዳንኤል 8:16, 17, 19, 27) እንግዲያውስ ዳንኤል ያየውን ነገር በጉጉት በመከታተል ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው እንመርምር።

ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ

3, 4. ዳንኤል በውኃው አጠገብ ቆሞ የተመለከተው እንስሳ ምን ነበር? የሚያመለክተውስ ማንን ነው?

3 ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በራእዩም አየሁ፤ ባየሁም ጊዜ በኤላም አውራጃ ባለው በሱሳ ግንብ ነበርሁ፤ በራእዩም አየሁ በኡባል ወንዝም አጠገብ ነበርሁ።” (ዳንኤል 8:2) ዳንኤል ከባቢሎን በስተ ምሥራቅ 350 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኤላም ዋና ከተማ በሱሳ የተገኘው በአካል ይሁን አይሁን አልተገለጸም።

4 ዳንኤል በመቀጠል “ዓይኔን አንሥቼ አየሁ፤ እነሆም፣ ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግ በወንዙ ፊት ቆሞ ነበር።” (ዳንኤል 8:3⁠ሀ) የአውራው በግ ማንነት ለዳንኤል ምሥጢር እንደሆነበት አይቀርም። ቆየት ብሎ መልአኩ ገብርኤል “ይህ ሁለት ቀንድ ያለው አውራ በግ የሜዶ ፋርስ መንግሥት ነው” ብሎታል። (ዳንኤል 8:20 NW) ሜዶናውያን የመጡት ከአሦር በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ተራራማ አካባቢ ሲሆን ፋርሳውያን ደግሞ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሰሜናዊ ክፍል በዘላንነት ኑሮ የሚተዳደሩ ሕዝቦች ነበሩ። ይሁንና የሜዶ ፋርስ ግዛት እየተስፋፋ ሲሄድ ነዋሪዎቹ የቅንጦትን ኑሮ ማጣጣም ጀመሩ።

5. ‘ዘግየት ብሎ የወጣው’ ቀንድ ረጅም የሆነው እንዴት ነው?

5 ዳንኤል “ሁለቱም ቀንዶቹ ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ አንዱ ግን ከሁለተኛው ከፍ ያለ ነበረ፣ ታላቁም ወደ ኋላው ወጥቶ [“የወጣው ዘግይቶ፣” NW] ነበር” ሲል ዘግቧል። (ዳንኤል 8:3⁠ለ) ቆየት ብሎ የወጣው ረጅሙ ቀንድ ፋርሳውያንን የሚያመለክት ሲሆን ሌላው ቀንድ ደግሞ ሜዶናውያንን ያመለክታል። መጀመሪያ ገደማ የበላይ የነበሩት ሜዶናውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በ550 ከዘአበ የፋርስ ገዥ የነበረው ቂሮስ በሜዶናዊው ንጉሥ አስታይጂዝ ላይ በቀላሉ ድል ተቀዳጀ። ቂሮስ የሁለቱን ሕዝቦች ባሕልና ሕግ በመቀላቀል መንግሥታቸውን ካዋሃደ በኋላ በኃይል የያዟቸው ግዛቶች እየሰፉ ሄዱ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ግዛቱ ጥምር ባሕርይ ያለው ሆኗል።

አውራው በግ ራሱን ታላቅ አደረገ

6, 7. አውራውን በግ ‘አራዊት ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ ያልቻሉት’ እንዴት ነው?

6 ዳንኤል ስለ አውራው በግ የሚሰጠውን መግለጫ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “አውራውም በግ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ ሲጎሽም አየሁ፤ አራዊትም ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ አልቻሉም፣ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፤ እንደ ፈቃዱም አደረገ፣ ራሱንም ታላቅ አደረገ።”—ዳንኤል 8:4

7 ለዳንኤል በተገለጠለት በፊተኛው ራእይ ውስጥ ባቢሎን ከባሕር በወጣችውና ሁለት የንስር ክንፍ ባላት አንበሳ የምትመስል አውሬ ተመስላ ነበር። (ዳንኤል 7:4, 17) ያች ምሳሌያዊ አውሬ በዚህ አዲስ ራእይ ውስጥ በታየው “አውራ በግ” ፊት ልትቆም አልቻለችም። ባቢሎን በ539 ከዘአበ በቂሮስ እጅ ወድቃለች። ከዚያ በኋላ በነበሩት 50 የሚያህሉ ዓመታት በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት አራተኛ የዓለም ኃይል የሆነውን የሜዶ ፋርስ ግዛት ሊቋቋም የቻለ ‘አውሬ’ ወይም የፖለቲካ መንግሥት አልነበረም።

8, 9. (ሀ) ‘አውራው በግ’ ‘ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጎሽም’ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የፋርሱን ንጉሥ ቀዳማዊ ዳርዮስን በመተካት ሥልጣን ላይ ስለወጣው ሰው የአስቴር መጽሐፍ ምን ይላል?

8 ‘ከፀሐይ መውጫ’ ማለትም ከምሥራቅ የመጣው የሜዶ ፋርስ የዓለም ኃይል እንደ ፈቃዱ “ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ” ይጎሽም ነበር። (ኢሳይያስ 46:11) ታላቁን ቂሮስን የተካው ንጉሥ ዳግማዊ ካምቢሰስ ግብጽን ድል አድርጎ ይዟል። ከእርሱ በኋላ የተነሣው የፋርሱ ንጉሥ ቀዳማዊ ዳርዮስ በ513 ከዘአበ የቦስፐረስን የባሕር ወሽመጥ ተሻግሮ በምዕራብ በኩል በማቅናት የትሬስን የአውሮፓ ክልል ወርሯል። መዲናዋ ባይዛንቲየም (የዛሬዋ ኢስታንቡል) ነበረች። በ508 ከዘአበ ትሬስን በቁጥጥሩ ሥር ያዋለ ሲሆን በ496 ከዘአበ ደግሞ መቄዶንያን ድል አድርጎ ይዟል። በመሆኑም በዳርዮስ ዘመን የሜዶ ፋርሱ “አውራ በግ” በሦስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች የተቆጣጠራቸው የግዛት ክልሎች የነበሩት ሲሆን እነዚህም በሰሜን ባቢሎንና አሦር፣ በምዕራብ ትንሿ እስያ እንዲሁም በደቡብ ግብጽ ናቸው።

9 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሜዶ ፋርስ ግዛት ታላቅነት ሲመሰክር በዳርዮስ ምትክ የነገሠውን ቀዳማዊ ዜርሰስ በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “ይህም አርጤክስስ [“አሕሻዊሮስ፣” NW] ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ።” (አስቴር 1:1) ይሁን እንጂ ይህ ታላቅ ግዛትም ራሱ ለሌላ ግዛት መንበርከኩ አይቀርም። በዚህ ረገድ የዳንኤል ራእይ በአምላክ የትንቢት ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ አስደናቂ ዝርዝሮችን ይዞልናል።

ፍየሉ አውራውን በግ መትቶ ጣለው

10. በዳንኤል ራእይ ውስጥ ‘አውራውን በግ’ መትቶ የጣለው እንስሳ የትኛው ነው?

10 ዳንኤል ቀጥሎ እየተመለከተ ባለው ነገር ምን ያህል እንደሚገረም አስበው። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እኔም ስመለከት፣ እነሆ፣ ከምዕራብ ወገን [“ከፀሐይ መግቢያ፣” NW] አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፣ ምድርንም አልነካም፤ ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው። ሁለትም ቀንድ ወዳለው በወንዝም ፊት ቆሞ ወዳየሁት አውራ በግ መጣ፣ በኃይሉም ቁጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ። ወደ አውራውም በግ ሲቀርብ አየሁት፤ እርሱም ተመረረበት፣ አውራውንም በግ መታ፣ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው ኃይል አልነበረውም፣ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራውንም በግ ከእጁ ያድነው ዘንድ የሚችል አልነበረም።” (ዳንኤል 8:5-7) የዚህ ሁሉ ነገር ትርጉም ምንድን ነው?

11. (ሀ) መልአኩ ገብርኤል ስለ ‘አውራው ፍየልና’ ስለ ‘ትልቅ ቀንዱ’ ምን ብሏል? (ለ) ጎላ ብሎ የሚታየው ቀንድ የሚያመለክተው ማንን ነው?

11 ዳንኤል የዚህን ራእይ ትርጉም መገመት አላስፈለገውም፤ እኛም አያስፈልገንም። መልአኩ ገብርኤል “አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው” ሲል ለዳንኤል አስታውቆታል። (ዳንኤል 8:21) የፋርስ ግዛት የመጨረሻው ንጉሥ የሆነው ሳልሳዊ ዳርዮስ (ካዶማነስ) የነገሠው በ336 ከዘአበ ነበር። በዚያው ዓመት እስክንድር የመቄዶንያ ንጉሥ ሆነ። በትንቢት የተነገረለት የመጀመሪያው “የግሪክ ንጉሥ” ታላቁ እስክንድር መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል። እስክንድር በ334 ከዘአበ ‘ከፀሐይ መግቢያ’ ማለትም ከምዕራብ ተነሥቶ ያደረገው የድል እንቅስቃሴ ፈጣን ነበር። ‘እግሩ ምድርን ሳይነካ’ የሄደ ያህል የግዛት ክልሎችን ድል አድርጎ ከመቆጣጠሩም ሌላ ‘አውራውን በግ’ መትቶ ጣለው። ግሪክ ሁለት መቶ ዓመት ለሚያህል ጊዜ የዘለቀውን የሜዶ ፋርስ የበላይነት ወደ ፍጻሜ በማምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጉልሕ ሥፍራ የተሰጣት አምስተኛ የዓለም ኃይል ሆናለች። ይህ እጅግ አስገራሚ የሆነ የመለኮታዊ ትንቢት ፍጻሜ ነው!

12. የምሳሌያዊው ፍየል “ታላቅ ቀንድ” ‘የተሰበረው’ እንዴት ነበር? በእርሱ ፋንታ የወጡትስ አራት ቀንዶች ምን ነበሩ?

12 ይሁን እንጂ የእስክንድር ሥልጣን ዕድሜው ረጅም አልነበረም። ራእይው በመቀጠል እንደሚያሳየው:- “አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፣ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።” (ዳንኤል 8:8) ገብርኤል ይህን ትንቢት ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፣ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፣ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።” (ዳንኤል 8:22) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው እስክንድር ከፍተኛውን ድሉን በጨበጠበት ወቅት በ32 ዓመቱ ‘ተሰብሯል’ ወይም ሕይወቱ አልፏል። በመጨረሻም ታላቁን ግዛቱን አራቱ ጄኔራሎቹ ተከፋፍለውታል።

ምሥጢራዊ ትንሽ ቀንድ

13. ከአራቱ ቀንዶች መካከል ምን ነገር ብቅ ብሏል? ምንስ አድርጓል?

13 ቀጣዩ የራእይው ክፍል ከ2,200 ለሚበልጡ ዓመታት የሚዘልቅ ሲሆን ፍጻሜው እስከ ዘመናችንም ይደርሳል። ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእነርሱም [ከአራቱ ቀንዶች] ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፣ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ወደ ጌጡ፣ እጅግ ከፍ አለ። እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፣ ረገጣቸውም። እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፤ እርሱም [ይሖዋ] የዘወትሩ መሥዋዕት ቀረበት፤ የመቅደሱም ቋሚ ስፍራ ተጣለ። ከዚያም ከኃጢአት የተነሣ ሠራዊት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር አልፎ ተሰጠ፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፣ አደረገም ተከናወነም።”—ዳንኤል 8:9-12 NW

14. መልአኩ ገብርኤል የምሳሌያዊውን ትንሽ ቀንድ እንቅስቃሴ በሚመለከት ምን ብሏል? ቀንዱስ ምን ይሆናል?

14 የእነዚህን ቃላት ትርጉም ከመረዳታችን በፊት የአምላክ መልአክ የሚለውን በትኩረት መከታተል ይኖርብናል። መልአኩ ገብርኤል ከእስክንድር ግዛት የወጡት አራት መንግሥታት ሥልጣን ስለ መጨበጣቸው ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “በመንግሥታቸውም መጨረሻ፣ ኃጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፣ እንቆቅልሽን የሚያስተውል ፊተ ጨካኝ ንጉሥ [“የሚያስፈራ ፊት ያለው ንጉሥ፣” NW] ይነሣል። ኃይሉም ይበረታል፣ ነገር ግን በራሱ ኃይል አይደለም፤ በድንቅም ያጠፋል፣ ያደርግማል፣ ይከናወንማል፤ ኃያላንንና የቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል። በመታለሉ ተንኮልን በእጁ ያከናውናል፤ በልቡም ይታበያል፣ ታምነውም የሚኖሩትን ብዙዎችን ያጠፋል፤ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቋቋማል [“የልዑላንንም ልዑል ይገዳደራል፣” NW]፤ ያለ እጅም ይሰበራል።”—ዳንኤል 8:23-25

15. መልአኩ ራእይውን በሚመለከት ዳንኤል ምን እንዲያደርግ ነግሮታል?

15 መልአኩ “የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ” ሲል ለዳንኤል ነግሮታል። (ዳንኤል 8:26) የዚህኛው የራእይው ክፍል ፍጻሜውን የሚያገኘው “ከብዙ ዘመን በኋላ” ስለሚሆን ዳንኤል ራእይውን ‘ዘግቶ’ ማስቀመጥ ነበረበት። ትርጉሙ ለዳንኤል ምሥጢር እንደሆነበት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ዛሬ እነዚያ ‘ብዙ ዘመናት’ እንዳለቁ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ‘የዚህን ትንቢታዊ ራእይ አፈጻጸም በተመለከተ የዓለም ታሪክ ምን ይላል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት እንችላለን።

ትንሹ ቀንድ ኃያል ሆነ

16. (ሀ) ትንሹ ቀንድ የወጣው ከየትኛው ምሳሌያዊ ቀንድ ነው? (ለ) ሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ስድስተኛ የዓለም ኃይል የሆነችው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ ትንሹ ቀንድ ሮምን የማያመለክተው ለምንድን ነው?

16 ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ትንሹ ቀንድ የተገኘው ከአራቱ ምሳሌያዊ ቀንዶች መካከል ወደ ምዕራብ ካቀናው ቀንድ ነው። ይህም በመቄዶንያና በግሪክ ላይ ይገዛ የነበረው የጄኔራል ካሳንደር ሄለናዊ መንግሥት ነው። ከጊዜ በኋላ ይህ መንግሥት የትሬስና የትንሿ እስያ ንጉሥ በነበረው በጄኔራል ላይሲመከስ ሥር ተጠቃልሏል። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት እነዚህ የሄለናዊው ግዛት ምዕራባዊ ክፍሎች በሮም ቁጥጥር ሥር ውለዋል። በ30 ከዘአበ ደግሞ ሮም ሁሉንም ሄለናዊ መንግሥታት በመጠቅለል በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ራሷን ስድስተኛ የዓለም ኃይል አድርጋለች። ይሁን እንጂ በዳንኤል ራእይ ውስጥ የተጠቀሰው ትንሽ ቀንድ የሮማ ግዛት አይደለም፤ ምክንያቱም የሮማ ግዛት እስከ ‘ፍጻሜው ዘመን’ ድረስ አልዘለቀም።—ዳንኤል 8:19

17. (ሀ) ብሪታንያ ከሮማ ግዛት ጋር የነበራት ተዛምዶ ምን ነበር? (ለ) የብሪታንያ ግዛት ከመቄዶንያና ከግሪክ ሄለናዊ ግዛቶች ጋርስ የሚዛመደው እንዴት ነው?

17 ታዲያ ጠበኛ እንደሆነና ‘አስፈሪ ፊት’ እንዳለው ተደርጎ ስለተገለጸው ንጉሥ ማንነት ታሪክ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ? እርግጥ ብሪታንያ ብቅ ያለችው ከሮማ ግዛት ሰሜናዊ ምዕራብ ነው። እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ድረስ በዛሬዋ ብሪታንያ አካባቢ የሮማ ግዛቶች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የሮማ ግዛት እየተዳከመ ሲመጣ የግሪካውያኑና የሮማውያኑ ሥልጣኔ በሮማ ቁጥጥር ሥር በነበሩት በብሪታንያና በሌሎችም የአውሮፓ ክፍሎች ውስጥ ቀጥሎ ነበር። የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ሜክሲኮአዊው ባለቅኔና ጸሐፊ ኦክታብዮ ፓዝ “የሮማ ግዛት ሲወድቅ ቤተ ክርስቲያን ቦታውን ተረክባለች” ሲሉ ጽፈዋል። በመቀጠልም “የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንዲሁም ከጊዜ በኋላ የተነሡት ምሁራን የግሪካውያንን ፍልስፍና ከክርስትና መሠረተ ትምህርት ጋር ቀላቅለዋል” ሲሉ ዘግበዋል። የ20ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋና የሒሳብ ሊቅ በርትረንድ ራስል ደግሞ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ከግሪክ የመነጨውና በፍልስፍናና ሳይንሳዊ ባሕል ላይ የተመሠረተው የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት የተጀመረው በሚሌተስ [በትንሿ እስያ የምትገኝ የግሪክ ከተማ] ነበር።” በመሆኑም የብሪታንያ ግዛት ባሕላዊ መሠረቱ የተጣለው በመቄዶንያ እና በግሪክ ሄለናዊ መንግሥታት ውስጥ ነው ለማለት ይቻላል።

18. ‘በፍጻሜው ዘመን’ ‘አስፈሪ ንጉሥ’ ሆኖ የተነሣው ቀንድ ማን ነው? አብራራ።

18 የብሪታንያ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት በ1763 ብርቱ ተቀናቃኞቿን ስፔይንና ፈረንሳይን ድል አድርጋ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የባሕር ላይ እመቤትና በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ሰባተኛ የዓለም ኃይል መሆኗን አሳይታለች። አሥራ ሦስቱ የአሜሪካ ቅኝ ግዛቶቿ በ1776 ከብሪታንያ ነፃ ወጥተው ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካን ከመሠረቱ በኋላም እንኳ አንድ አራተኛውን የምድር ክፍልና ሩብ የሚያክለውን ነዋሪ እስከ መቆጣጠር ደርሳ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ከብሪታንያ ጋር በመተባበሯ የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ሲመሠረት ሰባተኛው የዓለም ኃይል የበለጠ ኃይል አግኝቷል። በእርግጥም ይህ የዓለም ኃይል በኢኮኖሚም ሆነ በጦር ኃይል ‘የሚያስፈራ ንጉሥ’ ሆኗል። በመሆኑም ‘በፍጻሜው ዘመን’ አስፈሪ ፖለቲካዊ ኃይል ሆኖ ብቅ እንደሚል የተነገረው ትንሽ ቀንድ የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ነው።

19. በራእዩ ውስጥ የተገለጸው “ጌጥ” ምንድን ነው?

19 ዳንኤል ትንሹ ቀንድ “ወደ ጌጡ እጅግ ከፍ እንዳለ” ተመልክቷል። (ዳንኤል 8:9 NW) ይሖዋ ለተመረጡት ሕዝቦቹ የሰጣቸው የተስፋይቱ ምድር እጅግ ውብ ከመሆኗ የተነሣ “የምድርም ሁሉ ጌጥ” ተብላ ተጠርታለች። (ሕዝቅኤል 20:6, 15) እርግጥ ነው ብሪታንያ በታኅሣሥ 9, 1917 ኢየሩሳሌምን ይዛ የነበረ ሲሆን በ1920 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበሩ ፍልስጤምን በሞግዚትነት የማስተዳደሩን ኃላፊነት ለታላቋ ብሪታንያ ሰጥቷት ነበር። ይህም እስከ ግንቦት 14, 1948 ድረስ ዘልቋል። ይሁን እንጂ ይህ ራእይ ብዙ ምልክቶችን የያዘ ትንቢታዊ ራእይ ነው። በዚህ ራእይ ውስጥ የተገለጸው ‘ጌጥ’ የሚያመለክተው ኢየሩሳሌምን ሳይሆን አምላክ በሰባተኛው የዓለም ኃይል ዘመን እንደ ቅዱስ አድርጎ የሚያያቸውን ሕዝቦቹን ምድራዊ ሁኔታ ነው። የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል የቅዱሳኑን ሕልውና ስጋት ለመጣል የሞከረው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

“የመቅደሱ ስፍራ” ተጣለ

20. ትንሹ ቀንድ ሊያወርዳቸው የሞከረው “የሰማይ ሠራዊት” እና “ከዋክብት” እነማን ናቸው?

20 ትንሹ ቀንድ “እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ።” በመልአኩ ማብራሪያ መሠረት ትንሹ ቀንድ ሊጥላቸው የሚሞክረው “የሰማይ ሠራዊት” እና “ከዋክብት” ‘የቅዱሳን ሕዝብ’ ናቸው። (ዳንኤል 8:10, 24) እነዚህ ‘ቅዱሳን’ በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ናቸው። በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት በተቋቋመው አዲስ ቃል ኪዳን በኩል ከአምላክ ጋር በመዛመዳቸው ተቀድሰዋል፣ ነጽተዋል እንዲሁም ለአምላክ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ለመስጠት የተለዩ ሆነዋል። (ዕብራውያን 10:10፤ 13:20) ይሖዋ እንደ ቅዱስ በመቁጠር በሰማያዊው ርስት ከልጁ ጋር ወራሾች አድርጎ ያስቀምጣቸዋል። (ኤፌሶን 1:3, 11, 18-20) በመሆኑም በዳንኤል ራእይ ውስጥ “የሰማይ ሠራዊት” የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው በሰማይ ከበጉ ጋር ከሚገዙት ‘ቅዱሳን’ 144,000 መካከል በምድር የቀሩትን ነው።—ራእይ 14:1-5

21. ሰባተኛው የዓለም ኃይል ወና ሊያስቀረው የፈለገውን ‘ቅዱስ ስፍራ’ የያዙት እነማን ናቸው?

21 ዛሬ ያሉት የ144,000ዎቹ ቀሪዎች ‘የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም’ ማለትም የከተማ መሰሏ የአምላክ መንግሥትና የቤተ መቅደስ ዝግጅቷ ምድራዊ ወኪሎች ናቸው። (ዕብራውያን 12:22, 28፤ 13:14) ከዚህ አንጻር ሲታይ ቅዱሳኑ ሰባተኛው የዓለም ኃይል ሊረግጠውና ወና ሊያስቀረው የሚፈልገውን ‘ቅዱስ ስፍራ’ ይዘዋል። (ዳንኤል 8:13) ዳንኤል ይህ ቅዱስ ስፍራ “የመቅደሱ [የይሖዋ መቅደስ] ቋሚ ስፍራ” መሆኑንም በመግለጽ እንዲህ ብሏል:- “እርሱም [ይሖዋ] የዘወትሩ መሥዋዕት ቀረበት፤ የመቅደሱም ቋሚ ስፍራ ተጣለ። ከዚያም ከኃጢአት የተነሣ ሠራዊት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር አልፎ ተሰጠ፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፣ አደረገም ተከናወነም።” (ዳንኤል 8:11, 12 NW) ይህ ነገር ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

22. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሰባተኛው የዓለም ኃይል ጉልህ “ኃጢአት” የፈጸመው እንዴት ነው?

22 የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበሩበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል! ስደቱ የጀመረው በናዚና በፋሽስት አገሮች ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ‘ትንሹ ቀንድ ኃያልነቱ ገንኖበት በነበረው የግዛት ክልል’ ሁሉ ‘እውነት ወደ ምድር ተጣለ።’ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች “ሠራዊት” እንዲሁም ‘ምሥራቹን’ የመስበክ ሥራቸው በብሪታንያ የኮመንዌልዝ አገሮች በሙሉ ለማለት ይቻላል ታግዶ ነበር። (ማርቆስ 13:10) እነዚህ ብሔራት ዜጎቻቸውን ለብሔራዊ ግዳጅ ሲመለምሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ሃይማኖታዊ አገልግሎት ሰጭዎች ታይተው ከግዴታ ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይህም ምሥክሮቹ የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለተሰጣቸው ሥራ ብሔራቱ ምንም አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የነበሩት የይሖዋ የታመኑ አገልጋዮች የሕዝብ ዓመፅና የተለያዩ ውርደት ደርሶባቸዋል። ሰባተኛው የዓለም ኃይል ሕዝቦቹ ለይሖዋ ዘወትር የሚያቀርቡትንና እንደ ‘ዘወትር መሥዋዕት’ የሚታየውን የምሥጋና መሥዋዕት ማለትም “የከንፈሮችን ፍሬ” ለማስቀረት የሞከረ ያህል ነበር። (ዕብራውያን 13:15) በዚህ መንገድ ይህ የዓለም ኃይል ለልዑሉ አምላክ የሚገባውን “የመቅደሱን ቋሚ ስፍራ” በመውረር “ኃጢአት” ሠርቷል።

23. (ሀ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ‘የልዑላንን ልዑል’ የተገዳደረው እንዴት ነው? (ለ) ‘የልዑላን ልዑል’ የተባለው ማን ነው?

23 ትንሹ ቀንድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ‘በቅዱሳኑ’ ላይ ስደት በማስነሣት ‘እስከ ሠራዊት አለቃ ድረስ ራሱን ከፍ አድርጓል።’ ወይም መልአኩ ገብርኤል እንዳለው ‘የልዑላንን ልዑል’ ተገዳድሯል። (ዳንኤል 8:11, 251980 ትርጉም) ‘የልዑላን ልዑል’ የሚለው ማዕረግ የሚያገለግለው ለይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። “ልዑል” ተብሎ የተተረጎመው ሳር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የበላይ መሆን” የሚል ትርጉም ካለው ግሥ ጋር የሚዛመድ ነው። ቃሉ የንጉሥን ልጅ ወይም የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆነን ሰው ከማመልከቱም ሌላ አንድን አዛዥ ወይም አለቃ ሊያመለክት ይችላል። የዳንኤል መጽሐፍ እንደ ሚካኤል ስላሉ ሌሎች መላእክታዊ አለቆችም ይጠቅሳል። አምላክ የእነዚህ ሁሉ ልዑላን ልዑል ነው። (ዳንኤል 10:13, 21፤ ከ⁠መዝሙር 83:18 ጋር አወዳድር።) በእርግጥ የልዑላን ልዑል የሆነውን ይሖዋን ሊገዳደር የሚችል ይኖራል ብለን ልናስብ እንችላለንን?

ወደ ትክክለኛ ሁኔታው የተመለሰ “ቅዱስ ስፍራ”

24. ዳንኤል 8:14 ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

24 ሌላው ቀርቶ እንደ አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ያለ ‘አስፈሪ’ ንጉሥም እንኳ ቢሆን የልዑላን ልዑል የሆነውን ይሖዋን ሊገዳደር የሚችል አይኖርም! ይህ ንጉሥ የአምላክን መቅደስ ወና ለማስቀረት ቢሞክርም አይሳካለትም። መልእክተኛው መልአክ እንዳለው “ከሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጠዋት በኋላ ቅዱሱ ስፍራ ወደ ትክክለኛው ሁኔታ ይመለሳል።”—ዳንኤል 8:13, 14ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል

25. የትንቢታዊዎቹ 2,300 ቀናት ርዝማኔ ምን ያህል ነው? ከየትኛውስ ክንውን ጋር የሚዛመድ ነው?

25 እነዚህ 2,300 ቀናት አንድን ትንቢታዊ ክፍለ ጊዜ የሚያመለክቱ ናቸው። በመሆኑም ዓመታቱ እያንዳንዳቸው 360 ቀናትን ያቀፉ ትንቢታዊ ዓመታት ናቸው። (ራእይ 11:2, 3፤ 12:6, 14) እንግዲያው እነዚህ 2,300 ቀናት 6 ዓመታት፣ 4 ወራትና 20 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ከመቼ እስከ መቼ ያለውን ጊዜ የሚያመለክት ነው? ከ1930 ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች በተለያዩ አገሮች ውስጥ ብዙ ስደት ይደርስባቸው ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በአንግሎ አሜሪካ ጥምር የዓለም ኃይል ግዛቶች ውስጥ ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። ለምን? ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ልንታዘዝ ይገባል’ የሚል የጸና አቋም ስለያዙ ነበር። (ሥራ 5:29) በመሆኑም እነዚህ 2,300 ቀናት ከዚያ ጦርነት ጋር የተያያዙ መሆን አለባቸው። * ይሁን እንጂ ይህ ትንቢታዊ ክፍለ ጊዜ ስለሚጀምርበትና ስለሚያበቃበት ጊዜ ምን ማለት ይቻላል?

26. (ሀ) የ2,300ዎቹ ቀናት መጀመሪያ ግፋ ቢል መቼ መሆን አለበት? (ለ) እነዚህ 2,300 ቀናት ያበቁት መቼ ነው?

26 ‘ቅዱስ ስፍራው’ ወደ ተገቢ ሁኔታው ‘ተመልሷል’ ወይም የቀድሞ ሥፍራውን ይዟል ማለት እንድንችል 2,300ዎቹ ቀናት የጀመሩት ቅዱስ ስፍራው በአምላክ ፊት ያለውን “ትክክለኛ ሁኔታ” ይዞ እያለ መሆን አለበት። ይህ ግፋ ቢል ከሰኔ 1, 1938 አያልፍም። በዚህ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ “ድርጅት” የሚለውን ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል አውጥቶ ነበር። ክፍል 2 በሰኔ 15, 1938 እትም ላይ ወጥቷል። ከሰኔ 1 ወይም 15 1938 ተነሥተን 2,300 ቀናት (በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ 6 ዓመት፣ 4 ወርና 20 ቀን) ስንቆጥር ጥቅምት 8 ወይም 22, 1944 ላይ እንደርሳለን። መስከረም 30 እና ጥቅምት 1, 1944 በዩ ኤስ ኤ ፔንሲልቫኒያ፣ ፒትስበርግ ውስጥ በተደረገው ልዩ ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት “ዛሬ የሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ ማስተካከያ” በሚል ርዕስ ንግግር አድርጎ ነበር። ጥቅምት 2 ቀን በተካሄደው ዓመታዊ የማኅበሩ ስብሰባ ላይ የማኅበሩ ቻርተር ይበልጥ ቲኦክራሲያዊ መልክ እንዲኖረው ሕጉ በሚፈቅደው መጠን ማሻሻያ ተደርጎበታል። የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃ በሰፊው ባብራሩ ጽሑፎች አማካኝነት ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ ተንጸባርቋል።

27. ስደት በሞላባቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዓመታት ወቅት ‘የዘወትር መሥዋዕቱ’ ተስተጓጉሎ እንደነበር የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

27 እነዚህ 2,300 ቀናት በሂደት ላይ በነበሩበት ወቅት ማለትም በ1939 የጀመረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲካሄድ በአምላክ መቅደስ የሚቀርበው ‘የዘወትሩ መሥዋዕት’ በስደት ምክንያት በእጅጉ ተስተጓጉሎ ነበር። በ1938 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት የሚከታተሉ 39 ቅርንጫፍ ቢሮዎች የነበሩት ሲሆን በ1943 ግን 21 ብቻ ሆነው ነበር። በዚህ መሃል የነበረው የአስፋፊዎች ጭማሪም እጅግ አነስተኛ ነበር።

28, 29. (ሀ) ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ማብቂያው ሲቃረብ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምን ለውጥ ተደርጓል? (ለ) ጠላት ‘ቅዱሱን ስፍራ’ ወና ለማስቀረትና ለማጥፋት ስላደረገው ብርቱ ሙከራ ምን ለማለት ይቻላል?

28 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመደምደሚያ ወራት በቲኦክራሲያዊው ድርጅት ውስጥ በማገልገል የአምላክን የበላይ ገዥነት ከፍ ከፍ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል። በ1944 በሥራቸውና በአስተዳደር መዋቅሩ ላይ ማሻሻያዎች ያደረጉትም ከዚሁ በመነሳት ነበር። እንዲያውም የጥቅምት 15, 1944 መጠበቂያ ግንብ “ለመጨረሻው ሥራ መደራጀት” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። በወቅቱ የወጡት ይህና ይህንን የመሳሰሉት በአገልግሎት ላይ ያተኮሩት ርዕሶች 2,300ዎቹ ቀናት እንዳለቁና ‘ቅዱሱ ስፍራ’ ‘ወደ ትክክለኛው ሁኔታ’ እንደተመለሰ የሚጠቁሙ ነበሩ።

29 ጠላት ‘ቅዱሱን ስፍራ’ ወና ለማስቀረትና ለማጥፋት ያደረገው ብርቱ ሙከራ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል። በእርግጥም በምድር ላይ የቀሩት “ቅዱሳን” እንዲሁም አጋሮቻቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” በድል አድራጊነት ተወጥተውታል። (ራእይ 7:9) ዛሬ መቅደሱም በትክክለኛ ቲኦክራሲያዊ ሁኔታ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረቡን ቀጥሏል።

30. ‘አስፈሪ የሆነው’ ንጉሥ በቅርቡ ምን ይጠብቀዋል?

30 የአንግሎ አሜሪካ ኃይል ዛሬም ሥልጣኑን እንደያዘ ነው። ይሁን እንጂ መልአኩ ገብርኤል እንዳለው ‘እጅ ሳይነካው ይሰበራል።’ (ዳንኤል 8:25) ይህ ሰባተኛ የዓለም ኃይል ወይም ‘አስፈሪ ንጉሥ’ በቅርቡ በሰብዓዊ እጅ ሳይሆን ከሰው በላይ በሆነ ኃይል በአርማጌዶን ይሰበራል። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16) በዚህ ጊዜ የልዑላን ሁሉ ልዑል የሆነው የይሖዋ አምላክ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥ መሆኑን ማወቅ እንዴት ደስ የሚያሰኝ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.1 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለየት ያለ ሥፍራ የተሰጣቸው ሰባቱ የዓለም ኃይሎች ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮምና የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ናቸው። ሁሉም ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ከነበራቸው ግንኙነት አንጻር ነው።

^ አን.25 ዳንኤል 7:25 ‘የልዑሉ ቅዱሳን ቀጣይ ይዘት ባለው መልክ ስለሚንገላቱበት’ ክፍለ ጊዜ ይናገራል። በፊተኛው ምዕራፍ ውስጥ እንደተገለጸው ይህ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው።

ምን አስተውለሃል?

• ቀጥሎ የተዘረዘሩት ነገሮች ምን ያመለክታሉ:-

“ሁለት ቀንድ” ያለው “አውራ በግ”?

“ታላቅ ቀንድ” ያለው “አውራ ፍየል”?

‘በታላቁ ቀንድ’ ፋንታ የወጡት አራት ቀንዶች?

ከአራቱ ቀንዶች መካከል ከአንዱ የወጣው ትንሽ ቀንድ?

• በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል “ቅዱሱን ስፍራ” ወና ለማስቀረት የሞከረው እንዴት ነው? ተሳክቶለታልን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 166 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሜዶ ፋርስ ግዛት

መቄዶንያ

ግብጽ

ሜምፊስ

ኢትዮጵያ

ኢየሩሳሌም

ባቢሎን

አሕምታ

ሱሳ

ፐርሴፐለስ

ሕንድ

[በገጽ 169 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የግሪክ ግዛት

መቄዶንያ

ግብጽ

ባቢሎን

ኢንደስ ወንዝ

[በገጽ 172 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሮማ ግዛት

ብሪታንያ

ኢጣሊያ

ሮም

ኢየሩሳሌም

ግብጽ

[በገጽ 164 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 174 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው ግለሰቦች:-

1. ጆርጅ ዋሽንግተን፣ የዩ ኤስ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት (1789-97)

2. የብሪታንያዋ ንግሥት ቪክቶሪያ (1837-1901)

3. ዉድሮው ዊልሰን፣ የዩ ኤስ ፕሬዚዳንት (1913-21)

4. ዴቪድ ሎይድ ጆርጅ፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር (1916-22)

5. ዊንስተን ቸርችል፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር (1940-45, 1951-55)

6. ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት፣ የዩ ኤስ ፕሬዚዳንት (1933-45)