ይሖዋ ለዳንኤል ቃል የገባለት አስደናቂ በረከት
ምዕራፍ አሥራ ስምንት
ይሖዋ ለዳንኤል ቃል የገባለት አስደናቂ በረከት
1, 2. (ሀ) አንድ ሯጭ ግቡን ለመምታት የሚረዳው በጣም አስፈላጊ ባህርይ ምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት የምናሳልፈውን የታማኝነት ሕይወት ከሩጫ ጋር ያወዳደረው እንዴት ነው?
አንድ ሯጭ ወደ መጨረሻው መስመር በኃይል ይሮጣል። ኃይሉ እየተሟጠጠ ያለ ቢሆንም የመጨረሻ ግቡ በቅርብ ስለሚታየው የቀሩትን ጥቂት እርምጃዎች ለመጨረስ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ይወረወራል። ጡንቻዎቹ ሁሉ ተገታትረው በመጨረሻ መስመሩን አልፎ ይገባል! ፊቱ ላይ የእፎይታና የድል መንፈስ ይነበባል። እስከ መጨረሻ ድረስ መጽናቱ ለውጤት አብቅቶታል።
2 በዳንኤል ምዕራፍ 12 መደምደሚያ ላይ የተወደደው ነቢይ ‘ሩጫውን’ ማለትም በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፈውን ሕይወቱን ሊፈጽም ወደ መጨረሻው መስመር ቀርቦ እንደነበር እናስተውላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ በቅድመ ክርስትና ዘመን ከነበሩት የአምላክ አገልጋዮች መካከል የእምነት ምሳሌ የሚሆኑትን በርካታ ሰዎች ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”—ዕብራውያን 12:1, 2
3. (ሀ) ዳንኤል ‘በጽናት እንዲሮጥ’ ያነሣሣው ነገር ምንድን ነበር? (ለ) የይሖዋ መልአክ ለዳንኤል የነገረው ስለ የትኞቹ ሦስት የተለያዩ ነገሮች ነው?
3 ከእነዚህ ‘እንደ ደመና ያሉ ብዙ ምሥክሮች’ መካከል አንዱ ዳንኤል ነው። በእርግጥም እርሱ ‘ሩጫውን በጽናት’ የሮጠ ሰው ነው። ይህንንም እንዲያደርግ ያነሳሳው ለአምላክ የነበረው ጥልቅ ፍቅር ነው። የዓለም መንግሥታትን የወደፊት ዕጣ በሚመለከት ይሖዋ ለዳንኤል የገለጸለት ብዙ ነገር ነበር፤ ይሁን እንጂ ለእርሱ በግሉም ማበረታቻ ዳንኤል 12:13) የይሖዋ መልአክ ለዳንኤል ሦስት የተለያዩ ነገሮችን ነግሮታል:- (1) ዳንኤል “እስከ ፍጻሜው ድረስ” መሄድ እንዳለበት፣ (2) ‘እንደሚያርፍ’ እንዲሁም (3) ወደፊት ደግሞ ‘እንደሚቆም’ ተነግሮታል። እነዚህ ቃላት ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች የሕይወትን ሩጫ እስከ መጨረሻ በጽናት እንዲሮጡ ሊያበረታቷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
ሰጥቶታል:- “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፣ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።” (“እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ”
4. የይሖዋ መልአክ “እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይህስ ለዳንኤል ፈታኝ ሊሆንበት የሚችለው ለምን ነበር?
4 መልአኩ ዳንኤልን “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ” ሲለው ምን ማለቱ ነበር? እስከ ምን ፍጻሜ? ዳንኤል ዕድሜው ወደ 100 ዓመት ተጠግቶ ስለነበር እዚህ ላይ የተጠቀሰው በጣም ቀርቦ የነበረው የሕይወቱ ፍጻሜ ይመስላል። * ዳንኤል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የታመነ ሆኖ እንዲጸና ማበረታታቱ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ቀላል ይሆንለታል ማለት አይደለም። ዳንኤል ባቢሎን ስትገለበጥና ቀሪዎቹ አይሁዳዊ ምርኮኞች ወደ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ለማየት በቅቷል። በዕድሜ ገፍቶ ለነበረው ነቢይ ይህ ነገር ታላቅ ደስታ አምጥቶለት መሆን አለበት። ይሁንና አብሯቸው እንደተጓዘ የሚገልጽ ምንም የተመዘገበ ታሪክ የለም። በወቅቱ በጣም አርጅቶና ሰውነቱም ደክሞ ይሆናል። ወይም ደግሞ እዚያው ባቢሎን እንዲቆይ የይሖዋ ፈቃድ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ዳንኤል የአገሩ ልጆች ወደ ይሁዳ ሲመለሱ ሲያይ ቅር ብሎት ይሆን? ብለን ማሰባችን አይቀርም።
5. ዳንኤል እስከ ፍጻሜው ድረስ እንደጸና የሚጠቁም ምን ነገር አለ?
5 ዳንኤል መልአኩ ከተናገራቸው “እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ” ከሚሉት የደግነት ቃላት ትልቅ ብርታት አግኝቶ እንደነበር የታወቀ ነው። ስድስት መቶ ዘመን የሚያክል ጊዜ ቆይቶ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” የሚሉትን ቃላት ያስታውሱን ይሆናል። (ማቴዎስ 24:13) ዳንኤልም ያደረገው ይህንኑ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። የሕይወትን ሩጫ እስከ መጨረሻው ድረስ በታማኝነት በመሮጥ እስከ ፍጻሜው ድረስ ጸንቷል። ከጊዜ በኋላ በአምላክ ቃል ውስጥ በመልካም የተጠቀሰበትም አንዱ ምክንያት ይህ ይሆናል። (ዕብራውያን 11:32, 33) ዳንኤልን እስከ ፍጻሜው ድረስ እንዲጸና የረዳው ነገር ምንድን ነው? ስላሳለፈው ሕይወት ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ መልሱን እንድናስተውል ይረዳናል።
በአምላክ ቃል ተማሪነት መጽናት
6. ዳንኤል የአምላክን ቃል በትጋት የሚያጠና ሰው እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
6 ዳንኤል እስከ ፍጻሜው እንዲጸና አስደሳች የሆኑትን የአምላክ ተስፋዎች ማጥናትና በእነርሱ ላይ ማሰላሰል አስፈልጎት ነበር። ዳንኤል የአምላክን ቃል በትጋት የሚያጠና ሰው እንደነበር እናውቃለን። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ በግዞት የሚቆዩበት ዘመን 70 ዓመት ስለመሆኑ ይሖዋ ለኤርምያስ የነገረውን ነገር እንዴት ማወቅ ይችል ነበር? ዳንኤል ራሱ “በቃሉ . . . የተናገረውን የዓመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 9:2፤ ኤርምያስ 25:11, 12) ዳንኤል በወቅቱ የነበሩትን የአምላክ ቃል መጻሕፍት ይመረምር እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም። ዳንኤል የሙሴን፣ የዳዊትን፣ የሰሎሞንን፣ የኢሳይያስን፣ የኤርምያስን፣ የሕዝቅኤልንና በጊዜው የነበሩትን ሌሎቹንም ጽሑፎች እያነበበ በማሰላሰል ይደሰት እንደነበር የተረጋገጠ ነው።
7. ያለንበትን ጊዜ ከዳንኤል ዘመን ጋር ስናወዳድረው የአምላክን ቃል በማጥናት በኩል እኛ ምን የተሻለ ነገር አግኝተናል?
7 ዛሬ እኛም ጽናትን ማዳበር እንችል ዘንድ የአምላክን ቃል ማጥናታችንና በዚያ መመሰጣችን የግድ አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 15:4-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15) ደግሞም አንዳንዶቹ የዳንኤል ትንቢቶች ከብዙ ዘመናት በኋላ እንዴት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ የሚገልጹትን የጽሑፍ መረጃዎች ጨምሮ የተሟላው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። ከዚህም በላይ በዳንኤል 12:4 ላይ በትንቢት በተነገረው ‘የፍጻሜ ዘመን’ የመኖር መብት አግኝተናል። በዘመናችን ቅቡዓኑ መንፈሳዊ ማስተዋል በማግኘት ስለተባረኩ በዚህ ጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ ቦግ ብሎ እንደሚታይ መብራት ብርሃናቸውን እያበሩ ነው። ከዚህም የተነሣ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትና ለእርሱ ምሥጢር ሆነውበት የነበሩት ጥልቅ ትርጉም ያላቸው አብዛኛዎቹ ትንቢቶች ዛሬ ለእኛ ፍንትው ብለው ይታዩናል። እንግዲያውስ እነዚህን ነገሮች አቃልለን ባለመመልከት በየዕለቱ የአምላክን ቃል ማጥናታችንን እንቀጥል። እንዲህ ማድረጋችን ለመጽናት ይረዳናል።
ዳንኤል በጸሎት ጸንቷል
8. ዳንኤል በጸሎት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
8 ዳንኤል እስከ ፍጻሜው ድረስ እንዲጸና የረዳው ሌላው ነገር ጸሎት ነው። በየዕለቱ በጸሎት ወደ ይሖዋ አምላክ በመቅረብ እምነትና ትምክህት በተሞላ ልብ ከእርሱ ጋር በግልጽ ይነጋገር ነበር። ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 65:2፤ ከዕብራውያን 11:6 ጋር አወዳድር።) ዳንኤል፣ እስራኤላውያን በተከተሉት የዓመፅ ጎዳና ልቡ ባዘነ ጊዜ ለይሖዋ የውስጡን አውጥቶ ነግሮታል። (ዳንኤል 9:4-19) ዳርዮስ ለ30 ቀናት ከእርሱ ሌላ ማንንም እንዳይለምኑ የሚደነግግ ትእዛዝ ባወጣ ጊዜ እንኳ ዳንኤል ወደ ይሖዋ አምላክ ከመጸለይ ወደ ኋላ አላለም። (ዳንኤል 6:10) ይህ የታመነ አረጋዊ ውድ በሆነው የጸሎት መብት ሳይጠቀም ከሚቀር አንበሶች ወደ ሞሉበት ጉድጓድ መጣልን በድፍረት መምረጡን ስናስብ ልባችን አይነካም? ዳንኤል በየዕለቱ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ እስከ ፍጻሜው ድረስ እንደቀጠለ ምንም ጥርጥር የለውም።
9. የጸሎትን መብት በፍጹም አቅልለን ልንመለከተው የማይገባን ለምንድን ነው?
9 መጸለይ ከባድ ነገር አይደለም። በማንኛውም ጊዜ፣ የትም ቦታ ሆነን ጮክ ብለንም ሆነ በልባችን መጸለይ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይህንን ውድ መብት በፍጹም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎትን ከጽናትና በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ ከመኖር ጋር ያያይዘዋል። (ሉቃስ 18:1፤ ሮሜ 12:12፤ ኤፌሶን 6:18 NW፤ ቆላስይስ 4:2) በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ካለው ከፍተኛ አካል ጋር ያልተገደበና ምን ጊዜም ክፍት የሆነ የግንኙነት መሥመር ሊኖረን መቻሉ ድንቅ ነገር አይደለምን? ደግሞም መሥመሩን ክፍት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ያዳምጠናል! ዳንኤል የጸለየበትንና ይሖዋም ለጸሎቱ መልስ መልአኩን የላከበትን አጋጣሚ አስታውስ። መልአኩ ከተፍ ያለው ዳንኤል ገና ጸልዮ ሳይጨርስ ነበር! (ዳንኤል 9:20, 21) በእኛ ዘመን መላእክት ተልከው የማይመጡ ቢሆንም ይሖዋ አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) የዳንኤልን ጸሎት እንደ ሰማ ሁሉ የእኛንም ጸሎት ይሰማል። በጸለይን ቁጥር ደግሞ ወደ ይሖዋ ስለምንቀርብ ልክ እንደ ዳንኤል እስከ ፍጻሜው ድረስ ለመጽናት የሚያስችለንን ዝምድና እንመሠርታለን።
በአምላክ ቃል አስተማሪነት መጽናት
10. የአምላክን ቃል እውነት ማስተማር ዳንኤል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር የነበረው ለምንድን ነው?
10 ዳንኤል በሌላም መልኩ ‘እስከ ፍጻሜው ድረስ መሄድ’ ነበረበት። እውነትን በማስተማር ሥራው መጽናት ይጠበቅበት ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች “እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር” በማለት የሚናገሩለት ብሔር አካል እንደሆነ ዘንግቶ አያውቅም። (ኢሳይያስ 43:10) ዳንኤል ይህንን ተልእኮ ለመፈጸም የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ሥራው በባቢሎን በምርኮ የነበረውን የገዛ ሕዝቡን ማስተማር ይጨምር እንደነበር እሙን ነው። ‘ባልንጀሮቹ’ እንደሆኑ ከተገለጹት ከአናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ጋር ከነበረው ግንኙነት በስተቀር ከሌሎች አይሁዳውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት እምብዛም የምናውቀው ነገር የለም። (ዳንኤል 1:7፤ 2:13, 17, 18) የቀረበ ወዳጅነታቸው እያንዳንዳቸው እንዲጸኑ በመርዳት በኩል የራሱ ድርሻ እንደነበረው የተረጋገጠ ነው። (ምሳሌ 17:17) ይሖዋ ልዩ ማስተዋል በመስጠት የባረከው ዳንኤል ለጓደኞቹ የሚያስተምረው ብዙ ነገር ነበረው። (ዳንኤል 1:17) ይሁን እንጂ ሌሎችንም ማስተማር ይጠበቅበት ነበር።
11. (ሀ) የዳንኤልን ሥራ ልዩ የሚያደርገው ምን ነበር? (ለ) ዳንኤል የተሰጠውን ለየት ያለ ኃላፊነት በመወጣት በኩል ምን ያህል ተሳክቶለታል?
11 ዳንኤል ከየትኛውም ነቢይ የበለጠ ለአሕዛብ ሹማምንት የመመሥከር ሥራ አከናውኗል። ብዙውን ጊዜ እነርሱን የሚያወግዝ መልእክት መናገር የነበረበት ቢሆንም ገዥዎቹን አልተጸየፋቸውም ወይም ከእርሱ በታች እንደሆኑ አድርጎ አልተመለከታቸውም። በአክብሮትና በጥበብ ያነጋግራቸው ነበር። ቀናተኛ እንደነበሩትና የሥልጣን ምኞት እንደተጠናወታቸው መሳፍንት ያሉ ዳንኤልን ለማጥፋት ያሴሩ ሰዎች ቢኖሩም ሌሎቹ ሹማምንት ያከብሩት ነበር። ይሖዋ ለነገሥታቱና ለጠቢባኑ እንቆቅልሽ የሆኑትን ምሥጢሮች የመግለጥ ችሎታ ሰጥቶት ስለነበር ነቢዩ በሰፊው ታዋቂ ሆኖ ነበር። (ዳንኤል 2:47, 48፤ 5:29) ዕድሜው ሲገፋ እንደ ወጣትነቱ ሮጥ ሮጥ ብሎ መሥራት እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ለተወደደው አምላኩ ምሥክር መሆን የሚችልበትን አጋጣሚ ሁሉ በታማኝነት በመጠቀም እስከ ፍጻሜው እንደቀጠለ ምንም አያጠራጥርም።
12. (ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በየትኛው የማስተማር ሥራ እንካፈላለን? (ለ) “በውጭ ባሉት ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
12 ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ እርስ በርስ እንደተጋገዙ ሁሉ ዛሬም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንድንጸና የሚረዱን የታመኑ ባልንጀሮች እናገኝ ይሆናል። እንዲሁም አንዳችን ሌላውን ‘በማጽናናትም’ እርስ በርሳችን እንማማራለን። (ሮሜ 1:11, 12) እኛም እንደ ዳንኤል ለማያምኑ ሰዎች የመመሥከር ተልዕኮ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) እንግዲያውስ እኛም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለ ይሖዋ ስንወያይ ‘የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም’ እንችል ዘንድ ችሎታችንን ማሻሻል ያስፈልገናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW) “በውጭ ባሉት ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክርም መከተላችን ይጠቅመናል። (ቆላስይስ 4:5) እንዲህ ያለው ጥበብ የእኛ ዓይነት እምነት ለሌላቸው ሰዎች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን ይጨምራል። ራሳችንን ከፍ አድርገን በመመልከት እነርሱን አናንቋሽሽም። (1 ጴጥሮስ 3:15) ከዚህ ይልቅ የአምላክን ቃል በጥበብና በዘዴ ተጠቅመን ልባቸውን ለመንካት በመሞከር ወደ እውነት ልናመጣቸው እንጥራለን። የአንድን ሰው ልብ ለመንካት መቻል እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው! እንዲህ ያለው ደስታ ልክ እንደ ዳንኤል እስከ ፍጻሜው ድረስ እንድንጸና ይረዳናል።
“ታርፋለህ”
13, 14. ብዙዎቹን ባቢሎናውያን ስለ ሞት ማሰብ ያስፈራቸው የነበረው ለምንድን ነው? የዳንኤል አመለካከት የተለየ የነበረው እንዴት ነው?
13 ቀጥሎ መልአኩ ለዳንኤል “ታርፋለህ” ሲል ማረጋገጫ ሰጠው። (ዳንኤል 12:13) የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? ዳንኤል ከፊቱ ሞት እንደሚጠብቀው አሳምሮ ያውቅ ነበር። ከአዳም ጀምሮ እስከ እኛ ዘመን ድረስ ሞት የሁሉም የሰው ልጆች የማይቀር እጣ ፋንታ ሆኖ ኖሯል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “ጠላት” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ይሁን እንጂ ዳንኤል ስለ ሞት የነበረው አመለካከት በዙሪያው የነበሩት ባቢሎናውያን ካላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ነበር። ለሐሰት አማልክት በሚቀርቡ 4,000 የሚያክሉ አምልኮዎች ለተጠላለፉት ባቢሎናውያን ሞት እጅግ በጣም አስፈሪ ነገር ነበር። በሕይወት ሳሉ ደስተኛ ያልነበሩ ወይም በግፍ የተገደሉ ሰዎች ከሞት በኋላ ሕያዋንን የሚያስጨንቁ ተበቃይ መናፍስት ይሆናሉ ብለው ያምኑ ነበር። በተጨማሪም በሰውና በእንስሳ መልክ የሚኖሩ አስፈሪ ጭራቆች የሞሉበት የሙታን ዓለም አለ የሚል እምነት ነበራቸው።
14 ዳንኤል ስለ ሞት ያለው አመለካከት ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው። ከዳንኤል ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን በመንፈስ አነሣሽነት “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” ሲል ጽፏል። (መክብብ 9:5) የሚሞቱ ሰዎችን በሚመለከት ደግሞ መዝሙራዊው “ነፍሱ [“መንፈሱ፣ የ1879 እትም] ትወጣለች፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” ሲል ዘምሮ ነበር። (መዝሙር 146:4) በመሆኑም ዳንኤል፣ መልአኩ የነገረው ነገር በትክክል እንደሚፈጸም ያውቅ ነበር። ሞት እረፍት ነው። ሐሳብ የለም፣ ቁጭት የለም፣ ሥቃይ የለም፤ ጭራቅ የሚባል ነገርም የለም። አልዓዛርም በሞተ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁኔታውን የገለጸው በተመሳሳይ መንገድ ነበር። “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል [“አርፏል፣” NW]” ብሏል።—ዮሐንስ 11:11
15. ከመወለድ ቀን የሞት ቀን የተሻለ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
15 ዳንኤል እንደሚሞት ቢያውቅም በፍርሃት ያልራደው ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ምክንያት ተመልከት። የአምላክ ቃል “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” ይላል። (መክብብ 7:1 NW) የሐዘን ወቅት የሆነው የሞት ቀን የደስታ ቀን ከሆነው የመወለድ ቀን እንዴት የተሻለ ሊሆን ይችላል? ምሥጢሩ ያለው “ስም” የሚለው ቃል ላይ ነው። “መልካም ሽቱ” ዋጋው እጅግ ውድ ሊሆን ይችላል። የአልዓዛር እህት የሆነችው ማርያም በአንድ ወቅት የአንድ ሰው የዓመት ደምወዝ የሚያክል ገንዘብ የሚያወጣ ውድ ሽቱ በኢየሱስ እግር ላይ አፍስሳ ነበር! (ዮሐንስ 12:1-7) የሰው ስም እንዴት ይህን ያህል ውድ ሊሆን ይችላል? የግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም በመክብብ 7:1 ላይ “መልካም ስም” ይላል። ይህን ያህል ውድ ዋጋ የሚኖረው ስሙ ሳይሆን ከስሙ በስተጀርባ ያለው ነገር ነው። አንድ ሰው ሲወለድ ያተረፈው ስም ሊኖር አይችልም፣ ምንም ዓይነት መልካም ሥራም አላስመዘገበም፤ ስሙ እንዲነሳ የሚያደርግ ጉልህ ባህርይ ወይም ጠባይም የለውም። ይሁን እንጂ በሕይወቱ ፍጻሜ ላይ ስሙ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያንጸባርቅ ይሆናል። በተለይ ደግሞ መልካም ሆኖ የተገኘው በአምላክ ፊት ከሆነ ከማንኛውም ቁሳዊ ንብረት እጅግ የላቀ ውድ ዋጋ ይኖረዋል።
16. (ሀ) ዳንኤል በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ የጣረው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል በይሖዋ ፊት መልካም ስም ለማትረፍ ያደረገው ጥረት እንደተሳካለት እርግጠኛ ሆኖ ወደ እረፍት ሊሄድ ይችል የነበረው ለምንድን ነው?
16 ዳንኤል በሕይወት ዘመኑ በሙሉ በአምላክ ፊት መልካም ስም ለማትረፍ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፤ ይሖዋም ጥረቱን ቆጥሮለታል። አምላክ “አቤቱ፣ መረመርኸኝ፣ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ” ሲል ለዘመረው ንጉሥ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ ዳንኤልንም በቅርብ ይከታተለው ነበር፤ ልቡንም መርምሯል። (መዝሙር 139:1, 2) ዳንኤል ፍጹም ሰው እንዳልነበር የታወቀ ነው። የኃጢአተኛው የአዳም ልጅ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአተኛ የሆነ ብሔር አካል ነበር። (ሮሜ 3:23) ይሁን እንጂ ዳንኤል ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ከአምላኩ ጋር በቅንነት ለመመላለስ ጥረት ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። በመሆኑም ይህ የታመነ ነቢይ ይሖዋ ኃጢአቱን ይቅር እንደሚልለትና እንደማይቆጥርበት እርግጠኛ መሆን የሚችልበት ምክንያት ነበረው። (መዝሙር 103:10-14፤ ኢሳይያስ 1:18) ይሖዋ የታመኑ አገልጋዮቹ የሚያደርጓቸውን መልካም ነገሮች ማስታወስ ይመርጣል። (ዕብራውያን 6:10) ከዚህም የተነሣ የይሖዋ መልአክ ዳንኤልን ሁለት ጊዜ “እጅግ የተወደድህ ሰው” ሲል ጠርቶታል። (ዳንኤል 10:11, 19) ይህም ዳንኤል በአምላክ ዘንድ የተወደደ ሰው ነበር ማለት ነው። ዳንኤል በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም እንዳተረፈ እርግጠኛ ሆኖ ማረፍ ይችላል ማለት ነው።
17. በይሖዋ ዘንድ ዛሬውኑ መልካም ስም ማትረፋችን አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 እያንዳንዳችን ‘በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም አትርፌያለሁን?’ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ይሆናል። የምንኖረው አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ማናችንም ብንሆን በማንኛውም ጊዜ ልንሞት እንደምንችል ማሰባችን እውነታውን መገንዘባችንን እንጂ ክፉ ነገር ማሰባችንን የሚያሳይ አይደለም። (መክብብ 9:11) እንግዲያውስ ዛሬውኑ ሳንዘገይ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው። እንደዚያ ካደረግን ሞትን የምንፈራበት ምክንያት አይኖርም። እንደ እንቅልፍ ያለ እረፍት ነው ማለት ነው። ከእንቅልፍ በኋላ ደግሞ መንቃት አለ!
“ትቆማለህ”
18, 19. (ሀ) መልአኩ፣ ዳንኤል ወደፊት ‘እንደሚቆም’ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ዳንኤል ከትንሣኤ ተስፋ ጋር ጥሩ ትውውቅ ይኖረዋል የምንለው ለምንድን ነው?
18 የዳንኤል መጽሐፍ የሚደመደመው አምላክ ለአንድ ሰብዓዊ ፍጡር ከገባቸው ቃሎች ሁሉ እጅግ ውብ በሆነው የተስፋ ቃል ነው። የይሖዋ መልአክ ዳንኤልን “በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ” ብሎታል። መልአኩ ምን ማለቱ ነበር? ትንሽ ቀደም ብሎ የጠቀሰው ‘እረፍት’ ሞት ማለት ስለሆነ ዳንኤል ‘እንደሚቆም’ መነገሩ ከትንሣኤ ሌላ ምንም ማለት ሊሆን አይችልም! * እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ትንሣኤ በቀጥታ የተጠቀሰበት የመጀመሪያው ቦታ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ነው ይላሉ። (ዳንኤል 12:2) ይሁን እንጂ ይህ አባባላቸው ስህተት ነው። ዳንኤል ስለ ትንሣኤ ተስፋ አሳምሮ ያውቅ ነበር።
19 ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ ከሁለት መቶ ዘመናት ገደማ በፊት የጻፋቸውን የሚከተሉትን ቃላት ዳንኤል ያውቃቸው እንደነበር ምንም አያጠራጥርም:- “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፣ . . . ምድርም ሙታንን ታወጣለችና፣ ንቁ ዘምሩም።” (ኢሳይያስ 26:19) ከዚህ ብዙ ጊዜ ቀደም ብሎም ቢሆን ኤልያስና ኤልሳዕ ትንሣኤ ለማከናወን የሚያስችል ኃይል ከይሖዋ አግኝተው ነበር። (1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37) ከዚያ በፊትም ቢሆን የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሃና፣ ይሖዋ ሰዎችን ከሲኦል ማለትም ከመቃብር ሊያወጣ እንደሚችል እምነት እንዳላት ገልጻለች። (1 ሳሙኤል 2:6) ከዚህ ጊዜ በፊትም የታመነው ኢዮብ የነበረውን ተስፋ በሚከተሉት ቃላት ገልጿል:- “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።”—ኢዮብ 14:14, 15
20, 21. (ሀ) ዳንኤል ከየትኛው ትንሣኤ እንደሚካፈል የተረጋገጠ ነው? (ለ) በገነት ውስጥ ትንሣኤ በምን መልኩ እንደሚከናወን የተረጋገጠ ነው?
ሉቃስ 14:14) ይህ ለዳንኤል ምን ዓይነት ጊዜ ይሆንለት ይሆን? የአምላክ ቃል ስለዚህ ጊዜ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ።
20 እንደ ኢዮብ ሁሉ ዳንኤልም አንድ ቀን ይሖዋ እርሱን ወደ ሕይወት መልሶ ለማምጣት እንደሚናፍቅ እርግጠኛ የሚሆንበት ምክንያት ነበረው። ያም ሆኖ ግን አንድ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ይህን ተስፋውን ሲያረጋግጥለት መስማት እጅግ የሚያጽናና ሆኖ አግኝቶት መሆን አለበት። አዎን፣ ዳንኤል በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በሚከናወነው ‘የጻድቃን ትንሣኤ’ ጊዜ ይቆማል። (21 ይሖዋ “የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 14:33) እንግዲያውስ በገነት ውስጥ የሚከናወነው ትንሣኤ በሥርዓት እንደሚከናወን ግልጽ ነው። ምናልባት ከአርማጌዶን በኋላ ጥቂት ጊዜ ማለፍ ያስፈልገው ይሆናል። (ራእይ 16:14, 16) የአሮጌው የነገሮች ሥርዓት ርዝራዥ ሁሉ መጽዳት የሚኖርበት ሲሆን ሙታንን ለመቀበልም አንዳንድ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ የተረጋገጠ ነው። ሙታን ወደ ሕይወት የሚመለሱበትን ሥርዓት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:23) ስለ ‘ጻድቃንና ዓመፀኞች’ ትንሣኤ ስናስብ ጻድቃን ቀድመው እንደሚነሱ መጠበቃችን ምክንያታዊ ይሆናል። (ሥራ 24:15) እንደዚያ ከሆነ እንደ ዳንኤል ያሉት የታመኑ የጥንት ሰዎች ወደ ሕይወት የሚመለሱትን በቢልዮን የሚቆጠሩ ‘ዓመፀኞችን’ ማስተማርን ጨምሮ የምድርን ጉዳዮች በማስተዳደሩ ሥራ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ።—መዝሙር 45:16
22. ዳንኤል መልስ ለማግኘት የሚጓጓላቸው አንዳንዶቹ ጥያቄዎች የትኞቹ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው?
22 ዳንኤል እንዲህ ያሉትን ኃላፊነቶች ከመቀበሉ በፊት አንዳንድ ጥያቄዎች እንደሚኖሩት የተረጋገጠ ነው። ደግሞም የተሰጡትን ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ትንቢቶች በሚመለከት “ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም” ብሎ ነበር። (ዳንኤል 12:8) እነዚህን መለኮታዊ ምሥጢሮች መረዳት ሲችል ምንኛ ይደሰት ይሆን! ስለ መሲሑም ሁሉንም ነገር መስማት እንደሚፈልግ ምንም አያጠራጥርም። ዳንኤል ከእርሱ ዘመን አንስቶ እስከ ጊዜያችን ድረስ የተፈራረቁትን የዓለም ኃያላን፣ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ስደት ቢደርስባቸውም የጸኑትን ‘የልዑሉን ቅዱሳን’ እንዲሁም ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ስለ መጥፋታቸው ሲሰማ እጅግ ይገረማል።—ዳንኤል 2:44፤ 7:22፤ 12:4
ዳንኤል በገነት ውስጥ የሚኖረው ዕጣና የአንተ ዕጣ ፋንታ!
23, 24. (ሀ) ዳንኤል ትንሣኤ አግኝቶ የሚነሣበት ዓለም እርሱ ከሚያውቀው የተለየ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል በገነት ውስጥ ቦታ ይኖረው ይሆን? እንዴት እናውቃለን?
23 ዳንኤል እርሱ ከኖረበት ዘመን እጅግ የተለየ ስለሚሆነው ስለዚያ ዓለምም ለማወቅ ይፈልጋል። እርሱ የሚያውቀውን ዓለም ሲያምስ የኖረው ጦርነትና ጭቆና ሁሉ ተጠራርጎ ጠፍቷል። ሐዘን፣ ሕመምና ሞት አይኖርም። (ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24) ሁሉም ሰው ግን የተትረፈረፈ ምግብ፣ በቂ መኖሪያና የሚያረካ ሥራ ይኖረዋል። (መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 65:21, 22) መላው የሰው ዘር ኅብረት ያለው አንድ ደስተኛ ቤተሰብ ይሆናል።
24 ዳንኤል በዚህ ዓለም ውስጥ ቦታ እንደሚኖረው የታወቀ ነው። መልአኩ “በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ” ብሎታል። እዚህ ላይ “ዕጣ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ጥሬ ፍችው የመሬት ርስትን የሚያመለክት ነው። * ዳንኤል ተመልሶ የተቋቋመውን የእስራኤል ምድር ስለመከፋፈል የተነገረውን የሕዝቅኤል ትንቢት አሳምሮ ያውቅ የነበረ መሆን አለበት። (ሕዝቅኤል 47:13–48:35) የሕዝቅኤል ትንቢት በገነት ውስጥ ፍጻሜውን ሲያገኝ ምን ትርጉም ይኖረዋል? የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ በገነት ውስጥ ቦታ ይኖራቸዋል። ምድሩም ሥርዓት ባለውና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይከፋፈላል። እርግጥ ዳንኤል በገነት ውስጥ የሚኖረው ዕጣ የመሬት ርስት ከማግኘት የበለጠ ነገርንም የሚጨምር ይሆናል። አምላክ በገነት በሚፈጽመው ዓላማው ውስጥ የሚኖረውንም ድርሻ ይጨምራል። ለዳንኤል ቃል የተገባለት ተስፋ አስተማማኝ ነው።
25. (ሀ) አንተን የሚማርኩህ የገነት ሕይወት ገጽታዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? (ለ) የሰው ልጆች መኖር ያለባቸው በገነት ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
25 ይሁን እንጂ ስለ አንተስ ዕጣ ምን ማለት ይቻላል? ይህ የተስፋ ቃል ኢሳይያስ 11:9፤ ዮሐንስ 6:45) አዎን፣ አንተም በገነት ውስጥ ቦታ አለህ። ዛሬ የገነት ተስፋ ለአንዳንድ ሰዎች እንግዳ ነገር ሊሆንባቸው ቢችልም ይሖዋ ገና ከመጀመሪያው እንድንኖር አስቦ የነበረው እንዲህ ባለ ቦታ መሆኑን አስታውስ። (ዘፍጥረት 2:7-9) እንደዚያ ከሆነ በምድር ላይ የሚኖሩት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትክክለኛው የመኖሪያ ሥፍራ ገነት ነው ማለት ነው። አዎን፣ መኖር ያለባቸው በዚያ ነው። ገነት ውስጥ ለመኖር መብቃት ወደ ቤታችን እንደ መመለስ ይቆጠራል።
ለአንተም ሊሠራ ይችላል። ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በዕጣ ክፍላቸው ‘እንዲቆሙና’ በገነት ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው ይፈልጋል። እስቲ አስበው! በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱትን ሌሎች የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ጨምሮ ዳንኤልን በአካል ማግኘት እጅግ የሚያስደስት ነገር ነው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ አምላክን ያውቁና ይወድዱት ዘንድ መማር የሚያስፈልጋቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎችም ከሞት ይነሣሉ። ምድራዊ መኖሪያችንን በመንከባከብ፣ ብዙ ኅብር ያላትና የማይደበዝዝ ውበት የተላበሰች ገነት እንድትሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ ስትካፈል ይታይህ። ከይሖዋ በመማር ለሰው ልጆች ባቀደው መንገድ መኖርን ስትማር ምን ዓይነት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ገምት። (26. ይሖዋ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ መጠባበቅ ቀላል ነገር አለመሆኑን እንደሚገነዘብ የሚያሳየው ምንድን ነው?
ዕንባቆም 2:3፤ ከምሳሌ 13:12 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ መጨረሻው ልክ በተቀጠረለት ጊዜ ይመጣል።
26 ይህን ሁሉ ነገር ስናስብ ልባችን በአድናቆት ይሞላል። አይሞላም እንዴ? አንተ ራስህስ በዚያ ለመገኘት አትናፍቅም? እንግዲያውስ የይሖዋ ምሥክሮች የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚመጣ ለማወቅ መጓጓታቸው ምንም አያስገርምም! ይህን ቀን መጠባበቅ ቀላል ነገር አይደለም። ይሖዋ ራሱ ፍጻሜው “ቢዘገይም” ‘ተጠባበቁት’ ሲል ስላሳሰበን መጠባበቁ ቀላል እንዳልሆነ ይገነዘባል። በዚሁ ጥቅስ ላይ “አይዘገይም” የሚል ማረጋገጫ ስለተሰጠን ቢዘገይም ሲል በእኛ አመለካከት የዘገየ መስሎ ሊታየን ይችላል ማለቱ ነው። (27. በአምላክ ፊት ለዘላለም ለመቆም እንድትችል ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
27 ፍጻሜው እየተቃረበ ሲመጣ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እንደ ተወደደው የይሖዋ ነቢይ እንደ ዳንኤል በታማኝነት ጽና። የአምላክን ቃል በትጋት አጥና። ከልብህ ጸልይ። ከእምነት ጓደኞችህ ጋር በፍቅር ተሰብሰብ። እውነትን ለሌሎች በቅንዓት አስተምር። ይህ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየቀረበ በሚሄድበት በእያንዳንዱ ዕለት የልዑሉ ታማኝ አገልጋይ ለመሆንና የታመንህ የቃሉ ጠበቃ ሆነህ ለመገኘት ባደረግኸው ቁርጥ ውሳኔ ጽና። በተቻለ መጠን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለዘላለም በደስታ በፊቱ የመቆምን መብት እንዲሰጥህ እንመኛለን!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ዳንኤል ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰደው በ617 ከዘአበ ሲሆን ዕድሜው ገና በአሥራዎቹ ውስጥ እንደነበር እሙን ነው። ይህንን ራእይ የተቀበለው በቂሮስ ሦስተኛ ዓመት ወይም በ536 ከዘአበ ነው።—ዳንኤል 10:1
^ አን.18 ዘ ብራውን ድራይቨር-ብሪገስ-ሂብሩ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን እንደሚለው ከሆነ እዚህ ላይ ‘መቆም’ ለማለት የገባው የዕብራይስጥ ቃል ‘ከሞት መነሣትን’ የሚያመለክት ነው።
^ አን.24 የዕብራይስጡ ቃል ዕጣ ለመጣጣል ከሚጠቀሙባቸው ‘ጠጠሮች’ ጋር ተዛምዶ አለው። አንዳንድ ጊዜ ርስት የሚከፋፈለው በዚህ መንገድ ነበር። (ዘኁልቁ 26:55, 56) ኤ ሃንድ ቡክ ኦን ዘ ቡክ ኦቭ ዳንየል የተባለው መጽሐፍ እዚህ ላይ የገባው ቃል “(አምላክ) ለአንድ ሰው የመደበው” የሚል ትርጉም አለው ይላል።
ምን አስተውለሃል?
• ዳንኤል እስከ ፍጻሜው እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው?
• ዳንኤል እንደሚሞት ቢያውቅም በፍርሃት ያልራደው ለምን ነበር?
• መልአኩ ‘ዳንኤል በዕጣ ክፍሉ እንደሚቆም’ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
• አንተ በግልህ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት በመከታተልህ የተጠቀምኸው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 307 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 318 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንተስ እንደ ዳንኤል የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ትከታተላለህ?