በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍ

ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍ

ምዕራፍ ሁለት

ዳንኤል—ክስ የቀረበበት መጽሐፍ

1, 2. የዳንኤል መጽሐፍ ችሎት ፊት እንደቀረበ ያህል የሆነው እንዴት ነው? የመከላከያ ማስረጃዎቹን መመርመሩ አስፈላጊ ነው የምትለውስ ለምንድን ነው?

አንድ ከፍተኛ ጉዳይ ለመስማት በተሰየመ የሕግ ችሎት ላይ ተገኝተሃል እንበል። አንድ ግለሰብ በማጭበርበር ወንጀል ተከስሷል። አቃቤ ሕጉ ሰውዬው ጥፋተኛ መሆኑን በእርግጠኝነት ይናገራል። ይሁንና ክሱ የቀረበበት ግለሰብ ለረጅም ጊዜ በሐቀኛነቱ የሚታወቅ ሰው ነው። የሚቀርበውን የመከላከያ መልስ ለመስማት አትጓጓም?

2 የመጽሐፍ ቅዱሱን የዳንኤል መጽሐፍ በሚመለከት ከፊትህ የተደቀነው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። የመጽሐፉ ጸሐፊ በሐቀኝነቱ የሚታወቅ ሰው ነው። በስሙ የሚጠራውም መጽሐፍ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ኖሯል። በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር በነበረ ዳንኤል በሚባል ዕብራዊ ነቢይ እንደተጻፈና ትክክለኛ ታሪክ የያዘ መሆኑን መጽሐፉ ራሱ ይመሰክራል። በትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስሌት መሠረት ይህ መጽሐፍ ከ618 እስከ 536 ከዘአበ ድረስ ባለው ጊዜ የተፈጸሙ ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን ተጽፎ የተጠናቀቀው በ536 ከዘአበ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ ክስ ቀርቦበታል። ጥቂት ኢንሳይክለፒዲያዎችና ሌሎች የማመሳከሪያ ጽሑፎች መጽሐፉ ፈጠራ ነው ለማለት ሲዳዳቸው አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ አፋቸውን ሞልተው እንደዚያ ብለው ይናገራሉ።

3. ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኛነት በሚመለከት ምን ይላል?

3 ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ የዳንኤል መጽሐፍ በአንድ ወቅት “ባብዛኛው ሰው ዘንድ ትክክለኛ ታሪክና እውነተኛ ትንቢት እንደያዘ ይታመን ነበር” ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። ይኼው ኢንሳይክለፒዲያ እውነታው ሲታይ ግን የዳንኤል መጽሐፍ “የተጻፈው አይሁዳውያን ብሔራዊ ቀውስ ገጥሟቸው ሳለ ማለትም [በሶርያው ንጉሥ] በአንታይከስ ኢፒፈኒስ አራተኛ ስደት ይደርስባቸው በነበረበት በኋለኛው ዘመን ነው” ብሏል። ኢንሳይክለፒዲያው እንደሚለው ከሆነ መጽሐፉ የተጻፈው ከ167 እስከ 164 ከዘአበ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የዳንኤል መጽሐፍ ጸሐፊ “ከእርሱ በፊት የተፈጸሙትን ታሪኮች ወደፊት እንደሚፈጸሙ ትንቢቶች አድርጎ አቀረበ” እንጂ ትንቢት አልተናገረም ሲል ይኸው ኢንሳይክለፒዲያ ተከራክሯል።

4. በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ትችት መሰንዘር የተጀመረው መቼ ነው? ከቅርብ መቶ ዓመታት ወዲህ ይህን ዓይነቱን ትችት ያቀጣጠለው ምንድን ነው?

4 እንዲህ ያሉ ሐሳቦች የመነጩት ከየት ነው? በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ትችት ሲሰነዘር ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ትችት መሰንዘር የጀመረው በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ፖርፍሬ የተባለው ፈላስፋ ነው። ክርስትና ያሳደረው ተጽዕኖ በሮም ግዛት እንደነበሩት ብዙ ሰዎች ሁሉ እርሱንም ስጋት ላይ ጥሎት ነበር። ይህንን “አዲስ” ሃይማኖት ለማዳከም ሲል 15 መጻሕፍት ጽፏል። ከእነዚህ መካከል 12ኛው በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ያነጣጠረ ነበር። ፖርፍሬ የዳንኤል መጽሐፍ በሁለተኛ መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረ አንድ አይሁዳዊ ፈጥሮ የጻፈው መጽሐፍ ነው ሲል አውግዞታል። በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመንም ተመሳሳይ ነቀፋ ተሰንዝሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችና ተጨባጭ ነገር ካላገኘን አናምንም በሚሉት ወገኖች አመለካከት ትንቢት መናገር ማለትም ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ ማሳወቅ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ዳንኤል በዚህ ረገድ የተመቻቸ ዒላማ ሆኖላቸዋል። እርሱም ሆነ የጻፈው መጽሐፍ ችሎት ፊት የቀረቡ ያክል ነው ለማለት ይቻላል። ተቺዎቹ ይህ መጽሐፍ አይሁዳውያን ባቢሎን ውስጥ በግዞት በነበሩበት ጊዜ በዳንኤል የተጻፈ ሳይሆን ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በሌላ ሰው የተጻፈ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ አለን ይላሉ። * እንዲህ ያለው ነቀፋ እጅግ ከመበራከቱ የተነሣ አንድ ጸሐፊ በመጽሐፉ ላይ የሚሰነዘረውን ትችት ለመከላከል ዳንኤል በተቺዎች ጉድጓድ የሚል መጽሐፍ አዘጋጅተዋል።

5. የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኝነት በሚመለከት የሚነሳው ጥያቄ ይህን ያህል አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ተቺዎቹ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሯቸው ነገሮች ማስረጃ አላቸው? ወይስ ማስረጃዎቹ የመከላከያውን መልስ የሚደግፉ ናቸው? ይህ ነገር አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ያስነሳል። የዚህ ጥንታዊ መጽሐፍ ስም መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን የወደፊት ተስፋችንም ጥያቄ ላይ ወድቋል። የዳንኤል መጽሐፍ የፈጠራ መጽሐፍ ከሆነ ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ተስፋ የሚናገረውም ነገር እንዲሁ ከንቱ ተስፋ ነው ማለት ነው። እውነተኛ ትንቢቶችን የያዘ ከሆነ ግን እነዚህ ትንቢቶች ለእኛ ምን ትርጉም እንዳላቸው ለመማር እንደምትጓጓ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህንን በአእምሮአችን እንያዝና በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የሚሰነዘሩትን አንዳንድ ውንጀላዎች እንመርምር።

6. አንዳንድ ጊዜ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ በሚመለከት ምን ክስ ይሰነዘራል?

6 ለምሳሌ ያህል በኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና የቀረበውን ክስ ተመልከት:- በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ [በባቢሎን የነበረውን የምርኮ ዘመን በመሰለው] በጥንቱ ዘመን የተፈጸሙ “ብዙ ታሪካዊ ክንውኖች በእጅጉ ተዛብተው ቀርበዋል።” ይህ አባባል በእርግጥ እውነት ነውን? ስህተት ናቸው የተባሉትን ሦስት ነጥቦች እስቲ አንድ በአንድ እንመልከት።

አይታወቅም የተባለው ንጉሥ ጉዳይ

7. (ሀ) ዳንኤል ስለ ብልጣሶር መጥቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችን ሲያስደስታቸው የኖረው ለምንድን ነው? (ለ) ብልጣሶር ልብ ወለድ ሰው ነው የሚለው ሐሳብ ምን ገጥሞታል?

7 ዳንኤል የባቢሎን ከተማ ስትወድቅ ንጉሥ ሆኖ ያስተዳድር የነበረው የናቡከደነፆር ‘ልጅ’ ብልጣሶር እንደሆነ ጽፏል። (ዳንኤል 5:1, 11, 18, 22, 30) ተቺዎች ብልጣሶር የሚለው ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ የትም ቦታ ተጠቅሶ ስለማይገኝ ይህ አባባል ስህተት ነው እያሉ ለረጅም ጊዜ ሲተቹ ቆይተዋል። የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ናቡከደነፆርን እንደተካና የባቢሎን የመጨረሻ ንጉሥ እንደነበር የሚናገሩለት ናቦኒደስ ነው። በመሆኑም በ1850 ፈርዲናንድ ሂትሲክ፣ ብልጣሶር የጸሐፊው ሐሳብ የወለደው ሰው እንደሆነ ግልጽ ነው ብለው ነበር። ነገር ግን ሂትሲክ ትንሽ የቸኮሉ አይመስልህም? ደግሞስ በዚያ የታሪካዊ መዛግብት ቁጥር እጅግ ውስን በነበረበት ዘመን የአንድ ንጉሥ ስም ተጠቅሶ አለመገኘቱ ጭራሽ እንደዚያ የሚባል ንጉሥ አልነበረም ለማለት በእርግጥ ማስረጃ ሊሆን ይችላልን? የሆነ ሆኖ በ1854 በዛሬዋ ኢራቅ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ኡር በምትባለው የጥንቷ የባቢሎን ከተማ አካባቢ በተደረገው ቁፈራ አንዳንድ ትናንሽ ሞላላ ሸክላዎች ተገኙ። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው እነዚህ የንጉሥ ናቦኒደስ መዛግብት ስለ “ታላቁ ልጄ ብልሳርሱር” በሚል ያቀረበውን ጸሎት ይዘው ተገኝተዋል። ተቺዎች ሳይቀሩ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ብልጣሶር መሆኑን ለመቀበል ተገደዋል።

8. ዳንኤል ብልጣሶርን በሥልጣን ላይ እንዳለ ንጉሥ አድርጎ መግለጹ እውነት መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?

8 ይሁንና ተቺዎች ይህ አላረካቸውም። ኤች ኤፍ ቶልበት የተባሉ አንድ ተቺ “ይህ ምንም ማስረጃ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል። በእነዚህ ሸክላዎች ላይ የተጠቀሰው ልጅ ሕፃን ልጅ ሊሆን ይችላል፤ ዳንኤል ግን የገለጸው በሥልጣን ላይ እንዳለ ንጉሥ አድርጎ ነው ብለዋል። ይሁንና የቶልበት አስተያየት በጽሑፍ ታትሞ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ብልጣሶር ጸሐፊዎችና የቤት ውስጥ ሠራተኞች እንደነበሩት የሚገልጹ ተጨማሪ ሰሌዳዎች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ብልጣሶር ሕፃን ልጅ አልነበረም! በመጨረሻም በአንድ ወቅት ናቦኒደስ ለተወሰኑ ዓመታት ከባቢሎን ወጣ ብሎ እንደነበር የሚገልጹ ሰሌዳዎች መገኘታቸው ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል። በተጨማሪም እነዚሁ ሰሌዳዎች በዚህ ወቅት ናቦኒደስ በባቢሎን የነበረውን “ንግሥና” ለትልቁ ልጁ (ለብልጣሶር) “በአደራ ሰጥቶ ” እንደነበር ገልጸዋል። በእነዚህ ጊዜያት ብልጣሶር ንጉሥ ወይም በሌላ አባባል ከአባቱ ጋር የሚገዛ ተባባሪ ገዥ ነበር ለማለት ይቻላል። *

9. (ሀ) ብልጣሶር የናቡከደነፆር ልጅ መሆኑን ዳንኤል ሊጠቅስ የሚችልበት መንገድ ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ተቺዎች ዳንኤል የናቦኒደስን መኖር የሚጠቁም ትንሽም እንኳ ፍንጭ አልሰጠም ማለታቸው ስህተት የሚሆነው እንዴት ነው?

9 ይህም ያላረካቸው አንዳንድ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ብልጣሶር የናቡከደነፆር ልጅ እንደሆነ እንጂ የናቦኒደስ ልጅ እንደሆነ አይደለም ብለው ተቃውሞ ያሰማሉ። አንዳንዶችም ዳንኤል፣ ናቦኒደስ የሚባል ሰው ስለመኖሩ እንኳን ምንም የጠቀሰው ነገር የለም ይላሉ። ይሁን እንጂ ቀረብ ብለን ከመረመርናቸው ሁለቱም ተቃውሞዎች መሠረት የላቸውም። ናቦኒደስ የናቡከደነፆርን ሴት ልጅ ያገባ ይመስላል። በዚህ መሠረት ብልጣሶር የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ ይሆናል ማለት ነው። የዕብራይስጡም ሆነ የአረማይኩ ቋንቋ “አያት” ወይም “የልጅ ልጅ” የሚል ቃል የሌላቸው በመሆኑ “ልጅ” ከተባለ “የልጅ ልጅ” አልፎ ተርፎም “ዝርያ” ማለት ሊሆን ይችላል። (ከ⁠ማቴዎስ 1:1 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ብልጣሶር የናቦኒደስ ልጅ ነው መባሉን አይቃወምም። ብልጣሶር በግድግዳው ላይ በታየው አስደንጋጭ ጽሕፈት በተጨነቀ ጊዜ የቃሉን ፍቺ ለሚነግረው ሰው በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛውን ቦታ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶ ነበር። (ዳንኤል 5:7) በመንግሥቱ ውስጥ ሁለተኛውን ሳይሆን ሦስተኛውን ቦታ እንደሚሰጥ ቃል የገባበት ምክንያት ምንድን ነው? ይህ አባባሉ አንደኛውና ሁለተኛው ቦታ በወቅቱ ተይዞ የነበረ መሆኑን ይጠቁማል። አዎን፣ በናቦኒደስና በልጁ በብልጣሶር ተይዞ ነበር።

10. የዳንኤል መጽሐፍ ስለ ባቢሎናውያን ንጉሣዊ አገዛዝ ያቀረበው ዘገባ ከሌሎች ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊዎች የበለጠ ዝርዝር ጉዳዮችን ሊያካትት የቻለው ለምንድን ነው?

10 እንግዲያው ዳንኤል ስለ ብልጣሶር መጥቀሱ ‘ታሪኩን አዛብቶ’ አቅርቧል ለማለት ማስረጃ አይሆንም። እንዲያውም በተቃራኒው ዳንኤል የባቢሎንን ታሪክ ለመጻፍ ብሎ ባይነሣም ስለ ባቢሎናውያን ንጉሣዊ አገዛዝ እንደ ሄሮዶተስ፣ ዜኖፎንና ቤራሰስ ካሉት የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች የተሻለ ዝርዝር አስፍሮልናል። ዳንኤል እነርሱ ሳይጠቅሷቸው የቀሩትን ነገሮች ሊዘግብ የቻለው ለምንድን ነው? በዚያው በባቢሎን ይኖር ስለነበር ነው። መጽሐፉ የዓይን ምሥክር የነበረ ሰው ሥራ እንጂ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በተነሣ አስመሳይ ሰው የተጻፈ አይደለም።

ሜዶናዊው ዳርዮስ ማን ነበር?

11. በዳንኤል ገለጻ መሠረት ሜዶናዊው ዳርዮስ ማን ነው? ይሁን እንጂ ስለ እርሱ ምን ተብሏል?

11 ዳንኤል ባቢሎን በወደቀች ጊዜ ‘ሜዶናዊው ዳርዮስ’ የተባለ ንጉሥ መግዛት እንደጀመረ ዘግቧል። (ዳንኤል 5:31) ሜዶናዊው ዳርዮስ የሚለው ስም እስካሁን በአርኪኦሎጂያዊም ሆነ በሌሎች ምንጮች ላይ አልተገኘም። በመሆኑም ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ ይህ ዳርዮስ “ልብ ወለድ ገፀ ባሕርይ” ነው ብሏል።

12. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ሜዶናዊው ዳርዮስ የሚባል ሰው አልነበረም ለማለት መቸኮል የማይገባቸው ለምንድን ነው? (ለ) የሜዶናዊው ዳርዮስን ማንነት በተመለከተ አንዱ አማራጭ ምንድን ነው? ይህንንስ የሚጠቁም ምን ነገር አለ?

12 አንዳንድ ምሁራን ግን ትንሽ ቆጠብ ብለዋል። ለነገሩማ ከአሁን ቀደምስ ተቺዎች ብልጣሶርን “ልብ ወለድ” ሰው ነው ብለውት አልነበር። የዳርዮስም ሁኔታ ከዚሁ የተለየ እንደማይሆን እሙን ነው። እስከ አሁንም የተገኙት የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው ሰሌዳዎች እንደሚጠቁሙት የፋርሱ ቂሮስ ከድሉ በኋላ ወዲያውኑ “የባቢሎን ንጉሥ” የሚል ማዕረግ አልተቀበለም። አንድ ተመራማሪ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “‘የባቢሎን ንጉሥ’ የሚል ማዕረግ የነበረው ሰው ካለ በቂሮስ ሥር ሆኖ የሚያስተዳድር እንደራሴ ንጉሥ ይሆናል እንጂ ቂሮስ ራሱ አይደለም።” ዳርዮስ የሚለው ስም በባቢሎን ለተሾመ ኃያል ሜዶናዊ ገዥ የተሰጠ የሥልጣን ስም ወይም ማዕረግ ሊሆን ይችል ይሆን? አንዳንዶች ዳርዮስ የተባለው ጉባሩ ሊሆን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ቂሮስ ጉባሩን በባቢሎን ላይ ገዥ አድርጎ ሾሞት የነበረ ሲሆን ትልቅ ሥልጣን ተሰጥቶት ያስተዳድር የነበረ ሰው ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብትም ይመሠክራሉ። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈበት አንድ ሰሌዳ ጉባሩ በባቢሎን ላይ የበታች ገዥዎችን ይሾም እንደነበር ይናገራል። የሚያስገርመው ዳርዮስም በባቢሎን መንግሥት እንዲያስተዳድሩ 120 መሳፍንት መሾሙን ዳንኤል ተናግሯል።—ዳንኤል 6:1

13. ሜዶናዊው ዳርዮስ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ በሌሎች የታሪክ መዛግብት ላይ ግን ሳይጠቀስ የቀረበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

13 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ስለዚህ ንጉሥ ትክክለኛ ማንነት ቀጥተኛ ማስረጃ ይገኝ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ግን አርኪኦሎጂ በዚህ ረገድ የሚለው ምንም ነገር አለመኖሩ ዳርዮስ “ልብ ወለድ” ሰው ነው ለማለትም ሆነ መላው የዳንኤል መጽሐፍ ፈጠራ ነው ለማለት የሚያስችል ምክንያት አይሆንም። ይልቁንም የዳንኤልን ዘገባ ዛሬ ካሉት የታሪክ መዛግብት ሁሉ ይበልጥ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተና አንድ የዓይን ምሥክር የሰጠው እማኝነት እንደሆነ አድርጎ መመልከቱ ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆናል።

የኢዮአቄም ግዛት

14. የንጉሥ ኢዮአቄምን የግዛት ዘመን በሚመለከት በዳንኤልና በኤርምያስ መካከል ልዩነት የለም ልንል የምንችለው እንዴት ነው?

14 ዳንኤል 1:1 እንዲህ ይላል:- “የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።” ተቺዎች ይህ ጥቅስ የኢዮአቄም አራተኛ ዓመት የናቡከደነፆር የመጀመሪያ ዓመት ነው ከሚለው ከኤርምያስ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ስለሚመስል ስህተት ነው ይላሉ። (ኤርምያስ 25:1፤ 46:2) ዳንኤል ኤርምያስን መቃረኑ ነውን? ተጨማሪ መረጃዎችን ከመረመርን ጉዳዩ ግልጽ ይሆናል። ኢዮአቄም በ628 ከዘአበ ፈርኦን ኒካዑ ለመጀመሪያ ጊዜ ንጉሥ አድርጎ ሲሾመው ለዚህ ግብጻዊው ገዥ የአሻንጉሊት መንግሥት ከመሆን አላለፈም ነበር። ይህም ናቡከደነፆር በ624 ከዘአበ በአባቱ ዙፋን ከመቀመጡ ከሦስት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው። ከዚያም ወዲያው (በ620 ከዘአበ) ናቡከደነፆር ይሁዳን በመክበብ ኢዮአቄም በባቢሎን ሥር የሚያስተዳድር እንደራሴ ንጉሥ አድርጎ ሾመው። (2 ነገሥት 23:34፤ 24:1) በባቢሎን ለሚኖር አንድ አይሁዳዊ የኢዮአቄም ‘ሦስተኛ ዓመት’ ማለት ለባቢሎን እንደራሴ ንጉሥ ሆኖ ማገልገል የጀመረበት ሦስተኛ ዓመት ማለት ነው። ዳንኤል የጻፈው ከዚህ አንጻር ነው። ኤርምያስ ግን የጻፈው በዚያው በኢየሩሳሌም ከነበሩት አይሁዳውያን አመለካከት አንጻር ነው። በመሆኑም የኢዮአቄም ንግሥና የጀመረው ፈርኦን ኒካዑ ንጉሥ ካደረገው ጊዜ አንስቶ እንደሆነ አድርጎ ገልጿል።

15. በ⁠ዳንኤል 1:1 ላይ የሚገኘውን የዘመን ስሌት መቃወም ደካማ የመከራከሪያ ነጥብ የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 እንዲያውም ስህተት ናቸው የተባሉት እነዚህ ነገሮች ዳንኤል መጽሐፉን የጻፈው ከአይሁዳውያን ግዞተኞች ጋር በባቢሎን ሳለ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይሁን እንጂ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተነሣው ጥያቄ ሌላም ጉልህ ስህተት ይታይበታል። የዳንኤል ጸሐፊ የኤርምያስ መጽሐፍ እንደነበረውና እንዲያውም ከዚያ መጽሐፍም ጠቅሶ እንደጻፈ ልብ በል። (ዳንኤል 9:2) የዳንኤልን መጽሐፍ የጻፈው ሰው ተቺዎቹ እንደሚሉት የተዋጣለት አስመሳይ ከሆነ እንደ ኤርምያስ ያለውን ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ምንጭ የሚቃረን ነገር ለዚያውም በመጀመሪያው ቁጥር ላይ ለመጻፍ ይነሳ ነበርን? እንደዚያ እንደማያደርግ የታወቀ ነው!

አስገራሚ ዝርዝሮች

16, 17. የአርኪኦሎጂ መረጃዎች (ሀ) ናቡከደነፆር ሰው ሁሉ እንዲሰግድለት ሃይማኖታዊ ምስል ስለማቆሙ (ለ) ናቡከደነፆር በባቢሎን በሠራቸው የግንባታ ሥራዎች ይኩራራ የነበረ ስለመሆኑ የሚገልጸውን የዳንኤል ዘገባ የደገፉት እንዴት ነው?

16 እስቲ አሁን ደግሞ አሉታዊ የሆኑትን ነገሮች እንተውና አዎንታዊ ወደሆኑት ነገሮች መለስ እንበል። ጸሐፊው ይዘግብለት ስለ ነበረው ዘመን ያለው እውቀት የስሚ ስሚ የተገኘ እንዳልነበር የሚጠቁሙ አንዳንድ ዝርዝሮችን ከዳንኤል መጽሐፍ ተመልከት።

17 ዳንኤል ስለ ጥንቷ ባቢሎን ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር በዝርዝር የሚያውቅ መሆኑ የዘገባውን ትክክለኛነት እንድንቀበል የሚያስገድድ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ለምሳሌ ያህል ዳንኤል 3:1-6 ናቡከደነፆር አንድ ትልቅ ምስል ስለማቆሙ ይናገራል። ሰው ሁሉ ለዚህ ምስል ወድቆ መስገድ ነበረበት። የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች ይህ ንጉሥ ሕዝቡን በብሔራዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ለማሳተፍ ይጥር እንደነበር የሚያረጋግጡ ሌሎች ማስረጃዎችን አግኝተዋል። በተመሳሳይም ዳንኤል ናቡከደነፆር በሠራቸው የግንባታ ሥራዎች እጅግ ይኩራራ እንደነበር ገልጿል። (ዳንኤል 4:30) የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች በባቢሎን ለተከናወነው ከፍተኛ የግንባታ ሥራ ዋናው አንቀሳቃሽ ናቡከደነፆር መሆኑን የተገነዘቡት በቅርቡ ነው። እጅግ ከመኩራራቱ የተነሣ ስሙን በጡቦቹ ላይ ሳይቀር አስጽፏል! የዳንኤል መጽሐፍ ተቺዎች አጭበርባሪ ነው የሚሉት በመቃብያን ዘመን (167-63 ከዘአበ) የኖረው ሰው እነዚህ ግንባታዎች ከተሠሩ ከአራት መቶ ዓመታት በኋላና በአርኪኦሎጂ ምርምር ከመገኘታቸው ከረጅም ዘመን በፊት ስለ እነዚህ ግንባታዎች እንዴት ሊያውቅ ቻለ ለሚለው ጥያቄ መልስ የላቸውም።

18. ዳንኤል በባቢሎናውያንና በፋርሳውያን አገዛዝ ይሰጥ ስለነበረው ቅጣት የገለጸው ልዩነት ትክክለኛነት የተንጸባረቀበት ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

18 ከዚህም በተጨማሪ የዳንኤል መጽሐፍ በባቢሎናውያንና በሜዶ ፋርስ ሕጎች መካከል ያሉትን አንዳንድ ቁልፍ ልዩነቶች ይጠቁመናል። ለምሳሌ ያህል በባቢሎናውያን ሕግ ሥር የነበሩት ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች የንጉሡን ትእዛዝ ለመፈጸም እምቢ በማለታቸው በእቶን እሳት ውስጥ ተጥለው ነበር። ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ ዳንኤል ሕሊናውን የሚያስጥሰውን የፋርስን ሕግ ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። (ዳንኤል 3:6፤ 6:7-9) አንዳንዶች ስለ እቶን እሳቱ የሚናገረው ዘገባ አፈ ታሪክ ነው ብለው በማሰብ ሊያወጡት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች በቀጥታ ይህን ዓይነቱን ቅጣት የሚጠቅስ በጥንቷ ባቢሎን ውስጥ የተዘጋጀ የግለሰብ ደብዳቤ አግኝተዋል። ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ግን እሳት ቅዱስ ነገር ነበር። በመሆኑም ወደ ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው የቅጣት ዓይነቶች ዘወር ብለዋል። ከዚህ አንጻር የአንበሶች ጉድጓድ መኖሩ ምንም አያስገርመንም።

19. የዳንኤል መጽሐፍ በባቢሎናውያንና በሜዶ ፋርሳውያን መካከል ያለውን የሕግ ሥርዓት ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየው እንዴት ነው?

19 ሌላም ልዩነት ይታያል። ናቡከደነፆር ሕጎችን ከመቅጽበት ሊደነግግና ሊለውጥ ይችል እንደነበር ዳንኤል ጠቁሟል። ዳርዮስ ግን ‘የሜዶንንና የፋርስን ሕግ፣’ ራሱ የደነገገውን እንኳ ፈጽሞ መለወጥ አይችልም ነበር! (ዳንኤል 2:5, 6, 24, 46-49፤ 3:10, 11, 29፤ 6:12-16) ታሪክ ጸሐፊው ጆን ሲ ዊትኮም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የጥንቱ ታሪክ፣ ሕጉ ለንጉሡ ተገዥ በነበረባት በባቢሎንና ንጉሡ ለሕጉ ተገዥ በነበረበት በሜዶ ፋርስ መካከል ያለውን ልዩነት በማስረጃ ያረጋግጣል።”

20. ዳንኤል ስለ ባቢሎናውያን ልማድ የሚያውቀው ነገር የስሚ ስሚ የደረሰው እንዳልነበር የሚያሳየው የብልጣሶርን ግብዣ በሚመለከት የሰጠው የትኛው ዝርዝር መግለጫ ነው?

20 በዳንኤል ምዕራፍ 5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ስለ ብልጣሶር ግብዣ የሚናገረው አስገራሚ ዘገባም በጣም ብዙ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል። ስለ ወይን ጠጅ ተደጋግሞ ስለተጠቀሰ እንደፈለጉ ይበሉና ይጠጡ የነበሩበት ግብዣ ይመስላል። (ዳንኤል 5:1, 2, 4) እንዲያውም ስለ ተመሳሳይ ግብዣዎች የሚገልጹ ውቅር ምሥሎች የሚያሳዩት ወይን ብቻ እንደቀረበ ነው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በወቅቱ እንዲህ በመሰሉ ግብዣዎች ላይ ወይን ጠጅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር። ዳንኤል በዚህ ትልቅ ግብዣ ላይ ሴቶችም ማለትም የንጉሡ ሚስቶችና ቁባቶች ተገኝተው እንደነበር ገልጿል። (ዳንኤል 5:3, 23) ስለ ባቢሎናውያን ልማድ የተነገረውን ይህን ዝርዝር ሐሳብ አርኪኦሎጂ ይደግፈዋል። በመቃብያን ዘመን በነበሩት አይሁዳውያንና ግሪካውያን ዘንድ ሚስቶች በግብዣዎች ላይ ከወንዶች ጋር መገኘታቸው እጅግ ነውር ነበር። የመጀመሪያዎቹ የግሪክ ሰፕቱጀንት የዳንኤል መጽሐፍ ትርጉም ቅጂዎች ስለ እነዚህ ሴቶች ሳይጠቅሱ የቀሩት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። * ይሁንና የዳንኤልን መጽሐፍ ፈጥሮ ጽፏል የሚባለው ሰው የኖረው በዚሁ የግሪካውያን አመለካከት በገነነበት (የግሪካውያን) ባሕል ውስጥ ሲሆን በጥቅሉ ሲታይም ሰፕቱጀንት በተዘጋጀበት ተመሳሳይ ዘመን ውስጥ ነበር ለማለት ይቻላል!

21. ዳንኤል በባቢሎን ግዞት ወቅት የነበረውን ዘመንና ልማድ ጠንቅቆ ያውቅ የነበረ ለመሆኑ ከሁሉ የተሻለው ምክንያታዊ ማስረጃ ምንድን ነው?

21 እነዚህ ሁሉ ዝርዝር ጉዳዮች እያሉ ብሪታኒካ የዳንኤልን መጽሐፍ የጻፈው ሰው ስለ ግዞት ዘመን ያለው እውቀት “ጥራዝ ነጠቅና የተሳሳተ ነው” ማለቱ እጅግ የሚያስገርም ነው። በኋለኞቹ መቶ ዘመናት የተነሳ አንድ አስመሳይ እንዴት ከጥንቶቹ ባቢሎናውያንና ፋርሳውያን ባሕል ጋር ይህን ያህል ጥልቅ ትውውቅ ሊኖረው ይችላል? ደግሞም ሁለቱም መንግሥታት የተዳከሙት ከሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ብዙ ጊዜ ቀደም ብሎ እንደነበር አስታውስ። በዚያን ጊዜ የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች አልነበሩም፤ በዘመኑ የነበሩትም አይሁዳውያን ቢሆኑ ስለ ባዕድ አገራት ባሕልና ታሪክ እናውቃለን ብለው የሚናገሩበት አፍ አልነበራቸውም። በስሙ የተጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሊጽፍ የሚችለው የተረከላቸውን ዘመናትና ክንውኖች በዓይን ምሥክርነት ከተከታተለው ከነቢዩ ዳንኤል ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።

ከመጽሐፉ ውጭ ያሉ ማስረጃዎች የዳንኤል መጽሐፍ ፈጠራ መሆኑን ያረጋግጣሉን?

22. ተቺዎች የዳንኤል መጽሐፍ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሰጠውን ቦታ በሚመለከት ምን ይላሉ?

22 የዳንኤል መጽሐፍን በተመለከተ ከሚነሡት በጣም የተለመዱ ክርክሮች አንዱ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅደም ተከተል ውስጥ የተሰጠው ቦታ ነው። የጥንቶቹ ረቢዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሕግ፣ ነቢያትና መጻሕፍት ብለው ለሦስት ከፍለዋቸዋል። የዳንኤልን መጽሐፍ የሚመድቡት ግን ከነቢያት መካከል ሳይሆን ከመጻሕፍት መካከል ነው። ተቺዎች ይህ ነገር የሌሎቹ ነቢያት ሥራዎች በተሰባሰቡበት ወቅት የዳንኤል መጽሐፍ እንደማይታወቅ ያረጋግጣል ብለው ይከራከራሉ። ከመጻሕፍት መካከል የተፈረጀው እነዚህ መጻሕፍት የተሰባሰቡት ከጊዜ በኋላ ስለሆነ ነው ይላሉ።

23. የጥንቶቹ አይሁዳውያን ለዳንኤል መጽሐፍ ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

23 የሆነ ሆኖ የጥንቶቹ ረቢዎች በድልድሉ በኩል ይህን ያህል ጥብቅ ነበሩ ወይም የዳንኤልን መጽሐፍ ከነቢያት መጻሕፍት መካከል አውጥተውታል በሚለው ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች አይደሉም። ይሁን እንጂ ረቢዎች ከመጻሕፍት መካከል መዝግበውታል ቢባል እንኳ ይህ ከጊዜ በኋላ ስለመጻፉ ማስረጃ ይሆናልን? አይሆንም። የታወቁ ምሁራን ረቢዎች የዳንኤልን መጽሐፍ ከትንቢቶች መካከል ያወጡበት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም የተለያዩ አስተያየቶች ሰንዝረዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፉ ስላላስደሰታቸው ወይም ዳንኤል በባዕድ አገር ባለ ሥልጣን ሆኖ በመሥራቱ ከሌሎች ነቢያት የተለየ እንደሆነ አድርገው ስላዩት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር የጥንቶቹ አይሁዳውያን ለዳንኤል መጽሐፍ ጥልቅ አክብሮት የነበራቸውና የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑን አምነውበት የነበረ መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት ተሰባስበው ያለቁት ከሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከረዥም ጊዜ በፊት እንደሆነ ማስረጃዎቹ ይጠቁማሉ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፉትን አንዳንድ መጻሕፍት ጨምሮ ከዚያ በኋላ የተዘጋጁ ነገሮችን መጨመር አይቻልም ነበር።

24. መጽሐፈ ሲራክ የሚባለው የአዋልድ መጽሐፍ የዳንኤልን መጽሐፍ ለመቃወም የሚጠቀሰው እንዴት ነው? ይህ ዓይነቱ ሐሳብ ምክንያታዊነት የጎደለው መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

24 ይህ እየታወቀ ደግሞ ከእነዚህ ተቀባይነት ካጡ የኋለኛው ዘመን ሥራዎች መካከል አንዱ የዳንኤልን መጽሐፍ ለመቃወም እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል። በጂሰስ ቤን ሲራክ የተዘጋጀው መጽሐፈ ሲራክ የሚባለው የአዋልድ መጽሐፍ የተጠናቀረው በ180 ከዘአበ መሆኑ ይታወቃል። ተቺዎች ይህ መጽሐፍ ከሚዘረዝራቸው ብዙ ጻድቃን ወንዶች መካከል ዳንኤል አልተጠቀሰም ይላሉ። ከዚህ በመነሳት ዳንኤል በወቅቱ አይታወቅም ነበር ማለት ነው ይላሉ። ይህ የመከራከሪያ ነጥብ በምሁራኑ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቷል። ይሁን እንጂ እስቲ አስበው:- በዚሁ ዝርዝር ውስጥ ዕዝራና መርዶክዮስ (ሁለቱም ከግዞት በኋላ በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ እንደ ጀግና የሚታዩ ናቸው)፣ ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮሣፍጥ እንዲሁም ቅን ሰው የነበረው ኢዮብ ያልተጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ ከመሳፍንት መካከል የተጠቀሰው ሳሙኤል ብቻ ነው። * የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ባልሆነ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኝና ሁሉንም የሚያቅፍ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት መግለጫ ባልተሰጠበት ዝርዝር ውስጥ እነዚህ ሰዎች ስለሌሉ ብቻ ልብ ወለድ ናቸው ብለን ልናስወጣቸው ይገባልን? ይህ ምክንያታዊነት የጎደለው ሐሳብ ነው።

ዳንኤልን የሚደግፉ ከመጽሐፉ ውጭ ያሉ ማስረጃዎች

25. (ሀ) ጆሴፈስ የዳንኤልን ዘገባ እውነተኝነት ያረጋገጠው እንዴት ነው? (ለ) ጆሴፈስ ስለ ታላቁ እስክንድርና ስለ ዳንኤል መጽሐፍ የተናገረው ነገር በሰፊው ከሚታወቀው ታሪክ ጋር ተስማሚ የሆነው በምን መንገድ ነው? (ሁለተኛውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) (ሐ) ቋንቋ ነክ ማስረጃዎች የዳንኤልን መጽሐፍ የሚደግፉት እንዴት ነው? (ገጽ 26⁠ን ተመልከት።)

25 እስቲ አሁንም አዎንታዊ ወደ ሆኑት ነገሮች መለስ እንበል። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል የዳንኤልን መጽሐፍ ያህል ትክክለኛነቱ የተረጋገጠለት መጽሐፍ እንደሌለ ይነገራል። ለምሳሌ ታዋቂው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ የመጽሐፉን ትክክለኛነት መሥክሯል። ታላቁ እስክንድር ከፋርሳውያን ጋር ጦርነት በገጠመበት በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ላይ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ካህናቱ የዳንኤልን መጽሐፍ ቅጂ እንዳሳዩት ገልጿል። እስክንድርም ራሱ በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የሚገኙት ስለ እርሱ የሚናገሩት ቃላት በፋርስ ላይ ያደረገውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚያመለክቱ ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር። * ይህ ደግሞ ተቺዎች እንደሚሉት ከሆነ “የማስመሰያ” ሥራው ከተሠራበት ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ይሆናል ማለት ነው። እርግጥ ጆሴፈስ ይህን በማለቱ ተቺዎቹ እጅግ ነቅፈውታል። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ትንቢቶች ተፈጽመዋል በማለቱም አብጠልጥለውታል። ይሁንና ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፍ ዲ ዊልሰን “[ጆሴፈስ] ስለዚህ ጉዳይ በዓለም ላይ ካሉት ተቺዎች ሁሉ ይበልጥ ሳያውቅ አይቀርም” ብለዋል።

26. የሙት ባሕር ጥቅልሎች የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኛነት የደገፉት እንዴት ነው?

26 በእስራኤል በኩምራን ዋሻዎች ውስጥ የሙት ባሕር ጥቅልሎች በተገኙ ጊዜም የዳንኤል መጽሐፍ ለእውነተኝነቱ ተጨማሪ ድጋፍ አግኝቷል። የሚያስገርመው በ1952 ከተገኙት ነገሮች መካከል የዳንኤል መጽሐፍ ጥቅልሎችና ቁርጥራጮች ነበሩበት። ከሁሉም ይበልጥ ረጅም ዕድሜ የቆየ ነው የተባለው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መገባደጃ ላይ የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም በዚያ ዘመን ሳይቀር የዳንኤል መጽሐፍ በሰፊው የሚታወቅና በብዙሐኑ ዘንድ አክብሮት ያተረፈ ነበር ማለት ነው። ዞንደርቫን ፒክቶሪያል ኢንሳይክለፒዲያ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “የዳንኤል መጽሐፍ በመቃብያን ዘመን ተጽፏል የሚለው ሐሳብ፣ መጽሐፉ በቅጂ መልክ ተጠናቅሮ በአንድ የመቃብያን ሃይማኖታዊ ኑፋቄ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እስኪቀመጥ ድረስ በመሃል የሚወስደውን ጊዜ ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ብቻ ውድቅ መሆን አለበት።”

27. ዳንኤል በባቢሎን ግዞት ወቅት በሰፊው ይታወቅ የነበረና በገሃዱ ዓለም የነበረ ሰው ለመሆኑ ጥንታዊው ማስረጃ ምንድን ነው?

27 ይሁን እንጂ ስለ ዳንኤል መጽሐፍ ከዚህም ቀደም ያለና ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ማረጋገጫ እናገኛለን። በዳንኤል ዘመን ከኖሩት ሰዎች መካከል አንዱ ሕዝቅኤል ነበር። እርሱም በባቢሎን ግዞት ወቅት በነቢይነት አገልግሏል። የሕዝቅኤል መጽሐፍ ዳንኤልን ደጋግሞ በስም ይጠቅሰዋል። (ሕዝቅኤል 14:14, 20፤ 28:3) ሕዝቅኤል ዳንኤልን ደጋግሞ መጥቀሱ በዚያ ዘመን ማለትም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዳንኤል በሰፊው የሚታወቅ ጻድቅና ጠቢብ ሰው እንደነበር እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ ከነበራቸው ከኖኅና ከኢዮብ ጋር ሊጠቀስ የሚገባው ሰው መሆኑን ይጠቁማል።

ከሁሉ የሚበልጠው ምሥክር

28, 29. (ሀ) የዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው ከሁሉ የላቀው አሳማኝ ማስረጃ ምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስን ምሥክርነት መቀበል የሚገባን ለምንድን ነው?

28 በመጨረሻ ደግሞ ከምሥክሮቹ ሁሉ የሚበልጠው ምሥክር የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኛነት በሚመለከት ምን እንደሚል እንመርምር። ይህ ምስክር ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት በተናገረ ጊዜ ራሱን ‘ነቢዩ ዳንኤልንና’ ከትንቢቶቹ አንዱን ጠቅሷል።—ማቴዎስ 24:15፤ ዳንኤል 11:31፤ 12:11

29 በመቃብያን ዘመን ተጽፏል የሚለው የተቺዎቹ ንድፈ ሐሳብ ትክክል ነው ከተባለ ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች አንዱ እውነት ይሆናል ማለት ነው። አንድም፣ ኢየሱስ በዚህ የፈጠራ መጽሐፍ ተታልሏል አሊያም ማቴዎስ ኢየሱስ ያላለውን ነገር እርሱ እንደተናገረ አድርጎ ጽፏል። ሁለቱም ቢሆን አያስኬድም። በማቴዎስ ወንጌል መተማመን ካልቻልን በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንዴት ልንተማመን እንችላለን? ዛሬ እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች ካወጣን የሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ከቅዱሳን ጽሑፎች ገጽ የትኞቹን ቃላት እንመዝ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው፤ ለትምህርት፣ . . . ነገሮችን ለማቅናት . . . ጠቃሚ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) በመሆኑም ዳንኤል አስመሳይ ነው ከተባለ ሌላው አስመሳይ ደግሞ ጳውሎስ ይሆናል ማለት ነው! ኢየሱስ ተታልሎ ሊሆን ይችላልን? በፍጹም። የዳንኤል መጽሐፍ ሲጻፍ እርሱ በሰማይ ነበር። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 8:58) እስከ ዛሬ ምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ስለ ዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኝነት መረጃ እንዲሰጠን ከኢየሱስ የተሻለ የምንጠይቀው አይኖርም። ይሁን እንጂ ዛሬ መጠየቅ አያስፈልገንም። የሰጠው ምሥክርነት ምንም የማያሻማ ነው።

30. ኢየሱስ የዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኛ ለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ የሰጠው እንዴት ነው?

30 ኢየሱስ በተጠመቀበትም ጊዜ የዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ሰጥቷል። ዳንኤል ስለ 69 የዓመታት ሳምንታት በተናገረው ትንቢት መሠረት ኢየሱስ በዚህ ጊዜ መሲህ ሆኖ ብቅ ብሏል። (ዳንኤል 9:25, 26፤ የዚህን መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ ተመልከት።) ዳንኤል የተጻፈው ከጊዜ በኋላ ነው የሚለው ንድፈ ሐሳብ እውነት ነው ቢባል እንኳ የዳንኤል ጸሐፊ ከሁለት መቶ ዓመታት አስቀድሞ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ያውቅ ነበር ማለት ነው። እርግጥ አምላክ ማንነቱን በደበቀ አስመሳይ ሰው ተጠቅሞ እውነተኛ ትንቢት እንዲነገር አያደርግም። አዎን፣ ለአምላክ የታመኑ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የኢየሱስን ምሥክርነት በሙሉ ልብ ይቀበላሉ። በዓለም ላይ ያሉት ኤክስፐርቶችና ተቺዎች በሙሉ ዳንኤልን ለማውገዝ አንድ ላይ ቢያብሩ እንኳ የኢየሱስ ምሥክርነት ብቻ ውድቅ ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም እርሱ ‘የታመነና እውነተኛ ምሥክር’ ነው።—ራእይ 3:14

31. አሁንም ቢሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ስለ ዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኛነት የማያምኑት ለምንድን ነው?

31 ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ግን ይህ ማስረጃ አያረካቸውም። አንድ ሰው ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ምን ያህል ማስረጃ ቢቀርብ እንደሚረኩ እያሰበ ከመገረም ሌላ የሚያደርገው ነገር አይኖርም። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ አንድ ፕሮፌሰር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “‘ከሰው በላይ በሆነ ኃይል እርዳታ ትንቢት ሊነገር አይችልም’ የሚለው መሠረታዊ የሆነ አሉታዊ አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ለተቃውሞዎች መልስ መስጠቱ ብቻ የሚፈይደው ነገር የለም።” በመሆኑም አሉታዊ አስተሳሰባቸው አሳውሯቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የእነርሱ ምርጫ ነው። የዘሩትን ያጭዳሉ።

32. ከዚህ በኋላ በምናደርገው የዳንኤል መጽሐፍ ጥናት ምን ነገር ይጠብቀናል?

32 አንተስ? የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኛነት የምትጠራጠርበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የሚሰማህ ከሆነ እጅግ አስደሳች የሆነውን የምርምር ጉዞ ለመጀመር ተዘጋጅተሃል ማለት ነው። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትረካዎች ማራኪ፤ ትንቢቶቹን ደግሞ የሚያስገርሙ ሆነው ታገኛቸዋለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ እያንዳንዱ ምዕራፍ እምነትን የሚያጠናክር ሆኖ ታገኘዋለህ። የዳንኤልን ትንቢት በጥልቀት በመመርመርህ ምንም አትቆጭም!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 አንዳንድ ተቺዎች አንዳንድ የጥንት መጻሕፍት በብዕር ስሞች ይጻፉ እንደነበረ ሁሉ የዳንኤል መጽሐፍ ጸሐፊም ዳንኤል የሚለውን ስም የተጠቀመበት እንደ ብዕር ስም አድርጎ ነው በማለት የፈጠራ መጽሐፍ ነው የሚለውን ክስ ትንሽ ለማለዘብ ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺ የሆኑት ፈርዲናንድ ሂትሲክ እንዲህ ብለዋል:- “የዳንኤል መጽሐፍ [ጸሐፊ] ሌላ ሰው ነው ካልን ጉዳዩ መልኩን ይቀይራል። እንደዚያ ከሆነ መጽሐፉ የፈጠራ መጽሐፍ ነው ማለት ነው፤ ጸሐፊው ለገዛ ጥቅማቸው አስቦም እንኳ ሊሆን ቢችል ዓላማው በጊዜው የነበሩትን አንባቢዎቹን ማታለል ነበር ማለት ይሆናል።”

^ አን.8 ባቢሎን በወደቀችበት ጊዜ ናቦኒደስ በዚያ አልነበረም። በመሆኑም በወቅቱ ብልጣሶር ንጉሥ ተብሎ መጠራቱ ትክክል ነው። ተቺዎች ሌሎች መዛግብት ብልጣሶርን ንጉሥ የሚል ኦፊሴላዊ ማዕረግ አይሰጡትም ብለው ይከራከራሉ። የሆነ ሆኖ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች አገረ ገዥዎችን ጭምር ንጉሥ ብለው ሊጠሯቸው እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ጥንታዊ ማስረጃዎች አሉ።

^ አን.20 የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር የሆኑት ሲ ኤፍ ኪል ዳንኤል 5:3⁠ን በሚመለከት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “LXX (ሰፕቱጀንት) ከመቄዶናውያን፣ ከግሪኮችና ከሮማውያን ባሕል አንጻር በመመልከት በዚህኛውና በ23ኛው ቁጥር ላይ ስለ ሴቶቹ ሳይጠቅስ ቀርቷል።”

^ አን.24 በተቃራኒው ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በመንፈስ አነሳሽነት ያሰፈረው የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ዝርዝር በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱትን ክስተቶች በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቅስ ይመስላል። (ዳንኤል 6:16-24፤ ዕብራውያን 11:32, 33) ሆኖም ሐዋርያው የጠቀሰውም ዝርዝር ቢሆን ሁሉንም የሚያቅፍ አይደለም። እንደ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ እና ሕዝቅኤል የመሰሉ በዚህ ዝርዝር ውስጥ በስም ያልተጠቀሱ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በሕይወት አልነበሩም ማለት አይደለም።

^ አን.25 አንዳንዶች እስክንድር የፋርስ የረጅም ዘመን ወዳጅ ለነበሩት እስራኤላውያን ያን ያህል ደግነት ያሳያቸው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል። በወቅቱ እስክንድር የፋርስ ወዳጅ የነበሩትን ሁሉ የማጥፋት ዘመቻ ይዞ ነበር።

ምን አስተውለሃል?

• የዳንኤል መጽሐፍ የቀረበበት ክስ ምንድን ነው?

• ተቺዎች በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የሚሰነዝሯቸው ትችቶች መሠረት የላቸውም የምንለው ለምንድን ነው?

• የዳንኤልን ዘገባ ትክክለኛነት የሚደግፈው ማስረጃ ምንድን ነው?

• የዳንኤል መጽሐፍ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጠው ከሁሉ ይበልጥ አሳማኝ ማረጋገጫ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የተጻፈበት ቋንቋ

የዳንኤል መጽሐፍ ተጽፎ ያለቀው በ536 ከዘአበ ገደማ ነው። ጥቂት የግሪክኛና የፋርስ ቃላት ቢኖሩትም የተጻፈው በዕብራይስጥና በአረማይክ ቋንቋዎች ነው። እንዲህ ያለው የቋንቋ ቅልቅል ብዙም የተለመደ ባይሆንም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግን እንግዳ ነገር አይደለም። በተመሳሳይም የዕዝራ መጽሐፍ የተጻፈው በዕብራይስጥና በአረማይክ ነው። ይሁንና አንዳንድ ተቺዎች የዳንኤል ጸሐፊ እነዚህን ቋንቋዎች የተጠቀመበት መንገድ ከ536 ከዘአበ ብዙ ቆይቶ እንደጻፈው የሚጠቁም ነው ብለው ይከራከራሉ። አንድ ተቺ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የግሪክኛ ቃላት መገኘታቸው መጽሐፉ የተጻፈው ከጊዜ በኋላ መሆኑን እንድንቀበል የሚያስገድድ ነው ማለታቸው በሰፊው ይነገራል። የዕብራይስጥ ቋንቋ መጠቀሙ በኋለኛው ዘመን ማለትም እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ድረስ ዘግይቶ ጽፎታል የሚለውን ሐሳብ የሚደግፍ ሲሆን የአረማይክ ቋንቋ መኖሩ ደግሞ በቀጥታ ይህን ባይደግፍ እንኳ አይቃረንም ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም የቋንቋ ምሁራን አይደሉም። አንዳንዶቹ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የዕብራይስጥ ቋንቋ እንደ መጽሐፈ ሲራክ ካሉት የአዋልድ መጻሕፍት በተለየ መልኩ ሕዝቅኤልና ዕዝራ ከተጠቀሙበት ዕብራይስጥ ጋር የሚመሳሰል ነው ብለዋል። ዳንኤል በአረማይክ መጠቀሙን በሚመለከት ከሙት ባሕር ጥቅልሎች ጋር የተገኙ ሁለት መዛግብትን ተመልከት። እነርሱም በአረማይክ የተጻፉ ሲሆን የተዘጋጁት በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማለትም ፈጠራ ነው የሚባለው የዳንኤል መጽሐፍ ተዘጋጀ ከሚባልበት ጊዜ ብዙም ሳይርቅ ነው። ይሁን እንጂ ምሁራኑ በእነዚህ መዛግብት ላይ በሚገኘው አረማይክና በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ባለው አረማይክ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አግኝተዋል። በመሆኑም የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው ተቺዎቹ ከሚሉት ጊዜ ብዙ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ።

በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ አሉ ስለሚባሉት “አጠያያቂ” ግሪክኛ ቃላትስ ምን ማለት ይቻላል? ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ጭራሹኑ ግሪክኛ ሳይሆኑ የፋርስ ቃላት መሆናቸው ተረጋግጧል! ዛሬም ግሪክኛ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ቃላት ቢኖሩ ሦስት የሙዚቃ መሣሪያዎች ስሞች ብቻ ናቸው። የእነዚህ ሦስት ቃላት መኖር ዳንኤል የተጻፈው ከጊዜ በኋላ ነው ለማለት የሚያስገድድ ይሆናልን? አይሆንም። የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች እንደደረሱበት የግሪክ ባሕል ተጽዕኖ ማሳደር የጀመረው ግሪክ የዓለም ኃያል ከመሆኗ ከብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ነው። ከዚህስ በላይ የዳንኤል መጽሐፍ የተዘጋጀው የግሪክ ባሕልና ቋንቋ አገር ምድሩን ባጥለቀለቀበት በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ቢሆን ኖሮ መጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ግሪክኛ ቃላት ሦስት ብቻ ይሆኑ ነበርን? ሊሆን አይችልም። ከዚያ የበለጡ ቃላትን በያዘ ነበር። በመሆኑም ቋንቋ ነክ ማስረጃዎቹም የዳንኤልን መጽሐፍ ትክክለኛነት ይደግፋሉ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(ከላይ) ይህ ጽሑፍ ናቡከደነፆር ያከናወነውን የግንባታ ሥራ በተመለከተ በጉራ የተናገረውን ሐሳብ ይዟል

(ከታች) የባቢሎናውያን ቤተ መቅደስ ሞላላ ሸክላ የንጉሥ ናቦኒደስንና የልጁን የብልጣሶርን ስም ይዟል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በናቦኒደስ ዜና ታሪክ መሠረት የቂሮስ ሠራዊት ወደ ባቢሎን የገባው ያለ ውጊያ ነው

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(በስተቀኝ) “የናቦኒደስ የታሪክ ሰነድ” ናቦኒደስ የመንግሥት ሥልጣኑን ለበኩር ልጁ በአደራ እንደሰጠው ይዘግባል

(በስተግራ) ናቡከደነፆር ይሁዳን ስለመውረሩ የሚገልጸው የባቢሎናውያን ዘገባ