በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ይህ ዓለም ከጥፋት ይተርፍ ይሆን?

ይህ ዓለም ከጥፋት ይተርፍ ይሆን?

ይህ ዓለም ከጥፋት ይተርፍ ይሆን?

ከዚህ ትውልድ የበለጠ ስለ ዓለም ፍጻሜ በብዛት ሲነገር የሰማ አንድም ሌላ ትውልድ የለም። ብዙዎች ዓለም በኑክሌር እልቂት ይጠፋል ብለው ይሰጋሉ። ሌሎች ሰዎች የአካባቢ ብክለት ዓለምን ሊያጠፋው ይችላል ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ የኢኮኖሚ ቀውስ የሰውን ዘር ከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲጨራረስ ያደርገዋል በማለት ይጨነቃሉ።

በእርግጥ ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜ ሊመጣ ይችላልን? ወደ ፍጻሜው ከመጣ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ምን ማለት ይሆን? ከዚህ በፊት የጠፋ ዓለም ነበርን?

አንድ ዓለም ጠፍቶ በሌላ ዓለም ተተካ

አዎን፣ አንድ ዓለም ጠፍቶ ነበር። በክፋት የተሞላውን በኖኅ ዘመን የነበረውን ዓለም እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያን ጊዜ የነበረውም ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ኃጢአተኞች በሚኖሩበት ዓለም ላይ የጥፋትን ውሃ ሲያመጣ የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አዳነ እንጂ ለቀድሞው ዓለም አልራራም።”—2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:6 የ1980 ትርጉም

የዚያ ዓለም ፍጻሜ ምን ማለት እንደሆነና ምን ማለት እንዳልሆነ ልብ በል። የሰው ዘር ፍጻሜ ማለት አልነበረም። ከዓለም አቀፉ የውሃ መጥለቅለቅ ኖኅና ቤተሰቡ ተርፈዋል። ፕላኔቷ ምድርና ውብ የሆኑት በከዋክብት የተሞሉ ሰማያትም እንደዚሁ ከጥፋቱ ተርፈዋል። ድምጥማጡ የጠፋው ‘የክፉ ሰዎች ዓለም’፣ ክፉው የነገሮች ሥርዓት ነው።

በመጨረሻም፣ የኖኅ ዘሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ሲመጡ ሌላ ዓለም ተፈጠረ። ይህ የኋለኛው ዓለም ወይም የነገሮች ሥርዓት እስከ ጊዜያችን ድረስ ዘልቋል። የዚህኛው ዓለም ታሪክ በጦርነት፣ በወንጀልና በዓመፅ የተሞላ ነው። ይህ ዓለም ምን ይደርስበት ይሆን? ከጥፋት ይተርፍ ይሆን?

የዚህ ዓለም የወደፊት ዕጣ

በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም እንደጠፋ ከተናገረ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ሲል ይቀጥላል:- “አሁን ያሉትም ሰማይና ምድር . . . በዚሁ . . . ቃል ለእሳት ተጠብቀው ይቆያሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:7፤ የ1980 ትርጉም) በእርግጥም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንደገለጸው አሁን ያለው “ዓለም ያልፋል።”—1 ዮሐንስ 2:17

በኖኅ ዘመን ግዑዟ ምድር ወይም በከዋክብት የተሞሉት ሰማያት እንዳላለፉ ሁሉ አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ግዑዛን ነገሮች ያልፋሉ ማለቱ አይደለም። (መዝሙር 104:5) ከዚህ ይልቅ ይህ ዓለም ‘ከሰማዮቹ’ ማለትም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ካሉት መንግሥታዊ ገዢዎች ጋር እንዲሁም ‘ከምድሩ’ ማለትም ከሰብዓዊው ኅብረተሰብ ጋር በእሳት የጠፋ ያህል ሆኖ ይጠፋል። (ዮሐንስ 14:30፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ይህ ዓለም ወይም የነገሮች ሥርዓት ልክ ከጥፋት ውኃ በፊት እንደነበረው ዓለም ድምጥማጡ እንደሚጠፋ አያጠራጥርም። እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ሲደርስ ምን ሁኔታዎች እንደሚከናወኑ በገለጸበት ጊዜ እንደ ምሳሌ አድርጎ በ“ኖኅ ዘመን” ስለነበሩት ሁኔታዎች ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:37–39

ኢየሱስ ስለ ኖኅ ዘመን የተናገረው “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነው?” ለሚለው የሐዋርያቱ ጥያቄ መልስ በሰጠበት ወቅት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) የኢየሱስ ተከታዮች ይህ ዓለም መጨረሻ እንዳለው ያውቁ ነበር። ይህን ማወቃቸው ስጋት ፈጥሮባቸው ነበርን?

እውነታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በፊት የሚከናወኑትን ነገሮች በዘረዘረ ጊዜ ‘መዳናችሁ ቀርቧልና ደስ ይበላችሁ’ በማለት አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 21:28) አዎን፣ ከሰይጣንና እርሱ ካመጣው ክፉ የነገሮች ሥርዓት ድነን ሰላም ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም እንገባለን!—2 ጴጥሮስ 3:13

ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ፍጻሜ የሚመጣው መቼ ነው? ኢየሱስ ‘ስለ መምጣቱና ስለ ዓለም መጨረሻ’ ምን ‘ምልክት’ ሰጥቷል?

“ምልክቱ”

እዚህ ላይ ‘መምጣት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፓሩሲያ የሚለው ነው። ትርጓሜውም “መገኘት” ማለት ነው። ይህም በቦታው መገኘት ማለት ነው። ስለዚህ “ምልክቱ” ሲታይ ክርስቶስ ሊመጣ ተቃርቧል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተመልሷል፣ እንዲሁም በቦታው ተገኝቷል ማለት ነው። ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መግዛት ጀምሯል፤ ጠላቶቹንም በቅርቡ ወደ ፍጻሜ ያመጣቸዋል ማለት ነው።—ራእይ 12:7–12፤ መዝሙር 110:1, 2

ኢየሱስ ‘ምልክት’ አድርጎ የሰጠው አንድ ክንውን ብቻ አይደለም። ብዙ የዓለም ክንውኖችንና ሁኔታዎችን ዘርዝሯል። እነዚህ ነገሮች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “የመጨረሻው ቀን” ብለው በጠሩት ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ‘የመጨረሻውን ቀን’ ለይቶ ማወቅ ከሚቻልባቸው ኢየሱስ ከተነበያቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ይመልከቱ።

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” (ማቴዎስ 24:7) በዘመናችን የተከናወኑት ጦርነቶች ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ጦርነቶች የበለጠ ሰፊ ይዘት አላቸው። አንድ ታሪክ ጸሐፊ በ1914 የጀመረው “የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ‘ሁሉንም ያካተተ’ የመጀመሪያው ጦርነት ነበር” በማለት ገልጸዋል። ሆኖም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከዚህ የበለጠ ጥፋት አስከትሏል። ጦርነት በምድር ላይ ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን ቀጥሏል። አዎን፣ የኢየሱስ ቃላት በጉልህ እየተፈጸሙ ናቸው!

“ራብም . . . ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:7) አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የመጣው ረሀብ በታሪክ ውስጥ ከታዩት የረሀብ እልቂቶች የከፋ ሳይሆን አይቀርም። ከፍተኛ እልቂት ያስከተለ ረሀብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ተከስቷል። የምግብ እጥረት መቅሰፍት አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የምድር ነዋሪ አዳርሷል፤ በዚህ ሳቢያ በየዓመቱ ወደ 14 ሚልዮን የሚጠጉ ሕጻናት ይሞታሉ። እውነትም ‘ረሀብ’ ሆኗል!

“ታላቅም የምድር መናወጥ . . . ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) ካለፉት መቶ ዘመናት በአማካይ ወደ አሥር ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በምድር መናወጥ ሳቢያ ከ1914 ወዲህ በየዓመቱ ሞተዋል። ዋና ዋና የሆኑትን ጥቂቶቹን ብቻ ይመልከቱ:- በ1920 ቻይና ውስጥ 200,000 ሰዎች ሞተዋል፤ በ1923 ጃፓን ውስጥ 99,300 ሰዎች የዚህ አደጋ ሰለባ ሆነዋል፤ በ1939 ቱርክ ውስጥ 32,700 ሰዎች በዚህ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፤ በ1970 ፔሩ ውስጥ 66,800 ሰዎች ሞተዋል፤ በ1976 ቻይና ውስጥ ወደ 240,000 የሚጠጉ (ወይም አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ 800,000) ሰዎች የዚህ አደጋ ሰለባ ሆነዋል። በእርግጥም “ታላቅ የምድር መናወጥ” ደርሷል!

“በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር . . . ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) አንደኛው የዓለም ጦርነት ልክ እንዳበቃ በኅዳር በሽታ የተነሣ ወደ 21 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ሞቱ። ሳይንስ ዳይጀስት የተባለው መጽሔት “በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንዲህ ያለ አደገኛና ቅፅበታዊ የሆነ ሞት ታይቶ አይታወቅም” ሲል ዘግቧል። ከዚያን ጊዜ በኋላም የልብ በሽታ፣ ካንሰር፣ ኤድስና ሌሎች ብዙ መቅሰፍቶች በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ፈጅተዋል።

የ“ዓመፃ ብዛት” (ማቴዎስ 24:12) ዓለማችን ከ1914 ወዲህ በወንጀልና በዓመፅ የታወቀ ሆኗል። በብዙ ቦታዎች ሌላው ቀርቶ በጠራራ ፀሐይ እንኳን በጎዳናዎች ላይ ተማምኖ የሚጓዝ ሰው የለም። ሌሊት ሌሊት ሰዎች ወደ ውጪ ለመውጣት በመፍራት በተቆለፉና በትልልቅ መቀርቀሪያዎች በተዘጉ ቤቶቻቸው ውስጥ ይወሸቃሉ።

በመጨረሻዎቹ ቀኖች ይፈጸማሉ ተብሎ ትንቢት የተነገረላቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህም ቢሆኑ በጠቅላላ እየተፈጸሙ ነው። ይህ ማለት የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል ማለት ነው። ደስ የሚለው ግን ከጥፋት የሚተርፉ መኖራቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም ያልፋል’ ካለ በኋላ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—1 ዮሐንስ 2:17

ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ መማርና ማድረግ ያስፈልገናል። ከዚያ በኋላ በአምላክ አዲስ ዓለም በረከቶች ለዘላለም እየተደሰትን ለመኖር ከዚህ ዓለም ፍጻሜ መትረፍ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ጊዜ “እግዚአብሔር . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—ራእይ 21:3, 4

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት “በ1993 ዓ.ም ከታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። አንዳንዶቹን ጥቅሶች በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በፎቶ የተባበሩን:- አውሮፕላን:– USAF photo. ሕፃን:– WHO photo by W. Cutting. የመሬት መንቀጥቀጥ:– Y. Ishiyama, Hokkaido University, Japan.