በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለደም ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ ጥራት ያላቸው አማራጮች

ለደም ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ ጥራት ያላቸው አማራጮች

ለደም ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ ጥራት ያላቸው አማራጮች

‘ደም መውሰድ አደገኛ ነው፤ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምን አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ጥሩ ጥያቄ ነው። እዚህ ላይ “ጥራት” የሚለውን ቃል ልብ በል።

ሁሉም ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮችም ጭምር፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ጥሩ ሕክምና ለማግኘት ይፈልጋል። ዶክተር ግራንት ኢ ስቴፈን ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን አመልክተዋል:- “አንድ ሕክምና ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ነው ሊባል የሚችለው በሕክምናው ውስጥ የተካተቱት ዘዴዎች ሕክምና ነክ የሆኑና ያልሆኑ ሕጋዊ ግቦችን የማሟላት ብቃት ሲኖራቸው ነው።” (ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን፣ ሐምሌ 1, 1988) “ሕክምና ነክ ያልሆኑ ግቦች” የተባሉት የበሽተኛውን ግብረ ገብ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሕሊና አለመጣስን ይጨምራሉ።​—⁠ሥራ 15:​28, 29

ከባድ የሆኑ የሕክምና ችግሮችን ደም ሳይሰጡ ለመቆጣጠር የሚቻልባቸው ውጤታማና ሕጋዊ የሆኑ መንገዶች አሉን? መልሱ አዎን የሚል መሆኑ ሊያስደስተን ይገባል።

አብዛኞቹ ቀዶ ሐኪሞች ደም የሚሰጡት የግድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ የቆዩ ቢሆንም የኤድስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ግን የደም አጠቃቀማቸው በጣም ቀንሷል። በማዮ ክሊኒክ ፕሮሲድንግስ (መስከረም 1988) ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ ይላል:- “ወረርሽኙ ካስገኛቸው ጥቂት ጥቅሞች አንዱ በሽተኞችም ሆኑ ሐኪሞች ደም ከመውሰድ የሚያድን የተለያዩ ዘዴዎችን መቀየሳቸው ነው።” አንድ የደም ባንክ ባለሥልጣን “የተለወጠው የመልእክቱ ኃይል፣ ሐኪሞች ለመልእክቱ ያሳዩት አቀባበልና (አደጋውን ይበልጥ ለማስተዋል ስለቻሉ) ሌሎች አማራጮችን የመፈለግ ጥያቄ እየተጠናከረ መምጣቱ ነው” ብለዋል።​—⁠ትራንስፍዩዥን ሜዲስን ሪቪውስ፣ ጥቅምት 1989

አማራጮች መኖራቸውን ልብ በል። ይህ ቁም ነገር ደም የሚሰጥበትን ምክንያት ስንመለከት ይበልጥ ግልጽ ይሆናል።

በቀይ የደም ሕዋሶች ውስጥ የሚገኘው ሄሞግሎቢን ለጥሩ ጤናና ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ኦክስጅን ይሸከማል። ስለዚህ አንድ ሰው ብዙ ደም ከፈሰሰው ያን የፈሰሰውን ደም መተካት ምክንያታዊ መስሎ ሊታይ ይችላል። አንድ ጤነኛ ሰው በ100 ኪዩቢክ ሴንቲ ሜትር ደም ውስጥ 14 ወይም 15 ግራም ሄሞግሎቢን ይኖረዋል። (ሌላው መለኪያ የሂማቶክሪት መጠን ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ 45 በመቶ ይሆናል።) ተቀባይነት አግኝቶ በቆየው “ሕግ” መሠረት የአንድ በሽተኛ የሄሞግሎቢን መጠን ከ10 በታች (ወይም 30 በመቶ ሄማቶክሪት) ከሆነ ቀዶ ሕክምና ከመደረጉ በፊት ደም ይሰጠዋል። ቮክስ ሳንግዊኒስ (መጋቢት 1987) የተባለው የስዊዘርላንድ ጋዜጣ “65 በመቶ የሚሆኑ [ሰመመን ሰጪዎች] የግድ አስፈላጊ ያልሆነ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው በሽተኞች ከቀዶ ሕክምናው በፊት በመቶ ሲሲ ደም ውስጥ 10 ግራም ሄሞግሎቢን እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ” ሲል ሪፖርት አድርጓል።

ይሁን እንጂ ፕሮፌሰር ሃዋርድ ኤል ዛውደር በ1988 ደም መስጠትን አስመልክቶ በተደረገ ኮንፈረንስ ላይ “ይህን ‘ምትሐታዊ ቁጥር’ ያገኘነው ከየት ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። “አንድ በሽተኛ ሰመመን ውስጥ እንዲገባ ከመደረጉ በፊት 10 ግራም ሄሞግሎቢን (Hgb) ሊኖረው ይገባል የሚለው መስፈርት በወግ ላይ ብቻ የተመሠረተ፣ ግልጽ ማብራሪያ የማይገኝለትና በክሊኒክ ወይም በቤተ ሙከራ ምርምሮች ያልተረጋገጠ ነው” ብለዋል። ‘ግልጽ ማብራሪያ ባልተገኘለትና ባልተረጋገጠ’ መስፈርት ሳቢያ ደም የወሰዱትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በሽተኞች አስብ!

አንዳንዶች ‘ከዚህ ባነሰ የሄሞግሎቢን መጠን መኖር ከተቻለ ትክክለኛው መጠን 14 ነው የሚባለው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ወይም ከባድ ሥራ ለመሥራት የሚያስችልህ ተጨማሪ የሆነ ኦክስጅን የመሸከም አቅም ስለሚኖርህ ነው። የደም ማነስ ባለባቸው ወይም አኔሚክ በሆኑ በሽተኞች ላይ በተደረገ ምርመራ እንደተረጋገጠው “በመቶ ሲሲ ደም ውስጥ የሄሞግሎቢን መጠን እስከ 7 ግራም ሲወርድ እንኳን የሥራ ብቃታቸው ቀንሶ አልተገኘም። ሌሎች ደግሞ አንዳንድ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከመቀነሳቸው በስተቀር ምንም ጉድለት እንዳልታየ አረጋግጠዋል።”​—⁠ኮንተምፓረሪ ትራንስፍዩዥን ፕራክቲስ፣ 1987

የሄሞግሎቢን መጠን ማነስ በአዋቂዎች ላይ የሚያስከትለው የጎላ ችግር የለም። በትናንሽ ልጆችስ ላይ ችግር ያስከትል ይሆን? ዶክተር ጀምስ ኤ ስቶክማን ሦስተኛ እንዲህ ብለዋል:- “ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ከቀናቸው በፊት የሚወለዱ ልጆች በመጀመሪያዎቹ ከአንድ እስከ ሦስት ወራት የሄሞግሎቢናቸው መጠን ዝቅ ይላል። . . . ለትናንሽ ሕፃናት ደም መስጠት አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔታ በግልጽ የታወቀ አይደለም። በእርግጥ ብዙ ሕፃናት የሄሞግሎቢናቸው መጠን በጣም ዝቅ ብሎ እንኳን ምንም ዓይነት የጤንነት መቃወስ አይታይባቸውም።”​—⁠ፔዲያትሪክ ክሊኒክስ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካ፣ የካቲት 1986

ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት መረጃዎች አንድ ሰው በአደጋ ወይም በቀዶ ሕክምና ምክንያት ብዙ ደም ሲፈሰው ምንም ነገር ማድረግ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንደሚያመለክቱ ሆነው መወሰድ የለባቸውም። ደሙ የሚፈሰው በከፍተኛ ፍጥነትና መጠን ከሆነ፣ የሰውዬው የደም ግፊት በጣም ይቀንስና ራሱን ሊስት ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስፈልገው የደሙን መፍሰስ ማቆምና በአካሉ ውስጥ ያለው የደም መጠን ወደ መደበኛው መጠን እንዲመለስ ማድረግ ነው። ይህም በሽተኛው ራሱን እንዳይስት ከማድረጉም በላይ በአካሉ ውስጥ የቀሩት ቀይ የደም ሕዋሶችና ሌሎች ንጥረ ነገሮች በሰውነቱ ውስጥ እንዲዘዋወሩ ያስችላል።

ሙሉ ደም ወይም የደም ፕላዝማ ሳይሰጡ የደምን መጠን ወደ መደበኛው መጠን መመለስ ይቻላል። * የደምን መጠን ከፍ የሚያደርጉ ደም ያልታከለባቸው የተለያዩ ፈሳሾች አሉ። ከሁሉም ቀላል የሆነው የጨው ውኃ (ሳላይን ሶሉሽን) ሲሆን በጣም ርካሽ ከመሆኑም በላይ ከደማችን ጋር ይስማማል። በተጨማሪም እንደ ዴክስትራን፣ ሄማሴልና ላክቴትድ ሪንገርስ ሶሉሽን የመሳሰሉ የየራሳቸው ልዩ ባሕርይ ያላቸው ፈሳሾች አሉ። ሄታስታርች (ኤች ኢ ኤስ) በቅርብ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለ የደምን መጠን የሚጨምር ፈሳሽ ሲሆን “[የቃጠሎ አደጋ ደርሶባቸው] ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ላልሆኑ በሽተኞች ሊሰጥ ይችላል።” (ጆርናል ኦቭ በርን ኬር ኤንድ ሪሃብልቴሽን፣ ጥር/የካቲት 1989) እንደነዚህ ያሉት ፈሳሾች ጉልህ የሆነ ጥቅም አላቸው። “ክሪስታሎይድ ሶሉሽንስ [እንደ ኖርማል ሳላይን እና ላክቴትድ ሪንገርስ ሶሉሽን ያሉት]፣ ዴክስትራንና ኤች ኢ ኤስ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ መርዛምነት የሌላቸው፣ ርካሽ የሆኑ፣ እንደ ልብ የሚገኙ፣ ማቀዝቀዣ በሌለበት ቦታ ሊቀመጡ የሚችሉ፣ ለበሽተኛው የሚስማሙ ስለመሆናቸው ምርመራ ማድረግ የማያስፈልጋቸውና ደም እንደመውሰድ በሽታ ያስተላልፋሉ የሚል ስጋት የማያስከትሉ ናቸው።”​—⁠ብለድ ትራንስፍዩዥን ቴራፒ​—⁠ኤ ፊዚሽያንስ ሃንድ ቡክ፣ 1989

ይሁን እንጂ ‘በሰውነቴ ውስጥ ኦክስጅን ለማዳረስ የሚያስፈልጉኝ ቀይ የደም ሕዋሶች ሆነው ሳለ ደም አልባ የሆኑ የደም መተኪያ ፈሳሾች ጠቀሜታ የሚኖራቸው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰውነትህ ለድንገተኛ ሁኔታ የተጠበቀ ተጨማሪ ኦክስጅን የመሸከም አቅም አለው። ደም ከፈሰሰህ ይህን ያጣኸውን ደም የሚያካክስ አስደናቂ የሆነ አሠራር ይጀምራል። ልብህ በእያንዳንዱ ምት ከወትሮው የበለጠ ደም ይረጫል። የፈሰሰው ደም ተስማሚ በሆነ ፈሳሽ ስለተተካ የቀጠነው ደምህ በትናንሾቹ የደም ሥሮች ሳይቀር በቀላሉ መዘዋወር ይጀምራል። በሚፈጠሩት ኬሚካላዊ ለውጦች ምክንያት ህብረ ሕዋሶችህ ብዙ ኦክስጅን ያገኛሉ። ሰውነትህ የተፈጠረውን አደጋ ለመቋቋም የሚያደርገው ይህ ጥረት በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሣ ከነበሩህ ቀይ የደም ሕዋሶች የቀሩህ ግማሾቹ ብቻ ቢሆኑ እንኳን በውስጥህ የሚኖረው የኦክስጅን አቅርቦት የመደበኛውን 75 በመቶ ይሆናል። እረፍት በመውሰድ ላይ ያለ አንድ በሽተኛ በደሙ ውስጥ ካለው ኦክስጅን የሚጠቀመው 25 በመቶውን ብቻ ነው። በተጨማሪም አብዛኞቹ አጠቃላይ ሰመመን የሚያመጡ መድኃኒቶች የሰውነትን የኦክስጅን ፍጆታ ይቀንሳሉ።

ዶክተሮች እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች ብዙ ደም ፈስሶት ቀይ የደም ሕዋሶች አነስተኛ የሆኑበትን በሽተኛ ሊረዱት ይችላሉ። የበሽተኛው የደም መጠን ወደ መደበኛው መጠን ከተመለሰ በኋላ ዶክተሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ኦክስጅን ሊሰጡት ይችላሉ። ይህም ሰውነቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ኦክስጅን እንዲያገኝ ስለሚያስችለው ብዙ ጊዜ በጣም አስደናቂ የሆነ ውጤት አስገኝቷል። የእንግሊዝ ዶክተሮች ብዙ ደም ፈስሷት “የሄሞግሎቢንዋ መጠን በመቶ ሲሲ ደም ውስጥ ወደ 1.8 ግራም በደረሰባት” አንዲት ሴት ላይ ይህን ዘዴ ተጠቅመው ነበር። “የተሰጣት ሕክምና ተሳክቷል። . . . ከፍተኛ መጠን ያለው ኦክስጅንና ጀላቲን ፈሳሽ [ሄማሲል] ተሰጣት።” (አኔስቴዥያ፣ ጥር 1987) በተጨማሪም ሪፖርቱ በከፍተኛ መጠን ደም የፈሰሳቸው ሌሎች ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ኦክስጅን በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ሆነው የተሰጣቸው ሕክምና የተሳካ ውጤት እንዳስገኘ ገልጿል።

በተጨማሪም ሐኪሞች የበሽተኞቻቸው ሰውነት የበለጠ መጠን ያለው ቀይ የደም ሕዋስ እንዲሠራ ሊረዱ የሚችሉበት መንገድ አለ። እንዴት? በጡንቻ ወይም በደም ሥር ብረት ያለበት መድኃኒት ሊሰጧቸው ይችላሉ። ይህም የበሽተኛው አካል ከመደበኛው ከሦስት እስከ አራት በሚደርስ እጥፍ ቀይ የደም ሕዋሶችን እንዲሠራ ያስችላል። በቅርቡ ደግሞ ለዚህ ዓላማ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሌላ ነገር ተገኝቷል። ኩላሊቶችህ በአጥንቶችህ መገጣጠሚያ መካከል የሚገኘው መቅን ቀይ የደም ሕዋሶችን እንዲሠራ የሚቀሰቅስ ኤሪትሮፖየቲን (EPO) የተባለ ሆርሞን ይሠራሉ። በአሁኑ ጊዜ ሰው ሠራሽ (በራሂያዊ ብወዛ በማካሄድ) ኢ ፒ ኦ ማግኘት ተችሏል። ዶክተሮች ይህን ሆርሞን ደም ላነሳቸው በሽተኞች ሊሰጡና ያጡትን ቀይ የደም ሕዋስ በፍጥነት እንዲተኩ ሊረዷቸው ይችላሉ።

ቀዶ ሕክምና በሚደረግበት ጊዜ እንኳን ጥሩ ችሎታ ያላቸውና ሥራቸውን በትጋት የሚያከናውኑ ቀዶ ሐኪሞችና አኔስቴዝዮሎጂስቶች (ሰመመን ሰጪዎች) ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚያደርጉ ዘዴዎችን በመጠቀም ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። እንደ ኤሌክትሮኮውተሪ የመሰሉት ጥንቃቄ የተሞላባቸው ቴክኒኮች ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ወደ ቁስሎች የሚፈሰው ደም ከተመጠጠ በኋላ ተጣርቶና ወደ ደም ሥር ተመልሶ እንዲዘዋወር ማድረግ ይቻላል። *

ደም አልባ የሆነ ፈሳሽ የተጨመረበት የልብና ሳንባ ማሽን የተደረገላቸው በሽተኞች የሚያጡት ቀይ የደም ሕዋስ አነስተኛ ስለሚሆን የደማቸው መቅጠን ጠቃሚ ሊሆንላቸው ይችላል።

በሽተኞችን ለመርዳት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህም መካከል በቀዶ ሕክምና ወቅት በሽተኛውን በማቀዝቀዝ የኦክስጅን ፍጆታውን መቀነስ፣ የደም ግፊትን የሚቀንስ ሰመመን መስጠት፣ የደምን የመርጋት ፍጥነት የሚጨምር ሕክምና መስጠት፣ ዴስሞፕሬሲን (ዲ ዲ ኤ ቪ ፒ) በተባለ መድኃኒት አማካኝነት ደም የሚፈስበትን ጊዜ መቀነስና በሌዘር “መቁረጫ መሣሪያዎች” መጠቀም ይገኝበታል። ይህ ዝርዝር ሐኪሞችና ጉዳዩ ያሳሰባቸው በሽተኞች ከደም ለመራቅ በፈለጉ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። ብዙ ደም እንዲፈስስህ የሚያደርግ ሁኔታ እንዳያጋጥምህ እንመኛለን። ቢያጋጥምህ ግን ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች ብዙ አደጋ የሚያስከትለውን ደም በደም ሥር የመስጠት የሕክምና ዘዴ ሳይጠቀሙ አስፈላጊውን ሕክምና መስጠት አያቅታቸውም።

ቀዶ ሕክምና​—ግን ያለ ደም

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ደም አይወስዱም። እነዚህ ሰዎች ደም አልባ የሆኑ አማራጭ መድኃኒቶችን በመጠቀም ጥራት ያለው ሕክምና እንዲሰጣቸው የሚጠይቁት ስለ ጤንነታቸው በማሰብ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በአንደኛ ደረጃ ደም አንወስድም የሚሉት በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሣ ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አለ ደም ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይቻላል። በዚህ ረገድ አሁንም የምትጠራጠርበት ምክንያት ካለህ ከሕክምና ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ ተጨማሪ ማስረጃዎች በማንበብ ይህን ጥርጣሬህን ሊያስወግዱልህ ይችላሉ።

የአንድን የይሖዋ ምሥክር አራት መጋጠሚያዎች ለመቀየር የተካሄደ ከባድ ቀዶ ሕክምና (“Quadruple Major Joint Replacement in Member of Jehovah’s Witnesses”) የተባለው ጽሑፍ (ኦርቶፔዲክ ሪቪው፣ ነሐሴ 1986) “በሁለቱም የጉልበትና የዳሌ መጋጠሚያዎች ላይ ከባድ ጉዳት ስለደረሰበት” ደም ያነሰው በሽተኛ ይናገራል። ከቀዶ ሕክምናው በፊትና በኋላ አይረን ዴክስትራን የተባለ መድኃኒት በመስጠት የተሳካ ቀዶ ሕክምና ለማከናወን ተችሏል። ብሪትሽ ጆርናል ኦቭ አኔስቴዥያ (1982) በ52 ዓመት ዕድሜ ላይ የምትገኝን አንዲት ምሥክር አስመልክቶ ሪፖርት አድርጓል። ይህች ምሥክር የሄሞግሎቢንዋ መጠን ከ10 ያነሰ ነበር። የደም ግፊት በሚቀንስ ሰመመን በመጠቀም ብዙ ደም እንዳይፈስሳት በማድረግ የዳሌዋንና የትከሻዋን መጋጠሚያ ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ ተችሏል። በአርካንሳስ (ዩ ኤስ ኤ) ዩኒቨርሲቲ የሚገኝ አንድ የቀዶ ሐኪሞች ቡድን መቶ በሚያክሉ ምሥክሮች የሆኑ በሽተኞች ላይ ይህንኑ ዘዴ በመጠቀም የዳሌ መጋጠሚያ ቀዶ ሕክምና አድርጓል። ሁሉም በሽተኞች ድነዋል። የዚህ ቡድን መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር “ከእነዚህ (ምሥክር የሆኑ) በሽተኞች የተማርነውን፣ የዳሌ መጋጠሚያ ቀዶ ሕክምና ለምናደርግላቸው በሽተኞች በሙሉ በመጠቀም ላይ ነን” ብለዋል።

አለ ደም ከሆነ የሌላ ሰው አካል ቢዛወርላቸው ሕሊናቸው የሚፈቅድላቸው የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የኩላሊት ማዛወር ሕክምና የተደረገላቸው የ13 በሽተኞች ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ከአጠቃላዩ ውጤት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የኩላሊት ማዛወር ቀዶ ሕክምና በአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያለ ምንም ችግርና አደጋ ማድረግ ይቻላል።” (ትራንስፕላንቴሽን፣ ሰኔ 1988) ደም አለመውሰድ የተሳካ የልብ ማዛወር ሕክምና ለማድረግም እንቅፋት አልሆነም።

‘ሌሎች ዓይነቶቹ ደም አልባ ቀዶ ሕክምናዎችስ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ሜዲካል ሆትላይን (ሚያዝያ/ግንቦት 1983) “[በዌይን ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ዩ ኤስ ኤ] ደም ሳይሰጣቸው ከባድ የማኅፀን ቀዶ ሕክምና ስለተደረገላቸው የይሖዋ ምሥክሮች” ሪፖርት አድርጓል። ይህ የዜና መጽሔት “በቀዶ ሕክምናው ምክንያት የሞቱትና የጤና መታወክ የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ደም ተሰጥቷቸው ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው የበዛ አይደለም” ብሏል። ከዚያም መጽሔቱ በመቀጠል “የዚህ ጥናት ውጤት የማኅፀን ቀዶ ሕክምና ለሚደረግላቸው ሴቶች በሙሉ ደም ስለመስጠት ያለንን አመለካከት እንድንለውጥ ሊያደርግ ይችላል” የሚል ሐሳብ ሰጥቷል።

በጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ (ጀርመን) በሚገኝ ሆስፒታል ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባልሆኑ 30 በሽተኞች ላይ ቀዶ ሕክምና ተደርጓል። “ደም ከወሰዱ በሽተኞች የተለየ ቀውስ አላጋጠማቸውም። . . . ደም የመውሰድ ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው አይገባም፤ በመሆኑም ደም አለመውሰድ አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነ ቀዶ ሕክምና ከማድረግ የሚያግድ ምክንያት ሆኖ መቅረብ የለበትም።”​—⁠ሪሲኮ ኢን ደር ቺሩርጊ፣ 1987

የአንጎል ቀዶ ሕክምና እንኳን በርካታ በሆኑ አዋቂና ሕፃናት በሽተኞች ላይ አለ ደም ተካሄዷል። በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል ውስጥ የተደረጉትን ቀዶ ሕክምናዎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የኒውሮሰርጀሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ጆሲፍ ራንሶሆፍ በ1989 እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአብዛኞቹ ሁኔታዎች፣ በተለይ ቀዶ ሕክምናውን በተቀላጠፈና በአንጻራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ማከናወን ከተቻለ በሃይማኖታቸው ምክንያት የደም ተዋጽኦዎችን አንወስድም የሚሉ በሽተኞችን አለደም ኦፕራስዮን ማድረግ እንደሚቻል በጣም ግልጽ ነው። በሽተኞቹ ድነው ሲወጡ ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ስላከበርኩላቸው ሲያመሰግኑኝ ትዝ ይለኛል እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን እንኳን እዘነጋለሁ።”

በመጨረሻ በጣም ረቂቅ የሆነ የልብና የደም ቧንቧዎች ቀዶ ሕክምና ለአዋቂዎችና ለሕፃናት አለ ደም ሊደረግ ይችላልን? ዶክተር ዴንተን ኤ ኩሊ እንዲህ ዓይነቱን ቀዶ ሕክምና በማድረግ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በገጽ 27-9 ላይ በሚገኘው ተጨማሪ ክፍል ላይ የወጣው የሕክምና ጽሑፍ እንደሚያሳየው ዶክተር ኩሊ ቀደም ሲሉ ያደረጉትን ጥናት መሠረት በማድረግ “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ያጋጠሙ ችግሮችና አደጋዎች ከሌሎች በሽተኞች የበለጠ አይደለም” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። 1,106 ቀዶ ሕክምናዎችን ካከናወኑ በኋላ “በሁሉም ጊዜያት ከበሽተኛው ጋር የገባሁትን ስምምነት ወይም ውል፣” ደም ላለመስጠት የገቡትን ውል ማለት ነው፣ “ለመጠበቅ ችዬአለሁ” ሲሉ ጽፈዋል።

የይሖዋ ምሥክሮችን ልዩ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ ያላቸው ጥሩ ዝንባሌ እንደሆነ ቀዶ ሐኪሞች ተገንዝበዋል። ዶክተር ኩሊ “የእነዚህ በሽተኞች ዝንባሌ በጥሩ ምሳሌነት የሚታይ ነው” በማለት በጥቅምት ወር 1989 ጽፈዋል። “እንደ አብዛኞቹ በሽተኞች በሽታውን የሚያባብስ ሁኔታ ይፈጠራል ወይም እንሞታለን ብለው አይፈሩም። በእምነታቸውና በአምላካቸው ላይ የጠለቀና ጠንካራ የሆነ እምነት አላቸው።”

እንዲህ ያለ ዝንባሌ የኖራቸው ግን የመሞት መብታቸውን ለማስከበር ስለሚፈልጉ አይደለም። ከበሽታቸው ለመዳን ስለሚፈልጉ ጥራት ያለው ሕክምና ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ መታዘዝ ጥበብ እንደሆነ ከልባቸው ያምናሉ። ይህ አመለካከታቸው ደም አልባ በሆነ ቀዶ ሕክምና ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድር ችሏል።

በፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ (ጀርመን) የቀዶ ሕክምና ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ዶክተር ቪ ሽሎሰር እንደሚከተለው ብለዋል:- “ከኦፕራስዮን በኋላ የሚከሰተው የደም መፍሰስ ችግር በእነዚህ በሽተኞች ላይ ብዙ ጊዜ አያጋጥምም። የሕመም መባባስ የሚያጋጥማቸውም በጣም ጥቂቶች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ለበሽታ ያላቸው የተለየ አመለካከት ከኦፕራስዮን በኋላ በሚኖረው ሂደት ላይ በጎ ተጽእኖ ያሳድራል።”​—⁠ኸርዝ ክራይስላውፍ፣ ነሐሴ 1987

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 ምሥክሮች ሙሉ ደም፣ ቀይ የደም ሕዋስ፣ ነጭ የደም ሕዋስ፣ ፕሌትሌቶችን ወይም የደም ፕላዝማ አይወስዱም። እንደ ኢምዩን ግሎቡሊን የመሰሉ በጣም አነስተኛ የሆኑ የደም ተዋጽኦዎች ስለተጨመረባቸው መድኃኒቶች መጠበቂያ ግንብ 11-111 ገጽ 30-1 ተመልከት።

^ አን.17 በመጋቢት 1, 1989 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ በገጽ 30-31 ላይ የፈሰሰን ደም መልሶ በመጠቀምና በደም ማዘዋወሪያ መሣሪያዎች ረገድ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተብራርተዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“በአሁኑ ጊዜ ከሚሰጣቸው ደምና የደም ተዋጽኦ ምንም ዓይነት ጥቅም ላያገኙ ለመጥፎ አደጋ የሚጋለጡ ብዙ በሽተኞች እንዳሉ ለማመን እንገደዳለን። ለአንድ በሽተኛ ከጉዳት በስተቀር ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማያስገኝ የሚያውቀውን ሕክምና ሆን ብሎ የሚሰጥ ሐኪም ፈጽሞ አይኖርም። ይሁን እንጂ አስፈላጊ ሳይሆን ደም በሚሰጥበት ጊዜ የሚደርሰው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም።”​—⁠“ትራንስፍዩዥን-ትራንስሚትድ ቫይራል ዲዝዝስ” 1987

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ከ2 እስከ 2.5 ግራም በመቶ ሲሲ የሚደርስ ዝቅተኛ የሄሞግሎቢን መጠን እንኳን ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል የሚናገሩ ተመራማሪዎች አሉ። . . . ደሙ የፈሰሰው ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ከሆነ 50 በመቶ የሚሆነውን ቀይ የደም ሕዋሳቸውን ቢያጡ እንኳን ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች አሉ።”​—⁠“ቴክኒክስ ኦቭ ብለድ ትራንስፍዩዥን፣” 1982

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ኦክስጅን በሰውነት ህብረ ሕዋሳት ውስጥ ስለሚዘዋወርበት ሁኔታ፣ ስለ ቁስል መዳንና ደም ስላለው ‘የምግብነት ባሕርይ’ ቀደም ሲል የነበሩት ጽንሰ ሐሳቦች ተቀባይነት እያጡ መጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ በሽተኞች ያገኘነው ተሞክሮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰን የደም ማነስ መቋቋም እንደሚቻል በተግባር አሳይቶናል።”​—⁠“ዚ አናልስ ኦቭ ቶራሲክ ሰርጀሪ፣” መጋቢት 1989

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ትንንሽ ልጆችም? “ቀዶ ሕክምናዎቹ ከባዶች ቢሆኑም አርባ ስምንት በሚያክሉ ሕፃናት ላይ የልብ ቀዶ ሕክምና አለደም ተደርጓል።” ሕፃኖቹ የነበራቸው ክብደት ከ4.7 ኪሎ ግራም ያልበለጠ ነበር። “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ባደረግናቸው ቀዶ ሕክምናዎች ላይ ሁልጊዜ የተሳካ ውጤት ስላገኘንና ደም መስጠት የሚያስከትላቸው ከባድ ችግሮች ስላሉ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹን በሕፃናት ላይ የሚደረጉ የልብ ቀዶ ሕክምናዎች የምናደርገው ያለ ደም ነው።”​—⁠“ሰርኩሌሽን” መስከረም 1984

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልብ-ሳንባ ማሽን ደም ለመውሰድ በማይፈልጉ በሽተኞች ላይ ለሚደረግ የልብ ቀዶ ሕክምና ትልቅ እርዳታ አበርክቷል