በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመምረጥ መብት አለህ

የመምረጥ መብት አለህ

የመምረጥ መብት አለህ

በአሁኑ ጊዜ በስፋት ሥራ ላይ የዋለ አንድ የሕክምና አመለካከት (ጥቅሙንና ጉዳቱን ማመዛዘን ይባላል) ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ በሽተኞች ከሐኪሞች ጋር የተሻለ መግባባት እንዲኖራቸው እያደረገ ነው። ዶክተሮች አንድ ዓይነት መድኃኒት ወይም ቀዶ ሕክምና ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ጋር ያመዛዝናሉ። በሽተኞችም በእንዲህ ዓይነቱ የማመዛዘን ሂደት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ።

በብዙ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን አንድ ምሳሌ ወስደን እንመልከት። ሥር የሰደደን የቶንስል በሽታ እንውሰድ። ይህ በሽታ ካለብህ ወደ ሐኪም መሄድህ አይቀርም። እንዲያውም የጤና ጠበብት ምን ጊዜም ቢሆን ሁለት ሐኪም ማማከር ጥሩ ነው ስለሚሉ በሁለት ሐኪሞች ታይተህ ይሆናል። አንደኛው ሐኪም ኦፕራስዮን ብትሆን ይሻላል ይልህ ይሆናል። ከዚያም ኦፕራስዮኑ ምን ያህል ጊዜ በሆስፒታል እንደሚያስተኛህ፣ ምን ያህል እንደሚያምህና ምን ያህል ወጪ እንደሚያስከትልብህ ይነግርሃል። ሕክምናው ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ በተመለከተም በጣም ብዙ ደም እንደማይፈስህና በዚህ ኦፕራስዮን ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ ይገልጽልሃል። ይሁን እንጂ ሌላው ሐኪም የአንቲባዮቲክ ሕክምና እንድትሞክር አጥብቆ ይመክርሃል። የምትወስደውን መድኃኒት ዓይነት፣ ምን ያህል እንደሚያስወጣህና የመዳን ዕድልህ ምን ያህል እንደሆነ ይነግርሃል። መድኃኒቱ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ በተመለከተም ለሕይወት የሚያሰጋ ጉዳት እንደማያመጣ ይገልጽልሃል።

እያንዳንዱ ጥሩ ብቃት ያለው ሐኪም የአንድን የሕክምና ዓይነት ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘኑ የማይቀር ቢሆንም ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ከጉዳቱ ማመዛዘንና ሌሎቹን በሚገባ የምታውቃቸው ሁኔታዎች በጥንቃቄ መመርመር የአንተ ኃላፊነት ነው። (ስሜታዊና መንፈሳዊ ጥንካሬህን፣ የገንዘብህን አቅም፣ በቤተሰብህና በምትከተለው ግብረ ገብ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ከአንተ የተሻለ ሊያውቅ የሚችል ሰው የለም።) ይህን ሁሉ ካመዛዘንክ በኋላ ምርጫህን ትወስናለህ። ባገኘኸው መረጃ ላይ ተመርኩዘህ አንዱን ሕክምና ትቀበላለህ፤ ሌላውን ደግሞ ትተዋለህ።

ሥር የሰደደ የቶንስል በሽታ የተያዘው ልጅህ ቢሆንም የምታደርገው ከዚህ የተለየ አይሆንም። የሕክምናው ውጤት ከአንተ የበለጠ በቀጥታ የሚመለከተው ሰው ስለማይኖርና ውጤቱንም የመሸከም ኃላፊነት የሚወድቀው በአንተ ላይ ስለሆነ አማራጮቹ የሕክምና ዓይነቶች፣ የሚያስከትሏቸው ጥቅሞችና ጉዳቶች ሊነገሩህ ይገባል። ጉዳዩን ከሁሉም አቅጣጫዎች ከመረመርክ በኋላ የልጅህን ጤንነት፣ እንዲያውም ሕይወቱን በሚነካው በዚህ ጉዳይ ላይ በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ ታደርጋለህ። ኦፕራስዮኑን ሊያስከትል ከሚችላቸው አደጋዎች ጋር ትመርጥ ይሆናል። ሌሎች ወላጆች ደግሞ የአንቲባዮቲኩን ሕክምና ሊያስከትል ከሚችላቸው አደጋዎች ጋር ይመርጡ ይሆናል። ሐኪሞች በሚሰጡት ምክር ረገድ አንዳቸው ከሌላው እንደሚለዩ ሁሉ በሽተኞች ወይም ወላጆችም በሚመርጡት ሕክምና ረገድ ይለያያሉ። (ጥቅሙንና ጉዳቱን በማመዛዘን) በመረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ የሚደረግበት ሁኔታ ይህን ይመስላል።

በደም አጠቃቀም ረገድስ? ሐቁን በሚዛናዊ አእምሮ የሚመረምር ማንኛውም ሰው ደም መውሰድ ከባድ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ሊክድ አይችልም። በጣም ትልቅ በሆነው በማሳቹሴትስ ጀነራል ሆስፒታል ደም የመስጠት አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቻርልስ ሃጊንስ እንዲህ ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል:- “ደም በመውሰድ ምክንያት የሚከተለው ጉዳት ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም አደገኛ መሆኑን መቀበል ይኖርብናል። በሕክምና ውስጥ ከምንገለገልባቸው ነገሮች በሙሉ የደምን ያህል አደገኛ ነገር የለም።”​—⁠ዘ ቦስተን ግሎብ ማጋዚን፣ የካቲት 4, 1990

ለሕክምና ባለሞያዎች የሚከተለው ምክር የተሰጠው አለበቂ ምክንያት አይደለም:- “በጥቅምና በጉዳት መካከል ያለውን ዝምድና በምናመዛዝንበት ጊዜ ደም መስጠት ለሚያስከትለው አደጋ የበለጠ ትኩረት መስጠትና ሌሎች አማራጮችን መፈለግ ይኖርብናል።” (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።)​—⁠ፐሪኦፐረትቭ ሬድ ሴል ትራንስፍዩዥን፣ የብሔራዊ ጤና ተቋሞች ጉባኤ፣ ሰኔ 27-29, 1988

ደም መስጠት የሚያስገኘውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት አስመልክቶ አንዱ ሐኪም ከሌላው ላይስማማ ይችላል። አንዱ ሐኪም ብዙ ጊዜ ደም የሰጠ ይሆንና ከጉዳቱ ጥቅሙ አመዝኖ ይታየው ይሆናል። ሌላው ሐኪም ደግሞ አለምንም ደም ካደረጋቸው ሕክምናዎች ጥሩ ውጤት ስላገኘ ደም መስጠት አስፈላጊ ላልሆነ አደጋ ማጋለጥ ሆኖ ሊታየው ይችላል። የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ ያለብህ ግን አንተ በሽተኛው ወይም ወላጁ ነህ። ለምን ቢባል ውሳኔው በቀጥታ የሚነካው የአንተን (ወይም የራስህን ልጅ) አካል፣ ሕይወት፣ ግብረ ገብና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ነው።

መብትህ የተጠበቀ ነው

በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች በሽተኛው ስለሚሰጠው ሕክምና የራሱን ውሳኔ የማድረግ የማይደፈር መብት አለው። “በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የማድረግ ሕግ በሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው:- አንደኛ፣ አንድ በሽተኛ ስለሚሰጠው ሕክምና በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ ለማድረግ እንዲችል በቂ መረጃ የማግኘት መብት አለው። ሁለተኛ፣ በሽተኛው ይበጅሃል ተብሎ በሐኪሙ የተነገረውን ሕክምና ሊቀበል ወይም ላይቀበል ይችላል። . . . በሽተኞች እምቢ ወይም እሺ፣ ወይም ደግሞ እሺ ከማለታቸው በፊት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች የማስቀመጥ መብት እንዳላቸው ተደርጎ ካልታየ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የማድረግ መብት በንኖ ይጠፋል።”​—⁠ኢንፎርምድ ኮንሰንት​—⁠ሊጋል ቲዎሪ ኤንድ ክልኒካል ፕራክቲስ፣ 1987 *

አንዳንድ በሽተኞች በዚህ መብታቸው ለመጠቀም ሲፈልጉ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የተቃወማቸው ቶንስልን በኦፕራስዮን ማስወጣት ወይም አንቲባዮቲክ መውሰድን በጥብቅ የሚደግፍ ወዳጃቸው ሊሆን ይችላል። ወይም አንድ ሐኪም ስለሚሰጠው ምክር ትክክለኛነት በጣም እርግጠኛ ስለሆነ ተቃውሟቸው ይሆናል። አለበለዚያም አንድ የሆስፒታል ባለሥልጣን ሕግ ነክ ወይም ገንዘብ ነክ ምክንያቶችን መሠረት በማድረግ ተቃውሟቸው ይሆናል።

ዶክተር ካርል ኤል ኔልሰን “ብዙ ኦርቶፔድስቶች [የይሖዋ ምሥክሮችን] ኦፕራስዮን ላለማድረግ መርጠዋል” ብለዋል። “በሽተኛውም ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና አልቀበልም የማለት መብት እንዳለው እናምናለን። ደም እንደመስጠት ያሉትን አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች አስቀርቶ ኦፕራስዮን ለማድረግ የሚቻል ከሆነ ይህን ምርጫ መስጠት ይገባል።”​—⁠ዘ ጆርናል ኦቭ ቦን ኤንድ ጆይንት ሰርጀሪ፣ መጋቢት 1986

አሳቢ የሆነ በሽተኛ አንድ ሐኪም የማይችለውን ዓይነት ሕክምና እንዲያደርግለት አይጫነውም። ይሁን እንጂ ዶክተር ኔልሰን እንዳሉት ራሳቸውን ለሞያቸው ያስገዙ በርካታ ሐኪሞች ለበሽተኞቻቸው እምነት አክብሮት ለማሳየት ችለዋል። አንድ የጀርመን ባለሥልጣን እንዲህ ሲሉ መክረዋል:- “አንድ ሐኪም . . . አንድን የይሖዋ ምሥክር በሚያክምበት ጊዜ በሁሉም የሕክምና አማራጮች ሊጠቀም አለመቻሉን ምክንያት በማድረግ የሕክምና እርዳታ አልሰጥም ሊል አይችልም። አማራጮቹ የተወሰኑ በሚሆኑበት ጊዜ እንኳን እርዳታ የመስጠት ግዴታ አለበት።” (ደር ፍራወንአርስት፣ ግንቦት-ሰኔ 1983) በተመሳሳይም ሆስፒታሎች የሚቋቋሙት በማንም ላይ አድልዎ ሳያደርጉ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለማገልገል ጭምር እንጂ ትርፍ ለማጋበስ ብቻ አይደለም። የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ሪቻርድ ጄ ዴቪን እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሆስፒታል የበሽተኛውን ሕይወትና ጤና ለመጠበቅ ማንኛውንም የሕክምና ጥረት ቢያደርግም የሚሰጠው ሕክምና [የበሽተኛውን] ሕሊና የማይቃወም መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ከዚህም በላይ ከማባበል አንስቶ ደም እንዲወስድ የሚያስገድድ የፍርድ ቤት ትእዛዝ እስከማውጣት ካለው ማንኛውም ዓይነት ግፊት መራቅ አለበት።”​—⁠ኸልዝ ፕሮግረስ፣ ሰኔ 1989

ከፍርድ ቤቶች ይልቅ

ግለሰቦችን የሚመለከቱ የሕክምና ጥያቄዎች መፈታት የሚኖርባቸው በፍርድ ቤት እንዳልሆነ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። በአንቲባዮቲክ መታከም መርጠህ እያለ አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሄዶ ኦፕራስዮን እንድትደረግ የሚያስገድድ ትእዛዝ ቢያወጣ ምን ይሰማሃል? አንድ ሐኪም ከሁሉ የተሻለ ነው ብሎ የሚያስበውን ሕክምና ሊያደርግልህ ይፈልግ ይሆናል። ቢሆንም መሠረታዊ መብትህን ለመርገጥ የሚያስችለው ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጠው የመጠየቅ ግዴታ የለበትም። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከደም መራቅንና ከዝሙት መራቅን እኩል በሆነ የሥነ ምግባር ደረጃ ላይ ስለሚያስቀምጥ አንድን ክርስቲያን አስገድዶ ደም መስጠት አስገድዶ ግብረ ሥጋ ከመፈጸም አይለይም።​—⁠ሥራ 15:​28, 29

ይሁን እንጂ ኢንፎርምድ ኮንሰንት ፎር ብለድ ትራንስፍዩዥን (1989) የተባለው ጽሑፍ እንደዘገበው አንዳንድ ፍርድ ቤቶች አንድ በሽተኛ በሃይማኖታዊ መብቶቹ ምክንያት የሚመጣውን አደገኛ ሁኔታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ ሲገኝ ተናድደው “ከሕግ ውጭ የሆነ የፈጠራ ምክንያት በማቅረብ ደም እንዲሰጥ ለማስገደድ ይሞክራሉ።” እርግዝናን የሚመለከት ጉዳይ ነው፣ ወይም አላሳዳጊ የሚቀሩ ልጆች ይኖራሉ የሚል ሰበብ በማቅረብ እርምጃቸው ትክክል እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል። “ግን እነዚህ ሁሉ የፈጠራ ምክንያቶች ናቸው” ይላል ጽሑፉ። “የአእምሮ ብቃት ያላቸው ለአቅመ አዳም የደረሱ ሰዎች በሙሉ አንድን ዓይነት ሕክምና አልቀበልም የማለት መብት አላቸው።”

ደም መውሰድ አለባቸው የሚል ግትር አቋም ካላቸው መካከል አንዳንዶቹ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አንቀበልም የሚሉት ሁሉንም ዓይነት ሕክምና አለመሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አያስገቡም። የይሖዋ ምሥክሮች አንቀበልም የሚሉት የሕክምና ሊቃውንት ሳይቀሩ በብዙ አደጋዎች የታጠረ ነው የሚሉትን አንድ ሕክምና ብቻ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አንድን የጤና ችግር ለማከም የሚቻልባቸው ከአንድ የበለጡ የተለያዩ መንገዶች ይኖራሉ። አንደኛው መንገድ አንድ ዓይነት አደጋ ሲኖረው ሌላው ደግሞ ሌላ ዓይነት አደጋ ይኖረዋል። ታዲያ አንድ ፍርድ ቤት ወይም ሐኪም የአንተን ቦታ ወስዶ “ለአንተ የሚበጀው የትኛውን አደጋ መቀበል” እንደሆነ ሊወስንልህ ይችላል? ይህን መወሰን የምትችለው አንተ ብቻ ነህ። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሌላ ሰው ውሳኔ እንዲያደርግላቸው ፈጽሞ አይፈልጉም። በአምላክ ዘንድ የሚጠየቁበት የግል ኃላፊነታቸው ነው።

አንድ ፍርድ ቤት ከፈቃድህ ውጭ አጥብቀህ የምትጸየፈው ሕክምና እንዲሰጥህ ቢያደርግ ይህ እርምጃ በሕሊናህ ላይም ሆነ ወደፊት በሕይወት ለመኖር ባለህ ፍላጎት ላይ ምን ዓይነት ውጤት ይኖረዋል? ዶክተር ኮንራድ ደረቢንገር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንድ ሐኪም አንድን በሽተኛ አስገድዶ የበሽተኛው ሕሊና የማይቀበለውን ሕክምና ቢሰጥና አካሉን አክሞ በመንፈሱ ላይ ግን ሊሽር የማይችል ቁስል ቢያስከትል ዓላማውንና አቅጣጫውን የሳተ የሞያ ፍቅር ማሳየት ይሆንበታል።”​—⁠ደር ፕራክቲሸ አርስት፣ ሐምሌ 1978

ለሕፃናት የሚደረግ ፍቅራዊ እንክብካቤ

ደምን የሚመለከቱ የፍርድ ቤት ጉዳዮች አብዛኛውን ጊዜ የሚነሱት በሕፃናት ላይ ነው። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች አክብሮት በተሞላ መንፈስ ቀርበው ለልጆቻቸው ደም እንዳይሰጥ ሲጠይቁ የሕክምና ባለሞያዎች በግድ ደም ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቶችን የጠየቁባቸው ጊዜያት አሉ። ክርስቲያኖች በልጆች ላይ በደል እንዳይፈጸም ወይም ልጆች ችላ እንዳይባሉ የሚደነግጉ ሕጎችንና የፍርድ ብያኔዎችን እንደሚያከብሩ የተረጋገጠ ነው። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን አላግባብ በመቅጣት አካላዊ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ወይም የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና እንክብካቤ እንዳያገኙ እንዳደረጉ የሚገልጹ ዜናዎችን አንብበህ ይሆናል። ይህ በእጅጉ የሚያሳዝን ነገር ነው! መንግሥት በደል ለደረሰበት ሕፃን ጥበቃ ማድረግ እንደሚችልና እንደሚገባውም ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ወላጅ ለሚያስብለት ልጁ ደም አልባ የሆነ ጥራት ያለው ሕክምና እንዲሰጥ የሚጠይቅበት ሁኔታ ከዚህ በጣም የተለየ እንደሆነ መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም።

እነዚህ የፍርድ ቤት ክሶች አብዛኛውን ጊዜ የሚያተኩሩት ሆስፒታል ገብቶ በተኛ ልጅ ላይ ነው። ይህ ልጅ ሆስፒታል ሊገባ የቻለው እንዴትና ለምንድን ነው? አሳቢ የሆኑ ወላጆች ልጃቸው ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኝ ብለው ስላመጡት አይደለምን? ኢየሱስ ለልጆች አሳቢነት እንዳሳየ ሁሉ ክርስቲያን ወላጆችም ለልጆቻቸው ደህንነት ያስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ልጆቿን ተንከባክባ ስለምታሳድግ እናት’ ይናገራል። የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው ይህን የመሰለ የጠለቀ ፍቅር አላቸው።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:​7፤ ማቴዎስ 7:​11፤ 19:​13-15

ማንኛውም ወላጅ የልጁን ደህንነትና ሕይወት የሚነኩ ውሳኔዎች ያደርጋል። ቤተሰቡ ቤቱን ለማሞቅ በእሳት ወይም በከሰል ይጠቀማል? ልጁን ይዞ ወደ ሩቅ አካባቢ ይጓዛል? ልጁ ዋና እንዲሄድ ይፈቅዳል? እነዚህ በሙሉ አደጋ ሊያስከትሉ፣ እንዲያውም ሕይወት እስከማጣት ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ወላጆች እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች ረገድ ተገቢውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው ስለሚቀበል ወላጆች የልጆችን ሕይወት በሚመለከቱ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ1979 የሚከተለውን ግልጽ ብይን ሰጥቷል:- “ሕጉ ለቤተሰብ የሚሰጠው እውቅና በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ውሳኔ በመስጠት ረገድ ልጆች የሚጎድላቸው ጉልምስና፣ ተሞክሮና የማመዛዘን ችሎታ በወላጆች ሊሟላ ይችላል በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። . . . የአንድ ወላጅ [ሕክምናን የሚመለከት] ውሳኔ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ስለሆነ ብቻ ውሳኔ የማድረጉ መብት ከወላጆች ተነጥቆ ለአንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ወይም ድርጅት ሊሰጥ አይችልም።”​—⁠ፓርሃም እና ጄ አር

በዚሁ ዓመት የኒው ዮርክ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሚከተለውን ብይን ሰጥቷል:- “አንድ ሕፃን በቂ የሕክምና እንክብካቤ የተነፈገው መሆኑን ለመወሰን በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር . . . ወላጆች ሁሉንም ሁኔታዎች ያገናዘበና ተቀባይነት ያለው ሕክምና ልጆቻቸው እንዲያገኙ ተገቢውን እርምጃ ወስደው እንደሆነ ማረጋገጥ ነው። ይህ የሚረጋገጠው ወላጅዬው ‘ትክክለኛ’ ወይም ‘ስህተት’ ውሳኔ ማድረጉን በማረጋገጥ አይደለም። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የሕክምና ሞያ ብዙ እድገት ያሳየ ቢሆንም ይህን የመሰለ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ ላይ አልደረሰም። ፍርድ ቤትም ቢሆን የወላጅን ቦታ ወስዶ የማደጎ አባት ሊሆን አይችልም።”​—⁠ኢን ሬ ሆፍባወር

ቀደም ሲል እንደ ምሳሌ የጠቀስነውን ከቀዶ ሕክምና ወይም ከአንቲባዮቲክ አንዱን እንዲመርጥ የተጠየቀውን ወላጅ ሁኔታ አስታውስ። ማንኛውም ሕክምና የራሱ አደጋዎች ይኖሩታል። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ሊከተል የሚችለውን ጉዳት፣ ጥቅሙንና ሌሎች ሁኔታዎችን አመዛዝነው ውሳኔ ላይ የመድረስ ኃላፊነት አላቸው። በዚህ ረገድ ዶክተር ጆን ሳሙኤልስ (አኔስተዝዮሎጂ ኒውስ፣ ጥቅምት 1989) ዳኞች ልጆችን የሚመለከቱ የሕክምና ትእዛዝ ሲያስተላልፉ የሚከተሉት መመሪያ እንዲሻሻል ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ የሚከተለውን አቋም ወስደዋል:-

“የሕክምና እውቀት አንድ ሐኪም እርግጠኛ ሆኖ በሽተኛው እንደሚድን ወይም እንደሚሞት በቅድሚያ እንዲናገር በሚያስችለው መጠን አላደገም። . . . በሕክምናው አሰጣጥ ረገድ ምርጫ ከኖረ፣ ለምሳሌ ያህል ሐኪሙ 80 በመቶ የማዳን አጋጣሚ የሚኖረው ሕክምና እንዲሰጥ ሐሳብ ቢያቀርብ፣ ወላጆቹ ግን የማይቀበሉት ቢሆንና ከዚህ ይልቅ 40 በመቶ የማዳን አጋጣሚ ያለውን ሕክምና ቢመርጡ ሐኪሙ የበለጠ አደጋ ያለውንና በወላጆቹ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ሕክምና መስጠት ይኖርበታል።”

ደምን ለሕክምና መጠቀም የሚያስከትላቸውን አደጋዎችና ውጤታማ የሆኑ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች መኖራቸውን ስንመለከት ደም አለመውሰድ አነስተኛ አደጋ ያለው ሕክምና መምረጥ አይሆንምን?

ክርስቲያኖች ልጃቸው ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገው ከሆነ የሚያመዛዝኗቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ። ማንኛውም ኦፕራስዮን፣ ደም ተሰጠም አልተሰጠ የራሱ አደጋ አለው። ሙሉ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል ቀዶ ሐኪም ይኖራልን? ወላጆቹ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች የይሖዋ ምሥክሮችን ልጆች አለ ደም ኦፕራስዮን አድርገው የተሳካ ውጤት እንዳገኙ ያውቁ ይሆናል። ታዲያ አንድ ሐኪም ወይም የሆስፒታል ባለሥልጣን ከወላጆቹ የተለየ ምርጫ ቢኖራቸው በዚህ ጉዳይ ላይ አድካሚና ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ክስ እንዲመሠረት ከማድረግ ይልቅ አፍቃሪ ከሆኑት ወላጆች ጋር ተባብረው ቢሠሩ ምክንያታዊ አይሆንምን? ወይም ደግሞ ወላጆቹ ልጃቸውን አለ ደም ኦፕራስዮን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑና ተሞክሮ ያላቸው ሐኪሞች ወደሚገኙበት ሆስፒታል ሊያዛውሩት ይችሉ ይሆናል። እንዲያውም ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አለ ደም የሚሰጠው ሕክምና ቤተሰቡ “ሕክምና ነክ የሆኑና ያልሆኑ ተገቢ ግቦችን” ለማሟላት ስለሚያስችለው ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ሕክምና ሊሆን ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በተጨማሪው ክፍል ገጽ 30-31 ላይ ከሌላ ጽሑፍ ተወስዶ የሰፈረውን “ደም:- መከበር ያለበት የማን ምርጫና ሕሊና ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከሕግ ተጠያቂነት ሥጋት ነጻ መሆን

‘አንዳንድ ዶክተሮችና ሆስፒታሎች ደም ለመስጠት የሚያስችላቸው የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት የሚቸኩሉት ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች በአብዛኛው እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያት በሕግ ተጠያቂ እንዳይሆኑ በመሥጋት ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ደም አልባ የሆነ ሕክምና እንዲሰጣቸው በሚመርጡበት ጊዜ በሕግ ተጠያቂ የመሆን ሥጋት ሊኖር አይችልም። የአልበርት አንስታይን የሕክምና ኮሌጅ (ዩ ኤስ ኤ) ባልደረባ የሆኑ አንድ ዶክተር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አብዛኞቹ [ምሥክሮች] ሐኪሞችንና ሆስፒታሎችን ከሕጋዊ ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገውን የአሜሪካ ሕክምና ማኅበር ቅፅ ለመሙላት ዝግጁ ናቸው። በተጨማሪም ብዙዎቹ የሕክምና ማስጠንቀቂያ [ካርድ] ይይዛሉ። በተገቢ ሁኔታ የተፈረመበትና ቀን የሰፈረበት ‘የደም ተዋጽኦዎች ለመውሰድ እምቢተኛ መሆንን የሚገልጽ ካርድ’ እንደ ሕጋዊ ውል ሊቆጠር የሚችል ከመሆኑም በላይ ሕጋዊ አስገዳጅነት አለው።”​—⁠አነስቴዝዮሎጂ ኒውስ፣ ጥቅምት 1989

አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሐኪም ወይም ሆስፒታል በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ደም አልባ ሕክምና ቢሰጥ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት እንደማይኖርበት ሕጋዊ ማረጋገጫ በመስጠት ይተባበራሉ። የሕክምና ባለሞያዎች በሰጡት ማሳሰቢያ መሠረት እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የሕክምና መረጃ ሰነድ ይይዛል። ይህ ሰነድ በየዓመቱ የሚታደስ ከመሆኑም በላይ ግለሰቡና አብዛኛውን ጊዜ የቅርብ ዘመዶቹ የሆኑ ምሥክሮች የፈረሙበት ነው።

በካናዳ የኦንታርዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጋቢት ወር 1990 እንዲህ ያለውን ሰነድ የሚደግፍ ብይን አስተላልፏል:- “ይህ ካርድ የካርዱ ባለቤት ከሐኪሙ ጋር በሚያደርገው ውል ላይ ሕጋዊ የሆነ የጽሑፍ ገደብ የጣለ መሆኑን የሚያሳውቅበት የአቋም መግለጫ ነው።” ፕሮፌሰር ዳንኤል አንደርሰን በመዲቺንስክ ኤቲክ (1985) ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በሽተኛው የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ደም እንዲሰጠው እንደማይፈልግ የሚገልጽ የማያወላውል በጽሑፍ የሰፈረ ቃል ካለ ለበሽተኛው የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት ያለን አክብሮት ይህን በቃል ቢናገር ኖሮ እናደርገው የነበረውን ያህል ፈቃዱን እንድናከብርለት ያስገድደናል።”

በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል ስምምነት ቅጾችን ይሞላሉ። በፍራይቡርግ፣ ጀርመን የሚገኝ አንድ ሆስፒታል የሚጠቀምበት ቅጽ ሐኪሙ ስለሚሰጠው ሕክምና ለበሽተኛው የሰጠውን መረጃ የሚያሰፍርበት ቦታ አለ። ከዚያም ይህ ቅጽ የሐኪሙና የበሽተኛው ፊርማ ከሚያርፍበት ቦታ በላይ እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል በመሆኔ ቀዶ ሕክምና በሚደረግልኝ ጊዜ ምንም ዓይነት ባዕድ ደም ወይም የደም ተዋጽኦ ሊሰጠኝ እንደማልፈልግ በማያወላውል ሁኔታ አረጋግጣለሁ። ይህ ሊሰጠኝ የታሰበውና አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው ሕክምና በሚያስከትለው ደም መፍሰስ ምክንያት አደገኛ ሁኔታ ሊያጋጥመኝ እንደሚችል እገነዘባለሁ። በተለይ ስለዚህ ጉዳይ በቂ ማብራሪያ ከተሰጠኝ በኋላ አስፈላጊው ቀዶ ሕክምና ምንም ዓይነት ባዕድ ደም ወይም የደም ተዋጽኦ ሳይሰጠኝ እንዲከናወን እጠይቃለሁ።”​—⁠ኸርዝ ክራይስላውፍ፣ ነሐሴ 1987

እንደ እውነቱ ከሆነ ያነሰ አደጋ ያለው አለ ደም የሚሰጥ ሕክምና ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ምሥክሮቹ በሽተኞች የሕክምና ባለሞያዎች ሞያቸው የጣለባቸውን ሰዎችን የማዳን ግዴታ በነጻነት እንዲወጡ ለማስቻል ከማንኛውም አስፈላጊ ያልሆነ ሥጋት ነጻ ለማድረግ ዝግጁዎች መሆናቸው ነው። ይህ ትብብራቸው ዶክተር አንጀሎስ ኤ ካምቡሪስ “ሜጀር አብዶሚናል ኦፐሬሽንስ ኦን ጀሆቫስ ዊትነስስ” በተባለው ጽሑፋቸው እንደሚከለተው በማለት እንዳብራሩት ሁሉንም ወገኖች የሚጠቅም ነው:-

“ከኦፕራስዮን በፊት የተገባ ውል በኦፕራስዮኑ ወቅትም ሆነ ከኦፕራስዮኑ በኋላ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር መከበር እንደሚኖርበትና ሕጋዊ አስገዳጅነት እንዳለው ሐኪሙ መገንዘብ ይኖርበታል። [ይህም] በሽተኞቹን ለሚሰጣቸው ቀዶ ሕክምና ጥሩ የአእምሮ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲረዳ ሐኪሙ ደግሞ ሕግ ነክ በሆኑና በፍልስፍና ጥያቄዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ሙሉ ትኩረቱን በቀዶ ሕክምናውና በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ለበሽተኛው የሚበጀውን በሙሉ ኃይሉ እንዲፈጽም ያስችለዋል።”​—⁠ዚ አሜሪካን ሰርጀን፣ ሰኔ 1987

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“በዛሬው ጊዜ የሕክምና ወጪ ከፍተኛ ከሆነባቸው ምክንያቶች ዋነኛው በሕክምና ቴክኖሎጂዎች ሳያስፈልግ መጠቀም ነው። . . . በዚህ ረገድ በሚያስከትለው ወጪም ሆነ አደጋ ከፍተኛውን ቦታ የያዘው ደም መስጠት ነው። ስለሆነም የአሜሪካ ሆስፒታሎች ፈቃድ ሰጪ ጥምር ኮሚሽን ደም መስጠት ‘ከፍተኛ መጠን ያለው አደጋ የሚያስከትልና ለስህተት የተጋለጠ ሕክምና ነው’ ብሏል።”​—⁠“ትራንስፍዩዥን፣” ሐምሌ-ነሐሴ 1989

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዩናይትድ ስቴትስ:- “የበሽተኛው መስማማት አስፈላጊ የሚሆንበት መሠረታዊ ምክንያት ግለሰቦች ያላቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው። ጉዳዩ የሚመለከተው ግለሰብ የገዛ ራሱን ዕጣ የመወሰን መብት አለው። የበሽተኛው ስምምነት አስፈላጊ እንዲሆን የሚያስገድደው ሕጋዊ ምክንያት አለበሽተኛው ስምምነት የሚፈጸም ማንኛውም የሕክምና ተግባር በግለሰቡ አካል ላይ በደል እንደ መፈጸም ስለሚቆጠር ነው።”​—⁠“ኢንፎርምድ ኮንሰንት ፎር ብለድ ትራንስፍዩዥን፣” 1989

ጀርመን:- “የበሽተኛው የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት ዕርዳታ ከመስጠትም ሆነ ሕይወት ከማዳን መሠረታዊ ሥርዓት ቅድሚያ ይሰጠዋል። በዚህም ምክንያት አለበሽተኛው ፈቃድ ደም መሰጠት የለበትም።”​—⁠“ኸርዝ ክራይሰላውፍ፣” ነሐሴ 1987

ጃፓን:- “በሕክምና ዓለም ውስጥ ‘ፍጹም’ የሆነ ነገር የለም። ዶክተሮች ከሁሉም የሚሻለው ዘመናዊው ሕክምና እንደሆነ ቢያምኑና ይህንንም አጥብቀው ቢከተሉም እያንዳንዱን የሕክምና ተግባር ‘ፍጹም ትክክል’ እንደሆነ አድርገው በማሰብ በበሽተኞቻቸው ላይ በግድ መፈጸም የለባቸውም። በሽተኞችም የመምረጥ ነጻነት ሊኖራቸው ይገባል።”​—⁠“ሚናሚ ኒሆን ሺምቡን” ሰኔ 28, 1985

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች በጣም የሚቀራረቡና እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ እንደሆኑ ተገንዝቤአለሁ” ሲሉ ዶክተር ሎረንስ ኤስ ፍራንከል ሪፖርት አድርገዋል። “ልጆቻቸው የተማሩ፣ ለሰው አሳቢዎችና አክባሪዎች ናቸው። . . . እንዲያውም የሚሰጣቸውን የሕክምና ትእዛዝ ከማንም የበለጠ ለመፈጸም ይጥራሉ። እንዲህ የሚያደርጉት እምነታቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ማንኛውንም ሕክምና የሚቀበሉ መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ሲሉ ሳይሆን አይቀርም።”​—⁠የሕፃናት ሕክምና ክፍል ኤም ዲ አንደርሰን ሆስፒታልና የቱሞር ተቋም፣ ሂውስተን፣ ዩ ኤስ ኤ፣ 1985

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዶክተር ጄምስ ኤል ፍሊቸር ጁንየር “የሞያ እብሪት በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተውን የሕክምና አመለካከት ማሸነፉ እየተለመደ ሄዷል ብዬ እሰጋለሁ” ብለዋል። “‘ዛሬ ተወዳዳሪ የለውም’ የሚባለው የሕክምና ዘዴ ነገ ማሻሻያ ይደረግለታል ወይም ጨርሶ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ይበልጥ አደገኛ የሆነው የትኛው ነው? ‘ሃይማኖተኛ የሆነ ወላጅ’ ወይስ የሚሰጠው ሕክምና የግድ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምን እብሪተኛ ሐኪም?”​—⁠“ፔዲያትሪክስ” ጥቅምት 1988