በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች የቀዶ ሕክምናና የግብረ ገብ ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች የቀዶ ሕክምናና የግብረ ገብ ጥያቄ

ተጨማሪ ክፍል

የይሖዋ ምሥክሮች የቀዶ ሕክምናና የግብረ ገብ ጥያቄ

በአሜሪካ ሕክምና ማኀበር ፈቃድ ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (JAMA) ከተባለው መጽሔት ተገለበጠ። ኅዳር 27, 1981፣ ጥራዝ 246፣ ቁጥር 21 ገጽ 2471፣ 2472። Copyright 1981, American Medical Association.

ሐኪሞች የይሖዋ ምሥክሮችን በማከም ረገድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። የዚህ እምነት አባሎች የራሳቸውን ወይም የሌላ ሰው ሙሉ ደም፣ የታመቁ ቀይ የደም ሕዋሳት፣ ነጭ የደም ሕዋሳት ወይም ፕሌትሌት መውሰድ የሚከለክል ጠንካራ የሆነ ሃይማኖታዊ እምነት አላቸው። ብዙዎቹ ከአካል ውጭ የሚኖረው የደም ዝውውር የማይቋረጥ ከሆነ (ደም አልባ በሆነ) የሳንባ-ልብ መሣሪያ፣ በዳያሊስስ ወይም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሌላ መሣሪያ ሕክምና እንዲደረግላቸው ይፈቅዳሉ። ምሥክሮች ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የሕክምና ባለሞያዎች በምንም መንገድ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያስችል በቂ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ስለሆኑ የሕክምና ባለሞያዎች ሕጋዊ ተጠያቂነት ይኖርብናል ብለው መስጋት አያስፈልጋቸውም። ለደም ምትክ የሆኑ ፈሳሾችን ይቀበላሉ። ሐኪሞች እነዚህንና ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላባቸውን ሌሎች ዘዴዎች በመጠቀም አዋቂዎችና ልጆች በሆኑ የይሖዋ ምሥክር በሽተኞች ላይ ሁሉንም ዓይነት ከባድ ቀዶ ሕክምና በማካሄድ ላይ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን በሽተኞች ለማከም የሚያስችል አንድ ወጥ የሆነ የሕክምና አሠራር ማዳበር ተችሏል፤ ይህ የሕክምና አሠራር “ሙሉውን ሰው” ስናክም ከምንከተለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው። (JAMA 1981;246:2471-2472)

ሐኪሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ትልቅ የሕክምና ጥያቄ ተደቅኖባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከግማሽ ሚልዮን የሚበልጡ ደም የማይወስዱ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የምሥክሮቹና የተባባሪዎቻቸው ቁጥር በመጨመር ላይ ነው። ከዚህ በፊት ብዙ ሐኪሞችና የሆስፒታል ባለሥልጣኖች ደም ባለመውሰድ ምክንያት የሚፈጠረው አለመግባባት በሕግ መፍትሔ ማግኘት እንደሚኖርበት በማመናቸው አስፈላጊ ነው ብለው ያመኑትን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችላቸውን ሥልጣን ከፍርድ ቤቶች ለማግኘት ይሞክሩ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የአስተሳሰብ ለውጥ መኖሩን በቅርቡ የወጡ የሕክምና ጽሑፎች ያመለክታሉ። ይህ የሆነው በጣም ዝቅተኛ የሄሞግሎቢን መጠን ላላቸው በሽተኞች ቀዶ ሕክምና በማድረግ ረገድ ብዙ ተሞክሮ በመገኘቱና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ስምምነት የማድረግ የሕግ መሠረታዊ ሥርዓት የበለጠ ግንዛቤ በማግኘቱ ሊሆን ይችላል።

በአሁኑ ጊዜ በድንገተኛ አደጋም ሆነ በበሽታ ምክንያት በአዋቂዎችና በሕፃናት ላይ የሚደረጉ በርካታ ቀዶ ሕክምናዎች አለ ደም በመከናወን ላይ ናቸው። በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች ተወካዮች በአገሪቱ በሚገኙ አንዳንድ ትላልቅ የሕክምና ማዕከሎች ከሚሠሩ የሕክምናና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው ነበር። እነዚህ ስብሰባዎች፣ የፈሰሰን ደም መልሶ ስለመጠቀም፣ የአካል ብልቶችን ከአንዱ ወደ ሌላው ስለማዛወርና ሕክምናንና ሕጋዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ የፍርድ ቤት ጭቅጭቆችን ስለማስወገድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከመርዳታቸውም በላይ በሐኪሞችና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የተሻለ መግባባት እንዲኖር አስችለዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ለሕክምና ያላቸው አቋም

የይሖዋ ምሥክሮች ቀዶ ሕክምናም ሆነ በመድኃኒት የሚሰጥ ሕክምና ይቀበላሉ። እንዲያውም ሐኪሞች አልፎ ተርፎም ቀዶ ሐኪሞች የሆኑ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ቢሆንም ምሥክሮቹ ለእምነታቸው በጣም ጥብቅ የሆነ አቋም ያላቸው በመሆናቸው “ነፍሱ፣ ደሙ ያለችበትን ሥጋ ብቻ አትበላም” (ዘፍጥረት 9:​3-4)፣ “ደሙን ታፈሳለህ፣ በአፈርም ትከድነዋለህ” (ዘሌዋውያን 17:​13-14)፣ “ከዝሙትና ከታነቀ፣ ከደምም ራቁ” (ሥራ 15:​19-21) እንደሚሉት ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ደም እንዳይወስዱ እንደሚከለክሉአቸው ያምናሉ።1

እነዚህ ጥቅሶች የተጻፉት ከሕክምና አንፃር ባይሆንም ሙሉ ደም፣ የታመቁ ቀይ የደም ሕዋሳት፣ ፕላዝማ፣ ነጭ የደም ሕዋሳትና ፕሌትሌት መውሰድን የሚከለክሉ ጥቅሶች እንደሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ። ይሁን እንጂ የምሥክሮቹ ሃይማኖታዊ ግንዛቤ እንደ አልቡሚንና ኢምዩን ግሎቡሊን የመሰሉትን ንጥረ ነገሮችና ሂሞፊልያ የተባለ የደም አለመርጋት ችግር ላለባቸው ሰዎች የሚሰጡትን መድኃኒቶች ሙሉ በሙሉ አይከለክልም። እነዚህን መውሰድና አለመውሰድ በእያንዳንዱ ግለሰብ ምሥክር ይወሰናል።2

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰውነት የወጣ ደም መፍሰስ አለበት ብለው ስለሚያምኑ ቀደም ሲል ከሰውነታቸው የተቀዳ ደም ተመልሶ እንዲሰጣቸው አይፈቅዱም። ቀዶ ሕክምና በሚከናወንበት ጊዜ የሚፈሰውን ደም አጠራቅሞ መስጠት በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ይሁን እንጂ ከሰውነት ውጭ የሚከናወነው የደም ዝውውር ያልተቋረጠ ከሆነ ብዙ ምሥክሮች (ደም አልባ በሆነ) በልብ-ሳንባና በዳያሊስስ መሣሪያ የሚሰጠውን ሕክምና እንዲሁም በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚፈሰው ደም እንዲመለስ የሚያስችለውን ዘዴ ይቀበላሉ። የግለሰቡ ሕሊና በዚህ ረገድ ምን እንደሚፈቅድለትና እንደማይፈቅድለት ለማወቅ ሐኪሙ በሽተኛውን ማነጋገር ይኖርበታል።2

ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስ የአካል ብልቶችን ከአንዱ ወደ ሌላው ስለማዛወር በቀጥታ ይናገራል የሚል እምነት የላቸውም። በዚህም ምክንያት ኮርኒያ፣ ኩላሊት ወይም ሌላ የአካል ክፍል ማዛወርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚወስነው ምሥክሩ ራሱ ነው።

ከባድ ኦፕራስዮን ማድረግ ይቻላል

ብዙ ቀዶ ሐኪሞች የደም ተዋጽኦዎችን በመጠ​ቀም ረገድ ምሥክሮቹ ያላቸው አቋም “ዶክተሩን እጀ ሰባራ ያደርገዋል” ብለው በመገመት እነርሱን ለማከም እምቢተኛ ሆነው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ችሎታቸውን የሚፈታተን ከመሆኑ ሌላ እምብዛም ለውጥ የማያመጣ እንደሆነ አድርገው በመመልከት ለማከም የመረጡ ዶክተሮች በርካታ ናቸው። ምሥክሮቹ የደም አማራጭ የሆኑ ኮሎይድ ወይም ክሪስታሎይድ ፈሳሾች ቢሰጧቸው አይቃወሙም፤ በተጨማሪም ኤሌክትሮኮውተሪ፣ ሃይፖቴንሲቭ አኔስቴዥያ3 ወይም ሃይፖቴርሚያ እንዲደረግላቸው ፈቃደኞች ስለሆኑ በእነዚህ ዘዴዎች በመጠቀም የተሳካ ውጤት ለማግኘት ተችሏል። ሄታስታርች በመስጠት፣4 በዛ ያለ መጠን ያለው አይረን ዴክስትራን በደም ሥር በመውጋትና5,6 በ“ሶኒክ መቁረጫ መሣሪያዎች”7 በመጠቀም ረገድ በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉና ወደፊት ሥራ ላይ የሚውሉ ዘዴዎች ተስፋ ሰጪ ከመሆናቸውም በላይ ከሃይማኖታዊ አቋም አንፃርም ተቀባይነት አላቸው። በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቅም ላይ የዋለው ፍሎሪን የተቀላቀለበት ለደም ምትክ ሆኖ የሚያገለግለው ፈሳሽ (Fluosol-DA) አስተማማኝና ውጤታማ8 ሆኖ ከተገኘ ለበሽተኛው ቢሰጥ ከምሥክሮቹ እምነት ጋር አይጋጭም።

በ1977 ኦትና ኩሊ9 ደም ሳይሰጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለተደረጉ 542 የሚያክሉ የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ይህ ሕክምና “አለብዙ ሥጋት” ሊከናወን እንደሚችል ገልጸዋል። በቅርቡ ኩሊ ከእኛ በቀረበላቸው ጥያቄ በመነሳት 1,026 በሚያክሉ ቀዶ ሕክምናዎች ላይ ስታቲስቲካዊ ጥናት አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት የተደረጉት በትናንሽ ልጆች ላይ ነበር። ባካሄዱት ጥናት ላይ በመመርኮዝ “የይሖዋ ምሥክሮች በሆኑ በሽተኞች ላይ የተደረጉት ቀዶ ሕክምናዎች በሌሎች በሽተኞች ላይ ከደረሰው የበለጠ አደጋ አላስከተሉባቸውም” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። በተመሳሳይም የሕክምና ዶክተር የሆኑት ማይክል ኢ ደባኪ፣ “በአብዛኞቹ ሁኔታዎች [በይሖዋ ምሥክሮች ላይ] ደም ሳይሰጥ በተካሄዱት ቀዶ ሕክምናዎች የተከሰቱት አደጋዎች ደም ከምንሰጣቸው በሽተኞች የበዛ አይደለም” ብለዋል። (በግል የሰጡት ቃል፣ መጋቢት 1981) በተጨማሪም ጽሑፉ ከባድ የሆኑ፣ የሽንት ቧንቧ አካላትንና10 የአጥንት ቀዶ ሕክምናዎች11 አለ ደም ተደርገው የተሳካ ውጤት እንደተገኘ ይገልጻል። የሕክምና ዶክተሮች የሆኑት ጂ ዲን ማክዊን፣ እና ጄ ሪቻርድ ቦወን፣ የአከርካሪ አጥንቶችን ለማስተካከል ‘20 በሚያክሉ [የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ልጆች] ላይ ቀዶ ሕክምና ተደርጎ የተሳካ ውጤት እንደተገኘ’ ጽፈዋል። (ያልታተመ መረጃ፣ ነሐሴ 1981) በተጨማሪም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንድ ቀዶ ሐኪም በሽተኛው ደም አልወስድም የማለት መብት እንዳለውና በበሽተኛው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ሊቀንሱ በሚችሉ የቀዶ ሕክምና ዘዴዎች ተጠቅሞ ተገቢውን እርዳታ መስጠት እንደሚኖርበት ማመን ይገባዋል።”

ኸርብስማን12 “በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት ብዙ ደም በፈሰሳቸው” በሽተኞች ላይ ቀዶ ሕክምና ተደርጎ የተሳካ ውጤት እንደተገኘ ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል ወጣቶችም ይገኛሉ። “ምሥክሮቹ ደም አለመውሰዳቸው የሚያስከትለው መጠነኛ ችግር ቢኖርም ደምን የሚተኩ አማራጮች እንዳሉን ግልጽ ነው” ብለዋል። ብዙ ቀዶ ሐኪሞች “ሕጋዊ ተጠያቂነት ይኖርብናል” ብለው በመስጋት ምሥክሮች የሆኑ በሽተኞችን ለመቀበል እንደሚያመነቱ በመመልከታቸው በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ሕግ ነክ ሥጋትና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች

ምሥክሮቹ የአሜሪካ ሕክምና ማኅበር ያዘጋጀውን ሐኪሞችንና ሆስፒታሎችን ከሕግ ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ቅጽ13 አለምንም ማመንታት ይሞላሉ። በተጨማሪም አብዛኞቹ ምሥክሮች ከሕክምናና ከሕግ ባለሥል​ጣኖች ጋር ምክክር በማድረግ የተዘጋጀውን ቀን የተ​ጻፈበትና ምሥክሮች የፈረሙበት የሕክምና ማስጠንቀቂያ ካርድ ይይዛሉ። እነዚህ ሰነዶች ከበሽተኛውም (ሆነ ከውርስ) ጋር ለተያያዙ ሕግ ነክ ጉዳዮች የሚጠቅሙ ናቸው። ከዚህም በላይ ዋረን በርገር የተባሉት ዳኛ እንዳሉት ይህን የመሰለ ከኃላፊነት ነጻ የሚያደርግ ሰነድ እያለ ሐኪሙ ተገቢውን ሕክምና አላደረገም የሚል ክስ ቢቀርብ “የሕግ ድጋፍ የማያገኝ” በመሆኑ ሐኪሞቹም ከተጠያቂነት ነጻ ይሆናሉ። በተጨማሪም ፓሪስ14 “በግዳጅ ስለሚሰጥ ሕክምናና የሃይማኖት ነጻነት” ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “ጽሑፎችን አገላብጦ የተመለከተ አንድ ተንታኝ ‘ሐኪሙ ፈቃደኛ ያልሆነውን በሽተኛ አስገድዶ ደም ባለመስጠቱ . . . በወንጀል . . . ይጠየቃል የሚለውን አባባል የሚደግፍ አንድም ምክንያት አላገኘሁም’ ብሏል። ይህ ዓይነቱ ስጋት ሐሳብ ወለድ እንጂ ሊያጋጥም የሚችለውን ሁኔታ ከማገናዘብ የሚመነጭ አይደለም።”

ከሁሉ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ የተገኘው የትናንሽ ሕፃናት ጉዳይ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉም በሚል ወንጀል ተከስሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይሁን እንጂ የምሥክሮችን ሁኔታ በሚገባ የሚያውቁና ምሥክር የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ የሚፈልጉ መሆናቸውን የሚያምኑ ብዙ ሐኪሞችና የሕግ ጠበቆች እንዲህ ያለውን ክስ አያምኑበትም። ምሥክሮቹ የቤተሰባቸው ሃይማኖታዊ እምነት እንዲከበርላቸው የሚጠይቁት የወላጅነት ኃላፊነታቸውን ገሸሽ ለማድረግ ወይም በዳኛ ላይ ወይም በሌላ ሦስተኛ ወገን ላይ ለመጣል ፈልገው አይደለም። የካናዳ ሕክምና ማህበር ጸሐፊ የነበሩት ዶክተር ኤ ዲ ኬሊ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:-15 “የትናንሽ ልጆች ወላጆችና ራሳቸውን የሳቱ በሽተኞች የቅርብ ዘመዶች የበሽተኛውን ፍላጎት የማስረዳት መብት አላቸው። . . . ስሜት አልባ የሆነ ፍርድ ቤት ከሌሊቱ በ8:​00 ሰዓት ተሰብስቦ አንድን ሕፃን ከወላጆቹ ሞግዚትነት ነጥሎ መውሰዱን አልደግፈውም።”

ወላጆች አንድ ቀዶ ሕክምና፣ የጨረር ወይም የመድኃኒት ሕክምና ሊያስከትለው የሚችለው ጥቅምና ጉዳት በሚገናዘብበት ጊዜም ሆነ ይህን በመሳሰሉት ሁኔታዎች ለልጆቻቸው የሚሰጠውን ሕክምና የመወሰን መብት እንዳላቸው የተረጋገጠ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች በሃይማኖታቸው የተከለከለ ሕክምና ለልጆቻቸው እንዳይሰጥ የሚጠይቁት ደም መውሰድ ሊያስከትለው ከሚችለው አደጋ16 ይበልጥ የሚያሳስባቸው የሥነ ምግባር አቋም ስላላቸው ነው። ይህ ጥያቄአቸው “መሉውን ሰው” ስናክም ከምንከተለው የሕክምና መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። የአንድን ቤተሰብ መሠረታዊ እምነቶች የሚጻረር ሕክምና በቤተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ዘላቂ የሆነ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቁስል ችላ ማለት አይቻልም። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የሚገኙ ትላልቅ የሕክምና ማዕከሎች የይሖዋ ምሥክሮችን በማከም በቂ ልምድ ስላገኙ ምሥክሮችን ለማከም ፈቃደኛ ካልሆኑ ተቋሞች የሚላኩላቸውን በሽተኞች፣ ትናንሽ ሕፃናትን ጭምር ይቀበላሉ።

ሐኪሙ የሚያጋጥመው ተፈታታኝ ሁኔታ

በእጁ የሚገኙትን የሕክምና ዘዴዎች በሙሉ ተጠቅሞ የበሽተኛውን ሕይወትና ጤና የማዳን ቀንበር የተሸከመው ሐኪም ለይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ እንዲያደርግ ሲጠየቅ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ሊፈጠርበት ቢችል የሚያስደንቅ ነገር አይሆንም። ሐርቬ17 በምሥክሮች ላይ ስለተካሄዱ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎች መቅድም ላይ በተጻፉ ተከታታይ ጽሑፎች አስተያየት ሲሰጡ “በሥራዬ ላይ ጣልቃ የሚገቡ እምነቶች ያናድዱኛል” ብለዋል። ይሁን እንጂ “እኛም ብንሆን ቀዶ ሕክምና በግለሰቦች የቴክኒክ ችሎታ ላይ የተመካ ዕደ ጥበብ መሆኑን በቀላሉ እንዘነጋለን። ማንኛውም ቴክኒክ ሊሻሻል ይችላል” በማለት አክለዋል።

ፕሮፌሰር ቦሉኪ18 በዴድ ካውንቲ ፍሎሪዳ የሚገኝ በድንገተኛ አደጋ የተጎዱ በርካታ በሽተኞችን የሚያስተናግድ ሆስፒታል የይሖዋ ምሥክሮችን “በጅምላ አላክምም የሚል” መርሕ እንዳለው የሚገልጽ አሳዛኝ ሪፖርት እንደደረሳቸው ገልጸዋል። “በእነዚህ በሽተኞች ላይ የሚደረጉ አብዛኞቹ ቀዶ ሕክምናዎች ከተለመደው ያነሰ አደጋ የሚከሰትባቸው” እንደሆኑ ገልጸዋል። በተጨማሪም “ቀዶ ሐኪሞቹ ዘመናዊ ሕክምና ያስገኘው አንድ መሣሪያ እንደተነፈጋቸው ሊሰማቸው ቢችልም . . . እነዚህን በሽተኞች ኦፕራስዮን በማድረግ ብዙ እውቀት ሊያገኙ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።

ምሥክር የሆኑ በሽተኞችን እንደ ችግር ከመመልከት ይልቅ እነርሱን ማከም የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። ይህንንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት ሲሉ እነዚህን በሽተኞች ለማከም የሚያስችል በመላ አገሪቱ በሚገኙ በርካታ የሕክምና ማዕከሎች ተቀባይነት ያገኘ የሕክምና አሠራር ለማዳበር ችለዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ለበሽተኛው ሁለንተናዊ ደህንነት የሚበጅ የሕክምና እንክብካቤ መስጠታቸው ነው። ጋርድነርና ባልደረቦቻቸው19 እንዳሉት ነው:- “የበሽተኛው አካላዊ ሕመም ድኖ በእርሱ እምነት መሠረት በአምላክ ዘንድ ያለው መንፈሳዊ ሕይወቱ ቢበላሽበትና ምናልባትም ከሞት የሚከፋ ትርጉም የሌለው ሕይወት ቢመራ ማን ይጠቀማል?”

ምሥክሮቹ አጥብቀው የሚከተሉት እምነታቸው በሕክምና ረገድ መጠነኛ የሆነ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችልና የሚሰጣቸውን የሕክምና እርዳታ እንደሚያወሳስብባቸው ይገነዘባሉ። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ለተሰጣቸው እንክብካቤ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ይናገራሉ። ጽኑ መሠረት ያለው እምነትና ጠንካራ የሆነ የመኖር ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ ከሐኪሞችና ከሕክምና ሠራተኞች ጋር ለመተባበር ዝግጁዎች ናቸው። በዚህ መንገድ ይህን በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት በሽተኛውም ሆነ ሐኪሙ አንድ ሆነው ይታገላሉ።

የማመሳከሪያ ጽሑፎች

1. Jehovah’s Witnesses and the Question of Blood. Brooklyn, NY, Watchtower Bible and Tract Society, 1977, pp. 1-64.

2. The Watchtower 1978;99 (June 15):​29-31.

3. Hypotensive anesthesia facilitates hip surgery, MEDICAL NEWS. JAMA 1978;239:⁠181.

4. Hetastarch (Hespan)​—⁠a new plasma expander. Med Lett Drugs Ther 1981;23:⁠16.

5. Hamstra RD, Block MH, Schocket AL:Intravenous iron dextran in clinical medicine. JAMA 1980;243:1726-1731.

6. Lapin R: Major surgery in Jehovah’s Witnesses. Contemp Orthop 1980;2:647-654.

7. Fuerst ML: ‘Sonic scalpel’ spares vessels. Med Trib 1981;22:1,30.

8. Gonzáles ER: The saga of ‘artificial blood’: Fluosol a special boon to Jehovah’s Witnesses. JAMA 1980;243:​719-724.

9. Ott DA, Cooley DA: Cardiovascular surgery in Jehovah’s Witnesses. JAMA 1977;238:1256-1258.

10. Roen PR, Velcek F: Extensive urologic surgery without blood transfusion. NY State J Med 1972;72:2524-2527.

11. Nelson CL, Martin K, Lawson N, et al: Total hip replacement without transfusion. Contemp Orthop 1980;2:​655-658.

12. Herbsman H: Treating the Jehovah’s Witness. Emerg Med 1980;12:​73-76.

13. Medicolegal Forms With Legal Analysis. Chicago, American Medical Association, 1976, p. 83.

14. Paris JJ: Compulsory medical treatment and religious freedom: Whose law shall prevail? Univ San Francisco Law Rev 1975;10:1-35.

15. Kelly AD: Aequanimitas Can Med Assoc J 1967;96:432.

16. Kolins J: Fatalities from blood transfusion. JAMA 1981;245:1120.

17. Harvey JP: A question of craftsmanship. Contemp Orthop 1980;2:629.

18. Bolooki H: Treatment of Jehovah’s Witnesses: Example of good care. Miami Med 1981;51:​25-26.

19. Gardner B, Bivona J, Alfonso A, et al: Major surgery in Jehovah’s Witnesses. NY State J Med 1976;76:​765-766.