በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደምን በደም ሥር መውሰድ—ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ደምን በደም ሥር መውሰድ—ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ደምን በደም ሥር መውሰድ​—⁠ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ማንኛውም አስተዋይ የሆነ ሰው ከበድ ያለ ሕክምና ለመውሰድ ራሱን ከማዘጋጀቱ በፊት ሕክምናው ስለሚያስገኝለት ጥቅምና አደጋ ለማወቅ ይፈልጋል። ደም ስለ መውሰድስ? በአሁኑ ጊዜ ደምን በደም ሥር መስጠት ዋነኛ የሕክምና መሣሪያ ሆኗል። ስለ በሽተኞቻቸው ደህንነት ከልባቸው የሚያስቡ በርካታ ሐኪሞች አላንዳች ማመንታት ደም ይሰጣሉ። እንዲያውም ደም መስጠት ሕይወት መስጠት ነው ተብሏል።

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደም ሰጥተዋል ወይም ወስደዋል። በካናዳ ከ1986-87 ባለው አንድ ዓመት 25 ሚልዮን ከሚያክሉት የአገሪቱ ነዋሪዎች መካከል 1.3 ሚልዮን የሚያክሉት ደም ለግሰዋል። “በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በጣም ቅርብ በሆነው ዓመት ከ12 ሚልዮን እስከ 14 ሚልዮን ዩኒት የሚደርስ ደም ለበሽተኞች በደም ሥር ተሰጥቷል።”​—⁠ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ የካቲት 18, 1990

ዶክተር ሉዊስ ጄ ኪቲንግ “ደም በሁሉም ዘመናት ‘ምትሐታዊ’ ኃይል እንዳለው ሲታመን ቆይቷል” ብለዋል። “በመጀመሪያዎቹ 46 ዓመታት የደም አቅርቦታችን ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንደሆነ በሐኪሞችም ሆነ በተራው ሕዝብ አለአግባብ ታምኖ ነበር።” (ክሌቭላንድ ክሊኒክ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን፣ ግንቦት 1989) በዚያ ጊዜ የነበረው ሁኔታ እንዴት ያለ ነው? ዛሬስ ምን ደረጃ ደርሷል?

ከ30 ዓመታት በፊት እንኳን ፓቶሎጂስቶችና የደም ባንክ ባለሞያዎች እንደሚከተለው ያለ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር:- “ደም ሳይጠበቅ የሚፈነዳ ድማሚት ነው! በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ወይም በጣም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ደም በመውሰድ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የኢተር ማደንዘዣ በመውሰድ ወይም በትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አያንስም። ደም ከሚሰጣቸው ከ1,000 እስከ 3,000፣ ምናልባትም 5,000 ከሚደርሱ ሰዎች መካከል በግምት አንዱ ይሞታል። በለንደን አካባቢ ለበሽተኞች ከሚሰጡ 13,000 የደም ማስቀመጫ ከረጢቶች መካከል አንዱን የወሰደው እንደሚሞት ተዘግቧል።”​—⁠ኒው ዮርክ ስቴት ጆርናል ኦቭ ሜዲስን፣ ጥር 15, 1960

ዛሬስ እነዚህ አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ተወግደው ደም መውሰድ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ሆኗልን? እውነቱን ለመናገር በወሰዱት ደም ምክንያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ የጤንነት ቀውስ የሚደርስባቸው ሲሆን ብዙዎችም በዚሁ ሳቢያ ይሞታሉ። እንዲህ ሲባል ወዲያው ወደ አእምሮህ የሚመጣው በደም አስተላላፊነት የሚዛመቱ በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ረገድ የሚያጋጥመውን ችግር ከመመርመራችን በፊት ደም በመውሰድ ምክንያት የሚመጡትን በብዙዎች ዘንድ የማይታወቁ አደጋዎች እንመልከት።

ደምና በሽታ የመከላከል ችሎታህ

የሳይንስ ሊቃውንት በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ባደረጉት ምርምር ምክንያት የሰው ልጅ፣ በጣም ውስብስብ ስለሆነው አስደናቂ ፈሳሽ ስለ ደም ያለውን ግንዛቤ ሊያሰፋ ችሏል። የሳይንስ ሊቃውንት የተለያዩ የደም ዓይነቶች መኖራቸውን ተገንዝበዋል። የደም ለጋሹ ደምና የበሽተኛው ደም አንድ ዓይነት መሆኑ በጣም ወሳኝ ነው። ኤ ዓይነት ደም ያለው ሰው ቢ ዓይነት ደም ቢወስድ ከባድ የሆነ የደም ቀውስ ሊያጋጥመው ይችላል። አብዛኞቹ ቀይ የደም ሕዋሶች ሊሞቱና በዚህም ምክንያት ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል። በዛሬው ጊዜ ደምን በዓይነት በዓይነት መለየትና ማመሳሰል ቀላልና በጣም የተለመደ ቢሆንም ስህተቶች መፈጠራቸው አልቀረም። የደም ዓይነቶች አለመመሳሰል በሚያስከትለው ቀውስ የተነሳ በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ይሞታሉ።

የደም ዓይነቶች ያለመመሳሰል ችግር ሆስፒታሎች እንዲመሳሰሉ በሚፈልጓቸው ጥቂት የደም ዓይነቶች የሚወሰን እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ዶክተር ዳግለስ ኤች ፖሲ ጁንየር “ደም በደም ሥር መስጠት:- ጥቅሙ፣ አግባብ ያልሆነ አጠቃቀሙና ጉዳቱ” በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “30 ዓመት ከሚያክል ጊዜ በፊት ሳምሰን ደምን በደም መስጠት መጠነኛ አደጋ የሚያስከትል ሕክምና እንደሆነ ገልጸው ነበር። . . . [ከዚያ ወዲህ ግን] ቢያንስ 400 የሚያክሉ የቀይ ሕዋስ ደም እንግዳ አካሎች (አንቲጅንስ) ተገኝተው ባሕርያቸው ተጠንቷል። የቀይ ሕዋስ ደም ሕዋስ ሽፋን እጅግ የተወሳሰበ በመሆኑ ይህ ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ አይጠረጠርም።”​—⁠ጆርናል ኦቭ ዘ ናሽናል ሜዲካል አሶሲዬሽን፣ ሐምሌ 1989

በአሁኑ ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት በደም ሥር የተሰጠ የሌላ ሰው ደም በሰውነት የበሽታ መከላከል ችሎታ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በማጥናት ላይ ናቸው። የምርምራቸው ውጤት ለአንተ ወይም ቀዶ ሕክምና ለሚያስፈልገው ዘመድህ ምን ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ሐኪሞች የሌላ ሰው ልብ፣ ጉበት ወይም ሌላ ብልት በተለዋጭነት ሲያስገቡ የተቀያሪው ብልት ተቀባይ የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ባዕድ አካል መሆኑን አውቀው ይቃወሙታል። በደም ሥር የሚሰጥ ደም ደግሞ ባዕድ ህብረሕዋስ ነው። “አንድ ዓይነት ነው” የተባለ ደም እንኳን የበሽታ መከላከል አቅምን ሊያዳክም ይችላል። በአንድ የፓቶሎጂስቶች ስብሰባ ላይ “ደም መውሰድ በበሽታ መከላከል አቅም ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር” የሚገልጹ በመቶ የሚቆጠሩ የጥናት ጽሑፎች ቀርበዋል።​—“ደም መውሰድ ጉዳት እንዳለው የሚገልጹ መረጃዎች ተበራክተዋል” ሜዲካል ወርልድ ኒውስ፣ ታኅሣሥ 11, 1989

በሽታ ተከላካይ ሕዋሶችህ ከሚያከናውኗቸው ዋነኛ ተግባራት አንዱ ቂመኛ የካንሰር ሕዋሶችን ተከታትሎ ማጥፋት ነው። ታዲያ የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም ካንሰርና ሞት ሊያስከትል ይችላልን? እነዚህን ሁለት ሪፖርቶች ልብ በል።

ካንሰር የተባለው መጽሔት (የካቲት 15, 1987) በኔዘርላንድ በተደረገ አንድ ጥናት የተገኘውን ውጤት ገልጿል:- “የደንዳኔ ካንሰር በያዛቸው በሽተኞች ረገድ ደም መውሰድ በዕድሜያቸው ርዝመት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ታይቷል። ጥናቱ ከተደረገባቸው በሽተኞች መካከል ለ5 ዓመት ሊኖሩ የቻሉት ደም ከወሰዱት መካከል 48% የሚሆኑት ሲሆኑ ደም ካልወሰዱት መካከል ግን 74% የሚሆኑት ናቸው።” በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ሐኪሞች የካንሰር ቀዶ ሕክምና በተደረገላቸው አንድ መቶ የሚያክሉ በሽተኞች ላይ ክትትል አድርገው ነበር። “የማንቁርት ካንሰር ይዟቸው ከነበሩ በሽተኞች ደም ካልወሰዱት መካከል 14% በሚሆኑት ላይ በሽታው ሲያገረሽባቸው ደም ከወሰዱት መካከል ግን 65% በሚሆኑት ላይ አገርሽቶባቸዋል። በአፍ፣ በሰርንና በአፍንጫ ወይም በሳይነስ ካንሰር ረገድ ደግሞ ደም ካልወሰዱት መካከል በሽታው ያገረሸባቸው 31% ሲሆኑ ደም ከወሰዱት መካከል ግን 71% የሚሆኑት አገርሽቶባቸዋል።”​—⁠አናልስ ኦቭ ኦቶሎጂ፣ ራይኖሎጂ ኤንድ ላሪንጎሎጂ፣ መጋቢት 1989

ታዲያ እነዚህ ጥናቶች ደም ስለ መውሰድ ምን የሚሰጡት ሐሳብ አለ? ዶክተር ጆን ኤስ ስፕራት “ደም በደም ሥር መስጠትና የካንሰር ቀዶ ሕክምና” በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ላይ “የካንሰር ቀዶ ሐኪም አለ ደም የሚያክም መሆን ሳያስፈልገው አይቀርም” ሲሉ ደምድመዋል።​—⁠ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ መስከረም 1986

የሰውነትህ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ሌላው ዋነኛ ተግባር ኢንፌክሽን መከላከል ነው። ስለዚህ ደም የተሰጣቸው በሽተኞች በኢንፌክሽን የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች መጠቆማቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ዶክተር ፒ አይ ታርተር በደንዳኔ በፊንጢጣ ላይ በተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ላይ ጥናት አድርገው ነበር። ደም ከተሰጣቸው በሽተኞች መካከል ኢንፌክሽን የያዛቸው 25 በመቶ ሲሆኑ ደም ካልተሰጣቸው መካከል ግን ኢንፌክሽን የያዛቸው 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል:- “ከቀዶ ሕክምና በፊት፣ ወይም በኋላ ወይም በቀዶ ሕክምናው ወቅት ደም በደም ሥር መስጠት በኢንፌክሽን ምክንያት ለሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ሆኗል። . . . በሽተኞቹ የወሰዱት ደም መጠን በጨመረ መጠን ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በኢንፌክሽን የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።” (ዘ ብሪትሽ ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ፣ ነሐሴ 1988) በ1989 በተደረገ የአሜሪካ የደም ባንኮች ማኅበር ስብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉ የሚከተለውን ተረድተዋል:- የዳሌ አጥንት ቀዶ ሕክምና በተደረገላቸው ወቅት የለጋሾች ደም ከወሰዱ በሽተኞች መካከል 23 በመቶ የሚሆኑት በኢንፌክሽን ሲያዙ ደም ካልተሰጣቸው በሽተኞች መካከል ግን አንዳቸውም በኢንፌክሽን አልተያዙም።

ዶክተር ጆን ኤ ኮሊንስ ደም መውሰድ የሚያስከትለውን ይህን ጠንቅ አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ምን ዓይነት ፋይዳ እንዳለው ማረጋገጫ ሊገኝለት ያልቻለ ‘ሕክምና’ እንዲህ ዓይነቶቹ በሽተኞች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዋነኛ የሆነውን ችግር የሚያባብስ ሆኖ መገኘቱ በጣም የሚያስደንቅ ነው።”​—⁠ወርልድ ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ፣ የካቲት 1987

ከበሽታ ነጻ የሆነ ወይስ በሽታ የታጨቀበት?

በደም የሚተላለፉ በሽታዎች አሳቢ የሆኑ በርካታ ሐኪሞችንና በሽተኞችን የሚያሳስቡ ሆነዋል። አነዚህ በሽታዎች ምንድን ናቸው? በግልጽ ለመናገር በጣም በርካታ ናቸው።

ቴክኒክስ ኦቭ ብለድ ትራንስፍዩዥን (1982) የተባለው መጽሐፍ በይበልጥ ስለታወቁት በሽታዎች ከገለጸ በኋላ እንደ ቂጥኝ፣ ወባና ሳይቶሜጋሎቫይረስ ኢንፌክሽን ያሉትን “ደም ከመውሰድ ጋር የተዛመዱ ሌሎች የኢንፌክሽን በሽታዎች” ይዘረዝራል። ከዚያም እንደሚከተለው ይላል:- “ሌሎች በርካታ የሆኑ በሽታዎችም ደም በመውሰድ እንደሚተላለፉ ሪፖርት ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል የሄርፐስ ቫይረስ ኢንፌክሽን፣ ኢንፌክሽየስ ሞኖኒውክልዮሲስ (ኤፕስታይን-ባር ቫይረስ)፣ ቶክሶፕላዝሞሲስ፣ ትሪፓኖሶሚያሲስ [የአፍሪካ የእንቅልፍ በሽታና የቻጋስ በሽታ]፣ ሊሽማኒያሲስ፣ ብሩሴሎሲስ [አንዱላንት ፊቨር]፣ ተስቦ፣ ፊላርያሲስ፣ ኩፍኝ፣ ሳልሞኔሎሲስና ኮሎራዶ ቲክ ፊቨር የተባሉት በሽታዎች ይገኛሉ።”

የእነዚህ በሽታዎች ዝርዝር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዷል። “የላይም በሽታ በደም ይተላለፋልን? የማይተላለፍ ቢመስልም ሊቃውንቱ በጥርጣሬ ዓይን እያዩት ነው” እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን በጋዜጣ ርዕሶች ሳታነብ አትቀርም። የላይም በሽታ እንዳለው ከታወቀ ሰው የተወሰደ ደም ምን ያህል አስተማማኝ ሊሆን ይችላል? አንድ የጤና ባለሞያዎች ቡድን እንዲህ ያለውን ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። “ሁሉም ባለሞያዎች አንወስድም ቢሉም እንደነዚህ ካሉት ሰዎች የተወሰዱ ደሞች ይጣሉ የሚለውን ሐሳብ አንዳቸውም አልደገፉም።” ታዲያ ሊቃውንቱ ራሳቸው አንወስድም ስላሉት በደም ባንኮች ውስጥ ስለሚገኝ ደም ተራው ሕዝብ እንዴት ሊሰማው ይገባል?​—⁠ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ሐምሌ 18, 1989

ሌላው አሳሳቢ ምክንያት ደግሞ አንድ ዓይነት በሽታ በጣም ተስፋፍቶ በሚገኝበት አገር የተወሰደ ደም ዶክተሮችም ሆኑ በሽተኞች ስለ በሽታው በማያውቁባቸው ሩቅ አገሮች ጥቅም ላይ ሊውል መቻሉ ነው። ሰዎች ከአገር ወደ አገር በብዛት በሚዘዋወሩበትና ስደተኞች በበዙበት በዚህ ዘመን በደም ተዋጽኦዎች ውስጥ ገና ያልታወቀ በሽታ ይኖር ይሆናል የሚለው ሥጋት እየጨመረ ሄዷል።

ከዚህም በላይ አንድ የተዛማች በሽታዎች ስፔሽያሊስት እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቀዋል። “ከዚህ በፊት ተላላፊ ናቸው ተብለው የማይታሰቡት እንደ ሉኪሚያ፣ ሊምፎማና ዲሜንሽያ [ወይም የአልዛይመር በሽታ] የመሳሰሉት በሽታዎችም ከአንዱ ወደ ሌላው እንዳይተላለፉ በደም ባንኮች ውስጥ የሚገኘውን ደም በሚገባ መርምሮ ማጣራት ያስፈልጋል።”​—ትራንስፍዩዥን ሜዲስን ሪቪውስ፣ ጥር 1989

እነዚህ አስጊ ሁኔታዎች ራሳቸው በጣም የሚያስፈሩ ቢሆኑም ከእነዚህ ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች በሽታዎች አሉ።

የኤድስ ወረርሽኝ

“ዶክተሮችም ሆኑ በሽተኞች ስለ ደም ያላቸው አመለካከት በኤድስ ምክንያት ለአንዴና ለሁልጊዜ ተለውጧል። ስለ ደም አሰጣጥ በብሔራዊ የጤና ተቋሞች ጉባኤ ላይ የተገኙ ዶክተሮች እንዲህ መሆኑ መጥፎ ነገር አይደለም ብለዋል።”​—⁠ዋሽንግተን ፖስት፣ ሐምሌ 5, 1988

በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለው የኤድስ ወረርሽኝ ሰዎች በደም አማካኝነት በሚተላለፉ በሽታዎች የመለከፍ አደጋ እንዳለ ተገንዝበው እንዲጠነቀቁ አስገድዷል። በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ ተለክፈዋል። ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ በመዛመት ላይ ነው። በበሽታው ከተለከፉት መካከል ከሞት የሚያመልጥ አንድም ሰው አይኖርም።

ለኤድስ ምክንያት የሚሆነው ኤች አይ ቪ የተባለው የሰውነትን የበሽታ መከላከያ የሚያሟጥጥ ቫይረስ ነው። ይህ ቫይረስ ደግሞ በደም አማካኝነት ከአንዱ ሰው ወደ ሌላ ሊተላለፍ ይችላል። ዘመን አመጣሹ የኤድስ ወረርሽኝ መኖሩ የታወቀው በ1981 ነበር። በቀጣዩ ዓመት የጤና ባለሞያዎች ቫይረሱ በደም ተዋጽኦዎች አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችል አወቁ። የኤች አይ ቪ ፀረ እንግዳ አካሎች (አንቲቦዲስ) የሚገኙበትን ደም ለመለየት የሚያስችል የምርመራ ዘዴ በተገኘበት ወቅትም እንኳን የደም ኢንዱስትሪ እርምጃ ለመውሰድ በጣም ዳተኛ ሆኖ እንደነበረ የታመነ ነው። የለጋሾችን ደም መመርመር የተጀመረው በ1985 * ቢሆንም ቀደም ሲል የተከማቹ የደም ተዋጽኦዎች በዚህ ጊዜ እንኳን አልተመረመሩም።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ‘በደም ባንኮች የሚገኘው ደም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነው’ የሚል ማረጋገጫ ተሰጠ። ይሁን እንጂ ኤድስ ሳይታወቅ የሚቆይበት ‘የተወሰነ ጊዜ’ እንዳለ ቆየት ብሎ ታወቀ። አንድ ሰው በኤድስ ከተለከፈ በኋላ በምርመራ ሊታወቁ የሚችሉ ፀረ እንግዳ አካሎች በሰውነቱ ውስጥ መገኘት የሚጀምሩት በወራት ከሚቆጠር ጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል። ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ እንዳለ ሳያውቅ በምርመራ ንጹሕ ሆኖ የሚታይ ደም ሊለግስ ይችላል። ይህ የደረሰ ነገር ነው። እንዲህ ያለ ደም ከተሰጣቸው በኋላ ኤድስ የያዛቸው ሰዎች አሉ!

እንዲያውም ሁኔታው ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን (ሰኔ 1, 1989) “ድምፁን አጥፍቶ የሚቆይ የኤች አይ ቪ ኢንፌክሽን” እንዳለ ሪፖርት አድርጓል። አንዳንድ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ በመለከፋቸው በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ በዋሉት ቀጥተኛ ያልሆኑ የምርመራ ዘዴዎች ሳይታወቅ የኤድስ ቫይረስ ተሸካሚዎች ሆነው ለብዙ ዓመታት ሊኖሩ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። ይህ አልፎ አልፎ ብቻ የሚያጋጥም ነገር ነው በማለት የዚህን አደገኛነት ሊያቃልሉ የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩም “በደምና በደም ተዋጽኦዎች አማካኝነት ኤድስ እንዳይተላለፍ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የማይቻል መሆኑን” ያረጋግጣሉ። (ፔሸንት ኬር፣ ኅዳር 30, 1989) የምርመራ ውጤት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ መሆንን ሊያረጋግጥ የሚችል አለመሆኑ በእርግጥ በጣም የሚያሳስብ ችግር ነው። ከአሁን በኋላ በደም ምክንያት በኤድስ የሚለከፉ ሰዎች ምን ያህል ይሆኑ ይሆን?

ቀጣዩ ኮቴ? ወይስ ኮቴዎች?

በአፓርታማ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከበላያቸው የሚኖረው ሰው ከበታቹ ያለውን ወለል በኃይል ሲረግጥ የሚያሰማውን የመጀመሪያ ድምፅ ከሰሙ በኋላ ጆሯቸውን ተክለው ቀጣዩን ድምፅ መጠበቅ ይጀምራሉ። ደም በመውሰድ ምክንያት በሚመጡ ችግሮች ረገድም ስንት ከባድ የኮቴ ድምፅ እንደሚሰማ በቅድሚያ ሊያውቅ የሚችል ሰው የለም።

ኤድስን የሚያመጣው ቫይረስ ኤች አይ ቪ የሚባል ስያሜ የተሰጠው ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን ቫይረስ ኤች አይ ቪ-1 ብለው መጥራት ጀምረዋል። ለምን? ኤድስ አምጪውን ቫይረስ የመሰለ ሌላ ቫይረስ (ኤች አይ ቪ-2) ስላገኙ ነው። ይህ ቫይረስ የኤድስ በሽታ ምልክቶችን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። ከዚህም በላይ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (ሰኔ 27, 1989) እንደሚለው “በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ በዋለው የኤድስ መመርመሪያ ዘዴ ሁልጊዜ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችል ቫይረስ አይደለም። ይህ አዲስ ግኝት . . . የደም ባንኮች የሚለገሳቸው ደም ከበሽታ ነጻ መሆኑን ማረጋገጥ በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ያመለክታል።”

ለኤድስ ቫይረስ የሩቅ ዝምድና ያላቸው ሌሎች ቫይረሶችስ? በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ትእዛዝ የተቋቋመ አንድ ኮሚሽን ከእነዚህ አንዱ የሆነው ቫይረስ “በትላልቅ ሰዎች ላይ ለሚከሰት የቲ ሴል ሉኪሚያ ወይም ሊምፎማ ለተባለው በሽታና ከባድ ለሆነ የነርቭ በሽታ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል” ብሏል። ይህ ቫይረስ በአሁኑ ጊዜ ደም በሚለግሰው ኅብረሰተብ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በደም አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል። ስለዚህ ‘ለበሽተኞች የሚሰጥ ደም ከእነዚህ ሌሎች ቫይረሶች የጸዳ ስለመሆኑ የሚደረገው ምርመራና ማጣሪያ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

ለበሽተኞች ሊሰጥ ተከማችቶ በሚገኝ ደም ውስጥ ምን ያህል ቫይረሶች እንደሚገኙ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ዶክተር ሃሮልድ ቲ ሜሪማን “ገና ያልታወቀው እስካሁን ከታወቀው የበለጠ አሳሳቢ ሳይሆንብን አይቀርም። በበርካታ ዓመታት የሚለካ የመቀፍቀፍ ዕድሜ ያላቸውን ተላላፊ ቫይረሶች ደም በመውሰድ ምክንያት የተላለፉ መሆናቸውንም ሆነ መኖራቸውን ለይቶ ለማወቅ በጣም አዳጋች ይሆናል። ኤች ቲ ኤል ቪ የተባለው የቫይረሶች ቡድን ከእነዚህ ቫይረሶች መካከል የመጀመሪያው ብቻ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። (ትራንስፍዩዥን ሜዲስን ሪቪውስ፣ ሐምሌ 1989) “የኤድስ ወረርሽኝ የሚያስከትለው ጭንቀት ያልበቃ ይመስል . . . በ1980ዎቹ ዓመታት ደም በመውሰድ ምክንያት የሚመጡ አዳዲስ አደጋዎች ታውቀዋል። ወደፊትም ሌሎች ከባድ የሆኑ የቫይረስ በሽታዎች እንደሚኖሩና ደም በመውሰድም እንደሚተላለፉ ለመገመት ብዙ ምርምር አይጠይቅም።”​—ሊሚቲንግ ሆሞሎገስ ኤክስፖዠር:- ኦልተርኔቲቭ ስትራተጂስ፣ 1989

አሁንም ቢሆን የብዙ “ኮቴዎች” ድምፅ ስለተሰማ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከላት “አጠቃላይ የሆነ ጥንቃቄ” እንዲደረግ በማሳሰብ ላይ ናቸው። ‘የጤና ባለሞያዎች ማንኛውንም በሽተኛ የኤች አይ ቪና የሌሎች ደም ወለድ የሆኑ በሽታዎች አስተላላፊ አድርገው መመልከት አለባቸው’ ማለት ነው። የጤና ባለሞያዎችና በርካታ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ስለ ደም የነበራቸውን አመለካከት እንደገና መመርመር የጀመሩት ያለበቂ ምክንያት አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.27 ባሁኑ ጊዜም ቢሆን በደም ባንኮች ውስጥ ያለው ደም በሙሉ ተመርምሯል ብሎ መገመት ያስቸግራል። ለምሳሌ ያህል በ1989 መጀመሪያ ላይ በብራዚል ከሚገኙት የደም ባንኮች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት መንግሥት ምንም ዓይነት ቁጥጥር የማያደርግባቸው ነበሩ። የኤድስ ምርመራም አልተደረገላቸውም።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ደም ከወሰዱ 100 በሽተኞች መካከል በአንዱ ላይ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ወይም ሽፍታ እንደሚታይ ይገመታል። . . . ቀይ የደም ሕዋስ ከተሰጣቸው 6,000 ሰዎች መካከል አንዱ በደም መቃወስ ምክንያት የሚደርስ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። ይህ ደግሞ ወዲያው ወይም ደም ከወሰደ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የሚከሰት የበሽታ መከላከያ ኃይል ቀውስ ያስከትላል። በዚህም ምክንያት [የኩላሊት] ሥራ ማቆም፣ ራስን መሳት፣ የደም መርጋት፣ ወይም ሞት ሊያጋጥም ይችላል።”​—⁠ናሽናል ኢንስቲትዩትስ ኦቭ ኸልዝ (ኤን አይ ኤች) ያደረገው ኮንፈረንስ 1988

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኒልስ የርነ የተባሉት የዴንማርክ ሳይንቲስት የ1984ን የሕክምና የኖቤል ሽልማት ከሌላ ሳይንቲስት ጋር በጋራ አሸንፈዋል። እኚህ ሳይንቲስት ለምን ደም አልወስድም እንዳሉ ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል:- “የአንድ ሰው ደም ልክ እንደ ጣቱ አሻራ ነው። ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት የሆነ ደም ፈጽሞ ሊገኝ አይችልም” ብለዋል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ደም፣ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ጉበቶች እና . .

“ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም በደም ምክንያት የሚተላለፈው ኤድስ . . . የሌሎቹን በሽታዎች ያህል፣ ለምሳሌ ያህል የሄፓታይተስን ያህል አስጊ ሆኖ አያውቅም” ሲል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

አዎን፣ በጣም በርካታ በሽተኞች በዚህ አስተማማኝ ሕክምና ባልተገኘለት ሄፓታይተስ ተለክፈው በጠና ከታመሙ በኋላ ሞተዋል። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት (ግንቦት 1, 1989) እንደ ዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ ደም ከተሰጣቸው መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት በሄፓታይተስ የሚለከፉ ሲሆን ይህም በየዓመቱ 175,000 ሰዎች በዚህ በሽታ ይያዛሉ ማለት ነው። ከእነዚህ መካከል ግማሾቹ የበሽታው ተሸካሚዎች ሆነው ሲኖሩ ቢያንስ ከአምስቱ መካከል የአንዱ በሽታ ሲሮሲስ ወይም የጉበት ካንሰር ደረጃ ላይ ይደርሳል። 4,000 የሚያክሉ እንደሚሞቱ ይገመታል። አንድ ጃምቦ ጄት አውሮፕላን ተከስክሶ የተጫኑት ሰዎች በሙሉ እንደሞቱ የሚገልጽ ዜና ብታነብ ምን እንደሚሰማህ አስብ። 4,000 ሰዎች ይሞታሉ ማለት በየወሩ አንድ ጃምቦ ጄት ተከስክሶ በላዩ የተጫኑት ሰዎች በሙሉ ይሞታሉ ማለት ነው!

ሐኪሞች ቀለል ያለው ሄፓታይተስ (ኤ ዓይነት) የሚተላለፈው በተበከለ ምግብ ወይም ውኃ አማካኝነት አንደሆነ ካወቁ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። ከጊዜ በኋላ ግን በደም አማካኝነት የሚተላለፈው ሄፓታይተስ ይበልጥ አደገኛ እንደሆነ አወቁ። ደም በሄፓታይተስ የተለከፈ መሆኑንና አለመሆኑን የሚመረምሩበት መሣሪያ ግን ወዲያው አላገኙም። በመጨረሻ በጣም ጎበዝ የሆኑ የሳይንስ ሊቃውንት የዚህን ቫይረስ (ቢ ዓይነት) “ዱካዎች” መመርመር የሚያስችላቸውን ዘዴ አገኙ። በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአንዳንድ አገሮች ለበሽተኞች የሚሰጠው ደም ከሄፓታይተስ ቢ ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ ማድረግ ተጀመረ። ደም የመስጠቱ ሂደት ብሩሕ ተስፋ ያለውና ምንም አደጋ የማያስከትል መስሎ ታየ! ይህ ግምት ትክክል ነበረን?

ብዙም ሳይቆይ ምርመራ የተደረገለት ደም የወሰዱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሄፓታይተስ እንደተያዙ ታወቀ። ብዙዎቹ በሚያዳክም በሽታ ሲማቅቁ ከቆዩ በኋላ ጉበታቸው ፈጽሞ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ አወቁ። ታዲያ የወሰዱት ደም የተመረመረ ሆኖ ሳለ በዚህ በሽታ የተለከፉት ለምን ነበር? ደሙ ነን ኤ፣ ነን ቢ ሄፓታይተስ (ኤን ኤ ኤን ቢ) የተባለ ሌላ ዓይነት ሄፓታይተስ ስለነበረው ነው። ይህ በሽታ ለበርካታ ዓመታት ደም የወሰዱ ሰዎች ሲቀስፍ ኖሯል። በእስራኤል፣ በኢጣሊያ፣ በጃፓን፣ በስፔይን፣ በስዊድንና በዩናይትድ ስቴትስ ደም ከወሰዱ ሰዎች መካከል ከ8 እስከ 17 በመቶ የሚደርሱ ሰዎች በዚህ በሽታ ተለክፈዋል።

ከዚያ በኋላ “ምሥጢር ሆኖ የቆየው ነን ኤ፣ ነን ቢ ቫይረስ ታወቀ፤” “የደም አደገኛነት ተወገደ” እንደሚሉ ያሉ የዜና አምዶች መውጣት ጀመሩ። ስለዚህ መልእክቱ ‘ምሥጢር ሆኖ የቆየው ነገር ተደረሰበት!’ የሚል ነበር። በሚያዝያ 1989 አሁን ሄፓታይተስ ሲ ተብሎ የሚጠራውን ኤን ኤ ኤን ቢ መመርመር የሚያስችል ዘዴ መገኘቱን የሚገልጽ ዜና ለሕዝብ ተበሰረ።

ይህ ዘዴ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ አስገኝቶ ይሆን ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የኢጣሊያ ተመራማሪዎች የተለየ ባሕርይ ያለው ሌላ ዓይነት የሄፓታይተስ ቫይረስ መኖሩንና አንድ ሦስተኛ ለሚሆነው የሄፓታይተስ በሽታ ምክንያቱ ይህ ቫይረስ ሊሆን እንደሚችል አስታወቁ። የሃርቫርድ ሜዲካል ስኩል ኸልዝ ሌተር (ኅዳር 1989) “አንዳንድ ሊቃውንት የሄፓታይተስ ቫይረሶች ዝርዝር በኤ፣ ቢ፣ ሲ እና ዲ ተወስኖ እንደማይቀርና ሌሎች ቫይረሶች ብቅ ሊሉ እንደሚችሉ ያላቸውን ሥጋት መግለጻቸውን” ሪፖርት አድርጓል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (የካቲት 13, 1990) “ለሄፓታይተስ ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች ቫይረሶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሊቃውንቱ የጠበቀ እምነት እንዳላቸውና፣ እነዚህ ቫይረሶች ሲገኙ ሄፓታይተስ ኢ፣ ወዘተ የሚል ስያሜ እንደሚሰጣቸው” ዘግቧል።

ታዲያ የደም ባንኮች ለበሽተኞች የሚሰጠውን ደም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያደርጓቸውን ምርመራዎች እየጨመሩ ይሄዱ ይሆን? የአሜሪካ ቀይ መስቀል ዳይሬክተር ይህ የሚያስከትለውን የገንዘብ ወጪ በማመልከት “ማንኛውም ተዛማች በሽታ አለመኖሩን ለማረጋገጥ ስንል በየቀኑ አዳዲስ የምርመራ ዓይነቶችን እየጨመርን ለመቀጠል አንችልም” የሚል አሳሳቢ አስተያየት ሰጥተዋል።​—⁠ሜዲካል ወርልድ ኒውስ፣ ግንቦት 8, 1989

የሄፓታይተስ ቢ ምርመራ እንኳን ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት አይደለም። አሁንም ደም በመውሰድ ምክንያት ሄፓታይተስ ቢ የሚይዛቸው ሰዎች አሉ። ከዚህም በላይ ተገኝቷል የተባለው የሄፓታይተስ ሲ ምርመራ አስተማማኝ ነውን? ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (ጥር 5, 1990) የበሽታው ፀረ-እንግዳ አካሎች በምርመራ የሚታወቁት አንድ ዓመት ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ደሙ የተሰጣቸው ሰዎች ጉበት ከጥቅም ውጭ ሊሆንና ሊሞቱ ይችላሉ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ ዓይነት በሽታ በደም አማካኝነት ወደ ሩቅ አካባቢዎች ሊወሰድ የሚችል ስለመሆኑ የቻጋስ በሽታ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። “ዘ ሜዲካል ፖስት” (ጥር 16, 1990) እንደዘገበው ‘በላቲን አሜሪካ የሚኖሩ ከ10-12 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎች በዚህ በሽታ የተለከፉ ናቸው።’ “በደቡብ አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ በደም ከሚተላለፉ በሽታዎች አንዱ” እንደሆነ ተነግሮለታል። አንድ ሰው ተኝቶ እንዳለ “አንድ ቀሳፊ ተባይ” ፊቱን ትነክሰውና ደሙን መጥጣና በቁስሉ ላይ ኩሷን ጥላ ትሄዳለች። ይህ ሰው ሳይታወቀው ለበርካታ ዓመታት የቻጋስ በሽታ ተሸካሚ ሆኖ ይኖርና (በዚህ ጊዜ ደም ሊሰጥ ይችላል) የልብ መቃወስ ደርሶበት ይሞታል።

ታዲያ ይህ ነገር ርቀው በሚገኙ አሕጉራት የሚኖሩ ሰዎችን የሚያሳስበው ለምንድን ነው? ዶክተር ኤል ኬ አልትማን ደም ከወሰዱ በኋላ የቻጋስ በሽታ ስለያዛቸው በሽተኞች በ“ኒው ዮርክ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ (ግንቦት 23, 1989) ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህ በሽተኞች መካከል አንዱ ሞቷል። አልትማን “[እዚህ ያሉ ዶክተሮች] ከቻጋስ በሽታ ጋር ስለማይተዋወቁና በሽታው በደም ሊተላለፍ እንደሚችል ስላልተገነዘቡ ሳይታወቅላቸው በዚህ በሽታ የሞቱ ሌሎች ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ጽፈዋል። አዎን፣ ደም በሽታዎች ረጅም ርቀት የሚጓዙበት መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዶክተር ክኑድ ሉንድ-ኦልሰን እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ለኤድስ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጡ ሰዎች ወዲያው የኤድስ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ስለሚያውቁ . . . ደም ለመለገስ ፈቃደኞች ይሆናሉ። ስለዚህ ደም ከመውሰድ ወደ ኋላ የምንልበት በቂ ምክንያት እንዳለ ይሰማኛል። የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ደም ለመውሰድ እምቢተኞች ሆነው ኖረዋል። የወደፊቱ ጊዜ ታይቷቸው ይሆን?”​—⁠“Ugeskrift for Læger” (የዶክተሮች ሳምንታዊ ጋዜጣ)፣ መስከረም 26, 1988

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሊቀ ጳጳሱ በጥይት ተመትተው የነበሩ ቢሆንም በሕይወት ተርፈዋል። ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ እንደገና ተመልሰው ለሁለት ወራት “በከባድ ሕመም” ተሠቃ​ይተዋል። ለምን? ከተሰጣቸው ደም በተላለፈባቸው ሳይቶሜጋሎቫይረስ የተባለ ሞት ሊያስከትል የሚችል ኢንፌክሽን ምክንያት ነበር

[ምንጭ]

UPI/Bettmann Newsphotos

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኤድስ ቫይረስ

[ምንጭ]

CDC, Atlanta, Ga.