ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7
5 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ። 2 ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦
3 “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ a ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
4 “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።
5 “ገሮች b ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።
6 “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ ይጠግባሉና። c
7 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።
8 “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና።
9 “ሰላም ፈጣሪዎች d ደስተኞች ናቸው፤ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።
10 “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
11 “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። 12 በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።
13 “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።
14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። 15 ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ e አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል። 16 በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።
17 “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም። 18 እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም። 19 በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። 20 ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ ልነግራችሁ እወዳለሁ።
21 “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም f ሊዳረግ ይችላል።
23 “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ 24 መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።
25 “ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ። 26 እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም።
27 “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 28 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል። 29 ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም g ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል። 30 እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም h ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።
31 “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’ ተብሏል። 32 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና i ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
33 “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤ ይልቁንም ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ። በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤ 35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና። 36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና። 37 ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው።
38 “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 39 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት። 40 አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤ 41 እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር እንድትሄድ ቢያስገድድህ ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው j ፊት አትንሳው።
43 “‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 44 እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ 45 ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል። 46 የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ? ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 47 ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 48 በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም k እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።
6 “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም። 2 በመሆኑም ምጽዋት l በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 3 አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤ 4 ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ያስችላል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
5 “በተጨማሪም በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 6 አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል። 7 በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል። 8 ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።
9 “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦
“‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። a 10 መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም። 11 የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፤ 12 የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን። 13 ከክፉው አድነን b እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’
14 “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ 15 እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።
16 “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነሱ መጾማቸው በሰው ዘንድ እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን ያጠወልጋሉ። c እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 17 አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ፤ 18 እንዲህ ካደረግክ የምትጾመው በሰው ለመታየት ሳይሆን በስውር ላለው አባትህ ስትል ብቻ ይሆናል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።
19 “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። 20 ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ። 21 ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና።
22 “የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ d ይሆናል። 23 ይሁን እንጂ ዓይንህ ምቀኛ e ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን!
24 “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።
25 “ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥም? 26 የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም? 27 ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል? 28 ስለ ልብስስ ቢሆን ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ 29 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። 30 አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? 31 ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። 32 እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።
33 “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል። 34 ስለዚህ ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።
7 “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ 2 በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል። 3 ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? 4 ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? 5 አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
6 “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ። አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።
7 “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። 8 የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል። 9 ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? 10 ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? 11 ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!
12 “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው። ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።
13 “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ 14 ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
15 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። 16 ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ? 17 በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። 18 ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም። 19 መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል። 20 በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
21 “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው። 22 በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ 23 እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።
24 “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል። 25 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም። 26 ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል። 27 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”
28 ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤ 29 የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።
a ወይም “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ።”
b ወይም “የዋሆች።”
c ወይም “ይረካሉና።”
d ወይም “ሰላማውያን።”
e እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።
f ከኢየሩሳሌም ውጭ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ ነው። ከጥንቷ ኢየሩሳሌም በስተ ደቡብና በስተ ደቡብ ምዕራብ ይገኝ ለነበረው ለሂኖም ሸለቆ የተሰጠ ከግሪክኛ ቃል የተገኘ ስም ነው። እንስሳት ወይም ሰዎች በሕይወት እያሉ ወደዚያ ተጥለው እንዲቃጠሉ ወይም እንዲሠቃዩ ይደረግ እንደነበር የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። በመሆኑም የሰው ነፍስ ለዘላለም በእሳት የሚሠቃይበት በዓይን የማይታይ ቦታ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ዘላለማዊ ቅጣትን ይኸውም ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅመውበታል።
i ፖርኒያ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን ይህ ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት አምላክ የሚከለክላቸውን አንዳንድ ወሲባዊ ድርጊቶች ለማመልከት ነው። ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ይጨምራል።
j ያለወለድ መበደር የሚፈልግን ሰው ያመለክታል።
k ወይም “ሙሉ።”
l ወይም “ለድሆች ስጦታ።”
a ወይም “የተቀደሰ ይሁን፤ ብሩክ ይሁን።”
b ወይም “ታደገን።”
c ወይም “ራሳቸውን ይጥላሉ።”
d ወይም “በብርሃን የተሞላ።”
e ቃል በቃል “መጥፎ፤ ክፉ።”