ማርቆስ 3:1-35

3  ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር።  ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር።  እሱም እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መካከል ና” አለው።  ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ነፍስ* ማዳን ነው ወይስ መግደል?” አላቸው። እነሱ ግን ዝም አሉ።  በልባቸው ደንዳናነት በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት።  በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑ ወጥተው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር በመሰብሰብ እንዴት እንደሚያጠፉት መመካከር ጀመሩ።  ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጣ ብዙ ሕዝብም ተከተለው።  ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች የሰሙ ብዙ ሰዎች ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስና ከዮርዳኖስ ማዶ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ እንኳ ሳይቀር ወደ እሱ መጡ።  ሕዝቡ እንዳያጨናንቀው በማሰብ ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ የሚጠቀምባት አንዲት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። 10  ብዙ ሰዎችን ፈውሶ ስለነበር ከባድ በሽታ የያዛቸው በሙሉ እሱን ለመንካት ይጋፉ ነበር። 11  ርኩሳን መናፍስት እንኳ ሳይቀሩ ባዩት ጊዜ ሁሉ በፊቱ ወድቀው “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። 12  እሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ በተደጋጋሚ አጥብቆ ያዛቸው ነበር። 13  ወደ ተራራም ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ጠራ፤ እነሱም ወደ እሱ ሄዱ። 14  ከዚያም የመረጣቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤ ይህንንም ያደረገው ከእሱ ጋር እንዲሆኑና ለስብከት እንዲልካቸው 15  እንዲሁም አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን እንዲኖራቸው ነው። 16  የመረጣቸውም አሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው:- ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣ 17  የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ (እነዚህን ቦአኔርጌስ ብሎ የሰየማቸው ሲሆን ትርጉሙም የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው)፣ 18  እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀናተኛው ስምዖን 19  እንዲሁም በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። ከዚያ በኋላም ወደ አንድ ቤት ሄደ። 20  እንደገና ብዙ ሕዝብ ከመሰብሰቡ የተነሳ እህል እንኳ ለመቅመስ አልቻሉም። 21  ዘመዶቹ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ሊይዙት መጡ። 22  ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም “ብዔልዜቡል አለበት፤ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር። 23  በመሆኑም ወደ እሱ ከጠራቸው በኋላ በምሳሌ እንዲህ ይላቸው ጀመር:- “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? 24  አንድ መንግሥት እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ መንግሥት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፤ 25  አንድ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ጸንቶ ሊቆም አይችልም። 26  እንደዚሁም ሰይጣን በራሱ ላይ የሚነሳና የሚከፋፈል ከሆነ ያከትምለታል እንጂ ሊጸና አይችልም። 27  ደግሞም ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት የገባ ሰው በቅድሚያ ብርቱውን ሰው ሳያስር ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል። 28  እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠሩ ወይም ምንም ዓይነት የስድብ ቃል ቢናገሩ ሁሉም ነገር ይቅር ይባልላቸዋል። 29  ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም፤ ከዚህ ይልቅ የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል።” 30  ይህንንም ያለው “ርኩስ መንፈስ አለበት” ይሉ ስለነበር ነው። 31  በዚህ ጊዜ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ ውጭ ቆመውም ሰው ልከው አስጠሩት። 32  በዙሪያውም ብዙ ሰዎች ተቀምጠው ስለነበር “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ሆነው ይፈልጉሃል” አሉት። 33  እሱ ግን መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ እነማን ናቸው?” አላቸው። 34  ከዚያም ዙሪያውን ከበው ወደተቀመጡት ሰዎች በመመልከት እንዲህ አለ:- “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! 35  የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እሱ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማር 3:4 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 7ኛውን ርዕስ ተመልከት።