ራእይ 5:1-14

5  እኔም በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ቀኝ እጅ ላይ በውስጥም በውጭም በኩል የተጻፈበት በሰባት ማኅተሞች በደንብ የታሸገ ጥቅልል አየሁ።  አንድ ብርቱ መልአክም በታላቅ ድምፅ “ማኅተሞቹን ሊፈታና ጥቅልሉን ሊከፍት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ።  ሆኖም በሰማይም ሆነ በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚችል አንድም አልነበረም።  ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚገባው ማንም ባለመገኘቱ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።  ሆኖም ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ። እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ስላደረገ ሰባቱን ማኅተሞችና ጥቅልሉን ሊከፍት ይችላል” አለኝ።  በዙፋኑ መካከል፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከልና በሽማግሌዎቹ መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች አሉት፤ ዓይኖቹም ወደ መላው ምድር የተላኩትን የአምላክ ሰባት መናፍስት ያመለክታሉ።  እሱም ሄዶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ ጥቅልሉን ወዲያውኑ ወሰደ።  ጥቅልሉን በወሰደ ጊዜም አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም በገናና ዕጣን የተሞሉ የወርቅ ሳህኖች ይዘው ነበር፤ ዕጣኑም የቅዱሳኑን ጸሎት ያመለክታል።  እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ:- “ጥቅልሉን ልትወስድና ማኅተሞቹን ልትከፍት ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤ 10  እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።” 11  እኔም አየሁ፤ ደግሞም በዙፋኑ፣ በሕያዋን ፍጥረታቱና በሽማግሌዎቹ ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም እልፍ ጊዜ እልፍና* ሺህዎች ጊዜ ሺህዎች ነበር፤ 12  በታላቅ ድምፅም “ታርዶ የነበረው በግ ኃይል፣ ሀብት፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብር፣ ግርማና በረከት ሊቀበል ይገባዋል” አሉ። 13  እንዲሁም በሰማይ፣ በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር ያለ ፍጡር ሁሉ፣ አዎ በውስጣቸው ያሉ ነገሮች ሁሉ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ በረከት፣ ክብር፣ ግርማና ኃይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ። 14  አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም “አሜን!” አሉ፤ ሽማግሌዎቹም ተደፍተው ሰገዱ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ራእይ 5:11 * ወይም፣ “አሥር ሺህ ጊዜ አሥር ሺህዎች።”