የሐዋርያት ሥራ 16:1-40
16 ከዚያም ጳውሎስ ደርቤና ልስጥራ ደረሰ። በዚያም አማኝ የሆነች አይሁዳዊት እናትና ግሪካዊ አባት ያለው ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤
2 እሱም በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች ዘንድ በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር።
3 ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ አብሮት እንዲሄድ እንደሚፈልግ ገለጸ፤ አባቱ ግሪካዊ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቅ ስለነበረም በእነዚያ አካባቢዎች ስላሉት አይሁዳውያን ሲል ወስዶ ገረዘው።
4 በየከተማዎቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ያሳውቋቸው ነበር።
5 በመሆኑም ጉባኤዎቹ በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።
6 ከዚህም ሌላ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በእስያ አውራጃ እንዳይናገሩ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አድርገው አለፉ።
7 ደግሞም ወደ ሚስያ በወረዱ ጊዜ ወደ ቢቲኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ሆኖም የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም።
8 ስለዚህ በሚስያ አልፈው ወደ ጥሮአስ ወረዱ።
9 ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ።
10 ጳውሎስ ይህን ራእይ እንዳየም አምላክ ምሥራቹን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል የሚል መደምደሚያ ላይ ስለደረስን ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።
11 ስለዚህ ከጥሮአስ መርከብ ተሳፍረን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ ሄድን፤ በማግስቱ ደግሞ ወደ ኔያጶሊስ ተጓዝን፤
12 ከዚያም ተነስተን የሮማውያን ቅኝ ግዛትና የአንድ የመቄዶንያ አውራጃ ቁልፍ ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ መጣን። በዚህች ከተማም ለተወሰኑ ቀናት ቆየን።
13 በሰንበት ቀንም የጸሎት ስፍራ ይገኝበታል ብለን ወዳሰብነው ከከተማው በር ውጭ ወዳለ አንድ ወንዝ ዳር ሄድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን።
14 ከትያጥሮን ከተማ የመጣች፣ ሐምራዊ ጨርቅ የምትሸጥና አምላክን የምታመልክ ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት እያዳመጠች ነበር፤ ይሖዋም ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት።
15 እሷና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ከተጠመቁ በኋላ “ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንኩ አድርጋችሁ ከቆጠራችሁኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ በእንግድነት እረፉ” ብላ ተማጸነችን። እንድንገባም አስገደደችን።
16 አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ እየሄድን ሳለ የጥንቆላ ጋኔን ያደረባት አንዲት አገልጋይ አገኘችን። እሷም በጥንቆላ ሥራዋ ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝላቸው ነበር።
17 ይህች ሴት ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው” በማለት ትጮኽ ነበር።
18 ለብዙ ቀናት እየደጋገመች ይህንኑ ትናገር ነበር። በመጨረሻም ጳውሎስ በዚህ ነገር በመሰላቸቱ ዞር ብሎ ያን መንፈስ “ከእሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው። መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣ።
19 ጌቶቿ የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው በንኖ መጥፋቱን ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጎተቱ ገዥዎቹ ወደሚገኙበት ወደ ገበያ ቦታው* ወሰዷቸው፤
20 ከዚያም የሕዝብ አስተዳዳሪዎቹ ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ:- “እነዚህ ሰዎች ከተማችንን ክፉኛ እያወኩ ነው፤ እነሱ አይሁዳውያን ሆነው ሳሉ
21 እኛ ሮማውያን ልንቀበለውም ሆነ ልንፈጽመው የማይገባንን ልማድ እያስፋፉ ነው።”
22 ሕዝቡም በአንድነት በእነሱ ላይ ተነሳ፤ የሕዝብ አስተዳዳሪዎቹም መደረቢያቸውን ከገፈፏቸው በኋላ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።
23 ብዙ ከደበደቧቸው በኋላ እስር ቤት አስገቧቸው፤ የእስር ቤቱንም ጠባቂ በደንብ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
24 እሱም እንዲህ ያለ ትእዛዝ ስለተሰጠው ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን በእግር ግንድ አጥብቆ አሰረው።
25 ይሁንና እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ይሰሟቸው ነበር።
26 ድንገት ከባድ የምድር ነውጥ በመከሰቱ የእስር ቤቱ መሠረት ተናጋ። በተጨማሪም በሮቹ ወዲያውኑ ከመከፈታቸውም በላይ ሁሉም የታሰሩበት ማሰሪያ ተፈታ።
27 የእስር ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የእስር ቤቱ በሮች መከፈታቸውን ሲያይ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።
28 ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ “በራስህ ላይ ጉዳት አታድርስ! ሁላችንም እዚህ አለን” ሲል ተናገረ።
29 በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂ መብራት እንዲያመጡለት ጠይቆ ዘሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ ፊት ወደቀ።
30 ወደ ውጪ ካወጣቸውም በኋላ “ጌቶቼ፣ ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” አለ።
31 እነሱም “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ትድናላችሁ” አሉት።
32 ከዚያም ለእሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ቃል ነገሯቸው።
33 ጠባቂውም ሌሊት በዚያው ሰዓት ይዟቸው ሄዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፤ እሱም ሆነ መላው ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ።
34 ወደ ቤቱም ወስዶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በአምላክ በማመኑም ከመላው ቤተሰቡ ጋር እጅግ ተደሰተ።
35 ሲነጋም የሕዝብ አስተዳዳሪዎቹ “እነዚያን ሰዎች ልቀቃቸው” ብለው እንዲነግሩት ሥርዓት አስከባሪዎቹን ላኩበት።
36 በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂ የላኩትን መልእክት እንዲህ ሲል ለጳውሎስ ነገረው:- “የሕዝብ አስተዳዳሪዎቹ ሁለታችሁ እንድትፈቱ ሰዎች ልከዋል። ስለዚህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ።”
37 ጳውሎስ ግን እንዲህ አላቸው:- “እኛ ሮማውያን ሆነን ሳለን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ገርፈው እስር ቤት ወረወሩን፤ ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ? እንዲህማ አይሆንም! እነሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን።”
38 ስለዚህ ሥርዓት አስከባሪዎቹ ይህን ነገር ለሕዝብ አስተዳዳሪዎቹ ነገሯቸው። እነሱም ሰዎቹ ሮማውያን መሆናቸውን ሲሰሙ ፍርሃት አደረባቸው።
39 በመሆኑም መጥተው ለመኗቸው፤ ከእስር ቤቱ ካወጧቸው በኋላም ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ጠየቋቸው።
40 ይሁንና ከእስር ቤቱ ወጥተው ወደ ሊዲያ ቤት አመሩ፤ እዚያም ወንድሞችን አግኝተው ካበረታቷቸው በኋላ ከተማዋን ለቀው ሄዱ።