የሐዋርያት ሥራ 18:1-28

18  ከዚህ በኋላ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።  በዚያም የጳንጦስ ተወላጅ የሆነውን አቂላ የተባለውን አይሁዳዊና ሚስቱን ጵርስቅላን አገኘ፤ ይህ ሰው ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ባዘዘው መሠረት በቅርቡ ከጣሊያን የመጣ ነበር። ጳውሎስም ወደ እነሱ ሄደ፤  ሙያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ እነሱ ቤት ተቀምጦ አብሯቸው ይሠራ ነበር፤ ሙያቸውም ድንኳን መስፋት ነበር።  ይሁን እንጂ በየሰንበቱ በምኩራብ ንግግር እየሰጠ አይሁዳውያንንና ግሪካውያንን ያሳምን ነበር።  ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ ጳውሎስ ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ፤ ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ መሆኑን እያስረዳ ለአይሁዳውያን ይመሠክር ነበር።  አይሁዳውያኑ መቃወማቸውንና መሳደባቸውን በቀጠሉ ጊዜ ግን ልብሱን በማራገፍ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን። እኔ ንጹሕ ነኝ። ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።  በዚህም መሠረት ከዚያ ተነስቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደሚባል አምላክን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህም ሰው ቤት በምኩራቡ አጠገብ ነበር።  የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ። መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር።  በተጨማሪም ጌታ ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው:- “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ 10  እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ ማንም አንተን ሊያጠቃና ጉዳት ሊያደርስብህ አይችልም፤ ምክንያቱም በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ።” 11  ስለዚህ በመካከላቸው የአምላክን ቃል እያስተማረ ለአንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቆየ። 12  ጋልዮስ የአካይያ አገረ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን ግምባር ፈጥረው በጳውሎስ ላይ ተነሱበት፤ በፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም 13  እንዲህ አሉ:- “ይህ ሰው ሕጉን በሚጻረር መንገድ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ እያሳመነ ነው።” 14  ይሁንና ጳውሎስ ሊናገር ገና አፉን ሲከፍት ጋልዮስ አይሁዳውያንን እንዲህ አላቸው:- “የአይሁድ ሰዎች ሆይ፣ አንድ ዓይነት በደል ወይም ክፉ ድርጊት ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ በትዕግሥት ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር። 15  ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ ከሆነ እናንተው ጨርሱት። እኔ እንዲህ ላለ ነገር ፈራጅ መሆን አልፈልግም።” 16  ከዚያም ከፍርድ ወንበሩ ፊት አስወጣቸው። 17  በዚህ ጊዜ የምኩራብ አለቃ የሆነውን ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ደበደቡት። ጋልዮስ ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች ምንም ደንታ አይሰጡትም ነበር። 18  ይሁንና ጳውሎስ በርከት ላሉ ቀናት እዚያ ከሰነበተ በኋላ ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስእለት ስለነበረበትም በክንክራኦስ ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ። 19  ኤፌሶን በደረሱ ጊዜም እነሱን እዚያው ተዋቸው፤ እሱ ግን ወደ ምኩራብ ገብቶ ከአይሁዳውያን ጋር ይወያይ ነበር። 20  ምንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሰነብት ደጋግመው ቢጠይቁትም ፈቃደኛ አልሆነም፤ 21  ከዚህ ይልቅ ተሰናበታቸውና “ይሖዋ ከፈቀደ እንደገና ተመልሼ እመጣለሁ” አላቸው። ከዚያም ከኤፌሶን በመርከብ ተሳፍሮ 22  ወደ ቂሳርያ ወረደ። ወጥቶም* ለጉባኤው ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ። 23  በዚያም የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ከዚያ ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ አገሮች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ደቀ መዛሙርትን ሁሉ አበረታታ። 24  በዚህ ጊዜ የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ የሚባል ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ያለው አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እሱም ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር። 25  ይህ ሰው የይሖዋን መንገድ በቃል የተማረ ሲሆን በመንፈስ እየተቃጠለ ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር። 26  እሱም በምኩራብ ውስጥ በድፍረት መናገር ጀመረ። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት። 27  በተጨማሪም ወደ አካይያ መሄድ ፈልጎ ስለነበር ወንድሞች በዚያ የሚገኙት ደቀ መዛሙርት በደግነት እንዲቀበሉት የሚያሳስብ ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያ በደረሰ ጊዜም ከአምላክ ጸጋ የተነሳ አምነው የነበሩትን በእጅጉ ረዳቸው፤ 28  ምክንያቱም ከአይሁዳውያን ጋር የጦፈ ክርክር በማድረግ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በማስረዳት በይፋ ይረታቸው ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሥራ 18:22 * ማለትም፣ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቶ።”