የሐዋርያት ሥራ 22:1-30
22 “ወንድሞችና አባቶች፣ አሁን ለእናንተ የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ።”
2 (እነሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከበፊቱ ይበልጥ ጸጥ አሉ፤ እሱም እንዲህ አለ:-)
3 “እኔ ኪልቅያ ውስጥ በምትገኘው በጠርሴስ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ ሆኖም የተማርኩት በዚህችው ከተማ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ ሲሆን የአባቶችን ሕግ በጥብቅ እንድከተል የሚያደርግ ትምህርት ቀስሜያለሁ፤ ዛሬ እናንተ ሁላችሁ እንዲህ እንደምትቀኑ ሁሉ እኔም ለአምላክ እቀና ነበር።
4 ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በማሰርና ለወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት ይህን መንገድ የሚከተሉትን እስከ ሞት ድረስ ስደት አደርስባቸው ነበር፤
5 ይህን በተመለከተም ሊቀ ካህናቱም ሆነ መላው የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊመሠክሩልኝ ይችላሉ። ከእነሱም በደማስቆ ላሉ ወንድሞቻችን የተጻፈ ደብዳቤ ተቀብዬ በዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት ለማስቀጣት በጉዞ ላይ ነበርኩ።
6 “በጉዞ ላይ ሳለሁ ግን ወደ ደማስቆ ስቃረብ እኩለ ቀን ገደማ ላይ በድንገት ከሰማይ የመጣ ከፍተኛ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤
7 እኔም መሬት ላይ ወደቅኩ፤ ከዚያም ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ።
8 እኔም መልሼ ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩት። እሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።
9 ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን ቢያዩም እሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም።*
10 በዚህ ጊዜ ‘ጌታ ሆይ፣ ምን ባደርግ ይሻላል?’ አልኩት። ጌታም ‘ተነስተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ እዚያም ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ ይነገርሃል’ አለኝ።
11 ከብርሃኑ ድምቀት የተነሳ ዓይኔ ማየት ስለተሳነው አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩ ደማስቆ አደረሱኝ።
12 “ከዚያም ሕጉን በሚገባ በመጠበቅ ለአምላክ ያደረና እዚያ በሚኖሩት አይሁዳውያን ሁሉ ዘንድ ጥሩ ስም ያተረፈ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው
13 ወደ እኔ መጥቶ አጠገቤ በመቆም ‘ወንድሜ ሳኦል፣ ዓይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ። እኔም በዚያው ቅጽበት ቀና ብዬ አየሁት።
14 እሱም እንዲህ አለኝ:- ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ድምፁን እንድትሰማ መርጦሃል፤
15 ይህንም ያደረገው ስላየኸውና ስለሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ምሥክር እንድትሆነው ነው።
16 ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ፤ ስሙንም እየጠራህ ኃጢአትህን ታጠብ።’
17 “ሆኖም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስኩ በኋላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየጸለይኩ ሳለሁ ሰመመን ውስጥ ገባሁ፤
18 ጌታም ‘ስለ እኔ የምትሰጠውን ምሥክርነት ስለማይቀበሉ ፍጠን፣ ከኢየሩሳሌም ቶሎ ብለህ ውጣ’ ሲለኝ አየሁት።
19 እኔም እንዲህ አልኩት:- ‘ጌታ ሆይ፣ በየምኩራቡ እየዞርኩ በአንተ የሚያምኑትን አስርና እገርፍ እንደነበረ እነሱ ራሳቸው በሚገባ ያውቃሉ፤
20 ደግሞም የአንተ ምሥክር የነበረው የእስጢፋኖስ ደም ሲፈስ እኔ ራሴ በድርጊቱ በመስማማት እዚያ ቆሜ የገዳዮቹን መደረቢያ ስጠብቅ ነበር።’
21 እሱ ግን ‘በሩቅ ወዳሉ አሕዛብ ስለምልክህ ተነስተህ ሂድ’ አለኝ።”
22 ሕዝቡ ይህን እስኪናገር ድረስ ጸጥ ብለው ሲያዳምጡት ከቆዩ በኋላ “ይህ ሰው ቀድሞውንም መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ።
23 እየጮኹ መደረቢያቸውን ይወረውሩና አፈር ወደ ላይ ይበትኑ ስለነበር
24 የሠራዊቱ ሻለቃ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት ትእዛዝ ሰጠ፤ እንዲህ የሚጮኹበት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ።
25 ሆኖም ሊገርፉት ወጥረው ባሰሩት ጊዜ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን መኮንን “አንድን ሮማዊ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋል?” አለው።
26 መኮንኑ ይህን ሲሰማ ወደ ሠራዊቱ ሻለቃ ሄዶ “ምን ለማድረግ ነው ያሰብከው? ይህ ሰው እኮ ሮማዊ ነው” አለው።
27 ሻለቃውም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ “ሮማዊ ነህ እንዴ?” አለው። እሱም “አዎ” አለው።
28 ሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለው። ጳውሎስ ደግሞ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” አለ።
29 ስለዚህ እየገረፉ ሊመረምሩት የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእሱ ራቁ፤ የሠራዊቱ ሻለቃም አስሮት ስለነበር ሮማዊ መሆኑን ሲያረጋግጥ ፈራ።
30 በመሆኑም በማግስቱ አይሁዳውያን የከሰሱት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ ፈታውና የካህናት አለቆቹ እንዲሁም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ጳውሎስንም አውርዶ በመካከላቸው አቆመው።