የሐዋርያት ሥራ 3:1-26

3  አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ሰዓት ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደሱ እየወጡ ነበር፤  ሰዎች በእናቱ ማህፀን ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ተሸክመው በማምጣት ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት* እንዲለምን ውብ በተባለው የቤተ መቅደሱ በር አጠገብ በየዕለቱ ያስቀምጡት ነበር።  ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገቡ ሲሉ አያቸውና ምጽዋት እንዲሰጡት ይለምናቸው ጀመር።  ጴጥሮስና ዮሐንስም ትኩር ብለው ካዩት በኋላ ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት” አለው።  ሰውየውም የሆነ ነገር ሊሰጡኝ ነው ብሎ በማሰብ ትኩር ብሎ ተመለከታቸው።  ይሁንና ጴጥሮስ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ:- በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!” አለው።  ከዚያም ቀኝ እጁን ይዞ አስነሳው። ወዲያውም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጠነከረ፤  ዘሎም በመነሳት ቆመ፤ ከዚያም መራመድ ጀመረ፤ እየተራመደና እየዘለለ እንዲሁም አምላክን እያመሰገነ ከእነሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።  ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና አምላክን ሲያመሰግን አዩት። 10  በተጨማሪም ይህ ሰው ውብ በተባለው የቤተ መቅደሱ በር አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው ሰው መሆኑን አውቀው በእሱ ላይ በተፈጸመው ሁኔታ እጅግ ይደነቁና ይገረሙ ጀመር። 11  ሰውየው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዟቸው ሳለ በዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደንቀው እነሱ ወዳሉበት የሰለሞን መተላለፊያ ወደሚባለው ስፍራ ግር ብለው እየሮጡ መጡ። 12  ጴጥሮስ ይህን ባየ ጊዜ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው:- “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? በእኛ ኃይል ወይም ደግሞ እኛ ለአምላክ ያደርን በመሆናችን የተነሳ ይህን ሰው እንዲራመድ ያስቻልነው ይመስል ለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? 13  የአባቶቻችን አምላክ ይኸውም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን አገልጋዩን ኢየሱስን አከበረው። 14  አዎ፣ እናንተ ይህን ቅዱስና ጻድቅ ሰው ክዳችሁ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሰው በነፃ እንዲፈታላችሁ ጠየቃችሁ፤ 15  በአንጻሩ ግን የሕይወትን ዋና ወኪል ገደላችሁት። አምላክ ግን ከሞት አስነሳው፤ እኛም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን። 16  በመሆኑም የኢየሱስ ስም ይኸውም እኛ በስሙ ላይ ያለን እምነት ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን ሰው አጠነከረው፤ በኢየሱስ አማካኝነት ያገኘነው እምነትም ሰውየው በሁላችሁም ፊት ፍጹም ጤናማ እንዲሆን አደረገው። 17  አሁንም ወንድሞች፣ ገዥዎቻችሁ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ይህን ያደረጋችሁት ባለማወቅ እንደሆነ አውቃለሁ። 18  ይሁንና አምላክ፣ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ ያሳወቀው ነገር በዚህ መንገድ እንዲፈጸም አድርጓል። 19  “ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ 20  እንዲሁም ለእናንተ የሾመውን ክርስቶስን ይኸውም ኢየሱስን ይልክላችኋል፤ 21  እሱም አምላክ በጥንቶቹ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው ሁሉም ነገር የሚታደስበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ በሰማይ መቆየት ይገባዋል። 22  ደግሞም ሙሴ እንዲህ ብሏል:- ‘ይሖዋ አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል። እሱ የሚነግራችሁንም ነገር ሁሉ ስሙ። 23  ያንን ነቢይ የማይሰማ ነፍስ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ፈጽሞ ይጠፋል።’ 24  በእርግጥም ከሳሙኤል ጀምሮ በተከታታይ የተነሱት ነቢያትም ሁሉ ስለ እነዚህ ቀናት በግልጽ ተናግረዋል። 25  እናንተ የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እንዲሁም አምላክ ለአብርሃም ‘በዘርህ የምድር ቤተሰቦች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችሁ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። 26  አምላክ አገልጋዩን ካስነሳ በኋላ እያንዳንዳችሁን ከክፉ ሥራችሁ በመመለስ ይባርካችሁ ዘንድ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ላከው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሥራ 3:2 ማቴዎስ 6:2 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።