1 ቆሮንቶስ 11:1-34
11 እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ።
2 በሁሉም ነገር ስለምታስቡኝና ለእናንተ ያስተላለፍኳቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
3 ይሁንና የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።
4 ራሱን ሸፍኖ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል፤
5 ሆኖም ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራሷን ታዋርዳለች፤ እንዲህ የምታደርግ ሴት ራሷን እንደተላጨች ሴት ትቆጠራለች።
6 አንዲት ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ ፀጉሯን ትቆረጥ፤ ፀጉሯን መቆረጧ ወይም መላጨቷ የሚያሳፍራት ከሆነ ግን ትሸፈን።
7 ወንድ የአምላክ አምሳልና ክብር ስለሆነ ራሱን መሸፈን የለበትም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።
8 ምክንያቱም ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም፤
9 ከዚህም በተጨማሪ ሴት ለወንድ ሲባል ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት ሲባል አልተፈጠረም።
10 ከዚህ የተነሳና በመላእክት ምክንያት ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።
11 ይሁንና ከጌታ ጋር በተያያዘ ሴት ያለ ወንድ አትኖርም፤ ወንድም ያለ ሴት አይኖርም።
12 ምክንያቱም ሴት ከወንድ እንደተገኘች ሁሉ ወንድም የተገኘው በሴት አማካኝነት ነው፤ ሆኖም ሁሉም ነገሮች የተገኙት ከአምላክ ነው።
13 እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ:- ሴት ሳትሸፈን ወደ አምላክ ብትጸልይ ተገቢ ይሆናል?
14 ወንድ ፀጉሩን ቢያስረዝም ውርደት እንደሚሆንበት ተፈጥሮ ራሱ እንኳ አያስተምራችሁም?
15 ሴት ግን ፀጉሯን ብታስረዝም ለእሷ ክብር አይደለም? ምክንያቱም ፀጉሯ የተሰጣት በመሸፈኛ ምትክ ነው።
16 ይሁን እንጂ ማንም ሰው ሌላ ልማድ መከተል አለብን በሚል ለመከራከር ቢፈልግ እኛም ሆን የአምላክ ጉባኤ ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
17 ሆኖም የምትሰበሰቡት ለሚጠቅማችሁ ሳይሆን ለሚጎዳችሁ ነገር ስለሆነ እነዚህን መመሪያዎች ስሰጣችሁ እያመሰገንኳችሁ አይደለም።
18 ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጉባኤ በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ ክፍፍል እንዳለ እሰማለሁ፤ ደግሞም ይህ በተወሰነ መጠን እውነትነት እንዳለው አምናለሁ።
19 ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች በመካከላችሁ ተለይተው እንዲታወቁ በእናንተ መካከል ኑፋቄዎች ብቅ ማለታቸው የግድ ነው።
20 ስለዚህ ያላችሁበት ሁኔታ፣ አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ የጌታን ራት ለመብላት የሚያስችል አይደለም።
21 ምክንያቱም የጌታን ራት በምትበሉበት ጊዜ እያንዳንዱ አስቀድሞ የራሱን ራት ስለሚበላ አንዱ ሲራብ ሌላው ደግሞ ይሰክራል።
22 የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት እንዳላችሁ የታወቀ ነው፤ የላችሁም እንዴ? ወይስ የአምላክን ጉባኤ በመናቅ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁ? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? ላመስግናችሁ? በዚህ ነገርስ አላመሰግናችሁም።
23 ምክንያቱም እኔ ከጌታ የተቀበልኩትና ለእናንተም ያስተላለፍኩት ይህ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት አንድ ቂጣ አንስቶ
24 ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ “ይህ ለእናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።
25 ከጽዋው ጋር በተያያዘም እንዲሁ አደረገ፤ ራት ከበላ በኋላ “ይህ ጽዋ በደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው። ከዚህ ጽዋ በጠጣችሁ ቁጥር ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።
26 ይህን ቂጣ በበላችሁና ከዚህ ጽዋ በጠጣችሁ ቁጥር ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ማወጃችሁን ትቀጥላላችሁ።
27 እንግዲህ የማይገባው ሆኖ ሳለ ከቂጣው የሚበላ ወይም ከጌታ ጽዋ የሚጠጣ ከጌታ አካልና ደም ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሆናል።
28 አንድ ሰው የሚገባው እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ራሱን ይመርምር፤ ከዚያም ቂጣውን ይብላ፣ ከጽዋውም ይጠጣ።
29 ምክንያቱም አካሉ ምን ትርጉም እንዳለው ሳይገነዘብ የሚበላና የሚጠጣ በራሱ ላይ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል እንዲሁም ይጠጣል።
30 ከእናንተ መካከል ብዙዎቹ ደካማና ታማሚ የሆኑት እንዲሁም ጥቂት የማይባሉት በሞት ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው።
31 ሆኖም ራሳችንን መርምረን ብናውቅ ኖሮ ባልተፈረደብን ነበር።
32 ይሁን እንጂ በሚፈረድብን ጊዜ ይሖዋ ይገሥጸናል፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኮነን ነው።
33 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ ይህን ራት ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።
34 የምትሰበሰቡት ለፍርድ እንዳይሆን የራበው ሰው ካለ እዚያው ቤቱ ይብላ። የቀሩትን ጉዳዮች ግን እዚያ ስመጣ አስተካክላለሁ።