1 ቆሮንቶስ 4:1-21

4  እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን የክርስቶስ የበታቾችና* የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር መጋቢዎች እንደሆን አድርጎ ይቁጠረን።  በተጨማሪም በዚህ ረገድ መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል።  በእናንተም ሆነ በሰዎች የፍርድ ሸንጎ ብመረመር ምንም ግድ አይሰጠኝም። እኔም እንኳ ራሴን አልመረምርም።  ምክንያቱም እኔ ሕሊናዬን የሚወቅሰኝ ምንም ነገር የለም። ሆኖም ይህ ጻድቅ መሆኔን ያረጋግጣል ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እኔን የሚመረምረኝ ይሖዋ ነው።  ስለዚህ ጊዜው ከመድረሱ በፊት በምንም ነገር ላይ አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ነገር ወደ ብርሃን የሚያወጣውም ሆነ በልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ የሚገልጠው ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጠብቁ፤ በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ምስጋናውን ይቀበላል።  እንግዲህ ወንድሞች፣ አንዱን ከሌላው በማስበለጥ በግለሰብ ደረጃ እንዳትታበዩ፣ ለእናንተው ጥቅም ራሴንና አጵሎስን ምሳሌ አድርጌ በማቅረብ እነዚህን ነገሮች የተናገርኩት “ከተጻፉት ነገሮች አትለፍ” የሚለውን መመሪያ እንድትማሩ ነው።  ለመሆኑ አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው? ደግሞስ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለህ? ከተቀበልክ ደግሞ እንዳልተቀበልክ ሆነህ የምትኩራራው ለምንድን ነው?  እንግዲህ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል ማለት ነዋ! ባለጠጎች ሆናችኋል ማለት ነዋ! ያለ እኛ ነግሣችኋል ማለት ነዋ! እኛም ከእናንተ ጋር መንገሥ እንድንችል ነገሥታት ሆናችሁ መግዛት ጀምራችሁ ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር።  በዓለም፣ በመላእክትና በሰዎች ፊት እንደ ትርዒት ስለምንታይ አምላክ እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደተፈረደባቸው ሰዎች በትርዒቱ መጨረሻ ላይ እንድንቀርብ ያደረገን ይመስለኛል። 10  እኛ በክርስቶስ የተነሳ ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ የተነሳ ብልሆች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ጠንካሮች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን ተዋርደናል። 11  እስከዚህ ሰዓት ድረስ እየተራብንና እየተጠማን፣ እየተራቆትን፣ እየተመታን፣ ቤት አጥተን እየተንከራተትን 12  እንዲሁም በገዛ እጃችን በመሥራት እየለፋን እንገኛለን። ሲሰድቡን እንባርካለን፤ ስደት ሲያደርሱብን ችለን እንኖራለን፤ 13  ስማችንን ሲያጠፉት በለሰለሰ አንደበት እንማጸናለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጉድፍና የሁሉ ነገር ጥራጊ እንደሆንን ተደርገን እንታያለን። 14  እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ላሳፍራችሁ ብዬ ሳይሆን እንደተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ ነው። 15  ምንም እንኳ በክርስቶስ አሥር ሺህ ሞግዚቶች ሊኖሯችሁ ቢችልም ብዙ አባቶች እንደሌሏችሁ ግን የተረጋገጠ ነው፤ ምክንያቱም በምሥራቹ አማካኝነት በክርስቶስ ኢየሱስ እኔ አባታችሁ ሆኛለሁ። 16  ስለዚህ እኔን እንድትኮርጁ እማጸናችኋለሁ። 17  በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን የምልክላችሁ ለዚህ ነው፤ እሱም በየስፍራው በሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ሳስተምር የምጠቀምባቸውን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን መንገዶች ያሳስባችኋል። 18  አንዳንዶች እኔ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሏቸው ታብየዋል። 19  ይሁንና ይሖዋ ከፈቀደ በቅርቡ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜም የእነዚህን ትዕቢተኞች ንግግር ሳይሆን ኃይላቸውን ማወቅ እፈልጋለሁ። 20  ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት በንግግር ሳይሆን ከአምላክ በሚገኝ ኃይል ላይ የተመሠረተ ነው። 21  ለመሆኑ የምትፈልጉት ምንድን ነው? ዱላ ይዤ ብመጣ ይሻላል ወይስ በፍቅርና በገርነት መንፈስ ብመጣ?

የግርጌ ማስታወሻዎች

1ቆሮ 4:1 * ወይም፣ “አገልጋዮች፤ ረዳቶች።”